Thursday, 21 January 2021 00:00

ኢየሱስ ወደ ሰርግ ቤት ተጠራ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሄደ። (ቅዱስ ያሬድ፣ ድጓ ዘቃና ዘገሊላ)

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ጋብቻ የራሱ የሆነ ዝግጅት አለው። ይህ ዝግጅት ደግሞ ሰርግ ይባላል፡፡ ‹‹ሰርግ›› የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹ሰረገ፣ ደገሰ፣ ሰርግ አደረገ፣ የሰርጉን ቤት ሸለመ፣ አስጌጠ፣ አንቆጠቆጠ” በማለት ሲገልጹት አያይዘውም “ሰርግ በቁሙ፣ ከብካብ፣ መርዓ፣ የጋብቻ በዓል ድግስ፣ የሚያጌጡበት፣ የሚሸለሙበት፡፡›› በማለት ያብራሩታል። (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ ፰፻፹፬) ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ከሣቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በተሰኘ መጽሐፋቸው ‹‹አካለ መጠን ያደረሰ ወንድ ልጅና አካለ መጠን ያደረሰች ሴት ልጅ ባልና ሚስት ሊሆኑ የሚጋቡበት ቀንና ተጋብተውም የዚህን ዓለም ኑሮ የሚጀምሩበት የሰርግ ቀን›› (ገጽ ፪፻፴፱) በማለት ይገልጹታል። ከሁለቱም ምሁራን አገላለጽ እንደምንረዳው ሰርግ የዕለት ክንውን ሲሆን ጋብቻውን ምክንያት አድርጎ የሚደገሰውን ድግስ የሚለበሰውን ልብስ፣ የሚታየውን ጌጣጌጥ የሚያካትት የማስተዋወቂያ ዝግጅት ነው፡፡ ማለትም ሰዎች ከብቸኝነት ሕይወት ወደ ጥንድነት የሚሸጋገሩበት ዝግጅት ነው፡፡ ይህ ዝግጅት የሁለቱ አንድነት የሚታወጅበት በሁለታችንም ፍላጎት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለዚህ በቅተናልና የደስታችን ተካፋይ ሁኑ በማለት ሙሽሮች በሚያስተላልፉት ጥሪ መሠረት ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ የሁለቱ ተዋሕዶ የሚታወጅበት ወይም አዋጁ የሚጸድቅበት ልዩ የዝግጅት ጊዜ ነው፡፡

 

ይህ የሰርግ ዝግጅት በብሉይ ኪዳንም ይከናወን እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ያዕቆብ የላባን ልጅ ያገባ ዘንድ ወዶ ለላባ ሰባት ዓመት ከተገዛ በኋላ ላባም ሰርጉን ደግሶ አጋብቶታል፡፡ ‹‹ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ ሰርግም አደረገ፡፡›› (ዘፍ. ፳፱፥፳፪) እንዲል። ስለዚህ የሙሽሮች እናት አባት አሊያም ራሳቸው ሙሽሮች ቤተ ዘመዳቸውን፣ የአካባቢውን ሰው እና ለሰርጋቸው ድምቀት ይሆነናል ያሉትን ሁሉ ሰብስው ደስታቸውን የሚያውጁበት መጣመራቸውን የሚያሳውቁበት ዝግጅት ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳንም እንዲህ ያለው ሥርዐት ቀጥሏል። በዚህ ልማድ ዶኪማስ ሰርጉን አዘጋጅቶ ዘመዶቹን ጠራ። በወቅቱ ከተጠሩት ታዳሚዎች መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱና  ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነበረ። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ቃና ዘገሊላን በአዘከረበት የድጓ ክፍሉ ይህን ሲያስረዳ “ከብካብ ኮነ ከብካብ ኮነ ወኮነ እሙነ በቃና ዘገሊላ ተጸውዐ ኢየሱስ ውስተ ከብካብ ወሖረ ምስለ አርዳኢሁ፤ በገሊላ ቃና  ሰርግ ኾነ፤ ሰርግ ኾነ፤ የታመነም ኾነ ኢየሱስ ወደ ሰርጉ ተጠራ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሄደ” በማለት ተናገረ። 

ይህ ታሪክ በቅዱስ ወንጌልም “በሦስተኛውም ቀን የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና ሰርግ ሆነ፤ የጌታችን የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች። ጌታችን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ።” (ዮሐ.፪፥፩) ተብሎ ተመዝግቧል። በዚህ ምንባብ ጠሪ አለ ተጠሪ አለ ተጠሪው ከማን ጋር ሄደ የሚለውና ለምን ተጠሩ የሚለውን እንመለከታለን።

