ሐመርን ያውርዱ
ስምዓ ጽድቅ ያውርዱ
የወሩ የማኅበረ መልእክት
Tuesday, 23 February 2021 00:00
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋትና የማጠናከር ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ ዲ/ን አንድነት ብርሃኑ ገለጡ።    በአብነት ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ መርሐ ግብር ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሌላቸው አካባቢዎች ተለይተው አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የሚቋቋሙ ሲሆን በማጠናከሪያ መርሐ ግብር ደግሞ የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማሻሻልና የመደገፍ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ም/ኃላፊው ገልጸዋል።    ማኅበረ ቅዱሳን ሃያ አምስት አህጉረ ስብከት ለይቶ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የገለጡት ኃላፊው “በዚህ ዓመት ብቻ በአራት አህጉረ ስብከት የአብነት ት/ቤቶችን ለመሥራት እቅድ ይዟል” ብለዋል። እቅድ ከተያዘላቸው አራት አህጉረ ስብከት መካከል አፋር፣ ሶማሌ፣ አርሲና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት እንደሚገኙበት ያስታወቁት ኃላፊው የሶማሌ ሀገረ ስብከት የአብነት ትምህርት ቤት በቅርቡ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ሲሆን በዚህ ወርም የግንባታ ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል።    ሌሎች ተመሳሳይ የአብነት ትምህርት ቤቶች ግንባታም በሂደት ሥራቸው እንደሚጀመር አስረድተዋል።    አዲስ በሚቋቋሙ የአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአካባቢያቸውን ባህልና ቋንቋ ጠንቅቀው የሚያውቁ ወጣቶች ተመልምለው እንደሚገቡ ያስረዱት ኃላፊው በሚኖራቸው የሁለት ዓመት ቆይታም የቤተ መቅደስና የዐውደ ምህረት አገልግሎትን እንደሚቀስሙ ተናግረዋል።    ኃላፊው አያይዘውም ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ት/ቤቶችን ከማቋቋምና ከማጠናከር ባሻገር ጊዜያዊ የገንዘብ ድጋፍም እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።    አጠቃላይ ለተማሪዎችና ለመምህራን የሚደረገው ወርኅዊ የገንዘብ ድጋፍ በዓመት እስከ አምስት ሚሊዮን እንደሚደረስም አስረድተዋል።    ባልታወቀ ምክንያት ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም የሳት ቃጠሎ አደጋ የደረሰበት የጨጎዴ ሃና የቅኔ ማስመሥከሪያ ጉባኤ ቤት በአዲስ መልክ እየተሠራ መሆኑን ም/ ኃላፊው ተናግረዋል።   የቅኔ ማስመስከሪያ ጉባኤ ቤት ፕሮጀክት የተጀመረው ፳፻፪ ዓ.ም ሲሆን ለፕሮጀክቱ የዋለውን ፳ ሺህ ካሬ መሬት የሰጠው የምዕራብ ጎጃም ዞን የቋሪት ወረዳት መንግሥት ነው።    ፕሮጀክቱ የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመምህራን መኖሪያ፣ የተማሪዎች መፀዳጃ ቤትና የምግብ ማብሰያ ያካተተ ሲሆን ሲጠናቀቅም በርካታ ነባርና አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ ም/ኃላፊው ገልጸዋል።    