Saturday, 02 January 2021 00:00

አባ ተክለ አልፋ

Written by  በክፍለ ማርያም

Overview

መግቢያ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል” (መዝ.፻፲፩፥፮) በማለት እንደተናገረው በሃይማኖት ጸንተው በምግባር በትሩፋት ተጸምደው በተሰጣቸው ውስን የዚህ ዓለም ዕድሜ እግዚአብሔርን ያገለገሉ ቅዱሳን ሁሉ መታሰቢያቸው ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል። በዚህ ዓለም የነበረ የተጋድሎ ቆይታቸው የተወሰነ ቢሆንም የተጋድሎ ዋጋቸው ግን ጊዜ የማይሽረው ዘለዓለማዊ ነው። በዚህ ወር የእናስተዋውቃችሁ ዓምዳችን በ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን በድንቅ ተጋድሏቸው እግዚአብሔርን ካስደሰቱትና ዘለዓለማዊ መታሰቢያ ከታደላቸው ቅዱሳን አንዱን አባ ተክለ አልፋን አቅርበናል። ልደት አባ ተክለ አልፋ ከአባታቸው ከአሮንና ከእናታቸው ከኦርኒ በዕለተ ሐሙስ ጥር ፳፩ በ፲፭፻፫ ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ደብረ ኤልያስ ወረዳ ጎፍጭማ ከምትባል ቦታ ተወለዱ። አባታቸው ከሸዋ ምድር ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ጎጃም የደብረ ኤልያስ አካባቢ ሰው ናቸው። አባታቸው በንጉሥ ይስሐቅ ዘመን ከሸዋ ተሰደው ደብረ ኤልያስ  ጎፍጭማ ከምትባል ቦታ ከወሰን አምባ ምድር ደረሱ፤ በውስጧም ተቀመጡ። በእግዚአብሔር ፈቃድ በንጹሕና በከበረ ጋብቻ አንድ ሁነው ወንድና ሴት ልጆችንም ወለዱ። አባ ተክለ አልፋ ከመወለዳቸው በፊት እናታቸው ኦርኒ ራእይ አይተው “ፀሐይ ስትወጣ በሆዴም እንደ መብረቅ ሲያበራ አየሁ” ብለው ለባለቤታቸው ነገሯቸው። ባዩትም ራእይ እየተደነቁ ሳለ ዕለተ ሐሙስ ጥር ፳፩  በ፲፭፻፫ ዓ.ም በእመቤታችን በዓለ ዕረፍት ተወለዱ።  የስማቸው ትርጓሜ  ተክለ አልፋ ማለት የአልፋ ተክል ማለት ነው። አልፋ ማለት ስመ አምላክ ሲሆን ተክለ አልፋ ማለትም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ተክል፣ የጽድቅ ፍሬን የሚያፈራ እንጨት፣ ከኃጢአት ሐሩር መጠለያ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም ወዘተ ማለት ነው። የትምህርት ሕይወት አባ ተክለ አልፋ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወላጆቻቸው በአካባቢያቸው ለሚገኙ መምህር ሰጧቸው። በአካባቢ ከሚገኙ መማህራንና ከሌሎችም መምህራን ዘንድ እየተዘዋወሩ የብሉያትና የሐዲሳትን ትርጓሜ ተምረዋል። ወደ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደመጡ በወቅቱ የገዳሙ አበ ምኔት ከነበሩት ከአባ ማቴዎስ ሥርዓተ ገዳምን ተምረዋል።  የምናኔ ሕይወት ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወላጆቻቸው  ሊያጋቧቸው አስበው ሚስት እንዳጩላቸው በሰሙ ጊዜ ከዚህ ዓለም ሙሽርነት ይልቅ ሰማያዊ ሙሽርነትን በመምረጥ እግዚአብሔርን የሕይወትን መንገድ ምራኝ በማለት ጸለዩ። ሰርጉ ሦስት ቀን ሲቀረውም መልአከ ገጻቸው (ጠባቂ መልአካቸው) እየመራ ወደ ዲማ ገዳም አደረሻቸው። ከተወለዱበት ቦታ ወደ ዲማ ገዳም ሲሄዱ መንገድ ላይ መሸባቸውና የሰንበት ከምትባል ቦታ አደሩ። ዕለቱ ዐርብ ነበርና በሰንበት መንገድ አልሄድም ብለው ከዚያው ቦታ ሰነበቱ። በዚህ ጊዜ ለጸሎት ሲቆሙ ዐሥሩ ጣቶቻቸው  ሲያበሩ ለካባቢው ምእመናን ይታዩ ነበር። በዚህም የአካባቢው ምእመናን እግዚአብሔርን አመስግነዋል። የቦታው ስያሜም የሰንበት የተባለው በዚህ ምክንያት እንደሆነ ከቀድሞ አባቶች የተገኘው ትውፊት ያስረዳል። ወደ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደመጡም በወቅቱ የገዳሙ አበ ምኔት ከነበሩት ከአባ ማቴዎስ ሥርዓተ ገዳምን ከተማሩ በኋላ አባ ማቴዎስ የአባ ተክለ አልፋን መንፈሳዊ ጽናት አይተው አመነኰሷቸው። በመቀጠልም በአባ ተክለ አልፋ ተጋድሎና ደግነት ስለተደሰቱ የገዳሙ አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው። በዚህ ጊዜ የገዳሙ አበምኔት የሚሆን ሰው ከግሸና ተክለ ሃይማኖት ይመጣ ስለነበር እንደ አዲስ ሥርዐት ተቆጥሮ በግሸና መነኰሳትና በዲማ መነኰሳት መካከል ጠብና ክርክር ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሡ ልብነ ድንግልና ሹማምንቱ በእርሱ ላይ ያደረውን ጸጋ እግዚአብሔር አይተው ለዲማ መነኰሳት ፈርደውላቸው የአባ ተክለ አልፋን ሹመት አጽድቀውላቸዋል።  ይህ ግሸና የሚባለው ቦታ የዲማን ገዳም የመሠረቱት አቡነ ተከሥተ ብርሃ ወደ ዲማ ከመምጣታቸው በፊት ለተወሰነ ጊዜ ቆይተውበት ስለነበርና እርሳቸው ከዚህ ቦታ ስለመጡ እንደ አንድ ይቆጠራልና እስከ አቡነ  ማቴዎስ ድረስ የገዳሙ አበምኔት የሚመጣው ከዚህ ቦታ ነበር። ከአቡነ ማቴዎስ በኋላ ግን ማለትም ከአቡነ ተክለ አልፋ ጀምሮ ከዚሁ ከዲማ የሚሾም ሆኗል። የጠቡና የክርክሩ መነሻም ይህው ነበር።  ጻድቁ አባት አባ ተክለ አልፋ ግን ለተመረጡለት ሹመት ፈቃደኛ አልነበሩም። በንጉሡም ፊት አይሆንም ለማለት ሞክረው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ኃላፊነት በጸጋ እንዲቀበሉና ገዳሙን በቅንነት እንዲያገለግሉ፣ የሹመቱንም ወንበር ትተው ከገዳሙ እንዳይወጡ አባ ማርቆስ የተባሉ ጳጳስ አወገዟቸው፤ የጳጳሱንም ቃል ይሽሩ ዘንድ አልቻሉምና በእሽታ ተቀበሉት። ጻድቁ አባ ተክለ አልፋ ምስማር ያለው ጫማ በመጫማት ከእግራቸው ደምና ዕዥ ይወርድ ነበር። በዚያ ደምና ዕዥም በሽተኞች ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር። በሚሄዱበት መንገድም ደምና ዕዥ ከእግራቸው ይፈስ ስለነበር ሕፃኑም አዋቂውም አባ ተክለ አልፋ ዛሬ በዚህ በኩል አልፏል ይላቸው ነበር።  ዕለተ ሞታቸው እንደተቃረበ ተረድተው ከገዳሙ በስተደቡብ በኩል ባለውና ሱባኤ ይይዙበት በነበረው ዋሻ ጸሎት ማድረግ ጀመሩ።  በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ አበ ምኔት ሁነው ለ፵፭ ዓመታት ያህል ገዳሙን በሥርዓትና በሕግ ካገለገሉ በኋላ በ፸፭ ዓመታቸው ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ታኅሣሥ ፰ ቀን ሐሙስ ማታ ለዐርብ አጥቢያ ከምሽቱ ፫ ሰዓት አርፈዋል። በዚህ ጊዜ መላ ዘመናቸውን ይዘዋት ትኖር የነበረች መቋሚያቸው ወደ መነኰሳቱ መጥታ አባታችን አርፈዋልና ቅበሯቸው ብላ በሰው አንደበት ተናግራለች። እስከ አሁንም ድረስ በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትገኛለች ሕሙማንም ይፈወሱባታል። ለገዳሙ የሠሩት ሥርዐት ከአቡነ ተከሥተ ብርሃን እስከ አቡነ ተክለ አልፋ ድረስ መነኰሳቱ በአንድ ቤት በአንድ ቅጽር ይሰበሰቡ፣ በአንድ በርም ይገቡ ይወጡ ነበር፤ እንደየማዕረጋቸውም መጀመሪያ አስኬማና ቆብ የተቀበሉት፣ ከዚህ በኋላ ደግሞ ባለ ቀሚስና ባለ ቅስና በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ ሰዴቃ ይበሉ ይጠጡ ነበር። በእንደዚህ ያለ ሥርዐት እያሉ ግራኝ ኢትዮጵያን ወረራት፤ ቤተ ክርስቲያንም ተዘጋች። አባታችን አቡነ ተክለ አልፋም የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ይዘው ወደ በጌ ምድር ተሰደዱ። ጥቂት መነኰሳትም አብረው ተሰደዱ። የቀሩት መነኰሳትም በዋሻ ውስጥ ገብተው መኖር ጀመሩ። ከዐሥራ አምስት ዓመት በኋላ ግራኝ ሲሞት ሞት ስደት ፀጥ አለ። ያን ጊዜም አባታችን አቡነ ተክለ አልፋ ከተሰደዱበት ተመለሱ፡ መነኰሳቱም ከተበተኑበት ተሰበሰቡ። ከዚህ በኋላ መነኰሳቱ ስደት አማቶናልና በአንድ ቤት ተሰብሰቡ አይበሉን፤ መቅኑናችንንም በየቤታችን እንብላ ብለው አባ ተክለ አልፋን ለመኗቸው። አባ ተክለ አልፋም የመነኰሳቱን ልመና ተቀብለው በተለያየ ቤት እንዲኖሩ መቅኑናቸውም በየቤታቸው እንዲሰጣቸው ፈቀዱላቸው። እነርሱም እየተከፋፈሉ በየግላቸው መውሰድና መብላት ያን ጊዜ ጀመሩ።  