Tuesday, 09 February 2021 00:00

ጥቅም ፍለጋ የገባሁበት ትዳር መውጫ አሳጥቶኛል

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ሰነበታችሁ ስሜ ወለተ ገብርኤል ይባላል የምኖረው አሜሪካን ሀገር ሲሆን እድሜዬ ወጣት ከሚባሉት ውስጥ ነው።  በዓለማዊ ትምህርት ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ በልጅነቴ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አድጌያለሁ ያቺ እርሾ ናት ወደ እናንተ እንድጽፍ ያነሳሳችኝ።  ወደ አሜሪካን ሀገር የሔድኩት ዲቪ የደረሰው የድሮ የትምህርት ቤት የክፍል ጓደኛዬን አግብቼ ነው።  ያገባሁት አሜሪካን ሀገር ለመሄድ እንጂ የምወደው እና ትዳር መስርቼ አብሬው ለመኖር የምፈልገው የምወደው ሌላ የልጅነት ጓደኛ አለኝ።  ያገባሁት ከዚህ ሀገር እንድወጣ ብቻ እንደሆነ ልቤ ቢያውቅም በተቃራኒው አግብቶ የወሰደኝ የክፍል ጓደኛዬ ግን ዛሬም ድረስ የእውነት ጋብቻ ከኔ ጋር እንደፈጸመ ነው የሚያውቀው።  እሱን ፈትቼው ፍቅረኛዬን አግብቼ ወደ አሜሪካን ሀገር ለመውሰድ እቅድ አለኝ ይህንንም ከፍቅረኛዬ ጋር ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እንደማልከዳው ነገሮች ሲመቻቹ ልጁን ፈትቼ እሱን በማግባት እንደምወስደው ቃል ገብቻለሁና ነው።  ውድ የስምዐ ጽድቅ አዘጋጆች አሁን እያስጨነቀኝ ያለው እንደ እውነተኛ ሚስቱ የሚያስበኝ የአሜሪካው ባለቤቴ እንድወልድ ይፈልጋል እኔ ደግሞ ገና የማገባውና የምጠብቀው ሰው ስላለ ይህንን መፈፀም አልችልም።  እውነቱን ነግሬው ለመለያየት እጅግ ተቸግሬአለሁ።  ምክንያት ፈልጌ ልጣላው ሁሉ ብዙ ሞከርኩ ነገር ግን ለማደርግበት ክፉ ነገር ሁሉ ይቅርታ እያደረገ ያልፈኛል።  ኢትዮጵያ ያለው ፍቅረኛዬ ደግሞ የፍቺዬን ቀን በጉጉት እየጠበቀ ነው።  የኔም አካል አሜሪካን ይሁን እንጂ ልቤ ኢትዮጵያ ካለው ፍቅረኛዬ ጋር ነው።  በዚህ ምክንያት ፍርሃቴ ጨምሮ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ መጸለይ ሁሉ አቁሜያለሁ።  ጥቅም ፍለጋ እንደ ቀልድ የገባሁበት ነገር መውጫ አሳጥቶ እንቅልፍ ነስቶኛልና ከዚህ ጭንቀት እንዴት ልውጣ? እባካችሁ ከጭንቀቴ የምገላገልበትን መንገድ ጠቁሙኝ። 

   

ወለተ ገብርኤል በቅድሚያ ከጭንቀቴ የምገላገልበትን መንገድ ጠቁሙኝ ‹‹ጥቅም ፍለጋ የገባሁበት ትዳር መውጫ አሳጥቶኛል›› ብለሽ ላቀረብሽልን ጥያቄ እናመሰግናለን።  ይህንን ጥያቄም ልታቀርቢ የቻልሽው አንቺው እንደ ገለጽሽው ዕድገትሽ ወቅት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሆኑ ክርስቲያን የሆነ ሰው ሁሉ ለችግሩ መፍትሔ የሚያገኘው ከቤተ ክርስቲያን መሆኑን ኅሊናሽ ስላመነ ነው።  

ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በትምህርቱ እንደገለጸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሐኪም ቤት ናትና።  ለችግሮች ሁሉ መልስ አላት።  ወለተ ገብርኤል ጋብቻን ጥንት ጥዋት የመሠረተ እግዚአብሔር መሆኑን በቅድሚያ ማመን ይገባሻል።  ለአንድ አዳም አንዲት ሔዋንን ፈጥሮ ጋብቻን የመሠረተ እርሱ ነውና።  በጥንተ ጠላት በዲያብሎስ ምክር ይህ ጋብቻን የመሠረተ እርሱ ነውና።  በጥንተ ጠላት በዲያብሎስ ምክር ይህ ጋብቻ ቢፈርስም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ በቃና ዘገሊላ በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ የፈረሰውን ጋብቻ ባርኮና ቀድሶ ዳግም መሥርቷል።  

