Wednesday, 26 August 2020 00:00

አጋጣሚዎችን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ይቁም!

Written by 

Overview

አጋጣሚዎችን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ይቁም! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ መከራዎችን አሳልፋለች። በዚህም  ከመገፋት ያረፈችበት፣ ከጥቃት የተረፈችበት ጊዜ የለም። እንዲያውም መገፋት ግብሯ እስከሚመስል ድረስ የመከራ ዶፍ የሚወድባት ግፍ ተቀባይና ተገፊ እየሆነች ነው። በየዘመናቱ አያሌ ፈተናዎችን ተሻግራ ዛሬ ላይ ብትደርስም አሁንም  እንደጥንቱ ከውጪም ከውስጥም ብዙ መከራዎች እየተፈራረቁባት ይገኛሉ። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነት በሌላቸው ምክንያቶች ሁሉ በርካታ ጥቃቶች እየተፈጸሙባት ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ መለያየትና መከፋፈል ከሌለ ህልውናቸው የሚያከትም የሚመስላቸው አካላት መከፋታቸውና ቤተ ክርስቲያንን በጠላትነት መፈረጃቸው የማይቀር ነው። ለዚህም ነው በሰበብ አስባቡ ቤተ ክርስቲያንን ማጥቃት ግብራቸው አድርገው የተያያዙት።  ፖለቲከኞች  እያራመዱት ያለው የዘውግ ፖለቲካና ርእዮተ ዓለም በታሪክ ስም በቤተ ክርስቲያን ላይ እየነዙት ያለው የሐሰት ትርክት ቤተ ክርስቲያንን በብዙኃኑ ዘንድ ጠላት አድርጎ በመፈረጅና ወዳጅ አልባ በማድረግ ለጥቃት እያመቻቿት  ነው። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ሃይማኖታዊ  አመክንዮ  የሌላቸው በለውጥ ስም የሚቀርቡ ጥያቄዎች ሁሉ የሚጠናቀቁት ቤተ ክርስቲያንን በማቃጠልና ኦርቶዶክሳውያንን በመግደል  ሆኗል። ሐምሌ ፳፻፲ ዓ.ም በሶማሌ ክልል በክልሉ መንግሥት የተደራጀውና ሂጎ የተሰኘው ቡድን በታቀደና በተጠና መንገድ አብያተ ክርስቲያናትን አቃጠለ፤ ካህናትንና ምእመናንን በአሠቃቂ ሁኔታ በማረድ አስከሬናቸውን በእሳት አቃጠለ፤ ነፍሰ ጡርና ሕፃናትን ጨምሮ ብዙ ሴት ኦርቶዶክሳውያን ተደፈሩ። ቤታቸውን አስቀድሞ ቀለም  በመቀባት በተቀናጀ መልኩ ሀብት ንብረታቸው በእሳት እንዲወድም አደረገ። በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ሪፖርት ሲደረግ እንደነበረው የክልሉ ርእሰ መስተዳደድር በነበረው ግለሰብ እና ግብረ አበሮቹ ላይ ክስ ቢመሠረትም ክስ ከተመሠረተባቸው በርካታ ተጠርጣሪዎች ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋሉ አሉ። ከደረሰውም ጥፋት አንጻር በአጥፊዎች ላይ የተወሰደው ርምጃ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ከዚያ በኋላ በተመሳሳይ መልኩ ጥፋት እያደረሱ ያሉ አካላትን ያበረታታ ይመስላል። 

 

በተመሳሳይ ሐምሌ !፻01 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ያቀረበውን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ ቀን ቆርጦ በተፈጸመ ጥቃት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ኦርቶዶክሳውያን ተገድለዋል። ዞኑ የክልል ልሁን ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ለመንግሥት፣ መልስም መጠበቅ የነበረበት ከመንግሥት ሆኖ ሳለ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማጥቃት መነሻው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ከስምንት ያላነሰ አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠልና  ኦርቶዶክሳውያን በመግደል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ግለሰቦች ክሳቸው ተቋርጦ በነጻ ተሰናብተዋል። 

