Saturday, 26 December 2020 00:00

ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን እንጂ የማይገባትን አትጠይቅም

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ ታሪኳ ወስጥ ለሀገራችን ዘርፈ ብዙ የሥልጣኔ ታሪኮችን አስመዝግባለች፤ ምክንያቱም ኦቶዶክዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ናትና።  ቤተ ክርስቲያን ሀገርን ከነድንበሩ፣ነፃነትን ከነክብሩ አስረክባለች፤ብራና ዳምጣ፣ ብዕር ቀርፃና ቀለም በጥብጣም የማይምነትን ጥላ ገፋለች።  የአድባራትና የገዳማቷ ጥንታዊነትና የኪነ ሕንፃ ጥበቦቿ እንዲሁም በውስጣቸው ያሏት ዘመን ተሻጋሪ ጥንታዊ ቅርሶቿ ከሀገሬው አልፎ ለውጭ ዜጋም ቢሆን የዐይን ማረፊያ ሆነዋል።  በዚህም ሀገርን፣ ባህልንና ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ለዓለም ማስተዋወቅ ተችሏል።  ሀገራችን ኢትዮጵያ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የአብሮነት እንዲሁም የጠንካራ ዕሴት ባለቤት የመሆኗ ምሥጢር ቤተ ክርስቲያን ከሰው ሁሉ በሰላም ኑሩ፣ ጠላቶቻችሁን ውድዱ በሚሉና በመሳሰሉት አስተምህሮዎቿ ትወልድን በመልካም ሥነ ምግባር በማነጽ ተግባር ላይ ለዘመናት መስራቷና ሰውን ሁሉ የሚወድ መሪዎቹን የሚያከብር ለሕገ መንግሥታቸውም የሚገዛ ትውልድን ማፍራት ነው።  በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ሀገር ሆና ኖራለች።  የህንን ደግሞ መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ በዐደባባይ “ኦርቶዶክስ ሀገር ናት” በማለት መስክረውላታል።  ይሁን እንጅ ቤተ ክርስቲያን የሀገር ክብርና ርስት መሆኗ ቢታወቅም ከውጭና ከውስጥ የተፈጠሩ ጠላቶች በየጊዜው ቤተ ክርስቲያንን እየተነኮሱ መብቷን ሲጥሱ ክብሯን ሲጋፉ ቆይተዋል።  የእምነቱ ተከታይ ምእመናንን እንደ አውሬ እያደኑ ከመግደል ባሻገር የሀገር ርስት የሆነችው ይህች ቤተ ክርስቲያን መሥዋዕት ሆና በመሠረተቻት ሀገር ርስት አልባ የማድረግ  መከራው ከተጀመረ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠጥሯል።  ከዛሬ ሦስት ዓመት ጀምሮ በሀገሪቱ መጣ በተባለው ‹‹የፖለቲካ ለውጥ›› ሳቢያ አክራሪ ሃይማኖተኞችና የስሁት ትርክት አቀንቃኝ ፖለቲከኞች በጥምረት የሚመሯቸው መንጋዎች የቤተ ክርስቲያንን መብት ሲነጥቁና ርስቷንም እንደቅርጫ ሲከፋፈሉ እንደቆዩ ማሳያው ቤተ ክርስቲያን መብቷ እንዲከበር በተደጋገሚ ያወጣቻችው መግለጫዎች ናቸው።  ርስቷ የተወረረባት ባለርስቷ ቤተ ክርስቲያንም ለእግዚአብሔር ታሰማ ከነበረው አቤቱታ በተጨማሪ ለዓለማዊው መንግሥት ዘወትር ጥያቄዋን በሕጋዊ መንገድ ስታቀርብ ቆይታለች፤ ነገር ግን ከዚህ በፊት የተሻለ መፍትሔ አላገኘችም ነበር።  አልፎ አልፎም ቢሆን የላይኛው የመንግሥት አካል ቤተ ክርስቲያን የተነጠቀችውን ርስቶች እንዲመለሱላት ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም የታችኛው የመንግሥት አመራር ጫፍ በረገጠ የተሳሳተ አመለካከ ተሸፍኖ የበላዩን ትዕዛዝ ለመፈጸም ፍላጎት ሲያሳይ አልተስተዋለም ነበር።  እነዚህ የታችኛው የመንግሥት አመራሮች ሕጋዊ አሠራረን ተከትለው የቤተ ክርስቲያንን የርስት ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የተሳሳተ የትርክት መርዝ በመርጨት ‹‹ቤተ ክርስቲያን ወራሪ ናት›› የሚል ተቀጽላ ስያሜ መስጠት ጀመሩ።  ምንም እንኳን ቤተ ክርስቲያን በስሁት ትርክት አቀንቃኞችና በጽንፈኛ ፖለቲከኞች አማካይነት ባልዋለችበት ሊያውሏት ቢሞክሩም፤ ክብሯንና ጥቅሟን ለማስከበር በተቻለ አቅም ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።  በመዓልትና በሌሊት ለፈጣሪዋ ይግባኝ ብላለች፤ ምድራዊ ባለሥልጣናቱንም ተማጽናለች።  ተማጽኖዋን ከምንም ያልቆጠሩ በተሳሳተ ትርክት የሰከሩ ፖለቲከኞች ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ በበደል ላይ በደል ጨምረውባታል።  በተለይ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚካሄደው የርስት ነጠቃ በደሎች በደቡብ  እና በኦሮምያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዋናነት ተስተውለዋል።  በኦሮምያ ክልል በተለይ በአርሲ ነገሌ ከዚህ ቀደም የአካባቢው ምእመናን የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ያከብሩበት የነበውረን ቦታ ሕገ ወጥ የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣኖችና አክራሪ ሃይማኖተኞች መንጠቃቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።  በወቅቱ ምእመናን ርስታቸውን ለማስከበር ሲሉ ደምተዋል፣ ቈስለዋል እንዲሁም አንብተዋል።  የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን በወቅቱ ‹‹ሌላ ምትክ ቦታ እንሰጣለን›› በሚልና የእኔ የሚሉትን ሃይማኖት ለማስደስት የወሰዱት ርምጃ እንደሆነ ምእመናን በጊዜው ያሰሙት የነበረው አቤቱታ ምስክር ነው።  በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለይ በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ተመሣሣይ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ርስት ነጠቃ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።  በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በመሎ ኮዛ ወረዳ ቤተ ክህነት የለሃ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለኀምሳ ሦስት ዓመታት የመስቀልና የጥምቀት በዓላትን ያከብሩበት የነበረውን ቦታ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ለመንጠቅ ርምጃ በወሰዱበት ወቅት ርስታቸውን ለመከላከል ጥረት ያደረጉ ከ፳፪ በላይ ምእመናን ያለምንም ጥፋት ለእስራትና ለገንዘብ መቀጮ እንደተዳረጉና እስካሁን ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።   በሃድያ ዞን ሆሣዕና ከተማ የሚገኘውንና በተለምዶ ‹‹ጎፈር ሜዳ›› ተብሎ የሚጠራውን የቤተ ክርስቲያን ርስትም እንዲሁም የአካባቢው የመንግሥት አመራሮች ከነጠቁ በኋላ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያህል የዐደባባይ በዓላት በቦታው ሳይከበሩ ቆይተዋል።  በወቅቱ ችግሩን ለመፍታት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ሀገረ ስብከት ከቤተ መንግሥት እስከ ዞን ድረስ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ምንም መፍትሔ ሳያገኝ እንደቀረ ይታወቃል።  በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም  የመስቀል አደባባይና የጃን ሜዳ ጉዳይ እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል።  የቤተ ክርስቲያን ርስት ጉዳይ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ጎልቶ ይታይ እንጂ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም ጭምር ችግሩ አሳሳቢ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።  በነዚህ ሁለት ሳምንታት ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ርስት የተመለከቱ መልካም ዜናዎች መሰማት ጀምረዋል።  ከዚህ ቀደም የከፋ ችግር የነበረባቸው አካባቢዎች ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተቀራርበው ለመሥራትና የቤተ ክርስቲያን የርስት ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎት ያሳዩ የዞንና የወረዳ እንዲሁም የከተማ አስተዳድር አመራሮች መኖራቸውን ከየሀገረ ስብከቱና ከጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መረዳት ተችሏል።  እንደ ኅብረቱ መረጃ ከሆነ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ፷፭ አጥቢያዎች  የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሠርቶ ተሰጥቷቸዋል።  በሀገረ ስብከቱ እስካሁን ድረስ ፴፰ የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ተሠርቶላቸዋል።  ጃንሜዳን ጨምሮ ሌሎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን የተያዙ የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች በሕጋዊ ስምምነት ቤተ ክርስቲያን የይዞታው ባለቤት መሆኗ ተረጋግጦ ውል እንዲፈጸም የውል ስምምነቱ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ኅብረቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዳስገባ አስታውቀዋል።   ከዚህ ጋር ተያይዞ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ጃንሜዳ በአትክልት ተራነት ሲያገለግል መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ኅብረቱ ባደረገው ጥረት ገበያው ተነሥቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት አመራሮች በቦታው ላይ ተገኝተው በአካባቢው የነበረውን ቆሻሻ የማጽዳት ሥራ ራሳቸው በመሥራት አስጀምረዋል።  የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ሳይቀሩ የጥምቀት በዓል መዋያ ቦታውን በማጽዳት ለመጭው የጥምቀት በዓል ዝግጁ አድርገዋል።  በደቡብ ክልል ከርስት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመፍታት በኅብረቱ በኩል ከክልል እስከ ዞን ድረስ ባሉ መዋቅሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፤ ችግሮቹም ተለይተው ቀርበዋል።  የባለሙያዎችን ግኝት መሠረት ያደረገ ውይይትና የውሳኔ ሐሳብም ቀርቧል።  በውሳኔውና በቀረቡት ጥያቄዎች መሠረት የበዓላት ማክበሪያ ርስቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች እየተሠሩላቸው እንደሆነ ከኅብረቱ ሪፖርት ማረጋገጥ ተችሏል።  