Friday, 04 December 2020 00:00

የጥያቄዎቻችሁ መልስ 

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ውድ አንባብያን በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዓምዳችን ወቅታዊውን የሀገራችረን ጉዳይ በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትን መምህር ግርማ ባቱን ጋብዘን። ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ንባብ። ሐመር፡- መምህር ወቅቱን መሠረት ያደረጉና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ለምናነሣቸው ሐሳቦች ምላሽ ለመስጠት ፈቀደኛ ስለሆኑልን አስቀድመን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።  መምህር ግርማ ባቱ፡- እኔም  ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። ሐመር፡-  በሀገራችን እየተስተዋለ ያለው ጦርነት በቤተ ክርስቲያን እይታ ሲታይ ከምን የመጣ ነው ብለው ያምናሉ? መምህር ግርማ ባቱ ፡- ታሪኩ ረጅም ነው በተቻለ መጠን በአጭሩ ለመመለስ አሁን እየታየ ያለው ውጤት የረጅም ጊዜ ሂደት ነው። ሂደቱ ያስከተለውን የብዙ ችግሮች ውጤት ነው አሁን እየተመለከትን ያለነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ላለፉት ከ፴-፵ ዓመታት ያህል ሀገሪቱ ስትከተለው የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት፡-

 

ሀ.  የቤተ ክርስቲያንን ሚና ያገለለና ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደጠላት የፈረጀ ነበር ማለት ይቻላል። ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፈውን ትምህርቷን፣ ሥርዓቷን፣ ባህሏን በሙሉ የናቀው አካሄድ ይህን አላመጣም ማለት አይቻልም። የረጅም ጊዜ ሂደት የሚያሰኘውም ይህ ነው። 

ለ. ይህን ካነሣን ዘንድ በእነዚህ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ ደግሞ ሰዎች በእኩልነት ተከባብረውና ተረዳድተው ከሚኖሩበት የኑሮ መስመር ይልቅ ልዩነታቸው ላይ የሚያተኩሩበትን መስመር ማቀንቀን ስለነበር ይህ ሁሉ ተደማምሮ አሁን የምናየውን ችግር አስከትሏል።

ሐ. የኋላ ታሪክ አጻጻፋችን፣ አጠናናችን በተለይ ከመካከለኛው ዘመን ፲፮ኛው እና ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ለዘመናዊ ቀረብ ባሉ ጊዜያት የተጻፉ የታሪክ መጻሕፍት፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን ደጋግሞ በማጠንጠን ብሔር ከብሔር እንዲጋጭ፣ ክልላዊ መዋቅሮች የበለጠ በተካረረና በተለያየ ሁኔታ እንዲቆሙ የተደረገበት የፖለቲካ ሥርዓት ለዚህ ትልቁን ዋጋ አስከፍሏል። ይህ እንደ መነሻ ከተጠቀምነው ዋናው ነገር ግን ሊታረቅ የማይችል ሆኖ ሳይሆን እንዳይታረቅ  አስታራቂ የነበሩ አካላት ተገልዋል ከመድረኩም ወጥተዋል። 

በአስታራቂነት ደግሞ ተቀዳሚ ሚና ስትወጣ የበረችው ቤተ ክርስቲያን ሚናዋን እንዳትጫወት፣ እንዳትወጣ የተደረገችበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ የቅርቡን እንኳ ብናነሣ በ፲፰፻፸ዎች ውስጥ በአፄ ዮሐንስና በአፄ ምኒልክ መካከል ትልቅ የተካረረ ጠብ ነበር። ወደ ጦርነት ይገባሉ የሚል ስጋትም ነበር። በዚህ መሀል ገብተው  ጉዳዩን በእርቅ የፈጽሙትና አፄ ዮሐንስንና አፄ ምኒልክን በአንድ ጉባኤ እንዲቀመጡ ያደረጓቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው።  

ወደ ኋላ እንሂድ ቢባልም በሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥትና የዛጉዌ ሥርወ መንግሥታት በሁለቱ መካከል ከፍተኛ ግጭቶች ይኖራሉ ተብሎ በታሰበበት በዚያ ጊዜ እንኳን እነ አቡነ ተክለሃይማኖት እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የሠሯቸው  የአስታራቂነት ሥራዎች የቤተ ክርስቲያናችንን ተደማቀጨነትና የአስታራቂነት ሚናዎች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። 