ጠሪ፡- ጠሪው ሰርጉን ያዘጋጀው ሰው ነው። ሰርጉ ከላይ እንደ ተገለጸው የደስታ መግለጫ እንደመሆኑ ደስታን የሚካፈል ሰው ያስፈልጋል። በሰው ሕይወት ላይ ልደት እንዳለ ሁሉ ሞት አለ። ደስታ እንዳለ ሁሉ ኀዘን አለ። ስለዚህ ደስታንም ሆነ ኀዘንን  በጋራ ሲያከናውኑት እጅግ ያምራል። ደስታውም ብቻን ከሆነ አያምርም፤ መደሰታችንን ዕወቁልን ብለን ስለሆነ የምንጠራው የእኛን ደስታ የሚመሰክሩ፤ የእኛን ደስታ ተመልክተው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ፣ ከእኛም ጋር የሚደሰቱ ሰዎች መኖር አለባቸው።

በኀዘን ጊዜም ቢሆን ከኀዘናችን የሚያረጋጉን፣ ኀዘናችንን የሚካፈሉልንና የሚያጽናኑን ሰዎች ያስፈልጉናል። እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሄሮድስ የተወደደ ልጇን እንዳይገድልባት በተሰደደች ጊዜ የተናገረችውን የኀዘን ቃል ሰቆቃወ ድንግልን የጻፈልን ሊቅ አባ ጽጌ ድንግል “ አይቴ ይእቲ ሐና እምየ፤ ወኤልሳቤጥኒ እንተ እምአዝማድየ፤ ይብክያኒ ሊተ በእንተ ንግደትየ ለሐወት ማርያም እንዘ ትብል ወይልየ ዘየአምረኒ ሊተ ኃጣእኩ በዝየ፤ ሐና እናቴ ወዴት ናት? ከዘመዶቼ ወገን የሆነች ኤልሳቤጥስ፤ ስለ ስደቴ ያለቅሱልኝ ዘንድ፤ በዚህ ቦታ የሚያውቀኝ (የሚያጽናናኝ) አጣሁ እያለች ማርያም አለቀሰች ” (ሰቆቃወ ድንግል) በማለት በኀዘን ጊዜ ሰው የሚያስፈልግ መሆኑን ያስረዳናል። 

በመጽሐፈ ሲራክ “ከሚያለቅሱ ሰዎችም አትለይ፤ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅስ። ሕመምተኛንም ሰው መጎብኘት ቸል አትበል፤ በዚህም ይወዱሃል” (ሲራ.፯፥፴፬-፴፭) ተብሎ ተጽፏል። ስለዚህ በኀዘንም ሆነ በደስታ ወቅት ሰው ከጎናችን ኾኖ ከደረሰብን ኀዘን ሊያጽናናን፣ ከአገኘነው ደስታ ደግሞ ሊካፈል ያስፈልጋል። ዶኪማስም ሰርጉን ደግሶ ዘመዶቹን የጠራው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የጠራ በዚህ ልማድ ነበር።

ተጠሪ፡- ወደ ሰርጉ የተጠራው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በኀዘናችንም ኾነ በደስታችን አስቀድመን እርሱን መጥራት ያለብን መሆኑን ያስገነዝበናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሊቃውንቱ ተደጋግሞ እንደተነገረው ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደኛ ሰው ኾኗልና በኀዘን ቤትም ተገኝቶ ኀዘንተኞችን አጽናንቷል፤ ስለሞተው ስለ አልዓዛር እርሱም አልቅሷል። በዚህ ያዩት ሁሉ እንዴት ይወደው ነበር? ብለው አድናቆታቸውን ገልጸዋል። (ዮሐ.፲፩፥፳፰-፴፯) 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ሕይወት እንደሚያስፈልገው በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም አስተምሯል። በኀዘን ቤት ተገኝቶ ኀዘንተኞችን እንዳጽናና በሰርግ ቤት ተገኝቶ ባለ ሰርጉን አስደስቷል። ባለ ሰርጉ አክብሮ እንደጠራው ሁሉ እርሱም ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠሪውን አክብሮ በሰርግ ቤት ተገኝቷል። ወደ ሰርጉ የተጠሩት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መሆኑን እንረዳለን።

