Wednesday, 28 April 2021 00:00

‹‹መመሪያውን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ማኅበሩና መዋቅሩ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ›› - (አቶ ውብሸት ኦቶሮ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ) ክፍል አንድ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ የአንድ ወር ያህል ጊዜ ብቻ ቀርቶታል። ምርጫ ቦርድም የጊዜ ሰሌዳ ነድፎ በቅደም ተከተል የሚካሄዱ ፕሮግራሞችን እያካሄደ ይገኛል። በአንደ ጎኑ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየው ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የእርስ በርስ ግጭትን በሌላ በኩል የምርጫ ፕሮግራምን ተሸክማ ወደፊት ለመራመድ እየሞከረች ያለችበት ሰዓት ላይ ነው ያለነው።  ከአጠቃላይ ሕዝቧ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመን በመሆነባት ሀገራችን እንደ አንድ ባለመብት ዜጋም ሆነ ከነገው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን  ጥቅም አንፃር ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚወክላትና በፓላማ ስለሚወሰነው ጉዳይዋ  ድምጽ የሚሆናት ተመራጭ ሊኖራት ይገባል። ይህንንም በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በየካቲት ፳፻፲፫ ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ ጸድቆ የወጣውን መመሪያና በመመሪያው ስለተካተተው የአባላት የፖለቲካ ተሳትፎ፣ መብትና ግዴታዎች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ  አቶ ውብሸት ኦቶሮ  ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሊቪቭን ጋር ባደረጉት ቆይታ በምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለአባላት፣ እንዲሁም በቅርብ ማኅበሩን ለሚከታተሉ የተለያዩ አካላት በቅርቡ ሰፊ ማብራሪያ  ሰጥተዋል። ማብራሪያው ሙሉ ሐሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል።

 

 በየካቲት ፳፻፲፫ ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ ጸድቆ የወጣውን መመሪያና በመመሪያው ስለተካተተው የአባላት የፖለቲካ ተሳትፎን አስመልክቶ የተሰጠው መስጠት ያስፈለገው በአባላቱ እንዲሁም በውጭ ማኅበሩን በቅርብ በሚያውቁ ሰዎች ዘንድ ብዥታ ስላለ እርሱን ለማጥራት ነው።

በተለይም አባላት በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው ተሳፎ እና አቋም የተለያየ ቢሆንም  ማኅበሩ ግን በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ እንደተቀመጠው በማንኛውም የፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ የትኛውንም ፓርቲ ሆነ ርዕዮተ ዓለም በተለየ መልኩ አይደግፍም፤ እንዲሁም አይቃወምም፤ አባላቱን በተመለከተ ግን እንደ አንድ ዜጋ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን፣ የመደገፍ፣ አቋም የመያዝ፣ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብቶች ያላቸው ሲሆን ይህንኑ ፍላጎታቸውን ተግባራዊ በሚያደርጉበት ጊዜ ግን የያዙትን ፖቲካዊ አቋም የማኅበሩ አቋም አድገው መውሰድ ተገቢ አይደለም። በሌላም በኩል ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አይሳተፍም ሲባል የማኅበሩ አባል በምንም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አይሳተፍም እንዲሁም ጣልቃ መግባት የለበትም የሚል አመለካከት በአንዳንዶች ዘንድ ስላለ እንዲህ ዓይነቱን ብዥታ ለማጥራት ነው በሰነድ ማስቀመጥ እና ማብራራት ያስፈለገው።

በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም የወጣው መመሪያ ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጣልቃ አይገባም። ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር  የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለመደገፍ የተሰባሰቡ አባላት የመሠረቱት ነው። ማኅበሩ መንፈሳዊ ማኅበር እንደመሆኑ መጠን እንደተቋም ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ውጪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሠሩትን ሥራ በአጠቃላይ አይሠራም፤ በማኅበሩ መመሪያ ላይ የተቀመጠው አንቀጽም ቢሆን ይህንኑ ሐሳብ ለማጽናት የተቀመጠ አንቀጽ ነው። 

ማኅበሩ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም፤ አይሠራም ሲባል ግን በሌላ መልኩ የሚሠራቸው ሥራዎች የሉትም ማለት አይደለም። ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ይቃወማል፤ አቋም ይይዛል፤ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና አቋም እንዲኖራቸውም ይሠራል።  በእርግጥ በመመሪያው አንቀጽ ሁለት ላይ ‹ማኅበሩ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ አይገባም› ማለት ብዙዎች እንደሚያስቡት ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፋ የመጣውን የፖለቲካ ፓርቲ አይቃወምም ማለት አይደለም። መመሪያው ይህንን በግልጽ አስቀምጦታል። የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን፣ ህልውናዋን፣ መብቷንና ጥቅሟን የሚጋፋ የፖለቲካ አቋም ላይ ማኅበሩ መንፈሳዊ ማኅበር እንደመሆኑ መጠን ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ግዴታ ስላለበት አቋም ይዞ ይሞግታል። 

