Wednesday, 28 April 2021 00:00

አሐቲ ቤተ ክርስቲያን ክፍል ሁለት

Written by  ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ እንደሰበከው

Overview

ውድ አንባብያን ባለፈው እትማችን ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? የሚለውን መሠረታውዊ ዕውቀት መረዳት ይቻል ዘንድ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የሰበከውን ተከታታይ ጽሑፍ እንደምናቀርብ ቃል ገብተን የመጀመሪያውን ክፍል አቅርበንላችኋል። በመጀመሪያው ክፍልም የቤተ ክርስቲያንን ምንነት፣ የቤተ ክርስቲያን ባሕርያት አራት እንደሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት። የሚለውን ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ ወር እትማችን ድግሞ ከባለፈው የቀጠለውንና ሁለተኛውን የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ “ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት” የሚለውን አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡- አንድ ሰው ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲያስብ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ማሰብ የለበትም። በፖለቲከኞች ውስጥ አንድ የሚያደርግ  ምንም የእግዚአብሔር መንፈስና ረቂቅ ኃይል የለም። ምድራዊና ጊዜያዊ ዓላማ፣ አሠራርና አስተሳሰብ ነው የሚያሰባስባቸው። በክርስትና ግን እንደዚህ አይደለም፤ በክርስትና ትልቁ ነገር ከእግዚአብሔር ጋራ እንድ መሆን ነው። አሁን ተመልከቱ ክርስቶስ ሳያድርብን ስለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ነው እኛ መቆርቆር የምንችለው? አናስብ ማለት አይደለም ግን ሐሳባችንን እንኳን በየትኛው መንገድ ልናቀርብ እንደሚገባን እንድናውቅ ነው። አንድ ሰው ንስሐ ሳይገባ፣ ሳይቈርብ፣ እውነተኛ ሳይሆን፣ ክርስቶስ በእርሱ ሳያድር እንዴት ሆኖ ስለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መናገር ይችላል? በጣም ከባድ ነው። በመናገራችን አንድነቱ የሚመጣ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፤ በመናገራችን ሳይኾን የክርስቶስ በመሆናችን ነው አንድነቱ የሚመጣው። በሁላችንም ክርስቶስ ከአደረ፥ የክርስቶስ ማደሪያ ከኾንን አንድ መሆናችን አይቀርም። አሁን ከክርስቶስ የተለየን ሽፍቶች ተጣልተን ምን አንድነት ልናመጣ እንችላለን? ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት በዚህ አንድነት ማመን አለብን። ክርስቶስ እንዳለው እርሱ በእኛ ማደር ይፈልጋል፤ ለሚያንኳኳው ጌታ የልባችንን በር ከፍተን ልናስገባው ያስፈልጋል። 

 

በተለይ ከተሐድሶ (reformation)፣ ከ፲፮ኛው መቶ ክ/ዘመን፣ ከነሉተር መነሣት በኋላ በ፲ ሺዎች የሚቆጠሩ የእምነት ተቋማት ተቋቁመዋል። የእንትና ቤተ ክርስቲያን፣ የነእገሌ ቤተ ክርስቲያን የሚሉ በዝተዋል፤ ብዙዎቻችን አሁን የሚነሣብን ጥያቄ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ከኾነች ለምን እንዲህ ተከፋፈለች? የሚል ነው። በተጨማሪም ወይም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሚባል ተቋም፤ (WCC- World council of Churches) አለ። ይህን ተቋም በአብዛኛው የመሠረተው የፕሮቴስታንቱ (Protestant) ዓለም ነው። እነርሱ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት የሚለውን ሊክዱ ስለማይችሉ እንዴት ነው ታዲያ እንደዚህ ተከፋፍላችሁ አንድ ነን ልትሉ የምትችሉት? ተብለው ሲጠየቁ ምሁራኖቻቸው ምንድን ነው የሚሉት? በWCC አንድ ነን፤ ነው የሚሉት። እንደ እነሱ አባባል የወይን ግንዱ WCC ሆነ ማለት ነው።  “ሁላችንም በክርስቶስ አምነናል በእዚያ እምነት ስንገናኝ በWCC አንድ እንኾናለን” ይላሉ። WCC የመጣ በ፳ኛው መቶ ክ/ዘመን ገና ፪፻ ዓመት እንኳን ያልሞላው ተቋም ነው። በዚህ አንድ ማኅበር አቋቁሞ እንዴት አንድ መሆን ይቻላል? ይህ ቀላል ጉዳይ አይደለም፤ ትልቁ የሃይማኖት ጥያቄ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ እምነት ካለ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ከሆነች፣ እንዴት ነው ይህ ሁሉ ክፍልፋይ አንድ ሊሆን የሚችለው?

