Monday, 05 October 2020 00:00

ለመልካም ዕሴቶቻችን ትኩረት እንሰጥ                                   ክፍል አንድ

Written by  ረቂቅ መቻል

Overview

በየዘመኑ ልብ ብለን ካስተዋልን  ብዙ የሚያስደስቱ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ዓመታት በተፈራረቁ ቁጥር የሚያበሳጩና አግራሞት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ተመልክተን ወይም ሰምተን ማለፋችን አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንዴም አስተማሪ የሆኑ ጉዳዮችን ልናይ እንችላለን፡፡ ታዲያ በዚህ ዓመት  ካስተዋልኳቸው ትዝብቶቼ መካከል አንዱን ለእናንተ ለማካፈል ወደድሁ፡፡  የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የተፈጠረበትን ዓላማ ዘንግቷል፡፡ መልካሙን ከማድረግ፣ የሚጠቅመውንና የሚበጀውን ከመፈጸም በተቃራኒው ከእግዚአብሔር ሕግጋት ርቆ ክፋትን በማመንጨት፣ በተንኮልና በቅናት ተነሣሥቶ በሌላው ላይ ጥፋት ከመፈጸም የተቆጠበበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ቃየል ወንድሙን አቤልን በቅናት እንደገደለው ሁሉ  አሁን አሁን በሀገራችን አንዱ በአንዱ ላይ በመነሣት ከንብረት ማውደም እስከ ደም ማፍሰስ ድረስ የክፋት መገለጫ የሆኑ ሥራዎች ሲፈጸሙ ማየት የተለመደ ግብር ሆኗል፡፡ ታዲያ እኔም ዕድሜ ለመንገዴ ብዬ አንድ አካባቢ ላይ እየተፈጸመ ያየሁትን ትዝብቴን እነሆ ብያለሁ፡፡ ራሳቸውን የበላይ ለማድረግና “የእኔ ብቻ” በሚል አስተሳሰብ ላይ በመመርኮዝ ሌላውን በጦርነት ለማንበርከክ ሲጣደፉና እርስ በእርስ ደም ለማፋሰስ ሲቻኮሉ የታዘብኳቸውን የአካባቢው የጸጥታ ዘርፍ ባለሙያዎችና የማኅበራዊ ድኅረ ገጽ አርበኞችም መመልከት ለኔ የዓመቱ የተለመደ ትዕይንት ነበር፡፡ 

 

 ዓለማችን የክፉ ሥራ መገለጫ የሆኑ ተግባራት ሲፈራረቁባት ኖራለች፡፡ ይህንን የሚደግፉ አካላት ግድያ፣ ዝሙት፣ መዳራት፣ ግብረ ሰዶም፣ ጦርነትና ዝርፊያ፣ …. የመሳሰሉትን  ዛሬም ድረስ የሥጋ  ግብራቸው እንዲሆን  በመትጋት ላይ ናቸው፡፡  ታዲያ ውስጤ በጣም ያዝንና እነዚህ ሰዎች ትውልድ እንዲቀጥል አይፈልጉም ማለት ነው እላለሁ፡፡   አሁን አሁን በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎችና ግለሰቦች እነዚህ ድርጊቶች ከነውርነት አልፈው በአደባባይ ሲፈጸሙ፣ እንደ ዘመናዊነት እየተቆጠሩም ይገኛሉ፡፡ 

ከዚህም አልፎ ሰዎች በአንድነት ክፉውንና ደጉን አብረው በመተሳሰብ፣ በፍቅር የኖሩበት ዘመን ተረስቶ አዳዲስ ትርክቶችን በመፍጠር፣ ዘመኑ ያፈራቸውን የጦር መሣሪያዎችና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የጥፋት እጆቻቸውን ሲሰነዝሩ እንመለከታለን፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ  “ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ” ተብሎ እንደተጻፈ ዓለማችን የፍቅርና የሰላም መገለጫ ከሆኑት መልካም ምግባራት ርቃ የጦርነትና የሽብር ዐውድማ ሆናለች፡፡ በዚህም ምክንያት በዘመናችን ዕለት ዕለት እየሰማን ያለነው የጦርነትና ሽብር ወሬ ነው፡፡

አሁን አሁን ለእኔም ሆነ ለሌሎች ወገኖቼ  በሀገራችን በኢትዮጵያ በብሔር፣ በሃይማኖትና በዘር በመከፋፈል ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በአሠቃቂ ሁኔታ ሲጠፋ፣ ለዘመናት ያፈሩት ቤት ንብረት ሲወድም ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ስጋትና ሽብር፣ ስደትና እንግልት ዘወትር የምንሰማውና የምናየው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ደግሞ በብሔራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ተከባብሮ፣ በፍቅር፣ በሰላም እንዲሁም በጋብቻና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ዕሤቶች ለዘመናት ተሳስሮ የኖረ ሕዝብን እንዳይተማመን ከማድረግ አልፎ ለእርስ በእርስ እልቂት የሚዳርግ ነው፡፡

በተለይም ወጣቱ ትውልድ አስተሳሰቡ በአውሮፓውያን መርዛማ የባሕል ወረራ በመመረዙ ቀድሞ ባልነበረ አዳዲስ የታሪክና የማንነት ትርክት ተጠምዶ ክቡር በሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ላይ የጥፋት በትሩን በማሳረፍ ሕይወትን እየቀጠፈ፣አካልን እያጎደለ ሀብት ንብረትንም እያወደመ ይገኛል፡፡ 

