Wednesday, 07 April 2021 00:00

እንደ ራባቸው ሊሄዱ አይገባም

Written by  ቀሲስ ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ቃሉን የተናገረው ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የተናገረበት ምክንያት ከየአቅጣጫው የተሰበሰቡት ሕዝብ ለተለያየ ፍላጎት እንደሆነ ያውቃልና ከፍላጎታቸው አንዱ ደግሞ አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት “በሉ እጅግም ጠገቡ ለምኞታቸውም ሰጣቸው። ከወደዱትም አላሳጣቸውም” (መዝ.፸፯፥፳፱) ተብሎ እንደተነገረ ኅብስት አበርክቶ ያበላናል ብለው የመጡ ነበሩ። እነዚህ ከየሰፈሩ የተሰበሰቡት ሰዎች እንደተራቡ ያውቃልና ደቀ መዛሙርቱ ቀድሞ እንዲያሰናብታቸው ሲጠይቁት “የሚበሉትን ስጧቸው እንጂ እንደራባቸው ሊሄዱ አይገባም” በማለት ተናገረ። ሙሉ ፅንሰ ሐሳቡን እንጥቀስና ዝርዝር ጉዳዩንም  እንመለከታለን። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው በቅዱስ ወንጌል “ጌታችን ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ በታንኳ ሆኖ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከየመንደሩ በእግር ተከተሉት። በወጣም ጊዜ ብዙ ሰዎችን አይቶ አዘነላቸው፤ ድውዮቻቸውንም አዳነላቸው። በመሸ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው ቦታው ምድረ በዳ ነው ሰዓቱም አልፏል፤ ወደ መንደር ገብተው ምግባቸውን ይገዙ ዘንድ ሕዝቡን አሰናብታቸው አሉት። ጌታችን ኢየሱስም እንደራባቸው ሊሄዱ አይገባም እናንተ የሚበሉትን ስጧቸው እንጂ አላቸው።” (ማቴ.፲፬፥፲፫-፲፮) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን።

 

ሰው የሚቸገረው በምግብ ብቻ አይደለም። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሊፈትነው ለመጣው ጠላት ዲያብሎስ  የመለሰለት መልስ በቅዱስ  ወንጌል “ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይኖር ተጽፏል አለው” (ማቴ.፬፥፬) ተብሎ እንደተጻፈ ከቃለ እግዚአብሔር የተለየ ይኖራል፤ የጤና ችግር ያለበት  ይኖራል፤ ከጎኑ ሆኖ አይዞህ የሚለው አጥቶ በብቸኝነት የሚቸገር ሊኖር ይችላል፤ በሥነ ልቡና ተጎድቶ ችግር ላይ የወደቀ ሊኖር ይችላል፤ በእንደዚህና በሌላውም መሰል ችግር የወደቀ ሰው ረኃብተኛ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በዋናነት ወደዚህ ዓለም የመጣው ድኅነተ ነፍስን ለሰው ልጅ ሁሉ ለማደል ቢሆንም ድኅነተ ሥጋንም እንዲሁ አድሏል። ከላይም እንደተገለጸው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ከወደዱትም አላሳጣቸውም” (መዝ.፸፯፥፳፱) በማለት እንደተናገረው በልዩ ልዩ ፍላጎት የመጡትን እንደየችግራቸውና እንደየ ፍላጎታቸው አስተናግዷቸዋል።

ሰዎቹ የሚደረግላቸው የአቀባበል ሁኔታ ትልቅ ዋጋ አለው። ሰው ለችግሩ መፍትሔ ከማግኘቱ በፊት መልካም አቀባበል ሲያደርጉለት እጅግ ደስ ይለዋል። አበው በብሂላቸው “ከፍትፊቱ ፊቱ” እንዲሉ። ወደ መፍትሔ ከመሄድ አስቀድሞም ችግሩ ምንድን ነው? ብሎ ሊረዱት ይገባል። በተረዱት መጠንም ሊያዝኑለትና የሚችሉትን ለማድረግ መወሰን ያስፈልጋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ዐይቶ አዘነላቸው” እንደተባለ ችግራቸውን ተረድቶ አዘነላቸው። 

