Monday, 11 January 2021 00:00

በሀገራችን እየተከሠተ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ኅብረተሰቡ ማኅበራዊ አንድነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በሀገራችን በየአቅጣጫው እየተከሠተ ያለውን አለመግባባትና ግጭት ኅብረተሰቡ በጥበብና በማስተዋል እንዲመለከተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ታኅሣሥ !፯ ቀን !)፲፫ ዓ.ም በዓለ ልደተ ክርስቶስን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጥሪ አቀረቡ።  እየተከሠቱ ያሉ አለመግባባቶች ግጭቶች ልማትን፣ ነፃነትንና፣ ሉዓላዊነትን የሚፈታተኑ በመሆናቸው ሁሉም ለሀገሩና ለሃይማኖቱ እንዲሁም ለወገኑ ተገቢ ትኩረት በመስጠት በጸሎትና በሚችለው ሁሉ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስነታቸው በመግለጫው ጠይቀዋል።  በሀገራችን የተከሠቱት አለመግባባቶች አየተካረሩ መጥተው ወደ ግጭት እንዳያመሩ የጠቆሙት ቅዱስነታቸው በግጭቶቹ ምክንያት የሰው ሕይወት እልቂት፣ ረኀብ፣ መፈናቀልና ሌሎች መኅበራዊ ቀውሶች እየተፈጠሩ እንደሆነም ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው አያይዘውም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝንና የኤች አይ ቪ ቫይረስ በሽታዎችን ለመከላከል ከቸልተኝነት መራቅ እንደሚገባ በመግለጫቸው አስገንዝበዋል።  በመጨረሻም የክርስቶስን ልደት ስናስብ ለእግዚአብሔር ክብር በመቆም ሰላምንም በመስጠትና በመቀበል ሊሆን ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው የታመሙና የታሰሩትን በመጠየቅ፣ የተራቡትንና የተጠሙትን በማብላት በማጠጣት፣ የታረዙትንም በማልበስ፣ ለእግዚአብሔርና ለወገን ያለንን ክብርና ፍቅር በመግለጽ በዓሉን ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል። 
Read 621 times