Friday, 04 September 2020 00:00

 “የተደራጀ አክራሪ ኃይል ቤተክርስቲያንን እያጠቃት እንደሆነ በተደጋጋሚ ለመንግሥት አሳውቀናል”

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

ክፍል አንድ    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እና ምዕመናን ላይ እየደረሰ  ያለው ግድያ እና ጥፋት እየተበራከተ መጥቶአል። በዚህ ዓመት ብቻ እንኳ በሻሸመኔ፣ በባሌ ፣ በአርሲ በጅማ እና  በሀረር እንዲሁም በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች  በተደራጁ ፅንፈኛ ኃይሎች ቤተክርስቲያን ላይ  የደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም ፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣  የቤተ ክርስቲያኒቷ ተከታይ ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ታርደዋል ፣ እጅና እግራቸው እየተቆረጠ በክርስቲያን ወግ የቀብር ስርዓት እንኳ ሳያገኙ በየሜዳው እና በየጫካው ተጥለዋል። ከዚህ አሰቃቂ እልቂት የተረፉት ከተወለዱበት ፣ ከኖሩበት እና  ሀብት ንብረት ካፈሩበት ቀዬ ተፈናቅለው በየአብያተ ክርስቲያናቱ ተጠልለው ይገኛሉ። በአንድ ወቅት ራሳቸውን እና ብዙዎችን የሚረዱ ሰዎች ተረጂ  እጃቸውን ለሌሎች የሚዘረጉ የምዕመናን እጆች ከሌሎች  ምጽዋትን ለመቀበል ተገደዋል።  ሰኔ 2012 ዓም. በአርቲስ ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ ከተፈፀመው ግድያ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ውስጥ በተነሳው አመፅ የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ ናቸው። የአርቲስቱን ሞት ሽፋን በማድረግ በተጠና እና በተደራጀ መልኩ ፅንፈኛ የሆኑ አክራሪ ሙስሊሞች ያደረሱትን እና እያደረሱ ያሉትን እጅግ ዘግናኝ ውድመት አስመልክቶ  በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ መረጃ እንዲሰጡን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት ሰብሳቢ እና የኮቪድ-19 ተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይል ፀሐፊ ከሆኑት ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ ጋር እንደሚከተለው ቆይታ አድርገናል። ስምዐ ጽድቅ፡- የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ሞት ሽፋን በማድረግ በተለያዩ የኦሮሚያና በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች በምእመናንና በንብረታቸው ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ደርሷል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

 

ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ፡- አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በድንገት ሕይወቱ ማለፉን የሰማነው ጥዋት ላይ  ሊነጋ ሲል ነው።በጊዜው  በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዞኖች የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ቤተክርስቲያንን እና ራሳቸውንን እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላልፈን ነበር ፡፡ እንደሚታወቀው በጥቅምት ወር ላይ አቶ ጁሀር መሀመድ ተከብቤአለሁ በሚል  በፌስ ቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ  በዚሁ መረጃ መነሻነት  በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ በርካታ ምእመናን በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ንብረታቸው ወድሞአል እንዲሁም ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል። አሁንም  ተመሳሳይ የሕይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ሊከሠት ይችላል በሚል ስጋት  አርቲስቱ መሞቱን ከሰማንበት ሰዓት ጀምሮ ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች ለሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች መረጃ ስናስተላልፍ ቆይተናል፡፡ ነገር ግን  የፈራነው ደርሶ በርካታ ንጹሐን ምእመናን በጭካኔ ተሠውተዋል፤ ለበርካታ ዓመታት ያፈሩት ሀብትና ንብረትም ወድሞ በህይወት የተረፉት ባዷቸውን ቀርተዋል፡፡ 

ይኽችን ቤተ ክርስቲያን በተቃራኒ የቆሙ ኃይሎች ሁሉ እንደጠላት ነው የሚመለከቷት። አሁን የአርቲስቱን ሞት ሽፋን በማድረግ በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ለየት የሚያደርገው አርቲስቱ የቤተ ክርቲያኒቱ ልጅ፣ ባለቤቱን ጨምሮ እህቶቹ  የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ መሆናቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ልጅ ላይ ጥቃቱ መፈጸሙ እንዲሁም በኦርቶዶክስ ምዕመናን ላይ የደረሰው የነፍስ ማጥፋት እና የንብረታቸው መውደም ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ወቅት የገጠማትን ሁለት ጉዳት ማየት ይቻላል፡፡፡ 

