Thursday, 21 January 2021 00:00

ታሪኩ

Written by  በመዝሙርና ሥነ ጥበባት አገልግሎት ማስተባበሪ

Overview

ሥራዬን አልወደውም፡፡ ፈጣሪ ሆን ብሎ የፈረደብኝ ይመስለኛል፡፡ ሥራዬን ብተወው ደግሞ እቸገራለሁ፤ ይርበኛል፡፡ እንዳልተወው ችግሩ እያስጨነቀኝ እንዳልቀጥል ደግሞ ጠልቼው ሁል ጊዜም እየተማረርኩ ወደ ሥራ ሄዳለሁ፡፡ እሠራለሁ እሠራለሁ…. ወገቤን … ወይኔ ሲያደክም ደሞ… የሆነ ችክ ያለ ሥራ ነው፡፡ እዚያ አንገቴን ደፍቼ ስቆፍር ስቆፍር እውልና… ፌቴን አጨፍግጌ ሲመሽ ወደ ቤቴ እያዘገምሁ እሄዳለሁ፡፡ መንገድ ላይ ሰው አያወራኝም፡፡ ልብሴ አቧራ ስለሆነ ይሁን… ፊቴ ስለተከሰከሰ… እኔ እንጃ ብቻ…ለነገሩ እኔም ቢያወሩኝ የምመልስላቸው አይመስለኝም፡፡ ደህናና ረዘም ያለ ወሬ ካወራሁ ረጅም ጊዜ ሆኖኛል ፡፡  ወደ ቤቴ ስሔድ እግሬ ለምዶበት ራት ወደምበላበት ቤት ይወስደኛል ገብቼ እንደተቀመጥሁ ከአፍታ በኋላ የተለመደችው ልጅ የተለመደውን ምግብ ታመጣልኛለች፡፡ የምበላውን ስለምታውቅ ሳልነግራት ነው የምታመጣልኝ… ለትዕዛዝ እንኳን አላወራም፡፡ እጄን በውኃ አርስና ቆረስ አድርጌ ወደ አፌ ሳስጠጋ ከንፈሬ ይላቀቃል… በቀስታ እበላለሁ፡፡ አላምጨ ስውጥ ራሱ ሔዶ ሆዴ ውስጥ ሲቀመጥ ድምፁ የሚሰማኝ ይመስለኛል፡፡ 

 

ትክ ብዬ አየዋለሁ የምበላውን ሽሮ ወጥ፡፡ በውስጤ እሰድበዋለሁ፡፡ በልቼ ስጨርስ መልስ እንዳይኖረው አድርጌ ከኪሴ ዝርዝር ፈልጌ ሒሳቡን ከፍዬ እወጣለሁ፡፡ መልስ ያለው ገንዘብ ስሰጥ ያወራሁ ይመስለኛል፡፡ የሆነ አለ አይደል… እየጠበቅሁሽ ነው መልሱን…. ዐይነት፡፡ በቃል ባናወራም ልቦቻችን አይኖቻችን ያወራሉ፡፡ እሱን ነገር አልፈልገውም፡፡ ዝርዝሩን አስቀምጨ እወጣለሁ ወደ ቤቴ፡፡ አንዳንድ ቀን ኪሴ ሲፈቅድልኝ ወደ አረቄ ቤት ጎራ ብየ የነደደውን ውስጤን እንደገና በአረቄ ቅጥልልልል… አረገውና “የታባህና!!” እላለሁ ለራሴ፡፡ ትንሽ ስደጋግም የተለመደው ጥያቄ ወደ አእምሮዬ ይመጣና ትንሽዬ የምጸት ፈገግታ ፈገግ እላለሁ… “ምን ቢያስብ ነው አያቴ ታሪኩ ብሎ ስም ያወጣልኝ???”ይላል መደበኛው ጥያቄ፡፡ 