ስለዚህ ይህ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከምን የመጣ ነው? ተብሎ ሲታሰብ ሰው በሰውነቱ አንድ ሆኖ ተከባብሮ እንዲኖር የምታስተምረው ቤተ ክርስቲያን የአደባባይ ሥራዋ የዐውደ ምሕረት ሚናዋም እንዲያው በማኅበረሰቡ ውስጥም ጠንከር ባለ መልኩ የምትጫወተው ሚና ተገፍቶ  ሰዎች ተለያይተው እንዲቆሙ እየተፈቀደ ያለበት ሥርዓት ነው።

ሐመር፡- ይህ እየተስተዋለ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ችግር ምን ሊሆን ይችላል?

መምህር ግርማ ባቱ ፡- የምንዘረዝራቸው ብዙ ናቸው። በመጀመሪያ የጦርነት መልካም ነገር ወይም መልካም ውጤት የለውም። ጦርነት የመጨረሻ አማራጭ ነው፣ የህልውና ጉዳይ፣ በሕይወት መጠበቂያ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ፣ የድንበር ማስከበሪያ ያም ሲከፋና አማራጭ ሲጠፋ የሚወሰድ ምርጫ ነው። ይሁን እንጂ ምን ምን ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል የሚለውን ስንመለከት   

፩. የሰው እልቂት፡- ጦርነት ሰላማዊነት ስለሌለው ደም አፍሳሽም ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ችግር ብዙ ነው። ከሁሉ አስቀድሞ መታወቅ ያለበት የሰው ልጆች አጠቃላይ ችግር የቤተ ክርስቲያን ችግር መሆኑ ነው። ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጆችን ሁለንተናዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ የቆመች መንፈሳዊ ተቋም ናት። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያስከትለው የመጀመሪያው ችግር ሰዎችን በአንድነት እንደ ኢትዮጵያዊነት እንዳይኖሩ ማድረግ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአንድነት መሠረት ቤተ ክርስቲያን ናት። የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በአንድነት ለማስተማር ወደ ድኅነት መንገድ ለመምራት በምታደርገው ጥረት ውስጥ የመጀመሪያው ችግር ግልጥ ሆኖ የሚታየው ሕዝቦች በተለያየ አቅጣጫ ቆመው ስላሉ አንድ አድርጋ ማስተማርና ሥርዓቱን መፈጸም የማትችል መሆኑ በዚህ ወቅት ከባዱ ችግር እርሱ ነው። 

፪. የቤተ ክርስቲያን ክፍፍል፡- አሁን እየተስተዋለ ያለውን ነገር እንኳን ብናይ አንዳንድ ፖለቲካውንም ሆነ ይህን የምናነሣውን ነገር እንደ ልዩነት በመቁጠርና አጋጣሚውን እንደ መልካም እድል በመጠቀም ጦርነቱ እየተካሄደ ያለባቸው አካባቢዎች ላይ የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን መሰል ተቋም ለማቋቋም እየተሯሯጡ ያሉ ሰዎች አሉ። ይህ ከፍተኛ ችግር ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አሁን ጦርነቱ እየተካሄደበት ያለው አካባቢ የክርስትናውም ሆነ ከክርስትና በፊትም የብሉይ ኪዳን እምነት መሠረት የሆነችው አክሱም የምትገኝበት አካባቢ ነው። ጥንታውያኑ ቀደምት ቅዱሳት መካናት፣ ገዳማት የሚገኙትም በዚያው አካባቢ ነው። ከነዚያ አካባቢዎች ነው ብዙ ጊዜ ሥርዓት፣ ትውፊት፣ ታሪክ የሚመነጨው። ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን ይህንን እንዳጋጣሚ በሚቆጥሩ አካላት ስትከፋፈል መታየቱ በምእምናኑም በሊቃውንቱም ልቡና ውስጥ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ በጣም ከባድ ነው። 

