Friday, 06 November 2020 00:00

ክብረ ክህነት (ክፍል አራት)

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

የካህናት ኀላፊነት  በክህነት አገልግሎት ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ማዕረጋት አሉ። እነርሱም ጵጵስና፣ ቅስና እና ዲቁና ናቸው። የየራሳቸው ዋና ዋና የአገልግሎት ድርሻም አላቸው። ለምሳሌ፡-  ጳጳሱ፡- አንብሮ እድ ላዕለ ጳጳስ ማለት ጳጳሳት ሲሾሙ እጁን በመጫን መሳተፍ፣ ቀሳውስትን መሾም፣ ዲያቆናትን መሾም፣ ማጥመቅና ቀድሶ ማቍረብ ናቸው። ቄሱ ፡- ማጥመቅና ቀድሶ ማቍረብ ናቸው። ዲያቆኑ፡- መላላክ ነው። በማቴዎስ ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ያስተማረው ትምህርት ይህን ያስረዳል። “መንገድ እንደሚሄድ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ” (ማቴ.፳፭፥፲፬-፲፭) ይህን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት መተርጕማኑ ባለአምስት ጳጳስ ባለሁለት ቄስ፣ ባለአንድ ዲያቆን ብለው ተርጕመውታል። ባለአምሰት ባለሁለትና ባለአንድ ብለው ለጳጳስ፣ ለቄስና ለዲያቆን የሰጧቸውም ካላቸው ድርሻ አንጻር ነው።  እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የአገልግሎት ድርሻዎች በእያንዳንዱ የክህነት ማዕረግ የሚከናወኑ ናቸው። ከላይ ወደታች መጥቶ ማገልገል ይቻላል። ለምሳሌ ጳጳሱ ዝቅ ብሎ የቄሱንም የዲያቆኑም አገልግሎት ማከናወን ይችላል። ቄሱም ዝቅ ብሎ የዲያቆኑን አገልግሎት ማከናወን ይችላል። ከታች ወደላይ ግን አይቻልም። ለምሳሌ ዲያቆኑ የቄሱን አገልግሎት ማከናወን አይችልም። ቄሱም እንዲሁ የጳጳሱን አገልግሎት ማለትም ከእርሱ የአገልግሎት በላይ የሆኑትን አገልግሎቶችን ማከናወን አይችልም። ለምሳሌ ካህናትን መሾም የጳጳስ እንጂ የቄስ ድርሻ አይደለም። ቄስ ክህነት መሾም አይችልም።  ከማሰር ከመፍታት ሥልጣን አንጻርም ፍትሕ መንፈሳዊ በየማዕረጉ ያለውን ሁኔታ  “ወኢይደሉ ለአሐዱሂ እምሊቃነ ጳጳሳት፣ ወጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት ከመ ይፍታሕ ዘአሠሮ ካልኡ ዘእንበለ እምድኅረ ሞቱ፤ ከሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳት ለአንዱስ እንኳን አንዱ ያወገዘውን አንዱ መፍታት አይገባውም ከመሞቱ በኋላ ቢሆን ነው እንጂ” (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፬ ቁጥር ፵፩) በማለት ያስረዳንና “ወሊቀ ጳጳሳትሰ ብውሕ ውእቱ ከመ ይፍታሕ ማእሠሮሙ ለእሉ ኵሎሙ ሶበ ርእየ ዝክተ፤ ሊቀ ጳጳሳት ግን ነገሩን መርምሮ ካወቀ በኋላ እሊህ ሁሉ ያወገዙትን መፍታት ይገባዋል። እስመ ውእቱ ከመ እግዚአ ቤት በላዕሌሆሙ፤ እርሱ በእነርሱ ላይ የሹመት ባለቤት ነውና” ብሎ ያለውን የሥልጣን ደረጃ ያብራራልናል። ይህን ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜው የበለጠ ግልጽ ሆኖ ተብራርቶ እናገኘዋለን። “ሊቀ ጳጳስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፤ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ቄስ ሳለም ከሞተም በኋላ አይፈታውም። ቄስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፣ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ሊቀ ጳጳስ ሳለም ከሞተም በኋላ ይፈታዋል። ሊቀ ጳጳስ ያወገዘውን ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ ያወገዘውን ጳጳስ፣ ኤጲስ ቆጶስ ያወገዘውን ኤጲስ ቆጶስ፣ ቄስ ያወገዘውን ቄስ በሕይወት እያለ መፍታት አይችልም ከሞተ በኋላ ግን ይፈተዋል።” እንዲል። ይህ የክህነት ማዕረግ የቤተ ክርስቲያንን ጽኑዕ የሆነ መዋቅራዊ አደረጃጀትና “እናት አባትህን አክብር” ብላ የምታስተምር ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ደረጃውን የጠበቀ አደረጃጀት እንዳላት ያስረዳናል።  ይህ በእያንዳንዱ የክህነት ማዕረግ የሚከናወን የአገልግሎት ድርሻ ነው። በአጠቃላይ ግን ካህናት በክህነት አገልግሎት ሲኖሩ ምን ምን ኀላፊነቶች አሉባቸው ቢባል የሚዘረዘሩት በርከት ያሉ ቢሆኑም በዚህ ጽሑፍ የሚከተሉትን ብቻ እንመለከታለን። ጠባቂ  ናቸው፡- ካህኑ መንጋዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገቡ ዘንድ ቁልፉ በእጁ ያለ በረኛ ነው። ምእመናን ዘለዓለማዊውን ርስት ይወርሱ ዘንድ ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል። “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል” (ማቴ.፲፮፥፲፱) ተብሎ ይህን ያህል ኃላፊነት የተሰጠው ካህን ምእመናን መንግሥተ ሰማያት ቢዘጋባቸው የእርሱ ድርሻ እንዳለበት ማመን ይኖርበታል። ምክንያቱም መክፈቻው በእጁ አለና። ስለዚህ ካህን ይህን ያህል ኃላፊነት ያለበት ነው።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው ትምህርት እና አንቀጸ አባግዕ ተብሎ በሚጠራው የወንጌል ክፍል “እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደበጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ ወንበዴም ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎቹ ጠባቂ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል።) (ዮሐ.፲፥፩-፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። በዚህ ምንባብ ጠባቂው በጎችን ከመጠበቅ ባለፈ በጎችን የሚጠብቀው እረኛ በበሩ የሚገባ፣ በጎቹን በየስማቸው የሚጠራቸው፣ በጎቹ የሚከተሉት፣ በጎቹን የሚያሰማራ እየተባለ ተገልጾ እናገኘዋለን። በበሩ የሚገባ ሲል በር የተባለው ሃይማኖት፣ ወንጌል፣ ንስሓ ነው፤ በሃይማኖት የሚኖር፣ በአማናዊት ሕግ በሕገ ወንጌል አምኖ የሚኖር እንደሰውነቱ የንስሓን አስፈላጊነት የተረዳና በንስሓ የሚመላለስ ማለት ነው። በጎቹን በየስማቸው የሚጠራቸው የተባለው ደግሞ የሚጠብቃቸውን ምእመናን በትክክል የሚያውቃቸውና አስፈላጊውን ጥበቃ የሚያደርግላቸው ማለት ነው። በጎቹ የሚከተሉት ሲልም ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት የሚያስተምራቸው፣ በሃይማኖት እርሱን መስለው እንዲኖሩ የሚያደርግ በጎቹ በትክክል በአባትነቱ አምነውበት የሚከተሉት ሲል ነው።  ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በሃይማኖተ አበው “የካህኑን ምክሩን፣ ትእዛዙን፣ ተግሣጹን አንሰቀቅ፤ ነፍስን የሚያድን ባለመድኃኒት ነውና፤ የነፍስን ደዌ የሚያርቅ ይቅርና የሥጋ በሽታ የሚያድን ባለመድኃኒትስ ወደ ሥጋዊ በሽተኛ በመጣ ጊዜ ለመድኃኒቱ ከማይስማሙ ምግቦችን ከመመገብ ይከለከል ዘንድ ያዝዘዋል፤ መራራ መራራ ቅጠልን ምረቱ ጭንቅ ሽታው ክፉ የሚሆን ከብዙ ወገን የተቀመመ መድኃኒትን ያጠጣዋል። በድውዩ አካል የተለያየ ሕዋሳትን አንድ ያደርግለት ዘንድ። (ሃ.