አባቴ የት ሄዶ እንደሆነ አላውቅም አያቴ ጋር ነው ያደግሁት፡፡ “ምንም የረባ ታሪክ ለሌለው ሰው ታሪኩ ብሎ ስም ማውጣት እንዴት ሞኝነት ነው…” እልና አረቄዬን ወደ ጉሮሮየ ወርወር አድርጌ የተለመደውን ዝርዝር አስቀምጨ ወደ ቤቴ እሄዳለሁ፡፡ ቤቴ የቀበሌ ቤት ነው፡፡ ከሱሪዬ ጋር ታስሮ ተንጠልጥሎ የሚውለውን ቁልፍ ዳበስ አድርጌ እፈልግና  በሩን ከፍቼ ወደ ቤቴ ገብቼ ጋደም ብየ ማሰብ እጀምራለሁ፡፡ ከፈጣሪ ጋር እከራከራለሁ… “ካልጠፋ ሥራ እንዴት መቃብር ቆፋሪ ታረገኛለህ?? ወይ አያዝናና ወይ ደህና ገንዘብ የለው… ምን አስበህ ነው??” እዚህኛው ሐሳብ ላይ ወይ ደግሞ ሌላ ሐሳብ ላይ እንቅልፍ ይዞኝ ይሄዳል፡፡ አንዳንዴ ፈጣሪ ከሰው ሁሉ ለይቶ “ታሪኩ ና ወዲህ… ላንተ የሚሆን ሁነኛ ሥራ አለኝ… እንደምታውቀው ሰው ማለት ሰብል ነው፡፡ መኸር ነው፡፡ ምርቱ ሲሰበሰብ እኔ ፍሬ ፍሬውን ወደኔ ሳመጣ አንተ ገለባውን እየሰበሰብህ ወደ ገደል ክተት፡፡ በል ሂድ፡፡” ያለኝ ይመስለኛል፡፡ የትም ሲባክን የነበረ ሰው ሁላ ማረፊያው የኔ መዳፍ ነው፡፡ ከባለ ሥልጣን እስከ የኔ ቢጤ፡፡ ከሀብታም እስከ ደሀ ሁሉንም እኩል እየተቀበልሁ አስተናግዳለሁ፡፡ እኔ ጋ ይመጣሉ አለቀ ከዚያ በኋላ የትም አይሄዱም፡፡ በዚህ ምክንያት መልአከ ሞት ራሱ “ታሪኩ እንደምን አደርህ አንተ ትልቅ ሰው፡፡” ሳይለኝ የሚውል አይመስለኝም፡፡ ፈጣሪ ነፍስን ወደ ሲኦልና ወደገነት ይሰበስባል፡፡ እኔ ሥጋቸውን ወደ መቃብር እሰበስባለሁ፡፡ በእንዲህ ዐይነት ሥራ እየሠራን መቼም አያየኝም አልልም፡፡ እንደዚህ ስሠቃይ… 

በጣም የምጠላው ነገር ጥሩምባ ነው፡፡ የእድር ጥሩምባ ለኔ በምድር ላይ ካሉ አሠቃቂ እና አናዳጅ ነገሮች አንደኛው ነው፡፡ ካልጠፋ ጊዜ በሐሳብ ስባዝን አምሽቼ ጥሩ እንቅልፍ በምተኛበት የንጋት ሰዓት … ካልጠፋ እቃ ሰቅጣጭ ድምፅ ያለውን ጥሩምባ መርጠው ማጮህ ምን የሚሉት ምቀኝነት ነው?? ይሄ ጥሩምባ ተነፋ ማለት ለኔ “ታሪኩ ሆይ ከጣፋጭ እንቅልፍህ ተነሣና ወደማትወደው ሥራህ ሂድ…” የሚሉት የንጋት መርዶ ነው፡፡ 

