Friday, 06 November 2020 00:00

ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት

Written by  ማኅበረ ቅዱሳን

Overview

ቤተ ክርስቲያን ከዓለመ መላእክት ጀምራ የውስጥም ሆነ የውጭ ፈተናዎችን እንደ አመጣጣቸው እያስተናገደች ኖራለች፤ ዛሬም አለች፤ ወደ ፊትም ትኖራለች። በሐዲስ ኪዳንም መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ  በደሙ የመሠረታት አማናዊት ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በመከራ ነውና መከራ መስቀሉን ተሸክማ አለች፤ ወደ ፊትም ትኖራለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መከራን እየሸሸች ሳይሆን በመከራም እያለፈች ለሀገር ያበረከተችው አስተዋጽኦ በየትኛውም ምድራዊ ሚዛን ሊለካ አይችልም። የምህንድስና ጥበብን፣ የትምህርት ማእከልን፣ የሥነ ጽሑፍ ሙያን፣ የዘመን አቆጣጠርን፣ የፍልስፍና ጥበብን ወዘተ. ከሁሉ  አስቀድማ  ለዓለም አበርክታለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ሁሉ አስተዋጽኦ አበርክታም፣ ፍትሕ በተጓደለበት ዓለም ነውና የምትኖረው ሊያጠፏት ሌት ከቀን የሚደክሙት በርካቶች ናቸው። ለዘመናት መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ጥቃቶችን እያስተናገደች አልፋለች፤ ዛሬም የግፍ ጽዋዕን እየተጎነጨች ትገኛለች። ይሁን እንጂ  ዕለት ዕለት ምእመናኗን “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት” ባለው በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ እያጽናናችና እያበረታች የምትገኝ እናት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ጥበብና ማስተዋል በተሞላበት አኪያሄድ ይህን የመከራ ዘመን በትዕግሥት እንድናልፍ አደራዋን ታስተላልፋለች። አሁን ያለንበት ዘመን  እጅግ የከፋ ነው። ሰው በሰውነቱ መኖር የማይችልበት፣ በማንነቱ ማለትም በሃይማኖቱና በዘሩ (በጎሣው) እየተለየ የግፍ ግፍ የሚፈጸምበት፣ የተገደለ ሰው የቀብር ቦታ እንኳን የሚከለከልበት፣ ሰውን ሰው የሚበላበት ዘመን ላይ እንገኛለን። በዚህም ሁሉ ግን “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት” ያለንን የሐዋርያውን ቃል በማስተዋል ወቅቱን የጠበቀ ራስን የመጠበቅና የመከላከል ሥራን ልንሠራ ይገባል። ለዚህም ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ አካል ድርሻውን መወጣት ይኖርበታል። ለምሳሌ፡- በአባቶች በኩል ከመንግሥት ጋር ጥብቅ የሆነ ውይይት በማድረግ መንግሥት በራሱ አደጋውን እንዲከላከል ያላሠለሰ ጥረት ማድረግ ይገባል። ይህ ካልሆነም ለምእመናኑ አግባብነት ያለው መመሪያ መስጠት ይገባል። መዋቅሩን ጠብቆ ወጣቱ እንዲደራጅ ማድረግ፣ በስሜት ሳይሆን ጥበብና ማስተዋል በተሞላበት መንገድ እንዲጓዝ ከፊት እየሆኑ መምራት የግድ ነው። አባቶቻችን ከውጭ ላለ ጠላት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ጠላት አሳልፎ የሰጠንን የእርስ በእርስ መለያየት፣ የውስጥ የአሠራር ብልሹነት፣ የአስተዳደር ክፍተት ወዘተ. አጥብቀው ማውገዝና የውስጥ ሰላም መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። የውስጥ ሰላም ሳይኖርና የእርስ በእርስ መበላላት ሰፍኖ ባለበት ሰዓት የውጭ ጠላትን እመክታለሁ ማለት ሞኝነት መሆኑን መረዳትና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማምጣት ይኖርባቸዋል። ዕለት ዕለት ‹‹ጸልዩ በእንተ ሰላም፤ ስለ ሰላም ጸልዩ›› እያለች የምታስተምርና የምትጸልይ ቤተ ክርስቲያን ሰላሟን ሊነፍጓት የሚሯሯጡትን አካላት ዘመኑን በዋጀ፣ ጥበብና ማስተዋል በሞላበት ኃይል መመከት ይኖርባታል። ለዚህም