ሐመርን ያውርዱ
ስምዓ ጽድቅ ያውርዱ
የወሩ የማኅበረ መልእክት
Thursday, 08 April 2021 00:00
ምእመናን በሀገራችን ኢትዮጵያ ፍትሕ ርትዕን የሚያሰፍን የፖለቲካ ድርጅት ሊመርጡ እንደሚገባ በኢ/ኦ/ተ/ቤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ አቶ ውብሸት ኦቶሮ አሳሰቡ።  ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በሀገራቸው ፍትሕ ርትዕን የሚያመጣ የፖለቲካ ድርጅት እንዲመርጡ ማኅበረ ቅዱሳን የድርሻውን እንደሚወጣ ያስታወቁት ዋና ጸሐፊው ምርጫ ላይ ባለመሳተፋቸው በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመጣ የሚችለውን ጫና እንዲረዱ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያናችን ከዚህ ቀደም በሀገራችን ፖለቲካ ላይ በበቂ ሁኔታ ባለመወከሏ ላለፉት በርካታ ዓመታት ግፍ ሲፈጸምባት እንደኖረች አክለዋል። 
Thursday, 08 April 2021 00:00
የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሥርዓተ ቀብር ረቡዕ መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።  ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (ዶር) ከአባታቸው ከባላምባራስ ተስፋ ተክሉ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ታህሣ ኃይሉ በግንቦት ወር ፲፱፻፴ ዓ.ም በትግራይ ክልል ብዛታ ወረዳ ፍልፍሎ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደረሰም በተወለዱበት አካባቢ ከአባታቸው ወንድም አባ ገብረ አረጋዊ ፊደል ንባብ የቃል ትምህርት ተምረዋል። በአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ ገዳም ከመምህር ገብረ እግዚአሔር መዝገበ ቅዳሴን፣ ከመሪጌታ ይትባረክ ጸዋትወ ዜማን አጠናቀው የተማሩ ሲሆን በጎጃም ጠቅላይ ግዛት እነማይ አውራጃ መንግሥቶ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ከመምህር ደጉ ቅኔን ከነ አገባቡ አጠናቀዋል። 
Thursday, 08 April 2021 00:00
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያን ሀገርን በሚመለከት ማንኛውም ጉዳይ ላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ስትሰጥ ቆይታለች። ተደጋግሞ እንደሚጠቀሰው የትምህርት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የማስታወቂያ ሚንስቴር፣ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ሆና ሀገርን እና ሕዝብን ስታገለግል ኖራለች። ኦርቶዶክሳውያን ልጆቿም ከቤተ መንግሥት ጀምሮ እስከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ በሀገራችን በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት፣ በአማካሪነት እንዲሁም በዲፕሎማትነት ሲያገለግሉ ኖረዋል። እነዚህ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ላይ ለነበራት ከፍተኛ ሥፍራ እና ተሰሚነት ማሳያዎች ናቸው። በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ ተቋማትም ሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የኋላ ታሪካቸው ሲታይ የቤተ ክርስቲያን አሻራ ያረፈባቸው ናቸው። በእምነት ተከታዮቿ ብዛት የሀገራችን ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሸፍን ምእመን ያላት ክርስቶሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ክብርና  ተሰሚነት የነበራት፣ ታላቅ ቦታም የሚሰጣት  ተቋም ነበረች። እንደዛሬው ሳይሆን በዚህ ወቅት በታላቁ የጾመ ሁዳዴ የመገናኛ ብዙኃኑ ሳይቀር ስለመንፈሳዊ ነገር የሚሰብኩ፣ በዘፈን ፈንታ የበገና መዝሙር የሚሰማባቸው ነበሩ። 
Wednesday, 07 April 2021 00:00