በምእመናንና በንብረታቸው ላይ ጥቃት የፈጸመው ጽንፈኛ አክራሪ ኃይል የአርቲስት ሀጫሉ ሁዴሳ መሞት አሳዝኖት ሐዘኑን ለመግለጥ የወጣ ሳይሆን ከኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የፀዳች ኦሮሚያን ለመመሥረት እያደርገ ያለውን ትግል እውን ለማድርግ የፈጸመውን የወንጀል ድርጊት የሚያመላክት ነው፡፡ በአርቲስቱ ግድያ ሽፋን ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን እያደኑ የመግደል የረጅም ጊዜ እቅድ እንደሆነም አመላካች ነው፡፡  ጥቃቱ እጅግ በረቀቀና በተደራጀ ሁኔታ መፈጸሙን የሚያመለክተው አርቲስቱ ገና መገደሉ ይፋ ሳይሆን ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ምእመናንና ንብረቶቻቸውን ማጥቃት መጀመሩና ድርጊቱን በበላይነት የሚመራው ኃይል እንዳለ የሚያመለክት መሆኑ ነው፡፡ ይኽ ከወራት በፊት ተሰልቶና ታቅዶ የተቀመጠ ጥቃት መሆኑንም ለማወቅ ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ 

ተደጋጋሚ የቤተክርስቲያንን ጥቃቶች ባየንና በሰማን ቁጥር ጥናት አጥንተን የተደራጀ ቡድን ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን እያጠቃ እንደሆነ ለመንግሥት ስናሳውቅ ቆይተናል፡፡ መንግሥት ግን በየወቅቱ ይሰጠን የነበረው መልስ  ”ቤተክርስቲያንን እያጠቃት ያለው የተደራጀ ኃይል አይደለም፤ ጥቃቱ ድንገታዊ ነው‘ የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን የአርቲስቱን ድንገተኛ ሞት ሽፋን ተደርጎ የተፈጸመው ጥቃት የተደራጀ አክራሪ ጽንፈኛ ኃይል ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን ያጠቃበት ሁኔታ ቀደም ሲል ስናነሣው ለነበረው ሥጋት ማረጋገጫ ነው፡፡  በዚህም የተደራጀው አክራሪ ጽንፈኛ ኃይል  የጥቃቱ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል  ከብዙ ውዝግብ በኋላ በቅርቡ ከመንግሥት ጋር መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ፡- ይኽን በተደጋጋሚ በሀገራችን በተለይም በኦሮሚያ ክልል በጽንፈኛው አክራሪ ቡድን  በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት ለማስቆምም ሆነ ዘላቂ የምእመናንና የቤተ ክርስቲያንን ህልውና  እና መብት ለማስከበር ቤተ ክርስቲያንም ሆነች በስሟ የተቋቋሙት ማኅበራት እየሠሩ አይደለም የሚል ሀሳብ በምእመናን ይነሣልና በዚህ ላይ የእርስዎ ሀሳብ ምንድን ነው?

ቀሲስ ሙሉቀን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ቤተክርስቲያንንና ምእመናንን አክራሪ እስላም እያጠቃቸው እንደሆነ ከመንግሥት አካላት ጋር መተማመን አልቻልንም ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም የመንግሥት አካላት ጉዳዩን በሚገባ ተረድተውታል፡፡ ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በተደራጀና ተቋማዊ መልክ ባለው ኃይል እየተጠቁ እንደሆነ በተደጋጋሚ ለመንግሥት እናመለክት ነበር፡፡ የመንግሥት ምላሽ ግን ”ቤተ ክርስቲያን ላይ  እየደረሰ ያለው ጥቃት ድንገት እንጂ በተደራጀ ኃይል አይደለም‘ የሚል ነበር፡፡ በእኛ በኩል ግን የተደራጀ ኃይል እያጠቃት መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች ነበሩን፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን የሚጠቁት አብዛኛውን ጊዜ ሕዝበ ሙስሊሙ በሚበዛባቸው የኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ነው፡፡ ሌላው ማርጋገጫ ደግሞ በቅርቡ ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ሽፋን ተደርጎ እስልምና በሚበዛባቸው አንዳንድ የኦሮሚያ  አካባቢዎች በምእመናንና በንብረታቸው ላይ የተፈጸመው አሳዛኝ ጥቃት ነው፡፡ ጥቃቱ በአመዛኙ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው በባሌ፣ በአርሲ፣ በጅማ፣ በሐረርጌና በከሚሴ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው ጥቃቱ እየተፈፀመ ያለው በአክራሪ ሙስሊም መሆኑን ነው፡፡ በተደጋጋሚ እየታየ እንዳለው እስላማዊው አክራሪ ቡድን ለመግደልና ንብረትን ለማውደም ብሔር አይመርጥም  ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሆኖ መገኘት ብቻ በቂ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ በኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በርካታ የሸዋ ኦሮሞዎች ኦርቶዶክስ ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ በአሠቃቂ ሁኔታ ተገለዋል፤ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፏል እንዲሁም ተቃጥሏል፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ የሌላ ብሔረሰብ አባላት የሆኑ ሙስሊሞች ሕይወታቸውም ሆነ ንብረታቸው ጉዳት ሳይደርስበት ሌሎች ብሔረሰቦች በአንጻሩ ኦርቶዶክስ በመሆናቸው ብቻ በአክራሪ ሙስሊሞች አሠቃቂ ግፍ ሲፈጸምባቸው ይስተዋላል፡፡ 