አሁን ያለንበት ወቅት እንደሚታወቀው ታላቁ ጾም ጾመ ኢየሱስ ነው። ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታም ስንመለከት በሰው ሰውኛው ችግሩን መፍታት ይቅርና ዘርዝረን መጨረስ እንኳን አይቻለንም። ስለሆነም የጀመርነውን ጾም መጾም ባለብን አግባብ ብናከናውነው አሁን ያለንበትን ሀገራዊ ችግርም ለመፍታት ያግዘናል። በማንኛውም ጊዜ መልካም ነገርን ለመፈጸም መትጋት ቢኖርብንም ከመቼውም ጊዜ በላይ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት መትጋት ይኖርብናል። ለምሳሌ፡-  ከጾም ጋር አብረው ሊፈጸሙ የሚገባቸው ወይም ከጾም የማይነጣጠሉ ተግባራት አሉ። ይህን በተመለከተ በርቱዐ ሃይማኖት እንዲህ ተጽፎ እናገኛለን። “በጽሐት ጾም እመ ኵሉ ምግባራት ጸሎት እኅታ ወምጽዋት ወለታ ለሠለስቲሆን አሐዱ ብሔሮን ወአሐዱ አቡሆን፣ ወአሐቲ እሞን እስመ ይትወለዳ ጥዩቀ እምቅድስት ማኅፀን ዘውእቱ ሃይማኖት በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ የምግባራት ሁሉ እናት የሆነች ጾም ደረሰች፤ ጸሎት እኅቷ፣ ምጽዋት ልጇ ናቸው። ለእነዚህ ለሦስቱ ሀገራቸው አንድ ነው፤ አባታቸው አንድ ነው፤ እናታቸውም አንዲት ናት፤ ከተቀደሰች ማኅፀን ተወልደዋልና። ይኸውም አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ማመን ነው” (ምንባብ ዘጥንተ ጾም) እንዲል። 

በዚህ ምንባብ የማይነጣጠሉ ሦስት ነገሮችን እነዚህ ሦስት ነገሮች ደግሞ የሚወለዱባትን (የሚገኙበትን) የተቀደሰች ማኅፀን እንመለከታለን። ጾም የበጎ ምግባራት ሁሉ መገኛ ስትሆን ጸሎት እኅቷ፣ ምጽዋት ደግሞ ልጇ እንደሆነች ይነግረናል። እነዚህ ቤተ ሰቦች አይነጣጠሉም። ሰዎች በዚህ ዓለም ሲኖሩ የሌሎች እርዳታ እጅግ ያስፈልጋቸዋል። እንኳንስ በሚታይ፣ ለመሸከም እጅግ በሚከብድ ችግር ውስጥ ወድቀው ሳለ የሰዎች መኖር ለእነርሱ መኖር ወሳኝ ነው። እነዚህ የተዘረዘሩት መንፈሳዊ ተግባራትም እንዲሁ የማይነጣጠሉ ናቸው።

ሊቁ ከተቀደሰች ማኅፀን ተወልደዋልና ይለንና የተወለዱባት የተቀደሰች ማኅፀን ደግሞ “አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ማመን ነው።” ይለናል። በእግዚአብሔር አንድነት ሦስትነት የማያምን ሰው አይጾምም ባይባልም በጾሙ ግን ዋጋ አያገኝም። በመጾሙ ዋጋ የሚያገኘው በእግዚአብሔር አንድነት ሦስትነት አምኖ ሲጾም ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ “ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው አስቀድሞ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጣቸው ሊያምን ይገባዋል” (ዕብ.፲፩፥፮) በማለት እንደተናገረው እምነት መሠረት ነው። ስለዚህ ሰው ሁሉ አስቀድሞ  በእግዚአብሔር አንድነት ሦስትነት ማመን ካልቻለ ጾሙ ዋጋ ሊያሰጠው አይችልም።  እንዲሁም ጾም እንደሚያድነው የማያምን ሰው አይጾምም። ስለዚህ የተወለዱባትን የተቀደሰች ማኅፀን “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ማመን” ናት በማለት ያስረዳናል።

በመሆኑም ስንጾም እኅቷን ጸሎትን መጋበዝ ይጠበቅብናል። ይህ ማለት ስለእኛም ሆነ ስለ ተቸገሩት ሁሉ ልንጸልይ፣ በረኀብ፣ በጥም፣ በመጠለያ እጦት፣ በፍትሕ መጓደል ወዘተ እየተቸገሩ ያሉትን በጸሎታችን ልናስባቸው ይገባል። እናቲቱን ስንጠራ ልጇ የተባለችውን ምጽዋትንም እንዲሁ እንጠራና የተራቡትን ልናበላቸው፣ የተጠሙትን ልናጠጣቸው፣ መጠለያ ያጡትን ልናስጠጋቸው፣ በሥነ ልቡና የተጎዱትን የምክር አገልግሎት በመስጠት መንፈሳዊ ሕክምና ልናደርግላቸው፣ ብቸኝነት ያንገላታቸውን ከጎናቸው ሆነን አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል። ምጽዋትም የሚፈጸምበት መንገዱ ብዙ ነውና ከላይ በተዘረዘረው ሁሉ መሳተፍ ይኖርብናል።   

