- Details
- Category: የማኅበረ መልእክት
የ ምንገኝበት ዘመን መከራ የበዛበት በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበርና መደጋገፍ የሚጠይቅ ነው። መከራ ሲገጥመን መተባበር እንደሚኖርብን የማንም ማሳሰቢያና ማባበያ አያስፈልገንም። በአገራችን እየደረሰ ያለው መከራ ሊያስተባብረን ካልቻል ሌላ የሚያፋቅረን ነገር ማግኘት አንችልም። የምንኖርባትን ዓለም ጣዕም የቀየሩት ራሳቸውን ብቻ ለማትረፍ ሲደክሙ የኖሩት ሳይሆኑ በመተባበር ለመከራ የተዳረጉትን ሰዎች ሕይወት ሲታደጉ የኖሩት መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል። ከመለያየት ይልቅ መተባበር፣ ከመቀበል ይልቅ ለተቸገሩት መስጠት የቻሉት የሰው ፍቅር የበለጠባቸው፣ ለእነርሱ የሚያስፈልጋቸው ለችግር ለተጋለጡትም የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የተረዱ ናቸው። መስጠት ደስታን ሲሰጥ መቀበል ኃፍረትን ያላብሳል። መተባበርና መደጋገፍ ኃይል ሲፈጥር መለያየት ደግሞ አገርን ስለሚያዳክምና ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ መልካም ነው ተብሎ የተነገረውን ስለሚቃረን መተባበር ይገባል። ዘመኑ መደጋገፍና መረዳዳት የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት ከራስ ወዳድነት መላቀቅ ታላቅነት ነው። ቀያቸውን ለቀው የተሰደዱ፣ ሀብት ንብረታቸውን አጥተው በችግር የሚሰቃዩ፣ ወገኖቻቸው አልቀው በኀዘን የተጨበጡ ወገኖቻችን ቍጥር ከሚሊዮን በላይ ሆኗል። የተቸገሩትን መርዳት ሃይማኖታዊ ግዴታችን፣ ሥነ ምግባራዊ መገለጫችን መሆኑን ተረድተን ከሌሎቹ ቀድመን ለተቸገሩ ወገኖቻችን መድረስ የሚገባን ክርስቲያኖች ነን። አገራችን ሰላም ውላ እንድታድር ታላቅ ኃላፊነት እንዳለብን መዘንጋት የለብንም። መልካም በማድረግ የተጎዱትን የምንደግፈው በሌሎች ላይ የደረሰው መከራ እንዲደርስብን ስለማንፈልግ ብቻ ሳይሆን ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ በአምላኩ ዘንድ የሚመሰገን በመሆኑ ጭምር ነው። የሃይማኖት ልዩነት ሳንፈጥር ለተቸገሩ ወገኖቻችን ስንደርስላቸው በአንድ በኩል ክርስቲያናዊ አስተምህሯችን ለሌሎች ይገለጣል። ከዚህ በተጨማሪም ክርስቲያኖች የተቸገሩትን በመደገፋችን የሞራል ልዕልናችንን ዓለም ያውቀዋል። ሰዎች ሲቸገሩ ዓይተው የሚያዝኑ ክርስቲያኖች ንዑዳን ክቡራን ተብለው ተመስግነዋል። ወገኖቻችን አገር ለቀው ተሰደው፣ ቀያቸውን ትተው ተፈናቅለው እያየን ለእነርሱ የምናደርገው ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለእነርሱ ማዘናችን ንዑዳን ክቡራን ያሰኘናል ማለት ነው። በእርግጥ ክርስቲያኖች ለተቸገሩ ወገኖቻችን ሁሉ መልካም የምናደርገው ሰዎች ያመስግኑን፣ ንዑድ ክቡር ይበሉን ብለን አይደለም። ሰዎችን መደገፋችን አምላካችንን ስለሚያስደስተው ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ስንኖር አምላካችንን የሚያስደስት በጎ ምግባር መፈጸም ስላለብን ነው። መከራ ሲመጣ ደግሞ የበለጠ መተባበርና መደጋገፍ ይኖርብናል። የተፈጠርንለት ዓላማ ሠርተን ያገኘነውን ራሳችን በልተን እንድንደሰት ሳይሆን ሠርተን ካገኘነው ለሌላቸው ወገኖቻችን እንድናካፍል፣ ተባብረን ወገኖቻችንን ከሞት እንድንታደግ ነው። ተጋግዘን ለተቸገሩ ወገኖቻችን በመድረስ ሕይወታቸው እንድትቀጥል፣ ዕድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሓ እንዲያገኙ ስናግዛቸው ደስታችን ፍጹም ይሆናል። በሃይማኖት የሚመስሉን ብቻ ሳይሆኑ የማይመስሉን ወገኖቻችንም በደረሰባቸው ችግር ምክንያት አገር ለቀው ሲሰደዱ፣ በስደት ወደ አሕዛብ አገር ሲሄዱ መታደግ ከክርስቲያኖች ሁሉ የጠበቅ ተግባር ነው። ለወገኖቻችን ራሳችንን ዐሳልፈን ለመስጠት የሚያስችል መንፈሳዊ ጥብዓት ባይኖረን እንኳ ከገንዘባችን ከፍለን ለተቸገሩ ወገኖቻችን መደገፍ ከሚጠበቅብን ክርስቲያናዊ ትሩፋት ትንሹ ነው። እስከ ሞት ድረስ የተቸገሩትን ሐመር ታኅሣሥ-፳፻፲፬ ዓ.ም. የማኅበሩ መልእክት ፫ በመርዳት መታደግ፣ ሰውን ሁሉ መውደድ እንደሚገባን የተነገረን ለራሳችን ከሚያስፈልገን ቀንሰን ሌሎችም እንደሚያስፈልጋቸው አምነን እንድንረዳቸው ነው። እውነተኛ ወገን የሚታወቀው በመከራ ዘመን በመሆኑ አገር ለቀው ለተሰደዱ፣ በችግር አሽክላ ታስረው ለሚሰቃዩ፣ ረሃብና ኀዘን ተጨምሮባቸው ለሚንገላቱ ወገኖቻችን በመድረስ አለኝታነታችንን በተግባር እናሳያቸው። ከመንፈስ ልዕልና የደረሱት ሰዎች ለራሳችን ይቅርብን ብለው ወገናቸውን ሲያስቀድሙ እኛ ደግሞ ቢያንስ ካለን በማካፈል ለወገን አለኝታነታችንን እናረጋግጥ። በዘመናችንም ቅዱሳን ከፈጸሙት ያልተናነሰ ተግባር በመፈጸም ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን የሚገልጠው ጦርነት በተነሣባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ምእመናን የፈጸሙት ተግባር ነው። በጦርነት ምክንያት ቀያቸውን ለቀው የተሰደዱትን፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ለችግር የተጋለጡትን ወገኖቻችንን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የቋንቋም ሆነ የመልክአ ምድር ልዩነት ሳናደርግ መርዳት ከክርስቲያኖች ሁሉ የሚጠበቅ በጎ ተግባር ነው። በአሳብ አንድ ሆነን የወገን ፍቅር በልጦብን ተባብረን የተቸገሩትን ከደገፍን “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ”፤ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም” ተብሎ የተነገረውን በተግባር ፈጸምን ማለት ነው። በክርስቲያናዊ ምግባራችን አልጫውን ዓለም ማጣፈጥ፣ ጨለማውን ዓለም ማብራት ሲገባ ገብር ሐካይ መሆን የለብንም።ክርስቲያኖች የተራራ ላይ ብርሃንና የምድር ጨው መሆናችን የሚገለጠው ሠርተን ካገኘነው ለወገኖቻችን ስንተርፍ ነው። ሰዎች ለመከራ በተጋለጡበት ዘመን የተቸገሩትን መረዳት ለተረጅዎች የሚኖረውን ጠቀሜታ ቃላት የመግለጥ አቅም የላቸውም። ተባብረን ወገኖቻችንን ስንረዳቸው ተጎጂዎች የሚያስብልን ወገን አለ ብለው ተስፋቸው ይለመልማል፤ ዙሪያው ገደል የሆነባቸው መውጫ መንገዱ ይታያቸዋል። ተስፋቸው መለምለም ብቻ ሳይሆን ተፈናቃዮች በደረሰባቸው መከራ ምክንያት በረሃብ እንዳያልቁ ያደርጋል። ልጆቻቸው ተርበው ሲያለቅሱባቸው ተስፋ ቆርጠው አምላካቸውን እንዳይክዱና ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ በመተባበር ወገኖቻችንን መርዳት ይኖርብናል። ተፈናቃዮች ዕድሜ ልካቸውን በሰው ድጋፍ ላለመኖርና ሠርተው ተለውጠው ራሳቸውን በመቻል ሌሎችን እንዲረዱም ተግባራዊ ትምህርት ያገኙበታል ብለን እናምናለን።
- Details
