Friday, 16 October 2020 00:00

በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ (የሐዋ.፫፥፮)

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

የቃሉ ተናጋሪ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፡፡ ቃሉን የተናገረበት ምክንያትም እንዲህ ነው፡፡ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ልምሾ ሆኖ የተወለደ በቤተ መቅደስ በር ላይ ተቀምጦ ምጽዋት የሚለምን አንድ ሰው ነበር፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ በበሩ ላይ ተቀምጦ ሳለ አያቸውና ምጽዋት ለመናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ “ወደእኛ ተመልከት አለው፡፡ ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጽዋት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡” ጴጥሮስም “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው ያን ጊዜም እግሩና ቊርጭምጭሚቱ ጸንቶለት ቆሞ እየሮጠ ተራመደ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደቤተ መቅደስ ገባ፡፡ በዚህ ታሪክ ሰውየው ከተቀመጠበት ቦታ፣ ሰውየው ከሚፈልገው ነገር፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ከተናገራቸው ንግግሮች፣ እንዲሁ ለሰውየው ካደረገለት መልካም ነገር በመነሣት ልንማረው የሚገባንን መሠረታዊ ትምህርት አንድ በአንድ ለመመልከት እንሞክር፡፡ ምን እንማራለን ከሰውየው ፡- ሰውየው ከታሪኩ መረዳት እንደቻልነው ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ልምሾ የሆነ ነው፤ በቤተ መቅደስ በር ላይ ሰዎች እየወሰዱት ልመና የሚያከናውን ነው፤ በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት ከደዌው የተፈወሰ ነው፡፡ ስለዚህ ልንማረው የምንችለው ነገር በመጀመሪያ፡- በቤተ መቅደስ በር መቀመጥ ይህ ሰው ችግሮቹ የተደራረቡ ናቸው፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር ለመለመን ተጨማሪ ልመና ማድረግ አለበት፡፡ ምን ማለት ነው ለልብሱ ለጉርሱ የሚሆን ለማግኘት  ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ሽባ በመሆኑ ሠርቶ መብላት አይችልም፡፡ ስለዚህ ያለው ብቸኛ አማራጭ ደግሞ መለመን ነው፡፡ ለመለመን ደግሞ ሰው የሚገኝበትና ምቹ የሆነ ቦታ መሄድ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም መሄድ የማይችል ልምሾ ስለሆነ የሚወስደው ሰው መኖር አለበት፡፡ ይህ ነው የተደራረቡ ችግሮችና ለልመናም ሌላኛ ልመና ማድረግ የግድ የሚያደርገው፡፡ ይሁን እንጂ በሰዎቹ እርዳታ ሰው ከሚበዛበት ምቹ ቦታ ላይ እየሄደ ይለምን ነበር፡፡ ይህ ምቹ ቦታ ደግሞ በወቅቱ የቤተ መቅደሱ በር ነበር፡፡ ይህ በወቅቱ ለሰውየው ምቹ ቦታ የነበረው ቤተ መቅደስ ዛሬም የሚያስፈልገንን ነገር በሙሉ ከእግዚአብሔር ለመጠየቅና ችግራችንን ለመንገር በቤተ መቅደሱ በር መቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በአለንበት ዘመንም ለሰዎች ርኅራኄ የሚሰበክበት፣ ሰው ለመስጠት ልቡናው የሚራራበት፣ ውስጡ የሚነካበትና ለመስጠት ፈቃደኛ የሚሆንባት ቦታ ቤተ ክርስቲያን ናትና በርካታ ችግረኞች ተቀምጠው የዕለት ጉርሳቸውን ይለምኑባታል፡፡ የተቸገሩት ሰዎች ለሥጋቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንደሚጠለሉ ሁሉ መንፈሳዊ ችግራቸውን ለመፍታትም ቤተ መቅደሷ፣ ቤተ ክርስቲያኗ መተኪያ የሌላት ተመራጭ ቦታ ናት፡፡ ለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” (መዝ.