Saturday, 02 January 2021 00:00

ቅጽል

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ውድ አንባብያን ባለፈው ዕትማችን ግልጠ ዘ ቅጽሎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ማቅረባችን ይታወሳል። የቀረበውን ትምህርት መሠረት አድርጋችሁም ግልጠ ዘ ብለን በዘረዘርናቸው ቅጽሎች በእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዐረፍተ ነገሮችን እንድትሠሩባቸው የቤት ሥራ መስጠታችን ይታወሳል። መልሳችሁን ለማረጋገጥ ያህል እንደሚከተለው እንመልሳቸው። “ዘ” ብፁዕ ብእሲ ዘኢሖረ በምክረ ረሲኣን፤ በዝንጉዎች መንገድ ያልሄደ ምስጉን ነው። (መዝ.፩፥፩) ዘወረደ እምሰማያት ዐርገ ውስተ ሰማያት፤ ከሰማያት የወረደው ወደ ሰማያት ዐረገ። “እንተ” ፡- ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህቺ ናት። (መዝ.፻፲፯፥፳፬) ብፅዕት ብእሲት እንተ ታፈቅር ብእሲሃ፤ ባሏን የምትወድ ሚስት ብፅዕት ናት። “እለ” ወተገሠፁ ኵልክሙ እለ ትኴንንዋ ለምድር፤ እናንተ የምድር ፈራጆች ተገሠፁ። (መዝ.፪፥፲) ብፁዐዓን ኵሎሙ እለ ተወከሉ ቦቱ፤ በእርሱ የታመኑ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። (መዝ.፪፥፲፪) ውድ አንባብያን መልሱ ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም በዚህ መልኩ በልዩ ልዩ መንገድ ሊሠራ ይችላልና ይህንም ልብ ማለት ያስፈልጋል። የቅጽል ሙያ ቃላት በማንኛውም ሰዋስዋዊ መዋቅር ውስጥ ያለአንዳች ሙያ አይቀመጡም። ቅጽልም ከቃል ክፍሎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን በማንኛውም ሰዋስዋዊ መዋቅር ሲገባ ሙያ አለው። ባለፉት ተከታታይ ዕትሞቻችን ምንነቱንና ክፍሎቹን ተመልክተናል። በዚህ ዕትማችን ደግሞ ቅጽልን በተመለከተ የመጨረሻ የሆነውን የቅጽልን ሙያ እንመለከታለን። ቅጽል በስም ላይ ተጨምሮ ስምን ከመጠን፣ ከግብር፣ ከፀባይ፣ ከዓይነት ወዘተ አንጻር የሚገልጽ የቃል ክፍል ነው። ይህን በተመለከተ መምህር ደሴ ቀለብ ትንሣኤ ግእዝ በተሰኘ መጽሐፋቸው “ቅጽል በስም ላይ እየተጨመረ የስምን ኩነት፣ አካል፣ መልክእ፣ ቅርጽ፣ ቅርበት፣ ርቀት፣ ዓይነት፣ መጠን፣ ወይም ማንነት የሚገልጥ የስም አጎላማሽ (ገላጭ) ነው።” በማለት ይገልጹታል። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘ መጽሐፋቸው “ቅጽል በስምና በግብር የሚጨመር ቃል የአካልንና የግብርን አኳሆን ጠባዩን፣ መልኩን፣ የሚገልጥና የሚያስረዳ ነው” (ገጽ ፰፻፬) በማለት ይገልጹታል። ከሁለቱም ምሁራን እንደምንረዳው ቅጽል በስም ላይ ተጨምሮ ስሙን ከመጠን፣ ከዓይነት፣ ከግብር፣ ከፀባይ ወዘተ አንጻር የሚገልጽ፣ ስለ ስም ተጨማሪ መረጃ የሚሰጥ የቃል ክፍል መሆኑን ነው። ከዚህ በመነሣት የቅጽል ሙያ ምንድን ነው? ብለን ስንመለከት የገላጭነት ሙያ አንዱ መሆኑን እንረዳለን። በተሻለ መልኩ ግልጽ ለማድረግ በምሳሌ እንመልከተው። መጠንን የሚገልጹ ቅጽሎች ፡- ነዊኅ፣ ሐጺር፣ ንኡስ፣ ብዙኅ፣ ዐቢይ…  ብዙኅ ሰብእ መጽአ ኀበ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ጸሎት፣ በጸሎት ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን  ብዙ ሰው መጣ። ነዊኅ ብእሲ ይትአመር በኀበ ኵሉ ሕዝብ፤ ረጅም ሰው በሁሉ ሕዝብ ዘንድ  ይታወቃል። ሐጺር ዘኬዎስ ኢክህለ ይርአይ ክርስቶስሀ ዘእንበለ ይቁም ላዕለ ኦም፤ አጭር ዘኬዎስ ዛፍ ላይ ሳይቆም ክርስቶስን ማየት አልቻለም። ንኡስ ወልድ ኢክህለ ይጹር ዕርፈ፤ ትንሽ ልጅ ዕርፉን መሸከም አልቻለም። ግብርን የሚገልጹ ቅጽሎች፡- ሐናጺ፣ ሐራሲ፣ ቀዳሲ፣ ጸሓፊ፣… ሐናጺ ሰብእ ገብረ ማኅደረ፤ አናጺ ሰው ቤትን ሠራ። ሐራሲ ወልድ የሐርስ ገራህተ ለአቡሁ፤ አራሽ ልጅ ለአባቱ እርሻን ያርሳል። ቀዳሲ ካህን ይትረከብ ቅድመ ውስተ ቤተ መቅደስ፤ ቀዳሽ ካህን አስቀድሞ ከቤተ መቅደስ ውስጥ ይገኛል። ጸሓፊ መምህር ጸሐፈ መጽሐፈ፤ ጸሓፊው መምህር መጽሐፍን ጻፈ።  ዓይነትን የሚገልጹ ቅጽሎች፡- ጸዐዳ፣ ጸሊም፣ ቀይሕ፣… ቀይሕ ብእሲ ቀነየ ጸዐዳ ላሕመ፤ ቀዩ ሰው ነጭ ላምን ገዛ። ጸሊም ብእሲ ያፈርህ ሕፃናተ፤ጥቊር ሰው ሕፃናትን ያስፈራል። ፀባይን የሚገልጹ ቅጽሎች፡- ሠናይ፣ እኩይ፣ የዋህ፣ ኄር፣ … የዋህ ብእሲ ይገብር ምሕረተ ለነዳያን፤ የዋህ ሰው ለችግረኞች ምሕረትን ያደርጋል። እኩይ ብእሲ ይወስድ ሀብተ ዘኢኮነ ዘዚኣሁ፤ ክፉ ሰው የእርሱ ያልሆነውንም ሀብት ይወስዳል። የባለቤትነት ሙያ፡- ቅጽል በዐረፍተ ነገር ውስጥ በገላጭነት እንደሚገባ ሁሉ በባለቤትነትም ይገባል። በዚህ ጊዜ በቃል ክፍሉ ቅጽል ሆኖ በሙያው ግን በስም ቦታ ገብቶ ስምን ተክቶ ባለቤት መሆን ይችላል። ለምሳሌ፡-  ሐራሲ ሐረሰ ገራህተ፤ አራሽ እርሻን አረሰ። ጸሓፊ ጸሐፈ መጽሐፈ፤ ጸሓፊ መጽሐፍን ጻፈ። ቀዳሲ ቀደሰ ቅዳሴ፤ ቀዳሽ ቅዳሴን ቀደሰ። ከላይ በምሳሌነት በቀረቡት ዐረፍተ ነገሮች ባለቤቶች በቃል ክፍላቸው ቅጽሎች ሲሆኑ በሙያ ደረጃቸው ግን ባለቤት ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለዚህ ቅጽል በስም ላይ ተቀጽሎ ስምን የሚገልጽ ብቻ ሳይሆን በስም ቦታም ገብቶ እንደስም ሁሉ ባለቤት ወይም ድርጊት ፈጻሚ ይሆናል ማለት ነው።   
Read 1021 times