Tuesday, 09 February 2021 00:00

የቤተ ክርቲስያን አብያተ መጻሕፍት ነገር

Written by  ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ

Overview

የኢትዮጵያ ጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ ታሪኮች የሚጠኑት በአመዛኙ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ምንጭ እየተደረጉ ነው።  የሀገራችንም የባህል፣ የትምህርት፣ የማኅበራዊ እሴቶች ቤተ መዛግብት ሆና ስታገለግል የኖረችው ቤተ ክርስቲያን ነች።  ስለዚህ የሀገራችንና የውጪ ሀገር ሊቃውንት የጥናት ማእከል ቤተ ክርስቲያንና የቤተክርስቲያን ሀብቶች ናቸው።  በተለይ የቤተ ክርስቲያን የጽሑፍ ሀብቶች እጅግ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው ናቸው።  ቅርስ ከመሆናቸውም አልፎ ለጥናት ምርምር ዋነኛ የመጀመሪያ ደረጃ ምንጮች ናቸው።    እነዚህ መጻሕፍት በየገዳማቱና አድባራቱ ዕቃ ቤቶች በክብር ተቀምጠው እንደሚገኙ ይታወቃል፤ ሌሎች ደግሞ ከቀደሙ ዘመናት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች/በምርኮና በዝርፊያ/ ከሀገር ወጥተው የሌሎች ሀገራት ሙዚየሞችና አብያተ መጻሕፍት ማክበሪያ ሆነዋል።  ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና ደቀ መዛሙርት ሳይቀሩ ለምርምርና ጥናት የሚፈልጓቸውን መጻሕፍት በቀላሉ ማግኘት እንዳይችሉ አድርጓል።  በአንድ በኩል በየገዳማቱና አድባራቱ መጻሕፍት መቀመጣቸው የማይጎዳ ሆኖ ለጥናትና ምርምር ግን በቀላሉ የማይገኙ፣ የማይፈቀዱ ሆነው ይታያሉ።  በውጪ ሀገራት ያሉት የገንዘብና የውጪ ጉዞ ሂደት ለማይቀናቸው ተመራማሪዎች በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም። 

 

የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት ግን ቤተ ክርስቲያን እንደ ሀብቷ ብዛትና በዚህ ረገድ እንዳላት የጎላ ስም የሚመጥን አንቱ የተባለ ቤተ መጻሕፍት በስሟ ማቋቋም አለመቻሏ ነው።  ቤተ ክርስቲያን አብያተ መጻሕፍት ቢኖሯትም በሚገባ ያልተደራጁ፣ የሚፈለገውን ያህል አቅርቦት የሌላቸው፣ በሥርዓት በመደበኛ ጊዜ አገልግሎት የማይሰጡ ሰዓቱን ጠብቀው የማይከፈቱና የማይዘጉ  . . . ወዘተ በመሆናቸው አርኪ አይደሉም።  ስለዚህ ተመራጭ አይደሉም ፤ ብዙ አንባቢም የላቸውም።  ለምሳሌ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚገኘው የተሻለ የሚባለው ቤተ መጻሕፍት እንኳን ከሚከፈትበት የሚዘጋበት ጊዜ ይበዛል፣ ያለው አቅርቦትም ከቤተ ክርስቲያን ብዙ ሀብት አንጻር ኢምንት የሆነ ሲሆን በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት አንቱታን ካገኙ የመንግስት ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አንጻርም ሲታይ በአግባቡ የተያዘ አይደለም።  

ሌሎች በማኅበራትና በሰንበት ትምህርት ቤቶች የተከፈቱ አብያተ መጻሕፍትም በሚሰጡት አገልግሎት ምስጉን ቢሆኑም ባላቸው የመጻሕፍት አቅርቦት አንጻር አጥኚና ተመራማሪ የሚፈለገውን ያህል አጥጋቢ  አይደሉም።  ቢያንስ አንዱ በአንድ መስክ ሌላው በሌላ መስክ/ዓይነት/ መጻሕፍትን በበቂ በመያዝ አማራጭ መሆን የሚችሉበትን ዕድል  አላሰፉም።  የሚቋቋሙትም በመዋጮ መጻሕፍት በመሆኑ እንደ ‹‹የኔ ቢጤ እህል›› በቂ ባልሆነ መጠን ደግሞም እጅግ በጣም የተደበላለቀ የመጻሕፍት ዓይነት በመያዝ ስለሚደራጁ የሚፈልጉትን አግኝቶ ለማንበብ ዕድል ይጠይቃል።  በዘመናዊ በካታሎግ አደረጃጀትም በቅደም ተከተል ሥርዓት አልተቀመጡም።  