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ስናጠና በዐፄ ዮሐንስ አንድኛ ዘመነ መንግሥት  ቅባትና ጸጋ የሚባሉ ኑፋቄዎች ነበሩ። እነርሱም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ያውኩ ስለ ነበረ ጉባኤ ተካሂዷል። የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አማናዊቱን ሃይማኖት መስክረው መናፍቃኑ ተረቱ። በዚህ ጉባኤ አስገራሚው ክሥተት ቅባቶችና ጸጎች የተለያዩ ኾነው ሳለ በአንድ ሆነው አባቶቻችንን ሊከራከሩ መጡ። በዚህ ጉባኤም የተዋሕዶው ሊቅ ሃይማኖት ስንት ናት? አላቸው። እነሱም አንድ እንዳይሉ ሁለት ናቸው፤ ሁለት እንዳይሉ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ይላል። ጨነቃቸውና ዝም አሉ፤ ምን ያህል መሠረታዊ ጥያቄ እንደሆነ መመልከት ይገባል። የቤተ ክርስቲያን አንድነት መሠረታዊ ጉዳይና የመናፍቃን ሁሉ መውጊያው ነጥብ ነው። እግዚአብሔር ይህን እውነት ተረድተን እንድንኖር ይርዳን። አሁን የፕሮቴስታንት አስተዋይ ምሁራን ይህን መሠረታዊ ጥያቄ መጠየቅ አለባቸው። ሃይማኖት አንድ ነው፤ ጌታ እንዳለው መንጋው አንድ ነው፤ እረኛውም አንድ ነው። ሌላ በረት የለም፤ በረቱም አንድ ነው። የነእገሌ የሚባል በረት የለም፤ ሌላ በረት ያሉትንም አመጣቸዋለሁ ነው ያለው ጌታ። 

ከአንድነት ሳንወጣ ሁለት ጥቅሶችን እናንሣ ይህ ቅርንጫፎቹን በተመለከተ በመኃልየ መኃልይ በምዕራፍ ፮፥፰-፲ "ስድሳ ንግሥታት፣ ሰማንያ ቁባቶች፣ ቍጥር የሌላቸው ቈነጃጅት አሉ፤ ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት፤ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት፤ ቈነጃጅት አይተው አሞገሷት።" ይላል። መኃልየ መኃልይ ከተለዩ የተለየ መዝሙር ነው፤ የተለየ ምስጋና ነው፤ የተለየ ምሥጢር ነው። ይህ የተነገረው ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ነው። ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት የሚላት ቤተ ክርስቲያንን ነው። ቅዱስ ኢጲፋንዮስ በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በእነቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘመን የነበረ የአሁንዋ ቆጵሮስ ሊቀ ጳጳስ ይህን አመስጥሮ እንዲህ ብሏል። እነዚህ ፷ ንግሥታት ፹ ቁባቶች ቍጥር የሌላቸው ቈነጃጅት የተባሉት  በክርስቶስ ስም የተከፈቱ ብዙ የሃይማኖት ድርጅቶች ናቸው። በዚህ ዓለም ያሉ እነዚህና ወደፊት የሚከፈቱት ሁሉ የአንድ ወንድ ናቸው። በሴተኛ አዳሪዎች መስሎ ማለት ነው፤ የሚያልፈው ወንድ ሁሉ እኔ ጋ ይገባል፤ እያሉ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ልክ  እንደዚሁ ሁሉ ክርስቶስ ያለው እኔ ጋር ነው፤ እኔ ጋር ነው፤ እያሉ ተስፋ ያደርጉታል። 