ፕሮጀክቱ ከ፵፭ በመቶ በላይ የደረሰ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን የበጀት እጥረት እንደገጠመው አስረድተው የተፈለገው ያህል በጀት የሚገኝ ከሆነ ግን በቅርቡ መጠናቀቅ እንደሚችል አስታውቀዋል።    የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጭ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን ከዚህ ቀደም ወጭ የተደረገው  ገንዘብ ከምእመናን ድጋፍ የተገኘ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው “አዳዲስ የሚቋቋሙና ነባር የአብነት ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን በገቢ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።   
Tuesday, 23 February 2021 00:00
ሠርክ ቃለ እግዚአብሔርን የምንሰማባቸው የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቶች እንደሰባክያኑ መልካቸው የተለያየ ነው።  ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ቃለ እግዚአብሔርን ሰምተው ሊታነፁበት፣ ወደ ንስሓ ሊመለሱበት ፣ ባጠቃላይ የጽድቅ ሥራ ሊሠሩበት ነው።  ዛሬ ዛሬ በየዐውደ ምሕረቶቻችን የምንሰማቸው አንዳንድ ስብከቶች ዓላማቸውን የሳቱ፣ በግለሰብ ፍላጎት እና ሓሳብ ላይ የተመሠረቱ ሆነዋል።  በተከበረው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ወንጌል መሰበክ ሲገባው ስለኳስ ጨዋታ፣ ስለሰባኪው የግል ዝንባሌና ምኞት፣ስለ ዘረኝነት ፣ ስለ ወቅቱ የሀገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት እንዲሁም ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ያተኮረ መልእክት ማስተላለፍ የተለመደ ሆኗል።  ከላይ ባነሳናቸው ሐሳቦች ዙሪያ ትኩረት የሚያደርጉ ምእመናንን ፍጹም የማያንፁ፣ በዓለማዊ ቋንቋና ሐሳብ የተሞሉ ፍጹም ግለሰባዊ ስብከቶች ከየዐውደ ምሕረቱ ሲሰሙ ሃይ የሚላቸውና ስሕተት ነው ባይ የላቸውም።   በአበይት በዓላት፣ በሠርክ ጉባኤና፣ በቅዳሴ ሰዓት የሚሰጡ ስብከቶችን ለመስማት የሚታደሙ ምእመናንም እንዲህ ዓይነት ከዓላማው የተፋታ ስብከት ሲሰሙ ለምን አይሉም።  ነገሩን በውል ተረድተው ልክ አለመሆኑን ቢያውቁም በአብዛኛው ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አይተው እንዳላዩ ወይም በይሉኝታና በፍርሃት ተይዘው እግዚአብሔርንም እንደመዳፈር ቆጥረውት ዝም ይላሉ።  ግን እስከመቼ? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በመንግሥተ ሰማያት፣ በዘር ፣ በእርሾ እየመሰለ ማስተማሩን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።   ዛሬ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሊቃውንት በተቀመጡበት ዐውደ ምሕረት በእነርሱ ፊት ወጥቶ የሚሰብከው ሰባኪ ከምእመኑ ጋር የማይገናኝ የምእመኑን ዕድሜ፣ የትምህርትና የኑሮ  ደረጃዎች ፣ጾታንና የመሳሰሉትን ሁኔታዎች ያላገናዘበ ትምህርት ሲሰጥ ዝም ሊባል አይገባም።  ምእመኑም የእግዚአብሔር ቤት ነው ብሎ አክብሮ የሚነገረውን ሰምቶ መሄዱ እንደተማረ ተቆጥሮ መታለፍ የለበትም።  ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ስብከቶችን በክርስትናው ባልተለወጡ ምእመናን ሕይወት እያየነው ስለሆነ ነው።  በተከበረው የእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥቶ ከምእመናን ልብ የማይደርስ ስብከት ሲሰጥ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዝም ሊሉ አይገባም።  የጉባኤው ተካፋይ ምእመንም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች ሲያይ ዝም ከማለት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አለዚያም ወደ ስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ቀርቦ እንዲስተካከል ማድረግ ይጠበቅበታል።   አንዳንዱ ሰባኪ እንደ ተከበረው የእግዚአብሔር ቤት ዐደባባይ ሳይሆን እንደራሱ ቤት በሚቆጥረው መድረክ ላይ የመጽሐፍ ቅዱሱን ቃል ሳይሆን የራሱን ሐሳብ ብቻ ተናግሮ  ይወርዳል።  ምእመኑ ዘንድ ስለሚደርሰው የእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን እርሱ በዚያች ሰዓት ስለሚያስተላልፈው ሐሳብ ብቻ ተጨንቆና ተጠቦ በመምጣት ያንኑ አስተላልፎ ሲወርድ ልክ አይደለህም ሊባል ይገባል።  እንዲህ ዓይነቱ ሰባኪ ሲያጠፋ ስላልተነገረው ብቻ ራሱን ትክክል አድርጎ በየሄደበት ዐውደ ምሕረት ከምእመናን ሕይወት ያልተገናኘ ስብከት ሲሰብክ ይኖራል።  በተሳሳተበት ቀንና ቦታ ስላልተነገረውም ከመንገድ የወጣ ትምህርቱ ሥር እየሰደደ ይሄድና ለመመለስ ይቸግራል።  ‹‹ ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ አባቶች ገና ከመነሻው ያልተነገረ ጥፋት በአድራጊው ዘንድ እንደ ትክክል ይቆጠራልና ሰባኪውም ሆነ ምእመኑን ወደ ፍጹም ስሕተት  ሳይገቡ እርምት ሊሰጥ ይገባል።  የዐውደ ምሕረቱ አስተባባሪ ወይም ፕሮግራም መሪ ‹‹እከሌ የተባሉት መምህር አሁን ያስተምሩናል›› ብሎ ለወንጌል ትምህርት የተፈቀደለትን መድረክ ተጠቅሞ እግዚአብሔርን ሳይሆን ራሱን የሚያስተዋውቀውን፣ቃለ ወንጌልን ሳይሆን ይዞት የመጣውን መጽሐፍ ወይም ሲዲ አስተዋውቆና በረከት የሚገኘው ከመጽሐፉና ከሲዲው ነው በማለት የወንጌሉን ቃል ወደ ጎን ሲተው ሃይ ባይ የሚገሥፅ ያስፈልጋል።  ዐውደ ምሕረቱ ለቃለ ወንጌሉ ነው በማለት ከስሕተቱ እንዲታረም ማድረግ ካልተቻለ ‹‹ቤቴን የንግድ ቤት አደረጋችሁት . . . ›› እንዳለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐውደ ምሕረቱ ወደ ንግድ ማዕከልነት ሳይለወጥ በጊዜ መላ ሊበጅለት ይገባል።    ትናንት ያየውን ዜናና ዓለማዊ ፊልም ለስብከቱ ማዳመቂያ አድርጎ መድረክ ላይ የሚወጣውም ሰባኪ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለመገብየት የመጣውን ምእመን ስላየው ዜናና ፊልም ዳግም እየነገረ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ስለሚያዋርደው ሰባኪ አንድ ነገር ሊባል ይገባል።  በዐውደ ምሕረቱ ያልተለመደ ፌዝና ስላቅ እያስተላለፈ ምእመኑን ‹‹ይሄ ነው ትክክለኛው›› እንዲሉ መንገድ የሚጠርገውን ሰባኪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዐውደ ምሕረቷ ዘወር ልታደርገው ይገባታል።  የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ቢሆኑ እንዲህ ዓይነት ቀልድና ፌዝ ከቃሉ ጋር ተቀላቅለው ሲነገሩ፤ ዓለምን ከነኮተቷ ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ሊያስገቡ ሲሞክሩ ‹‹ይህ የአባቶቻችን ትምህርት አይደለም›› በማለት ለቤተ ክርስቲያናቸው ክብር ሊቆረቆሩ ይገባል።   ቃለ እግዚአብሔርን ለመስማት ፣ መንፈሳዊ ዕውቀቱን ለማሳደግ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ውስጥ ለተሰበሰበ ምእመን የተነሣበትን ርእሰ ጉዳይ ትቶ ከርእሱ ወጥቶ ወይም የሆነው ያልሆነውን ሲዘባርቅ የዕለቱንም በዓል አስመልክቶ አንድም ሳያስተምር የጉባኤውን ሰዓት የሚጨርስ ራሱን እንዲያስተካክል መንገር ከቤተ ክርስቲያን አባቶችም ሆነ ከምእመናን ይጠበቃል።  ጊዜውን ተጠቅሞ ለምእመኑ ማስተላለፍ ያለበትን መንፈሳዊ መልእክት ሳያስተልልፍ ፤ ምእመኑን መጀመሪያ ላይ የሰማው ርዕሰ ጉዳይ እስኪጠፋበት እና አንድም ፍሬ ነገር የማያገኝበትን እንቶ ፈንቶ ሲያወራ ቆይቶ ከመድረክ ላይ የሚወርደውን ሰባኪ ተብዬ ‹‹ ቃለ ሕይወት ያሰማልን›› ማለት ሳይሆን ከሕስተቱ ተምሮ እንዴት ማስተማር እንዳለበት አቅጣጫ መስጠት ተገቢ ነው።    ታላላቅ በዓላት በሚከበሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ላይ ምእመኑን ‹‹ ዕልል በሉ፤ አጨብጭቡ›› ከማለት ያለፈ ስለ ዕለቱ አንድም ነገር ሳይናገሩ ከመድረኩ ለሚወርዱ ሰባኪዎቻችን አስቀድሞ ርእስ እና አቅጣጫ መስጠት ተገቢም ነው።  የዕለቱን ክብረ በዓል ምንነት ለምእመናን ከማስተማር ይልቅ ገንዘብ ስለመለመን ብቻ አውርተው የሚወርዱ ሰባኪዎቻችን በምእመኑ አንደበት ሳይቀር ‹‹ ምን እነሱ ብር መለመን ብቻ ነው›› እስከመባል ደርሰዋልና ቤተ ክርስቲያን ይህን ልታስብበት ይገባል።    የቤተ ክርስቲያን አምባሳደር ሆነው በቆሙበት መድረክ ላይ የወንጌልን ቃል ሳይሆን ዘረኝነትን የሚዘሩ፤ ዘለዓለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ከማስተላለፍ ይልቅ ሰሞነኛ የፖለቲካ ትኩሳት ማቀንቀን የሚቀናቸው ሰባክያንን ‹‹ቦታው እዚህ አይደለም›› በማለት ወደ ትክክለኛው መሥመር እንዲገቡ ማድረግ ከቤተ ክርስቲያን ልጆች ይጠበቃል።  ሞልቶ ከተረፈው የእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ከዓለም በቃረሙት ቃላትና ምሳሌ ወደ ዐውደ ምሕረት አምጥተው ምእመናንን የሚያደነቁሩ ሰባክያን ልክ አይደለም ሊባሉ ይገባል።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአለባበስ ሥርዓት በመጣስ ያልተፈቀደላቸውንና የማይገባቸውን የቤተ ክርስቲያን ልብስ በመልበስ ወደ መድረክ ብቅ የሚሉ ሰባኪዎቻችንን ቤተ ክርስቲያን ችላ ልትላቸው አይገባም።   ዐውደ ምሕረቱን ተጠቅመው የእግዚአብሔርን ቃል የሚሸቃቅጡትን፤ ‹‹ በነፃ የተሰጣችሁን በነፃ ስጡ ›› የሚለውን ቃል ዘንግተው ኪሳቸውን ለመሙላት ብቻ የምእመኑን ኪስ የሚያራግፉትን (ዋጋ ተምነው ይህን ያህል ሊከፈለኝ ይገባል በማለት በድርድር ዐውደ ምሕረት ላይ የሚቆሙ) ሰባክያን ቤተ ክርስቲያን ለይታ ልታወጣቸው ይገባል።  በዚያው ልክ ለቤተ ክርስቲያን ክብር የቆሙ ጨዋ የወንጌል ሰባክያንን (ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ደሃ አይደለችምና) ወደ መድረክ ልታመጣ ፣ ልትጋብዝ፣ እንዲያስተምሩ ልታደርግም ይገባል።  ባጠቃላይ ምእመኑ ጥሎት የመጣውን ዓለም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ በድፍረት የሚያስተዋውቁ የወንጌል ነጋዴዎች ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ምእመኑን እየጎዱ ነውና ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቷን  በትኩረት ልታየው ይገባል።
