Wednesday, 30 September 2020 00:00

የዝዋይ ገዳም በጎርፍ አደጋ ጉዳት ደረሰበት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምና መንፈሳዊ ኮሌጅ ሰሞኑን በተከሠተ የጎርፍ አደጋ ጉዳት እንደደረሰበት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አስታወቁ፡፡  የዝዋይ ሀይቅ ከልክ በላይ በመሙላቱ ምክንያት በገዳሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ብፁዕነታቸው አስታውቀው በገዳሙ እርሻ ላይ፣ በከብቶች ማደሪያ እንዲሁም በአብነት ተማሪዎች መኖሪያ ቤቶችና መማሪያ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡  የገዳሙ ግቢ ሙሉ በሙሉ በውኃ በመሸፈኑ በገዳሙ በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ከመማሪያ ክፍላቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው መሄድ እንዳልቻሉ ብፁዕነታቸው ገልጠዋል፡፡ በገዳሙ ግቢ ውስጥ በሰፊው የተኛውን ውኃ ለመቀነስ የአምስት የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ድጋፍ ከግለሰቦች በመገኘቱ ውኃውን የመምጠጥ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ያስረዱት ብፁዕነታቸው እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ ባለመሆኑ መንግሥትም ሆነ ምእመናን አስፈላጊውን ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  በማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማዕከልና ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለገዳሙ ጊዜያዊ ድጋፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ የጎርፍ አደጋ በገዳሙ ላይ ከደረሰ በኋላ የተቋቋመው ኮሚቴ ከሁለት መቶ ሽህ ብር በላይ ሰብስቦ ለገዳሙ ገቢ ማድረጉን  የገለጹት ደግሞ የማዕከል ጸሓፊ የሆኑት አቶ ዳኛቸው ዘለቀ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በገዳሙና በአንዳንድ በጎ አድራጊ ግለሰቦች ትብብር በውኃ የተሸፈነው የተወሰነው የገዳሙ ክፍል ጠጠር እየተደፋበት እንደሆነም አቶ ዳኛቸው አክለው ተናግረዋል፡፡    አቶ ዳኛቸው አያይዘውም ‘’በማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማዕከል ሙያና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ለገዳሙ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ መደረጉን ተከትሎ ባለሙያዎቹ በአካባቢው ተገኝተው በገዳሙ ላይ የደረሰውን ጉዳት ከተለመለከቱ በኃላ ዘላቂ የልማት ሥራ ለመሥራት አቅደዋል›› ብለዋል፡፡   
Read 322 times