፫. የሕዝቦች መከፋፈል፡- ቀጥሎ ደግሞ በጦርነቱ ማግስት እግዚአብሔር ፈቅዶና እግዚአብሔር ታድጐን በአጭሩ ከተቋጨ ይዘዋቸው የሚመጡ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ፡- ተቃርኖ ይፈጥራል፤ ሕዝብ ከሕዝብ ሊያቀያይም ይችላል። ምክንያቱም ነገሮችን ሰዎች ሁሉ በአንድ አቅጣጫ አይረዱምና። አሁንም እንደምናስተውለው ቤተ ክርስቲያኒቱን የአጥፊ ወገን አጋርና ተባባሪ አድርገው የሚመለከቱ አሉ። ያ ምን ድረስ ይቀጥላል እነዚያ ተንኮለኞችስ ሥራቸው ምንድነው? አካሄዳቸውስ በአሰቡት መልኩ ያስኬዳቸዋል ወይ የሚለውን አሁን ስለማናውቀው እንዲያው ብቻ እንደ ክፉ ጐን ቆጥረነው ልንሄድ እንችላለን። 

፬. የገዳማት መፍረስ፡- ገዳማት ሊፈርሱ ይችላሉ። የገዳማት መፍረስ በሁለት ወገን ሊከሠት ይችላል። የመጀመሪያው በቀጥታ ከአባቶች ሞትና እልቂት ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም ይችላል። ጦርነት ነውና ምን ድረስ ጥንቃቄ ታክሎበታል የሚለውን ማወቅ ስለማይቻል ማለት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በጦርነቱ ወቅት የሚቃጠሉና የሚወድሙበት ሁኔታ ሊከሠት ይችላል። ስለዚህ ገዳማቱ በቀጥታ በጦርነቱ ሲቃጠሉ የአገልጋዮችም ሕይወት በዚህ መልኩ ሲቀጠፍ ገዳማቱና አድባራቱ ሊፈርሱ ይችላሉ። 

፭. የምእመናንን ስደት፡-  አሁንም እንደምንሰማው ብዙ ምእመናን ወደ ባዕድ ሀገር እየተሰደዱ ነው። የምእመናን ስደት በሃይማኖትም በባህልም ወደማይመስሏቸው ሕዝቦች እየተሰደዱ ስለሆነ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸውን አሁን ላይ ቆመን አናውቀውም። ገና ወደፊት ታሪክና ውጤቱ የሚያመጣው የሚተነትነው ስለሆነ እንዲያው በቀላሉ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያመጣውን ችግር ማንሣት እንችላለን።  

ሐመር፡- ቤተ ተክርስቲያን መዋቅራዊ የሆነ ጭቆና ሲደርስባት እንደነበር ይታወቃል። ምን አልባት ከዚህ ጦርነት በኋላ የተሻለ ለውጥ ሊኖር ይችላል ብለን ማሰብ የሚያስችል ነገር ይኖር ይሆን?

መምህር ግርማ ባቱ፡- ሌላ ትርጉም እንዳይሰጠው ጉዳዩን በጥንቃቄ መመልከት ያስፈልጋል። ይህ ሆኖ ግን እንችላለን። ግልፁን ለመናገር አሁን የጦርነቱ ዋና ምክንያት የሆኑት ጥቂት ሰዎች (ቡድኖች) ላለፉት ፴-፵ ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቅ መከራ ሲደርስ የመከራው ምክንያቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እነርሱ ናቸው ብለን ማንሣት እንችላለን። በእነዚህ ቡድኖች ቤተ ክርስቲያን ጠላት ተደርጋ ተፈርጃለች። በግልፅ በየ አደባባዩ አንዳንዴ “እንዳታንሰራራ አድርገን መታናት ሲሉ” አንዳዴ ደግሞ “መጥፋት አለባት” ብለው ለወደፊቱ ሲተነብዩም ሲዝቱም የሰማንባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

