Wednesday, 28 April 2021 00:00

“መልካም ማድረግን አትርሱ” (ዕብ.፲፫፥፲፮)

Written by  ዲ/ን ተስፋዬ ምትኩ

Overview

ኃይለ ቃሉን የተናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው። ሙሉ ቃሉን ስናነበው “መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” ይላል። (ዕብ.፲፫፥፲፮) ይህን የቅዱስ ጳውሎስን ሐሳብ ያብራሩት መተርጕማነ መጻሕፍት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም “ለነዳያን መመጽወትን አትተዉ እናንተ በመስጠት እነሱ በመቀበል አንድ መሆናችሁንም አትርሱ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” ብለዋል። (የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡ ከነትርጓሜው ፲፱፻፵፰ ዓ.ም ገጽ ፬፻፸) የመልካምነት መገለጫዎች ብዙ ናቸው። በርግጥ እንደየ ሰዉ አመለካከት፣ እምነትና ባህልም ይለያያል። ከዚህም የተነሣ ለአንዱ መልካም የሆነው ለሌላ ክፉ የሚሆንበት አጋጣሚም ብዙ ነው። በዙህም መሠረት እንደ ክርስትና ግን ነገሮችን መልካምና ክፉ፣ ኃጢአትና ጽድቅ፣ ጥሩና መጥፎ፣ ክብርና ውርደት፣… ብለን የምንለየው ሕግጋተ እግዚአብሔርን መሠረት አድርገን እንጂ የሰዎችን ባህልና አስተሳሰብ ወይም ዕድገትና ትምህርት መሠረት በማደረግ አይደለም።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ሥጋዌው አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ “መምህር ሆይ፥ የዘለዓለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ “ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” በማለት ነበር የመለሰለት። (ማቴ.፲፱፥፲፮-፲፯) 

 

ያም ሰው ጥያቄውን በዚያ ሳይቆም “ትእዛዛቱ የትኞቹ ናቸው?” በማለት ጠይቆት ነበር። ጌታም፦ “አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” በማለት ትእዛዛቱ እነማን እንደሆኑ ነግሮታል።  በመጨረሻም “ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው?” ብሎ በመጠየቁ ጌታም የመልካምነት የመጨረሻ ጥጉን ሲነግረው “ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ” አለው። (ማቴ.፲፱፥፲፰-፳፩) 

በርግጥ ንብረቱን ሁሉ ሽጦ ገንዘቡን ለድሆች መጽውቶ ዓለምንና አምሮቷን ሁሉ ጥሎ ክርስቶስን መከተል ለሁሉ የሚቻል አይደለም። (ማቴ.፲፱፥፲፩) ይህም ሆኖ ግን ይህን ሕይወት ማለትም ዓለምንና ፍላጎቷን ትተው ገዳማዊ ሕይወትን በተግባር ኖረው ያሳዩን ጥቂቶች አይደሉም። ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ኤልሳዕ ይህን አድርጓል። ኤልሳዕ በግብርና ሥራ የሚተዳደር ባለጸጋ ሰው ነበረ።  እግዚአብሔር በነቢዩ ኤልያስ አድሮ ለመንፈሳዊ ተልእኮ ሲጠራው ግን ያርስባቸው ከነበሩት በሬዎች ከፊሉን በእርሻው ጥሎ፣ ከፍፊሉንም አርዶ ለድሆች መግቦ እናቱንና አባቱን ተሰናብቶ በእግዚአብሔር ጥሪ መሠረት ወደ አገልግሎት ተሰማርቷል። 

“የሣፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን በአሥራ ሁለት ጥማድ በሬዎች ሲያርስ፥ እርሱም ከአሥራ ሁለተኛው ጋር ሆኖ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ አልፎ መጐናጸፊያውን ጣለበት። በሬዎቹንም ተወ፥ ከኤልያስም በኋላ ሮጦ አባቴንና እናቴን እስማቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ተወኝ፥ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ አለው። እርሱም፦ ሂድና ተመለስ ምን አድርጌልሃለሁ? አለው። ከእርሱም ዘንድ ተመልሶ ሁለቱን በሬዎች ወስዶ አረዳቸው፥ ሥጋቸውንም በበሬዎቹ ዕቃ ቀቀለው፥ ለሕዝቡም ሰጣቸው፥ በሉም እርሱም ተነሥቶ ኤልያስን ተከትሎ ሄደ፥ ያገለግለውም ነበር” እንዲል። (፩ኛ ነገ.፲፱፥፲፱-፳፩)

በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ከንቱነት የዘለዓለም ሕይወትን ምንነት በነገራቸው ጊዜ መተዳዳሪያ ሥራቸውን፣ ሹመታቸውንና ሥልጣናቸውን፣ ሀብታቸውንና ንብረታቸውን፣ ሁሉ ጥለው የተከተሉ ብዙዎች ናቸው። ከእነዚህም መካከል ጌታን የተከተሉ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ተጠቃሽ ናቸው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያትን ሁሉ ወክሎ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?” ብሎ ጌታውን የጠየቀው። (ማቴ.፲፱፥፳፯) 

ዘኬዎስ የተባለው ባለጸጋም  ጌታን ወደ ቤቱ ጋብዞ ከሀብቱ እኩሌታውን ለድሆች ለመስጠት ቃል ገብቶለታል። “ዘኬዎስም ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው” እንዲል። (ሉቃ.፲፱፥፰)

ሰው ከሀብት ከንብረቱ እኵሌታውን ከፍሎ ለድሆች መስጠት ለጥቂቶች እንጂ ለሁሉ የተሰጠ አይደለም። ይሁን እንጂ ካለው ቀንሶ ለድሆች ማካፍል ማለትም ቆርሶ ማጉረስ፣ ቀዶ ማልበስና የመሳሰሉትን መልካም ምግባራት መፈጸም የምእመናን ሁሉ መንፈሳዊ ግዴታዎች፣ የመልካም ክርስቲያናዊ ሕይወትም መገለጫዎች ናቸው። ይህ ስለሆነም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ ፍርድ ቀን ሊሆን ያለውን በተናገረበት ትምህርቱ በቀኙ ለሚቆሙት ጻድቃን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና” እንደሚላቸው የነገረን። ጻድቃን ደግሞ ትሕትና ልማዳቸው ስለሆነ መልካም ነገር ሠርተው አልሠራንም ይላሉና፤ ይህን ሲሰሙ “ጌታ ሆይ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?” ብለው ይጠይቃሉ። እርሱም መልሶ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” ይላቸዋል። ኃጥአንን ደግሞ  “ተርቤ፣ ተጠምቼ፣ ታርዤ፣ ታሥሬ ታምሜ ከእኔ ጋር አልነበራችሁምና ከእኔ ወግዱ” ይላቸዋል። ኃጥአን ግን ጥፋታቸውን ከማመን ይልቅ ለስንፍናቸው ምክንያ ማቅረብ ልማዳቸው ነውና “መቼ አገኝተንህ አላደረግንልህም” ብለው ይከራከሩታል። ጌታ ደግሞ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም” ብሎ ይመልስላቸዋል። (ማቴ.፳፭፥፴፬-፵፭)

