Friday, 04 September 2020 00:00

“ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው” (፩ቆሮ.፱፥፳፪)

Written by  መ/ር ተስፋ ማርያም ቢሰጥ

Overview

በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ አንዳችን ለአንዳችን እንዴት መኖር እንዳለብን የቅዱስ ጳውሎስንና የሌሎችን ቅዱሳን ሕይወት መሠረት በማድረግ  ለመዳሰስ እንሞክራለን ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የቀደመ ማንነቱን በመተው ምርጥ ዕቃ ከተባለ በኋላ  ወንጌል በማስተማር የተበተኑትን በመሰብሰብ የደካሞችን ድካም ተሸክሟል ፡፡ ክርስቶስ የእኛን ድካም ተሸክሞ በዚህ ዓለም ሲኖር በኋላም በመስቀል ሲገልጸው አንድም ቀን ራሱን ደስ እንዳላሰኝ  ይህም ሐዋርያ በተመሳሳይ የክርስቶስን ፈለግ በመከተል እንዲህ አለ፡፡ “የሚገባስ እኛ ብርቱዎች ደካሞችን በድካማቸው እንድንረዳቸው ነው፤ ለራሳችንም አናድላ። ሁላችንም በእውነትና በመልካም ሥራ ይታነጽ ዘንድ ለባለንጀራችን እናድላ ፡፡ ክርስቶስም አንተን የነቀፉበት ነቀፋ በእኔ ላይ ደረሰ ብሎ መጽሐፍ እንደተናገረ ለራሱ ያደላ አይደለም ፡፡›› (ሮሜ ፲፭፥፩-፪) ብሏል፡፡  የክርስትናን አኗኗር ስንኖር ራሳችንን ለመጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌላውን ለመጥቀምና ለማስደሰት መሆን አለበት ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳን የራሱን ጥቅም አይፈልግ” (፩ቆሮ.፲፥፳፬) በማለት እንዳስተማረን ከራሳችን ይልቅ ሌላውን ለመጥቀምና ለማስደሰት መትጋት ይኖርብናል። ገታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን በተግባር አሳይቶናል ፡፡ እሱ ተሰዶ እኛን ከተሰደድንበት መለሰን፡፡ የማይራበው እሱ ተርቦ የተራብነው እኛን ሥጋውንና ደሙን በመስጠት አጠገበ፡፡ የማይጠማው ተጠምቶ የተጠማነውን እኛን ደሙን በመስጠት አረካን ፤ የማይታመመው ታሞ የታመምን እኛን ከሕማመ ሥጋ  በተአምራት ከሕማመ  ነፍስ በትምህርት ፈወሰ፡፡  መከራ በባሕርይው የማይስማማው መከራን ተቀብሎ እኛን ከመከራ አዳነ፡፡ በፍርድ አደባባይ መቆም፣ መወቀስ፣ መከሰስ የማይገባው አምላክ በፍርድ አደባባይ በጲላጦስ ፊት ቆሞ በመወቀስ፣ በመከሰስ፣ በመገረፍ በፊቱ መቆም የማይገባን እኛን በቸርነቱ ብዛት በፊቱ እንድንቆም በማድረግ ከዘለዓለም ፍርድ በማውጣት ደስ አሰኘን ቸርነቱ ያራራዋልና ለርሱ ግን ደስታ ጎሎበት ይህን በማድረግ ደስታን አላተረፈም ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፡፡ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የእኛን ደስታ አጸናልን። ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ‹‹ እኔን የምትሹ ከሆነ እነዚህን ተዋቸው ይሂዱ›› (ዮሐ. ፲፰፥፰) በማለት በከፈለው ዋጋ እኛን ነፃ አወጣን ፡፡ እጅና እግሩን ታስሮ እኛ የታሰርንበትን የኃጢአት ሰንሰለት ቆረጠ፡፡ የእኛን ኃጢአት ፤ ድካም ፤. . . .