ስለዚህ መጨረሻውን የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው። ግን እግዚአብሔር ፈቅዶ እነዚህ ቡድኖች ለሕግ ቀርበው ጉዳዩም በሕግ ተይዞ መገሮች በሰላም ተቋጩ ብለን ብናስብ ቤተ ክርስቲያን የምታገኘውም እፎይታ አለ። በሌላ መልኩም ደግሞ እነዚህ ሰዎች የሚናገሩት እውነት፣ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ እንዲያውም ለሀገር የሚበጅ መስሎት የሚከተለው ወገን ደግሞ አለ። ለዚህስ ምን ያህል ጉዳዩን አስተውሎ ለጥያቄዎቹ ሁሉ መልስ ሰጥቶ መስደድ ይቻላል? የሚለው አነጋገሪ ነገር ስለሆነ በጥልቀት መገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚያም ተጐጂዎች ናቸውና። ነገር ግን እነርሱም እውነታው ገብቷቸው ወንጀለኞችም ለፍትሕ ቀርበው ጉዳዩ በሰላም ቢጠናቀቅ ቤተ ክርስቲያን እፎይታ ታገኛለች። ላለፉት የሕይወት መጥፋቶች፣ የካህናቱ ሞት እልቂት የአብያተ ክርስቲያናቱ መፍረስ መቃጠል ወዘተ እነዚህ ሁሉ ማን አመጣቸው ቢባል አሁን መረጃዎች ግልፅ እያደረጓቸው ነው።

እነዚህን ካነሣን ዘንድ እነዚህን ችግሮች የሚያመጡ አካላት በሕግ ጥላ ሥር ሆኑ ማለት ቤተ ክርስቲያን እፎይታ ታገኛለች። ግን በአንድ አቅጣጫ እንዳናየው በየክልሉ የእነርሱን ሥራ የሚያስፈጽሙ ቅጥረኞች አሉ። ጉዳዩ ሰፊ በመሆኑና ዘላቂ ሥራ ከመጠየቁ አንጻር በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዳንመለከተው እንጂ ለጊዜው መጠነኛ እፎይታ ታገኛለች። ግን አሁንም እንዲሠመርበት የምፈልገው ጉዳይ ምን አልባት ዋናው ሰንኮፉ ከተነቀለ ሌሎቹ ግብር አበሮቹም አብረው ይጠፋሉ የሚለውን መውሰድ ይቻል ይሆናል እንጂ ሥራው ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ ነው ። 

ሐመር፡- ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ነገር ሲከሠት ሊኖራት የሚችለው ሚና በዘመናት ሲቃኝ ምን ይመስል እንደነበር ቢገልጹልን? 

መምህር ግርማ ባቱ፡- ቀደም ሲል በመጠኑ ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ ጎልቶ የተስተዋለው ሚናዋ አስታራቂነት ነው። አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በቀጥታ ለማገናኘት የቤተ ክርስቲያን ሚና አስታራቂነት፣ መካሪነት፣ መላሽነት ነው። አሁን በወቅታዊ ሁኔታ እንኳ በተቻለ መጠን ቤተ ክርስቲያን ያደረገቻቸው ጥረቶች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። በሚጠቀሰው አካባቢ  ማለትም ጦርነቱ ባለበት አካባቢ ሁሉ ምንም እንኳን ባይሳካላቸውም አባቶች ሄደዋል። በሁለቱም ወገን ሰዎችን ለመምከር ለመመለስም ጥረዋል። በታሪክ ውስጥ በተወሰነ አጋጣሚ ብናነሣውም ቀደም ሲል ያነሣኋቸው አጋጣሚዎችም አሉ። 

