Friday, 06 August 2021 00:00

‹‹የቄስ መቃብሩ የሚሳምበት ጊዜ ይመጣል የሚባለው ሰው አልቆ አይደለም›› (ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ክፍል ሁለት

Written by  መጽሐፈ ሲራክ

Overview

የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ቀጣዩን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡                                                                             በዚያ ዓመት ነሐሴ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ደብረ ሊባኖስ አልሄዱም ነበር መርካቶ ደብረ አሚን መጥተው ገድለ ተክለ ሃይማኖትን ጥሩ አድርጌ ሳነብ ስተረጉም ፣ ሳስተምር ደስ ብሎአቸው አተኩረው እያዩኝ ይሰሙኝ ነበርና ታቦቱ እንደገባ አስጠርተው ‹‹ደብዳቤ ሳይደርስ ከዚህ እንዳትሄድ›› አሉኝ ፤እኔም የመተሐራውን ሐሳባቸውን እንደቀየሩ ገባኝ።‹‹ድሮስ ያለ ደብዳቤ እንዴት እሄዳለሁ?›› አልኩኝ።በዚያው ወደ መተሐራ መመለሴ ቀረ ማለት ነው።  ደብረ አሚን አለቃ ሁኜ እያገለገልኩ ሳለ  ጻድቁ የተሰጣቸው ቃል ኪዳን ነው ለምን ፀበል አላጠምቅም ብዬ ገድላቸውን እያነበብኩ ምእመናንን ማጥመቅ ጀመርኩ እንዲሁ እግዚአብሔር ነው ያነሳሳኝ።ካህናቱም በተራ እንዲገቡ አደረግሁ በኔ የመጣ ጸጋ አይደለም የጻድቁ ነው አልኳቸው እነሱም ደስ ብሎአቸው ያጠምቁ ነበር።ደብረ አሚን ፱ ዓመት በልቅና ካገለገልኩ በኋላ በ፲፱፻፸፱ ዓ.ም ጵጵስና ውድድር ውስጥ ገብተሀል የሕይወት ታሪክህን አምጣ አሉኝ የሕይወት ታሪኬን ጽፌ አስገባሁ ውድድሩን አልፌ መዓረገ ጵጵስናው ተሰጠኝ ወዲያው ወደ ወላይታ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶስ ሆኜ በመሄድ አንድ ዓመት አገለገልኩ።የሚገርመው ብዙ ጊዜ ለአገልግሎት የምመደብባቸው ቦታዎች የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ነበር።እነሱም የተክለ ሃማኖት ልጅ ነው እያሉ ነበር ወደ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ይልኩኝ የነበረው።

 

ወላይታ አንድ ዓመት እንደቆየሁ በ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ወደ ትግራይ ሀገረ ስብከት ተቀየርኩ ያን ጊዜም የደርግ መንግሥት ትግራይን ለቆ ወጥቶ ኢህአዴግ ገብቶ ነበር።ብዙዎች ‹‹መንግሥት ትቶት የሄደውን›› አሉኝ እኔም ‹‹እኔ የምሄደው ለመእመናን ነው›› አልኩኝ መጨረሻ ላይ አስቀሩኝ በርግጥ መንግሥት ነው የከለከለው።ነገሩ እግዚአብሔር ፈቅዶ ሙት ሳይለኝ ቀርቶ ነው።ከዚያ በኋላ ሊቀ ጳጳስ ሆኜ ወደ ምዕራብ ሀረርጌ  ተዘዋወርኩ።በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም ኢህአዴግ መላውን ሀገር ሲቆጣጠር ከምዕራብ ሀረርጌ ወደ ወለጋ ሀገረ ስብከት ተዘዋወርኩኝ በ፲፱፻፹፬ ዓ.ም እንደገና አጠቃላይ የሀረር ሀገረ ስብከትን እንዳገለግል ኃላፊነት ተሰጠኝ።እዚያ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቆይቼ በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆኜ ወደ ኢየሩሳሌም ሄድኩኝ።በኢየሩሳሌም ለአራት ዓመታት ያህል ሳገለግል ቆይቼ በ፲፱፻፺፯ ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተጠርቼ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆኜ ተመደብኩ ይኸው እስከ አሁን ደብረ ሊባኖስን ጨምሮ እያገለገልኩ እዚያው ነው ያለሁት።

ስምዐ ጽድቅ፦ በአብነት ትምህርት ቤት ሕይወት  አብነት ሆነውኛል የሚሏቸው መምህራን ካሉ ቢነግሩን?    