ወለተ ገብርኤል በዓለማዊ ትምህርትም ሁለተኛ ድግሪ አለኝ በልጅነቴም እድገቴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ብለሽናል። የመማር ጥቅሙ ለማወቅ፤ ያወቁትን ለመተግበር ነው።  በልጅነትሽ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስታድጊ ስለጋብቻ ያለሽ ግንዛቤ የተሳሳተ ነበር ማለት ነው።  ምክንያቱም ለአንድ አዳም አንዲት ሔዋንን የፈጠረ እግዚአብሔር መሆኑን አላስተዋልሽምና።  

ወለተ ገብርኤል ወደ አሜሪካ የሄድሽው አንቺው እንደገለጽሽልን ጥቅም ፍለጋ እንጂ እውነተኛ ትዳር መሥርተሽ አይደለም ይህንንም ልብሽ እያወቀ በማድረግሽ አሁን አብረሽው ያለሽው የትዳር አጋርሽን ዋሽተሽዋል።  በነቢየ ልዑል ኢሳይያስ አድሮ እግዚአብሔር እንዲህ ማለቱን ልብ በዪ።  ‹‹ጌታም።  ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና በከንፈሮቹም ያከብረኛልና ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና›› (ኢሳ.፳፱፥፲፫)። በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ እግዚአብሔርን መፍራት ለእንዲህ ዓይነት ፈተና ይዳርጋል።  

ወለተ ገብርኤል ከሁሉም በላይ መረዳት ያለብሽ ዐቢይ ጉዳይ ደግሞ የሚከተለው ነው።  ‹‹መፋታትን እጠላለሁ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር›› (ሚል.፪፥፲፭) እንግዲህ ወለተ ገብርኤል እግዚአብሔር አምላክ መፋታትን እጠላለሁ ካለ እግዚአብሔር የጠላውን የሚወድ ደግሞ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ መሆኑን ልትገነዘቢ ይገባል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አይሁድን ሲገሥጽ ያስተማረውን ቃል አስተውይ።  ቃሉም እንዲህ ይላል።  ‹‹እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ።  የአባታችሁንም ምኞች ልታደርጉ ትወዳላችሁ እርሱ ከመጀመሪያ ነፍስ ገዳይ ነበረ እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ የሐስትም አባት ነውና። ››( ዮሐ.፰፥፵፬)

ወለተ ገብርኤል በቅድሚያ የሐሰት መገኛ ምንጩ ዲያብሎስ መሆኑን በጌታችን ትምህርት መረዳት ከቻልን አንቺ በቅድሚያ ወደ ሀገረ አሜሪካ ለመሄድ ብለሽ በዲቪ ይዞሽ ለሄደው ወንድማችንም ከልብሽ ሳይሆን ‹‹ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው›› በማለት ጌታችን ከተናገረላቸው ሕዝቦች ጎራ ያስመድብሻል።  ምክንያቱም አንቺም አጋርሽን በከንፈርሽ እያከበርሽ በአፍሽም እየወደድሽ በልብሽ ግን ከእርሱ በመራቅሽ ዋሽተሽዋልና ነው።  

በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው ትንሹ ልጅ ‹‹አባቴ ሆይ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው።  አባትም ገንዘቡን ከፍሎ ሰጠው።  ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደሩቅ ሀገር ሄዶ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ።  ሁሉንም ካከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ረኀብ ሆነ እርሱም ይጨነቅ ጀመር።  ሄዶም ከዚያች ሀገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ እርሱም እሪያ (ዓሳማ) ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።››

እሪያዎችም ከሚባሉት አስር ሊመገብ ይመኝ ነበር።  የሚሰጠውም አልነበረም።  ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፡- እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔግን በዚህ በረኀብ እሠቃያለሁ።  ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና።  አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልሁ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።  ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት።  ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።  ልጁም አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልሁ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው።  አባቱ ግን አገልጋዮቹን አለ ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ አምጡና አልብሱት ለጣቱ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ።  የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት።  እንብላም ደስም ይበለን።  ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል።  ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም ደስም ይላቸው ጀመር።›› (ሉቃ.፲፭፥፲፪-፳፬)

ወለተ ገብርኤል ይህ ከአባቱ ቤት ጠፍቶ የነበረው ልጅ ወደ ልቡ ተመልሶ ለአባቱም አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልሁ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም በማለት መናዘዙን ልብ በዪ።  ይህ ልጅ ከአባቱ ተለይቷል፣ ከአባቱም ቤት ወጥቷል፣ ከአባቱም ቤተሰብ ተለይቷል።  የሁላችን አባት እግዚአብሔር ስለሆነ ስንጸለይ አባታችን ሆይ ብለን እንለምነዋለን።  