ቀደም ሲል በነበረው በአክሱማውያን ዘመናትም በነገሥታትና በመሳፍንት በመኳንንቱ መካከል በሚፈጠረው ግጭት በአመፀውና በሸፈተው ሁሉ መሀል እየገቡ እልቂት እንዳይፈጠር ሲያደርጉ ኑረዋል። ከዚህ  በተጨማሪም ነው የዛጉዌና የሰሎሞን ሥርወ መንግሥትና የአፄ ዮሐንስንና የአፄ ምኒልክን ግጭት እንደማሳያ አድርገን የጠቀስነው። ከዚያም ወደዚህ የቀረቡትን ሁሉ ማንሣት ይቻላል። እንዲሁ በአጭሩ ለማንሣት ቤተ ክርስቲያን የአስታራቂነትና አንድ የማድረግ ሚና አላት። እንኳን እንደዚህ ችግሩ በግልጽ  እየታየና ሀገራዊ ቀውሶችን እያስከተለ ይቅርና ችግር ከመፈጠሩ በፊትም ቢሆን ምንም እንኳን “መስማትስንስ ትሰማላችሁ ነገር ግን አታስተውሉም” ተብሎ እንደተነገረው ሰምቶ የሚያስተውል ትውልድ ቢጠፋም ሰላም የቤተ ክርስቲያን ታላቁ ጉዳይዋ ነው። አዘውትራ የምትሰብከው ዕለት ዕለት የምታስቀምጠው መሠረቷም ነው። ሁለቱ አካላት ማለትም መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ቤተ ክርስቲያንን  ቢሰሙ ሀገራችን ለዚህ ችግር ባልተደረገች ነበር። 

እንዲያው ነገሩን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰው ልጅ ማንነት የምታስተምረው ትምህርት በራሱ በቂ ነው። መከባበርን፣ መተሳሰብን፣ በፍቅር መኖርንና መረዳዳትን ሰው ከሰው ያለውን ግንኙነት ይቅርና ከሥነ ምኅዳር፣ ከእንስሳት፣ ከአራዊት ወዘተ. ሁሉ ጋር ተስማምቶ መኖር እንደሚገባ የምታውጀው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የተሠወረ አይደለም። ሚናዋን በዚህ መልኩ መቃኘት እንችላለን። 

ሐመር፡-  በቅርብ ቀን የሃይማኖት አባቶች በአካልም ተገኝተው ለማስማማት ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል። ግን ብዙም ለውጥ አልመጣምና ተሰሚነታቸውን ያጡበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? 

መምህር ግርማ ባቱ፡- ይህ በጣም መሠረታዊ የሆነው ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ለምን አልሰሙም? ሲባል ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ይመለከቷታል? እንዴትስ ይረዷታል? ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚሉት ነገርስ ምንድን ነው? የሚለው መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው። ቀደም ሲልም መግለጽ እንደሞከርኩት እነዚህ ሰዎች አሁን እንዲህ ተካሮ ወደ ጦርነት ከመገባቱ በፊት ቤተ ክርስቲያን መጥፋት አለባት ብለው በግልጽ አነጋገር ፈርጀው አስቀምጠዋል። እስከመጨረሻው ድረስ መጥፋት አለባት ባይ ናቸው። መጥፋት አለበት  ከሚሉትና እንደ ጠላት ከሚታይ ወገን የሰላምን ጥሪ ሊቀበሉ አይችሉም። በዋናነት ቤተ ክርስቲያንም ሆነች የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነትን ያጡት ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ መልሱ እነዚህ አካላት አስቀድመው በጠላትነት ተፈርጀዋልና ተሰሚነትን ሊያገኙ አይችሉም የሚለው ነው።

ቤተ ክርስቲያን ደግሞ  እውነታውን ስለምታውቅ ምንም ጠላት ቢያደርጓትም ሁል ጊዜም ሰላምን ትሰብካለች። ስለሰላም ጥሪ ማድረግ ደግሞ ካህናት  ምእመናን ብለን መለያየቱ ይቅርና ለሁሉም የሚጠበቅበት ተግባር ነው። ምክንያቱም በአጠቃላይ ለሰው ልጅ አሁን ያለውን  ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲመለከት ይህን አስከፊ ድርጊት ማውገዙ ተገቢ ነው። የመከላከያ ሠራዊት እየተባለ አሁን በሰፊው የሚነገረው ሀገር የሚጠብቅ ሕዝብን የሚታደግ ሠራዊት እርሱም ይቅርና ሰው በሰውነቱ እንዲህ ባለ ጭካኔ ሲገደል ቤተ ክርስቲያን ማውገዙ ትክልል ነው። ይህን ግን እነዚያ ወገኖች በምን አዩት ከተባለ አሁንም ከአንድ ወገን ወግኖ ለመቆም ነው። ይህ ከምን ጋር የተያያዘ ነው ስንል መጀመሪያ ከያዙት አቋም ጋር ቤተ ክርስቲያንን በምን አሰቧት በምን አዩአት ስንል በግልጽ የተናገሩት ካላይ ደጋግመን እንደ ተናገርነው መጥፋት አለባት የሚለውን አቋም ስለያዙ አሁንም ቢሆን የሰላም ጥሪዋን አይቀበሉም። 

ሐመር፡-  በአሁኑ ሰዓት ይህን ጦርነት ከማረጋጋት አንጻር ቤተ ክርስቲያን ሊኖራት የሚችለው ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?

