Monday, 05 October 2020 00:00

የዋሁ ነቢይ                                                                             

Written by   ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ 

Overview

ተወዳጅ የሆናችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከርማችኋል? በእግዚአብሔር ጥበቃ በሰላምና በጤና እንደቆያችሁን ተስፋ እናደርጋለን፤ በቤታችሁ ሆናችሁ ትምህርታችሁን በንቃት እየተከታተላችሁ ነው? በጣም ጎበዞች! በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋልና በርቱ! ልጆች! ዛሬ ስለአንድ ነቢይ ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ በጥሞና አንብቡ እሺ! መልካም፡፡  ዮናስ የሚባል አንድ ነቢይ ነበር፤ የስሙ ትርጉሙም ርግብ ወይንም የዋህ ነው፡፡ በአንድ ወቅትም እግዚአብሔር አምላክ ‹‹ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ነነዌ ሂድ ከክፋታቸው እንዲመለሱ ስበክ›› በማለት አዘዘው፡፡ ዮናስ ከትውልድ ሀገሩ ወጥቶ በአሕዛብ ሀገር እግዚአብሔርን ወደማያውቁ  ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል የሰበከ ብቸኛ ነቢይ ነው፡፡  እግዚአብሔር ሲያዘው ዮናስ ግን  እግዚአብሔር መሐሪ ስለሆነ ‹‹ከጥፋት ቢያድናቸው ውሸታም እባላለሁ›› ብሎ ፈርቶ በጀልባ ከነነዌ ወጣና ከእግዚአብሔር ፊት እምቢ ብሎ እግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ ተነሣ፡፡ ኢዮጴም ወደምትባል ሀገርም ሄደ፡፡ ወደ ተርሴስ የምታልፍ መርከብ አገኘ፡፡ ከእግዚአብሔር ለመሸሽ ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ከፍሎ ወደ መርከቧ ገባ፡፡ 

 

እግዚአብሔርም ዮናስ በተሳፈረበት መርከብ በምትጓዝበት ባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስ አመጣ፡፡ ማዕበልም ተነሣ፤ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች፤ መርከበኞቹም ፈሩ፤ እያንዳንዳቸውም ወደ አምላካቸው ጸለዩ፡፡ መርከቢቱ ከማዕበሉ አደጋ ድና ጉዞዋን እንድትቀጥል በውስጧ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፤ መርከበኞቹ ያንን ሁላ ጭንቀት ሲጨነቁ  ዮናስ ግን እንቅልፉን ተኝቶ ነበር፡፡ 

የመርከቡ አለቃ ወደ አንቀላፋው የዋሁ ነቢይ ወደ ተኛበት ቀርቦ ‹‹ምነው ተኝተሃል? ተነሥተህ አምላክህን ጥራ›› አለው፤ ዮናስም ከእንቅልፉ ተነሣ፡፡ መርከቡም በማዕበል እንደተናወጸችና ተሳፋሪዎቹም እንደተጨነቁ አየ፡፡ መርከበኞቹ እርስ በርሳቸው ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ ዕጣ እንጣጣል›› ተባባሉ፤ ዕጣም ተጣጣሉ፡፡ 

ልጆች ዕጣው በማን ላይ የሚወድቅ ይመስላችኋል?

ዕጣው ከእግዚአብሔር ሊሰወር ሊሸሽ በሞከረው በዮናስ ላይ ወደቀ፡፡ ዮናስንም ‹‹ማዕበሉ እንዲቆም ምን እናድርግ?›› አሉት፡፡ ዮናስም ‹‹ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃችኋልና እኔን ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ያን ጊዜ ባሕሩ ጸጥ ይልላችኋል›› በማለት ነገራቸው፡፡

ምንም እንኳን ዮናስ በራሱ ላይ ቢፈርድም ሰዎቹ ግን እርሱን ለማዳን ወደ ምድር ለመቅዘፍ ሞከሩ፡፡ ነገር ግን ባሕሩ አብዝቶ ይናወጥ ነበር፡፡ በመጨረሻም እግዚአብሔር እንዳያዝንባቸው ጸልየው ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ባሕሩም ከመናወጥ ጸጥ አለ፡፡ ሰዎቹ እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ ስዕለትም ተሳሉ፡፡