እነሣና እሄዳለሁ፡፡ የሆነ ሰው ሞቷል፡፡ ጃኬቴን ደርቤ ባርኔጣየን አድርጌ እጀን በኪሴ እከትና አቀርቅሬ ወደ ፊት ሳላይ እሄዳለሁ፡፡ ዐይኔን ብታሰር እንኳን እግሮቼ ራሳቸው በዘልማድ ቀጥ አድርገው ይወስዱኛል ወደዚያ የመቃብር ስፍራ፡፡

ስደርስ ቀሳውስት ተሰብስበው ዕጣን እያሻተቱ ፍትሐት እየፈቱ የሞተው ሰው ቤተ ሰቦች ጥቁርና ነጭ ደበላልቀው ለብሰው ከበው እያለቀሱ(አንዳንዴ ደክመው ሰው የደገፋቸውም ይመጣሉ) ይታያሉ፡፡ እስኪጨርሱ አካፋየን ተደግፌ አያቸዋለሁ፡፡ አያስቁኝም አያሳዝኑኝም፡፡ ጥቂት ስለ ሬሳው እና ስለ አልቃሾቹ አስባለሁ፡፡ ሰዓቱ ሲደርስ ሬሳውን አስቀድሞ አስተካክየ በቆፈርኩት ጉድጓድ ቀስ አድርገን እንከተውና ተጋግዘን ከየት መጣ ባልተባለ ፍጥነት አፈር እናለብሰዋለን፡፡ ምንድነው ግን እዚህ ጋር ስንደርስ እንደዚህ የሚያስቸኩለን? የሟች ቤተሰቦች እንዳይሳቀቁ ነው? እኔ ራሴ በራሴ እገረማለሁ … ከየት እንደማመጣው ሞራል እና ፍጥነቴን፡፡ ቀኑን ሙሉ ስለፋበት የዋልኩትን አፈር በደቂቃ መልሰን ደፍነነው እርፍ፡፡

የሚቀበሩት ሰዎች ላይ ትንሽ በሐሳብ መጫዎት ልማዴ ነው፡፡ አንዳንድ ሬሳዎች ወፍራም እና በብዙ አልቃሽ ታጅበው የሚመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሕይወት እያሉ ወይ የተመቻቸው ናቸው፡፡ ባለሥልጣን ምናምን ነገር… አንዳንድ ሬሳዎች ደግሞ ጸጥ ረጭ ያሉ ናቸው፡፡ ብዙ አልቃሽ የላቸውም፡፡ የመጡትም ብዙ አያለቅሱም፡፡ አፈር ሳለብሳቸው አብሬ ካልተቀበርሁ ብሎ የሚያስቸግረኝ ሰው የላቸውም፡፡ እንደኔ ምድብ እነዚህ ሰዎች ሰላማዊ ሰዎች ይባላሉ፡፡ አካላቸውም ቀላል ነው፡፡ አይረብሹም፡፡ በጸጥታ ነው የኖሩት እዚህም ሲቀበሩ በጸጥታ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሰላማዊ የምላቸው፡፡ ሌሎቹ ተቀብረውም አያርፉም፡፡ በየቀኑ ስመጣ ሳያቸው መቃብራቸው ላይ ሻማ አበባ ምናምን…ብዙ ጩኸት ሰብስበው ነው ማገኛቸው፡፡ ይህ ለኔ ጩኸት ነው፡፡ እየኖሩም ቅራቅምቦ ያበዙ ነበር ተቀብረውም ያው ናቸው፡፡ 