መምህር ግርማ ባቱ፡- አሁንም የቤተ ክርስቲያን ሚናዋ አገልግሎቷ የታወቀ ስለሆነ ይህ ሆነ ተብሎ ጥረት አይቋረጥም። በችግር፣ በመከራ፣ በእሳት ውስጥም ቢሆን ጥረቱን መቀጠል አለባት። ቀደም ሲል አንድ አቅጣጫ ለመጠቆም ሞክረናል። እርሱም እነዚህ ወገኖች እግዚአብሔር ፈቅዶ ለሕግ ለፍትሕ ይቀርቡ ይሆናል። ግን መስሎት የሚከተል ደግሞ ስፍር ቁጥር የሌለው ብዙ ሕዝብ አለ። ይህንን ሕዝብ ማዳንም አሁንም የቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ሚናዋ ነው። ቤተ ክርስቲያንን በዚህ በጠቆረ ፊት እና በተለየ ገጽታ መሳሉ እንዳለ ሁኖ ለራሳቸውም ሕይወት ለቀጣይም የሕይወት ዘመናቸው የሚበጀውን ነገር ለማወቅ የቤተ ክርስቲያን ሚና አሁንም ጠንከር ብሎ መቀጠል አለበት። 

ገፍቶ ማስተማር፣ እውነታውን ማሳወቅ፣ ይህ አገልግሎት መንግሥቱን ለመውረስና ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመቀዳጀት ወይም ለሥጋዊ ድኅነት ብቻም ሳይሆን በታሪክም ሊወጡት የሚገባ፣ ይልቁንም  እንደ ኢትዮጵያዊ አብሮ የመኖር ድርሻቸውንም ከማሳወቅ አንጻር ሥራው ጠንከር ብሎ መቀጠል አለበት እላለሁ። እንዲያውም ከቀደመው በተሻለ መልኩ መሠራት አለበት። ሕዝብ ከሕዝብ መታረቅ አለበት። የተለያዩ ወገኖች በፓርቲ ደረጃ የሚጠቀሱም በተለያየ መደብም ይጠሩ እንደ ሀገር ለመቀጠል የቤተ ክርስቲያን ሚና አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው እኔ የማስበው። 

ሐመር፡-  በግለ ሰብ ደረጃስ ምን ቢደረግ ብለው ይጠቁማሉ? ለምሳሌ ሰባክያነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ወዘተ.?

መምህር ግርማ ባቱ፡- መጀመሪያ መደረግ በሚገባው ጥንቃቄ ላይ የተወሰነ አስተያየት ሰጥቶ ማለፍ ጥሩ ነው። ጥንቃቄው ማለት ሰዎች ልብ ማለትም ያለባቸው ነገር ስለ አንድ ጉዳይ  መናገርና  ማራገብ መቻል ብቻውን በቂ አይደለም። መቼና የት የሚለውንም ማየት በጣም ወሳኝ ነው። ቤንዚን ይዞ ወደ እሳት መቅረብ አደጋው ከባድ ነው። ይህ እሳት የሆነ ዘመን ነው። በዚህ ወቅት ላይ የሚባለውንና የማይባለውን መለየት ትልቅ ዋጋ አለው ብዬ አስባለሁ። እኔ በዚህ ወቅት ላይ የብሔር ጉዳዮችን ማራገብ ልዩነቶችን ማቀጣጠል ምን ይፈይዳል? ብለን ብንጠይቅ ከፋይዳው ይልቅ ጉዳቱ ይከብዳል። 

