Search results for: ሐመር መጽሔት - ሐመረ ጽድቅ
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ስሜ  ገብረ ሚካኤል ይባላል የምኖረው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን በድኅረ ገጽ የሚወጡ የስምዐ ጽድቅ እና ሐመር መጽሔት ሥራዎችን እከታተላለሁ። በተለይ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ‹‹ ምሥጢሬን ላካፍላችሁ›› በሚለው ዐምድ ሥር የሚወጡ ጽሑፎችን ትኩረት ሰጥቼ እከታተላለሁ፤ ብዙ ቁም ነገሮችንም አግኝቼበታለሁ። የራሴን ጥያቄ ላቀርብ የተነሣሣሁትም መልስ ትሰጡኛላችሁ ብዬ በማመን ነው።  ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! ከልጅነት ጀምሮ አብሮ አደግ የሆነ ጓደኛ አለኝ የአንድ ሰፈር ልጆች ስንሆን ከሠላሳ ዓመታት በላይ አብረን ኖረናል። ጓደኛዬን የራሴን ያህል አምነዋለሁ ቤተኛዬም ነው። በአንድ ወቅት በጣም ስለቸገረው ገንዘብ ከመንግሥት ለመበደር ፈልጎ ቤቴን አስይዤ ዋስ ሆንኩት፤ ነገር ግን ገንዘቡን ከወሰደ በኋላ ዕዳውን ለመንግሥት መመለስ ባለመቻሉ የእርሱን ዕዳ ለመክፈል ቤቴ እስከመሸጥ ደረሰ በዚያም ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋለጥኩኝ። ይህ የልጅነት ወዳጄ ቤቴ ከመሸጡ በፊት ገንዘቡን እንዲመልስ ብዙ ጊዜ ጠየኩ አስጠየኩት ፤ነገር ግን ‹‹ቸግሮኝ ነው›› በሚል ምክንያት ዕዳውን ሳይከፍል ቀርቶ ለችግር አጋለጠኝ። በፍርድ ቤት እንዳልከሰው ‹‹ክርስቲያን ሆኜ›› የሚል ይሉኝታ ያዘኝ እንዳልተወው ከላይ እንደጠቀስኩት የከፋ ችግር ላይ ነኝ። እግዚአብሔርን በመፍራት ክሱን ብተወውም ያደረገውን ክፉ ሥራ ግን መርሳት አልቻልኩም። ከነገ ዛሬ ይመልስልኛል በሚል ተስፋ ምንም እንዳልተፈጠረ ስቄ ባናግረውም ያደረገውን ነገር በጥላቻ ከማሰብ አልቦዘንኩም። ቂም ኃጢአት እንደሆነ ባውቅም መተው ግን አልቻልኩም። ጓደኛዬን ባገኙሁትም ሆነ አጠገቤ በሌለ ሰዓት የሠራው ነገር ወደ ልቤ እየመጣ ተቸግሬአለሁ እና በእርሱ ላይ ያለኝን ቂም እንዴት ልተው? መፍትሄ ጠቁሙኝ። ገብረ ሚካኤል ‹‹ቂሜን እንዴት ልተው?›› በማለት ቂመኛ እንድትሆን ያደረገህን ምክንያት ዘርዝረህ መፍትሔ ፍለጋ ጥያቄህን ስላቀረብክልን በቅድሚያ ምስጋና እናቀርብልሃለን። ሰው በሥጋው ሲታመም መታከም ስላለበት የትኛው ሐኪም ቤት ሄዶ የትኛውን የጤና ባለሙያ እንደሚያገኝና ታክሞም ከሕመሙ እንደሚድን በቅድሚያ እንደሚያስበው ሁሉ አንተም በክርስትና ሕይወትህ ላጋጠመህ ፈተናና የኅሊናህ ዕረፍት ለነሳህ ጉዳይ ከእናንተ መፍትሔ አገኛለሁ ብለህ ሳትደብቅ ጥያቄህን አቅርበህልናል። አበው ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም›› እንዲሉ ።  አንተው እንደገለጽክልን የምትኖረው በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን ከሠላሳ ዓመታት በላይ አብረህ እንደቤተኛ ሆነህ ከምትኖረው ጓደኛህ የገጠመህ ችግር ነው። ልበ አምላክ የተባለውን ንጉሥ ዳዊት ሲያስረዳ ‹‹ከቸር ሰው ጋር ቸር ሁነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሁነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ።›› መዝ.፲፯፥፳፭-፳፮ ይላል።     ገብረ ሚካኤል በቅድሚያ ከሌላ ሰው ጋር አብሮ አደጌ ነው ጓደኛዬ ነው ብለህ ሙሉ ልብህን ሰጥተህ አብረህ ከመጓዝህ በፊት ልበ አምላክ ዳዊት እንዳለው በተሰጠህ ዕውቀት ጓደኛህን በቅድሚያ መመርመር ግድ ይላል። ቸር ነው፣ ቅን ነው፣ ንጹሕ ነው፣ ጠማማ ነው ለማለት እንኳን ሠላሳ ዓመታትን ይቅርና ጥቂት ወራትም ዓመታትም በቂ ናቸውና። በመጽሐፍ ‹‹የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል?›› ኤር.፲፯፡፱ እንዲል።  መጽሐፍ ቅዱስ በገንዘብ እና በክህደት ምክንያት በቤተሰባቸው ሳይቀር የተፈተኑ ሰዎች መኖራቸውን ይገልጽልናል። ለምሳሌ የያዕቆብን ልጅ ዮሴፍን ለግብጽ ነጋዴዎች የሸጡት የአባቱ ልጆች ወንድሞቹ ናቸው (ዘፍ ፴፯፥፳፯።) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ እንኳን አብሮ አደግ ጓደኛ ይቅርና ‹‹ለሰውም ቤተሰቦቹ ጠላቶቹ ይሆኑበታል›› (ማቴ.፲፥፴፮) ብሎናል። ይህ የሚያሳየን እንኳን በሥጋ የማትዛመደው በሆነ ጊዜ ላይ ያገኘኸው ጓደኛ ይቅርና ቤተሰብ (የሥጋ ዘመድ) እንኳ ቢሆን ላይታመን ይችላል። በመሆኑም የልብ ጓደኛዬ ነው ብለህ ልብህን የጣልክበት ጓደኛህ እንዲህ ዓይነት ሥራ በመሥራቱ ብዙ ሊደንቅህ አይገባም። አንተ ግን ‹‹ለሚለምንህ ስጥ ከአንተም ይበደር ዘንድ የሚወደውን አትከልክለው›› (ማቴ.፭፥፵፪) የተባለውን አምላካዊ ቃል በመተግበርህ ዋጋህ ሰማያዊ ተግባርህ ክርስቲያናዊ መሆኑ በቅድሚያ ኅሊናህን ልታሳምነው ይገባል።   በእርግጥ ጓደኛህን ከማመንህና ከመውደድህ የተነሳ በተቸገረ ጊዜ ቤትህን አስይዘህ ዋስ እንደሆንክለትና እርሱም ገንዘቡን መክፈል ባለመቻሉ ቤትህን እስከመሸጥ እና ዕዳውን እስከመክፈል መድረስህን በዚህም ለጓደኛህ ስትል ለክፉ ችግር መጋለጥህን ጠቅሰህልናል።  መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔርን ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።›› ሮሜ.፷፡፳፷ እንዲል። ጓደኛህ ባደረገህ ነገር እጅግም ሳታዝን ለበጎ  ነው ብለህ መቀበል ይገባሃል። በተጨማሪ ራስህን በእርሱ ቦታ ማስቀመጥም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ማንም ሰው በራሱ ፍጹም አይደለምና። ገብረ ሚካኤል ይህ ፈተና በጓደኛህ በኩል ላንተ መቅረቡ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አለመሆኑን ማወቅ ይገባሃል። ፈተናውንም በጸጋ ትቀበል ዘንድ ጽናቱን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። እንደ ኢትዮጵያዊያን ባሕል ጓደኛህን በሽማግሌ አስጠይቀው። የሽማግሌዎችን ድምፅ አልሰማም ካለም ጉዳዩን ለእግዚአብሔር ብቻ አሳውቀህ ከልብህ ተውለት። ይቅርታ ማድረግ ምሬትን፣ መብሰልሰልን ስለዚያ ክፉ ነገር በተደጋጋሚ ማሰብን ያስወግዳል። በእርግጥ ይቅርታ ማድረግ በደልን መርሳት ወይም የተሰራውን ስህተት ትክክል ነው ብሎ መቀበል አይደለም ይልቁንም ‹‹ይቅርታ ማድረግ›› በውስጥህ ያሳደረብህን መጥፎ ስሜት መቆጣጠር መቻልና መተው ነው።   በጥያቄህ ውስጥ እንደገለጽክልን ለመክሰስ አስቤ ‹‹ክርስቲያን ሆኜ›› እንዴት እከሰዋለሁ እያልኩ ከኅሊናዬ ጋር እየተሟገትኩ እገኛለሁ ብለሃል። ከላይ እንደገለጽክልን በሸማግሌዎች ጠይቀኸው እንቢ ካለ አንተ ቂም መያዝ አይገባህም። ምክንያቱም አበው ‹‹ቂም ይዞ ጸሎት›› ዋጋ እንደሌለው ይገልጻሉና። አንተም ጸሎትህ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ መሻትህን ይፈድምልህ ዘንድ ለነፍስ አባትህ ጉዳዩን አስረዳና ቀኖና ተቀበል።  ስለ ይቅርታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትልቅ ምሳሌያችን ነው። የሰው ልጆች ያለባቸው እዳ ራሱን አሳልፎ በመስጠት ከፍሏልና። የአዳምን በደልና ኃጢአት ወደዚህ ምድር መምጣቱ ፣ ሥጋን መዋሃዱ ፣ በምድር ላይ ተመላልሶ ማስተማሩ የሰው ልጆች በአዳም ምክንያት ያጡትን ገነት እንዲወርሱ ነበር። ነገር ግን ጌታችን በምድር በነበረበት ጊዜ ላደገላቸው ልካም ነገር ሁሉ ክፉን መልሰውለታል። ይህም ሳይበቃቸው በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት አድርገውታል። ነገር ግን ያበላቸው፣ ከበሽታ ያዳናቸው፣ ከሰው እኩል ያደረጋቸው በአደባባይ ወጥተው ‹‹ ይሰቀል! ይሰቀል! ይሰቀል!