በየቀኑ እዚህ መቃብር ስፍራ ላይ ነኝ፡፡ ሌላ ቦታ አልሄድም፡፡ ሰው የማይሞትበት ቀን የለም፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ቆይ……ቶ ቆይቶ የሆነ ቀን አመመኝና አልጋዬ ላይ ተኝቼ በጸጥታ አስባለሁ፡፡ እይታዬ እንደ መደብዘዝ አስተሳስቤ እንደ መደንዘዝ እያለ መጣ፡፡ ቤቴ ሰው ገብቶ አያውቅም ነበር፡፡ ትንሽ ዐይኔን ገርበብ አድርጌ ሳይ ቤቴ ውስጥ ሰው ያየሁ መሰለኝ፡፡ በየመሃሉ የሆነ ጥራት የሌለው የማይሰማ ወሬ የምሰማ ይመስለኛል፡፡ ተመልሶ ጸጥ ይላል፡፡ ትንፋሽ እያጠረኝ መጣ፡፡ “ምን ሆኘ ነው ልሞት ነው እንዴ?” አልኩ ለሐሳቤ፡፡ አዎ ነው ማለት ነው፡፡ አልቀረልኝም ሞት ወሰደኝ፡፡ ሌላ ዓለም ውስጥ የገባሁ መሰለኝ፡፡ ሰዎች ተሰበሰቡ ግን አያለቅሱም፡፡ እሰይ እንኳንም አያለቅሱ፡፡ ሰላማዊ ሟች ነው መሆን የምፈልገው፡፡ ሰውነቴን ገነዙኝ እና በእድሩ የሬሳ አልጋ አድርገው ተሸክመው ሲወስዱኝ በጣም ደነገጥሁ፡፡ አሁንም ሞቼም ወደ ሥራ ቦታ ልሄድ ነው?? በሕይወት እያለሁም የማልወደው የሚያማርረኝ ሥራዬ አሁንም ሞቼ ልሄድበት ነው? ምን ዓይነት አለመታደል ነው ይሄ?? ማን ቢረግመኝ ነው እንደዚህ ከሞትም በኋላ የምማረረው?? “አውርዱኝ ወደ ሥራ ቦታ መሄድ አልፈልግም! እቤቴ ውስጥ ቅበሩኝ የሥራ ቦታዬን አልወደውም!” ብየ መጮህ ፈለግሁ፡፡ አልቻልኩም፡፡ ይዘውኝ ሄዱ ድሮ በእግሬ በምሄድባት መንገድ፡፡ ደግሞ ፍጥነታቸው፡፡ ምንድነው የሚያጣድፋቸው?? አናደዱኝ፡፡ ቢያንስ ቀስ ብለው አይወስዱኝም?? 

የመቃብር ቦታው ስንደርስ አውርደው ገጭ አደረጉኝ፡፡ “ኧረ ቀስ! እንዴ ገና ለገና ሞቷል ተብሎ ወገቤን ሊሰብሩት ነው እንዴ?” ቄሶቹ ጸሎተ ፍትሐት ጀመሩ፡፡ በሕይወት እያለሁ ለሌላ ሰው ሲያደርሱ አካፋዬን ተደግፌ እንደማዳምጣቸው አሁንም ዝም ብየ አዳመጥኳቸው፡፡ ሲጨርሱ ከአልጋው አንሥተው የተቆፈረው መቃብር ውስጥ አስተኙኝ፡፡ ምን ዓይነት ቀሽም መቃብር ቆፋሪ ነው የቆፈረው ባክህ…. አይመችም ወጣ ገባ አድርጎ ነው የቆፈረው፡፡ ኤጭ!... ዶማ ዝም ብሎ እጅ እንዳመጣ ይጣላል እንዴ? አቆፋፈርም እኮ ጥበብ አለው፡፡ መቃብር መቆፈር እኮ ኪን ነው፡፡ ዝም ብሎ መሬት ስለሆነ ብቻ በመቆፈሪያ አይደለዝም… ስንት ዓይነት ሰው አለ በናታችሁ፡፡ ወይ ምናለበት የራሴን መቃብር እንድቆፍር ቢነግሩኝ ሳልሞት፡፡ እንዴት አላሰብኩትም? ለዚያ ሁሉ ሰው ፍራሽ የተነጠፈበት አስመስየ ስቆፍር ስደለድል እንዴት ለራሴ መቃብር ሳልቆፍር ቀረሁ? ወይኔ! “እሽ ቢያንስ አፈር ከስር ደልድሉልኝ ይህ ሰውዬ መቃብር ሳይሆን የቆፈረው ተራ ገደል ነው፡፡” ማለት አማረኝ ግን እንዴት..፡፡ ግድ የላቸውም፡፡ አፈር አለበሱኝና ፊታቸውን አዙረው ሄዱ፡፡ ወይኔ ሲቆረቁር…፡፡ 