ከዚህ ሁሉ የምንገነዘበው ድሆችን ማሰብ፣ ችግራቸውን መካፈል፣ ከደስታችንም ተካፋዮች እንዲሆኑ መጋበዝ የምእመናን ሁሉ መንፈሳዊ ግዴታቸው መሆኑን ነው። ክርስቲያናዊ ሕይወት ደግሞ ዕለት ዕለት የምንኖረው ነውና ድሆችን ማሰብም የሁል ጊዜ ተግባራችን ሊሆን ይገባል። በተለይም የጻድቃንን፣ የሰማዕታትን፣ የቅዱሳን መላእክትንም በዓላቸውን በምናደርግበት ዕለት ከማንም አስቀድመን ድሆችን በቤታችን ልንጋብዛቸው ይገባል። በዓሉን በምናከብርለት ቅዱስም ስም ድሆችን ቆርሰን ማጉረስ ቀደን ማልበስ ይገባል። በዚህም “ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ አንዲት ጽዋ ቀዝቃዛ  ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙሬ ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።” ተብሎ እንደተጻፈልን የምንዘክርለት ቅዱስ ያገኘውን ጸጋና በረከት እንወርሰለን። (ማቴ.፲፥፵፩-፵፪) አስተውሉ በዓሉን የምናከብርለት ቅዱስ ለዚህ ክብር የበቃው በብዙ ተጋድሎ ሲሆን እኛ ደግሞ በቅዱሱ ስም ቁራሽ እንጀራ፣ ጥርኝ ውኃ፣ ድቃቂ ሳንቲም እላቂ ጨርቅ በመስጠት ብቻ ቅዱሱ በብዙ ተጋድሎ ያገኘውን ጸጋና በረከት ተካፋይ እንሆናለን። 

ከሁሉ በላይ ደግሞ የሕይወት መሠረት፣ የቅድስና ምንጭ፣ የጸጋም ሁሉ ባለቤት የሆነውን የክርስቶስን በዓል ስናከብር በተለይም እርሱ ከዘለዓለማዊ ረኀብና ጥም የሚያድነንን ሥጋውንና ደሙን የሰጠበትን ሞትንም ድል አድርጎ የተነሣበትን በዓለ ትንሣኤን ስናክብር ድሆች ከእኛ ጋር አብረው የደስታችን ተካፋይ እንዲሆኑ መጋበዝ ክርስቲያናዊ ግዴታችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ያለበለዚያ በዓሉን በማክበራችን ክርስቶስን አስደስተናል ማለት አንችልም። በእውነቱ ከሆነ ከልጆቹ መካከል ግማሾቹ ተርበው ሲያለቅሱ ሌሎች ደግሞ ጠግበው ሲጨፍሩ፣ የተራቡትን ትቶ ከጠገቡት ጋር አብሮ የሚጨፍር አባት ይኖራልን? በርግጥ ይኖር ይሆናል። የእኛ አባት ክርስቶስ ግን እንዲህ ያለ ርኅራኄ የሌለው አባት አይደለምና ድሆች ሲራቡ ያዝናል። የሚያዝነው ግን እንደ ድሃ አባት የሚሰጠውን አጥቶ አይደለም፤ እኛ እንድንጸድቅበት ያዘጋጀልንን ዕድል መጠቀም ባለመቻላችን ነው እንጂ። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “ለድሃ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል” በማለት የገለጸው ይህንን እውነት ነው። (መዝ.፲፰፥፲፯) 

እንደሚታወቀው “ብድር” ያጣና የተቸገረ ሰው ለጊዜአዊ ችግር ማለፊያ ብሎ ካለው ሰው የሚቀበለው ገንዘብ ነው እንጂ የሚቀር አይደለም። ምን አልባት አበዳሪውም ለጊዜው የሚያበድረው  ስላለው እንጂ ስለ ተረፈው ላይሆን ይችላል። ባለው ጊዜ ያበደረው ገንዘብ  በእጁ ያለው ገንዘብ በሚያልቅበት ጊዜ ስለ ሚደርስለት ትልቅ ተስፋ ይኖረዋል። በርግጥ ለሰው ያበደርነው በችግራችን ጊዜ ላይደርስልን ይችል ይሆናል፤ ተበዳሪ መልሶ የመክፈል አቅምም ሊያጣ ይችል ይሆናል። አበዳሪው ግን ያለ ተያዥ ስለማያበድር በተያዡ በኩል ገንዘቡን ያገኛል። ለመሆኑ ተያዡስ ማን ነው ለገባለት ቃሉ ታምኖ በቸገረን ጊዜ የገባልንን ቃል መፈጸም ይቻለው ይሆን? ለድሃ ለምናበድረው ገንዘብ (ለምንመጸውተው ምጽዋት) ግን አስተማማኝ ተያዥ አለን። 

