Monday, 28 June 2021 00:00

“በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያሉ ጥንታዊ ገዳሞቻችን አስቸኳይ ጥበቃና ክብካቤ ይፈልጋሉ! ክፍል አንድ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ውስጥ ካሏት ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት በተጨማሪ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ከስድስት በላይ ገዳማት ያሏት ሲሆን ይህም በኢየሩሳሌም የራሳቸው የገዳም ይዞታ ካሏቸው ጥቂት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ያደርጋታል። በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የግሪክ፣የአርመን፣የኢትዮጵያ እንዲሁም የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው የገዳም ይዞታ አሏቸው። ይሁን እንጂ በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ሥር ያሉ ገዳማዊ ይዞታዎች ከአወዛጋቢነታቸው በተጨማሪ በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል የቁርሾና የብጥብጥ መነሻ ሲሆኑ ይስተዋላል። ይህ የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ለዓለም ሕዝብ የታሪክ ማእከል ነው። ክርስቲያኑም እስላሙም፣ ካቶሊኩም፣ ፕሮቴስታንቱም በኢየሩሳሌም ይዞታ እንዲኖረው ይፈልጋል። ይህ የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም። ዓለምን የለወጠ፣ ጨለማን ያሰወገደ፣ ለዘለዓለማዊ ሕይወት መሠረት የሆነ ተአምር ተፈጽሞበታልና ነው። ብዙዎቹ በእምነቱ ባይገኙም ቦታውን መያዝን እንደ ትልቅ ጀብድ ቈጥረውትና የጽድቅ ማረጋገጫ አድርገውት ይታያሉ። በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያሉ ጥንታዊ ገዳማት የብዙ አካላት ዐይን ያረፈባቸው በመሆናቸው አንዱ የሌላውን ይዞታ ለመንጠቅ የሚያደረገው ጥረት ከመቸውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። በዚህ ምክንያት በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል ከትብብርና መከባበር ይልቅ መገፋፋት ይስተዋላል። በሃይማኖታዊ ወንድማማችነት መንፈስ ከመተያየት ይልቅ እንደባላንጣ በመተያየት የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን ቅድስና የማይመጥኑ ተግባራት ሲፈጸሙ ቆይተዋል፤ እየተፈጸሙም ይገኛሉ።  

 

በቅድስት ሀገር ኢሩሳሌም  የሚገኙ ገዳማትን የጥንት አባቶቻችን በባዶ እግራቸው ተጉዘው ብዙ ፈተናና መከራ አሳልፈው የመሠረቷቸው ናቸው። በእነርሱ ድካም እና ተጋድሎ የተመሠረቱት ገዳማት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተከብሮ ከትወልድ ወደ ትወልድ ሲተላለፉ ቆይተዋል። በዚህ ዘመን ያሉ የገዳማቱ መነኮሳት አባቶች ደግሞ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶችን ተቋቁመው አለፍ ሲልም የሕይወት መሥዋዕትነት እየከፈሉ በተወሰነ ደረጃ የገዳማቱ ክብር ተጠብቆና የቤተ ክርስቲያን የይዞታ ባለቤትነቷ ተረጋግጦ ቆይቷል። በዚህ ወቅት ለገዳማቱና ለገዳማውያኑ ከውስጣዊ ችግሮች በላይ ውጫዊ ችግሮች ፈተና ሆነዋል። የገዳማቱና የገዳማውያኑ ውጫዊ ፈተና ምንጭ ከሆኑት አካላት መካከል  በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው። እነዚህ አባቶች ከዚህ ቀደም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታ የሆኑ ገዳማትን በወረራ ከመውስዳቸው በተጨማሪ የቀሩ ሌሎች ገዳማትን ለመውረር ጥረት ማድረግ ከጀመሩ ዘመናት አልፈዋል። በየጊዜው ገዳማቱን ለመውረር ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በአባቶች ላይ ትንኮሳ፣ድብደባ፣ዘለፋ ከመፈጸማቸው በተጨማሪ በገዳሙ ውስጥ ባለ የቅዱስ ሚካኤልና አርባዕቱ እንስሳ አብያተ ክርስቲናት  ውስጥ ገብተው “አንወጣም” እስከማለት የደረሱበት ጊዜም ነበር። 

በአጠቃላይ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ጥንታዊ የኢየሩሳሌም ገዳማት ላይ ዘመን የማይሽረው ትውልድ የማይረሳው በደል ሲፈጽሙ ቆይተዋል፤ እስካሁን ድረስም እየፈጸሙ ይገኛሉ። አባቶቻችን በግብፃውያን አባቶች እተፈጸመባቸው ያለውን ግፍ ሁሉ ተቋቁመው ቀሪ ገዳማትን ከወረራ ታድገው ይዞታችንን አስከብረዋል። በቅርቡ (የትንሣኤ በዓል መዳረሻ ወቅት) የግብፅ ወራሪ መነኰሳት አባቶች እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ የዴር ሱልጣን ገዳምን ለመውረር ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በገዳማቱ ሁከትና ብጥብጥ ያስነሡ ቢሆንም በገዳሙ አባቶች፣በምእመናን፣ በሌሎች ኢትዮጵያውያን፣በእስራኤል መንግሥትና በኢትዮጵያ ኢምባሲ በእስራኤል የጋራ ትብብርና  ቅንጅታዊ ሥራ ከሽፎ ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል። በወቅቱ ስለተፈጠረው ነገር ማብራሪያ እንዲሰጡ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል። ቆይታቸውንም በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።            

ስምዐ ጽድቅ፡- በአሁኑ ወቅት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አገልጋይ አባቶች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? 