ነፍሴን መልአከ ሞት ይዞ ወደ ሰማይ እየወጣ እያለ አየሁት… አየኝ… ከፍ እያልን ስንሄድ ብርሃኑ እየተለወጠ የማላውቀው ዓይነት ብርሃን ውስጥ ገባን፡፡ ትንሽ ፍርሀት እየተሰማኝ መጣ፡፡ መልአከ ሞት ለአንድ ሌላ መልአክ አቀበለኝና ያ መልአክ በስተምዕራብ በኩል ይዞኝ ወደ ሲኦል  ነጎደ፡፡ ፈራሁ ጩኸቱ እየበረታ ሰቅጣጭ ድምፁ እየጎላ መጣ፡፡ “ወደየት ነው የምትወስደኝ?” አልኩት፡፡ ጥቂት ዝም ብሎኝ ቆየና… የሆነ ከዚህ በፊት ሰምቸው በማላውቀው ድምፅ “ ዝቅ ብለህ ተመልከት፡፡ ይህ ሲኦል ይባላል፡፡  ለሰባት ቀን ይህንን ትጎበኛለህ፡፡ ይህ በምድር እያሉ ፈጣሪያቸውን አምላካቸውን የረሱ …ኃጢአት ሲሠሩ ሰው ሲበድሉ የነበሩ ነፍሶች መኖሪያ ነው፡፡ አለቃቸው ዲያብሎስ ነው እንደወደደ ያደርጋቸዋል፡፡..” በምን ቋንቋ እንደሚያወራ ባላውቅም ግን ይገባኛል… በልጅነቴ አአትሪኮን፣ ቦርፎሪኮን፣ እና አተርጋዎን የሚባሉ ቋንቋዎች እንዳሉና ከነዚህ ውስጥ የትኛው እንደሆነ ባላስታውስም አንደኛው የመላእክት ቋንቋ እንደሆነ በልጅነቴ የተማርኩት ትዝ አለኝ፡፡ እንዴት ረሳሁት…፡፡ 

የሲኦልን አስፈሪነት ሳይ ልቤ ወከክ አለ፡፡ ብዙ ነፍሶች ገብረተው እየተቃጠሉ ይጮሀሉ፡፡ አጋንንት በላይ በላይ ስቃዩን ያጸኑባቸዋል፡፡ ይጨክኑባቸዋል፡፡ እንባዬ እየፈሰሰ ነበር…፡፡ ነፍሴ እየተንቀጠቀጠች ነው፡፡ ለሰባት ቀናት አስከፊ የሚባሉትን የሲኦል ጉራንጉር ሁሉ የጭካኔን ጥግ አየሁ፡፡ ነፍሴ ለሳምንት ተሸማቅቃ ሰነበተች፡፡ እውነት ለመናገር ሰባቱ ቀናት እንደ ሰባት መቶ ዓመታት ነው የረዘሙብኝ፡፡ መልአኩ በሰባተኛው ቀን መጨረሻ “በምድር ክፉ ሠርተህ ከሆነ ቀሪውን ዘመን እስከ ዕለተ ምጽአት እዚህ ትቆይና ከዕለተ ምጽአት በኋላ ወደ ባሰው ሥቃይ ወደ ገሀነም ትሄዳለህ፡፡ በዚያ ለዘለዓለም ትኖራለህ፡፡ ዓለምም ታልፋለች፡፡” አለኝ፡፡ እኔ ምንም አልመልስለትም በፍርሃት ብቻ አየዋለሁ፡፡ 