እግዚአብሔር ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አንበሪ አዘጋጀ፡፡ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ቆየ፡፡ በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሆኖ እጅግ ስለተጨነቀ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፣ ልመናም አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም የዮናስን ጸሎት ሰማ፡፡ ዓሣውንም አዘዘው፤ ዓሣውም ዮናስን ወስዶ በየብስ (በምድር) ላይ ተፋው፡፡

ልጆች! እግዚአብሔር የሚያዘንን እየፈጸምን በታማኝነት ማደግ አለብን፡፡ የትም ብንሄድ ወይንም በየትኛውም ቦታ ብንደበቅ እግዚአብሔር ያየናል፡፡ ከፊቱም መሸሽ አይቻልም፡፡ እግዚአብሔርን በመከራ ጊዜም ስንጠራው ጸሎታችንን ሰምቶ ያድነናል፡፡ በመከራም ጊዜም እግዚአብሔርን መለመን ይገባናል፡፡

ዮናስ ከዓሣ አንባሪው ሆድ ከወጣ በኋላ ወደ ታላቂቱ ከተማ ነነዌ ሄደ፡፡ ‹‹ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ ንስሐ ግቡ፤ በሦስት ቀን ነነዌ ትጠፋለች›› እያለ በከተማዋ አስተማረ፡፡ የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም ዓዋጅ ነገሩ፤ ሁሉም ማቅ ለበሱ፤ ሦስት ቀን ጾሙ፤ ጸለዩም፡፡

እግዚአብሔርም በሕዝቡ መመለስ ተደሰተ፡፡ ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፡፡ ቁጣውን በምሕረት መለሰ፡፡ ዮናስ ግን ተቆጣ፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይቅርታ ማድረጉ አላስደሰተውም፡፡ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፡፡ ‹‹በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህን አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፣ ታጋሽ፣ ምሕረትህም የበዛ አምላክ እንደሆንክ አውቄ ነበርና፡፡ ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኮብለል ፈጥኜ ነበር፡፡ አሁንም ከሕይወት ሞት ይሻለኛል፡፡ አቤቱ እባክህ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ›› አለ፡፡

የዋሁ ነቢይ ዮናስም ደክሞት ተቀመጠ፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር ቅል አዘጋጀ፡፡ ቅሉም ለዮናስ ጥላ እንድትሆን ከፍ ከፍ አደረጋት፡፡ ዮናስም ስለ ቅሉ እጅግ ደስ አለው፡፡ በማግሥቱ ግን ቅሉን ትል በላው፤ ደረቀም፡፡ ዮናስንም እስኪዝል ድረስ ፀሐይ ራሱን መታው፡፡ በዚህን ጊዜ ዮናስም ተቆጣ፡፡ እግዚአብሔር ዮናስን ‹‹አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምክባት፣ ላላሳደግሃትም በአንድ ሌሊት ለበቀለች ቅል ካዘንክ እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን ለማያውቁ ከመቶ ሃያ ሺሕ ለሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሳት አላዝንምን?›› አለው፡፡

የዋሁ ነቢይን እግዚአብሔር አምላክ በቅል፣ በትል እና በፀሐይ አማካኝነት ያስተምረውን ትምህርት ተቀብሎ በነነዌ ሰዎች መዳን፣ በእግዚአብሔር መሐሪና ቸርነት ተደስቶ በሰላም ኖረ፡፡ በመስከረም ሃያ አምስት ቀንም የዋሁ ነቢያ ዮናስ በመቶ ሰባ ዓመቱ ሞተ፡፡ 

ልጆች! እግዚአብሔር መሐሪ፣ ታጋሽ ቸርና ይቅር ባይ ስለሆነ በምሕረቱና በይቅርታው ደስ ይበላችሁ፡፡ 

ለየዋሁ ነቢይ አምላክ እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በነቢዩ ጸሎት ይማረን! በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ፤ አሜን፡፡

ምንጭ፡ ትንቢተ ዮናስ፤ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መስከረም  

 

 

Read 698 times