መቼም ቢሆን ልዩነት ጥሩ ባይሆንም ከምንጊዜውም በላይ በዚህ ሰዓት የምንለያይበት ጊዜ አይደለም። ማተኮርና ጠንክረን መሥራት ያለብን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ማስቀጠል የሚቻልበት ሐሳብ ላይ ነው። ይህን ደግሞ ማድረግ እንዲችሉ ሕዝቦቿን በአንድነት አስተባብሮና አስተሳስሮ የቀደመውን ጉልበት መመልስ የሚችሉበትን ሐሳብና አቅም ማስጨበጥ ያስፈልጋል። እንደ ሰባክያን እንደዘማርያን እንደ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያዊነት በቡድን ወይም በግለሰብ መናገር የምችለው ከመቼውም በላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ነው። ምክንያቱም ጦርነቱና ጦርነቱን በተመለከተ የሚነገሩ ሐሳቦች ለትርጕም የተጋለጡ ናቸው። ሰዎች በተለያየ ሐረግ ሲገልጹ መታዘብ እንችላለን። በየማኅበራዊ ሚዲያው፣ የተለያዩ ጉዳዮች ይንጸባረቃሉ። 

ሁሉም በየብሔሩ የሚያደርገውን እንቅስቃሴና ልዩነትን የሚያሰፋውን ጉዳይ መናገርን ትቶ እንደ ሀገር በተለይ ደግሞ እንደ ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ ያልሆነው ጉዳይ ወደ ውስጣችን ሲገባ ይስተዋላል። በዚህ ሰዓት አጠንክረን መሥራት ያለብን ክርስቲያናዊ ማንነታችን በተለይም በምሥጢራት የተፈጸመውን ኅብረት በምሥጢራት ያደግንበትን እውነታ አስመልክቶ መሆን አለበት። እንደ ሰው ማሰብ ያለብንን ነገር ማጠንከር እንጂ ሌሎች ነገሮችን ማራገብ ወቅቱ ይፈቅድልናል ብዬ አላስብም። ሁሉም ወደዚህ መለስ ብሎ አንድነት ላይ ቢሠራ ሁሉም የቤተ ክርስቲያንን ዓላማ ቢያስፈጽም፣ ከግል ጉዳዮች ይልቅ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ቢኖሩን እንኳ ወደዳር ብናቆያቸው አስፈላጊ ነው እላለሁ። አሁን ወቅታዊ ያልሆኑ ጉዳዮችም አብረው መጥተው የአገልጋዮች ፈተና በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲሆኑ ይስተዋላልና ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል እላለሁ።         

ሐመር፡-  ሰዎች በብሔራቸው እየተገፉ ከመሆናቸው የተነሣ አጠቃላይ መንፈሱ ሕዝብን ከሕዝብ የሚነጥል እየሆነ ነውና ቤተ ክርስቲያን ከዚህ አንጻር ምን ማድረግ አለባት ብለው ያምናሉ?

መምህር ግርማ ባቱ፡- አሁን ብዙ ወገኖች እየሰጡት ካለው አስተያየት እንነሣ። ቀደም ሲል እንዳልነው ዋናው የችግሩ ምንጭ ከደረቀ ርዝራዡ ይከስማል  ወይም ደግሞ ይደርቃል የሚሉ አስተያየቶች  በዚህ ሰሞን ተደጋግመው ሲነገሩ ይሰማሉ። ግን በሀገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ስናየው ችግሩ ከዚያ በላይ በጣም የሰፋ ይመስላል። ምክንያቱም ክፋቱን ከዋናው ምንጭ የወረሱት ሰዎች ሥራዬ ብለው የያዙትም ይመስላል። አሁን በተለይ ይህ የተጠቀሰው ችግር ማለትም ሰዎቹ በማንነታቸው ሲሳደዱ፣ ሲገደሉ በአጠቃላይ በርካታ ግፎችና በደሎች ሲደርስባቸው እንዲያው እነዚህ ሰዎች እኛ አይደለንም ቢሉ እንኳን በፍርድ በሕግ ጥላ ሥር ውለው ችግሩ ይከስም ይሆናል ወይም ይደርቅ ይሆናል ብለን ስናስብ  የሚያጠራጥሩ ነገሮች አሉ።