አበ.፴፯፥፫) በማለት እንደገለጸው ቃሉን በትክክል ሰምተው የሚከተሉት መሆን አለበት። በጎቹን የሚያሰማራ ሲልም  የበጎች መሠማሪያ የተባለች ቤተ ክርስቲያን፣ መንግሥተ ሰማያት ናትና ወደቤተ ክርስቲያን የሚያቀርባቸው በቤተ ክርስቲያን እንዲኖሩ የሚያደርግ ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸው ጽኑ አደራ በመጽሐፍ ቅዱስ “አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (ሐዋ.፳፥፳፰) ተብሎ ተጽፎ እናገኘዋለን። ስለዚህ ካህናት የምእመናን ጠባቂዎች ናቸው። ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው ‹‹ኦ ካህናት አንትሙ ውእቱ አዕይንተ እግዚአብሔር ብሩሃት፤ እናንተ ካህናት ሆይ የእግዚአብሔር ዐይኖች ናችሁና ኃጢአተኛውን እንደ ወንድማችሁ ገሥጹት።” በማለት በቅዳሴው ገልጾት እናገኛለን። ይህም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም ፤ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ በማለት የሰጣቸውን ክህነት እንዳይዘነጉ በማስታወስ ያላቸውን ልዕልና ያስረዳል። ከላይ በገለጽነው ሐሳብ ልዕልናቸውን ብቻ ሳይሆን ኀላፊነታቸውንም ያስረዳል። ምክንያቱም ካሀናት ባያስተምህሩ በሚጠፉት ነፍሳት ሁሉ የመጀመሪያ ተጠያቂዎች እነሱ ናቸውና። የእግዚአብሔር ዐይኖች ከፈጠሯቸው ፍጥረታት ለቅጽበት ያህል እንኳ በጥበቃቸው አይለዩም። ካህናትም ከንስሓ ልጆቻቸው መለየት እንደሌለባቸው ሲያስረዳ አዕይንተ እግዚአብሔር ይላቸዋል።   ሊቁ ካህናትን ብቻም ሳይሆን ዲያቆናትንም እንዲህ ይላቸዋል። “ኦ ዲያቆናት ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ወላዕካኒሃ ምልሑ ውስቴታ ኢየሀሉ ተኵላ ምስለ በግዕ አንቄ ምስለ ርግብ፤ የቤተ ክርስቲያን ፋና የምትሆኑ ዲያቆናት አገልጋዮቿም የሆናችሁ ተኵላ ከበግ ጭልፊትም ከርግብ ጋር እንዳይኖር ለዩ።›› ተኵላ የተባሉ መናፍቃን ናቸው። እነዚህ ከምእመናን ጋር ጭልፊት የተባሉት ደግሞ ኃጥኣን ናቸው። እነዚህም ከጻድቃን ጋር ተቀላቅለው እንዳይኖሩ ለዩ እያለ ዲያቆናትም እንደ አቅማቸው ያስተምራሉና የየድርሻቸውን በትጋት መወጣት እንዳለባቸው ሲያስረዳ እናገኛለን። በቅዱስ ወንጌል “ምሳም ከበሉ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው እርሱም አዎን ጌታዬ ሆይ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው ፤ ጌታችን ኢየሱስም በጎቼን ጠብቅ አለው። ዳግመኛም የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን አለው፤ እርሱም አዎን ጌታዬ ሆይ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ አለው። ሦስተኛ ጊዜ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን? አለው፤ ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን ስላለው ተከዘ ጌታየ ሆይ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ አለው፤ እንኪያስ ግልገሎቼን ጠብቅ አለው።” (ዮሐ.