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ በአብነት ትምህርት ቤት ሕይወት ሁሉም መምህሮቼ መናኞች ነበሩ።አባ አፈ ወርቅ ጥሩ መነኵሴ ነበሩ፤አካላቸው የተጎዳ እጅ እና እግራቸው የሚያስቸግራቸው ብርቱ መምህሬ ለኔ አብነቴ ነበሩ።አባ ወርቁ የሚባሉትም እንዲሁ መናኝ ሽማግሌ ነበሩ።በተለይ አባ አፈ ወርቅ ብልህ አባት ነበሩ።ጥበብ ያላቸው አባት ስለነበሩ ብዙ ቅርጻ ቅርጽ ሥራዎችን በቃል እየነገሩ ሌላ ሰው ያስቀርጹ ነበር።ጉባኤያቸው ሰፊ ስለነበር የአካባቢውን ልጆች ሁሉ ሰብስበው ያስተምሩ ነበር።ሌላው አብነቴ አባቴ ናቸው እርሳቸው በሁሉም ነገር ችሎታ ያላቸው የግእዙን አካሄድ ጠንቅቀው የሚያውቁ ስለነበሩ የሚሰጡትም ትምህርት የማያዳግም ነበረ።

ስምዐ ጽድቅ፦ በአብነት ትምህርት ቤት ቆይታዎ ስንት ተማሪዎችን አፍርተዋል? 

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ያኔ ብዙ አይደለም ተማሪዎቹ ፳ እና ፴ ነበሩ።ጊዜው የደርግ ሥርዓት ስለነበር ኅብረት በኅብረት የሚባል ዘመቻ ነበረ።ብዙ ተማሪም አልነበረም ቅድም እንዳልኩት ደሞዛችንንም ስለያዙት እንዲሁም ውጣ ውረድ የበዛበት ዘመን ስለነበረ ወደ ፴ ይሆኑ ነበር።እኔ ሁኔታውን አይቼ ብዙም ስላላማረኝ ወደ ደብረ ሊባኖስ ነው የሄድኩት።

ስምዐ ጽድቅ፦ ካስተማሩዋቸው ተማሪዎች ወንበር ዘርግተው የሚያስተምሩ አሉ? በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ የሚያገለግሉስ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ፦ ወንበር ዘርግቶ የሚያስተምር አንድ ልጅ ነበር ሞተ።ዲያቆናት ብዙ አሉ።በየቤተ ክርስቲያኑ በተለያየ ቦታ ላይ በተለያየ መዓርግ የሚያገለግሉ ብዙ ናቸው።ጳጳሳትም የሆኑ አሉ።ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ቀሌምጦስ ከኔ ተማሪዎች አንዱ ናቸው።

ስምዐ ጽድቅ፦ እንደ እርሰዎ ያሉ መምህራን አባቶች እንዲበዙ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለባት ይላሉ በተለይ የአብነት ትምህርት ቤት ላይ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ የአብነት ትምህርት ቤት አሁን እየተዳከመ ነው።ድሮ የአብነት ትምህርት ቤት ቀለብ ሰፋሪ ሕዝቡ ነበረ።ምእመኑ ትኩስ እንጀራ እያጠፈ እየሰጠ ነበር እኛን ያስተማረን።ተማሪውም መንደሩን ተካፍሎ እየለመነ ይማር ነበረ።አሁን ያ ሁሉ ቀርቷል።አሁን አሁን ያ ትውፊት ይኑር ይቅር አላውቅም።ዋናው ወደ ፊት ሊታሰብበት የሚገባው የአብነት ትምህርቱ ሕልውና ነው።በቤተ ክርስቲያን የነበረው ዜማ፣ የነበረው ቅኔ ፣የነበረው መጽሐፍ ቤት ባጠቃላይ የአብነት ትምህርቱ እንዲቀጥል እና ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ነው።የአብነት ትምህርት ቤቱን ከዚህ የተሻለ መዋቅር ውስጥ በማስገባት ለዚሁ አገልግሎት ብቻ የሚውል በጀት መድቦ ለመምህሩ እና ለደቀ መዛሙርቱ በተገቢው መንገድ የሚደርስበትን ሥርዓት በመዘርጋት በጀቱንም መንገድ ተጠናክሮ ሊሠራበት ይገባል። 

