Friday, 06 August 2021 00:00

ለገዳማቱ መንፈሳዊ ጉብኝት ባለቤቱ ማነው?

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ብዙም ዘመናዊ መጓጓዣ ባልነበረበት እንደዛሬው ማስታወቂያ በማይነገርበት በጥንቱ ዘመን አባቶቻችን ባሕር አቋርጠው፣ ተራራ ወጥተው እና ወርደው የብዙ ቀናት አሊያም ወራት መንገድ በእግራቸው ተጉዘው ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ፣ ከበዓሉ በረከት ለመሳተፍ ወደ ተለያዩ መንፈሳዊ ቦታዎች መንፈሳዊ ጒዞዎችን ሲያደርጉ ኖረዋል።በዚህ መንፈሳዊ ጉዞም የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያድግ አድርገዋል፤ ወንጌል እንዲስፋፋ የራሳቸውን አስተዋጽኦም አበርክተዋል።ለዚህም በሐዋ. ሥራ ምዕራፍ ፰ ላይ የምናገኘው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አንዱ ምሳሌ ነው። ዛሬ ከዚያ በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ጉብኝቶች ዘመኑን በዋጀ መልኩ በማስታወቂያ ታጅበው ለምእመናት ይደርሳሉ።ምእመናን መጓጓዣ ከማይገባባቸው  ቦታዎች በስተቀርም ዘመኑ ባመጣው መጓጓዣ ይገለገላሉ።የመንፈሳዊ ጉዞ ማስታወቂያዎች እንደ አሸን በፈሉበት በዚህ ዘመን ከየትኛው ቤተ ክርስቲያን (ገዳም) ልሂድ የሚለው ብዙም አሳሳቢ አይደለም።የማስታወቂያዎቹ ዓይነቶችም እንደ ባሕሪያቸው የተለያዩ ናቸው። ከእነዚህ ብዛት ያላቸው ማስታወቂያዎች በተለይ ‹‹ዘወትር እሑድ ወደ . . . ገዳም››  የሚል ማስታወቂያ በየቦታው ማየት እየተለመደ መጥቷል። የቤተ ክርስቲያንን ውጫዊ ቅጽሮች፣  የአውቶብስ ፌርማታዎች ፣ የመንገድ ዳር አጥሮች እንዲሁም የከተማ ታክሲዎች ባጠቃላይ የትራንስፖርት መጓጓዣዎች  በጉዞ ማስታወቂያዎች የተሞሉ ናቸው።ከዚህ አለፍ ሲልም ጉዞው የሚደረግበትን ቦታ የሚያስተዋውቁ በራሪ ወረቀቶች በየመንገዱ ማየት የተለመደ ነው።

 

የነዚህ ማስታወቂያዎች ዐቢይ ዓላማ  የንግሥ ቀናትን ማስተዋወቅ እና ምእመናን በቦታው ሄደው ከበዓሉ በረከት ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስተዋውቅ ነው።ሌላው ሰዎች በዕለተ እሑድ ወደ የተለያዩ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት በመሄድ ከቦታው በረከት እንዲያገኙ ፣ ከተአምራቱ እንዲሳተፉ የሚያስተዋውቅ ሲሆን አልፎ አልፎ አብያተ ክርስቲያናት ሲታነጹ ሥራውን በገንዘብ ለመደገፍ እና ከበረከቱ ለመሳተፍ የሚደረጉ ጥሪዎችም ይገኙበታል።

ማስታወቂያዎቹ ከግለሰብ እስከ ቡድን ከሰንበት ት/ቤት እስከ ማኅበራት እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ደረጃ ይሠራሉ።ሰዎችን ከመንፈሳዊ በረከት እንዲሳተፉ ጥሪ ማድረጉ፣ መንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚታነጽበትን የተለያየ መንገድ ፈልጎ መንቀሳቀሱ፣ የማይታወቁ፣ የተረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታወቁ ማድረጉ ለገዳማቱም ሆነ ለምእመናኑ ጥሩ የግንኙነት መሥመር ነው።ሰዎች ወደ ቅዱሳት መካናት ሄደው ቦታውን ካዩ በኋላ ለቦታው የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ይልቁንም በቦታው ላይ በመሄድ ከበረከቱ መሳተፍ በምእመናን ላይ የሚያሳድረው የገዳም ፍቅር ቀላል አይደለም።ምእመናን ወደ እነዚህ ቦታዎች ሲሄዱ ለአብያተ ክርስቲያናቱ የሚያደርጉት የጧፍ፣ የሻማ፣ የዕጣን ፣ የአልባሳት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ቀላል አይደለም።

ቅዱሳት መካናትን የመሳለሙ ሂደት ከሀገር ውስጥ ጀምሮ እስከ ውጭው ዓለም ይዘልቃል።እነዚህ የቅዱሳት መካናት የተሳትፎ ጥሪዎች በዓል ተኮር ሲሆኑ በአብዛኛው በዕለተ እሑድ በሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው።ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ‹‹ዘወትር እሑድ ወደ . . . ገዳም(ቤተ ክርስቲያን)  የሚለው ማስታወቂያ ግን  ከሁሉ ገዝፎ ይታያል።