ነገር ግን ለክርስቶስ ያለችው ሙሽራይቱ አንዲት ናት፤ እርሱ የሚያድርባት፤ የሚዋሐዳት፤  አካሉ የሆነችው፤ አንዲት ናት። እርሷ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ የተባለችው አንዲት ቤተ ክርስቲያን ናት። ይህን በማነጻጸር ያመሠጠረውም በእርሱ ዘመን በሀገረ ስብከቱ መልስ የሰጠባቸው ፹ የሚሆኑ የሃይማኖት ድርጅቶች ስለነበሩባት ነው። ይህ ቅዱስ አባት በ፬ኛው መ/ክ/ዘ እነዚህ ፹ ቁባቶች እነዚህ ናቸው ይላቸዋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል ርግቤ አንዲት ናት፤ መደምደሚያዬ አንዲት ናት፤ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፤ እኔም ከእርሷ ጋር ነኝ። የእኔን ስም ስለ ጠራችሁ ብቻ፣ በእውነት ካልፈለጋችሁኝ ወደ እናንተ አልገባም፤ ብሎ በትንቢት አንቀጽ የተናገረበት ነው፤ ይላል። 

እነዚህ ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ስም የተቋቋሙ እንደ ቁባት ያለፈውን ወንድ ሁሉ ተስፋ እንደሚያደርጉ ሴቶች ይቈጠራሉ። በእውነት ምሥጢሩን ሳንረዳ ‘ምን ችግር አለው? እዛም ወንጌል ነው፤ እዚህም ወንጌል ነው፤’ ማለት አይገባም። ስሙንማ አጋንንትም ይጠራሉ፤ በእርሱ የማያምኑ ደቂቀ አስቄዋ ስሙን ይጠሩ ነበረ፤ ተአምራትም ያደርጉ ነበረ። ይህ ሁሉ ሰዎቹን የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አካል አያደርጋቸውም። የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አካል የሚያደርገን ዋናው ክርስቶስ በእኛ አድሮ በአንዲት እምነት፣ በአንዲት ጥምቀት፣ በአንድ ሥጋ ወደሙ፣ ስንኖር ብቻ ነው። በዚህ እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን።

፪ኛው ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት፡- ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት የሚለው ብዙ ነገር የሚያስነሣ ነው። "ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ ጵርስፎራ ከመ ብከ ንሕየው፤ አቤቱ የአንተ በሆነ መንፈስ ቅዱስ አንድ እንድንሆን እርዳን፤ በዚህ በሥጋ እና በደምህ አድነን አንድ አድርገን ባንተ ሕያው እንኾን ዘንድ።" እያልን ነው የምንጸልየው። ያለ ሥጋውና ደሙ አንድነት የለም፤ ሁልጊዜም የምንጸልየው በዚህ አንድነት ነው። የምንጸልየውን በእውነት የምንሰማው ከሆነ ከላይ እንደተገለጸው በአባ ብንያም ታሪክ እንደተፈጸመው፣ ከእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ጋር አንድ ሆነን እነአባ መቃርስ እንዳሉት፣ ሰማዕታቱ እነቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ባሉበት፣ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢራትን በሚፈጽምበት፣ ሁላችንን በሚባርክበት፣ በሚያነጻበት፣ አንድነት ውስጥ ነው የምንኖረው። አሁንም እግዚአብሔር ይህን አስተውለንና አክብረን እንድንጠቀም ይርዳን።  

