Friday, 22 January 2021 00:00

“የጥምቀት በዓል ለሀገራችን አንድነት ታላቅ ምሳሌ ነው” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

‹‹ የጥምቀት በዓል ለሀገራችን አንድነት ታላቅ ምሳሌ ነው›› ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጥር ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በጃንሜዳ በተከበረው የከተራ በዓል ላይ ተናገሩ፡፡  ቅዱስነታቸው አያይዘውም ‹‹ይህ በዓል  በዩኒስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች የተመዘገበ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ እና ብዙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የሚሳተፉበት በዓል ነው›› ብለዋል፡፡ በዓሉ በክርስትናችንና በእምነታችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆንን የምንገልጽበት ታላቅ በዓል በመሆኑ ምእመናን በአንድነት እና በፍቅር ሆነው ማክበር እንደሚገባቸው ጭምር አሳስበዋል፡፡ በዚሁ ታላቅ በዓል ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ “የጥምቀት በዓል የመልካችን ሰሌዳ የገጽታችን መገንቢያ ነው” ሲሉ  ባስተላለፉት መልእክት ተናግረዋል፡፡ የገጽታችን መገንቢያና የታሪካችን መንገሪያ  የሆነውን የጥምቀት በዓል ማጉላትና መጠበቅ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚጠበቅ ያነሱት ከንቲባዋ “የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ ቅርሱ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ ሆኗል” ብለዋል፡፡ እንደ ከንቲባዋ ገለጻ ልዩ በህል፣ቋንቋ፣ማንነትና ቀለም ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሰባስበው በአንድ ላይ በዓሉን ማክበራቸው የጥምቀትን በዓል ልዩ ገጽታ አጎናጽፎታል፡፡ ነገር ግን ልዩነታችንን ምክንያት አድርገን ጫፍ ለጫፍ  ቆመን ሀገር መገንባት፣ እግዚአብሔርን ማምለክና በዓላትን በነጻነት ማክበር አንችልም፡፡  የጥምቀት በዓል አንድነታችን የሚጠናከርበት፣ሰላማችን የሚረጋገጥበት እና ከፍቅር ስፍር የማንጎልበት በዓል ይሁን ሲሉም  ከንቲባዋ ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡  የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ለበርካታ ዓመታት የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ጃንሜዳ የይዞታ ማርጋገጫ ካርታ ተሠርቶ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሰጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድርን የጠየቁ ሲሆን ቦታውንም ለማልማትና ምቹ ለመድረግ ቤተ ክርስቲያን ዝግጁ መሆኗንም በዕለቱ አስታውቀዋል፡፡   
Read 550 times