›› ብለው ሲጮሁበት  ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ›› ሉቃ ፳፫፥፴፬ በማለት ሲጸልይላቸው እናያለን። ገብረ ሚካኤል አንተ ጌታችን ድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደረሰበት በደል የበለጠ በደል፤ ከደረሰበት መከዳት የበለጠ መከዳት አልደረሰብህምና እርሱን አብነት አድርገህ ልትጽናና ይገባሃል።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕዳ ስለተያዘው ባርያ እና ዕዳውን ስለሰረዘለት ጌታው በምሳሌ ባስተማረበት አንቀጹ  ‹‹መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቆጣጠራቸው የወደደ ንጉሥን ትመስላለች። ሊቆጣጠራቸውም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት የሚከፍለውን አንድ ባለ ዕዳ ወደ እርሱ አመጡ። የሚከፍለውም ባጣ ጊዜ ጌታው እርሱንና ሚስቱን፣ ልጆቹም፣ ያለውም ሁሉ እንዲሸጡና ዕዳውን እንዲከፍል አዘዘ። ወዲያውም ያ አገልጋይ ወድቆ ሰገደለት፦ ‹‹ አቤቱ ታገሠኝ ሁሉን እከፍልሃለሁ እያለ ለመነው። ጌታውም ያን አገልጋይ አዘነለትና ፈታው ዕዳውንም ተወለት። . . . ›› ሉቃ ፲፰፥፳፫— ፴፭ ይለናል። ገብረ ሚካኤል አንተም እንደነገርከን ምንም እንኳ ቢቸግርህ ጓደኛህ ቸግሮት ሊከፍልህ ባለመቻሉ ይሆናል ብለህ ነገሩን በቅንነት በማየት ልትተውለት ብሎም በእርሱ ላይ ያለህን ቂም ከውስጥ አውጥተህ ልትጥል ይገባሃል። በመጽሐፈ ሲራክ እንደተገለጸው ‹‹እንዳንተ ያለውን ሰውን ይቅር ሳትል ኃጢአትህን ያስተሠርይልህ ዘንድ እንግዲህ እንዴት ትለምነዋለህ›› ሲራ ፳፷ ፥ ፬ ብሏልና። በቅድሚያ አንተ የይቅርታ ሰው ሁነህ መገኘት ይገባሃል። ይህ ያንተ ጓደኛ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንተን በመካዱ ኃጢአት ሠርቷል። ለእርሱ የሥራውን የሚከፍለው እግዚአብሔር እንጂ አንተ ስላልሆንክ ስለተደረገብህ ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ንገርለት (ጸልይለት)። መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና ለሰዎች ግን ኃጢአተኛውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።›› (ማቴ.፮፥፲፬-፲፭) ይላል።  ‹‹በይቅርታ የሚገኝ ድል በጦርነት አይገኝም›› የሚል የኢትዮጵያውያን ብሂልም አለ።  አንተ የበደለህን በተለይም ‹‹ የልቤ ወዳጅ›› የምትለው ሰው ያደረሰብህን በደል መተው በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ፊት የምታገኘው ይቅርታ ሲሆን ሁለተኛው ስለ ጓደኛህ የምታስበው መጥፎ ነገር በአንተ ስነ ልቦና ላይ የሚያስከትለውን ጫና ያስቀርልሃል። አንተም እንዳልከው ወደዚህ ዝግጅት ክፍል እንኳ ለመጻፍ የተገደድከው የጓደኛህ ድርጊት ሰላም ስለነሳህ ነው። ባንተ ላይ ያደረገውን ነገር ሙሉ በሙሉ ብትተውለት ደግሞ በራስህ ላይ ድልን ትጎናፀፋለህ፣ ሰላማዊ ትሆናለህ ማለት ነው። ስለዚህ አካላዊና ህሊናዊ ሰላም ለማግኘት እንዲሁም በጤንነት ለመኖር ጓደኛህን ይቅር ማለት ይገባሃል።  ስለዚህ ገብረ ሚካኤል ጓደኛህን ከልብህ ይቅር ማለት የሚገባው ፩ኛ. አንተም በማወቅም ባለማወቅም የሠራኸውን ኃጢአት ይቅር እንድትባል ነው። አለበለዚያ ይቅር አይላችሁም ተብሏሏና። ፪ኛው ለበደለህ ሰው ይቅርታ ማድረግ የውስጥህን ሰላም ይመልሳልና ነው። ይልቁንም እንደ ክርስቲያን ለጓኛህም ስመ ክርስትናውን ወደ ገዳማዊ አባቶች ላክና እንዲጸልዩለት አስደርግ። ‹‹በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ›› (ማቴ.