ስለ ቤተ ክርስቲያን ቅድስትነት ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፳፭ ላይ በሰፊው ተንትኖልናል። ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ሲባል ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ባል እና ሚስት በተናገረበት አንቀጹ ዘርዝሮ ሲናገር "እደውኒ ያፍቅሩ አንስትያሆሙ ከመ ክርስቶስ አፍቀራ ለቤተ ክርስቲያን ወመጠወ ርእሶ በእንቲአሃ፤" ባሎች ሚስቶቻቸውን በፍጹም ይውደዱ፤ እንዴት አድርገው ይውደዱ? ትለኝ እንደሆነ ክርስቶስ ቤተ ክርቲያንን እንደ ወደዳት ይውደዷቸው። ይልና ወረድ ብሎ "ቤተ ክርቲያን ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤" ይላል። ቤተ ክርስቲያን ምንም ነውር የለባትም። ይህ በጣም ታላቅ ነገር ነው፤ ከላይ እንደገለጽነው ቤተ ክርስቲያን የምድራውያንና የሰማያውያን አንድነት፥ የቅዱሳን ኅብረት ናት። ስለዚህ ቅድስና የሌለው ሰው ገብቶ  አይሠራም። በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል። እናንተም በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ ነው የተባለው። 

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ ልዩ ልዩ ድንጋዮች ይገባሉ፤ ዳሩ ግን ሳይስተካከሉ፣ ሳይጠረቡና ሳያምሩ በዘፈቀደ አይከመሩም። ለግንቡ በሚስማማ መልክ ተስተካክለው እንደሚቀርቡትና ያልተስተካከሉት ድንጋዮች ግንብ ውስጥ እንደማይገቡት ሁሉ ልክ እንዲሁ እኛ ምእመናንም የክርስቶስ አንድ ሕያው ቤተ መቅደስ ለመኾን በንስሓ፣ በምግባራተ ሠናያትና በተጋድሎ መስተካከል አለብን። በቅድስና፣ በነቢያትና በሐዋርያት ከሚሠራው የቅድስና መቅደስ ጋር አብረን ለመሠራት ያን መልክ መምሰል አለብን። የትኛውን መልክ? የቅዱሳንን መልክ፤ እሱ ምንድን ነው? ቅድስና፤ ያለ ቅድስና አንሠራም ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ሲባል እንዲሁ ድንጋዩ ሁሉ ቅዱስ ነው ለማለት አይደለም። በዚያ የሚገኙ ግዑዛኑ ሁሉ ይባረካሉ፤ ቅድስናው ግን የእኛ የአማኞቹ ነው። 

ስለዚህ አንድ ሰው የቤተ ክርስቲያን አባል ነኝ ማለት የሚችለው በቅድስና ከቅዱሳን ጋር ኅብረት ሲኖረው ብቻ ነው። አንድ ቀላል ምሳሌ ላምጣና ላስረዳ የምንጠቀምበት ኮምፒውተር (Computer) ኔትዎርክድ (Networked) የሆኑ በገመድ ተገናኝተው የአንዱን መረጃ ሁሉም የሚያገኙበት አውታረ መረብ አላቸው። በዚህም መሠረት እዚያ ያለውን ኮምፒውተር እዚህ ያለው ኮምፒውተር ያውቀዋል፤ ያገኘዋል። ልክ እንደዛው በቅድስና ጉዞ ላይ ያለ አማኝ እንደዚያ ነው የሚሆነው። ምን ማለት ነው? የቅዱሳኑ ገንዘብ ሁሉ የኛ ይሆናል የኛ ገንዘብም የእነሱ ይሆናል። አንድ ነን፤ አንድ ላይ ተሳስረናል፤ ተያይዘናል፤ አሁን ከዛ በረከት ከወጣን  ተቆርጠን ወድቀናል ማለት ነው። ከግንዱ ተቆርጣ የወደቀች ቅጠል ግንዱ ላይ ያሉ ቅጠሎች የሚያገኙትን ምግብ ልታገኝ አትችልም። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ስንል የቅዱሳን አንድነት ናት ማለታችንም ነው። የሰበካ ጉባኤ አባል መሆን እንችላለን፤ የሰንበት ት/ቤት አባል መሆን እንችላለን፤ የሆነ ማኅበር አባል መሆን እንችላለን፤ የቤተ ክርስቲያን አባል ላንሆን ግን እንችላለን። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የምትባለው የቅዱሳን አንድነት ናትና። ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስለ ኾነች ቅድስና የሌላቸው፣ ንስሓ የማይገቡ ደንዳኖችና ኀጢአተኞች ሰዎች ከቅዱሳን ጋር አንድ ሆነው አይቆጠሩም፤ ሊቆጠሩም አይችሉም። እንዲህ ካልኾነ ግን ቅዱሳንን መስደብ፣ እግዚአብሔርንም መዝለፍ ነው። 