ውድ አንባብያን በዚህ ዓምድ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ነገ ምን መሆን እንዳለባት የሚያሳይ፣  ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን አባል ቤተ ክርስቲያን ልትደርስበት የሚገባትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ፣ አኮኖሚያዊና ልማታዊ አቅጣጫዎችን ማሳየት፣ ትውልዱም የድርሻውን እንዲወጣ ማመላከት ነው። በመሆኑም አስቀድመን ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? የሚለውን መሠረታውዊ ዕውቀት መረዳት ይቻል ዘንድ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የሰበከውን በተከታታይ አቅርበንላችኋል መልካም ንባብ።  እንደ እግዚአብሔር ቸርነት በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው "አሐቲ ቤተ ክርስቲያን፤ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፤" የሚል ይሆናል።
Wednesday, 07 April 2021 00:00
የቀኑ ሐሩር አናት ይበሳል፣ ከአስፋልቱ ግለት የሚወጣው ወላፈን ፊትን ከመለብለብ አልፎ ልብ ይሰልባል። በዚያ ጠራራ ፀሐይ እመቤት ከንስሓ አባቷ ጋር ለያዘችው ቀጠሮ በሰዓቱ ለመድረስ እየተጣደፈች ከአራት ኪሎ ቁልቁል በመውረድ፣ በፓርላማ በኩል አድርጋ ወደ ታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም አቀናች። ቁና ቁና እየተነፈሰች ታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ስትደርስ አማትባ ወደ ውስጥ በመግባት በስተቀኝ ካለው ዛፍ ሥር ድንጋይ ላይ ዐረፍ አለች። ቀይ ፊቷ ብስል ቲማቲም መስሏል፤ በነጠላዋ ጫፍ የፊቷን ላብ ጠርጋ በረጅሙ “ኡፍፍፍፍ…” ብላ የድካም አየር አስወጥታ ዛፎቹና ንፋሱ ከሚፈጥሩት ቀዝቃዛ አየር ወደ ውስጥ ሳበች። ጥቂት ዕረፍት አድርጋ አስፋልቱን ይዛ በቀዝቃዛ አየር ታጅባ ወደ ቤተ ክርሰቲያኑ አመራች። የታእካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ግቢ በጥንታዊ ሀገር በቀል ዛፎች እንደተከበበ ግርማ ሞገሱን ተላብሶ ይታያል፣ ነፋሻማው አየር ደግሞ ለነፍስ ሐሤትን ያጎናጽፋል፣ የአዕዋፋቱ ዝማሬ በተመስጦ ሰማየ ሰማያት አድርሶ ይመልሳል። እመቤት ቅዳሴ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለደረሰች ግቢው ውስጥ የሰው ዘር አይታይም። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንዳቀናች በሴቶች መግቢያ በኩል በማምራት ተንበርክካ በመሳለም የልቡናዋን መሻት ይፈጽምላት ዘንድ ፈጣሪዋን፣ እንዲሁም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በምልጃዋ እንድትረዳት ስትማጸን ቆየች። 
Wednesday, 07 April 2021 00:00
ቃሉን የተናገረው ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የተናገረበት ምክንያት ከየአቅጣጫው የተሰበሰቡት ሕዝብ ለተለያየ ፍላጎት እንደሆነ ያውቃልና ከፍላጎታቸው አንዱ ደግሞ አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት “በሉ እጅግም ጠገቡ ለምኞታቸውም ሰጣቸው። ከወደዱትም አላሳጣቸውም” (መዝ.፸፯፥፳፱) ተብሎ እንደተነገረ ኅብስት አበርክቶ ያበላናል ብለው የመጡ ነበሩ። እነዚህ ከየሰፈሩ የተሰበሰቡት ሰዎች እንደተራቡ ያውቃልና ደቀ መዛሙርቱ ቀድሞ እንዲያሰናብታቸው ሲጠይቁት “የሚበሉትን ስጧቸው እንጂ እንደራባቸው ሊሄዱ አይገባም” በማለት ተናገረ። ሙሉ ፅንሰ ሐሳቡን እንጥቀስና ዝርዝር ጉዳዩንም  እንመለከታለን። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው በቅዱስ ወንጌል “ጌታችን ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ በታንኳ ሆኖ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከየመንደሩ በእግር ተከተሉት። በወጣም ጊዜ ብዙ ሰዎችን አይቶ አዘነላቸው፤ ድውዮቻቸውንም አዳነላቸው። በመሸ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው ቦታው ምድረ በዳ ነው ሰዓቱም አልፏል፤ ወደ መንደር ገብተው ምግባቸውን ይገዙ ዘንድ ሕዝቡን አሰናብታቸው አሉት። ጌታችን ኢየሱስም እንደራባቸው ሊሄዱ አይገባም እናንተ የሚበሉትን ስጧቸው እንጂ አላቸው።” (ማቴ.፲፬፥፲፫-፲፮) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን።

ማስታወቂያ