፭፥፵፭) ተብሏልና። ጓደኛዬን ባገኘሁትም ሆነ አጠገቤ በሌለ ሰዓት ያደረገኝ ነገር ወደ ልቤ እየመጣ ተቸግሬአለሁ ስላልክ ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች›› (ያዕ.፭፥፲፮) ተብሏልና ለራስህም  ወደ ገዳማውያን አባቶች መብዓ ይዘህ በመሄድ እንዲጸልዩልህ አስደርግ።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ብለው መጸለይ እንደሚገባቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ጠይቀውት የጸሎት ሁሉ አባት የሆነውን ጸሎት አስተምሯቸዋል። ማቴ.፮፥፱-፲፫ በዚህ የጸሎት ክፍል ውስጥ ክርስቲያኖች ዘወትር ልብ ብለው ማስተዋል ከሚገባቸው ሐሳቦች ውስጥ አንዱ ‹‹የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን  ይቅር በለን።›› የሚለው ጸሎት ነው። እኛ የበደሉንን ይቅር ካላልን ይቅር አንባልምና ነው። ይቅር እንድንባል የይቅርታ ሰዎች የፍቅር ሰዎች ሆነን መገኘት ይገባናል። ‹‹ሙሉ ደመወዝ እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።›› (፪ኛዮሐ.፩፥፷) ተብለናል። በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በክርስትና ጉዞህ ከእግዚአብሔር ሙሉ ደመወዝ እንድትቀበል አንተን እየፈተነ ባለው ቂም ከልብህ ተነቅሎ እንዲጠፋ ከነፍስ አባትህ ጋር ተነጋግረህ ሱባዔ ይዘህበት ጸልይ። ቂም ይዘህ የምትጸልይ ከሆነ ግን ጸሎትህ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ለጥያቄ መልስ አያሰጥህም።  ሐዋርያው ‹‹እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገርን እናውቃለን። ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል”፡ ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይይኖር ታውቃላችሁ።›› (፩ኛ.ዮሐ.፫፥፲፬-፲፭) ብሏል። ስለዚህ ገብረ ሚካኤል አሁን ካለህበት የሞት መንገድ ወጥተህ በሕይወት መንገድ ለመጓዝ ጓደኛህን ከልብ ይቅር በለው። ያኔጊዜም እግዚአብሔር የተወሰድብህን ንብረት እንደ ጻድቁ ኢዮብ እጥፍ አድርጎ ይከፍልሃል። ይህን ካደረግህ ክርስትናውን በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ኖረህበታልና። ምድራዊውን ሀብት ብቻ ሳይሆን ሰማያዊውን ርስት እግዚአብሔር እንደሚያወርስህ እመን። ‹‹በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።›› ተብሏልና (ሉቃ.፰፥፲፭።) ገብረ ሚካኤል ቂም እንድንይዝ የሚያደርገን መንፈስ ከጠላት ከዲያብሎስ የሚመጣ መንፈስ ነው። ስለዚህ ክርስቲያን ደግሞ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ እንጂ በጠላት ክፉ መንፈስ መኖር አይገባውም። ‹‹የጌታችን ጽዋና የአጋንንት ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፣ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም።›› (፩ኛ ቆሮ.፲፥፳፩) ተብሏልና ቂም ኃጢአት መሆኑን እያወቅህ ቂም መያዝ ከአንተ አይጠበቅም። ‹‹ራቁቱን እንዳይሄድ አፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ለብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።›› (ራእ.፲፮፥፲፭) ተብሏልና ልብስ የተባለው ልጅነትህን ከቂም ርቀህ ከበቀል ወጥተህ ክርስቲያናዊ ሥርዓትና ሕግን ጠብቀህ ዋጋ እንድታገኝ አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር ይርዳህ።