፻፳፩፥፩) በማለት ያስረዳን፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ ያለው ችግሮቹ ሁሉ ስለሚፈቱለት ነው፡፡ እኛም የነቢዩን የዳዊትን የትንቢት ቃልና የዚህን የችግረኛ መንገድ የምንከተል ከሆነ ችግራችን በሙሉ ሊፈታ የሚችለው ከቤተ ክርስቲያን በር ስንቀመጥና ችግራችንን ለሚመለከተው አካል ስንናገር ነው፡፡ ችግረኛው ከቤተ መቅደሱ በር ላይ በመቀመጡ ብርና ወርቅ ከሚሰጡት ሰዎች ባሻገር ከደዌው ፈውሰው ዘላቂ መፍትሔ የሚያስገኙለትን ሐዋርያትን አገኛቸው፡፡ እኛም ወደቤተ ክርስቲያን ብንመላለስ ከነፍስም ከሥጋም ቁስል የሚፈውሱንን ካህናትን እናገኛለን፡፡ ከሥጋችን ቁስል ብቻ ሳይሆን ከነፍሳችን ቁስል ተፈውሰን እንደበሽተኛው እግዚአብሔርን እያመሰገንን በሰላም ወደቤታችን እንመለሳለን፡፡  ለምኖ ማግኘት (ጥቂት ለምኖ ብዙ ማግኘት) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከት ላይ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ “ለምኑ ይሰጣችኋልም፤ ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋልም፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልግም ያገኛልና ደጅ ለሚመታም ይከፈትለታልና፡፡” (ማቴ.፯፥፯-፰) የሚል ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ ሰው የፈለገውን እንደሚያገኝ በማመን ከቤተ መቅደሱ በር ላይ ተቀምጦ ይለምን ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምኑ ብቻ ሳይሆን ከምንለምነው በላይ አብዝቶ አትረፍርፎ እንደሚሰጠንም ነግሮናል፡፡ በዚህ መሠረት ይህ ችግረኛ እርሱ ከለመነው በላይ አግኝቷል፡፡ ምክንያቱም እርሱ የለመነው ጊዜያዊ ወርቅና ብር ነው ሐዋርያት ግን  ጤንነትን፣ ፈውስን በነጻነት እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲመላለስ አደረጉት፡፡  እግዚአብሔር አምላካችን ሰጭ እርሱ እንደሆነ አምነን እርሱን እንድንለምን መልካም ፈቃዱ ነው፡፡ እርሱም ለምነነው እንደማያሳፍረን ይልቁንም አብዝቶና አትረፍርፎ እንደሚሰጠን በማይታበል ቃሉ ነግሮናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም ይህን ሲያስረዳ “ጥበብን ያጣት ሰው ቢኖር ሳይነቅፍና ሳይነፍግ ለሁሉ በልግስና የሚሰጥ እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል፡፡” በማለት ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር ሰጭ እንደሆነ አምኖ ለሚለምነው ሁሉ ሳይነቅፍና ሳይነፍግ የሚሰጥ መሆኑን የተረዳው ሐዋርያ አምኖ እግዚአብሔርን ይለምን አለን፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ የእርሱ ገንዘቡ ነውና ሀብታም ድሃ፣ ነጭ ጥቁር፣ ዘር ቀለም አይለይም፡፡ ለሚያምኑት ሁሉ የለመኑትን ያድላቸዋል፡፡ የለመኑትን ብቻ ሳይሆን አብዝቶና አትረፍርፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ለምኖ ማግኘትን ብቻም ሳይሆን ጥቂት ለምኖ ብዙ ማግኘትንም ከአባቶቻችን ሕይወት እንማራለን፡፡ ለማስረጃ ያህል የተወሰኑትን