በመስቀል ላይ በመሸከም ዕዳችንን ፤ ሸክማችንን አቀለለ፡፡ የውርደት ሞትን በፈቃዱም ቢሆን ሞቶ እኛን ለክብር አበቃን ፡፡ በአጠቃላይ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ የፈፀማቸው ሁሉ እኛ የከበርንባቸው ናቸው፡፡ ይህም ታላቅ የወንጌል መምህር ቅዱስ ጳውሎስ  ‹‹ እኔ ክርስቶስን እንደመሰልኩ እናንተም እኔን ምሰሉ›› (፩ቆሮ. ፲፩፥፩) ብሎ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመልእክቱ የጻፈው  ለሌሎች እንደመኖርና የሌሎቹን ድኅነት እንደማሰብ ድካማቸውንም እንደመሸከም የሚያስደስት የለምና ነው። አንድ ሰው ብዙ ቢጾም፤ ቢጸልይ ፤ ቢሰግድ፤ አርምሞ ቢይዝ  የሌሎች ወገኖች ጉዳይ መራብ፣ መጠማት፣መታመምና መጎስቆል፣ በኃጢአት መውደቅ… የማያሳስበው ከሆነ ከክርስቶስ ብዙ ርቋል ፡፡ ሐዋርያውም “ወንድሞቼ ሆይ የልቤ ምኞት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርበው ጸሎትም እስራኤል  እንዲድኑ ነው ፡፡” (ሮሜ ፲፥፩) በማለት ምኞቱና ጸሎቱ ስለሌሎች መዳን መሆኑን በአጽንኦት ይነግረናል። ሐዋርያው በልቡ እንዲህ አይነት በጎ ፈቃድ ስላለው የቆሮንቶስንም ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት አስተማሯል “እኔ ከሁሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እሰበስባቸው ዘንድ  እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ ፡፡ አይሁድን እጠቅም ዘንድ ለአይሁድ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁላቸው፤ ከኦሪት በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ እኔ ራሴ ከኦሪት በታች ሳልሆን ከኦሪት በታች ላሉት ከኦሪት በታች እንዳለ ሰው  ሆንሁላቸው፤ የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋሁ ሳልሆን በክርስቶስ ሕግም ሳለሁ ሕግ የሌላቸውን እጠቅማቸው ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሆንሁላቸው፤ ደካሞችንም  እጠቅማቸው ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶቹን አድን ዘንድ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደነርሱ ሆንሁ፡፡ በወንጌልም ትምህርት አንድነት ይኖረኝ ዘንድ  ስለወንጌል ትምህርት ሁሉን አደርጋለሁ፡፡ (፩ቆሮ. ፱፥፲፱-፳፫) ይህ ታላቅ ሐዋርያ ሰዎችን ይረዳ ይጠቅም ድካማቸውንም ይሸከም ዘንድ ፤ ለአይሁዳዊውም ሕግ ለሌለውም ከሕግ በታች ላሉትም ለደካሞችም የሚያድንበትን መንገድ ለማስፋት የቻለውን አድርጓል፡፡ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ›› (፩ቆሮ. ፲፩፥፩)ያለበት ዋነኛው ምክንያትም ይህ ነው። ክርስቶስ እኛን ከወደቅንበት ለማንሣት እያሳደድነው፣ እየደበደብነው፣ እየገፋነው እርሱ ግን እስከ ሞት ድረስ ወደደን። በመንጸፈ ደይን መውደቃችንን በእግረ አጋንንት መጠቅጠቃችንን አይቶ ልዑል ባሕርይውን ዝቅ በማድረግ እኛን ከወደቅንበት ለማንሣት ወደኛ መጥቷል ፡፡ እርሱ በባሕርዩ የማይስማማውን መራብን፣ መጠማትን፣ መሰደብን፣ መገረፍን መሞትን ለኛ ሲል እንደተቀበለ እኛም ለሌሎች መዳን የቻልነውን ማደረግ ይጠበቅብናል፡፡  ቅዱስ ጳውሎስ ሌሎችን ለመጥቀም ሲል ለኅሊና የማይመቹ ብዙ ነገሮችን አድርጓል ፡፡ ሀ. ራስን መላጨት ፡- ቆሮንቶስ የአካይያ ዋና መዲና ስትሆን ጋልዮስ በአካይያ አገረ ገዥ በነበረበት ጊዜ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ . . ..ጋልዮስም  ‹‹በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድም በማለት ከፍርድ ወንበር አስወጥቷቸዋል . . . . ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጅግ ቀን ተቀምጦ ወንድሞቹንም ተሰናብቶ በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ ስለትም ነበረበትና ራሱን በክርንክራአስ ተላጨ ድርስቅላና አቂላም ከእነርሱ ጋር ነበሩ፡፡ (ሐዋ.፲፰፥፲፪-፲፰) ብፅዐት ያለበት ሰው ስድስት ቀን ከሰው ተለይቶ በሰባተኛው ቀን ጠጉሩን ተላጭቶ ገላውን ታጥቦ ልብሱን አንፅቶ መሥዋዕት አሠውቶ ማየ ምንዛህ (ውኃ) ተረጭቶ ከሰው ይገናኝ ነበር ፡፡ (ዘኊ.፮፥፱) ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን መላጨቱ ለእሱ ምንም ጥቅም ሳይኖረው ሌሎችን ለመሳብ አድርጓል ይህ ሐዋርያ እየተራበም እየተጠማም፤ እየተገፋም ሌሎችን ለመሳብ የሚያደርገው ጥረት እጅግ የሚደንቅ ነው ፡፡ ለ. ግዝረት ፡- ቅዱስ ጳውሎስ ስለግዝረት ምንነት በሰወፊው አስተምሯል “ኦሪትንም ብትፈጽም ግዝረት ትጠቅምሃለች ኦሪትን ባትፈጽም ግን ግዝረትህ አለመገረዝ ትሆንብሃለች። አንተ ሳትገዘር ብትኖር ኦሪትንም ብትጠብቅ አለመገዘርህ መገዘር ትሆንልሃለች። ተገዝረህ ኦሪትን ከምታፈርስ በተፈጥሮ ያገኘሃት አለመገዘርህ አብራህ ብትኖር ይሻልሃል፤ ኦሪት ከምታፈርስ ካንተ ከተገዘርኸው ያ ያልተገዘረው ኦሪትን የሚፈጽመው ይሻላል።… ›› (ሮሜ ፪፥፳፭-፳፱) በማለት በሐዲስ ኪዳን ግዝረት ማለት በመንፈስ ቅዱስ ምላጭነት በልብ ያለውን የኃጢአት ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣልና ሕገ እግዚአብሔርን መፈፀም እንደሆነ በግልፅ አስረዳ ፡፡ በመሆኑም መገረዝም አለመገረዝም ምንም ዓይነት ጥቅም ባይኖረውም ሌሎቹን ለመጥቀምና ድካማቸውን ለመሸከም ክርስቶስም ተገርዟል፡፡  ክርስቶስ የግዝረትን ሥርዓት የፈጸመው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሥርዓቱን ግን የፈጸመው የአባቶቻችን ሥርዓት አይፈጽምም ብለው በእርሱ እንዳይሰናከሉ ሠራዔ ሕግ ሲሆን ፈጻሜ ሕግም ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ደርቤንና ልሳጥልን በሚባል ቦታ በግሪክ አገር ከሲላስ ጋር በደረሰ ጊዜ ወደፊት ታማኝና ተወዳጅ ልጅ የሚሆነውን ጢሞቲዎስን አገኘና ከእርሱ ጋር ይወስደው ዘንድ ወደደ ነገር ግን በዚያ ሥፍራ አይሁድ ስለነበሩ እነርሱ ደግሞ ያልተገዘረን ሰው ደቀ መዝሙር አድርጎ ሲወስድ ቢያዩ የኦሪት ግዝረት ምንም ዋጋ የሌለው መሆኑን ተምረው እስኪያውቁ ድረስ እንዳይሰናከሉና በዚህም ምክንያት ወንጌልን ከመስማትና ሰምተውም ከማመንና ከመዳን ራሳቸውን እንዳያርቁ ለእነርሱ ሲል ገዘረው፡፡ ‹‹በዚያም ስለነበሩ አይሁድ ጢሞቲዎስን ይዞ ገዘረው›› (ሐዋ.