Tuesday, 23 February 2021 00:00
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ፈተና ያልተለያት እንደሆነች በዘመናት ውስጥ ከተጻፉ የታሪክ ድርሳናት  መረዳት ይቻላል። ቤተ ክርስቲያን በፀረ ክርስቲያን ኃይሎች መፈተኗ አላጠፋትም፤ ምእመናንንም ከአምልኮተ እግዚአብሔር አላራቃቸውም።   ይልቁንም ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እያሰፋች ለዓለም ብርሃን መሆኗን ቀጥላለች።    ከዘመናዊ ትምህርት ዘርፉ ከሚገኝ ዕውቀት በበለጠ የቋንቋ፣ የሥነ ጥበብ፣ የኪነ ሕንፃና የፍልስፍና ምንጭ ሆና መቀጠሏ ዓለም ያወቀው ገሃድ ነው።  ይሁን እንጂ ኃያልነቷንና ታሪካዊነቷን የተረዱና ያልተረዱ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን ከሚያልሙ ፀረ ክርስቲያን ኃይሎች መገኛ ሀገራት መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ናት።    
Saturday, 27 February 2021 00:00
በዓለም ላይ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት አብዛኞቹ  ምእመኖቻቸው ዐቢይ ጾምን እንዲጾሙ ያዛሉ። በተለይ የምሥራቅና የኦሪየንታል ኦርቶዶክሶች በጉጉት ከሚጠብቋቸው ጊዜያት አንዱ ይህ ወቅት ነው። የሶሪያ አብያተ ክርስቲያናት ይህን ታላቁን ጾም ‹‹Sawma Rabba›› ይሉታል - ጾመ ረቢ - ጾመ ኢየሱስ እንደ ማለት ነው። ጾሙን የሚቀበሉት ከበዓለ ትንሣኤው ከአምሳ ቀናት በፊት ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዐቢይ ጾም ሥርዓት ሳምንታቱ የየራሳቸው ስያሜ እንዳላቸው ኹሉ በሶሪያውያንና በሌሎችም የምሥራቅና የኦሪየንታል ኦርቶዶክሶች ዘንድ ስያሜያቸው የሚታወቁ ዕለታት አሉ። ከእነዚህም አንዱ ‹‹ንጹሕ ሰኞ›› (Clean Monday) ነው። ‹‹ንጹሕ ሰኞ›› የሚሉት ዐቢይ ጾምን የሚጀምሩበት ዕለተ  ሰኞን ነው። እንደሚታወቀው የጾሙ የመጀመሪያ ዕለት ሰኞ ሲሆን፡ ጾም ከብዙ ኃጢአት የምንታቀብበት፣ በንስሐ ሳሙና  የምንታጠብበትና የንጽሕና ምግባራትን የምንፈጽምበት በመሆኑ፡ ይህን ያመለክት ዘንድ የመጀመሪያውን የጾሙን መግቢያ ዕለት ንጹሕ ሰኞ ብለውታል። በሶሪያ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት የዐቢይ ጾምን ስድስተኛ ዓርብ ‹‹የአልዓዛር ዓርብ›› ይሏታል። ሰባተኛዋን ሰንበት ደግሞ ‹‹ሰንበተ ኦሻና›› (የሆሣዕና ሰንበት) ብለው ይጠሯታል። ምሴተ ሐሙስ፣ የስቅለቱ ዓርብና ቀዳም ስዑርም ከበዓለ ትንሣኤ በፊት የሚታሰቡ ዕለታት ናቸው። (የተጠቀምናቸው ምንጮች ሌሎቹ ዓርቦችና ሰንበታት ስያሜ ይኑራቸው፣ አይኑራቸው አይገልጹም)። አንዳንዶች የምዕራባውያኑ አጠራር ተጽዕኖ አድርጎባቸው ‹‹ንጹሕ ሰኞ››ን፡ ‹‹የአመድ ሰኞ›› (Ash Monday) ብለው ይጠሩታል።
Saturday, 27 February 2021 00:00