፳፩፥፲፭-፲፯) የሚል ኀይለ ምንባብ እናገኛለን። በዚህ ምንባብ ለቅዱስ ጴጥሮስ ከተሰጠው የጠባቂነት ድርሻ በተጨማሪ ልብ የምንለው ጉዳይ አለ። እርሱም አደራውን ለመስጠት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ነው። በጎቹን በአደራ ለመቀበል የበጎቹን ባለቤት መውደድ መቻል አለበት። እርሱን ደግሞ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስላላወቀ አይደለም የጠየቀው። እንደሚያውቅማ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስም  “እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” በማለት ወዳጅነቱን ገልጾአል። ይሁን እንጂ የእርሱን አሰረ ፍኖት ተከትለው በእርሱ መንበር ተቀምጠው ለመንጋው እረኛ የሚሆኑ ካህናት አደራው እጅግ ጥብቅ እንደሆነ እንዲረዱት፣ አስቀድመውም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች መሆን እንዳለባቸው እንዲያውቁት ነው። ምክንያቱም በጎች የደም ዋጋ የተከፈለላቸው ናቸው። በወርቅ በብር ሳይሆን በደም የተገዙ ናቸውና ኀላፊነቱን በትጋት የሚወጣና የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጆች መሆን ይኖርባቸዋል። መንጋውን ይጠብቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር በአደራ የተቀበለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቋቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን” (፩ጴጥ.፭፥፪) በማለት እርሱም እረኞች እንዲጠብቁ ብቻ ሳይሆን በምን መንገድ መጠበቅ እንዳለባቸውም ይናገራል። መሪ ናቸው፡- ጌታቸን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው የእረኝነት ትምህርት “ሁሉንም አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል በጎቹም ይከተሉታል ቃሉን ያውቃሉና” (ዮሐ.፲፥፬) የሚል ኀይለ ምንባብ እናገኛለን። በዕብራውያን ባህል እረኛ በፊት በፊት እየሄደ በጎቹ ይከተሉታል። እረኛው ካልተንቀሳቀሰ እነርሱም አይንቀሳቀሱም። ካህኑ የምእመናን እረኛ ነውና ከምእመናን ቀድሞ መገኘት አለበት።  እረኛው መሪ ነው ሲባል እንዲሁ በፊት ሆኖ ተከተሉኝ የሚል ብቻ አይደም። ሲከተሉት ተከታዮቹን ወስዶ በመልካም መሰማሪያ ላይ የሚያደርስ ማለት ነው። መልካም መሰማሪያ የተባለች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም መንግሥተ ሰማያት ናት። ስለዚህ መልካም ሥራ ሠርቶ እርሱም የሚጸድቅ መንጋውንም ወደ መልካም ነገር እየመራ የሚያጸድቅ መሆን አለበት። ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠውና በቅዱስ ወንጌል የተጻፈው የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ኀላፊነት “ጠቦቶቼን አሰማራ” የሚል ትእዛዝ ነበረበት። አሰማራ የሚለው ትእዛዝ ከመጠበቅ ባለፈ አቅጣጫ ማሳየትን፣ መምራትን፣ መዋያቸውን፣ ማደሪያቸውን፣ ምግባቸውን፣ አጠቃላይ ለሕይወታቸው አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሙሉ ከማሰብና ከማዘጋጀት ጋር የተያያዘ ነው።   ካህኑ መሪ ነው ሲባል ክርስቲያናዊ ሕይወትን በተግባር እየኖረ የሚያሳይ መሆን አለበት። እንዲህ ከሆነ ሕዝቡም የእርሱን ፈለግ የሚከተል ይሆናል። ይህን አስመልክቶ በፍትሕ መንፈሳዊ “በከመ ይቤ ሆሴዕ ነቢይ እስመ ከመ ይከውን ካህን ከማሁ ካዕበ ሕዝብኒ፤ ነቢዩ ሆሴዕ መምህሩ ደግ ቢሆን ሕዝቡም እንደርሱ ደጋግ ይሆናሉ ብሎ እንደተናገረ ደግ መሆን አለበት” የሚል ኀይለ ቃል እናገኛለን። ይህንም ሲያጠነክር “ ወዓዲ መምህርነ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነ ወጠነ ቅድመ ከመ ይግበር ወይምሀር፤ ዳግመኛም ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ሠርቶ ያስተምር ዘንድ ጀመረ። ወይቤ እስመ ዘይገብር ወይሜህር ዐቢየ ይሰመይ በመንግሥተ ሰማያት፤ ሠርቶ የሚያስተምህር መምህር በመንግሥተ ሰማያት ደገኛ እንዲሆን ተናገረ” ተብሎ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተግባራዊ አስተምህሮ በማስረጃነት ተጠቅሶ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ካህኑ በተግባር እያሳየ መንጋውም እርሱን እንዲከተል ማድረግ እንደአለበት ነው።