- Category: የማኅበረ መልእክት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንን የምትደግፈው ኃላፊነቷ በመሆኑ ነው። የሰውን ልጅ ሁሉ የምትረዳውም ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሳትለይ ሰው መሆናቸውን በማየት ብቻ ነው። መመሪያዋም “ለድኃና ለምስኪን የሚያስብ ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል። እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ ሕያውም ያደርገዋል፤ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፣ በጠላቶቹ እጅ አሳልፎ አይሰጠውም” የሚለው አምላካዊ ቃል ነው (መዝ.፵፥፩-፪)። ይህ ቃል ለተቸገረ መርዳት በእግዚአብሔር እንድንጠበቅ ከማድረግ በተጨማሪ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ድርጊታችንን ዓይተው፣ ሥራችንን ከግምት ውስጥ አስገብተው እንዲያመሰግኑን ምክንያት ይሆናል። ወደ ሃይማኖት እንዲመጡም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ቤተ ክርስቲያን በመዋቅርም ሆነ ልጆቿ በተናጠል ለተቸገሩት መድረሳቸው ሁሉን ሰብሳቢና ለሁሉ ደራሽ ሲያሰኛት ኖሯል። ሐኪም ሰዎችን የሚያክመው ዘር ሳይለይ፣ ቋንቋ ሳይመርጥ ፣ ወገን ጠላት ብሎ ሳይከፋፍል በጦርነት ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሁሉ መሆኑ ይታወቃል። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ርዳታና ድጋፍ ደግሞ ከሐኪምም በላይ ነው። ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ በየዘመናቱ ለተቸገሩት ስትደርስ የኖረችው አምላካዊ ትእዛዝ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሕይወት ለአደጋ መጋለጥ ስለሚያሳስባትም ጭምር ነው። ቤተ ክርስቲያን እንዲህ በማድረጓም “መልካሙን ሥራችሁን ዓይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” የሚለውን አምላካዊ ቃል በተግባር ትገልጣለች (ማቴ.፭፥፲፮)። ይህም አሕዛብ ሥራዋን አይተው የክርስቶስ አካል፣ የቤተ ክርስቲያን አባል እንዲሆኑ መንገድ ይከፍታል። በዘመናችን በተከሠተው ጦርነት ወገኖቻችን ሀብትና ንብረታቸውን አጥተዋል። ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህል አካባቢ ሳይለይ ለስደትና ለረኃብ ተዳርገዋል። በጦርነት የተሰለፉትም ከግራም፣ ከቀኝም እየቆሰሉ ነው። ችግሩ ያሳሰባቸው ወገኖች የተፈናቀሉትን ለመርዳት አቅማቸው የፈቀደውን በማድረግ ላይ ናቸው። ምንም እንኳ ርዳታን ምክንያት አድርገው ለችግር በተጋለጡ ወገኖቻችን ቍስል እንጨት የሚሰዱና ሕመማቸውን የሚያባብሱ አካላት ቢኖሩም ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን የምትረዳው ሰው በመሆናቸው ብቻ በመሆኑ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን በማጣት ከችግራቸው እንዲላቀቁ፣ ከሥነ ልቡና ስብራት ተላቀው ነገ አዲስ ሕይወት መኖር እንዲጀምሩ ለማድረግ ጭምር ነው። የተጎዱት ወገኖቻችን ከዚህ ደረጃ እንዲደርሱ ብዙ መሥራት፣ ልጆቿን አስተባብራ ለተቸገሩት ሁሉ በመድረስ ከመከራ እንዲያወጧቸው ማድረግ ይኖርባታል። ‹‹ለተቸገረ የሚረዳ ብፁዕ ነው›› ሐመር ጥቅምት-፳፻፲፬ ዓ.