ወዲያው ወደ ምሥራቅ ይዞኝ ሄደ፡፡ እጅግ የሚያምር ቦታ ነው፡፡ ገነት ነው አልኩ በውስጤ፡፡ ብዙ ነፍሶች አሉ፡፡ ነጫጭ ናቸው፡፡ ጸዓዳ፡፡ የሚያስጎበኘኝ መልአክ በሚያወራበት ልሳን ነው ሚያወሩት፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ነገር በአንድነት ይላሉ፡፡ “ቅዳሴ ነው?” አልኩት መልአኩን ቀና ብዬ፡፡ “ይህ ገነት ነው፡፡ በምድር ሳሉ መልካም ነገርን የሚያዘወትሩ ደጋግ ነፍሶች መንፈሳዊ ሕይወት የነበራቸው እና ፈጣሪ በምሕረት የጎበኛቸው ናቸው፡፡ ለሰባት ቀናት  በዚህ ትቆያለህ፡፡ በምድር ደግ ነገርን የሠራህ ቢሆን ወይም ፈጣሪ በምሕረት ቢጎበኝህ በዚህ ትኖራለህ፡፡…” እያለ ይዘረዝርልኝ ጀመር፡፡ እኔ በሁኔታው ተደንቄ አፌን ከፍቼ ወደ ገነት እያየሁ ተገርሜ ቀረሁ፡፡ ነፍሴ መለምለም ጀመረች፡፡ በጣም ደስታ ተሰማኝ፡፡ እንዴት እንደሆነ ሳላውቀው ሰባተኛው ቀን አለቀና መልአኩ መልሶ ይዞኝ ሔደ፡፡ 

አሁን ደግሞ ወደ የት ይዞኝ ሊሄድ ነው ስል “ አሥራ አራት ቀናትን ሁሉንም እያየህ ቆይተሀል፡፡ አሁን ፍርድን ወደሚሰጠው ፈጣሪህ ፊት ቆመህ ፍርድህን ትቀበላለህ፡፡” አለኝ፡፡ ወደየት እወድቅ ይሆን ብየ ደነገጥሁ፡፡ 

እጅግ ያማረ አይቼው የማላውቀው ብርሃን ውስጥ ይዞኝ ገባ፡፡ ነፍሴ ከፍርሀት የተነሣ መቆም አልቻለችም፡፡ ጥቂት ቆይቶ አንድ ሌላ መልአክ ሚዛን ይዞ ቀረበና ጽድቅና ኵነኔዬን በግራና በቀኝ አድርጎ አስቀመጣቸው፡፡ በግራ በኩል ከመጠን በላይ አጋደለ፡፡ ኵነኔዬ መብዛቱ ነበር፡፡ ሌላው መልአክ ቆሞ አንድ ተለቅ ያለ መጽሐፍ ይዞ ያነብ ጀመር፡፡ ይሄኛው ጠንቅቆ የሚያውቀኝ ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዷን ሥራዬን ነው እየዘረዘረ የሚያነባት፡፡ ጠባቂ መልአክ የሚባለው ይህ ነው እንዴ? “በቃ አለቀልኝ የሲኦል ራት ሆንኩ” ብየ ተስፋ ቆረጥሁ፡፡ ጥቂት ቆይቶ “ታሪኩ ልጄ እኔ አምላክህ ነኝ፡፡ ሕይወትህን ሙሉ በዝምታ እና በቸልተኝነት ጨረስካት፡፡ በየቀኑ በተግባር የሚመከር ሞትን ፊት ለፊት የሚያይ እንዳንተ ማን ነበር… ነገር ግን ለመሞት አልተዘጋጀህም ነበር … ሞትህን ዐውቀህ ተዘጋጅተህ አታውቅም፡፡ በዕድሜ ካንተ የሚያንሰውን.. በዕድሜ ካንተ የሚበልጠውን … በሀብት ካንተ የተሻለውን …ካንተም የደኸየውን ሞት ወዳንተ ሲያመጣው… ስለምን ልብህ አልደነገጠም? ግብአተ መሬትህን ሲፈጽሙ በስብሶ ስለሚቀር ስለ ሥጋህ ዕረፍት እንጂ ስለ ነፍስህ መውደቂያ ለምን ማሰብ አልቻልክም?  አሁንም ቤትህን አስተካክለህ ለዘለዓለም ሕይወት እንድትበቃ በጎ ሥራንም እንድትሠራ ስለምሻ መላእክት ነፍስህን ከሥጋህ መልሰው ያዋሕዳሉ፡፡ ሕይወትህ ባይታደስ ለጽድቅም ባትበቃ እጣ ፋንታህ ሲኦል ይሆናል፡፡” ብሎኝ ሲጨርስ ያ የሚጣፍጥ ድምፅ ከጎኔ የነበረው መልአክ መለከቱን ጆሮዬ ላይ ነፋው፡፡ 