ስለዚህ እኔ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አባል ነኝ የምንል ከሆነ ቅድስናችንን እንጠብቅ። አናመንዝር፣ አንስረቅ፣ አንዋሽ፣ ኃጢአትንም ሠርተን እንደኾነ ንስሓ እንግባ፤  ቅድስናው ሲኖረን ከቅዱሳን ጋራ ኅብረት ይኖረናል። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ማለት ተጋድሎዋቸውን ያልጨረሱ ምእመናንና ተጋድሎዋቸውን የጨረሱ ቅዱሳን አንድነት ናትና። ቅድስት ናት የምንላት ይህችን ነው፤ ይህን አንድነት ነው ቅድስት የምንለው። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን ምን መሆን ይጠይቃል ማለት ነው? ቅድስና። መታወቂያና ሰርተፊኬት ብቻውን በቂ አይደለም፤ እርሱ በምድር ላይ ላለው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ይጠቅማል እንጂ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን የሚጠቅመው ቅድስና ነው። ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያን እኛን ለመቀደስ የምትደክመው። ቃለ እግዚአብሔር ታስተምረናለች፣ ታጾመናለች፣ ታሰግደናለች፣ ኃጠአታችንን እንድንናዘዝ ታደርጋለች፣ ተናዘዙ ትላለች፣ ከስህተታችሁ ታረሙ ትላለች፣ ቀኖና ትሰጠናለች፣ አለባበስ፥ አካሄድ አኗኗር፥ አስተካክሉ ትለናለች። እንቀደስ ዘንድ ታዘጋጀንና አባሎቿ ታደርገናለች። 

አማኞችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባላት ሳይኾኑ ሸንግለን ብንልካቸው ምንም ጥቅም የለውም። የባሰውን ፍርድ በመቀበል እንቀጣለን እንጂ፤ ተያይዞ መጥፋት ነው ትርፉ። ተሰብስበን ተምረን፣ ጾመን፣ ጸልየን፣ ሰግደን፣ መጽውተን፣ የሰበካ ጉባኤ አባል ብንኾን፣ አሥራት በኩራት አውጥተን ቅድስና ከሌለን ምን ዋጋ አለው? በአንድ በኩል እየገነባን በአንድ በኩል የምንንድ ከሆነ ምን ፋይዳ አለው? እነዚህን ነገሮች እየፈጸምን መልሰን በኃጢአት ከናድናቸው ምንም ትርጕም የለውም። ስለዚህ አንድ ሰው በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አምናለሁ ሲል ምን ማለቱ ነው? ያለ ቅድስና ከቅዱሳን አንድነት መጨመር እንደማይቻል አምናለሁ እያለ ነው። መቀደስ እንደሚያስፈለገኝ አምናለሁ፤ ያለ ቅድስና በባሕርይው ቅዱስ የሆነ ጌታዬ የወይኑ ግንድ ቅዱስ ስለ ኾነ ቅርንጫፉ እኔም ቅዱስ መኾን አለብኝ ማለቱ ነው። ቅዱስ ግንድ ላይ ርኩስ ቅርንጫፍና ፍሬ ሊኖር አይችልም፤ "ወእምፍሬሆሙ ተአምርዎሙ ይቀሥሙሁ እምአሥዋክ አስካለ፤ ወእምአሜከላ በለሰ፤ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ ወይን፥ ከአሜከላም በለስ ይለቀማልን?"  (ማቴ.፯፥፲፮) ያለው ለዚህ ነው። የእኛም ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ስንል የቅዱሳን አንድነት ናት፤ ያለ ቅድስና  ወደዚያ  ማኅበር መቀላቀል አይቻልም፤ በመንፈስ አብሮ መሠራት አይቻልም። ተጋድሏቸውን ያልጨረሱ የሚለው ቃል የሚገልጸው ይህን ነው። ተጋድሏችን ምን ለመሆን ነው? ለመቀደስ ነው። ውጣ ውረዱ፣ ገዳም መሳለሙ፣ መጾሙ፣ መጸለዩ፣ መስገዱ፣ መታረቁ፣ የቀሙትን መመለሱ፣ የበደሉትን መካሱ፣ ይህ ሁሉ ለመቀደስና የቅዱሳንን አንድነት ገንዘብ ለማድረግ ማለትም የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን ነው። 