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፡- በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ውስጥ የሚያገለግሉ አበው መነኰሳት በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም እግዚአብሔር በሰጣቸው ኃይልና ጸጋ በሁሉም ገዳማት እየወጡ እየወረዱ መደበኛ አገልግሎት ከመፈጸማቸው ባሻገር ገዳማቱን ከውጭ ወራሪ እየተከላከሉ ይገኛሉ። ባለፉት ጊዜያት የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑና ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ገዳሞቻችን ድረስ በመምጣት ይጠይቁንና ያጽናኑና ነበር፤ ችግር ሲመጣም አብረው ይጋፈጡ ነበር። ነገር ግን በዚህ ወቅት በተከሠተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መጥተው የሚጠይቁን የኢትዮጵያውያን ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ቀንሷል። በመሆኑም ከውጭ አካላት የሚደርስብንን ጫናና ጥቃት ብቻችን መቋቋም አልቻልንም። 

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉልንን እገዛ ከመጠበቅ ይልቅ የእግዚአብሔርን ኃይል እገዛ አድርገን በስድስቱም ገዳማት የተጠናከረ አገልግሎት እየሰጠንና ከወርራ እየጠበቅን እንገኛለን፤ ዘወትር ከውጭ አካላት  ተፅዕኖ፣ ጥቃትና ፈተናዎች ይገጥሙናል፤ የሚገጥሙንን እያንዳንዳቸው ፈተናዎች ሁሉ ሕዝብ በይፋ የሚያውቃቸው፣የሚረዳቸውና ጎልተው የሚታዩ አይደሉም። በተለይ ግብጻውያን በተደጋጋሚ በዴርሡልጣን ገዳማችን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ምን ያህሉ የሀገራችን ሕዝብ ያውቀዋል የሚለው ጉዳይ ጥያቄ የሚያስነሣ ነው። በገዳሞቻችን የሚፈጸሙት ትንኮሳዎችና ጥቃቶች በአብዛኛው በትንሣኤ በዓል መዳረሻ ወቅት የሚከሠቱ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ በገዳማቱ በዓለ ትንሣኤን የሚያከብሩ በርካታ ምእመናን መኖራቸው ከግብጻውያን የሚመጣውን ትንኮሳ ለመከላከል ከፍተኛ አቅም ይፈጥሩልናል። እንደሚታወቀው አካባቢው ከጅምሩ የፈተናና የመከራ ቦታ ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማስተማር ጀምሮ ግፍና መከራ የተቀበለበት ቦታ ነው። በእኛ ላይ እየተፈጸመ ያለው መከራና ግፉ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተቀበለው ግፍ የቀጠለ ነው። 

ወደ ኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት በሊቀ ጳጳስነት ተመድቤ ከመጣሁበት ጊዜ አንሥቶ በቦታው ላይ ፈተናው ሳይቋረጥ ቀጥሏል፤ ይልቁንም መልኩ እየተዋቀረ ይዘቱም እየጨመረ መጥቷል። ይህ ችግር በተለይ በታላቁ ገዳማችን ዴርሡልጣን የሚስተዋል ነው። የሚገጥሙንን ችግሮች ሁሉ በጥበብና በትዕግሥት በማለፍና እግዚአብሔርን ኃይል አድርገን ስናገለግል ቆይተናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረግንና በደላችንን ከኢትዮጵያውያን ባሻገር መላው ዓለም እንዲያውቅልን ርብርብ እያደረግን እንገኛለን። የእግዚአብሔር ርዳታ ተጨምሮበት ሁላችንም አንድ ላይ ከቆምን ይዘገያል እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን ማሸነፏ አይቀርም። 

ስምዐ ጽድቅ፡- በሀገረ ስብከትዎ ያለው አጠቃላይ ችግር ወይም ፈተና ምንድን ነው?