፲፮፥፩-፬) ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ጉባዔ አድርገው በወሰኑት ውሳኔ “ሥርዓት እንዳናከብድ ሌላም ሸክም እንዳንጨምር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር ነውና፤ ነገር ግን ይህን በግድ ትተው ዘንድ እናዝዛችኋለን።ለአማልክት የተሠዋውን ፣ ሞቶ የተገኘውን፣ ደምንም አትብሉ ፤ ከዝሙትም  ራቁ፤ በራሳችሁ የምትጠሉትንም በወንድሞቻችሁ ላይ አታድርጉ ከእነዚህ ሥራዎችም ሰውነታችሁን ብትጠብቁ በሰላም ትኖራላችሁ ደኅና ሁኑ” (ሐዋ. ፲፭፥፳፰-፳፱) ብለው ወስነዋል። በዚህም ውሳኔያቸው ከአሕዛብና ከአይሁድ ወደ ክርስትና የሚመጡትን ወገኖች ሲያወዛግቡ የነበሩትን ግዝረትን በኦሪት የታዘዘውን ይህን ካሉ ይህን አትብሉ የሚለውን ገለጹ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም አላስፈላጊነቱን እርሱም ባለበት በኢየሩሳሌም  ጉባዔ የተወሰነውንና ብዙ ጊዜም በመልእክታቱ ምንም ጥቅም እንደሌለው የተናገረበትን ግዝረትን ለጊዜው ከሰዎች ደካማነት የተነሣ  የእነርሱን ድካም በመሸከም ይህን ፈጽሟል ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ለራሱ ሳይሆን ለሌላው በመኖር ጨውም ቅመምም በመሆኑ መራራ በነበሩ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ክርስትናውን አጣፍጦታል ፡፡ ሐ. ገንዘብ አለመውደድ (አለመቀበል) ፡- አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሲልካቸው ምንም ነገር መያዝ እንደሌለባቸው “በመቀነታችሁ ወርቅ ወይም ብር ወይም መሐለቅ አትያዙ። ለመንገድም ስልቻ ወይም ሁለት ልብስ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ ለሠራተኛ ዋጋው ይገበዋልና ›› (ማቴ.፲፥፲) በማለት በሔዱበት የዕለት ምግባቸውን እንዲያገኙ እንጂ ሌላ ነገር እንዳይዙ አዟል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን ቃለ እግዚአብሔርን ከሚመግባቸው ምእመናን ለዕለት ኑሮው የሚያስፈልገውን ምግብ ማግኘት መብቱ ቢሆንም ከእነርሱ ምንም ገንዘብ ሳይቀበል ድንኳን እየሰፋ ይተዳደር ነበር። ምክንያቱም ሰው ገንዘብ አምጣ ሲሉት ፊቱ ይጠቁራል ውስጡም ይቀየማል ፡፡ ስለዚህ ገንዘብ ወዳድ ሆኖ የነርሱን ቢቀበል የሚያስተምረውን ወንጌል በንጹሕ ልብ እንዳይቀበሉ እንቅፋት ይሆንብኛል ብሎ ወንጌልን መስበክ ወደደ፡፡  በተለይም ለቆሮንቶስ ሰዎች ‹‹ እነሆ ወደ እናንተ ልመጣ  ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ነገር ግን አልተፋጠንሁም ገንዘባችሁን ያይደለ እናንተን እሻለሁና፤ ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና እኔ ግን ስለነፍሳችሁ ገንዘቤን በብዙ ደስታ እከፍላለሁ፡፡›› (፪ቆሮ.