እንጥቀስ፡፡  ዳዊት ፡- ዳዊት እንደልቤ የተባለ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኘ ታላቅ አባት ነው፡፡ በሰውነቱ ቢበድልም ፈጥኖ ወደ ንስሓ የተመለሰና በንስሓ ሕይወቱም አብነት የሚደረግ ሰው ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቅርብ ከመሆኑ የተነሣ ጥቂት ነገር ለምኖ ብዙ ያገኘ አባት ነው፡፡ ዳዊት የለመነውንና የልመናው ምላሽ ሁኖ የተሰጠውን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፡፡   “አቤቱ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤ ለእግዚአብሔር እንደማለ፣ ለያዕቆብ አምላክም እንደተሳለ፤ ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም ወደ መኝታዬም አልጋ አልወጣም፤ ለዐይኖቼም መኝታን ለቅንድቦቼም እንቅልፍን ለጉንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም የእግዚአብሔርን ቦታ የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ እንደተሳለ ዐስብ፡፡ እነሆ በኤፍራታ ሰማነው ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንሰግዳለን” (መዝ.፻፴፩፥፩-፯) እንዲል፡፡ ዳዊት የለመነው ወደ ቤቴም አልገባም ብሎ የተሳለው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስቦ ነበር፡፡ ይህ ካልተፈቀደልኝ ወይም የእግዚአብሔርን ቦታ የያዕቆብን አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ አልተኛም ብሎ ነበር፡፡ ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ቤቱ እንዲሠራለት የፈቀደው በሌላ ሰው ቢሆንም ለእርሱ የተሰጠውና የተፈቀደለት ግን ከዚህ እጅግ የሚበልጠውን ነገር ነው፡፡ ይህ የሚበልጠው ነገርም ነገረ ሥጋዌ ነገረ ድኅነት ነው፡፡ ይህን ደግሞ የእግዚአብሔርን ቦታ የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ሲል የነበረው “እነሆ በኤፍራታ ሰማነው ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን” በማለት የተገለጸለትን ልዩ ምሥጢር እርሱም የምሥጢረ ሥጋዌ የነገረ ድኅነት ጉዳይ እንደሆነ የተናገረው ኃይለ ቃል ያስረዳናል፡፡   በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ፡- በእርግጥ ይህ በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ የለመነው ልመና ጥቂት የሚባል አልነበረም፡፡ እንዲያውም እኛ የዕለት ተዕለት ልመናችን ሊሆን የሚገባው የሰማያዊው ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ እንደ ፈያታዊ ዘየማን በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ ልንል ይገባናል፡፡ ፈያታዊ ዘየማን አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ ብሎ በቅን ልቡና በትሑት ሰብእና በተሰበረ ኅሊና ፈጣሪውን ሲጠይቅ የሚያስፈልገንን ሁሉ ሳንለምነው የሚያውቅና የሚያዘጋጅ እንዲሁ የሚያድለን አምላክ የመለሰለት መልስ ግን ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ የሚል ነበር፡፡ በመጀመሪያ ለማኙ የለመነው ነገር ከዚያም ደግሞ የተለመነው አምላክ የመለሰው ምላሽ እጅግ የሚገርም ነበር፡፡ ለማኙ የኋለኛውን ይጠይቃል ሰጪው ደግሞ ከአሁን ጀምሮ ነው እንጂ እስከኋለኛው ለምን ትጠብቃለህ በማለት መልሱን በቅጽበት መልሶለታል፡፡ ስለዚህ እኛም በእምነት ሁነን ስንለምነው እኛ ከለመነው በላይ የተሻለ፣ ጊዜያዊውን ሳይሆን ዘለዓለማዊውን፣ ሥጋዊውን ሳይሆን መንፈሳዊውን ሀብት ያድለናል፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ያዕቆብ  “አምኖ ይለምን፤ አይጠራጠር፤ የሚጠራጠር በነፋስ የሚገፋና የሚነዋወጥ የባሕር ማዕበልን ይመስላልና” (ያዕ.