Saturday, 26 December 2020 00:00

ጾም

Written by  ቀሲስ ዘክርስቶስ ጸጋዬ

Overview

የተወዳዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁ? መልካም፤ እግዚአብሔር አምላካችን የተመሰገነ ይሁን።  ባላችሁበት ሆናችሁ ትምህርታችሁን  በጥሞና ተከታተሉ!  ልጆች! ለዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ትምህርት ስለ ጾም ነው።  በመጀመሪያ ጾም ምን ማለት እንደሆነ እና እናንተ ሕፃናት ከሰባት ዓመት ዕድሜያችሁ ጀምሮ እንዴት መጾም እንዳለባችሁ እናስተምራችኋለን።   ልጆች! ጾም ማለት ክርስቲያን የሆነ ሰው ሁሉ ለተወሰነ ጊዜና ሰዓት ከእህል ከውኃ ተከልክሎ መቆየት ማለት ሲሆን ከሥጋ፣ ከቅቤና፣ ከእንቁላል ደግሞ እንድንጾምባቸው የተወሰኑ የአጽዋማት ሳምንታት እስኪጠናቀቁ የምንከለከልበት ወቅት ማለት ነው።  (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭) ከዚያም በተጨማሪ ጾም ዓይን ክፉ ከማየት ጆሮ ክፉ ከመስማት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፣ እጅ ክፉ ከመሥራት በአጠቃላይ ሰውነት የኀጢአት ሥራ ከመሥራት የሚገታበት፣ የሚከለከልበት ሁኔታ ማለት ነው።   ጾም የአዋጅ እና የፈቃድ ተብሎ በሁለት ይከፈላል።   ሀ. የዐዋጅ ጾም የዐዋጅ አጽዋማት በቤተ ክርስቲያን ለምእመናን ሁሉ አውቀውት በአንድነት የሚጾም ጾም ነው።  ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው።  ‹‹በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ ጉባኤውንም ዐውጁ›› (ኢዩ. ፪፥፲፭) የዐዋጅ ጾሞች ሰባት ናቸው።  እነርሱም፤ የነቢያት ጾም፣ የገሃድ ጾም፣ የነነዌ ጾም፣ ዐቢይ ጾም፣ የሐዋርያት ጾም፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ)፣ ጾመ ፍልሰታ ናቸው።    ለ. የፈቃድ ጾም የፈቃድ ጾም  ደግሞ ራሳችን አስበንና ፈልገን የምንጾመው ጾም ነው።  የፈቃድ ጾም ሁለት ናቸው፤ የጽጌ ጾም እና ጾመ ዮዲት ተብለውም ይጠራሉ።  ይህም ጥፋት ወይንም ኀጢአት ስንሠራ ለንስሓ (ይቅርታን ለማግኘት) ስለሚረዳን እንጾመዋለን።    ልጆች! እያንዳንዱን ጾም የምንጾምበት ምክንያት አለን።  ለምሳሌ አሁን ያለንበት ወቅት የነቢያት ጾም የሚጾምበት ነው፤ ከኅዳር ፲፬ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፰ ድረስም ይጾማል።   ይህን ጾም ነቢያት የአምላክን መወለድ በተስፋ በመጠበቅ ስለጾሙት እኛም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ተወልዶ እንዳዳነን በማመን እስከ የልደት በዓል ዋዜማ ታኅሣሥ ፳፰ ድረስ እንጾመዋለን።   ልጆች! ወደፊት ስለተቀሩት የዐዋጅ እና የፈቃድ አጽዋማት ወቅታቸውን እየጠበቅን በተናጠል እናስተምራችኋለን።  ለዛሬ ግን በዚህ ይብቃን፤ በሚቀጥለው ትምህርታችን እስክንገናኝ በጸሎትና ጾም እንድትበረቱ እንመክራችኋለን፤ በደኅናም ሰንብቱ! የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነትና የእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለያችሁ።  
Read 647 times