አባቶቻችን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉና ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። በየጊዜው እየተወሰነ ነገር ግን ተግባራዊ መሆን ያልቻለውን መሪ ዕቅድ በአግባቡ ትኩረት በመስጠትና ወደ ተግባር በመለወጥ የቤተ ክርስቲያን ችግር እንዲፈታ መታገል ያስፈልጋል። በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል በየወቅቱ ጥሩ ጥሩ የሆኑ ውሳኔዎች ይወሰናሉ፤ ይህም ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ መሆኑን እንድናምን የሚያስችል መሆኑን እንረዳለን። ይሁን እንጂ በውሳኔው ደስ ሲለን ወደ ተግባር ባለመለወጡ ውሳኔ ባገኘው ችግር ሁሉ በተደጋጋሚ እንሠቃይበታለን። ይህ እንዳይሆን ከውሳኔው ጋር የተግባር ሰው ለመሆንም ቆርጦ መነሣት ይገባል። ምእመኑ የአባቶችን ትእዛዝ ከዐይኑ ብሌን ባልተናነሰ እየጠበቀ ከስሜት የወጣ የውስጥ አንድነት መፍጠር፣ ጥበብ የተሞላበትን ጉዞ መጓዝ፣ በሆነው ሁሉ የሚሸበረውን ግያዝን ሳይሆን ‹‹ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ›› (፪ነገ.፮፡፲፮) ያለውን ኤልሳዕን በዐይነ ልቡና መቃኘት፣ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የሚመጣበትን አቅጣጫ መምረጥ ይኖርበታል። ሀገሩን፣ ቤተ ክርስቲያኑን፣ ሃይማኖቱን መጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ መተባበርና መደራጀት እንደሚያስፈልግ ተረድቶ ጥቃቅን ከሆኑት መለያየት ወጥቶ የጠነከረ ኅብረት መፍጠር ይኖርበታል። ወጣቱ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደ ተባለው ከአካባቢ፣ ከአጥቢያ፣ ከጎጥ ወዘተ በወጣ እና ሰፊ በሆነ አንድነት መተባበር ይኖርበታል። እንደ ሀገር የሚስተዋለው መለያየት እንደ አጥቢያም ይስተዋላል። ለምሳሌ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ከማኅበረ ካህናቱ፣ ማኅበረ ካህናቱ ከስብከተ ወንጌል ክፍሉ፣ ስብከተ ወንጌል ክፍሉ ከሰንበት ትምህርት ቤቱ፣ … ወዘተ ተናቦ አገልግሎት የሚፈጸምባቸው አጥቢያዎች በጭራሽ የሉም ማለት ባይቻልም ግን ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ እንደዚህ ያለውን መለያየት በማስወገድ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን፣ ሁሉም በፍቅርና በመደማመጥ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዘብ ሊቆም ይገባዋል። መንግሥትም በሕዝብና፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ ይህ ሁሉ መከራ እየተፈራረቀ ዝም ብሎ ማየት አግባብነት እንደሌለው ተገንዝቦ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል። በሚመራው ሕዝብና በሚያስተዳድራት ሀገር ሰዎች በማንነታቸው እየተመረጡ መታረዳቸው፣ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው፣ ከተጎጂዎች ባልተናነሰ ሕመሙ ሊሰማው ይገባል። ሕገ ወጥነት ሰፈነ ሲባል ማጣፊያው የሚያጥረው ለራሱ እንደ ሆነ በመረዳት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የሚመጣበትን መንገድ መቀየስ አለበት። በመንግሥት መዋቅር ሆነው ለሕዝብ ሰላምና ለሀገር ሉዓላዊነት ከመትጋት ይልቅ የግል ጉዳያቸውን ብቻ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱትን ራሱ መንግሥት አትወክሉኝም ሊላቸው ይገባል። ጥፋተኞችም ከእንዲህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር ተቆጥበው ዘመኑን የዋጀ የአመራር ጥበብን፣ የአስተዳደር ስልትን፣ ለእነርሱም ቢሆን የሚጠቅም የኑሮ ዘይቤን ሊከተሉ ይገባል።  
Read 1039 times