ከማን ጋር ሄደ፡- ባለ ሰርጉ መምህሩን ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠራ። ዛሬ ዛሬ የጥሪ ወረቀት ይዘጋጅና በመጨረሻው ላይ “ለሕፃናት ቦታ የለንም” የሚል ማስታወሻ ይጨመርበታል። የዶኪማስ ሰርግ ግን እናት ከልጅ፣ መምህር ከደቀ መዝሙር ተነጣጥለው የሚለዩበት አልነበረም። ምክንያቱም እናት ከልጅ አትነጠልም፤ ልጅም ከእናት አይነጠልም። መምህር ከደቀ መዝሙር ደቀ መዝሙርም ከመምህር አይነጠሉም።

በቅዱስ ወንጌል (ዮሐ.፪፥፩) ላይ የተጻፈውንና ከላይም የተጠቀሰውን ፅንሰ ሐሳብ መተርጕማኑ ሲያብራሩ “እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ፈሊጥ አይደለምና እናታችን ቅድስት ማርያም ስትጠራ ልጇም ተጠራ። መምህርን ጠርቶ ደቀ መዝሙርን መተው አግባብ አይደለምና ጌታችን ሲጠራ ደቀ መዛሙርቱም አብረው ተጠሩ” ብለው አብራርተውታል። በመሆኑም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አክብሮ ወደጠራው ባለ ሰርግ ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሄደ።

መምህር የሚደምቀው በደቀ መዛሙርቱ ነው። ደቀ መዛሙርትም የሚከበሩት በመምህራቸው ነው። ምንም እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ድምቀት ሆኑት ባንልም ግን በቅዱስ ወንጌል “ያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” (ማቴ.፳፬፥፱) እንደተባሉ ስሙን ለአሕዛብ አሳውቀዋል፤ በስሙ መከራ ተቀብለዋል። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ስለ እርሱ ሁልጊዜ ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎችም ኾነናል፡” (መዝ.፵፫፥፳፪) በማለት እንደተናገረው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ “ስለ አንተ ዘወትር ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎችም ኾነናል፤ ነገር ግን በወደደን በእርሱ ሁሉን ድል እንነሣለን” (ሮሜ.፰፥፴፮) በማለት እንደገለጸው በስሙ መከራን ተቀብለው፣ መከራ ተቀብለው ብቻ ሳይቀሩ በስሙ አጋንንትን አውጥተው፤ በስሙን ሕሙማንን ፈውሰው፤ በስሙ ሙታንን አስነሥተው፤ በስሙ የዚህን ዓለም መከራ ድል አድርገው አምላክነቱን ላላወቁት አሳውቀዋልና በእነርሱ የታወቀ ሆኗል። እነርሱም በእርሱ ከብረዋል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰርግ ቤት ሲሄድ ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ሄደ ሁሉ ዛሬም በመምህራን ላይ አድሮ ይኖራልና ካህናቱን መምህራኑን፣ በእግዚአብሔር ስም የተላኩትን ሁሉ ስንጠራ ጌታችንም እንደማይለይ ያስረዳናል። ምእመናን ካህናቱን ወደ ሰርግ ቤት ሲጠሩ መምህራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ አብሯቸው እንደሚጠራ መረዳት ይኖርባቸዋል። በቅዱስ ወንጌልም “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” (ማቴ.፲፥፵) ተብሎ ተጽፏል።

ለምን ተጠሩ፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠራው ለሰርግ ነው። ሊቃውንቱ ተባብረው እንደገለጹት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ ወኮነ ሰብአ ከማነ ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ፤ ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደኛ ሰው ሆነ” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) ተብሎ እንደተነገረ በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰርግ ቤት ተጠራ። እርሱም በሰርጉ ቤት በመገኘት ጋብቻቸውን ይባርክ ዘንድ ጥሪውን አክብሮ ከደቀ መዛሙርቱና ከእናቱ ጋር ሄደ።

ጌታችን መድኃኒታችን ለሰርግ ሲጠራ ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ ሄደ። ይህም በማኅበራዊ ሕይወት እርሱ እንደተሳተፈ ደቀ መዛሙርቱም መሳተፍ እንዳለባቸው ሲያስረዳ ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን በዚህ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ለባለ ሰርጉ ያደረገው ተአምር፣ ዛሬም በእርሱ እግር የተተኩትና ለክርስቶስ እንደራሴ ሆነው ምእመናንን ከክርስቶስ የሚያገናኙ መምህራን በሰርግ ቤትም ተገኝተው ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ያስረዳል።

