Friday, 06 November 2020 00:00

የአደራ ደብዳቤ

Written by  ዲ/ን አሸናፊ ደሳለኝ

Overview

ታላቁ የሕይወት መምህሬ አለቃ ዜና በሕይወተ ሥጋ በግዙፉና በተዳሳሹ ኑባሬ  ዛሬን የሉም ልበል እንጂ ‹‹ሞቱ›› የሚለውን ገዳይ ቃል ለእርሳቸዉ መጠቀም ታላቅ በደል ሆኖ ይሰማኛል።  ምክንያቱም ምንም እንኳን በአካለ ሥጋ በላገኛቸዉም ዘወትር በየዕለቱ ምክርና ተግሣጻቸዉን እንደ ተናፋቂ ዘመድ በመንፈስ ደብዳቤ ከትበው በዐጸደ ነፍስ ይልኩልኛልና። እነዚያን ልዩ የሕይወት ደብዳቤዎች ባነበብኩ ቁጥር  መንፈሴ ይበረታል፤ በወንዝ ዳር እንደ በቀለች፣ ፍሬዋንም በየጊዜው እንደምትቸር ተክል (መዝ. ፩፥፫) ልምላሜ ይሰማኛል። ለዛሬ  ከእነዚህ ልቤን ከሚያበረቱት ጦማሮች አንዱ የሆነውን አካፍላችሁ ዘንድ እሻለሁ ። ቀን /፲፪/፪/፳፻፲፪ ዓ.ም የተላከ ከአለቃ ዜና  ይድረስ ለመንፈስ ልጄ ………. ልጄ ሆይ እንደ ምን አለህ? ጤናህስ እንዴት ይዞሃል? በትጋት ከሐኪምህ ዘንድ ዕለት ዕለት   እየተከታተልህ ነዉን? አየ. . . ልጄ አንተ እኮ የዋሕ ነህ። አሁን ይህንን ባልኩህ ጊዜ  አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ስለ ክቡር ሞቱና  ትንሣኤዉ ለመንገር በሕንጻ ቤተ መቅደስ እንደ መሰለላቸዉ (ዮሐ.፪፥፲፱)፣ አይሁድም ስለ ሕንጻ ቤተ መቅደስ የሚናገር እንደ መሰላቸው ሁሉ፡ አንተም ይህን ደዌ ሥጋን የጠየኩህ መስሎህ ስለ ራስ ምታትና ቁርጠት እያሰብክ ይሆናል . .    እንዲያም አይደል ልጄ፤  እርግጥ ነው እንበለ ሥጋ …  እንዲሉ አበው  የሥጋ ጤንነትህ ቢያሳስበኝም . .  እኔን የበለጠ የሚያስጨንቀኝና የሚያሳስበኝ፣ የጠየኩህም የነፍስህን፣ የመንፈስህን ደኅንነት ነዉ። ሐኪሙም መምህረ ንስሓህ (የንስሓ አባትህ) ነው። እናም  የቀለም ልጄ የመከርኩህንና ያሰተማርኩህን አደራ፤ ዘወትር  የነፍስህ ሐኪም ወደ ሆነዉ የንሰሐ አባትህ ብቅ እያልክ እራስህን በኑዛዜ አስመርምረህ የፈውስህ ምክንያት ይሆን ዘንድ ቀኖና መድኃኒትህን በሚገባ ትከታተል ዘንድ አደራ እልሃለሁ።  ይህንን ለሰላምታ ያህል ካልኩህ ዘንዳ  ዛሬ  ነፍሴ የታዘበችህንና ላስታውስህ  የምሻውን ቁም ነገር  ልጽፍልህ ወደድኩ።  ሰላመ እግዚአብሔር አይለይህ ።

 