ለምሳሌ አሁን ከኛ መሐል አንድ ሰው ስለ ሠራው በጎ ሥራ የክብር ዶክትሬት ቢሰጠው በጣም ይደነቃል። ምክንያቱም ልክ ሳይማርና በዚያ የትምህርት ሥርዐት ሳያልፍ ከእነዚያ ጋር የሚተካከል ሥራ ስለ ሠራ ለዚያም ክብር ስለበቃ ነው የሚደነቀው። ወይም አሁን ከመካከላችን አንዱ አያድርግበትና ስለ ሠራው በጎ ሥራ ብላ አሜሪካ የምትባል ሀገር የክብር ዜግነት ሰጥቼዋለሁ ብትል ሰው ሁሉ እንኳን ደስ አለህ አይለውምን? እኛም የቅዱሳንን ዜግነት ለማግኘት ነው የምንደክመው። አንድ ሰው የአንዲት ምድራዊት ሀገር ዜግነት አገኘ ተበሎ እንኳን ደስ አለህ የሚባል ከሆነ፣ የቅዱሳንን ሀገር ዜግነት ማግኘት ምን ያህል ደስ ያሰኛል? ቤተ ክርስቲያንን፣ ምድራዊ ተቋሟን እንደ ኤምባሲ ልንወስዳት እንችላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የአሜሪካ ኤምባሲ የሚሠራው ለማን ነው? ለአሜሪካ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የምትሠራው ለሰማያዊው መንግሥት ነው። እዚያ ሀገር ስንሄድ ዜግነታችን ቅድስና ነው። 

ስለዚህ ሰዎችን ታዘጋጅና (ታሠለጥንና)፣ ጾም ምስጋና ታለማምድና፣ የመላእክትን ሥራ፥ የቅዱሳንን ሥራ አለማምዳ፣ የቅዱሳንን ዜግነት ሰጥታ ወደ ሰማያዊት ሀገራቸው፣ ወደ ዋናው ሀገራቸው ትልካቸዋለች ማለት ነው። ዓላማዋ ይህ ነው፤ ጉባኤ የሚዘረጋው፣ አባቶች የሚያገለግሉት፣ የምትናዘዙት፣ መዝሙር የሚዘመረው፣ ቆመን የምንናገረው፣ ሌላ ምንም ዓላማ የለውም። ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ሲባል በዋናነት ከእኛ የራቀ አንድን ሕንጻ፣ ገዳም፣ ቅዱስ ነው ብሎ ማመን አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ማለት እኛ ራሳችን መቀደስ አለብን፤ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን አንድነት ናትና ወደዚያ ማኅበር መግባት አለብን፤ ሰማያዊውን ዜግነት ማግኘት አለብን፤ ወደዚያ የሚያሳልፈውን ቅድስና የሚባል ደብተርና ፓስፖርት ወይም ቪዛ ከቤተ ክርስቲያን ማግኘት አለብን፤ ሥጋ ወደሙ የሚባል ማኅተም ማሳተም አለብን፤ ያን ጊዜ የእነርሱ አባል፣ ዜጋ ሆን ማለት ነው። የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በቤተ ክርስቲያን ማመን ማለት ይህችን አንዲትና ቅድስት ጉባኤ ፥ ይህን የቅዱሳን አንድነት  በደንብ አድርጎ ማመን ማለት ነው። ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያን ከእኛ ከስብስባችን በላይ ናት የምንል። አሁን እኛ ስንሰበሰብ ቢያንስ የእያንዳንዳችን ጠባቂ መላእክት አሉ። በቅዳሴያችን ጊዜ "ሠራዊተ መላእክቲሁ ለመድኃኔ ዓለም ይቀውሙ ቅድሜሁ ለመድኃኔ ዓለም፤ የመድኃኔ ዓለም ሠራዊት በፊቱ ይቆማሉ።"  የመድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ሥጋውና ደሙ ሲፈተት እሱ ራሱ ሲለውጥ፣ እሱ ራሱ ሲቀድስ፣ ሲያነጻ፣ መላእክት ይከባሉ። እንደ አሸን ረግፈው (ወድቀው) ነው፤ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው መላእክት አይረገጡም፤ መናፍስት ናቸውና በእግረ ሥጋ አይረገጡም። ግን የሉም ማለት አይደለም፤ አሉ፤ ስላሉም ነው የምንጠራቸው። 