ከዚያም በኋላ ጥቅምት !፻0፪ ዓ.ም መንግሥት ጥበቃዎቼን ሊያነሣብኝ ነው የሚል የአንድ ግለሰብን የተከብቤያለሁ ጩኸት ተከትሎ በተከፈተ ሃይማኖት ተኮር ጥቃት ንጹሐን ዜጎች ተገድለዋል። ከዚህ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኦርቶዶክሳውያን ሲሆኑ በተለይም በባሌ፣ በዶዶላ፣ በኮፈሌ፣ በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ብዙ ኦርቶዶክሳውያን ተገድለዋል። ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ወድሞባቸዋል። በዚህ ጥፋት የተወሰደውን ርምጃ ስንመለከት ደግሞ ክስ ከተመሠረተባቸው ውስጥ የሚበዙት አጥፊዎች ሳይሆኑ ተጠቂዎች ነበሩ። ለማሳያ ያህል እነዚህን ጠቀስን እንጂ በተለያዩ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ ተደራራቢ ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ በአጥፊዎችም ላይ ምንም ርምጃ ሳይወሰድ በአጸፋው ቤተ ክርስቲያን እንዳይቃጠልም ሆነ ራሳቸውን ከሞት ለማዳን የተከላከሉ ኦርቶዶክሳውያን እስርና እንግልት ሲፈጸምባቸው ታይቷል።

በሰኔ ወር ፳፲፲፪ዓ.ም ደግሞ  በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች የጥፋት ኃይሎች በሰነዘሩት ጥቃት የንጹሐን ዜጎች ሕይወት ሲያልፍ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኦርቶዶክሳውያን ናቸው። በአዲስ አበባና በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ኦርቶዶክሳውያን በሃይማኖታቸው ምክንያት ብዙ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ብዙ ናቸው። ቤታቸውና ለብዙ ዓመታት በድካም ያፈሩት ሀብት ንብረታቸው እንዳልነበረ ሆኖ በእሳት ወድሞባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን የማንኛውም ሰው ሞት የማያስደስታት ብትሆንም በሞት ያጣችው የራሷ ልጅ ሆኖ ሳለ፣ በሐዘን ላይ ሐዘን ለመጨመር ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሌሎች ልጆቿንም በሞት አጥታለች። 

በአጠቃላይ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ አካላት የሚያደራጁት ቡድን ጥቃት፣ የዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄ፣ የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች አቀባበል፣ የግለሰቦች የተከብቤያለሁ ጩኸትና የግለሰቦች ሞት ቤተ ክርስቲያንን ማጥቂያ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል። በእነዚህ ሁከቶች መሣሪያነት ቀድሞ የታሰበና የታቀደ በሚመስል መልኩ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ከጥቃቱም በኋላ ጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞች ምንም ሳይደረጉ ሲቀሩና በተቃራኒው ተጠቂዎች ሲንገላቱና ሲታሰሩ ሲታይ ጥቃቱ መዋቅራዊና ስልታዊ ሆኖ የተፈጸመ ይመስላል። 

ቤተ ክርስቲያን በሠራችው አገር፣ ባቀናቸው ቀዬ በሁሉ እየተገፋች ነው። እነዚህ ሁሉ ጥቃቶችና መገፋቶች ሕዝበ ክርስቲያኑን በአገሩ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ የሚጠብቀው መንግሥት እንደሌለ በማሰብ ራሱን ለመጠበቅ ወደ መገደድ ጠርዝ እየገፉት ይገኛሉ። ይህ ቀቢጸ ተስፋ ደግሞ በአገር ላይ የማያባራ ግጭት ሊያመጣ የሚችል ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች ከዚህ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ጥቃት እያደረሱ ባሉ አካላት ላይ መንግሥት የማያዳግም ርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ በተጨማሪም በተቃራኒ የጥቃቱ ሰለባ በሆነው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ የሚደርሱ መገፋቶችና እንግልቶችም ሊቆሙ ይገባል። 

 

Read 651 times

Latest from Gidey Gebre