ሰሞኑን በተዛባ ሚዛን የመንፈሳዊ አገልግሎትህን ስኬት እየመዘንህ የምታሳየዉን ከንቱ እርካታ እና ተዐብዮ ነፍሴ ተመልክታ እጅግ አዝናብሃለች። እናም ‹‹ልጄ የአበው ሐዋርያትን ፈለግ አልተከተለምን›› ስትል  ነፍሴ ተጨንቃለች። ልጄ ‹‹እንግዲህ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ የማንጠቅም  ባሪያዎች ነን  ልናደርግ የሚገባንን አድርገናል በሉ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ አላስተዋልክምን? (ሉቃ.፲፯፥፲)። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሥጋን ተዋሕዶ የምሥራቹን ወንጌል በሚሰብክበት ዘመን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ መዘገቡት ዕለተ ሆሣዕና እና ዓሣና እንጀራን አበርክቶ ያበላበት ዕለት ብዙ ቍጥር ያለው ሕዝብ በደስታና በእልልታ በጌታችን ዙሪያ ከተሰበሰበባቸው ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው። 

ልጄ ልብ ብለህ አድምጠኝ የበጎቹ ሁኔታ ግድ የሚለው ትጉኅ እረኛ የሆነ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ዓሣና እንጀራን በበረከተ ጊዜ ቁጥሩ የበዛ ህዝብ ተከትሎት ነበር።  ነገር ግን ልብ አድርግ ልጄ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ዘገቡት አበው መተርጉማን ሊቃውንት እንደ ተነተኑት ከዚህ ሁሉ ሕዝብ ቅዱስ ቃሉን ሰምተው የዘለዓለምን ሕይወት ይወርሱ ዘንድ መከራ መስቀሉን ተሸክመው ዓለምን እስከ ግሳንግሷ ትተው በንጹሕ ልብ የተከተሉት እጅግ ጥቂቶች ነበሩ። ብዙኃኑ ግን ምድራዊ ምክንያትን  አንግበው፣ ሥጋዊ ጥቅምን ሽተው፣ የተገኙ ነበሩ (ትርጓሜ ወንጌል)። ልጄ ያቺ  የቁርጥ ቀን በመጣች ጊዜ በጌታችን  የሕማሙ ሰሞን በቀራንዮ አደባባይ እነዚህ በመንጋ የተከተሉት ምሥጢሩን ያላወቁት ብቻ ሳይሆኑ ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል እንኳ ከጥቂቶች በቀር ብዙኃኑ ሸሽተው እየተሸሸጉ ‹‹አላውቀውም›› ሲሉ የከዱት ለዚህ ነው። 

እናም ውድ ልጄ ሁሌም በመንፈሳዊ አገልግሎትህ ዙሪያ ብዙኃን በከበቡ በተከተሉህ ጊዜ በስሜት ሳይሆን በመንፈስ ትቃኝ ዘንድ ግድ ነው። በእያንዳንዱ መንፈሳዊ አገልጋይ ሕይወትና አገልግሎት (የዝማሬ፣ የደስታና፣ የሐሤት ጊዜ) አለ፤ ነገር ግን ከዚህም ሁሉ በኋላ ድካም፣ ሕማም፣ ኀዘንና ሰማዕትነት መኖሩ የክርስትናው ግዴታ  የክርስትናው መሥዋዕትነት ነው። እናም ልጄ በእነዚህ የመንፈሳዊ አገልግሎት ሂደቶች ውስጥ አንድ አገልጋይ የመንፈሳዊ አገልግሎቱን ስኬት መችና እንዴት መለካት እንዳለበት ልብ ልትለው ይገባሃል። በዘመናችን አንተንም ጨምሮ የብዙ አገልጋዮች ትልቁ ጉድለት የመንፈሳዊ አገልግሎትን ስኬት በተዛባ ሚዛን፣ መንፈሳዊ ውጤትን በሥጋ መለኪያ፣ ዘላለማዊ ተልእኮን በሚያልፍ በሚጠፋ መስፈርት ሊለኩ፣ ሊዳኙና ሊመዝኑ መውተርተራቸው ነው።