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፡- በሀገረ ስብከቱ ከሚታየው ችግር  ጥልቀትና ስፋት አንጻር በውስን ጊዜ ለመዘርዘር ያስቸግራል። በአካባቢው ያለው ፈተና በየጊዜው የሚከሠት ከመሆኑ ባሻገር በጣም ውስብስብ ነው። ቢሆንም ግን ችግሮቹን በትብብር፣ በጥበብና በውይይት ለመፍታት እንዲሁም መፍትሔ በማስቀመጥ ለማለፍ ጥረት ይደረጋል። ገዳሞቻችን ባሉበት ቦታ ሁሉ ፈተናዎች አሉ። ያሉብን ችግሮች ውስጣዊና ውጫዊ ቢሆኑም ውስጣዊ ችግሮቹን እርስ በእርስ በመመካከር እያስተካከልን እንገኛለን። በተጨማሪም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት የተለያዩ ይዞታዎች ስላሉ ከግብጻውያን ጥቃትና ወረራ በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ በቻልነው አቅም ጥረት እያደረግን እንገኛለን። 

ከዚህ ቀደም በሕግ የሚፈቱትን በሕግ እየፈታን በውይይት የሚፈቱ ቀላል ችግሮችን ደግሞ በውይይት እየፈታን የገዳሞቻችንንና ሌሎች ይዞታዎችን ስናስከብር ቆይተናል፤ እያስከበርንም እንገኛለን። እየገጠሙን ያሉ ፈተናዎች አንዳዶቹ በመገናኛ ብዙኃን ሊነገሩ የማይችሉ በመሆናቸው ከመዘርዘር ልቆጠብ እንጂ የፈተናዎቹ ብዛትና ጥልቀት እጅግ ከፍተኛ ነው። እኛ በኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ለአገልግሎት የተመደብን አባቶች አባቶቻችን ያስረከቡንን የከበሩ ቅርሶች ተንከባክበንና ጠብቀን ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ጥረት እናደርጋለን። ይህንን ጥረታችንን የሚያደናቅፉ አንዳንድ የውስጥ አካላት ቢኖሩም በትዕግሥት በማለፍ ወደፊትም በሕይወት እስካለን ድረስ ርስታችን እናስከብራለን። ማኅበረ ቅዱሳን ከሚያደርግልን የሚዲያ ሽፋን በተጨማሪ በተለያዩ ዓለማት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በችግሮቻችን ወቅት ‹‹አይዟችሁ›› ይሉናል፤ ያግዙናል። ችግሮችም በሚከሠቱበት ወቅት በምናደርግላቸው ጥሪ መሠረት ፈጥነው ምላሽ ይሰጡናል። 

ስለሆነም ድጋፍ በሚያደርግልን ሕዝባችን እንኮራለን፤ እንመካለንም። የጥንት አባቶቻችን በእግር ጉዞ የግብፅን በረሃ አቋረጠው በውኃ ጥም፣ በረኀብና በድካም ሞተው ያስረከቡንን ጥንታዊ የኢየሩሳሌም ገዳሞቻችን ታሪካዊነታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ እኛም የሚከፈለውን  ዋጋ ሁሉ ከፍለን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ አልመን እየሠራን ነው። እኛ የአባቶቻችን ልጆች እስከሆነ ድረስ የእነርሱን ፈለግ በመከተል የተቀበሉትን መከራ ለመቀበል ሁልጊዜም ዝግጁዎች ግን። ፈተናውን ለመቀበል መፍቀዳችንና ነገሮችን በጸጋ ማለፍ በመቻላችን እስካሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያናችን ርስቶች የሆኑትን ገዳሞቻችንን ጠብቀንና ተንከባክበን አቆይተናል። ይሁን እንጂ ፈተናው ብርቱ ነው፤ ይጨምራል እንጂ አይቀንስም። በቅድስት ሀገር እየሩሳሌም ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ገዳማት የሀገር ሀብቶች መሆናቸውን በመረዳት የተጋረጠባቸውን ውስብስብና ጥልቅ ፈተና በጋራ በመቆም መመከት ያስፈልጋል።

ስምዐ ጽድቅ፡- በቅርቡ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትና መነኮሳት ትንኮሳና ወረራ ማድረጋቸው ይታወሳል፤ በትንኮሳው ወቅት በአባቶችም ሆነ በገዳሙ ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ ቢነግሩን?

ብፁዕ አቡነ ዕነባቆም፡- ግብጻውያን አባቶች በገዳማችን ላይ የፈጸሙት ትንኮሳ በገዳሙ ተሰቅሎ የሚኖር የሀገራችን የሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ከማውረድ የጀመረ ነበር። ከዚያም ከገዳሙ መነኮሳት ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገቡ። የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ያለ አግባብ ባንዲራው እንዲወርድ ባዘዘው መሠረት አውርደን እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማው ከዚህ ቀደም የነበረ መሆኑን እንደገና አስረድተን ሰንደቅ ዓላማው ተመልሶ በገዳሙ እንዲሰቀል አድርገናል። ይህ ከሆነ ብኋላ በማግስቱ ግብጻውያኑ መነኮሳት ጳጳሳትንና ሌሎችን  አስከትለው ጨለማን ተገን አድርገው የዴርሡልጣን  ገዳምን ለመውረር መጡ። እኛ ቀድሞ መረጃ ደርሶን ስለበር ለሀገሪቱ የተለያዩ  የመንግሥት አካላት ደብዳቤ ጻፍን። ከበቂ በላይም ተዘጋጀን። ቅድመ ዝግጅት ያደረግነው ከዚህ ቀደም ግብጻውያኑ በበዓለ ትንሣኤ መዳረሻ ላይ የሚያደርጉትን ትንኮሳ ስለምናውቅ ነበር። 

 

Read 609 times

Related items