Monday, 09 November 2020 00:00

በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ግፍና መከራ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ

Written by  ካሣሁን ለምለሙ

Overview

በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ግፍና መከራ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው ግፍና መከራ እንዲቆምና በየምክንያቱ የታሠሩ ካህናትና ምእመናን ጉዳያቸው በጥንቃቄ ታይቶ ከእስር እንዲፈቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳሰበ፡፡ የታችኛው የመንግሥት መዋቅር ባለሥልጣናት ለጥፋተኞች ከሚያደርጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው አሳስቦ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ለደረሰው ጥፋትና ለወደፊትም ለሚደርሰው የሕግ ክትትል በማድረግ ችግሩን የሚከላከሉ የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉር ስብከት ድረስ እንዲቋቋም መወሰኑን አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱ ያለው ወቅታዊ የሰላም እጦትና አለመግባባት ለዜጎች ተረጋግቶ አለመኖር እንዲሁም ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ በመሆኑ በቀጣይ አላስፈላጊ ሁከት ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ እርቅና ሰላም ማምጣት አስፈላጊ እንደሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አስገንዝቧል፡፡ የእርቅና የሰላም ሂደቱን የሚያስፈጽሙ ብፁዓን አባቶችም በአስታራቂነት መሰየማቸውን አስታውቋል፡፡ አገራዊ ሰላምና አንድነት እንዲኖር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት የእርቅ ሂደቱ እንዲቀጥል የፌዴራልና የክልል መንግሥታት መሪዎች ጥረት እንዲያደርጉ እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሀገሩ አንድነትና ሰላም ዘብ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አፈጻጸምን በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየተወሰኑ የተፈጸሙና ያልተፈጸሙትን በመለየት ያልተፈጸሙትን ምክንያታቸውን በመለየት ለፊታችን ግንቦት ርክበ ካህናት ውጤቱ እንዲቀርብ መወሰኑንም መግለጫው አመልክቷል፡፡  
Read 689 times