መልካም ግልጋሎትህን አይቶ መንፈሱን ሳይሆን ጊዜያዊ ስሜቱን ብቻ አንግቦ ወዳንተ የመጣውን ምዕመን ተመልክተህ ራስህን አስታብየህ የመንፋሳዊ አገልግሎት የስኬት ማማ ላይ እንደ ወጣህ ካሰብክ እውነት እውነት እልሃለሁ ልጄ ያኔ የውድቀትህ መጀመሪያ እንደ ሆነ ያለ ጥርጥር እነግርሃለሁ . . . አዎ ልጄ ‹‹ምን አይቶብኝ ነው፤ ምን አጉድየ ነው፤ የቀለም አባቴ  እንዲህ የሚወቅሰኝ?›› እያልህ እንደ ሆነ በዓይነ ኅሊና እየተመለከትኩህ ነው . . . እናም እነግርሃለሁ ለብዙ የአገልግሎትህ ዘመናት ታዝቤሃለሁ ዝም  ብየ አልፍህ ዘንድ አልችልም፤ ምንም እንኳ ጆሮዎችህ ውዳሴን እንጂ ተግሣጽን ለመስማት ባይጓጉም ተሳስተሃልና ደግሜ ደጋግሜ እነግርሃለሁ። 

አሁን እንኳ በዚህ ሰሞን ባዘጋጀኸው ‘ታላቅ!’ ብለህ በጠራህው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ በንስሓ ወደ ልቡ የተመለሰውን ፤ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘቡ አድርጎ  ቅዱስ  ሥጋውንና ክቡር ደሙን የተቀበለውን፤ በስብከተ ወንጌሉ፣ በቃለ እግዚአብሔሩ ልቡ ተሰብሮ ከኃጢአት ዓለም  ከካራን ወደ ከነዓን የተመለሰውን ልትቃኝ ሲገባህ በዐውደ ምሕረቱ ቅጥር ግቢ የታጨቀውን የምዕመን ብዛት ለመቁጠር እየተቸገርህ . . . ጠጠር መጣያ ጠፋ፤ እንበዛለን ገና፤ ጠላት ዓይኑ ይፈሰስ፤ ወዘተ…  እያልህ  ከጌታችን መሰቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ ያለውን የቅዱስ ጳዉሎስን ቃል ረስተህ በእግዚአብሔር መመካት  ትተህ በራስህና በአገልግሎት ትጋትህ ሰትመካ በማየቴ፣ ይህንኑ ቁጥር የሚስተካከል ምዕመን ከእግዚአብሔር ርቆ የሥጋውን ደስታ ጠብቆ እንደሚንከራተት በመዘንጋትህ እውነት አዝኜብሃለሁ፡ 

በዐውደ ምሕረቱ ቅጥር ሙሉ ቅዳሴውን ሳይታደም፣ ከሥርዓተ ቅዳሴው መጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት እንደ ደራሽ የውኃ ሙላት የተግተለተለውን ምእመን አይተህና ተመልክተህ  ልብህ በሐሤት ጮቤ ስትረግጥ፤ በዕለቱ ‹‹እሰመ ኃያል አንተ›› ብለው ልዑካኑ የዘለዓለም ሕይወትን ያቀብሉ ዘንድ በክብር በቆሙ ጊዜ፡  ይቀበል ዘንድ የተገባ ራሱን አዘጋጅቶ  የተጠጋ አንድም ሰው አለመቅረቡን ችላ ብለህ እንዳላየህ ስታልፍ በኀዘን ስመለከትህ ነበር። እውነት እልሃለሁ ልጄ  ከአንጀቴ ነው ያዘንኩት።

ደግሞ ይባስ ብሎ ባለፈው ለበዓለ ጥምቀት ቅዱስ ታቦቱን አጅቦ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን የምናስታውስበትን ነጭ ነጠላ በትዕምርተ መስቀል ሳይላበስ፤ በእጆቹ  መከራ መስቀሉን፣  መንፈሱን ሳይሆን ስሜቱንና ሞቅታውን  ይዞ የወጣውን  በአካለ ሥጋ  የገዘፈ በመንፈስ (በነፍስ) ግን የቀጨጨ ወጣት እያነሣህ፡ ይህንን ወጣት እንዴት ወደ ሕይወት መንገድ እንደምትመልሰው ከማሰብ ይልቅ  በኩራት ስትታበይና በደስታ ስትዘል  ሰምቼሃለሁ፤ ይህንም በማየቴ እጅግ አዝኛለሁ አልዋሽህም  ልጄ።