ከዚህ ምን እንማራለን

አንዱን ከሌላው ሳይነጣጥሉ  መጥራትን፡- ከላይም እንደተገለጸው ባለ ሰርጉ መምህሩን ሲጠራ ደቀ መዛሙርቱን፣ እና እናቱን አብሮ ጠራ። ዛሬም በኀዘን በደስታችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጠርተን እናቱን ድንግል ማርያምንና እርሱ ያከበራቸው ቅዱሳንን መጥራት እዳለብን ያስተምረናል። እንዲሁ ሰርጋችንን አዘጋጅተን መምህራንን ስንጠራ ደቀ መዛሙርቱንም መጥራት እንዳለብን፣ እናት አባትን ጠርተን ልጆችንም መጥራት እንዳለብንም ያስተምረናል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዣ እንኳን አዘጋጅተን ሰዎችን ስንጠራ ማንን መጥራት ማንን ደግሞ መጥራት እንደሌለብን ሲያስተምር እንዲህ በማለት ተናግሯል። “በበዓል ምሳ ወይም ራት በምታደርግበት ጊዜ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን፣ ዘመዶችህንና ጎረቤቶችህን፣ ባለጸጎች ባልንጀሮችህንም አትጥራ፤ እነርሱም ይጠሩሃልና፤ ብድርም ይሆንብሃልና። ነገር ግን በበዓል ምሳ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፤ ዕውሮችን፣ እጅና እግርም የሌላቸውን ጥራ። አንተም ብፁዕ ትሆናለህ የሚከፍሉህ የላቸውምና፤ ነገር ግን ጻድቃን በሚነሡበት ጊዜ ዋጋህን ታገኛለህ” (ሉቃ.፲፬፥፲፪-፲፬) እንዲል። ይህ ቃል የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምሳ ግብዣ ከተጠሩት አንዱን ሰው በዚህ መልኩ አስተምሮታል። ለጊዜው ለሰውየው የተሰጠው ይህ ትምህርት ሰዎች እስከ ዘለዓለሙ ድረስ  ሲማሩበት ይኖራል። 

ተጠርቶ አለመቅረትን፡- ጌታችን መድኃኒታችን አስወድዶ አስፈቅዶ የሚገዛ አምላክ ነው። ስለዚህ ለድኅነታችን ሁሉ እኛ ፈቃደኛ ሁነን በፍጹም እምነት ልንጠራው ይገባል። ሲጠሩም ጥሪን አክብሮ መሄድ እንዳለብን እንማራለን። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠርቶ አልቀረም። ዛሬም ድሀም ይጥራን ሀብታምም  ይጥራን “ሳትጠራ አትሂድ፤ ተጠርተህም አትቅር” እንዲሉ አበው ጥሪን አክብሮ መሄድ እንዳለብን ያስረዳናል።

በመጽሐፈ ሲራክ “ለባለጸጋውና ለከበርቴው ለድሃውም ክብራቸው እግዚአብሔርን መፍራት ነው። ድሃውን ስለ ድህነቱ ይንቁት ዘንድ አይገባም፤ ኃጢአተኛውንም ሰው ስለ ባለጸግነቱ ያከብሩት ዘንድ አይገባም” (ሲራ.፲፥፳፪-፳፫) ተብሎ እንደ ተጻፈ ማንም ሰው የደስታዬ ተካፋይ ሁኑልኝ ብሎ ሲጠራን ድሃና ሀብታም ሳንለይ ጥሪውን አክብረን መሄድ ይኖርብናል። ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የምንማረውም ይህን ነው። ምክንያቱም ማኅበራዊ ሕይወትን ሊባርክ በድሃ ቤትም በሀብታም ቤትም፣ በሰርግም በኀዘንም ተገኝቶ መስተናገድ ባለበት አግባብ ተስተናግዷል። 

የባለ ጉዳዩን ችግር መረዳትን፡- እኛን የጠራ አካል  አስቦና አክብሮ ሲጠራን በወቅቱ የሚኖረውን ችግር መረዳት ያስፈልጋል። በክብር ተጠርተው ከሄዱ በኋላ በሆነ ባልሆነው የሚያኮርፉ፣ መስተንግዶው ሳያልቅ አቋርጠው ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ሰዎች ይስተዋላሉ። በአስተናጋጆች ላይ የሚቆጡ፤ ቦታ አልተመቸኝም የሚሉ፣ ቅድሚያ አልተሰጠኝም ወዘተ የሚሉ አሉ።  ነገር ግን  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ካደረገው ተአምር የምንረዳው አስቀድሞ የጠሪውን ጉድለት ማወቅና ለመሙላት ፈቃደኛ መሆን የምንችለውንም ሁሉ ማድረግ እንዳለበን ነው።