እየተፈጸሙ ያሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለማስቆምም ሆነ ዘላቂ የቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር ለማስጠበቅ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች በስሟ የተቋቋሙት ማኅበራት ሥራ እየሠሩ አይደለም ብሎ ማሰብ ከባድ ቢሆንም ነገር ግን የተሻለ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች በስሟ የተቋቋሙ በርካታ ማኅበራት ከወቅቱ አንፃር እንዲሠሩ የሚጠበቁባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ሊሠሩም ይገባቸዋል፡፡ እንደሚታወቀው የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች የሀገር አንድነት የማያሳስባቸው፣ ለሰው ሕይወት ዋጋ የማይሰጡ በመሆናቸው የሰውን ሕይወት በከንቱ ከመንጠቃቸው ባለፈ ኦርቶዶክሳውያን ለአርባና ሃምሳ ዓመታት ያፈሯቸውን ሀብትና ንብረት ጭምር በአንድ ጀንበር ማውደማቸው የሃይማኖት፣ የሞራል እንዲሁም የመንግሥት ሕግ የማይገዛቸው አካላት መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ  ከእስላማዊ  አክራሪ ኃይል አስተሳሰብ በተቃራኒው የቆሙ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ምእመናን ለሀገር አንድነት የሚያስቡ፣ ለሰው ሕይወት ዋጋ የሚሰጡ፣ በሃይማኖት፣ በሞራል እንዲሁም በመንግሥት ሕግ የሚገዙ ናቸው፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን ሀገርን ከጠላት ጠብቃ አንድነትንም አስጠብቃ የኖረች በመሆኗ ብቻ ከእስላማዊ አክራሪ ኃይል በሚያደርስባት ትንኮሳ ተሳቃ ከያዘችው ሀገራዊ ዓላማ ፈቀቅ ማለትን አትፈቅድም፤ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር አንድነትና ለሃይማኖት እኩልነት ዋጋ ባትስጥ ኖሮ እስላማዊውን አክራሪ ኃይል እንደአመጣጡ መመለሱ በጣም ቀላል ይሆን ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሰው ሞት አይደለም የእንስሳ ሞትም የሚያስጨንቃትና ዕፀዋትን ሳይቀር ተንከባክባ የማሳደግ የዘመናት ልምድ ያላት በመሆኗ የሞራል ልዕልናው ከወረደ ኃይል ጋር እንካ ስላንትያ መባባሉ ያላትንና የነበራትን ክብር ማውረድ ይሆናል፡፡ ወጣቶቻችንና ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ሥነ ምግባር ያደጉ በመሆናቸው በሌሎች እምነቶች ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት ፈጽመው አያውቁም፡፡ በመሆኑም በዚህ ሰዓት በአጥቂና በተጠቂ መካከል ያለው ፍልስፍናና ርዕዮተ ዓለም የተለያዩ ናቸው፡፡ የእስላማዊውን አክራሪ ቡድን ፍልስፍና እንከተል ቢባል ሀገራችን አንድነቷ የተናጋና እንደአንዳንድ የዓረቡ ዓለም ሀገራት የፈረሰች ትሆናለች፡፡ 

አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በድንገት የሞተው አዲስ አበባ ከተማ ሆኖ ሳለ ኦርቶዶክሳውያን ሲገደሉና ንብረታቸው ሲወድም የነበረው ግን ሐረርጌ፣ ባሌ፣ አርሲ እና ጅማ ነው፡፡ የሀጫሉ በድንገት መገደልና ክርስቲያኖችን በጭካኔ መግደልም ሆነ ንብረታቸውን ማውደም ምን አገናኘው? ድርጊቱ አንድ የሚነግረን ነገር እንዳለ እንረዳለን፡፡ እስላማዊ አክራሪ ኃይል ‹‹የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል›› የሚለውን አባባል በመጠቀም ለዓመታት የወጠነውን ጥቃት ለመፈጸም የአርቲስቱን ሞት ተጠቅሞበታል፡፡ ከዚህ ነውረኛ ድርጊት በኋላ ከኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የፀዳች ኦሮሚያን የመመሥረት ዓላማን እውን ለማድረግ አልሟል፡፡ ይህ ይሳካለት ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ግን ጊዜ የሚፈታው ይሆናል፡፡

በአክራሪ እስላማዊ ቡድን  እየተፈጸመ ያለውን መቋጫ ያጣ ጭፍጨፋ ለመከላከል እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብን ማወቁ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ምእመናን በእስላማዊው አክራሪ ቡድን ላይ የኃይል ርምጃ  እንዲወስዱ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ሀገር እንደሀገር የመቀጠሏ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ እርግጥ ነው ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ቆሞ በእስላማዊ አክራሪ ቡድን ሰይፍ መገደል እንደሌለበት እናምናለን፡፡ 

ይቆየን

Read 617 times