Friday, 11 December 2020 00:00

“ከትናንቱ በመማር ዛሬ ላይ ጠንክረን ልንሠራ ይገባል” - መልአከ ገነት ቀሲስ መልአኩ ደሳለኝ  (የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ) ክፍል ሁለት

Written by  እህተ ሚካኤል

Overview

የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል ባለፈው እትማችን ላይ ማቅረባችን ይታወሳል።  በዚህ እትማችን ደግሞ ክፍል ሁለትን ይዘንላችሁ ቀርበናል፤  ትከታተሉ ዘንድ ግብዣችን ነው።  የተወደደዳችሁ አንባብያን በመጀመሪያው ክፍል ‹‹ቀሲስ መልአኩ›› ተብሎ የተጻፈው የእንግዳችን ስም ‹‹ቀሲስ ንጋቱ›› መሆኑን እየገለጽን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።  ስምዐ ጽድቅ፦ ሞተ የተባለው እና የተመዘገበው የጥቃቱ ሰለባ የሆነ ሰው ነው? መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ፦ አዎን ለምሳሌ አለማያ ላይ አንዲት እናት ሙተዋል።  ቤተ ሰቦቻቸውም ጭንቅላታቸውን ተፈነካክተው እጃቸው ሁሉ ተሰባብሯል።  እናትየው ባልቴት ናቸው፤ በጣም ተደብድበው ስለነበር ሆስፒታል ሲደርሱ ሞቱ።  እንግዲህ በእርሳቸው ስም ፴ ሺህ ብር ቡክ ተከፍቶአል፤ ቡኩ በልጃቸው ወይም በቤተሰቡ ስም መሆን ነበረበት፤ የእርሳቸው ካሳ ለልጆች መሰጠት ነበረበት።  ያው እንደሚታወቀው በሞተ ሰው ስም ሲደረግ ደግሞ ውርስ እና ተያያዥ ነገሮች ሲባሉ ብዙ ጊዜ ይፈጃል።  በእርግጥ ይህ ስለተስተካከለ ችግር የለውም። 

 

ስምዐ ጽድቅ፦ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን እጣ ፈንታ እንዴት ይገልጹታል?

መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ፦ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ መገመት ይቻላል።  በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመባት ላለው ጥቃት የመንግሥትም እጅ አለበት ነው የምንለው።  እንዲህ ለማለት ያስደፈረን ነገሩን ፊት ለፊት ስላየን እና ስለተረዳን ነው።  ለምሳሌ ጥምቀት በምናከብርበት ጊዜ በታቦታቱ፣ በካህናቱ ላይ ሳይቀር አስለቃሽ ጪስ ይለቀቅ የነበረ።  በዓሉን በሥርዓት 

የሚያከብረው አካል ላይ ነው ወይስ ነውጥ እየፈጠረ ያለው አካል ነው በአስለቃሽ ጪስ መባረር የነበረበት፤ ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ነበር።  ከትናንቱ ተምረን ዛሬ ላይ ጠንክረን ካልሠራን ነገ የባሰ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም።  

ለምሳሌ ዛሬ ዛሬ በመንግሥት በኩል በተለይ በኦሮሚያ ክልል እኛ ባለንበት በምሥራቁ ከፍተኛ ተጽዕኖ ነው ያለው።  የቤተ ክርስቲያኒቷ ንብረት በሌላ አካባቢ ጠቅላላ ሲመለስ በምሥራቅ ሐረርጌ ግን አልተመለሱላትም ንብረቶቹ የቤተ ክርቲያኒቱ ለመሆናቸው መረጃ ስላለው ነው የምናገረው።  ለቤተ ክርስቲኒቱ የነገ መልካም እጣ ፈንታ ዛሬ ትልቅ ሥራ ከቅዱስ ሲኖዶስ ይጠበቃል እላለሁ።   

የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ጠንክሮ የቤተ ክርስቲያንን፣ የምእመናንዋን መብት ማስከበር ይጠበቅበታል።  ይህ ነገር ካልተደረገ፤ ለቤተ ክርስቲያን እና ለመእመናኗ ጥበቃና ከለላ ካልተደረገ ወደፊት አአስቸጋሪ ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለሁ።    

ስምዐ ጽድቅ፦ የቤተ ክርስቲያን ንብረቶች የተወሰዱባት ከዚሁ ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ ነው?

መመልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ፦ አይደለም የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወድቆ ሀገሪቱን የደርግ መንግሥት ሲረከብ በአዋጁ መሠረት ተብሎ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ብዛት ያላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች ተወስደውባታል፤ ከዚያ ውስጥ አንዱ በሀረር ከተማ የሚገኙት ንብረቶቿ ናቸው።  ለምሳሌ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ያሠሩት በሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና ሥር ያለ እና  የተማሪዎች  አዳሪ ቤት እንዲሁም መማሪያ የነበረ ዘመናዊ ሕንፃ አንዱ ነው።  ይህ ሕንፃ እነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ እነ ቅዱስ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ እነ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የመሳሰሉ ታላላቅ አባቶች የተማሩበት ትምህርት ቤት ነው የተወረሰው።  አሁንም አልተመለሰም የግብርና ጽ/ቤት አድርገው እየሠሩበት ነው።  

ሌላ ትምህርት ቤትም ነበረ ትምህርት ቤቶች የሕዝብ መገልገያ ናቸው ስለተባለ ትምህርት ቤቶቹን አልጠየቅንም የቤተ ክርስቲያን ማስረጃ ያላቸውን የተለያዩ ሕንፃዎችን ግን ጠይቀን እስካሁን አልተመለሰልንም።  በካቢኔ ተወስኖ መልስ ይሰጥበታል ስለተባለ በተስፋ እየተጠባበቅን ነው።  

ስምዐ ጽድቅ፦  በቦታው ላይ ያሉ ክርስቲያኖችን የማጽናቱ እና የማበረታታቱ ነገር በሀገረ ስብከቱ ደረጃ እንዴት እየተካሄደ ነው? ወጥ በሆነ ደረጃ እየተሠራ ነው ለማለት ይቻላል?

መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ፦ እንግዲህ ወጥ የሆነ ሳይሆን ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ቅዳሜ እና እሑድ እየጠበቅን መምህራንን ሰባክያነ ወንጌልን ከከተማውም ከሀገረ ስብከቱም እያቀናጀን እንዲማሩ፣ እንዲጽናኑ እያደረግን ነው።  ሀገረ ስብከቱ ሙሉ አበል የትራንስፖርት እና ልዩ ልዩ ወጪዎችን እየሸፈነ እያገዘ ነው።  ጥቃት የደረሰባቸው ቦታዎች ላይ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ በአካል በመገኘት አበረታትተናል።  ሀገረ ስብከቱ በትምህርተ ወንጌሉም በማጽናናቱም እየሠራ ነው።  

ከዚህ በፊት ራስህን ጠብቅ፣ አንተ ተጠንቀቅ እየተባባልን ነበር የምንኖረው።  በተለይ የሃይማኖት አባቶችን የበላይ ጠባቂዎችን  ይገድላሉ፣ ይመታሉ የሚባል መረጃ ስላለ እና ስለሚወራ ራሳችንን አቀርቅረን፣ዘ ግተን ነበር ያለነው፤ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች አሉ።  አሁን  ባለው እንቅስቃሴ የሕግ የበላይነት ይከበር በሚለው ሂደት ትንሽ ፋታ እያገኘን ነው ያለነው።  በአንፃራዊነት ትንሽ ሻል ያለ ሰላም አለ ብዬ አምናለሁ።  በተረፈ  እግዚአብሔር እርሱ በቸርነቱ ሰላሙን ያምጣ መጨረሻውን ያሳምርልን እላለሁ።   

ስምዐ ጽድቅ፦  በቀጣይስ ምን ለመሥራት ታስቦአል?

መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ፦ በቀጣይ በሀገረ ስብከቱ ደረጃ የተወሰነ ነገር አድርጎ  ቤት ለመሥራት ቆርቆሮ፣ ሚስማር እና የመሳሰሉትን ለመግዛት እያስተባበርን ነው።  አንዳንድ በጎ አድራጊዎች ሲመጡም የሚያሥፈልገንን እየነገርን ቃል እያስገባን ነው።  በዚህ አጋጣሚ ማኅበረ ቅዱሳንን ላመሰግን እወዳለሁ፤ ከፍተኛውን ጥረት እያደረጒ ነው፤ ዳታውንም በመሰብሰብ ብዙ ረድተውናል። ለተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት የቀዳሳያንን አልባሳት ልከዋል።  እንዲሁም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የገንዘብ እርዳታ አድርገዋል።  የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ ለመሥራት ዲዛይን አውጥተው ፕላኑን ሠርተው የላኩልን እነርሱ ናቸው።  በገንዘብ ሲገመት ከ፫፻፶ ሺህ ብር በላይ ያወጣል፤ እንግዲህ ይኽን ነው ማኅበሩ የሸፈነው።  ወደፊት ደግሞ የበለጠ ከኛ ጎን እየሆኑ እንዲሠሩ እንፈልጋለን።  አሁንም በእኛ ሥር ሆነው እየሠሩ ነው፤ ቢሮም የሰጠናቸው እኛ ነን፤ በብፁዕነታቸው በአቡነ መቃርዮስ መልካም ፈቃድ  አሁንም አስፋፍተው እንዲሠሩ ቦታ ሰጥተናቸዋል።  እንግዲህ እጅ ለእጅ ተያይዘን የበለጠ ብዙ ሥራ እንሠራለን ብዬ አምናለሁ። 

ስምዐ ጽድቅ፦ ፴፱ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለመካፈል ነው ሀገረ ስብከትዎን ወክለው የመጡት ከጉባኤው ምን አገኙ?

መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ፦ ፴፱ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ከአምናው ትንሽ ለየት የሚለው ሪፖርቶች በየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች ይነበቡ ነበር።  ዘንድሮ ግን ያ ቀርቶ ስለ ወቅታዊው የቤተ ክርስቲያኒቷ ሁኔታ ላይ ውይይት እንደምናደርግ ተነግሮን ነበር።  እኛም ውይይት እናደርጋለን፣ ሓሳብ እንለዋወጣለን ብለን አስበን ነበር ነገር ግን ውይይቱ አልቀረበም። በኋላም በኮቪድ ምክንያት ስብሰባውም አጠረ ስለዚህ ምንም የተወያየነውም ነገር የለም።  በነበረው ጊዜ የዋና ሥራ አስኪያጁን ሪፖርት፣ የአህጉረ ስብከቱን ሪፖርት ደግሞ በሰበካ ጉባኤው መምሪያ ሓላፊ ነው የቀረበው፤  መሰላቸትም ነበረ።  ከዚያም በተጨማሪ ሪፖርቶቹ ተቀንጭበው ስለሚወጡ ሁሉም የራሱ ቅሬታ ውስጥ ነበር።  ዋና ዋና መነገር የነበረባቸው ነገሮች አልተነገሩም የሚል ቅሬታዎች ካንዳንድ የጉባኤው አባላት ይነሡ ነበር። 

በጉባኤው ላይ ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያወራነውም ሆነ የተወያየነው ነገር የለም።  ቅዱስነታቸውም ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬአቸውን ሰጥተው ራሳችንን እንድንጠብቅ እንድንደራጅ የሚል መመሪያ ነው ያስተላለፉት።  ከላይ ካነሣሁት ውጪ ፴፱ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሰላምና በጥሩ ሁኔታ ተጠናቋል ማለት ይቻላል።  

ስምዐ ጽድቅ፦ የቅዱስ ፓትርያርኩ መሪ ቃል ራስን ለመከላከል መደራጀት የሚል ነበር መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ ይሆናል ብለው ያስባሉ?

መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ፦ መግለጫው ከወጣ በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚኖረው ምልዐተ ጉባኤ ላይ ተወያይቶ በሚያወርደው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።  ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቆት በየሀገረ ስብከቱ መመሪያ ሲተላለፍ በዚያ መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የቻለውን ሁሉ ይሠራል።  

ስምዐ ጽድቅ፦ እንደ አጠቃላይ ቀረ የሚሉት እና የሚጨምሩት ነገር ካለ?

መልአከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ፦ ቀረ ሳይሆን ትኩረት እንዲሰጠው የምፈልገው ከላይ ያነሳሁት በሀገረ ስብከታችን ለጥቃት የተጋለጡትና እርዳታው ሳይደርሳቸው የቀሩት ምእመናን በሙሉ ተካተው እርዳታውን የሚያገኙበት መንገድ ቢፋጠን እላለሁ።  

ሌላው በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ላይ ስለተካሄደው ሽልማት ማንሳት ፈልጋለሁ።  በሽልማቱ ዙሪያ ተጨባጭነት ያለው ሥራ ቢሠራ ጥሩ ነው እላለሁ።  አንድ አህጉረ ስብከት ከመሰሉ አህጉረ ስብከት ጋር ነው መወዳደር ያለበት ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት  ያሉት አብያተ ክርስቲያኛት ፶፫ ወረዳዎቹም አምስት ናቸው በጣም አናሳ አብያተ ክርስቲያናት ያሉት የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ከሀዋሳ እና ከድሬ ዳዋ ሀገረ ስብከት ጋር ውድድር ውስጥ መግባት የለበትም።  ከሚመሳሰለው ጋር ነው መወዳደር የነበረበት እላለሁ።  አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል መከራና ፍዳ የደረሰባቸው ብዙ ነገር ተጋፍጠው በእሳት ውስጥ ያለፉ ሀገረ ስብከቶች ባላቸው አቅም ሠርተው ሪፖርት ማቅረባቸው በመሸለም ሞራል ሊሰጣቸው ይገባ ነበር።  ይኽ ቅሬታን ያመጣል፤ እገሌ እገሌ ከማለት ይልቅ ለሁሉም የተሳትፎ የምሥክር ወረቀት ሰጥቶ መሸኘት ይሻል ነበር። 

የመጨረሻው ቤተ ክርስቲያን አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ችላ መባል የለበትም። ካለፈው በመማር ራስን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው እላለሁ።  እኔ ስለፖለቲካ ብዙ አላውቅም ።  የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ባለው የመንግሥት የሥልጣን እርከን ላይ ብዙም አይታዩም ጭራሽ የሉም ማለት ይቻላል።  ይኽ ይመስለኛል በተወሰነ መልኩ ቢሆን ሃይ ባይ በሌለበት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለጥቃት ያጋለጣት እና ያስጠቃት።  ቢያንስ አንድ ሁለት ሰው ቢኖር መከላከል አልፎም አስቀድሞ መረጃ ማግኘት እና ራስን መጠበቅ ይቻል ነበር ብዬ አስባለሁ።  

የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ከፊታችን የሚመጣውን ሀገራዊ ምርጫ በቸልታ ሊያልፉት አይገባም።  አጋጣሚውን እንደ በጎ እድል በመውሰድ በምርጫው ላይ የቤተ ክርስቲያንቱን ልጆች በመምረጥም ሆነ በመመረጥ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል።  በየትኛውም ጉዳይ ላይ ቸል ልንል አይገባም፤ ቸልተኝነት ዋጋ እንዳስከፈለን አይተናልና።  ጠንክረን ሁላችንም በያለንበት ለምርጫው ትኩረት ሰጥተን ብንሠራበት ጥሩ ነው የሚል ግንዛቤ አለኝ።  እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

 

Read 533 times