Friday, 04 September 2020 00:00

ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ (ዘሌዋውያን. ፲፱፥ ፲፰)

Written by  እንድርያስ ስንታየሁ

Overview

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁ? መልካም፤ እግዚአብሔር አምላካችን የተመሰገነ ይሁን፡፡ ልጆች የእግዚአብሔር ቃል ነውና ሰው ራሱን እንደሚወድ ባልንጀራውን መውደድ እንዳለበት ዛሬ እንማራለን፡፡ ከዐሥርቱ ትእዛዛት ውስጥም ዐሥረኛው ባልንጀራህን ወይንም ጓደኛህን እንደራስህ ውደድ ይላልና ነው፡፡ (ዘሌዋውያን. ፲፱፥ ፲፰) ልጆች! እናንተ ወላጆቻችሁን ‹አባዬ እወድሃለሁ፤ እማዬ እወድሻለሁ› ትላላችሁ አይደል?  ሁሉም እናቱንና አባቱን ስለሚወድ ነው፡፡ ታዲያ የምንወዳቸው በአንደበታችን በመናገር ብቻ  መሆን የለበትም፡፡  መውደድ በተግባር መገለጽ አለበት፤ ይህም ማለት እነርሱ ሲያሳድጉን ትምህርት እያስተማሩ የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ አሟልተው ነው፤ ማለትም ልብስ፣ ጫማ፣ ቦርሳ፣ ደብተር፣ እስክርቢቶ እና መጫወቻ ገዝተው በእንክብካቤ ያሳድጉናል፡፡  የእነርሱ መውደድ በተግባር ተገለጸ ማለት እንደዚህ ነው፡፡ እናንተ ደግሞ ባልንጀራችሁን በመውደድ ጥሩ ነገር ማድረግ አለባችሁ፡፡ ልጆች ባልንጀሮቻችሁ የወላጆጃችሁ ጓደኞች ልጆቻቸው፣ በትምህርት ቤት እና ከጎረቤት የምትተዋወቋቸው ሕፃናት ማለት ናቸው፡፡ እነርሱም የዕድሜ እኩዮቻችሁ በመሆናቸው አብረዋችሁ ይማራሉ፣ ያጠናሉ እንዲሁም ይጫወታሉ፡፡ በመሆኑም ልክ እንደራሳችሁ ልትወዷቸው ይገባል፡፡ ለእናንተ የተደረገላችሁ ነገር ለእነርሱም እንዲረግላቸው ማሰብ ይጠበቅባችኋል ማለት ነው፡፡ 

 

ይህም ስታጠኑ እንዲያጠኑ መንገር፣ ስትበሉ እንዲበሉ፣ ስትጠጡ እንዲጠጡ መጋበዝ እና ስትጫወቱ በሥርዓቱ ከእነርሱ ጋር መጫወት ይጠበቅባችኋል፡፡ ጓደኞቻችሁ ሲታመሙም ልታዝኑላቸው እና ለአስተማሪዎቻችሁ ነግራችሁ እንዲታከሙ ልትረዷቸው ያስፈልጋል፡፡ 

ነገር ግን መጣላት አያስፈልግም፡፡ ልጆች! አንዳንድ ሥርዓት የሌላቸው ሕፃናት ሰበብ እየፈለጉ ሊረብሷችሁ ይችላሉ፡፡ አብረዋችሁ ሲቀመጡም ደብተራችሁን በመውሰድ፤ በመቅደድ ወይንም በእርሳስ እና በእስክሪቢቶ በመሞነጫጨር ሊያናድዷችሁም ይችላሉ፡፡ ስትጫወቱ ተራችሁን ሊወስዱባችሁ ወይንም ገፍተው ሊጥሏችሁም ይችላሉ፤ ሆኖም እናንተ ለአስተማሪዎቻችሁ መንገር ነው እንጂ መጣላት ወይንም መስደብ የሰነፍ ልጅ ጠባይ ነው፡፡ እነዚያን ተማሪዎችም ተመክረው ጎበዝና ጥሩ ልጆች እንዲሆኑ ካደረጋችሁ እግዚአብሔር በእናንተ ደስ ይለዋል፤ ይወዳችኋልም፡፡  

ልጆች! አምላካችን እግዚአብሔር እርስ በርስ እንድንዋደድ ያዘዘን አብረን በፍቅር እንድንኖር ነው፤ ፍቅር ካለ ሁሉም ደስተኛ ይሆናልና፤ በቤትም ሆነ በትምህርት ቤት ከቤተሰቦቻችሁና ከአስተማሪዎቻችሁ ጋር  በደስታ ትውላላችሁ፤ ትኖራላችሁ፡፡ ሁላችንም ፍቅር ቢኖረን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሚሆን በሽታ እንዳይዘን ይጠብቀናል፡፡ አሁን የመጣው መድኃኒት የሌለው የኮሮና በሽታ ወደ ሀገራችን አይገባም ነበር፡፡ ልጆች ራሳችሁን ለመከላከል በየዕለቱ ጭንብል ማድረግ ወይንም ከሰው በሁለት ሜትር ርቃችሁ በፍራቻ እንድትሄዱም አይደረግም ነበር፡፡ 

ስለዚህ ልጆች! እግዚአብሔር እኛን ከበሽታ ሁሉ ይጠብቀን ዘንድ ባልንጀራችንን ልንወድና እርስ በርስ ልንዋደድ ይገባል፡፡ ካልተዋደድን ግን እርሱ በእኛ ስለሚያዝንና ስለሚቆጣ ከበሽታም ሆነ ከችግር አይጠብቀንም፡፡ 

የእግዚአብሔር ጥበቃ እንዳይለየን በፍቅር እንኖር ዘንድ ፈጣሪያችንን ይርዳን፤ አሜን፡፡      

 

 

 

 

 

 

Read 79 times