እንዲህ ዓይነት የአገልግሎት መስመር በመዘርጋት የአብነት ትምህርት ቤቱን መታደግ ካልቻልን ቤተ ክርስቲያንን ችግር ላይ ትቀወድቃለች።የሚያሳስበው ይሄ ነው።በአሁኑ ዘመን ለምነህ ተማር ማለት አይቻልም።ተማሪው ቀለብ የሚሠፈርለት ከሆነ  ለትምህርቱ ወደ ኋላ አይልም። መምህሩም እንደዚያው።እኔ የምመክረው ወይም ደግሞ ተቀባይ ከተገኘ ልናገረው የምፈልገው ለተማሪዎችም ሆነ ለመምህራን የተሻለ እና ሊኖራቸው የሚችል ደሞዝ ቢመደብላቸው መልካም ነው።እስከ ዛሬ እኮ ለመምህሩም ቢሆን የአኩፋዳ እንጀራ ተማሪዎቹ እያመጡ እያበሉት እንጂ ደሞዝ ኖሮት አይደለም ሲያስተምር የነበረው ይኼም የግፍ ግፍ ነው።በእውነት ቤተ ክርስቲያን ለመመምህሩ እንኳ ደሞዝ መመደብ ነበረባት።

እስካሁን በዚህ መንገድ ተመጥቷል መምህሮቻችን ገንዘብ የማይፈልጉ መናኞች ነበሩ፤ አሁን ግን ጊዜው አስተምሮአቸዋል።እነርሱ ያስተማሯቸው ደቀ መዛሙርቶቻቸው የ፲ሺህ፣ የ፲፭ሺህ ብር ደመወዝተኛ ሲሆኑ እነርሱ ግን አንድ መቶ ብር እንኳ አጥተው በአኩፋዳ እንጀራ አስተምሩ ማለት በጣም ይከብዳል በዚህ መልኩ ኑሮአቸውን ለመግፋት ስለሚከብዳቸው እነሱም ከእንግዲህ ወዲያ አይቀበሉትም።ቤተ ክህነቱ ጉዳዩን አስቦበት ለመምህራኑም ለደቀ መዛሙርቱም ቀለብ የመሥፈር የደመወዝ ሥርዓትን በመዘርጋት ጥንታዊው የአብነት ትምህርት እንዲካሄድ ቢደረግ ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኘው።ቤተ ክርስቲያን እንዳለች የምትቀጥለው።አለበለዚያ ግን ብዙ ችግር ይደርስባታል።እስከመዘጋት ትደርሳለች ‹‹ የቄስ መቃብሩ ይሳማል፤ የቄስ መቃብሩ የሚሳምበት ጊዜ ይመጣል የሚባለው ሰው አልቆ አይደለም።ሁሉም ጭልጥ ብሎ ወደ ዘመናዊው ይሄዳል፤ እንጀራ ፍለጋ ይሄድና በዚያው ጭልጥ ብሎ ይቀራል፤ ተማሪ ይጠፋል፤ በመሀል ተተኪ ከጠፋ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ባዶ ትሆናለች ማለት ነው።ያ ችግር እንዳይፈጠር መምህራንን ካህናትንና ዲያቆናትን በማፍራት ቤተ ክርስቲያን ከወዲሁ መሥራት  አለባት።ቤተ ክህነቱ በጥልቀት አስቦ ደሞዙን ሊያስብበት ይገባል።

ስምዐ ጽድቅ፦ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወንበር ታጠፈ አባቶች ተሰደዱ ጉባኤም የተፈታበት አካባቢ አለ ይባላል።ቤተ ክርስቲያን ይህን በውል ተገንዝባዋለች ብለው ያስባሉ?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ሁሉም እንጀራ ፍለጋ እንደተሰደዱ ታውቋል።እንጀራ ፍለጋ ነው እንጀራው ከተገኘ    ይመለሳሉ። ብዙዎቹ እዚህ አዲስ አበባ ነው የገቡት። አዲስ አበባ አንዳንዶቹ ትምህርታቸውን ትተው የኮብል እስቶን ሞያን እየተማሩ ድንጋይ እያነጠፉ   ናቸው። ከድንጋይ ጋራ ከሚታገሉ ደሞዝ ካገኙ ወደ ጥንት ቦታቸው ይመለሳሉ።ስደት አይደለም።ያሰደዳቸው ዳቦ ፍለጋ ነው።

ስምዐ ጽድቅ፦ በሥራ ደረጃ ያከናወኗቸው የተለያዩ ተግባራት፣ እንዲሁም የጻፏቸው መጻሕፍት ካሉ ቢነግሩን 

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ፦ ወደዚህ ከመጣሁ ወዲህ በተጓዳኝ ባይባልም የምሠራው ያው ዓይነተኛ ሥራዬን ነው።የፈረሱ ቤተ ክርስቲያናትን ማሳደስ፣ መሠረት ጥሎ መሥራት ነው።ቁጥሩን አልያዝኩም እንጂ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ሠርቼአለሁ ደግሞ በሄድኩበት ይቀናኛል።ጀምሬ ያልፈጸምኩት የለም።በየሔድኩበት አስተምራለሁ፣ አስተባብራለሁ፤ ጥረቴ ደግሞ የአብነት ትምህርት ቤት እንዳይዘጋ ነው።በአሁኑ ሰዓት እዚያ ሀገረ ስብከቴ ወደ ሁለት መቶ የድኃ ልጆች ሰብስቤ አስተምራለሁ አሁን በኮረናው ምክንያት መቶ ስልሳ ሆነዋል።አምስት መምህራን  ሴቶችም ወንዶችንም ቀጥሬ የዘመናዊውን ትምህርት እያስተማርኩ ነው።