በመጽሐፈ ሲራክ “በደስታህ ጊዜ አትታጣ፤ በጎ ድርሻህም አያምልጥህ” (ሲራ.፲፬፥፲፬) ተብሎ እንደተጻፈ ከላይም እንደተገለጸው አስቀድሞ ጥሪን አክብሮ መገኘት ከተገኙ በኋላም የድርሻን መወጣት ያስፈልጋል። ማለትም ከደስታው መካፈል በተጠራንበት ወቅት የሚጎድል ነገር ቢኖር ደግሞ የጎደለውን ነገር በአግባቡ ተረድቶ ለመሙላት መዘጋጀት ያስፈልጋል።

ችግሩን መሙላትን፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ሁሉ ይቻለዋልና የባለ ሰርጉን ጉድለት ሞላለት። እንደ ሰው ወደ ሰርግ ቤት ተጠርቶ መብላቱ፣ መጠጣቱ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ደግሞ በተገኘበት ቤት የጎደለውን መሙላት መቻል ደግሞ እጅግ የሚደንቅ ነው። ዛሬ እኛ ምንም እንኳን “ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል” (ማር.፱፥፳፫) ተብሎ በቅዱስ ወንጌል ቢነገርም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ መለወጥ ላይቻለን ይችላል። ምክንያቱም ተአምር እንደ እምነታችን መጠንና እንደተሰጠን ጸጋ መጠን ስለሆነ ነው። ነግር ግን ቢያንስ አስቀድመን ችግሩን መረዳት፣ ከዚያም የምንችለውን ሁሉ ማድረግ የክርስቶስን ፈለግ መከተል ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአግባቡ የጠራውን ሰው የሚያስተናግድ እህልና ውኃ ሳይኖርህ ለምን ጠራህ ብሎ ጥሎት አልሄደም። በእርግጥ ይህ ሰዓት ለባለሰርጉም ለአሳላፊዎችም እጅግ የሚያስደነግጥና የሚያሸብር ሰዓት ነበር። ግን ጭንቀታቸውን የተረዳች ድንግል ማርያም ወደ ልጇ አመለከተች፤ የሁሉን ችግር የሚሞላ፣ ሁሉን የሚያደርግ አምላክም የሰዎችን ችግር ተደርቶ የጎደለውን ሞላላቸው።

በአጠቃላይ “በገሊላ ክፍል በቃና ሰርግ ኾነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰርግ ቤት ተጠራ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሄደ”  በማለት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የገለጸው በቅዱስ ወንጌልም የተጻፈው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ወደዚህ ዓለም በመጣበት ወራት በቃል ያስተማረው፣ በተግባር የፈጸመው እኛም በሕይወታችን እንድንኖረው የሠራልን ሥርዓት ነው። በማኅበራዊ ሕይወታችን እንድንገለገልበት ከሠራልን ሥርዐት ባለፈ ነገረ ድኅነትን የምንረዳበት ትምህርቱም ነው። 

ስለዚህ ባለ ሰርጉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከእናቱ ጋር እንደጠራ እርሱም  ጥሪውን አክብሮ  ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ሰርግ ቤት እንደሄደ ሁሉ እኛም በኀዘን በደስታችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱ ክርስቶስን ስንጠራ እናቱና ደቀ መዛሙርቱ እርሱ ያከበራቸው ቅዱሳንም የማይቀሩ መሆናቸውን፣ በማኅበራዊ ሕይወታችን መምህርን ከደቀ መዝሙር እናትን ከልጅ እየለዩ መጥራት አግባብ እንዳልሆነ እንማርበታለን። ጌታችን ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በመጠራቱና በመሄዱ የሰርጉን ቤት ጐደሎ እንደሞላ ሁሉ የእኛንም ዝግጅት የሚያከናውነው “እናንተን የተቀበለ እኔን ተቀበለ” (ማቴ.፲፥፵) በማለት በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረው መምህራንን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መጥራት እንዳለብን ያስረዳናል። በዚህም የጎደለንን ሁሉ እንደሚሞላልን ልናምን ይገባናል። በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ የጎደለውን የሞላ አምላካችን በእኛም ሕይወት ሁል ጊዜ እየተገኘ የጎደለንን እንዲሞላልን የእርሱ አባታዊ ቸርነት፣ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳኑ ተራዳኢነት አይለየን አሜን።

 

Read 185 times