ም. የማኅበሩ መልእክት ፫ ቤተ ክርስቲያን ዘር፣ ሳትመርጥ፣ ቋንቋ ሳትለይ ሁሉንም የምትረዳውም ተልእኮዋ ሰማያዊ በመሆኑ ነው። በተጎዱት አካባቢዎች የሚገኙ አባቶች ሆስፒታል ሔደው የቈሰሉ ወገኖቻችንን ሲጠይቁ የተመለከትነው፣ ከችግረኞች ጋር አብረው በዓል ሲያከብሩ ያየነው ሰዎች ችግር በገጠማቸው ጊዜ እንድትደርስላቸው ከአምላኳ በመታዘዟ ነው። በግል ከመሮጥ ይልቅ እየተሰባሰቡና እየተደራጁ ለችግረኞች የሚያስፈልጋቸውን በማሰባሰብ ማድረስ ያስፈልጋል። ክርስቲያኖች ይህን የምናደርገው የሰው ልጅ ሁሉ ጉዳት ጉዳታችን መሆኑን ስለምናምንና በሌሎች የደረሰ ክፉ ነገር እንዲደርስብን ስለማንፈልግ ነው። ምእመናን ልጆቿ ለችግር ለተጋለጡት የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብና የቍሳቁስ ድጋፍ ለማሟላት የበኩላችንን እናበርክት የምንለው እንደሌሎች በችግረኞች ጉዳት ለመነገድ እና ታዋቂነትን ለማግኘት ሳይሆን ለተቸገረው ሁሉ መድረስ ከአምላካችን የታዘዝነው በመሆኑና እየተሠራ ካለው የበለጠ መሥራት ስለሚጠበቅብን ጭምር ነው። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተግባሯ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ማገናኘት ብቻ ሳይሆን በችግራቸው ጊዜ ቀድማ በመድረስ መርዳት መሆኑን መረዳት ይገባል። ቤተ ክርስቲያን ችግረኞችን ከረኃብና ከጊዜያዊ ችግር ነፃ እንዲወጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አጽናንታ በገጠማቸው ጊዜአዊ ችግር ሳይሸነፉ ነገ ታላቅ ደረጃ ሊደርሱ እንደሚችሉ ጭምር መንፈሳቸውን ማነቃቃትም እስከ አሁን ከተሠራው የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ክርስቲያናዊ ተግባር መሆኑን ክርስቲያኖች ሁሉ እንረዳ። ስለዚህ የገንዘብ ችግር ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቡና ስብራት የገጠመውንም በመንፈሳዊ ምክር መርዳት ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን መረዳት ይገባል። የቤተ ክርስቲያን ብርሃንነት ለአሕዛብ ከሚገለጥበት ይህ ነውና። ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራዊ ተግባራት አንዱ ለችግር የተጋለጡትን ለመርዳት ቀድሞ መገኘት ነው። ማኅበራት፣ መምህራነ ወንጌል፣ ዘማርያንና ምእመናን ሁሉ እየተባበሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለአደጋ የተጋለጡትን ሁሉ በመርዳት ለወገን ደራሽነታቸውን፣ ከራሳቸው ይልቅ ሌሎችን የሚያስቀድሙ መሆናቸውን ካስመሰከሩ የቤተ ክርስቲያን ብርሃንነት ለአሕዛብ ሁሉ እንዲገለጥ ያደርጋል። እንዲህ ማድረጋችንም “ተርቤ አብልታችሁኛልና፣ ተጠምቼም አጠጥታችሁኛልና፣ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፤ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፣ ታምሜም ጠይቃችሁኛል፣ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና” ተብለው ከሚመሰገኑትና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ግቡ ከሚባሉት ወገኖች ጋር አንድ ያደርገናል። በምድርም የአእምሮ ሰላም እንደምናገኝ አስበን ምክንያት ሳናበዛ ሰውን ሁሉ ለመርዳት ጊዜ ሳንወስድ ተግባራዊ ሥራ መሥራት ችግሩ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ተባብረን ወገኖቻችንን ከችግር በመታደግ ለተቸገረ የሚደርስ ብፁዕ ነው የተባለውን አማላካዊ ቃል በተግባር መግለጥ እንደሚገባ ማስገንዘብ እንወዳለን።
- Details
- Category: የማኅበረ መልእክት