ይህም ተያዥ የዕለት ጉርስ አጥተን በተራብን ጊዜ ወይም የዓመት ልብስ አጥተን ስንራቆት  ከብዙ ደጅ ጥናት በኋላ የሚደርስልን ምድራዊ ባልንጀራ አይደለም፤ ስለ እኛ የተራበ፣ ስለ እኛ የተጠማ፣ ስለ እኛ ርቃኑን የተሰቀለ፣ እስከ መስቀል ሞት፣ እስከ መቃብርም ድረስ ዋጋ የከፈለልን፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ፣ “ብሉ፤ ጠጡ፤ ከዘለዓለም ረኃብም ዳኑ፤” ያለን፣ በጸጋው ርቃናችንን የሸፈነልን፣ በሞቱ ሞታችንን ድል የነሣልን፣ በትንሣኤውም ትንሣኤያችንን ያወጀልን፣ ዕድሜ ዘመናችንን ሙሉ ከፍለን የማንጨርሰውን  የበደላችንን ዕዳ ከፍሎ ከፍጹም ባርነት ነፃ ያወጣን፣ ሳይገባን ልጅነትን የሰጠን፣ ከገቡ መውጣት ካገኙም ማጣት የሌለበትን ፍጹሙን ተድላ መንግሥቱን ሊያወርሰን የታመነ የማያልቅበት ፍጹም ባለጻጋ እግዚአብሔር አምላካችን ነው።   

ስለዚህ ይህን ታላቅ የአባትነት ውልታ በምንዘክርበት በበዓለ ትንሣኤ ክርስቶስ እንደራራልን ለድሆች መራራት፣ ከችግራችን ነፃ እንዳወጣንም የድሆችን ችግር መጋራት፣ ደስታችንን እንዳበዛልንም ድሆችን ማስደሰት አይገባንምን  ብቻችንን በልተን፣ ጠግበን፣ ለብሰንና አጊጠን ስንደሰት የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ የሌላቸውን ከዘነጋናቸው ግን ራስ ወዳዶች ሆነናል። “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” ያለውን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃልም ዘንግተናል። (ዮሐ.፲፭፥፲፪) ስለዚህም “ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፤ … ከእኔ ወግዱ” መባላችን አይቀርም። 

ስለሆነም ምእመናን ሳይሳሳ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ከዘለዓለም ረኀብ ያዳነንን ጌታ ትንሣኤውን ስንዘክር ድሆችንና ጾም አዳሪዎችን እናት አባት የሞቱባቸውን ልጆችና ጠዋሪ ቀባሪ ያጡ አረጋውያንን ልናስባቸውና ደስታችንን ልናጋራቸው ይገባል። ያለበለዚያ ግን የክርስቶስን በዓል ያለ ክርስቶስ ብቻችንን እንደ ማክበር ይቆጣራል። ምክንያቱም የክርስቶስ ማደሪያዎች የሆኑትን ድሆችን አላገለገልንምና። በክርስቶስ በዓል ከክርስቶስ ተለይቶ ብቻ ከመዋል በላይ ብክነት የለም። ለዚህ መልካም ምሳሌ የምትሆነን ማርታ ነች።