ድምፁ አስበርግጎኝ ብንን ብየ ነቃሁ፡፡ ቤቴ ውስጥ አልጋዬ ላይ ነኝ፡፡ ቀስ ብየ አማተብኩ፡፡ የቅድሙ መለከት ሚመስለው ድምፅ መልሶ ተነፋ፡፡ የእድሩ ጥሩምባ ነበር፡፡ ዙሪያዬን ቃኘሁ በመስኮቱ እና በበሩ የገባው ደብዛዛ የብርሃን ጭላንጭል ወገግ እያለ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ 

በሕልሜ ነው ወይስ እውነት ሞቼ ነበር?? ከሞትኩ….. ተቀብሬ ነበር…እንዴት አልጋዬ ላይ ሆንኩ አሁን?? እንደዚህ ዓይነት ሕልም አለ እንዴ??  አእምሮዬ በጥያቄ ተወጠረ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ጥሩምባው ከቤቴ አጠገብ መጥቶ ጮኸ፡፡ ደንገጥ ብዬ ተነሣሁና ጫማዬን ለብሼ ልብሴን እንደነገሩ አድርጌ፡፡ ወደ መቃብር ስፍራው በጥድፊያ ሄድኩ፡፡ እርምጃዬ ከወትሮው የተለየበት የመንገዱ ዳር ባለ ሱቅ አንገቱን ወጣ አድርጎ ከዓይኑ እስክሰወር ያየኛል፡፡ ሐሳቤ በሙሉ መቃብር ቦታው ላይ ነው፡፡ እግሬ ስለለመደበት ነው ዝም ብሎ የሚወስደኝ እንጂ መንገዴን አላስተውልም፡፡

ደረስኩ፡፡ ትናንት የቆፈርኩትን መቃብር ሄድኩና አየሁት፡፡ የለቅሶ ድምፅ ሰማሁ፡፡ ሬሳ በአልጋ ተይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ገባ፡፡ ኪዳን እየተደረሰ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን ሦስት ጊዜ አዞሩት እና በወንዶች መግቢያ በር ፊት ለፊት አስቀመጡት፡፡ ቀስ እያልኩ ሬሳውን ብቻ እያየሁ ተጠጋሁት፡፡  ወደ አንድ ጥግ አንሥተው ወሰዱና ጸሎተ ፍትሐት ተጀመረ፡፡ ሐሳቤ ከሕልሜ ሳይላቀቅ ፍትሐቱ እስኪያልቅ ደንዝዤ ቆምኩ፡፡ ስለ ሟች አሰብኩ አሰብኩ… ድንገት አስከሬኑን አንሥተው አራት ሰዎች ሲሸከሙት ከሐሳቤ ገታ አልኩና ወደሚሄዱበት ተከተልኳቸው፡፡ ወደ መቃብሩ ሲደርሱ ከፊት ቀደም ብዬ የቆፈርኩትን መቃብር በሕልሜ እኔን እንደቆረቆረኝ እንዳይቆረቁረው አስተካከልኩለት፡፡ ቀስ አድርገን አስተኛንና አፈር አለበስነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሙት አዘንኩ፡፡ እንባዬ ሊመጣ ፈለገ፡፡ አገድሁት እና ዋጥሁት፡፡ መቃብር ቆፋሪ አያለቅስም!