ከዚህም በተጨማሪ ማኅበሩ  ኦርቶዶክሳውያን ለሀገር የሚጠቅም የቤተ ክርስቲያንን  መብት የሚያስጠብቅ ፍትሕ ርትዕን የሚያሰፍን አካል በመምረጥ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይመክራል።  ትላንት ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን በማሰብ ዛሬ ላይ ለምን ብሎ የሚናገርላትን፣ አቋም ይዞ የሚሞግትላትን እንዲሁም ጉዳት ሲደርስባት የሚቃወምላትን አካል አስበው እና ዓላማ አድርገው ይመርጡ ዘንድ ሕገ እግዚአብሔርን በጠበቀ መልኩ በንቃት እንዲሳተፉም ያስተምራል።

ምእመናን በሀገሪቱ ላይ ፍትሕ ርትዕን የሚያሰፍን የፖለቲካ ፓርቲን እንዲመርጡ እና አቋም እንዲይዙ ማኅበሩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን ይሠራል። ይህም ሲባል  የትኛውንም የእምነት ተከታይ ለማለት ነው እንጂ ማኅበሩ በተለየ ኦርቶዶክስ ሀገር ይምራ የሚል አቋም የለውም። የየትኛውም ሃየማኖት ተከታይ ይሁን አለዚያም ሃይማኖት የሌለው ነገር ግን ሀገርን የሚጠቅም እና ሁሉን በእኩል አይቶ የሚያስተዳድር አካልን ምእመኑ እንዲመርጥ ነው ማኅበሩ የሚያበረታታው። የትኛውም አካል ሀገርን ለመምራት ሥልጣን ላይ ቢወጣ ማኅበሩ ምንም ዓነት ቅራኔ የለውም። ሀገርን እንደ ሀገር በእኩልነት፣ ለሕዝብ ሰላምን በማምጣት ይምራ እንጂ ማኅበሩ ከዚህ የተለየ አቋምም ሆነ እምነት የለውም።     

በመመሪያው አንቀጽ ፫.፫ ላይ እንደተቀመጠው ማኅበሩ ለየትኛውም ርዕዮተ ዓለም፣ ፓርቲ፣ ዕጩና ተመራጭ ይሁንታ አይሠጥም ይላል በሌላው አንቀጽ ፪.፭ ላይ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ልሂቃን እንደ አስፈላጊነቱ የቤተ ክርስቲያንንና የምእመናንን መብት ማስጠበቅን በተመለከተ ያላቸውን አቋም እንዲያሳውቁ፣ እንዲሞግቱ እና እንዲያሟግቱ እንዲጠየቁ ሊያደርግ ይችላል የሚሉት ሁለት ሐሳቦች የሚጋጩ አይደሉም ምክንያቱም የአንቀጹ ትርጓሜ ማኅበሩ እንደ ተቋም የማይፈጽማቸው ጉዳዮች ብሎ በመመሪያው ከጠቀሰው ውስጥ ለየትኛውም ርዕዮተ ዓለም፣የፖለቲካ ፓርቲ፣ ዕጩና ተመራጭ ይሁንታን አይሠጥም የሚል ነው። ይሁንታ ማለት ይኸኛው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ያኛው ዕጩ እኛን ይወክለናል፣ ለኦርቶዶክስ የሚበጀው ይሄ ነው ብሎ ዕውቅና አይሰጥም ማለት ነው።  የማኅበሩ ገለልተኝነት አጽንኦት የተሰጠው እና የተሠመረበት ዐቢይ ጉዳይ ነው ሲባልም የማኅበሩ መዋቅር፣ መልካም ስም፣ ሀብት፣ንብረት  ለማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ሥራ እንዳይውል ይከለክላል ማለት ነው። እነዚህም መመሪያዎች ማኅበሩን ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ አድርገው የሚያስጠብቁ ሚዛኖች ናቸው።

ማኅበሩ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲ እና የፖለቲካ ልሂቃን እንደ አስፈላጊነቱ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናንን መብትና ጥቅም በተመለከተ ያላቸውን አቋም እንዲያሳውቁ ያደርጋል ማለት ዕውቅና መስጠት አይደለም። ይልቁንም የፖለቲካ ልሂቃኑም ሆኑ መንግሥት ሐሳባቸውን የሚያሳውቁበት መንገድ ማመቻቸት ነው። ሕዝብ ሐሳባቸውን ሰምቶ የመምረጥ ዕድል እንዲያገኝ ግንዛቤ ከመስጠት አንፃር የማመቻቸት እንጂ እዚህ ስለቀረበ ማኅበሩ ዕውቅና ሠጥቶአል ማለት አይደለም። ማኅበሩ ለማንኛውም አካል ዕውቅና በክልከላ ከሚያስቀምጣቸው መካከልም ሊሰመርበት የሚገባው አንዱ ጉዳይ ይህ ነው። 