ማርታ ከዕታት አንድ ቀን ጌታ ቤቷ ውስጥ በመጣ ጊዜ እኅቷ ማርያም በጌታ እግር ሥር ቁጭ ብላ ስትማር እርሷ ግን እንግዳ መጣብኝ ብላ ምግብ ልትሠራ ትባክን እንደነበር ታሪኳ ይናገራል። የማርታ ነገር የሚያሳዝነው ምግበ ሥጋ ምግበ ነፍስን የፈጠረ፤ ለእስራኤል አርባ ዘመን ሙሉ መና የመገበ፣ ጥቂቱን እንጀራና ዓሣ አበርክቶ የአምስት ገበያ ሕዝብን የመገበ ጌታ በቤትዋ ሳለ ብቻዋን መባከኗ ነው። ዛሬም ብዙዎቻችን ድሆችን ወደ ቤታችን የማንጠራቸው፣ አቅማችን አይፈቅድልንም፣ የደገስነውም ለሁላችን አይበቃም በሚል ሥጋት ነው። የሚገርመው ግን እኛ ድሆችን ወደ ቤታችን ጠርተን ከእነርሱ ጋር አብረን ስንበላ አብረንም ስንጠጣ ከእነርሱ ጋር አብሮ ወደ ቤታችን ከሚገባው ክርስቶስ ጋር አብረን እንደምንበላ አብረንም እንደምንጠጣ ያለማስተዋላችን ነው። ታዲያ በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣ የአምስት ገበያ ሕዝብ የመገበውን፣ ውኃውን ለውጦ ጣፋጭ የወይን ጠጅ አድርጎ የዶኪማስን ልብ ያሳረፈውን በአጠቃላይ ጥቂቱን ማብዛት ብቻ ሳይሆን የሌለውን እንዲኖር ማድረግ የሚቻለውን ጌታን ወደ ቤታችን ጠርተን ለመጋበዝ እንዴት እምነት አጣን? ማርታም የባከነችው ጥቂት እምነት አጥታ ነበር፤ ጌታም “ማርታ፥ የሚያስፈልገው ጥቂት ሆኖ ሳለ ስለምን ትባክኛለሽ” አላት። በእግሩ ሥር ቁጭ ብላ ቃሉን ትመገብ ስለነበረችው ስለ እኅቷ ስለ ማርያምም ሲናገር “ማርያም ግን መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” ብሏል። (ሉቃ.፲፥፴፰-፵፪)  

ዛሬም እንደ ማርታ ብኩን የሆንን ብዙዎች ነን። ለበዓሉ የሚያስፍልገንን ዶሮውን፣ በጉን፣ ቁርጡን፣ ጥብሱን፣ ማሩን፣ ጠጁን፣ ለማዘጋጀት ብዙ እንደክማለን፤ ልክ እንደማርታ፣ የሀብሻ ልብስ፣ የፈረንጅ ልበስ እያልን እንጨነቃለን። የበዓሉን ባለቤት ክርስቶስን ግን ሳንጋብዘው እንቀራለን፤ በዓሉ የማን እንደሆነ ከማን ጋርም ማክብር እንዳለብን፣ ማንን መጋበዝም እንደሚገባን አናውቅም። በየቤቱ በልቶ የጠገበውን ጠጥቶ የሰከረውን ጋብዘን አልበላ አልጠጣ በሚልበት ጊዜ ባይጣፍጥ ነው እንጂ ምግቡና መጠጡ ቢጣፍጠውማ ይበላልን ነበር በሚል ተጨማሪ ጭንቀት ውስጥ እንገባለን። ከዚህ በላይ ብክነት ምን አለ? በድሆች አድሮ “ራበኝ፤ ጠማኝ፤ አብሉኝ፤ አጠጡኝ” እያለ ያለውን በደጃችን የቆመውን ክርስቶስን ገፍተነዋልና፤ ሁሉ እያለን ባዶነት ይሰማናል፤ በደስታችንም ቀን በከንቱ እንጨነቃለን። የክርስቶስን በዓል ያለ ክርስቶስ ማክብር ማለት ይህ ነው። ማርታም የገጠማት ይህ ነበር። ለክርስቶስ የሚያስፍልገው ምን እንደሆነ ሳታውቅ፣ ክርስቶስን ለማስደሰት ትባክን ነበረና፤ አልፎ ተርፎም ለክርስቶስ የሚያስፍልገውን ዐውቃ ለክርስቶስ ልቧን የሰጠችውንና በእግሩ ሥር ቁጭ ብላ መማርን የመረጠችውን እኅቷንም ትቃወም ነበር። እንግዲህ እኛ ማርታን ሳይሆን ማርያምን እንሁን፤ ክርስቶስን ለማስደሰት ብዙ መጨነቅ ሳይሆን እርሱ የሰጠንን ጥቂቱን ከድሆች ጋር ተካፍሎ መብላት በቂ መሆኑን እንገንዘብ።

Read 2172 times