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልም በተግባርም አስተምሯል። የቅደም ተከተል ጉዳይ ካልሆነ በቀር በተግባር ያልፈጸመውን እኛ እንድንፈጽመው አላዘዘንም። ለዚህም ነው ከላይ በጠቀስነው በፍትሕ መንፈሳዊ “ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ሠርቶ ያስተምር ዘንድ ጀመረ።” የተባለው። ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የሾማቸው ካህናትም እንዲሁ ምእመናንን ሲመሩ እነርሱ በተግባር እያከናወኑ መሆን አለበት።  መጋቢ ናቸው፡- በክህነት አገልግሎት መኖር የክርስቶስ እንደራሴ ሁኖ የክርስቶስን ጸጋ ለምእመናን ማድረስ ነው። በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፬ ቍጥር ፵፯ “ሊቀ ጵጵስና ህየንተ ክርስቶስ ውስተ ዓለም፤ በዚህ ዓለም ሊቀ ጵጵስና መሾም እንደ ክርስቶስ መሆን ወይም የክርስቶስ ምስለኔ መሆን ነው። በእንተ ዐቂበ ሃይማኖት፤ ሃይማኖትን ለማጽናት፣ ወመግቦተ መሃይምናን፤ ምእመናንንም ለመመገብ” ተብሎ ተገልጾ እናገኘዋለን። ስለዚህ ሃይማኖትን አጽንቶ ምእመናንን ከነጣቂ ተኵላ ጠብቆ፣ የሚያሻቸውን ምግብ እየመገበ ይኖራል።  ካህኑ የሚጠብቃቸውን መንጋዎቹን መመገብ የግድ ይለዋል። ጠባቂነቱ፣ አባትነቱ መንፈሳዊ ነውና መንፈሳዊውን ምግብ የእግዚአብሔርን ቃል ዕለት ዕለት እየመገበ ማኖር አለበት። በቅዱስ ወንጌል “ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰቡ ላይ የሚሾመው ደግ፣ ታማኝና ብልህ መጋቢ ማን ይሆን? ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው አገልጋይ ብፁዕ ነው” (ሉቃ.፲፪፥፵፪-፵፫) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ካህኑ እግዚአብሔር በምእመናኑ ላይ የሾመው መጋቢ ነው። በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው ተግቶ የሚመግብ ደግሞ እጅግ የላቀ ዋጋ ያገኛል። የሰው ልጅ በባሕርዩ ምግበ ሥጋም ምግበ ነፍስም የሚያሻው ሆኖ ተፈጥሯል። የተለየ ጸጋ ኖሮት ያለ ምግበ ሥጋ መኖር ቢችል ያለምግበ ነፍስ መኖር አይችልም። ካህኑ እንዲጠብቃቸው በአደራ የተሰጠውን መንጋዎቹን ምግበ ሥጋቸውንም  ምግበ ነፍሳቸውንም ማዘጋጀትና መመገብ ግዴታው ነው። ምን አልባት ምግበ ሥቻውን በተመለከተ እርሱ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ማገዝ ባይችል እንኳን ልጆቹን እያስተባበረ በማኅበራዊ ኑሯቸው እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ እያደረገ ችግራቸውን እንዲፈቱ ማድረግ አለበት።  ምክንያቱም በሥጋዊ ችግራቸውም አቅሙ በፈቀደ መጠን መሳተፍ አለበት። ይህን በተመለከተ በመጽሐፈ ዲድስቅልያ “ሰውን ወዳጅ፣ እንግዳን የሚቀበል፣ ፊት አይቶ የማያዳላ፣ ለባለጸጋና ደሃ የማያዳላ፣ ፈራጅ፣ ጥበብ ያለው፣ ለመስጠት እጁን የሚዘረጋ፣ ረዳት የሌለውን የሚቀበል፣ ድሆችን፣ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን የሚወድ ይሁን፤ ዳግመኛም ልጆች ያሏቸውን ይመግብ” (ዲድስቅልያ አንቀጽ ፬ ቍጥር ፲፬) የሚል የሐዋርያትን ትእዛዝ እናገኛለን። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም በመልክቱ “ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቀቡት” (ያዕ.፭፥፲፬) በማለት የገለጸው በደዌ ነፍሳቸው ብቻ ሳይሆን በደዌ ሥጋቸውም መጨነቅ እንዳለባቸው፣ በነፍስ ረኀባቸው ብቻ ሳይሆን በሥጋዊ ረኀባቸውም እንዲጨነቅ ሲያስረዳን ነው። መሪ ነው ሲባልም እንዲህ ያለውን ሁሉ እያስተባበረ የመፍትሔ አካል መሆን እንዲችል ነው። ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ ካህኑ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ግን የመንፈስ ልጆቹ ናቸውና ለመንፈሳዊ ምግባቸው ነው። ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ምግባቸው ምንድን ነው? ከተባለ ተፈጥሯቸው በአንድ በኩል ከባሕርየ እንስሳ ነውና  ምግበ ሥጋ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ በሌላ በኩል ደግሞ በባሕርየ መላእክት ነውና እንደ መላእክት ምግባቸውም ቃለ እግዚአብሔር ነው። የመላእክትን ምግብ በተመለከተ ሊቁ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ “ወሲሳዮሙ ለመላእክት ቅዳሴ ወስብሐት ወስቴሆሙ ፍቅረ መለኮት፤ የመላእክት ምግባቸው የእግዚአብሔር ቃል መጠጣቸውም የመለኮት ፍቅር ነው” (አክሲማሮስ ዘዕለተ እሑድ ክፍል ፬ ቍጥር ፲፮) በማለት ያስረዳናል። እንደ መላእክት የእግዚአብሔርን ቃል የሚመገቡ መሆናቸውን ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወኅብስተ መላእክት በልዑ እጓለ እመሕያው፤ የመላእክትንም እንጀራ የሰው ልጆች በሉ” (መዝ.፸፯፥፳፭) በማለት ያስረዳናል። ስለዚህ ካህኑ የመንጋዎቹ መጋቢ ነው። ሲባል ሊመግባቸው የሚገባው የእግዚአብሔርን ቃል ነው። በእግዚአብሔር ቃል ኮትኩቶ ማሳደግ ቃለ እግዚአብሔር የዕለት ተዕለት ምግባቸው እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል። በቅዱስ ወንጌልም “ ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተጽፏል” (ማቴ.፬፥፬) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ካህኑ ለምእመናን የእግዚአብሔርን ቃል እየመገበ ከቤቱ እንዲኖሩ ማድረግ፣ በንስሓ ሕይወት እንዲመላለሱም ማስቻል፣ መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰውን፣ የተዘጋችውን የገነትን በር የከፈተውን ሥጋ ወደሙ ማቀበል ዋነኛ ድርሻውና ኃላፊነቱ መሆኑን  ነው። የጠፉትን የሚፈልጉ ናቸው፡- በቅዱስ ወንጌል የዐመፅ ጥያቄን ያዥጎደጉዱት ለነበሩት ጸሐፍት ፈሪሳውያን ኃጢኣተኞችን ይቀበላል ከኃጢኣተኞችም ጋር ይበላል ብለው ላቀረቡለት ጥያቄ የሚሆን መልስ “ከእናንተ መካከል መቶ በጎች ያሉት ሰው ቢኖር ከእነርሱ አንዲቱ ብትጠፋው ዘጠና ዘጠኙን በምድረ በዳ ትቶ እስኪያገኛት ድረስ ይፈልጋት ዘንድ ወደጠፋችው በግ ይሄድ የለምን? በአገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በትከሻው ይሸከማታል” (ሉቃ.