ለመነሻ ያህል ከላይ ያነሳኋቸው  ዐበይት ትዝብቶቼ ሲሆኑ  ወጣቱና የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ሌሎች ለግል የፖለቲካ ፍጆታና ለእኩይ ተግባራቸው  መፈጸሚያ በቀደዱለት ቦይ ዝም ብሎ መፍሰሱ ሳይ ዝም እንዳልል ተገደድኩ፡፡

ጽንፈኛ የሆኑ አካላት  በጎሳና በብሔር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ቦይ እየተጓዙ ለዘመናት በበርካታ መልካም ዕሤቶች ተጋምዶ የኖረውን ሕዝብ ለመለያየት ሕዝብን ከሕዝብ እያፋጁ የሴረኞች ዓላማ ማሳኪያ መሣሪያ ሆነዋል ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህም ሲባል ሴረኞች ወጣቱን በስሜታዊነትና ራሱን መግዛት ባልቻለ አእምሮው ውስጥ መርዛማ የበቀል ጥንስሳቸውን በመጋት የጥፋት ተልእኮአቸው ማስፈጸሚያ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሴራቸውም ውስጥ የእናቶችና የሕፃናት ዋይታና ሰቆቃ፣ የአዛውንቶች እንግልት ሳይገዳቸው የጥፋት ክንዳቸውን እየዘረጉ ናቸው፡፡ ውሎ ሳያድር ከዚህ ወደሚከፋ ሀገርን ወደ ሽብርና አለመረጋጋት በመውሰድ ሰዎች እርስ በርስ ከመተባበር ይልቅ ወደ መፈራራት፣ ከመፈራራትም አልፎ ሳይቀድመኝ ልቅደመው ወደሚል አስተሳሰብ ውስጥ በመግባት ምድሪቱን የደም መሬት ለማድረግ ይሽቀዳደማሉ፡፡ 

ብዙዎች በተወለዱበትና እትብታቸው በተቀበረበት፣ ክፉና ደጉን ካዩበት ቀዬ መጤ እየተባሉ የመከራ ሰይፍ ሲመዘዝባቸው፣ ቤትና ንብረታቸው የእሳት ሲሳይ ሲሆን፣ ቤተሰብ ሲበተን፣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ የድረሱልን ጩኸት ሲጮኹ በዓይናችን ማየቱ፣ በጆሮአችን መስማቱ  የዓመቱ ስንክሳር ሆኖ ሳይደረስ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ በተለይ አንዳንድ እናቶችና እኅቶች በየቤተ ክርስቲያኑና በየሚዲያ መስኮቱ እንደ ራሔል ዕንባቸውን ወደ ሰማይ እየረጩ ማየቱ የሚያሳዝንና አቤቱ ጌታ ሆይ ወዴት ነው ያለኸው የሚያሰኝ ከሆነ ሰነባብቷል ፡፡ 

በቅዱስ መጽሐፍ “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” (መዝ.፷፯፥፴፩) እንዳልተባለች ዛሬ የንጹሓን ደም እንደ ጎርፍ ሲፈስባት፣ በብሔር ፖለቲካ ተተብትባ በተንኮለኞች የተቀበረው የክፋት ፈንጂ ፈንድቶ የብዙዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ አካላቸው ሲጎድል፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለስደት፣ ለእንግልትና ለረኀብ በመዳረግ ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ለጥፋት መሣሪያነት እየዋለ ያለው ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ 

 በጣም የሚሳዝነው ጉዳይ አሁን ያለው ጽንፈኛ ኃይል ሀገር ተረካቢውና ነገ ይህችን  ሀገር ይመራል  ተብሎ የሚጠበቀው ትውልድ  የዚህ  ሰለባ  ማድረጉ ሳያንስ ወጣቱን ወደ ልማት በማዞር ከድህነት ለመውጣት ከመፍጨርጨር ይልቅ አሁን ላይ ጥፋትን መተዳደሪያው እያደረገ ማየቱ ነው፡፡ 

“በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍን ምክር ከአእምሮው አውጥቶ በመጣል ጥፋትን እንደ በጎ ተግባር ደጋግሞ በመሥራት ላይ የተሰማራው ይህ አካል ለዚህ  በምክንያትነት የሚጠቀሱ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም  በዋናነት ግን ከእግዚአብሔር ሕግጋትና ከመልካም ሥነ ምግባር ማፈንገጥ፣ወጣቱ ትውልድ ዘመናዊነትን በማይገባ መንገድ በመረዳትና በመተግበር ኢትዮጵያዊ ዕሤቶችን በመጣል ራሱን ለአውሮፓውያንና ለመሰሎቻቸው መጤ ባህልና ሴራ ተጋላጭ ያደረገ ይመስላል፡፡ በዚህም ቀድሞ የነበረውን እግዚአብሔርን የመፍራትና ክብር ለሚገባቸው ክብርን የመስጠት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ዕሤቶችን አሽቀንጥሮ በመጣል በዘመናዊነት ካባ ሥር ተወሽቆ ለሌሎች እኩይ ተግባር ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ በሃይማኖት ስምና በብሔር ፖለቲካ በሚነግዱ ቡድኖችና ግለሰቦች እጅ ላይ ወድቋል ቢባል ሐሰት አይደለም፡፡ 

 

Read 611 times