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በእስራኤል ዘንድ የነበረውን ጾምና እነርሱ እየጾሙበት የነበረበትን መንገድ “ስለምን ጾምን አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን አንተም አላወቅኸንም? ይላሉ። እነሆ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ ለጠብና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ ድሃውንም በጡጫ ትማታላችሁ፤ በምትጮኹበት ጊዜ ድምፃችሁ እንዲሰማ ለእኔ ትጾማላችሁን?  ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም እኔ ይህን ጾም የመረጥሁት አይደለሁም፤ እንደዚችም ባለች ቀን ሰው ራሱን ቢያሳዝን አንገቱንም እንደቀለበት ቢያቀጥን ማቅ ለብሶ በአመድ ላይ ቢተኛ ይህ ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠ አይደለም። ይህን ጾም የመረጥሁት አይደለም ይላል እግዚአብሔር።” በማለት ገልጾት እናገኛለን። 

ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ያለውን ጾም እግዚአብሔር እንዳልተቀበለላቸው፣ ያልተቀበለበት ምክንያትም ምን እንደሆነ ከነገራቸው በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲያስረዳ እንዲህ ይላል። “ነገር ግን የበደልን እስራት ፍታ፤ ጠማማውን ሁሉ አቅና፤ የተጨነቀውንም ሁሉ አድን፤ የዐመፃ ደብዳቤንም ተው። ለተራበውም እንጀራህን አጥግበው፤ ድሆችን ወደ ቤትህ አስገብተህ አሳድራቸው፤ የተራቆተውንም ብታይ አልብሰው፤ ከሥጋ ዘመድህ አትሸሸግ። ያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፤ ፈውስህም ፈጥኖ ይወጣል፤ ጽድቅህም በፊትህ የሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይጋርድሃል” (ኢሳ.፶፰፥፮-፰)። 

በዚህ ኃይለ ቃል ነቢዩ ኢሳይያስ በርከት ያሉ ቁም ነገሮችን አስተላልፏል። ከተናገራቸው ቁም ነገሮች መካከል በተወሰነ መልኩ ዘርዘር አድርገን ስንመለከታቸው የሚከተሉትን ነጥቦች እናገኛለን።

ሀ. የበደልን እስራት ፍታ፡- ዛሬ ዛሬ እየተፈጸመ ያለውን በደል እንኳንስ ልንቋቋመው ስንሰማው ይዘገንናል። ይህን ግፍ እየፈጸሙ ያሉ አካላት ሊያሳኩት የሚፈልጉት ዓላማ ስላላቸው በአርአያ እግዚአብሔር በተፈጠረ ሰው ላይ እንዲህ ያለ ግፍ ሲፈጽሙ ምንም መስሎ አይታያቸውም፤ ይሁን እንጂ ይህን ግፍ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም በመተባበርና በመደጋገፍ ልንቀንሰው እየተገፉ ላሉትም ልንደርስላቸው ይገባል። “የበደልን እስራት ፍታ” ስንባልም ሕግ ጥሶ፣ ወንጀል ሠርቶ የጠባይ ማስተካከያ እንዲያደርግ በሕግ አግባብ የተያዘውን አይደለም። በግፍ ያለምንም ወንጀል የታሰሩ፣ ምን አልባትም ለመሪዎች የተሳሳተ አሠራር አልመች ስላሉ የግፍ ቀንበር የተጫነባቸው በርካታ ናቸው። ለእነዚህ ሁሉ በመድረስ የምንችለውን ልናደርግ ይገባል። 

ለ.የተጨነቀውንም ሁሉ አድን፡- የሰዎች ጭንቀት በብዙ መልኩ ሊመጣ ይችላል። በእነርሱ ደረጃ መፍታት የማይቻል መስሏቸው በጭንቀት ውስጥ ያሉትን እንደየችግራቸው ዓይነትና መጠን በመቅረብ ከገቡበት ጭንቀት የሚወጡበትን መንገድ መፈለግ የግድ ይላል። ምን አልባትም በቃል አትጨነቁ ከማለት ባለፈ ቀረብ ብሎ የችግሩን ሁኔታ በመረዳት ተግባራዊ ምላሽ የሚያስፈልገውን በተግባር እየመለሱ ሰዎችን ማረጋጋት ይገባል። ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ የእስራኤልን መከራ ሲገልጽ “በከተማ ጎዳና እንደ ተወጋ ሰው በዛሉ ጊዜ ነፍሳቸውም በእናቶቻቸው ብብት እለይ እለይ ባለች ጊዜ እናቶቻቸውን እህልና ወይን ወዴት አለ? ይሏቸዋል።” (ሰቆ.ኤር.፪፥፲፪) በማለት እንደተናገረው ሕፃናት ልጆቻቸውን እንዳዘሉ ከቤታቸው ተፈናቅለው ሕፃናቱ የእነርሱን ችግር ሳይረዱ ቀርተው ምግብ እንዲሰጧቸው በየሰዓቱ ሲያለቅሱባቸው እናቶች በውስጣቸው ሊፈጠር የሚችለውን ጭንቀት መረዳት አይከብድም። በዚህ ሁሉ ከጎናቸው ሆነን አይዟችሁ ልንላቸውና ልናረጋጋቸው ይገባል።