በአዲስ ዓመት አዲስ ሰውነት አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ሰው ለመሆን ተዘጋጅቶ መጠበቅ ከመንፈሳውያን ሁሉ የሚጠበቅ በጎ ተግባር ነው። ሰዎች ካልተቀየርን የዘመኑ መቀየር ብቻውን ጠቀሜታ የሌለው መሆኑን ተረድተን በዘመኑ ለመጠቀም መወሰን ይኖርብናል። ከዘመን ዘመን ስለተሸጋገርን ብቻ የምንደሰት ከሆነ የተፈጠርንበት ዓላማ፣ የመኖራችንም ትርጕም አልገባንም ማለት ነው። አዲስ ዘመን ሲመጣ ሕይወትን ለመቀደስ ካልተጠቀምንበት ተፈጠሩ ሞቱ መባል ብቻ ይሆናል። ነቢዩ ዳዋት “በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ፣ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ፤ የምድረ በዳ ተራሮችም ይረካሉ፤ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ”(መዝ.፷፬፥፲፩-፲፪) በማለት የተናገረው በኃጢአት ባሕር ሲዋኝ የኖረውን፣ ከእግዚአብሔር ተለይቶ፣ ከመጥፎ ነገር ጋር ተባብሮ ይኖር የነበረውን መልካም እንዲያስብ፣ ሟች መሆኑንም እንዲገነዘብ በማድረግ የጽድቅን ጎዳና እንዲከተል ልቡናውን የቀሰቀሰው እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ለመመስከር ነው።
- Details
- Category: የማኅበረ መልእክት
ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሐዋርያዊት ርትዕት የሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር መባልዋም እግዚአብሔርን በብሉይ ኪዳን የአመለከች፣ በልደቱ ቤተ ልሔም ድረስ አምኃ ይዛ የሄደችና ሰግዳ መባዕ ያቀረበች (መዝ. ፸፩፥፱-፲፩)፣ በስደቱ ጌታን ከእናቱ ጋር የተቀበለች፣ በጃንደረባው አማካይነት በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ወንጌልን ተሰብካና አምና በሐዋርያት እጅ ተጠምቃ ክርስትናን የተቀበለች (ሐዋ.፰፥፳፯-፵) ሀገር በመሆኗ ነው፡፡ ወደ ፈጣሪዋ የተዘረጉት እጆቿ በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ ከማንም አገር በተለየ ሁኔታ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ከእግዚአብሔር ተቀብለዋል፡፡ ለአብነትም በዘመነ ብሉይ ታቦተ ጽዮን ከብዙ ንዋያተ ቅድሳት ጋር፣ በዘመነ ሐዲስ ኪዳን ደግሞ ግማደ መስቀሉንና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አባቶቻችን በሃይማኖታቸው ጸንተው በጎ ምግባር ሠርተው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር በመቻላቸው ነው፡፡
በዚህም አባቶቻችን ሃይማኖታቸውን ከአገራቸው አልፈው በኢየሩሳሌምና በሌላውም ዓለም አስፋፍተዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቅዱሳንም ኢትዮጵያን በመንፈስ ተረድተው ከሀገራቸው ተሰደው ተሸሽገውባታል፤ ሃይማኖትንም ሰብከውባታል፡፡ ለአብነትም ዘጠኙ ቅዱሳንንና አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያን አገሪቱን በታሪክ በቅርስና በጀግንነት ማማ ላይ ሆና ከፍ ብላ እንድትታይ አብቅታለች፡፡ የክርስትና ሃይማኖት በሌሎች አገሮች የተሰበከው በብዙ የደም ሰማዕትነት ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ግን በእግዚአብሔር ቸርነትና ፈቃድ ሃይማኖት ከቤተ መንግሥቱ ጀምሮ ወደ ሕዝቡ ስለተሰበከ የክርስትናው ሃይማኖት በሰላም