ምስጋናችን፣ ቅዳሴያችን፣ ማሕሌታችን ሁሉ የሚናገረው ይህን አንድነት ነው። ቅዱሳን የሌሉበት አንድነት ምን ያደርግልናል? ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ማለት የእነዚህ የቅዱሳን ስብስብ ናት ማለት ነው። እነዚያ ዛሬ መታሰቢያ የሚደረግላቸው ቅዱሳን አሉ። ስማቸውን ስንጠራ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ስታነቡ ተጠንቀቁ ይላል። አንድ ቅዱስ ገድሉ፣ ድርሳኑ ወይም ተአምሩ ሲነበብ ራሱ ቅዱሱ መጥቶ ይቆማል፤ ድርሳኑ የእሱ ቃል፣ ታሪኩ የእሱ ታሪክ፣ ተአምሩም የእሱ ተአምር ነዋ! የእግዚአብሔር መንፈስ እኮ ከዚህ ከሞገዱ ይበልጣል፤ በዚህ በሞገዱ፣ በስልክ፣ በኢንተርኔት እንኳን እንገናኛለን። እንኳን መንፈሰ እግዚአብሔር ሳይንሱ በፈጠረው ሞገዱም የተራራቀው መገናኘት ችሏል። በእግዚአብሔር ጥበብ የበለጠ ነው የምንተሳሰረው። ስለዚህ ከቅዱሳን ጋር አንድነት አለን። በዚህ ዓለም ላይ በአውሮፕላን እንደምንሄደው ቅዱሳንም መጓጓዣ የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። 

ቅዱሳን በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠኑ ናቸው፤ የሚያጓጉዛቸው፥ የሚያመጣቸው፥ ከእኛ አንድነት የሚደምራቸው፥ በባሕርይው በሁሉ የመላው፣ ምሉዕ  የሆነው እግዚአብሔር ነው። እርሱ መንፈስ ነው፤ የሌለበት ቦታ የለም፤ የሚሳነው ነገር የለም፤ ከእኛ ጋር አንድነት አላቸው፤ ይህን ቅድስና ለማግኘት ስንጋደል ደስ ይላቸዋል። በቅዱስ ወንጌል  "እላችሃለሁ እንዲሁ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ደስታ ይሆናል።" (ሉቃ.፲፭፥፲) በማለት ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው እግዚአብሔርን ፈልገነው ወደዚህ ኅብረት ስንመጣ ይደሰታሉ። ዛሬ ጠባቂ መላእክቶቻችን በእኛ ፍላጎትና ጥረት ደስ ይሰኛሉ። እስከ መጨረሻው እነሱን ለማስደሰትና የቅዱሳን አንድነት ማለትም የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን ያብቃን። እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ እስከዚህ ሰዓት በቸርነቱ ጠብቆ በመግቦቱ ሳይለይ ቅዱስ የሆነ ቃሉን አንብበን እንድንጠቀምበት የቅዱሳን አምላክ አባታችን መድኃኒታችን አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን። ስለ ቤተ ክርስቲያን ይህን ያህል እንድንገልጽ የረዳን አምላክ የተመሰገነ ይሁን። ይቀጥላል…

 

Read 1220 times