ሐ. ለተራበውም እንጀራህን አጥግበው፡- ይህ የችግር ዓይነቱም በሚገባ ተለይቷል፤ ሌላ ችግር አይኖርበትም ባይባልም ግን በስም ተጠቅሶ የተራበውንም እንጀራ አጥግበው ተብሏል። በረኀብ እየተሠቃየ ያለውን ሰው ልምከርህ፣ ላረጋጋህ፣ ወዘተ. ቢሉት ሊሰማን አይችልም። ስለዚህ በምንችለው መጠን አነሰ በዛ ሳንል ያገኘነውን ማድረግ ይኖርብናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማድነቅ እንደተናገረላት “ጌታችን ኢየሱስም በሙዳየ ምጽዋት ፊት ለፊት ተቀምጦ በሙዳየ ምጽዋቱ ገንዘብ የሚጨምሩ ሰዎችን ያይ ነበር፤ ብዙ ባለጸጎች ብዙ ገንዘብ ይጨምሩ ነበር። አንዲት ደሃ መበለትም መጥታ ቆንደራጢስ የሚሉትን ሁለት መሐልቅ አገባች። ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ በሙዳየ ምጽዋቱ ውስጥ ገንዘብ ካገቡት ሁሉ ይህቺ ደሃ መበለት አብዝታ አገባች። ያገቡ ሁሉ ከትርፋቸው አግብተዋልና፤ እርሷ ግን ከድህነቷ የነበራትን ንብረቷን ሁሉ አግብታለችና።” (ማር.፲፪፥፵፩-፵፬) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ስለዚህ በምንችለው መጠን ማገዝ እንጂ እየተራበ እያየን እንዲሁ ማለፍ የለብንም። ከላይም እንደተጠቀሰው በዚህ በጾም ወቅት እናቲቱን ጾምን ገንዘብ ስናደርግ ልጇን ምጽዋትንም አብረን ከመንፈሳዊው አገልግሎት ማሳተፍ ይኖርብናል።

መ. ድሆችን ወደ ቤትህ አስገብተህ አሳድራቸው፡-  ድህነት የባሕርይ አይደለም። ነገር ግን እንግዚአብሔር ባወቀ አንዱን ደሃ አንዱን ሀብታም ያደርገዋል። ይልቁንም በአሁኑ ወቅት በሰው ሠራሽ ችግሮች ብዙዎች ከድህነት  ጎጆ  እንዲጠለሉ ሆነዋል። በዚህ ጊዜ ፈጥኖ መድረስና ቤቴ የእግዚአብሔር እንጂ የእኔ አይደለምና በደህነት የሚቸገሩ ሰዎች ሊያርፉበት ይገባል ልንልና ልናስጠጋቸው ይገባል። እግዚአብሔር በቤታችን ያድር ዘንድ ቤታችንንም ይባርክ ዘንድ ከፈለግን ከቤታቸው ተፈናቅለው ስደተኛ ሆነው የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር የሚፈራረቅባቸውን ሰዎች ከቤታችን እናሳድራቸው። እንዲህ የመሰለውን መልካም ሥራ እየሠራን ስንጾም ጾማችንም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል።

ሠ.የተራቆተውንም ብታይ አልብሰው፡- ብዙዎች ሀብት ንብረታቸው ተዘርፎ ሀብታም የነበሩት ደሃ ሆነው፣ ቤት ንብረት የነበራቸው አሁን ምንም የሌላቸው ሆነው፣ በየጊዜው ልብስ እያማረጡ ይለብሱ የነበሩት አሁን መቀየሪያ እንኳን ሳይኖራቸው እንዲያውም በብርድ እየተሠቃዩ ይገኛሉ። በዚህ ጊዜ የተራቆተውን ማልበስ ጾማችንን እውን ያደርገዋል። በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሰው ራቁቱን ሆኖ ሲሠቃይ እያዩ እንዳላዩ ሆነው ቢያልፉት እግዚአብሔርን ራቁቱን እያየነው ዝም ብለን እንዳለፍነው መቊጠር ይኖርብናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን የቆረሰለት፣ ደሙን ያፈሰሰለት ክቡር ፍጥረት ነውና ይህ ሰውነት ራቁቱን ሆኖ በቀን ሐሩር በሌሊት ቁር ሲሠቃይ ማየት እጅግ የሚከብድ ችግር ነውና ልናስብበት ይገባል።