፩፥፮) በማለት እንደተናገረው የሰው ልጅ ያለምንም ጥርጥር የፈለገውን መለመን ይኖርበታል፡፡ ከቅዱስ ጴጥሮስ ምን እንማራለን፡- ቅዱስ ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ ከመንገድ ላይ ተቀምጦ ወርቅ ብር የሚለምነውን ሰው አገኙት፡፡ በዚህ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ መሄዳቸው፤ እኛም ዛሬ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ጸሎት ማድረግ እንደሚገባን የሚያስረዳን ነው፡፡ ምክንያቱም ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት ወደቤተ መቅደስ ወጡ ብሎ ነው መጽሐፍ ቅዱሱ የሚያስረዳን፡፡ ስለዚህ የጊዜያት ጸሎትንም ሐዋርያት ያደርጉ እንደነበር እንረዳለን፡፡ የሚቀድመውን ማስቀደም  ሕመምተኛው የለመናቸው ወርቅና ብር ነበር፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ከወርቁና ከብሩም ሊሰጠው ከሚችለው ፈውስም በፊት መቅደም ያለበትን ነገር ነገረው፡፡ እርሱም ወደ እነርሱ እንዲመለከት ነበር፡፡ ወደነርሱ እንዲመለከት ማለት በእነርሱ ሃይማኖት እንዲያምን፡፡ እነርሱ የሚያምኑትን ሃይማኖት ካላመነ ሊሰጠው የሚችለው ነገር እውን አይሆንለትም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለችግረኛው የሚሰጠው ነገር ከነበረበት ሕመም መፈወስ ነው፡፡ ከዚህ ከነበረበት ሕመም ለመፈወስ ደግሞ የሚፈወሰው ሰው አስቀድሞ ማመን አለበት፡፡ ስለዚህ ወደእኛ ሃይማኖት ተመለስ አለና የሚቀድመውን ሃይማኖት አስተማረው፡፡ በዚህ የቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር ልንማረው የሚገባው ነገር ቢኖር ማንም ከምግባረ ነፍስም ከምግባረ ሥጋም በፊት ሊያውቀው፣ ሊረዳው፣ ገንዘብ ሊያደርገው የሚገባው ነገር ሃይማኖት እንደሆነ ነው፡፡ ተቀባዩ ብቻ ሳይሆን ሰጪውም ቢሆን አስቀድሞ ለተቸገሩት ሃይማኖትን ማስተማር እንደሚገባ ያስረዳል፡፡ ይህም በተራራው ስብከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብፁዓን መሓርያን፤ የሚራሩ ብፁዓን ናቸው” (ማቴ.፭፥፯) ብሎ ያስተማረውን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሦስት መንገድ ተርጉመውታል፡፡  የወንጌሉ ትርጓሜ እንዲህ ነው፡፡ የመጀመሪያው ምሕረት ሥጋዊ፡- ቀዶ ማልበስ፣ ቈርሶ ማጉረስ፣ ቢበድሉ ማሩኝታ ቢበደሉ ይቅርታ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ምሕረት መንፈሳዊ፡- ክፉውን ምግባር፣ በጎ ምግባር መስሎት ይዞት ሲኖር መክሮ አስተምህሮ ወደ በጎ ምግባር መመለስ ነው፡፡ ሦስተኛው ምሕረት ነፍሳዊ፡- ክፉውን ሃይማኖት በጎ ሃይማኖት መስሎት ይዞት ሲኖር መክሮ አስተምህሮ በጎውን ሃይማኖት ማስያዝ ነው፡፡ ብለው በትርጓሜ ወንጌል አብራርተውታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ያደረገው ከእነዚህ ከሦስቱ አንዱን ምሕረት ነፍሳዊን ነበር፡፡ ይህንም አስቀድሞ ወደ እኛ ተመልከት በማለት የእርሱን ሃይማኖት አስተማረው