እንዲሰበክ ጥሩ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ይሁንና ይህን የሰላምና የጥበብ ጉዞ ለማደናቀፍ ጠላት ተኝቶ አያወቅም፡፡ ከምንጩ ቀድታ በሰላም ስትመራው የኖረችውን ክርስትና ከምንጩ ያልቀዱት በተንሸዋረረ መንገድ የተሰበኩት ምዕራባውያኑ ግን መስመሯን ሊያስቱ ሲታገሏት ሲፈታተኗት መኖራቸው የማይዘነጋ ሐቅ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ብናይ በአፄ ሱሱንዮስ ዘመን፣ በፋሽሽት ጣሊያን ወረራና በየጊዜው ነገሥታቱን በመሣሪያና በመሳሉት በመደለል ቤተ ክርሰቲያንን ለመከፋፈል የተከናወኑ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን አንተ ዐለት ነህ ባንተ ዐለትነት ቤተ ክርስቲያንን እሠራታለሁ፡፡ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፡፡ (ማቴ.፲፮፥፲፰) እንዳለው አጽራረ ቤተ ክርስቲያናት ምንም ቢጥሩ ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፉ አልቻሉም፡፡ እነርሱ እየጠፉ ቤተ ክርስቲያን ግን እያበበች፣ እያፈራችና እየተስፋፋች ኖረች እንጂ፡፡
ዲያብሎስ በየዘመናቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ በውስጥም በውጭም ፈተና እያስነሣና የፈተናውን መልክ እየለዋወጠ ምእመናንን ሲያምስና ሲያውክ ኖሯል፡፡ በውጭ ካሉት የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች በሚነሣ ፈተና ብቻ ሳይሆን በውስጥ ባሉ ሐሰተኛ መምህራንም ፈተናው እንደሚነሣ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ዘመን ያለው ዋና ፈተና ደግሞ የዘረኝነትና የፖለቲካ መንፈስ ነው፡፡ ድንበር የለሽ የሆነውን ዋናውን የክርስትና ዓላማና ጉዞ ዘንግተን በዘር በጎሣ በቋንቋ በአካባቢ እየተከፋፈልን በመሆኑ ይህ ክፉ ሥራችን ቤተክስቲያንን ማዕበል ሆኖ እያናወጣት ይገኛል፡፡ ቤተክርስቲያን ሰማያዊት ናት፡፡ ቤተክርስቲያን አምነው የተጠመቁ ከእርስዋ ለተወለዱ ሁሉ እናት ናት፡፡ ዘር ቀለም ቋንቋ እውቀት ውበት ጉስቁልና ወንዝ መንደር አይወስናትም፡፡ ድንበር የለሽም ናትና በእኛ የአስተሳሰብ ልክ ልንወስናት አንችልም፡፡
አባቶቻችን በእምነት ጉዞ ውስጥ አንዳንድ የአመለካከት መለያየቶች እንኳ ሲፈጠሩ ተረጋግተው ተወያይተው ተከራክረው ለመፍታትና ፍቅርና አንድነት ለመፍጠር ብዙ ጥረት ያደርጉ የነበረው ፍቅርን ማስቀደም ስለሚበልጥ ነው፡፡ ወደ መጨረሻው ውሳኔ የሚደርሱት አማራጭ ከጠፋና የሃይማት ልዩነት ሆኖ ሲገኝ ነው ፡፡ ያውም ቢሆን እንደዘመናችን ለግል ፍላጎትና ጥቅም ወይም የሥልጣን ፍላጎት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንና መንጋውን ከአደጋ ለመታደግ ሲሉ ነበር የተፈለገውን መሥዋዕትነት ለመክፈል የሚተጉት፡፡ በዘመናችን ሕግና ሥርዓት በሰፈነበት ተወያይቶና ተመካክሮ ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ሲቻል በሠለጠነ ዘመን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የአገርን ሰላማዊ ጉዞ የምእመናንን ፍቅርና አንድነት በሚያናጋ መልኩ ፅንፍ ይዞ ያለመንገዱ መሄድ ለማንም የማይጠቅም ነው፡፡