ስለዚህ ነቢዩ ኢሳይያስ ጾማችን ከእነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት ጋር መፈጸም እንዳለበት ያስገነዝበናል። ካልሆነ ግን የግፍ ግፍ እየሠራን፣ ተበድለው እያየናቸው ሳናዝንላቸው ጾምን የምንል ከሆነ እግዚአብሔር አይቀበለውም። ነቢዩም “ይህን ጾም የመረጥሁ አይደለም ይላል እግዚአብሔር” (ኢሳ.፶፰፥፮) በማለት የነገረን መልካምነት ሳይታከልበት የሚጾምን ጾም ነው።  

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “እናንተ ግን በሥራው ሁሉ እየተጋችሁ በእምነት በጎነትን ፣ በበጎነትም ዕውቀትን ጨምሩ፤… እግዚአብሔርንም በማምለክ ወንድማማችነትን፣ በወንድማማችነትም ፍቅርን ጨምሩ፤ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጋችኋልና” (፪ጴጥ. ፩፥፭-፰) በማለት ማንኛውም ሰው በሃይማኖት ሲኖር ገንዘብ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ነገሮችን አስረድቶናል። እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት አንዱን ብቻ ይዘን ይበቃኛል የምንላቸው ሳይሆን አንዱን በሌላው ላይ እየጨመርን መንፈሳዊ ሕይወታችንን የምናሳድገባቸው መንግሥቱን የምንወርስባቸው ምግባራት ናቸው። ሃይማኖታችን፣ በበጎነት፣ በወንድማማችነት፣ እርስ በእርስ በመዋደድ ሲገለጽ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንሆናለን በእንደዚህ ያለው መልካም ሥራችንም እግዚአብሔር ይደሰትበታል።

ፍቅር የሕግ ሁሉ ማሰሪያ፣ በሃይማኖት የመኖራችን መሠረት ነው። እግዚአብሔርን ልንወድ ማለትም ሕጉን ልንፈጽም እንዲሁም ባልንጀራችንንም ልንወድ ይገባናል። ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ “እኛም እርስ በእርሳችን እንዋደድ፤ እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና። እግዚአብሔርን እወደዋለሁ የሚል ወንድሙን ግን የሚጠላ ሐሰተኛ ነው፤ የሚያየውን ወንድሙን የማይወድ ግን የማያየውን እግዚአብሔርን እንደምን ሊወደው ይችላል? እግዚአብሔርን እንወደው ዘንድ ወንድማችንንም እንወድ ዘንድ ከእርሱ የተቀበልነው ትእዛዝ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ወንድሙን ይወዳል” (፩ዮሐ.፩፥፲፱-፳፩) በማለት የሕይወታችን መሠረት የሆነውን ገንዘብ ማድረግ እንዳለብን ያስረዳናል። 

በአጠቃላይ በምንኖርባት ዓለም አንዱ ለአንዱ አስፈላጊ ነው። ሰው በራሱ ፍጹምና ምሉእ አይደለም። ስለዚህ እርስ በእርስ መረዳዳት፣ የአንዱን ጉድለት ሌላው መሙላት ይኖርበታል። ይልቁንም በአሁኑ ወቅት ችግረኞች የበዙበት፣ ችግራቸውም በየዘርፉ የሆነበት፣ ከፊሉ የሚራብበት፣ ከፊሉ መጠለያ አጥቶ በሜዳ ላይ የወደቀበት፣ ከፊሉ፣ በሥነ ልቡና ጫና ወድቆ መመለሺያ የሌላው በሚመስል የአእምሮ ሕመም የወደቀበት፣ ብቻ ዘርፉ ብዙ በሆነ መልኩ እየተቸገረ ያለበት ነው። በዚህ ጊዜ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ  “ከእኔ ተማሩ” ብሎናልና እርሱን አብነት አድርገን ለችግረኞች ልንደርስላቸው “እንደራባቸው ሊሄዱ አይገባቸውም” ልንላቸው ይገባል። ለዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን።   

Read 894 times