ከዚያ በኋላ ለበሽተኛው የሚገባውን ሐዋርያውም የሚችለውን አደረገለት፡፡   ማድረግ የሚችሉትንና የማይችሉትን መለየት  ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ አስቀድሞ በእጁ ያለውንና የሌለውን፣ ማድረግ የሚችለውንና የማይችለውን ጠንቅቆ አውቋል፡፡ ይህም “ወርቅና ብር የለኝም ካለኝ ግን እሰጥሃለሁ”  በማለቱ ይታወቃል፡፡ ሐዋርያት ወርቅና ብር እንዳይኖራቸው ያደረገው ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ “በመቀነታችሁም ወርቅ ወይም ብር ወይም መሐልቅ አትያዙ፡፡ ለመንገድም ስልቻ፤ ወይም ሁለት ልብስ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋልና” (ማቴ.፲፥፱-፲)  በማለት በተልእኳቸው ሁሉ ስንቅ ልብስ፣ ጫማ፣ ወርቅ፣ ብር ወዘተ የመሳሰለውን ሁሉ ካልያዝን ምን እንሆናለን እንዳይሉ አስተምሯቸዋል፡፡ ይህ እንዳትይዙ ያላቸው ነገር ለአገልግሎታቸው መሰናክል እንዳይሆንባቸው፡፡ ደግሞም በአጋንንት ላይ ሥልጣን እንደሰጣቸው፣ እባቡን ጊንጡን መጨበጥ እንደሚችሉ ጽኑዕ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋልና ለሚደረግላቸው ሁሉ ጥበቃ እነርሱ በያዙት ነገር የዳንን እንዳይመስላቸው የእርሱን አምላካዊ ጥበቃ በፍጹም እንዲረዱት መልካም ፈቃዱ ስለነበር ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ትምህርት መሠረት በማድረግ አገልግሎቱን የጀመረው ሐዋርያ ምን ማድረግ እንደሚችል ምን  ማድረግ እንደማይችል ከተረዳ በኋላ በቀጥታ በሌለው ነገር አልተጨነቀም ማደረግ የሚችለውን ብቻ አደረገ፡፡ በሌለው ነገር አለመጨነቅ፡- ቅዱስ ጴጥሮስ አስቀድሞ በእጁ ያለውንና የሌለውን፣ ማድረግ የሚችለውንና የማይችለውን ጠንቅቆ ካወቀና ከተረዳ በኋላ እርሱ እጅ ላይ በሌለው ነገርና ሊወቀስበት በማይችለው ጉዳይ መጨነቅ አልፈለገም፡፡ ስለሆነም ሰውየው የሚፈልገው ወርቅና ብር ቢሆንም እርሱ ግን ወርቅና ብር የለኝም ካለኝ ግን እሰጥሃለሁ በማለት የእርሱ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት ተናገረ፡፡ ዛሬም “ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም” ይባላልና በሌለ ነገር ሳይጨነቁ ባለ ነገር ላይ ተመሥርቶ የሚገባውን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ባለን ነገር ላይ ተመሥርተን መልካም ሥራ እንድንሠራ ይጠብቅብናል እንጂ በሌለን ነገር አይጠይቀንም፡፡ የምንችለውን ባለማድረጋችን ግን ተጠያቂዎች ነን፡፡ ያለውን አለመንፈግ፡- አንዳንድ ሰው ያለውን መስጠት አይችልም በሌለውና ሊያደርገው በማይችለው ነገር ግን ይጨነቃል፡፡ ነገር ግን ለመስጠት መሠረቱ ፍላጎት ነው፡፡ የመስጠት ፍላጎት ያለው ሰው ከጥቂቱም ቢሆን ይሰጣል፡፡ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው አንዲት መበለት ካላት ነገር ሰጠች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ አመሰገናት፡፡ ደግሞ ሰው ያለ አንድ ስጦታ አልተፈጠረምና ያለውን ከሰጠ እግዚአብሔር እጅግ ይወድለታል፡፡ ሐዋርያት ወርቅ ብር የላቸውም ይሁን እንጂ ያላቸውን ነገር ከመስጠት ግን ወደኋላ አላሉም፡፡ ምን ነበራቸውና ከምናቸው ይሰጡ ነበር ቢባል መጽሐፍ ቅዱስ “ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ያወጧቸው ዘንድ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ ይፈውሱ ዘንድ በርኩሳን መናፍስት ላይ ሥልጣንን ሰጣቸው” ማቴ.