፲፪፥፲፬-፲፭) በማለት እንኳንስ የእነርሱን ገንዘብ ሊቀበል ድንኳን ሰፍቶ የሚያገኘውን ገንዘቡንና ራሱንም ጭምር ለእነሱ እንደሚከፍል በግልጽ ነግሯቸዋል ፡፡ ይህንም የተናገረበት ምክንያት የቆሮንቶስ ምእመናን ገንዘብን ከመውደዳቸው የተነሣ ብዙዎች ዳኞች ባለሥልጣናት ገና አረማውያን በነበሩበትና ክርስትና ገና እየተስፋፋ በነበረበት ጊዜ እነዚህ ክርስቲያኖች ‹‹ ክርስቶስ አባታችን መንግሥተ ሰማይ ርስታችን ሀገራችን በሰማይ እያሉ በዚህ ዓለም ገንዘብ እየተጨቃጨቁ ይካሰሳሉ›› እያሉ ክርስትናን ያስነቀፉ ስለነበር ነው፡፡ “ይህንም የምላችሁ ስዘልፋችሁ ነው፤ እንግዲህ  ከመካከላችሁ ወንድማማቾችን ከወንድሞቻቸው ጋር ማስታረቅ የሚችል ሽማግሌ የለምን? ነገር ግን ወንድም ከወንድሙ ጋር ይካሰሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል። እንግዲህ ጸብና ክርክር ካላችሁ ከመጀመሪያው ጀምሮ ውርደት እንደሚሆንባችሁ ዕወቁ፤ እንግዲያማ እንዴት አትነጠቁም? እንዴትስ አትገፉም? አሁንም ቢሆን እናንተ ዐመፀኞችና ቀማኞች ናችሁ፤ እንደዚህም ወንድሞቻችሁን ትበድላላችሁ፡፡›› ያለበት ምክንያት ይህን ለመግለጽነው (፩ቆሮ.፮፥፭-፰) በኃላፊ ጠፊ ገንዘብ ምክንያት ከወንድም ጋር መካሰስ ተገቢ እንዳልሆነ በግልፅ ጻፈ፡፡ የዋሁ ጳውሊም ከወንድሙ ጋር በገንዘብ ተካሶ ሲሄድ ሬሳ ለቀብር ሰዎች ተሸክመውት በማየት ለዚህ ነው ወንድሜን የምከሰው ወንድሜ ተመለስ ሁሉ ላንተ ይሁን ብሎ ይችን ዓለም በምናኔ ተሰናብቶታል ፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስም በገንዘብ ፍቅር ከሚቃጠሉና ከሚካሰሱ ሰዎች ምንም ነገር መቀበል ያልፈለገው ፡፡ ይልቁንም እርሱ ወንጌልን እያስተማራቸው ልጅነት፤ ጥምቀት፤ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር እየመራቸው የድካሙን ዋጋ የዕለት ጉርሱን ቢቀበል መብቱ እንደሆነም አስረድቷቸዋል ፡፡ ‹‹ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንም ? ወይስ ሥራ ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን? ከቶ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማነው ?ወይስ ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማነው ? ወይስ  መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማነው ? ይህን  በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁ ? ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ በሙሴ ሕግ ተጽፏል፡፡ እግዚአብሔር ስለበሬዎች ይገደዋልን ?ይህን የሚለው ስለ እኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲከፍል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው በእውነት ስለኛ ተጽፏል፡፡ እኛ መንፈሳዊ ነገር የዘራንላችሁ ብንሆን የእናንተን ሥጋዊ ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን በመቅደስ የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሚሆነውን ነገር እንዲመገቡ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠውያው እንዲካፈሉ አታውቁምን ?እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጓል ፡፡ እኔ ግን በዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምኩም እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፡፡” (፩ቆሮ.