ቃል ኪዳን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለታት አንድ ቀን ተገልጾ በዚህ ዓለም እንዳከበርከኝ እኔም በወዲያኛው ዓለም አከብርሃለሁ። ስለ ስሜም እንደደከምክ የምሕረት ቃል ኪዳን እሰጥሃለሁ በመንግሥተ ሰማያትም ዋጋህ እጽፍ ድርብ ይሆንልሃል። ስምህን የጠራውን በጸሎትህ የታመነውን መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። በተለየ ሁኔታ ለአባ ተክለ አልፋ የተሰጧቸው በርከት ያሉ ቃል ኪዳኖች አሉ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡- ፩. በአንድ ወቅት ረኀብ ሆኖ አንዲት ድሀ ለተከታታይ ስድስት ቀናት እየመጣች ለመነቻቸውና ስድስቱንም ቀናት የእርሳቸውን የዕለት ምግብ ሰጧት። በሰባተኛውም ቀን እንደ ለመደችው መጥታ ቆመች። በዚህ ጊዜ ረኀብ ቢሰማቸውም “ተርቤ አላበላችሁኝምና” (ማቴ.፳፭፥፵፪) የሚለው የወንጌል ቃል ሊፈርስብኝ አይደለም እንዴ በማለት ሰጧት። ከዚህ በኋላ ጠይቋቸው የማያውቅ ባለጸጋ ምግባቸውን ይዞላቸው መጥቷል። ጌታም ተገልጦ ከእንግዲህ ወዲህ በዘመንህ ረኀብ አላመጠብህም ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ፪. በገዳሙ ክልል ጅብና እባብ ሰውንም ሆነ እንስሳ እንዳይተናኮል ስለገዘቱት በእነዚህ አውሬዎች ምእመናን ፍራቻ የለባቸውም። ዛሬም እንስሳቱ ሌሊት በሜዳው ሲያድሩ ምንም ሳይነካቸው ያድራሉ። እባቡም ከመታየት በዘለል ምንም ሰው አይናከስም። ፫.ሚያዝያ ፳፫ ቀን የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ሲከበር ታቦቱ ከዋሻው ወጥቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን እስከሚገባበት ጊዜ ድረስ በሚያርፍበትና በሚነሣበት ጊዜ ሁሉ ከፊት ለፊት የሚሄድ ጥቅል አውሎ ነፋስ አለ። ከዚህም በተጨማሪ ከሚያዝያ ፩ በዓሉ እስከሚከበርበት ሚያዝያ ፳፫ ድረስ በስድስት በስድስት ሰዓት በጉልላቱ ገብቶ ቤተ መቅደስ ቆይቶ ተመልሶ የሚወጣበት ምልክት አለ። ይህም ቦታውን በረድኤት አልለየውም ብሎ ለጻድቁ የገባላቸው ቃል ኪዳን ምልክት ሁኖ ይኖራል። ፬.ሀገሪቱ (ዲማ) እንደመቃብሬ እንደኢየሩሳሌም ትሆንልሃለች የሚል ቃል ኪዳንም ገብቶላቸዋል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ቃል ኪዳኖች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጻድቁ ከገባላቸው ጥቂቶች ናቸው።  በአጠቃላይ ጻድቁ አቡነ ተክለ አልፋ በሃይማኖት ጸንተው በምግባር በትሩፋት ተጸምደው በሕይወት ዘመናቸው እግዚአብሔርን አስደስተው ጽኑዕ የሆነ ቃል ኪዳን ከእግዚአብሔር ተቀብለው ታኅሣሥ ፰ ዐርፈዋል። ዛሬም ተጋድሏቸውን በፈጸሙበትና እግዚአብሔርን ባገለገሉበት ቦታ በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታኅሣሥ ፰ ዓመታዊ በዓላቸው፣ በየወሩም ማለትም ወር በገባ በ፰ ደግሞ ወርኃዊ መታሰቢያቸው ይከበራል። ከጻድቁ በረከት ያድለን አሜን።  (ምንጭ ገድለ ተክለ አልፋና በገዳሙ የተዘጋጀ የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ገዳም አጭር ታሪክ የሚዘክር መጽሔት)
Read 1447 times