ባጠቃላይ የማኅበሩ ድርሻ ሰዎች የእያንዳንዱን አቋም እንዲያውቁ ማድረግ ነው። ከመንግሥት ፣ከምርጫ ቦርድ፣ ከሲቪክ ማኅበራት እና ከመገናኛ ብዙኃን የሚጠበቀውም ተመራጮች አቋማቸውን የሚያሳውቁበት መድረክ ማመቻቸት ነው። በአንቀጽ ፪.፭ ላይ የተቀመጠው  ይህንን ነው ዕድል መፍጠር የሚለውም ሁሉም እኩል ታውቆ ሰው የቱ ይጠቅመኛል? ለሀገር የሚጠቅመው የቱ? ነው ብሎ ሚዛን ላይ እንዲያስቀምጥ ዕድል ይሰጣል የሚል ነው። ስለሆነም እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ አንድ ተቋምም ይህንን ድርሻ እንወጣለን ማለት ነው እንጂ ይሁንታ እና ዕውቅና ከመስጠት ጋር የተገናኘ አይደለም። 

ሌላው በመመሪያው ላይ ከተቀመጡት አንቀጾች መካከል በማኅበሩ በአመራርነት እና በአባልነት ደረጃ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ መሳተፍ የሚችሉና የማይችሉ ተብሎ በተቀመጠው አንቀጽ ላይ ማኅበሩ በፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሲል አንቀጽ ፫.፪ ላይ እንደተጠቀሰው የማኅበሩ መዋቅር፣ መልካም ስም፣ ሀብት እና ንብረት ለማንኛውም የፖለቲካ ሥራ እንዲውል አይፈቅድም ማለት ነው። ይህንን የሚያስፈጽሙ አካላት እነማን ናቸው? ብሎ ነው በዋናነት ያሰመረበት። ማንኛውም አካል ወይም ዜጋ በፖለቲካ ጉዳይ የመሳተፍ መብት ቢኖረውም ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ሲባል ግን ተለይተው ይህንን መብት የተከለከሉ አካላት አሉ። 

እነዚህም ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚመራው የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ያሉ ማዕከላትን በሰብሳቢነት፣ በምክትል ሰብሳቢነትና በጸሓፊነት የሚመሩ አካላት፣ በጽ/ቤት ደረጃ ያሉ በየሀገረ ስብከቱ ባለው መዋቅር እንደ ማዕከል የሚመሩ በሀገር ውስጥ እና በሀገር ውጪ ያሉ ማዕከላት፣ ወረዳ ማዕከላት፣ ግቢ ጉባኤያት፣ ኤዲቶርያል ቦርድ፣ ኦዲትና ኢንስፔክሽን፣ የማኅበሩ ሚዲያዎች እና መምህራን ናቸው። ክልከላው በዐደባባይ የፖለቲካ አቁዋማቸውን እንዳያራምዱ፣ ምልክቶችን እንዳይዙ እንዲሁም የፖለቲካ አቋምን እንዳያስተጋቡ የሚሉ ጉዳዮችንም   በዝርዝር ያስቀምጣል። ይህን በተመለከተ አባላቱ ታች እስካለው መዋቅር ድረስ ደብዳቤም ደርሶአቸዋል። ከላይ በዝርዝር ከተቀመጡት አካላት ውጪ ያሉ የማኅበሩ አባላት ግን በማንኛውም እነሱ በፈለጉት እና በመረጡት የፖለቲካ ፓርቲ የመሳተፍ፣ የመደገፍ የመምረጥ፣ የመመረጥ መብት አላቸው። 

ከዚህ ቀደም በማኅበሩ በአመራርነት ላይ የነበሩ ከአመራርነት ከለቀቁ በኋላ የተለያየ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሲገቡ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር አይይዞ ማየት እንዲሁም የማኅበሩ አቋም ነው በሚሉ ብዥታዎች ዙሪያ ማኅበሩ መልስ ሳይሰጥ ቆይቷል አሁን ግን በመመሪያው ተካቷል። ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ አባላት በፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በአባልነት አይገቡም ሲባል መቼ? የሚለውን ብዙ ሰዎች አይረዱትም። አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ሲያገለግል የነበረና አባል ዕድሜ ልኩን ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለ ይመስላቸዋል። በፊትም አሁንም ያለው መመሪያ የሚለው በማኅበረ ቅዱሳን በየትኛውም መዋቅር ላይ ያሉ የተከለከሉ አባላት የሚከለከሉት ከላይ በተጠቀሱት የአገልግሎት መደብ ላይ በሚያገለግሉበት ጊዜ ውስጥ ነው። ከዚህ ወጥተው በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ወደ ማኅበሩ ተመልስው መጥተው በተከለከለው መደብ ላይ ማገልገል ቢፈልጉ በመጀመሪያ ከፖለቲካ አባልነት ወጥተው ራሳቸውን ከአባልነት አግልለውና ነፃ አድርገው  መምጣት ይኖርባቸዋል። ይህንን ብዥታም ለአባላቱ ግልጽ ተደርጓል።

 

Read 486 times