Saturday, 15 May 2021 00:00

የዴር ሡልጣን ገዳም የነገ ዕጣ ፈንታ

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ከ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በገዳምነት ይጠቀሙበትና ይኖሩበት  እንደነበረ የሚጠቀስለት የዴር ሡልጣን ገዳም በተለያየ ጊዜ በተለያዩ አካላት የባለቤትነት ጥያቄ ሲነሣበት መቆየቱ ይታወቃል። በተለይ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት እና  በተለያየ መንገድ አዲስ ታሪክ በመፍጠር ገዳሙን ለመንጠቅ ሙከራ ስታደርግ መቆየትዋን ጭምር ማኅበረ ቅዱሳን በ፳፻፲፩ ዓ.ም ባሳተመው ‹‹ስምዐ ተዋሕዶ›› ልዩ ዕትም መጽሐየት ስለ ዴር ሡልጣን የተለያዩ ሊቃውንትንና የታሪክ ድርሳናትን ዋቢ በማድረግ ጽፎት እናገኛለን።  በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ጌታ በተወለደበት፣ በአደገበት፣ በአስተማረበት፣ በተሰቀለበት፣ በተቀበረበት እንዲሁም በተነሣበት በጎልጎታ ተራራ የተመሠረተው የዴር ሡልጣን ገዳም በኢትዮጵያውያን ነገሥታት፣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ባለሀብቶች እና መነኰሳት እንደተሠራ የታሪክ መዛግብት የሚናገሩ ሲሆን  እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ገዳሙን እና በገዳሙ የሚኖሩ ኢትዮጵያን መነኰሳት ሲረዱ መኖራቸው ይታወቃል። ገዳሙ ከንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ርስት ሆኖ መቆየቱ ሲገለገሉበት መቆየታቸው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ‹‹ዜና ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም›› በሚለው መጽሐፋቸው ተገልጾ እናገኛለን። በዘመን ብዛት እና በተለያዩ ሁኔታዎች ግብፅን የመሳሰሉ ‹‹የእኔ ነው›› ባዮችን አፍርቶ እስከ ዛሬ ድረስ መፍትሔ ያልተበጀለት የውዝግብ ምክንያት ሲሆን መቆየቱን ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ‹‹ ኢየሩሳሌምን እወቁ›› በሚለው ሌላኛው መጽሐፋቸው ላይ ጽፈውት እናገኛለን።  ገዳሙ የውዝግብ መነሻ ከመሆኑም ባሻገር ከዘመን ብዛት የተነሣ በማርጀቱ በመፈራረስ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተጨማሪም ለዘመናት በውስጡ የሚኖሩ የበላይ ጠባቂ አባቶች ካህናትና መነኰሳት የሚገባቸው እንክብካቤ እየተደረገላቸው አለመሆኑ . . . ወዘተ ለገዳሙ የዘመናት ተድዳሮት ሆነው ቆይተዋል። እነዚህንና የመሳሰሉ ችግሮችን እያስተናገደች ያለችው የገዳሙ ባለቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳሙን ማደስ እንኳን በማትችልበት መልኩ  መብቷን ተነፍጋ ቆይታለች።  በመሠረቱ የዴር ሡልጣን ገዳም ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርስ እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስም ጭምር ነው። ኢትዮጵያ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዚህ ታላቅ ቅርስ ባለቤት መሆናቸው በዓለም ላይ ታላቅ ክብር የሚያሠጣቸው ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት፣ በተቀበረበት እና በተነሣበት ታሪካዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ ኢትዮጵያውያን አስበው እና አስቀድመው ገዳም መመሥረታቸው በዚያ ዘመን የበረውን የኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሥልጣኔ፣ ብልህነት እና አርቆ አስተዋይነት የሚገለጽበት ቋሚ ምስክር ጭምርም ነው የዴር ሡልጣን ገዳም።  ሆኖም እንደ ታሪካዊ አመጣጡ፣ እንደ ባለቤትነታችን ለዴር ሡልጣን ገዳም እየሰጠነው ያለው ትኩረት በጣም አናሳ ነው። ግብፃውያኑ ያልነበሩበትን ያልኖሩበትን ይህን የተቀደሰ ቦታ ቀምቶ ለመውሰድ ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ተራው ሕዝብ ድረስ ዓላማ አድርገው ሲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እንደሚገባው ይዞታውን ለማስከበር ብዙ ርቀት ሲሄዱ አልታዩም። ባለቤት ሆነው የማያውቁ፣ በታሪክ ያልነበሩ በጉልበት የራሳቸው ለማድረግ አዲስ ታሪክ ለመፍጠር ሲሯሯጡ ኢትዮጵያውያን ዝም ብለው መመልከት የለባቸውም። ይልቁንም ስለ ዴር ሡልጣን የሚናገሩትን የታሪክ ድርሳናት ወደ ፊት በማምጣት የገዳሙ ባለቤት መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።  ከጥቁር ሕዝቦች መካከል ተለይታ በሀገረ በእስራኤል በተቀደሰችው ከተማ በኢየሩሳሌም የገዳማት ይዞታዎች ያሏት ኢትዮጵያ መሪዎቿ እንደ ሀገር ከፊት ቀድመው ይዞታዋን በማስከበር ረገድ ከአቻቸው የእስራኤል መንግሥት  ጋር በመነጋገር ዘመናት ለቆየው ችግር እልባት ሊሰጡት ይገባል። ምክንያቱም ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የሀገርም ቅርስ ነውና መንግሥት እንደ መንግሥት ሊያስብበት ይገባል።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበላይ አካላት የሆኑት ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስለ ዴር ሡልጣን የተጻፉ የታሪክ መዛግብትን አደራጅተው በማቅረብ የገዳሙን ታሪካዊ ባለቤትነት ማረጋገጥ ከእነርሱ ይጠበቃል። ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም የሚያትቱ በርካታ የታሪክ ድርሳናት ከኢትዮጵያውያን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽፈዋልና እነዚያን ታሪካዊ ድርሳናት በማስረጃነት በማቅረብ እስከ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ድረስ በመሞገት የባለቤትነት መብትን ማስከበር ተገቢ ነው።  በገዳሙ የሚኖሩ መነኮሳት እና በየጊዜው ለገዳሙ የሚመደቡ የበላይ አባቶች በሚነሣው ውዝግብ ውስጥ የገዳሙን ባለቤትነት ለማረጋገጥ ብዙ መንገድ መሄዳቸው ቢታወቅም ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከቤተ ክህነቱ የሚሰጧቸው ድጋፎች አናሳ በመሆናቸው ችግሩ ዘላቂ እልባት ማግኘት አልቻለም። በመሆኑም መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኅብረት የዴር ሡልጣንን የባለቤትነት መብት ከዳር ሊያደርሱት ይገባል።  በአሁኑ ሰዓት በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለ ሙሉ ሥልጣን ክቡር አምባሳደር ረታ ዓለሙ የገዳሙ የበላይ አባቶችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያሉትን ጥረት ከማመስገን ባሻገር ከጎን በመሆን ጭምር መንግሥት እንደ መንግሥት ከአቻው የእስራኤል መንግሥት ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአቻ አኃት አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ከግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ውይይት በማድረግ ለዘመናት የዘለቀውን ችግር ለዘመናት መፍታት ይጠበቅባቸዋል።  ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለመሳለም በየጊዜው የሚሄዱ በሀገር ውስጥ ያሉም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በበኩላቸው  በግብፃውያን ለመነጠቅ ጫፍ ላይ የደረሰውን የዴር ሡልጣን ገዳም ጉዳይ እልባት ያገኝ ዘንድ ድምጻቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሰማት ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ከቤተ ክህነት የበላይ አባቶች ጋር በመነጋገር ከገዳሙ ጋር ተጣብቀው በየጊዜው ከግብፃያን የሚደርስባቸውን ትንኮሳና ጫና ተቋቁመው ያሉ በኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን ገዳም አባቶችን በሞራልም ሆነ በገንዘብ መደገፍ ተገቢ ነው። የዓለም ማዕከላዊ ቦታ በሆነቸው በኢየሩሳሌም የሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም የኢትዮጵያውያን ቅርስ ነውና ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ቅርስነት ተመልክተው ከቤተ ክርስቲያን ጎን ሊቆሙ ይገባል።  በተለይ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በግልና በኅብረት በመሆን የገዳማችን ባለቤትነት ይረጋገጥ ዘንድ  በቤተ ክህነቱም ሆነ በመንግሥት ላይ ጫና ሊያደርጉ ይገባል። በየጊዜው የሚነሣው የግብፃውያን ትንኮሳ እና ‹‹የእኔ ነው›› ባይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቆም ዘንድ ያዝ ለቀቅ በሆነ መልኩ ሳይሆን በሀገር ውስጥም ሆነ በተለያየ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም፣ የሕግ ሰዎችን በአማካሪነት በመያዝ እና ታሪካዊ ሰነዶችን በመረጃነት በማቅረብ የዴር ሡልጣንን የባለቤትነት ጥያቄ ለዘለቄታው ካልተመለሰ የነገ ዕጣ ፈንታው እጅግ አሳሳቢ ይሆናል።  
Read 569 times