በተለይ በሃድያ ዞን ሆሣዕና ከተማ እንዲሁም በጋሞ ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ከቤተ ክርስቲያን  የይዞታ መነጠቅ ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በተደረገው ውይይት በመንግሥት አካላት የተነጠቁ የቤተ ክርስቲያን የበዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ለቤተ ክርስቲያን ተመላሽ እንዲደረጉ ከስምምነት ላይ መደረሱን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።  በተጨማሪም በመሎ ኮዛ ወረዳ ቤተ ክህነት ታሥረው የነበሩ ምእመናን በአጭር ጊዜ እንዲፈቱና የቤተ ክርስቲያን የይዞታ ጥያቄም ተገቢ በሆነ መንገድ እንዲፈታ ከስምምነት ላይ መድረሱን ኅብረቱ በሪፖርቱ አስታውቋል።  በ፴፱ኛው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ርክበ ካህናት  ወቅት የቀረበው የድሬደዋ ሀገረስብከት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከዚህ ቀደም የይዞታ ማረጋገጫ ያላገኙ አብያተ ክርስቲያናትና መካነ መቃብሮች ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ማግኘታቸው ተረጋግጧል።  በሀገረ ስብከቱ ለቤተ ክርስቲያን ማስፋፊያነት የተጠየቁ ተጨማሪ የመሬት ይዞታዎችም ተፈጻሚ ሆነዋል።  የቤተ ክርስቲያንን ክብር እና መብት ለማስጠበቅ የተቋቋመው ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠበቂ ኅብረት በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ባለሥልጣናት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱትን በደልና የሚፈጽሙትን አድሏዊ አሠራር ለማስቆም ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ አስታውቋል። የአብያተ ክርስቲያናትና የአደባባይ በዓላት መክበሪያ ቦታዎች ይዞታ እንዲከበሩ ከ፳፻፲፪ ዓ.ም. ጀምሮ ሰነዶችን በማዘጋጀት ወደ ተለያዩ ክልሎች በአካል በመጓዝ ለክልሎቹ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥያቄዎችን አቅርቦ ጉዳዩን ሲከታተል መቆየቱን ገልጦ፤ ከክልል መስተዳድሮችና ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር  በተከታታይ ከተደረጉ ውይይቶች በኋላ ተጨባጭ ውጤቶችን መስመዝገቡን አስታውቋል።  በተለይ የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች ኅብረቱ ላቀረበላቸው የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ጥያቄዎች በጎ ምላሽ በመስጠት ቀዳሚ ተጠቃሾች እንደሆኑ አስታውቋል። ለሐረሪ ክልል ባለሥልጣናት ከቀረበላቸው “ይዞታ ይከበርልን” ጥያቄዎች መካከል ክልሉ ቃል በገባው መሠረት የተወሰኑት ምላሽ አግኝተዋል። በሐረር ከተማ የሚገኙ አምስት አብያተ ክርስቲያናት እና የባሕረ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ተሰጥቷል። ኅብርቱም ለሐረሪ ክልል ባለሥልጣናት በጎ ምላሽ ምስጋናውን አቅርቧል።  በቀጣም ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ቦታዎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ የይዞታ ማርጋገጫ ሰነድ ተሠርቶ እንደሚሠጣቸው የኅብረቱ ሰብሳቢ ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ በሪፖርታቸው አስረድተዋል።  በተጨማሪም በጋሞ ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ እና በሆሳዕና ከተማ አስተዳድር የተፈጠረውን የቤተ ክርስቲያን  የይዞታ ችግር ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል። ችግሩ እልባት እንዲያገኝ የተሔደበትን መንገድ እና  የተገኘውን ውጤትም በቅርቡ እንደሚገለጽ ከኅብረቱ ሪፖርት ለማውቅ ተችሏል።  ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን እንጂ የማይገባትን አልፋ አትጠይቅምና መንግሥት የሚገባትን ያህል ርስት /ይዞታ/ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሊሰጣት ይገባል።  በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን የሀገሪቱ የመሬት አስተዳደር ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ተፈጻሚ ማድረግ ለመንግሥትም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን አዋጭ ነው።  ቤተ ክርስቲያን ካላት የምእመናን ብዛት አንጻር የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ማስፋፊያ የመካነ መቃብር ቦታዎችን ጨምሮ የዐደባባይ በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ይዞታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።  በሕጋዊ ቦታዎች የሚከበሩ የዐደባባይ በዓላት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች በመስህብነት የሚያገለግሉ በመሆናቸው ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ እንደምትሆን ሳይዘነጋ መንግሥት የሃይማኖትና የመንግሥትን ግንኙነት የወሰነውን ሕገ መንግሥታዊ አሠራር ተከትሎ የቤተ ክርስቲያንን የባለቤትነትን መብትና ጥቅም ሊያከብር ይገባዋል።  እግዚአብሔር ሀገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቅልን። 
Read 547 times