Saturday, 26 June 2021 00:00

ማኅበረ ቅዱሳን ለገቢ ማስገኛ እንዲውል የገዛውን የጋራ መኖሪያ ቤት ለገዳሙ ማስረከቡን አስታወቀ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

ማኅበረ ቅዱሳን ለገቢ ማስገኛ እንዲውል የገዛውን የጋራ መኖሪያ ቤት ለዋልድባ ዳልሻ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ ደናግል የእናቶች እንድነት ገዳም ተወካይ ካርታውን ማስረከቡን የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርትቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ ዲ/ን አንድነት ተፈራ አስታወቁ።    የጋራ መኖሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ችሎት በተባለው አካባቢ እንደተገዛ የገለጡት ም/ኃላፊው አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሥልሳ ሥድስት ሽህ ሥድስት መቶ ሰማንያ ሥድስት ብር ወጪ እንደተደረገበት ተናግረዋል። የጋራ መኖሪያ ቤቱ በገዳሙ የሚኖሩ እናቶች አቅመ ደካሞች በመሆናቸው ሠርተው መኖር ባለመቻላቸው ዘላቂ የሆነ የገቢ ማስገኛ እንዲሆናቸው ታስቦ የተገዛ ነው። ከአሜሪካ ሀገር ዳላስና ሀገር ውስጥ ከሚኖሩ ምእመናን በተሰበሰበ ገንዘብ ማኅበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቱን መግዛቱንም ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል።    በተጨማሪም ገዳሙ የተገዛለትን የጋራ ምኖሪያ ቤት አስፋፍቶ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሊሆን በሚችል መንገድ መሥራት እንዳለበት የጠቆሙት ም/ኃላፊው ማኅበሩም ለገዳሙ አስፍላጊውን  ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። የጋራ መኖሪያቤቱ ሲገዛ ከፍተኛ እገዛ ያደረጉ ምእመናንም ለወደፊቱም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።    አያይዘውም ገዳሙ ያሉበትን የውኃና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ማኅበሩ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርግ ጠቅሰው የጋራ መኖሪያ ቤት ግዥው እውን እንዲሆን እገዛ ያደረጉትን የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስንና የወረዳ ማእከል አባላቱን አመስግነዋል።    የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሤ መብራቱ በበኩላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቱ እንዲገዛ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ድጋፍ ላደረጉ ምእመናን ምስጋናቸውን አቅርበው ገዳሙ የበለጠ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የተለመደ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።     የጋራ መኖሪያ ቤቱን ካርታ የተረከቡት የገዳሙ ተወካይ እማሆይ አስካለ ማርያም ማኅበሩ ላደረገላቸው ድጋፋ አመስግነው ለወደፊቱም የማኅበሩም ሆነ የምእመናን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዳይለያቸው አሳስበዋል።  
Read 516 times