አስተውል ልጄ ዓይኖችህ  የነፍስን  መዳን በትኩረት እና በጉጉት ይመለከቱ ዘንድ አጥብቄ እሻልሁ የአገልግሎትህን ስኬት፤ የልፋትህን ዋጋና የድካምህን ውጤት ልትመዝን ካሻህ ትኩረትህ ልታደርግ የሚገባህን እነግርሃለሁ ልብ ብለህ አድምጠኝ …. አምላክህ የዘለዓለም ሕይወትን ሊወርስ የሚሻ ሰውን ጭምር እንጂ የሕዝብ ቁጥር ብዛት ብቻ አይሻም። ይህንንም ልብ ትለው ዘንድ አስታውስ ከዚያ ሁሉ የስጦታ ጋጋታ ከውስጧ ተጨንቃና ተጠባ ያለቻትን ትንሽ መክሊት የቸረችውን ያችን መበለት በፍቅር ዓይን ተመልክቶ ከፍ ከፍ  ያደረጋትን፤ ከስምዖን የገነነ የማዕድ ግብዣ ይልቅ በንስሓና ጸጸት የታጀበዉን የማርያም ባለ ሽቶዋን ስጦታ በፍቅር መቀበሉን፤ አስራ ሁለቱን ሐዋርያት ጨምሮ ቁጡሩ እጅግ የበዛ  ህዝብ እየተጋፋዉ ባለበት ሁኔታ በእምነት የሆነዉን ያቺ አስራ ሁለት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረች ሴት የልብሱን ጫፍ ስትዳስስ መቀበልን ልብ ልትል ይገባል።

ስለዚህ ልጄ ሁሌም ከአገልገሎትህ በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ትጠይቅ  ዘንድ አደራ እልሃለሁ። ‹‹በእኔ አገልግሎት ስንት ሰው በቃለ እግዚአብሔር ልቡናው በርቶ ወደ ራሱ ተመለሰ? በእኔ አገልግሎት ስንት ሰው ወደ ንስሓ ሕይወት ተቀላቀለ? በእኔ አገልግሎት ስንት ሰዉ ወደ መምህረ ንሰሓው ተመላልሶ ኑዛዜና ቀኖናውን ፈጽሞ ለታላቁ ክብር ለቅዱስ ሥጋው ለክቡር ደሙ በቃ? እንዲያው በጥቅሉ ወደ መልካሙ ጎዳና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ምን ያክል ነፍሳትን አሻገርኩ?›› ማለትን ልማድህ ታደርግ ዘንድ ይገባሃል ውድ ልጄ።

ይህን ምክር ‹‹አልሰማም፣ አያሻኝም›› ብለህ ግን ሁሌም አገልግሎትህን በዕልልታና በሆታ መንፈሱን ጥሎ ስሜቱን ብቻ አንጠልጥሎ የሚከተልህን የሕዝብ ጋጋታ ተመልክተህ፤ በከንቱ ውዳሴ ተታለህ፣ መንፈስህ በቀላሉ ሐሴት የሚያደርግ ከሆነ እውነት እልሃለሁ ድካምህና ልፋትህ ጉምን እንደ መዝገን ነፋስን እንደ መጨበጥ ከንቱ ነው ። መጻሕፍትን ከግል ስሜትህና ከሥጋ ፈቃድህ ታቅበህ በንጹሕ አእምሮ በፍቅር ለመመልከት ጥረት አድርግ። እውነተኛና ጥቡዓን ሊቃውንትንም መርጠህ ጠይቅ ያኔ አገልገሎትህ ሰዎችን ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚያስደስት ይሆንልሃል።

ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር 

የቀለም አባትህ አባ ዜና

በነፍስ የሚታይ ፊርማና ማኅተም

 

Read 1067 times