ይህን የሚያሰኘን በምሥራቅ ጎጃም ከቅባት ትምህርት ጋር በተያያዘ የተከሠተው የመለያየት አጀንዳ ነው፡፡ በመጀመሪያ በጥንቃቄ ማየት ያለብን መለያየት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ አለመሆኑን ነው፡፡ ከወገኖቻችን እንደችግር የተነሡትም ጉዳዮች መፍትሔ የሚፈልጉ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ቢሆኑም ለቀኖና እና በሕግ ጥሰት የሚዳርጉ ግን ሊሆኑ አይገባም፡፡ በአንዲት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና የሚመራ ማንኛውም ተከታይ የሐዋርያትን ዶግማና ቀኖና በግብታዊነት ሊንድ ሊሽር ፈጽሞ አይችልም፡፡ ማዕከላዊነትን ሳይጠብቁ በየፊናቸው የፈለጋቸውን የመሾም በፈለጉት መንገድ የመጓዝ አካሄድ የፕሮቴስታንቶች ባህል እንጂ የኦርቶዶክሳውያን ትውፊትም ባህልም አይደለም፡፡ ኦርዶቶዶክስ ተዋሕዶ ማእከላዊነትን የጠበቀ አሠራር ነው የምትከተለው፡፡ የምትመራውም ከፍ ባለ ሐዋርያዊ ልዕልና በቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን እውቅና፣ ሕግና ቀኖና ውጭ ሊቀ ጳጳስ እስከ መሾም መድረስ አሳዛኝና አስደንጋጭ ኦርቶዶክሳዊ ያይደለ ምናልባትም ሁሉም ሰው ያልተገነዘበው ተቆርቋሪ መስሎ ቀርቦ የዋሁን ሕዝብ በማነሳሳት በኩል የጠላት እጅ ሊኖርበት የሚችል ባእድ ተግባር ነው፡፡
ቀደምት አባቶቻችን ሃይማኖቱን ብቻ ሳይሆን በእምነት ጉዞ ውስጥ የምንመራበትን ሕግና ሥርዓት ትልቅ መንፈሳዊና ተቋማዊ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ቅዱስ ሲኖዶስን መሥርተው አልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት በመሆኗ የትምህርት የቀኖና ሥርዓት አላት፡፡ ለመሾምም ለመሻርም ለማጥመቅም ለማውገዝም የራስዋ ሐዋርያዊ ቀኖና አላት፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር ያሉ ተቋማትም የሚመሩት በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ነው፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የወጣ ነገር በሚኖርበት ጊዜ ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቦ ሐዋርያዊ የሆነውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ተከትሎ የሚስተካከል ጉዳይ እንጂ እከሌ ወእከሊት እንዲህ አለ እንዲያ አለ ተብሎ በወፍ በረር ወሬ ቤተ ክርስቲያንን የሚያክል ታላቅ ነገር የሚለያይ ሥራ መሥራት በምንም ሚዛን ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ ቆም ብሎ ማሰብ ማረምም ይገባል፡፡
የቤተ ክርስቲያንን ወገኖች አይጠቅምም፡፡ ከጀርባ ሆነው የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማናጋት ለሚሠሩ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ለጥፋት ተልኮአቸው እድል መስጠት ነው፡፡ በአንዲት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል የቀኖና ወይም የዶግማ አረዳድና አተገባበር ላይ ልዩነት ከተፈጠረ በትምህርት የሚመለሰውን በትምህርት ፣ በውይይት የሚታረመውን በውይይት፣ በቀኖና ውሳኔ የሚፈታውን በውሳኔ ማስተካካል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ የወጣና የማይታረም ካለ አውግዞ እስከ መለየት ሊዘልቅ ይችላል፡፡ የቤተ ክርስያንን ሐዋርያዊ ዶግማና ቀኖና የማስጠበቅ ኃላፊነት ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ የተመላው በጥበብና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የታገዘ አካሄድና ውሳኔ ሊሰጡበት ይገባል፡፡
አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ምእመናንን ለመከፋል በየዘመናቱ የሚፈጥሯቸውን ተንኮሎች አባቶቻችን በጥንቃቄ ይዘው በምክርና በትምህርት እያከሙ ያቆዩትን ጉዳይ ምክንያት ፈልጎ በመቀስቀስ ከቤተ ክርስቲያን የመገንጠል፣ ሕዝብን የመከፋፈልና ለቤተ ክርስቲያን ጠላቶች መሣሪያ የመሆን አዝማሚያ ሊታረም ይገባል፡፡ ይህን የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለማኮሰስ፣ ሰላሟን ለማደፍረስ ለሚሠሩ አካላት መሣሪያ መሆን ነው፡፡ ይህን ዝም ብለን የምንመለከተው ጉዳይ አይደለም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ በጉዳዩ ተወያይቶ አስተማሪ የሆነ በቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ላይ የተመሠረተ የእርምት ርምጃ ሊወስድበት በቦታውም ሄዶ ሕዝቡን ማወያየት ማስተማር ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን በትምህርት በሥልጠናና በውይይት መፍታት ያስፈልጋል፡፡
ቀኖናዊ ውሳኔዎች የሚያስፈልጉአቸውን ጉዳዮችን ደግሞ ለይቶ መወሰን ይገባል፡፡ እንደዚህ በማድረግ ክፉ ልብና ሕሊናን በትምህርትና በንስሓ በተግሣጽም ጭምር ማስተካከል ካልተቻለ እሾሁ ካደገ መንቀል ይቸግራል፡፡ ጠላት በከፈተው በር ለመግባት ደግሞ ብዙ አሰፍስፎ የሚጠብቅ ወንበዴ ስላለ በዛ ቀዳዳና ክፍተት ገብቶ መንጋውን ይዘርፋል፡፡ ክፉውን ሕሊና አስወግደን በጎ በሆነ ሕሊና ጠንክሮና ተግቶ አብሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ይህን ክፉ ሥራ ጠላት አደረገው እንዳለ ጌታ ሁልጊዜ የሚያለያይ የሚከፋፍል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያናጋ ሥራ ከጠላት ከዳቢሎስ ነውና አውጥተን ልንጥለው በጎውን ቀናውን የፍቅር የሆነውን ልንይዘው ይገባል፡፡ ዓላማችን ቤተክርስቲያንን ማገልገል ፍጻሜያችንም መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ከሆነ አማራጩ ክፉውን ነገር ከመካከላችን አውጥቶ ፍቅርና ሰላምን መመሥረት ብቻ ነው፡፡
በአጠቃላይ ለዚህ የመለያየትና የመጠላላት ከንቱ ፍላጎት ሲባል የቤተ ክርስቲያን አንድነትና የምእመናን ሰላም ፈተና ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ስለሆነም የሚመለከተን ሁሉ ደግ የሆነውን ነገር ከክፉው በመለየት እግዚአብሔር ለሚወደውና ለበለጠው ነገር መሣሪያና ምክንያት ለመሆን የምንተጋ እንጂ በተቃራኒው ሆነን ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚጎዳ ተግባርን እየፈጸምን የምንገኝ አንሁን፡፡ ክፉውን ሐሳብ የሚለያየንን፣ መንጋውን የሚበትነውን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን የሚጎዳውን ለሀገር ለወገን የማይጠቅመውን ክፉ ሐሳብ አውጥተን እንጣለው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ደቀ መዛሙርቱ “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት” እንዳለው እኛም ክፉውን አውጥተን መልካሙን ይዘን የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን እግዚአብሔር ይፍቀድልን፤ አሜን፡፡