“አብዬ…”  “አንተ…” ትለኛለች። አያቴ ናት። የቤቱ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብየ ከራሴ ጋር ብይ እየተጫወትኩ ነበር። ቅዳሜ ከቀኑ አሥር ሰዓት ገደማ ይሆናል። ከቤት ውስጥ መስኮቱ ባለበት ግድግዳ በኩል የተሠራ መደብ ላይ ተኝታ ነው ምትጠራኝ። የመጀመሪያውን ጥሪዋንም ሰምቸዋለሁ… ለምን እንደሆነ አላውቅም ብዙ ጊዜ በሁለተኛው ጥሪ ነው መልስ የምሰጠው። የጠራኝ ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ተጣርቶ ካቆመ በቃ እኔም እየሰማሁት  ሳልመልስ እሱም ሳይደግም እንለያያለን። ለዚህ ነው አያቴ ስትጠራኝ መጀመሪያ ስሜን አቆላምጣ ትጠራኝና እንደሰማሁ ስለገባት በሁለተኛው “አንተ..” ትለኛለች። ለምን እንደዚህ እንደማደርግ ለኔም አይገባኝም።  “ኧ ኧ ኧ…” የተለመደ መልሴ ነው። አቤት የምለው ለማላውቀው ሰው ነው። ለምን?  እንደሆነ እኔ እንጃ! “ነገ ጠዋት በተስኪያን ህደህ የቅዳሴ ጸበል እንድታመጣልኝ እኔ አሞኛል እግሬ እሽ አይለኝም።” አለች። “እሽ።” አልኩ። ቀዝቀዝ አድርጌ ህጄ ብይ ማንከባለሉን ሳላቆም። 
Saturday, 27 February 2021 00:00
የሰው ልጅ ፍላጎቱ ገደብ የሌለው፣ አንዱ ሲሟላለት ሌላ የሚያስብ፣ በወቅቱ ያሰበው ሲከናወንለት ደግሞ ሌላ የሚፈልግ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ አሳቢ አእምሮ ተሰጥቶት ስለተፈጠረ እንደሆነ ይታወቃል። ምን አልባትም እንደ አደገበት ሁኔታ፣ እንደተማረው የትምህርት ዓይነት፣ እንደኑሮ ዘይቤው የሚያስበው ነገር ሊለያይ ይችላል እንጂ የማያስብ ሰው ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ይሁንም እንጂ ስላሰበ ያሰበው ሁሉ አይሟላለትም፣ የጀመረውን ሁሉ አይፈጽምም፤ የተመኘውን ሁሉ አያገኝም። ምክንያቱም ፍላጎቱ ገደብ የለሽ ሆኖ የተፈጠረው የሰው ልጅ ፍላጎቱን ለማከናወን ያለው ዐቅም ውሱን ስለ ሆነ ነው። ይህም ሆኖ ለመኖር መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች መሟላት አለባቸው። ከእነዚህ መካከል ፍቅር፣ የእርስ በእርስ መተሳሰብ፣ የተቸገሩትን መርዳት ተጠቃሾች ናቸው። ስለዚህ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ከወንድሞቻችሁ ጋር በፍቅር ኑሩ” በማለት የተናገረው ለሰው ልጅ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ስለሆነ ነው።  በመሠረቱ ወንድምነት በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። ከሥነ ፍጥረት አንጻር ከተመለከትነው  ምንም እንኳን ብዙዎቻችን በዚህ መልኩ ባንረዳውም ሁሉም የአዳምና የሔዋን ልጅ ስለሆነ ሁላችንም ወንድማማቾች ነን። ከምናመልከው አምላክና ከምንከተለው ክርስትና አንጻር ስንመለከተው ደግሞ በክርስቶስ ስም ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በአርባና በሰማንያ ቀን ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ሲቀበል የቤተ ክርስተያን አባል የክርስቶስ አካል ሲሆን ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ተወልዶ ሁሉም የሥላሴ ልጅ ይሆናል። ስለዚህ በዚም በኩል ሁላችንም ወንድማማቾች ነን። ይህን በአግባቡ መረዳት ባንችልም እንኳ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ኑሮ የሚያስፈልገውና ብቻውን ምሉእ እንዳልሆነ ሊገነዘበው ይገባል።

ማስታወቂያ