Friday, 11 December 2020 00:00

ያልተቆጠረው ሀብት

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ

Overview

አንድ ምሽት በምሥራቅ የኦሮሚያ አካባቢ ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከቶች ስላሉ ክርስቲያኖች መከራና የስጋት ሕይወት እያሰብኩ ሳለ አንድ ሐሳብ መጣልኝ፤ በእነዚህ ሀገረ ስብከቶች ለአደጋ የተጋለጡ ስንት አብያተ ክርስቲያናት ይኖሩ ይሆን? ማን ማን ይባሉ ይሆን? ምን ያህልስ ምእመናንና ካህናት ይኖሩ ይሆን? አልኩ።   ወዲያውኑ ስልኬን ከፍቼ የኢንተርኔቱን የመረጃ መስጫ መረብ ተቀላቀልኩ።  በተለመደው መንገድ በጎግል ልፈልግ ብዬ የሀገረ ስብከት ስምና የቤተ ክርስቲያን ቃላት ዓይነት እያማረጥኩ አሰሳዬን ቀጠልኩ።  ነገር ግን አልፎ አልፎ መከራ ስለደረሰባቸው አንዳንድ አጥቢያዎች በግርድፉ ከሚጠቅሱ የዜና ዘገባዎች ውጪ መሠረታዊ መረጃ የያዘ ገጽ ድርም ሆነ የጥናት ጽሑፍ ማግኘት አልቻልኩም።  ሀገረ ስብከቶቹ ራሳቸውን የሚገልጹበት፣ አጥቢያዎች ስለአሉበት ሁኔታ የሚነግሩበት አንድም የማኅበራዊ ሚዲያ ሽፋን የለም።  ለምን? ከዚያ አልፌ በጠቅላይ ቤተ ክህንት ደረጃ እነዚህን መሠረታዊ መረጃዎች በቀላሉ ተደራሽ የሚያደርግ ገጸ ድር ወይም ጥናት ላገኝ አልቻልኩም።   ወዳጆቼ! የተቀነሰብንን፣ ያጣነውን፣ የተቸገርንበትን ነገር መጠኑን የምናውቀው የነበረንን በውል ስናውቅ ነው።  

 

ስንት አህጉረ ስብከቶች ነበሩን? አሁን ስንት አሉን? በእነርሱ ሥር ስንት ወረዳ ቤተ ክህነቶች አሉ? በእነርሱ ሥር ስንት አጥቢያዎች አሉ? ከእነርሱስ ስንት ገዳማት ስንት ደብሮች ስንት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አሉን? መቼ ተሠሩ? መቼ ታደሱ? በእነርሱስ ስር ምን ያህል ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ መርጌቶች …አሉ? እነርሱስ የሚያገለግሏቸው ምእመናን ቁጥር ስንት ነው? ስንቶቹስ ከአጥቢያቸው ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ያለንን ሀብት መጠን እንድናውቅ ይጠቅመናል፤ ይህ ግን በጥቂቱም ይሁን ተሟልቶ የተሠራው በየትኛው ሀገረ ስብከት ነው? ከተሠራውስ ምን ያህሉን ግልጽ አድርገናል? 

ይህ ከሌለን ዛሬ ወይም ነገ የሚጎድልብንን ማወቅ አንችልም።  ይህንን ማወቅ ብንችል ባለፉት ፴ ዓመታት እንኳን ከነበረን ምን ያህል እንዳጣን ለመተንተን ይመች ነበር።  ዛሬ መከራ እና ስጋት አለባቸው በምንላቸው አህጉረ ስብከቶች ካሉ አጥቢያዎች ምን ያህሉ ተቃጠሉ ተዘጉ ብለን በስም ጠቅሰን ለማዘን ለማሳሰብ ለመጸለይም ይበጀን ነበር።  ከእነዚህ ከተጎዱ አህጉረ ስብከት የተሰደዱ ካህናት እና ምእመናን ስንት ናቸው? ቤተክህነትን በመሰለ ተቋም ውስጥ ‹‹ቤት ይቁጠረው›› ብሎ ማለፍ ያሳፍራል።  እያንዳንዱ የእኛ ቤት ነውና ቤተ ክህነት እንደ አንድ ቤተሰብ ሊቆጥረው ሊያውቀው እና ሊያሳውቀው የሚገባ ነበር። 

ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትናንትም ስንታዘበው የነበረው ጉልህ እውነታ አለ።  የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች በአፅራረ ቤተ ክርስቲያንና በሌቦች ብዙ እንደተመዘበሩ ስንተርክ ነበር፤ አሁንም እንተርካለን።  ነገር ግን በእርግጠኝነት የተጎዳንበትን ልክ እናውቀው ይሆን? እንዴት አድርገን? ቀድመን በየአጥቢያዎቻችን ያሉ ቅርሶችን መዝግበን ቆጥርን ሰፍረን መቼ አወቅን! ያን ብናውቅ ስንቱ በቃጠሎ፣ ስንቱ በስርቆት፣ ስንቱ በአያያዝ እንደጠፋ አውቀን እናለቅስ ነበር።  ይህ ሁሉ ግን ባለመሆኑ ትዝብት ላይ ጥሎናል። 