በመጽሐፍ ደረጃ ሁለት መጽሐፍ ጽፌያለሁ።አንደኛው ፲፱፻፺ ‹‹ይግባኝ ለክርስቶስ›› የሚል መጽሐፍ ጽፌ ነበር።የዘመኑን ሁኔታ ያሳያል አቡነ ጴጥሮስን ምክንያት አድርጌ ነው የጻፍኩት።ሌላው ደም እየተቀቡ በየወንዙ የሚዞሩ እሱ ጥሩ አይደለም እግዚአብሔር የማይወደው ነው።ይህን በክርስቶስ ደም የተቀደሰውን ሕዝብ እንዴት በእንስሳት ደም ታረክሳላችሁ ልክ አይደለም ‹‹ይግባኝ ለክርስቶስ›› ያሰኛል ብዬ ጻፍኩኝ።እንዳጋጣሚ በበሻሻ የተገደሉት ክርስቲያኖች (ሙስሊሞቹ ክርስቲያኖቹን) በቆንጨራ የጨፈጨፏቸው መጽሐፉ በወጣ ማግስት  ነው።                

ሁለተኛው መጽሐፍ ተሀድሶዎች በተነሱ ጊዜ ‹‹ዓለም ጉድ ወለደች›› በሚል ርእስ የተጻፈ ነው።በጊዜው ተሀድሶዎቹ መጽሐፍ እየጻፉ ይበትኑ ነበር መጽሐፎቹን ካየን ከመረመርን በኋላ እንዲወገዙ አደረግን ካወገዟቸው ከተቃወሟቸው አባቶች መካከል እንዱ ነበርኩ።በዚያ ምክንያት ነው ‹‹ዓለም ጉድ ወለደች›› በሚል ርእስ ስለ ቅዱሳን፣ ስለ እመቤታችን ስለ ጾም ስለ ጸሎት ባጠቃላይ ሁሉንም የሚዳስስ መጽሐፍ የጻፍኩት።ስምዐ ጽድቅ፦ እርስዎ ከመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ጋር አብረው ሠርተዋል፤ከንጉሡ ጀምሮ የተለያዩ መንግሥታትን አሳልፈዋል በነዚህ ዘመናት የቤተ ክርስቲያን መልክ ምን ይመስል ነበር?

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ ቤተ ክርስቲያን በንጉሡ ጊዜ ክብርዋ የተጠበቀ ነበር።የመጀመሪያው ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስም ሥርዓት  ሲጣስ አይወዱም ነበር ንጉሡ የሚሳዝን ነገር ሲሰሩ ተቀይመው ወደ ደብረ ሊባኖስ ይመጣሉ።እንዲህ ሲሆን ጃንሆይ ራሳቸው መጥተው          ‹‹ይቅርታ ይህንን ከጠሉብን አንደግመውም›› ብለው አባብለው፣ ተለማምጠው ነው የሚወስዷቸው።እንደ አባትና ልጅ ይከባበሩ ነበር።ቤተ ክርስቲያኒቱም ክብርዋ እንደተጠበቀ ነበረ።

እንደ አሁኑ ያለ ድፍረት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ አይተን አናውቅም።ያኔ በዓሉ ሲከበር ‹‹የእምነቱ ተከታዮች ማለት የለም›› ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የልደት በዓል ይከበራል የትንሳኤ በዓል ይከበራል›› ተብሎ ይነገራል እንጂ አሁን እንደሚነገረው በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እየተባለ አይነገርም።ነውር ነው ሁሉም የዚያ ተከታይ ነዋ ያኔ።እንዲህ ያለ ነገር የለም።ያኔ የበዓሉም አከባበር በሬድዮ ሁሉ ይሠራጭ ነበር።ሥርዓቱ ልዩ ነው ጎናጭ የለም ራሳቸው ንጉሡም የሃይማኖቱ ተከታይ ስለሆኑ እንደልብ ነበረ ያኔ ችግር አልነበረም።

 

Read 836 times