ሰዎቹ ወዲያው ወደ መጡበት ተመለሱ፡፡ እኔና ሟቹ ብቻ ቀረን በቦታው፡፡ መጨረሻው እኔ ነኝ መጨረሻዬ እሱ ነው… አየሁት በትካዜ አተያይ፡፡ ከጎኑ በጎ ቦታ አየሁና ቀስስስ ብዬ ተነሣሁ፡፡ “ለምን ከመሞቴ በፊት የራሴን መቃብር እዚች ቦታ ላይ እንደምፈልገው አድርጌ ማልቆፍረው??” ራሴን አማከርኩት፡፡ ተስማማሁ፡፡ መቆፈሪያየን አስደግፌ ካስቀመጥኩበት ዛፍ ለማምጣት ስሔድ … አንድ ካህን ዛፉ ስር ቁጭ ብለው ዳዊት ይደግማሉ፡፡ ደነገጥኩና በቆምኩበት እርሳቸውን አሻግሬ ማየት ጀመርኩ፡፡ ቄሰ ገበዙ ናቸው፡፡ ያውቁኛል፡፡ ውስጤ በድጋሜ ተምታታ፡፡  በቀስታ እርምጃዬን የመቆጠብ ያክል ወደ ካህኑ መጠጋት ጀመርኩ፡፡ መቆፈሪያዬ ከጎናቸው ዛፉን ተደግፎ ይታየኛል፡፡ 

ቀስ ብየ ሳልረብሻቸው መቆፈሪያዬን ማምጣት ነው ያሰብኩት፡፡ ወደ ርሳቸው ለመድረስ ጥቂት እርምጃ ሲቀረኝ አንድ የደረቀ ቅጠል ተጠጋሁና ተንኮሻኮሸ፡፡ ባለሁበት ቆምኩ፡፡ “እንደምን አደርህ ታሪኩ…” አሉኝ ጥቂት ካስተዋሉኝ በኋላ፡፡  ወዲያው በሰማይ የሆነው ትዝ አለኝና… ከእግራቸው ስር ቁጭ ብዬ ብዙ ካሰብኩ በኋላ የሆነውን ሁሉ ነገርኳቸው፡፡ አዘኑልኝ… ንስሓ እንድገባ አደረጉኝ፡፡ ቀኖናዬን ተቀብዬ መቆፈሪያዬን አንሥቼ ነገ ሌላ ሰው መሞቱ ስለማይቀር በዝምታ አዲስ መቃብር ስቆፍር ውዬ ሲመሻሽ የራሴን መቃብር መቆፈሩን ለሌላ ቀን ብዬ ወደ ሰፈሬ መንገድ ጀመርኩ፡፡ 

አንደበቴ ከሰው መነጋገር ጀመረ፡፡ በሄድኩበት ሁሉ ከሰዎች ጋር አወራሁ፡፡ ራቴን በልቼ አረቄ ቤቱን አልፌ ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ ፈገግ ብዬ ነበር፡፡ ማታ ሕልም ካየሁባት አልጋ ላይ ጋደም አልኩ፡፡ እረፍት ተሰማኝ፡፡ ሰላማዊ እና ማጉረምረም የሌለበት እንቅልፍ ተኛሁ፡፡  የነገው ጥሩምባ ድምፅ አያነጫንጨኝም፡፡ ይልቁንም ነፍሴን ለንስሓ የሚቀሰቅስ የሚጎሽም መለከት ነው፡፡ አያቴ ልክ ነበር፡፡ ታሪኩ ብሎ ስም ያወጣልኝ፡፡ 

 

Read 1046 times