ምክንያቱም  ወራሾቹ ከአውራሾቹ በላይ  ይዘው ለመቀጠል ያሰቡ ጠንክረው እየሠሩ ያሉም ይመስላል። ለዚህ ነው ቀደም ሲል የቤተ ክርስቲያን ሥራ ወይም ሚናዋ ምንድን ነው የሚለው ላይ ከጦርነቱ ማግስት እግዚአብሔር ፈቅዶ ጉዳዩ ሲያበቃ ከዚያ ማግስት ያሉ ሥራዎች ይህን በማመላከት ጠንከር ያሉ ሥራዎች መሠራት አለባቸው ያልኩት። ምክንያቱም ችግሩ በጣም ሰፍቷል፤ ተዛምቷል፤ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ የሚታይ ችግር ሁኗል። ስለዚህ በየክልሎቹ፣ ፍተሻ እንዲደረግ፣ ምን ያህል መሪዎች ማለትም ዋና ዋና የክልል ባለሥልጣናት፣ የየወረዳና የየአካባቢው ባለሥልጣናት እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው መዋቅር መፈተሽ እንዳለበት የሚያመለክቱና የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው። ስለዚህ ሰፋ ያሉ ችግሮች አሉ። 

ስለዚህ ምንድን ነው መደረግ ያለበት? ቀጣዩ ሥራስ ምንድን ነው? ሲባል እውነት ለመናገር ለመንግሥት ባለሥልጣናትና ለፖለቲካ መሪዎች ብቻ እንዳንተው በውስጣችን ያለውንም መዘንጋት የለብንም። እንዲያውም ለእነርሱ ዕድሉን የሰጣቸውና ብርታት የሆናቸው በውስጣችን ያለው ችግርም ይመስለኛል። በእያንዳንዳችን ውስጥ የሠረጸውንና እየገፋ ያለውን ችግር እንደምንም በመፍታት አንድ ሆነን ቀሪውን ለሌሎች ማሳሰብ የሚኖርብን ይመስለኛል። እኛ ላይ ያለውን ችግር ከፈታን በኋላ ሌሎችን ደግሞ እስከ መንግሥት ድረስ በመድረስ ወርዶ ማነጋገር የመንግሥትንም አቋም መረዳትና እስከ ታች ድረስ የሚወርድ ሥራ መሥራት፤ ለተለየ ወገንና አካል መተውን ችላ ብሎ ቤተ ክርስቲያን ራሷ በኮሚቴም ይሁን ወይም ራሱን የቻለ አካል ተዋቅሮ ጉዳዩ ላይ ክትትል የሚደረግበትና ለቤተ ክርስቲያንም ይሁን ለሀገር የሚጠቅም ሥራ መሠራት አለበት ብየ አስባለሁ።

ሐመር፡- በመጨረሻም እንዲያው ቀረ የሚሉትና ማስተላለፍ አለብኝ የሚሉት ሐሳብ ካለ ቢገልጹልን

መምህር ግርማ ባቱ፡- ከጉዳዩ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር ብዙ የምንታቀብባቸው ነገሮች አሉ እንጂ ብዙ የሚባሉ ጉዳዮችማ ነበሩ። የምንታቀብበት ምክንያትም የምንናገረው ሁሉ ለተለየ ትርጉም የመጋለጥ ዕድሉ የሰፋ ስለሆነ ነው። ይህንኑ ወደሌላ ወስደውና በሌላ መንገድ ቀይረው ለብዙ ዓላማ ሊያውሉት ስለሚችሉ በሚል ከብዙ ነገሮች እንድንታቀብ አድርጎናል እንጂ ከዚህም በላይ ብዙ የሚያስብሉ ነገሮች ነበሩ። በዋናነት ከተነሡት ጠያቄዎች አንጻር ግን የቀረ ያለ አይመስለኝም።

ሐመር፡- መምህር ላነሣናቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ስለሰጡን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን። እግዚአብሔር ያክብርልን።

መምህር ግርማ ባቱ፡- አሜን እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ እግዚአብሔር ሁላችንንም  ከዚህ መከራ ይጠብቀን።  

Read 908 times