ያለንን ቆጥረን ሰፍረን ማወቅ ያለብን ለማዘን ብቻ አይደለም፤ እግዚአብሔርንም ለማመስገን ነው።  የነበሩንን የምእመናን ቁጥር አውቀን ቢሆን ሰብከን ያመጣናቸውን፣ አስተምረን ያጠመቅናቸውን አዳዲስ አማንያን ቁጥር እየተናገርን እግዚአብሔርን እናመሰግን ነበር፤ እንደ ሐዋርያትም ‹‹ በጌታችንም የሚያምኑ ብዙዎች ይጨመሩ ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙዎች ነበሩ።(የሐዋ  ፭፥፲፬ )እያልን የመንፈስ ቅዱስን ሥራ እንመሰክር ነበር።  

ወደፊት አቅዶ ለመሥራትም ያለንን ማወቅ አስፈላጊ ነው።  በየጊዜው ቤተ ክህነት በሚያቀርበው ሪፖርት ለምሳሌ በዚህ ዓመት ጠቅላይ ቤተክህነት ብቻ ፫፻፶ ሚሊየን ብር ያህል ‹‹ፐርሰንት›› መሰብሰቡን የሰማነውን ያህል ከትናንት ዛሬ ስለተጨመሩልን ምእመናን፣ ስለተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር በየሀገረ ስብከቱ ለጥምቀት ስለተዘጋጁ ንኡሰ ክርስቲያን በየደረጃው ወጥቶ ዜና የሆነ ቁጥር አለን?! የለንም።  ለምን? ትዝብት ላይ የሚጥል ነው።  

ቤተ ክህነት ተከታዩን ምእመን ቁጥር በውል ያውቀዋል? ስንት ካህናት አሉን? ይህንን እንደተጠየቀ ‹‹ይህን ያህል ሺህ አካባቢ፣ ይህን ያህል ይገመታል፤  እጅግ ብዙ…›› ወዘተ እያሉ ከመናገር ተላቆ ወይም ሺህና መቶ እያሉ በድፍን ከመቁጠር ርቆ በትክክል ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር የሚችል ይኖር ይሆን? 

በዚህ ዓመትስ ስንት ካህናት ተሾሙ በየት ሀገረ ስብከት? እነማን ናቸው? ይህ ሁሉ መታወቅ ያለበት እውነት ነው።  ሕዝብ ካህኑን ሳያውቅ ካህን መስሎ በመጣው ሁሉ ግራ የሚጋበው እኮ በአደባባይ እያንዳንዱ አጥቢያ ወይም ወረዳ ቤተ ክህነት በሥሩ ያሉትን ካህናት ማንነት በፎቶግራፍ ጭምር አስደግፎ በአደባባይ ስለማይገልጽ ነው።  ምነው ይህንን እንኳን ከአኃት አብያተ ክርስቲያት ብንማር! እነርሱ የተሾመውን ብቻ ሳይሆን ያጯቸውን በአደባባይ ምስክርነት እንዲሰጥላቸው ያደርጉ የለምን? ነቀፋ ከተገኘበትስ ሳይሾም ያቆዩት የለም እንዴ!

ይህ ሁሉ ለትዝብት የሚዳርግ ሰንፍና ለምን ሆነብን ስንል ስላልሠራን ብቻ ሳይሆን የሠራነውን ወይም ያልሠራነውን ስለማንቆጥር፣ ቆጥረንም ቢሆን ይፋ ስለማናደርግ፣ አድርገንም ቢሆን ለውጦችን (update) ስለማናካትት ነው።  ለምን አንቆጥርም? ጥቅሙን ባለማወቅ? ጽድቅ ስለሆነ? በስንፍና? ይህን ራሳችንን መመርመር ይገባናል።  ይህንን ካላደረግን ሰዎችስ ስለእኛ እንዴት ይወቁ? ጋዜጠኞችስ ስለእኛ ደስታም ሆነ ሐዘን እንዴት ይዘግቡ? ተመራማሪዎች ስለእኛ እንዴት ያጥኑ ?….

የማንቆጥረው በአስተምህሮ ምክንያት ነው እንዳንል ‹‹ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ።›› (ዘኍ ፫፥፵፪) ብለን እናስተምራለን።  ኦሪት ዘኍልቍ የሚለው መጽሐፍም የቅዱሳት መጻሕፍት አንድ አካል ባልሆነ ነበር።  የእግዚአብሔር ወገን በሰላሙ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመከራው ጊዜ እንኳን የእርሱ የሆነውን ቆጥሮ ሰፍሮ ያውቃል።  ልጆቹንና ሀብቱን ሁሉ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በስምም ማወቅ አለበት! ‹‹የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን ከማረካቸው ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ወደ እየከተማቸው የተመለሱት የሀገር ልጆች እነዚህ ናቸው።›› (ዕዝራ  ፪፥፩) የተባለውን የምታነብ ቤተ ክርስቲያን ነችና።  ቤተ ክህነት ልጆቹን ስንትና እነማን እንደሆኑ ማወቅ፣ መግለጽ ይገባዋል ክርስቶሳዊ ነውና ‹‹ የእናንተስ የራስ ጠጕራችሁ ሁሉ የተቈጠረ ነው፤›› (ሉቃስ ፲፪፥፯) ያለውን ክርስቶስን መምሰል አለበት።  ‹‹ልጄ ጠፋ፣ የጠፋው ልጄ ተመለሰ›› ለማለትም የሚመቸው ልጆችን በውል ሲያውቅና ሲያሳውቅ ነው። 

ስለዚህ ዘርን ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ሀብት መቁጠር እንልመድ።  የምንቆጥረው ለመመካት አይደለም ለመጠበብ እንጂ።  ሰላሙን ይስጠን።

 

Read 525 times