Monday, 21 September 2020 00:00

በግብፅ ክርስቲያኖችን ከአሸባሪዎች ጥቃት ለመከላከል ያለመ ምክክር ተደረገ 

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የአርመንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዞሃረብ ማናፃከናያን በግብፅ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ከኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታኦድሮስ ዳግማዊ ጋር ክርስቲያኖችን ከአሸባሪዎች ጥቃት ለመከላከል ያለመ ምክክር ማድረጋቸውን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነብቧል፡፡  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በመከሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የአረመንያና የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የረጅም ጊዜ የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጠው  ይህንን ግንኙነታቸውን ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና ቅዱስ ፓትርያርኩ በበርካታ ርእሰ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ያስነበበው የኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘገባ በዋናነትም አናሳ ቁጥር ባላቸው ክርስቲያኖች ደኅንነት ዙሪያና በሃይማኖቶች መካከል ሊኖር ስለሚገባው መቻቻልና አብሮነት መሆኑን አመልክቷል፡፡ አሸባሪዎች በክርስቲያኖችና በሃይማኖታዊ ቅርሶቻቸው የሚያደረሱትን ጥቃት የመከላከል ሥራ ስለሚሠራበት ሁኔታም መምከራቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡  አርመንያ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች ከጥቃት ለመከላከል የተለያዩ ዓለም አቀፍ የግጭት መፍቻ ስልቶችን በመጠቀም የሃይማኖት ልዩነትን የማቻቻልና ሰላምን የማረጋጋት ሥራ እየሰራች መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በውይይቱ አንስተዋል፡፡  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታኦድሮስ ሁለተኛ በበኩላቸው ሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ዘላቂ የሆነ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡      
Read 605 times