አብያተ ክርስቲያናቱን እንዲሁም ገዳማቱን ማስተዋወቅ በጎ ተግባር ሆኖ ሳለ ከማስተዋወቁ ጀርባ ያሉ ጉዳዮች ግን ጥንቃቄ እና ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል።ከግለሰብ እስከ ማኅበራት የሚደረጉት ቅዱሳት መካናትን የመሳለም ተግባር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ኃላፊነት ወስዶ የሚያርማቸው አካል ወይም ባለቤት አስፈላጊ ነው።ከመነሻው የቤተ ክርስቲያንን ባለቤትነት የሚያሳጡ ወይም ተጠቃሚ የማያደርጉ ለመንፈሳዊ ጉዞ የተዘጋጁ ሰዎች ካሉም የቤተ ክርስቲያንን ጥቅም በሚያስከብሩበት መንገድ እንዲዋቀሩ ቤተ ክርስቲያን ትልቁን ኀላፊነት ልትወስድ ይገባታል።

ምእመናን ከመንፈሳዊ ቦታዎች በረከት ለመሳተፍ የሚጠሩበት መንገድ ካልተስተካከለ አሠራር ማእከል ወጥ ወደሆነ እና ተጠያቂነት ወዳለው መስመር እንዲገባ ማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ከነግ ወቀሳ ያድናታልና እዚህ ላይ አጥብቆ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ተገቢ ነው።ምክንያቱም ከግለሰብ እስከ ማኅበራት የሚደረጉት መንፈሳዊ ቦታዎችን የመሳለም ተግባር እንደየግለሰቦቹ እና ማኅበራቱ ዥንጉርጉር ናቸውና።ለብዙዎቹ ከመንፈሳዊ በረከቱ ይልቅ የትርፍ ማጋበሻ የሆኑ መንፈሳዊ ጉዞዎችና ማስታወቂያዎች በተጓዦች ላይ የሚያመጡት መንፈሳዊ ለውጥ ወይም እድገት ቤተ ክርስቲያንን ሊያሳስባት ይገባል።

በሀገራችን ውስጥ ከግማሽ በላይ የቱሪስት መዳረሻ ሀብቶች ባለቤት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቱሪዝም መስሪያ ቤት ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊኖራት ሲገባ ከዚያ መገፋቷ ሳያንስ ከአብያተ ክርስቲያናት እና ከገዳማት የምታገኘው ጥቅም የግለሰቦች አሊያም የማኅበራት እጅ ላይ መውደቁን በማጤን ከሀብቷ መጠቀም በምትችልበት መንገድ ላይ አጥብቃ መሥራት ይጠበቅባታል።ከባለቤትነት በተገፋች እና እየራቀች በሄደች ቁጥር ለነገ መንፈሳዊ አገልግሎቷ መሰናክል ነውና።በግለሰብም ሆነ በማኅበራት የሚካሄዱት እነዚህ መንፈሳዊ ጉዞዎች ሐዋርያዊ መሆናቸውንም መፈተሽ ተገቢ ነው።ምእመናን መንፈሳዊ ጉዞዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ ሊያገኙ የሚገባቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት እያገኙ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ በሚቻልበት መንገድ  እንዲህ ዓይነት አገልግሎቶችን ወጥ አሠራር መዘርጋት ድርሻው የቤተ ክርስቲያን ነው።ሰዎች በሚኖራቸው መንፈሳዊ የጉዞ አገልግሎት ከግለሰቦች ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ድምጽ እንዲያዳምጡ ማድረግ ከቤተ ክርስቲያን ይጠበቃል።  

ከዚህም ባሻገር የሚሄድበትንም ሆነ የሄደበትን ዐቢይ መንፈሳዊ ጉዳይ የተረዳ መንፈሳዊ ምእመን ለማፍራት ቤተ ክርስቲያን ቀጥተኛ ተሳታፊ እና ባለቤት መሆን ይጠበቅባታል።ከመንፈሳዊ ሕይወት የተፋታ ጉዞ ፤የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፃረር መንፈሳዊ ጉብኝት ለማስቀረት ወጥ የሆነ የቤተ ክርስቲያን አሰራር እና መመሪያ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።ለተለያዩ መንፈሳዊ ሥራዎችን እና በረከት ለማግኘት የሚኬድባቸው ቅዱሳት ገዳማት እና አድባራት በየሳምንቱ ዘወትር . . . እየተባሉ መፈራታቸው እና መከበራቸው እየተረሳ ነውና ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው።በአጠቃላይ ወደ ገዳም ለሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ ባለቤት ሊኖረው ይገባል እንላለን።

Read 399 times