የትኞቹ አብያተ መጻሕፍት ገድላትን በመጻሕፍት፣ በቅጂ፣ በማይክሮፊል አሟልተው በመያዝ የገድል አጥኚዎችን ያስደስታሉ? የትኞቹ በነገረ ሃይማኖት  /ዶግማ/ መጻሕፍት የተደራጁ ሆነው በዓይነት እነሱን በብርቱ ለሚፈልግ አንባቢ የሚጠቁሙ አብያተ መጻሕፍት ሆነዋል? ስንቶቹስ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በቀኖና ወዘተ ጉዳዮች ልዩ ቤተ መጻሕፍት ሆነው በመደራጀት ከሩቅም ከቅርብም አንባቢን ይጠራሉ? በዚህ ረገድ ያለንበት ደረጃ ዝቅተኛ ለመሆኑ በዓላማ በተለይም በጥናትና ምርምር መስክ ሥራዬ ብሎ ለመሰማራት በሚሞክሩ ሰዎች በቀላሉ ለማግኘት ይረዳል። 

ቤተ ክርስቲያን አብያተ መጻሕፍትን በስፋት ማደራጀት የሚኖርባት የምእመናንን ሕይወትበቃለ መጻሕፍት ለማነጽ ነው።  ይህ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የቤተ ክርስቲያን የሆኑ በቂ የጽሑፍ እና የሰነድ አቅርቦት ያላቸው አብያተ መጻሕፍት ሲደራጁ ነው።  ተመራማሪዎችም በቂ ማስረጃ ባገኙ መጠን ቤተ ክርስቲያንን በበቂ የሚገልጥ የጥናትና ምርምር ውጤት ይኖራቸዋል። ከማስተዋወቅ ባለፈም የአገልጋዮችን አቅም በበቂ ይገነባል። በግርድፍ ዕውቀት አገልጋይ ሆኖ ከመሰለፍ ደቀ መዛሙርትን ያንጻል።  ያላወቅናቸው ያልተረዳናቸውን ቤተ ክርስቲያዊ ጉዳዮች በጥናትና ምርምር በስፋትና በብቃት እንድናውቃቸው ያደርጋሉ።  በተጨማሪም የማኅበራዊ አገልግሎትን ከመስጠት አንጻርም ለሀገርና ለመንግሥት በመስኩ የንባብ ማእከላትን በማስፋት ምስጉን ተብለው ከሚጠሩት ተቋማት አንዱና ዋነኛ መሆን ያስችላል።  በተጨማሪም አብያተ መጻሕፍት ገቢ ማስገኛ እና ለአእምሮ ማሳረፊያ ሆነው ያገለግላሉ። 

የቤተ ክርስቲያን አብያተ መጻሕፍት በበቂ ሊደራጁ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል አለ።  በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ አጥቢያዎች ያሉ ለጥናትና ምርምር የሚረዱ መጻሕፍትና ሰነዶችን በቅጂ በማግኘት ሀገራዊ ሀብት ማሰባሰብ ይቻላል።  ምእመናን መጻሕፍትን በድጋፍና ትብብር እንዲሰጡ ቢጠየቅ በግዢና በስጦታ በርካታ መጻሕፍትን በአጭር ጊዜ ማግኘት ይቻላል።  

የተወሰነ በጀት መድቦ ደግሞ በሌላ አማራጭ ያልቀረቡና አዳዲስ የሆኑ መጻሕፍትን በመግዛት ማሟላት ይቻላል።  

ይህ ባለመሆኑ ግን የሀገሪቱ የመጻሕፍት ዋነኛዋ ባለሀብት ቤተ ክርስቲያን በደረጃ አነስተኛ የሆኑ አብያተ መጻሕፍት ቢኖሯትም አንድ እንኳን ስም ያለው፣ ግዙፍ፣ በሥርዓት እና ዘመናዊ በሆነ መንገድ የሚሠራ ቤተ መጻሕፍት ሊኖራት አልቻለም።  

ይህ ደግሞ የመጻሕፍት እናት ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነቷን ያሳጣታል።  ስለዚህ በነበሩት ላይ አስፍቶ ማደራጀት ካልሆነም በአንድ ግዙፍ ፕሮጄክት ይህን ሐሳብ እውን የሚያደርጉ ሰዎችን እንዲያነሣ ወደ እግዚአብሔር መጸለይና የራስንም ጥረት ማድረግ ይገባል እንላለን።

Read 493 times