፲፭፥፬) ተብሎ እንደተጻፈ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን አዳምን ይፈልግ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ። የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን አዳምን እንደፈለገ ሁሉ እርሱ የሾማቸው ካህናትም ዋነኛ ተግባራቸው የጠፋውን የአዳምን ልጅ መፈለግ ነው። መጥፋት በአካል ብቻ ላይሆን ይችላል። በመንፈስም መጥፋት አለ። ካህናት መንፈሳዊ ጠባቂዎች ናቸውና በመንፈስ የጠፋውን ፈልጎ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። ጌታችን ጠፍተው ስለተገኙ ሦስት ነገሮች እና ጠፍተው በመገኘታቸው በባለቤቶቹ ዘንድ ምን ያህል ደስታ እንደሚደረግ ሲያስተምር ጠፍተው ከተገኙት ከሦስቱ ነገሮች መካከል አንዱ በቤት ውስጥ የጠፋ ነበር። ጠፍታ የተገኘችው በግ በጠባቂው ግዴለሽነት የጠፋች ናት፤ የጠፋው ልጅ ደግሞ በጥጋቡ ከቤት ኮብልሎ የወጣና ከአባቱ ቤት መለየቱ አላዋጣህ ሲለው በራሱ ጊዜ ተመልሶ የመጣ ነው። ጠፍቶ የተገኘው ድሪም ግን በቤት ውስጥ ከቆሻሻ ጋር ተቀላቅሎ የነበርና ባለድሪሟ በመብራት ፈልጋ ያገኘችው ነው። (ሉቃ.፲፭፥፩-፳፬) ካህናት እረኞች ናቸውና ቢቻል አስቀድመው መንጋቸው እንዳይጠፋ ተግቶ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ካልተቻለ የጠፋበትን ምክንያት፣ የት እንደጠፋ ማለት እንደበጊቱ በእረኛው ግዴለሽነት ነው? ወይስ እንደጠፋው ልጅ በራሱ ጥጋብ ነው? ወይስ ደግሞ በቤት ውስጥ ከጥራጊ ወይም ቆሻሻ ጋር የተደበቀ ነው? በማለት መለየትና ፈልጎ ማግኘት ይኖርባቸዋል። እንደ ዲናሩ ከቤቱ እያለ ግን በዓለም ቆሻሻ ተውጦ ይሆን፣ በቤተ ክርስቲያን እየተመላለሰ፣ በሚገባ የማይጸልይ ከሆነ፣ የማይጾም ከሆነ፣ ንስሓ የማይገባ ከሆነ፣ ሥጋ ወደሙ የማይቀበል ከሆነ በቤቱ አለ ግን በኃጢያት ቆሻሻ ተውጦ መገኘት አልቻለም ማለት ነው። ስለዚህ እንደባለዲናሯ መብራት ማብራትና መፈለግ የካህኑ ድርሻ ይሆናል። ካህናት እነዚህንና የመሳሰሉትን ኃላፊነቶች ለመቀበል በቅድሚያ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መረዳት፣ ለዚህ ኃላፊነት የሚያበቃ ዝግጅት ማድረግ፣ ማለትም በትምህርትም፣ በምግባርም፣ በቁርጠኝነትም ወዘተ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲሁ የክርስቶስ ወዳጅ መሆን አለባቸው። ምክንያቱም በኃላፊነት የሚቀበሏቸው መንጋዎች በምድራዊ ወርቅና ብር የተገዙ ሳይሆኑ በደም የተገዙ ናቸው። ይህን በተመለከተ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ። ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ” (፩ጴጥ. ፩፥፲፰-፲፱) በማለት ያስረዳናል። ስለዚህ እንደዚህ የከበረ ዋጋ የተከፈለላቸውን ምእመናን ለመጠበቅ የሚያበቃ ትጋት ያስፈልጋል።  በአጠቃላይ በክህነት አገልግሎት የሚኖሩ ካህናት ኃላፊነታቸው እጅግ ከባድና በአግባቡ ከተወጡት ግን ሰማያዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ መሆኑን መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም መንጋውን በአግባቡ ሊጠብቁት፣ ወደሚፈለገው ቦታ ሊመሩት፣ የሚያስፈልገውን ምግብ ሊመግቡትና ቢጠፋ እንኳን ፈልገው ከጠፋበት ሊመልሱት እንደሚገባቸው ራሳቸው ካህናቱም መረዳት አለባቸው ምእመናንም እንዲሁ ይህን ጥብቅ አደራ ተረድተው በተቻለ መጠን የካህናት ትእዛዝ ሊቀበሏቸው ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ ኀላፊነቱን በሚገባ የሚወጣ ጠንካራ አባት እንዲያድለን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን።  
Read 1277 times