Monday, 11 January 2021 00:00

የአፍሪካ ክርስቲያኖችን ከጥቃት ለመከላከል ያለመ ውይይት ተካሄደ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የአፍሪካ ክርስቲያኖች በአክራሪዎች የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል ዓላማው ያደረገ የበይነ መረብ ቀጥታ ውይይት መደረጉን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነብቧል።  ውይይቱ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክና በሩሲያ የሃይማኖት ነፃነት መከላከያ ማኅበር አነሳሽነት የተጀመረ ሲሆን በአፍሪካ የሚገኙ ክርስቲያኖችንና ቅርሶችን ከአክራሪዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ለመከላከል የመፍትሔ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት እንደሆነ ዘገባው አስረድቷል።  በቀጥታ ውይይቱ የተገኙት የሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ የውጭ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሂላሪዮን ቮሎኮላማስሴ ‹‹በአክራሪዎች ጥቃት እየተሠቃዩ ያሉ አፍሪካውያን ክርስቲያን እኅት ወንድሞቻችንን መደገፍ የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ታሪካዊ ተልእኮ ትቀበለዋለች›› ማለታቸውን ከዘገባው ለማወቅ ተችሏል።  የሞስኮው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል እና ሁሉም ሩሲያዊ በግፍ ከሚገደሉትና ከሚሠቃዩት አፍሪካውያን ክርስቲያኖች ጎን እንደሚቆሙ ዘገባው ያስረዳ ሲሆን የአክራሪዎች ድርጊትም በተባበሩት መንግሥታቱ የሕግ ማዕቀፍ መሠረት መፍትሔ እንዲሰጠው እንደሚደረግም ዘገባው አስነብቧል።  ዓለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት የአፍሪካ ክርስቲያኖች ግድያና ስደት ጨምሯል ያሉት ደግሞ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ታኦድሮስ ሁለተኛ ናቸው።  የኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ሶሳይቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ፋዘር ዶክተር ያዕቆብ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለው የብሔር ልዩነት የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለተደጋጋሚ ጥቃት እንዳጋለጣት አንሥተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መደገፍ የሁሉንም ምእመናን መብት ማስከበር እንደሆነም ተናግረዋል።  በበይነ መረብ የቀጥታ ውይይቱ ወቅት የአፍሪካና የተለያዩ ዓለማት እምነት ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅና ፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሶሳይቲ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በተወያዮቹ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
Read 544 times