፱፥፮-፲፩፤፲፫-፲፭)  ይህን ካለ በኋላ ለምን በዚህ መብት እንዳልተጠቀመ ሲገልጽ “በእኛ ሹመት ሌላ የሚቀድመን ከሆነ የሚሻላችሁን እናንተ ታውቃላችሁ እኔ ይህን አልፈለግሁትም። ነገር ግን የክርስቶስን ትምህርት እንዳላሰናክል በሁሉ እታገሣለሁ” አለ፡፡ (፩ቆሮ.፱፥፲፪) ይህ ታላቅ ሐዋርያ ለእርሱ የተፈቀደውን እንኳ ሳይጠቀም አሁን እኛ ባለንበት ዘመን ጓደኛ ጓደኛውን አላምን ብሎ በሩን ዘግቶ ለራሱ ብቻ ከመኖር ይልቅ በዚህ በክፉ ወቅት አንዱ የአንዱን ድካም ቢሸከም እጅግ መልካም ነበር ፡፡ ምክንያቱም የአንዱ መኖር ለሌላው እጅግ ወሳኝ ነውና። መቼም ሕዝብ ሳይኖር ወታደር፤ ወታደር ሳይኖር መንግሥት ለማን ይነግሣል፡፡ ሕዝብ ሳይኖር ሀገር፤ ሀገር ሳይኖር ሕዝብ ምን ይሆናል? ገበሬ ሳይኖር በሬ ማርባት ለእርድ ብቻ ነው የሚሆነው ስለዚህ ምርት የለም ማለት ነው ፡፡ ምርት ሳይኖር ገበሬው ኑሮ ፤ ገበሬ ሳይኖር የከተማ ኑሮ የእምቧይ ካብ ነው የሚሆነው ፡፡ ስለዚህ የአንዱ መኖር ለሌላው መኖር መሠረት ማለት ነው ፡፡ ለምሳሌ፡-  የትንሹ ዓሣ በትልቁ ዓሣ ነባሪ በሻርኩ ላይ መኖር፡-  ዓሣ ነባሪው ሲመገብ የሚተርፈውን እርሱ ይመገባል፤ ለዓሣ ነባሪው የፅዳት ሥራ ይሠራል፤ ለራሱ ደግሞ የዕለት ምግቡን ከማግኘት በዘለለ በሌሎቹ ምግብ ፈላጊዎች እንዳይዋጥ ጉዳት እንዳይደርስበት ይረዳዋል ፡፡ ይህም ሂደት የጋራ ጥቅም ተብሏል ፡፡ ይህም እርስ በርስ መጠቃቀም ማለት ሲሆን የትንሹን ዓሣ ድካም ዓሣ ነባሪው ተሸክሞ ሲኖር ድካም ተሰምቶት አያውቅም፡፡ ምክንያቱም ስንት ኪሎ ግራም የሚመዝን የራሱን ክብደት ተሸክሞ ይኖራል ፡፡ ስለዚህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የደካሞችን ድካም ተሸክሞ ማለፍ በዓላማው ዝለት ልዩ ልዩ የዓለማችን ድክመት ያፈራረሰውን የሰው ልጅ ልቦና ማነጽ ማለት ነው ፡፡  በአጠቃላይ የክርስትና ሕይወት ለራስ ብቻ ሳይሆን በራስ መኖር ውስጥ ስለሌላውም ጭምር የሚኖርበት ሕይወት ነው። ክርስቶስ እከብር አይል ክቡር፣ እነግሥ አይል ንጉሥ፣ እጸድቅ አይል ጻድቅ ሲሆን ክብር ያጣውን ሊያከብር፣ በጠላት እግር ሥር የወደቀውን ከጠላት አገዛዝ ነጻ ሊያወጣ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ይህን ዓለም እንዳዳነ ሁሉ እርሱን አብነት አድርገው የኖሩት ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሁሉ ለሰው ሲሉ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ትተው ሰዎች ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የሚያገኙበትን ተግባር አከናውነዋል። እነርሱ እየተራቡ ለሌላው ሲያበሉ፣ እነርሱ እየተጠሙ ለሌላውን ሲያጠጡ ኑረዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው” (፩ቆሮ.፱፥፳፪) በማለት የገለጸው እንዲህ ያለውን ተግባር እንድንረዳ ነው። እኛም በእንደዚህ ያለው መልካም ተግባር እንድንኖር እግዚአብሔር ይፍቀድልን።    ወስበሐት ለእግዚአብሔር  ወለወላዲቱ ድንግል  ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !                                               
Read 1429 times