፲፥፩) “ድውያንን ፈውሱ፤ ሙታንንም አንሡ፤ ለምጻሞችንም አንጹ፤ አጋንንትንም አውጡ፤ ያለ ዋጋ የተቀበላችሁትን ያለ ዋጋ ስጡ” (ማቴ.፲፥፰) በማለት የተሰጣቸውን ነገር ያስረዳናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ያለዋጋ የተቀበለው እንዲሁ ያለዋጋ እንዲሰጠው የታዘዘው ብዙ ጸጋ ነበረው፡፡ የተወሰኑትን እንኳን እንደማስረጃ ለመጥቀስ ሃይማኖትን ተቀብሏል፤ ክህነትን ተቀብሏል፤ ሀብተ ፈውስን ተቀብሏል፡፡ ከመንገድ ላይ ተቀምጦ ይለምን ለነበረው ችግረኛም ከእነዚህ ስጦታዎች ሁለቱን ሰጥቶታል፡፡ እነዚህም ስጦታዎች ሃይማኖትና ፈውስ ናቸው፡፡ አስቀድሞ ሃይማኖትን አስተማረው ከዚያም ባመነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲነሣና እንዲሄድ አደረገው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ከተከናወኑለት በኋላ ሰውየውም ያመነውንና የፈወሰውን አምላክ ከሐዋርያት ጋር እያመሰገነ ወደቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ብዙዎች ችግራቸው ከተፈጸመላቸው በኋላ ዙረው አይመለከቱም ይህ ሰውየ ግን የፈወሰውን አምላክ እያመሰገነ ወደቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ከበር ላይ ተቀምጦ ወርቅና ብር ይለምን የነበረው ችግረኛ ወደቤተ መቅደስ ገብቶ እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመረ፡፡ በዚህ ዘመን ዓለምን እያስጨነቀ ያለ ወረርሽኝ እንዲወገድልን ከአባቶች እንደቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጡትን ጸጋ ሳይነፍጉ መለገስ ይጠበቃል፡፡ ከምእመናንም አስቀድሞ ማመንና ከልብ መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን ልመናችንን፣ ጸሎታችንን፣ ጩኸታችንን ሁሉ ላይቀበልልንም ይችላል፡፡ ይህንም በእስራኤል ሕይወት መማር ይቻላል፡፡ ብዙ ጾመው፣ ብዙ ጸልየው፣ ብዙ ጩኸው ነገር ግን እነርሱ የጾሙት እግዚአብሔር በሚፈቅደው መንገድ ስላልነበረ እንደተነቀፈባቸው ነቢዩ ኢሳይያስ ጽፎት እናገኛለን፡፡ (ኢሳ. ፶፰፥፩-ፍጻሜ) የእኛም ጾምና ጸሎት፣ ጩኸታችን ሁሉ እንዳይነቀፍብን አስቀድመን ማድረግ የሚኖርብንን ልናደርግ ግድ ይላል፡፡  በአጠቃላይ ችግራችንን ለመፍታት አስቀድመን ወደቤተ መቅደስ መቅረብ ከዚያም የሐዋርያትን ቃል፣ የካህናትንና የመምህራንን ትምህርት መስማት፣ ርትዕት የሆነችውን የቅዱሳንን ሃይማኖት መከተል፣ ያስጨንቀን የነበረው ችግር ሲፈታልን ደግሞ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል፡፡ ለመምህራን ደግሞ አስቀድሞ እንደቅዱስ ጴጥሮስ መቅደም ያለበትን ነገር ማስቀደም፣ ሃይማኖትን መስበክ፣ እግዚአብሔርን እንዲያውቅ ማድረግ፣ ከዚያም የሚያስፈልገውን ነገር በተቻለ መልኩ ማሟላት ይገባል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ ሰውየው የሚበላው አጥቶ በራብ ሊሞት የተቃረበ ከሆነ ለማናገርና ሃይማኖትን ለማስተማርም እያሰቃየው ካለው የረኀብ ስሜት መውጣት ስላለበት አንገብጋቢ የሆነውን ችግር መመልከት ያስፈልጋል፡፡  እግዚአብሔር አምላካችን ለመምህራንም ጥበቡን ገልጾላቸው፤ ለችግረኞችም ችግራቸውን የሚፈታ አባት አድሏቸው ዕድሜ ልኩን ተደራራቢ ችግሮች ሲያስጨንቁት የነበረው በሽተኛ ባንዲት ቃል ከችግሩ እንደተገላገለና እግዚአብሔርን ለማመስገን እንደበቃ የእኛንም የዕለት ተዕለት ችግር እንዲያስወግድልን የእግዚአብሔር አምላካዊ ፈቃድ ይሁንልን አሜን፡፡   
Read 908 times