ከአባቱ ቤት የጠፋው ልጅ በሰው ቤት አሽከርነት መግባቱ ሳያንስ የእሪያውን ምግብ እስከ መመገብ መድረሱን ልብ በዪ።  ወለተ ገብርኤል የእሪያ ምግብ የተባለው የአሕዛብ ተግባር ነው።  ጋብቻን እንደ ቀላል ነገር ተመልክተው ለፍቺ የሚነሳሱ እና በጋብቻ ላይ ጋብቻ የሚፈጽሙ አሕዛቦች ናቸውና።  

እግዚአብሔር በሊቀ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አድሮ ‹‹የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞት የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃናልና። ›› (፩ኛ ጴጥ.፬፥፫) ብሏል።  ወለተ ገብርኤል መፋታት እግዚአብሔር የሚጠላው ዲያብሎስ የሚወደው ተግባር መሆኑን እና የአሕዛብ ተግባር መሆኑን በቅድሚያ መረዳት ይገባሻል።  

ከአባቱ ቤት የጠፋው ልጅ ወደ ልቡ እንደተመለሰና ወደ አባቴ ቤት እመለሳለሁ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም በማለት ወስኖ ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረጉንም ልብ በዪ ይህ ከአባቱ ቤት የጠፋው ልጅ ነፍሱ ከሥጋው ሳይለይ ነው ወደ አባቱ የመጣው አባቱም ገንዘቤን በትኖ፣ ስሜን አጉድፏል ብሎ ሳይጠላው ሩጦ አቅፎ እንደሳመው ቃሉ ይመሰክራል።  ልጁ በቁም የሞተ መሆኑንም አባቱ መስክሯል።  ይህ ልጄ ሞቶ ነበር እንዲል።  

ሲመለስ ግን ሕያው ሆነ ተብሏልና።  ወለተ ገብርኤል ይህ የአንቺ ጉዞ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ተግባር አለመሆኑን በቅድሚያ ልትገነዘቢ ይገባል።  ለጠፋው ልጅ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጥታችሁ አልብሱት አባቱ ማለቱንም አስተውይ።  ከሁሉ የተሻለው ልብስ የተባለው ንስሐ ነው፣ ስለዚህ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ላደረግሻቸውም፣ ላሰብሻቸውም ንስሐ ግቢ፣ ከዚያም ከሁሉ የተሻለ ልብስ መልበስሽን ማስታወስ ይገባሻል።  በጠቢቡ ሰሎሞን አድሮ እግዚአብሔር ‹‹ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።›› (ምሳ.፳፰፥፲፫) ብሏል።  

ወለተ ገብርኤል በቅድሚያ የገባልሽልን ሀሳብ ሁሉ እንደ አንድ ክርስቲያን ኃጢአት መሆኑን ልትረጂ ይገባል።  እርሱም ትዳርን ያህል ትልቅ ተቋም ለማፍረስ ማሰብና በጋብቻ ላይ ጋብቻን መመኘት በሕግ ወንጀል በሃይማኖትም ኃጢአት ነውና።  ስለዚህ አሁን ከአንቺ የሚጠበቀው በቅድሚያ የነፍስ አባት መያዝ፣ ከዚያም ንስሐ መግባት፣ ሀገር ውስጥ ለሚገኘው ለቀድሞ ጓደኛሽ የራሱን የትዳር አጋር እንዲፈልግና የራሱን ሕይወት እንዲመሠርት በግልጽ ንገሪው።    

አንቺ ደግሞ የመሠረትሽውን ትዳር እውነተኛ ትዳር መሆኑን ከልብሽ እመኚ ከነፍስ አባትሽ ጋር ከተነጋገርሽ በኋላ አሁን አብረሽው ያለሽውን የትዳር አጋርሽን በግልጽ ነግረሽው ይቅርታ ጠይቂው።  ክርስቲያን በፈተናው ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን እየገሠገሠ ችግሩን ለእግዚአብሔር ተናግሮ መፍትሔ እንደሚያገኝ እመኚ። ዛሬ ከቤተ ክርስቲያንና ከጸሎት የለየሽ መንፈስ ነገ ደግሞ ወደ ክሕደት ሳይወስድሽ የመዳን ቀን ዛሬ ነው ተብሏልና በጸሎት በርቺ።  ከቤተ እግዚአብሔር አትለይ ስለ ደረሰብሽ ፈተና ደግሞ ገዳማዊያኑ አባቶቻችን እንዲጸልዩልሽ ሀገር ቤት ባሉት ቤተሰቦችሽ በኩል መባ በመላክ በጸሎት እንዲያስቡሽ አስደርጊ።  ምክንያቱም ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች›› (ያዕ.፭፥፲፮) ተብሏልና።  

ወለተ ገብርኤል ከአባቱ ቤት እንደጠፋው ልጅ አንቺም ወደ ልቡናሽ ተመልሰሽ ንስሐ ገብተሽ፣ ትዳርሽን አጽንተሽ ይዘሽ ክርስትናን በሕይወት እንድትኖሪ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም ምልጃ፣ የቅዱሳን ጸሎት ይርዳሽ።

Read 682 times