Thursday, 04 November 2021 00:00

በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ቸርነት፣ ደግነት፣ ምሕረትና ይቅር ባይነት የባሕርይ ገንዘቦቹ የሆኑት አምላካችን እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠራቸው የሰው ልጆች ከመንገዱ በመውጣት በጠላት ወጥመድ ተይዘው እንዳይቀሩ “ወደ እኔ ተመለሱ” እያለ ዘወትር ይጠራቸዋል፡፡ ይህ ጥሪ የንስሓ ጥሪ ነው፡፡ ንስሓ መጸጸት፣ መቆጨት፣ በሠሩት ክፉ ተግባር ማዘን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ንስሓ በሙሉ ልብ መመለስንና መለወጥን ያመለክታል፡፡ የሰው ልጅ ድካም የሚስማማውን ሥጋ እንደ መልበሱ ይደክማል፤ ይዝላልም፡፡ ከእውነት መንገድ፣ ከጽድቅ ሕይወት ወጥቶ ይስታል፡፡ ይሁን እንጂ የሚያስብ አእምሮና የሚያመዛዝን ሕሊና ያለው ፍጡር በመሆኑ የሠራውን ስሕተት አስተውሎ ይጸጸታል፡፡ ጸጸቱ የአሳብ ለውጥ መኖሩን ያመለክታል፡፡ ይህ የአሳብ ለውጥ ብቻ መፍትሔ አይሆንምና በተግባር መገለጥ አለበት፡፡ በአሳብም በተግባርም መለወጥ ማለት የንስሓ ጥሪን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ጠቅለል አድርገን ስንመለከት ንስሓ እከብር ባይ ልቡና የሚያሳስበንን ሥጋዊ ፍላጎት ተከትለን፣ ስላጠፋነው ጥፋት፣ ስለበደልነውም በደል ምሕረትና ይቅርታ የምንጠይቅበት ለኃጢአትና ለጥፋት የጋበዘንን ሥጋችንን የምንገሥጽበት እና የምንቀጣበት፣ የእግዚአብሔርንም ቸርነት ደጅ የምንጠናበት ሥርዓት ነው፡፡ ስለዚህ ንስሓን ስናስብ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን መዘንጋት የለብንም። እነሱም፡- መናዘዝ፣ የሚሰጠንን ቀኖና መፈጸምና፣ ለኃጢአታችን ሥርየት የተሠዋልንን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም መቀበል የሚሉት ናቸው። ፩. ኃጢአትን መናዘዝ የራስን ጥፋት አውቆ ለእግዚአብሔርም ለሰውም መናዘዝ የንስሓ የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አስተምህሮ መናዘዝ ስንል ሰው በአሳብ፣ በንግግር እና በተግባር በፈጸመው ኃጢአት ተጸጽቶ “እባክህ ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቀኝ” ብሎ ጥፋቱን ለካህን ዘርዝሮ የሚናገርበት ሥርዓት ነው፡፡ አንድን ተነሳሒ እና ካህንን የንስሓ ልጅና አባት የሚያሰኘው ዋናው ጉዳይም ይህ ነው፡፡ የክርስቲያኖች የንስሓ አባት የመያዛቸው መሠረታዊ ዓላማም ይህ ነው፡፡ መናዘዝ የሚለውን ቃል ስናነሣ በሉቃስ ወንጌል የተጻፈውን የጠፋውን ልጅ ታሪክ ማስታወስ ይገባል፡፡ አንድ አባት ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ ከሁለቱ ልጆች መካከል ታናሹ ከአባቱ ንብረት የሚደርሰውን ተካፍሎ ለመውጣት ፈለገ፡፡ አባቱም ከሀብቱ ለልጁ ሊደርሰው ይገባል ያለውን ድርሻውን ከፍሎ ሰጠው፡፡ ልጁም ድርሻውን ተቀብሎ ወደ ሩቅ ሀገር በመሔድ ሀብቱን አባክኖ ጨረሰው፡፡ ኋላም በሚኖርበት ሀገር ጽኑ ራብ በሆነ ጊዜ ለአንድ ገበሬ የእሪያ ጠባቂ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ ረሃብ ስለጸናበትም እሪያዎች ከሚበሉት አሰር ሊመገብ ቢፈልግም የሚሰጠውአልነበረም። ረሃብ ሲጸናበት “ወደ ልቡ ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በረሃብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ ልሔድ። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ” አለ፡፡ ወደ አባቱ ሲሔድ አባቱ ገና ሩቅ ሳለ አይቶ አዘነለት። ሮጦም አንገቱን አቀፈና ሳመው። ጎረቤቶቹንም ጠርቶ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይበለን ብሎ ታላቅ ድግስ ደገሰ ይለናል (ሉቃ.፲፭፥ ፲፩-፴፪)፡፡ ይህን አምላካዊ ቃል በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ሊቃውንት በብዙ መንገድ ያመሠጥሩታል፡፡ እኛ ግን አንዱን ብቻ ብንመለከት የሁለት ልጆች አባት የተባለው የሁሉ ፈጣሪና አባት እግዚአብሔር ነው፡፡ ሁለቱ ልጆች ደግሞ ቅዱሳን መላእክትና አዳም /የሰው ልጆች/ ፣ የጠፋው ታናሹ ልጅ የተባለውም አዳም ፣ ወደ ልቡ መመለሱ ደግሞ ንስሓ ለመግባት መወሰኑን፣ ጥፋተኛ ነኝና ልጅህ ልሆን አይገባኝም አገልጋይህ አድርገኝ ማለቱም ጥፋተኛነቱን አምኖ፣ ተጸጽቶ መናዘዙን ያስረዳልናል፡፡ የሰው ልጅ የለበሰው ሥጋ ለኃጢአት የሚስማማ ከመሆኑ የተነሣ ዕለት ዕለት አውቆ በድፍረት፣ ሳያውቅ በስሕተት እንዲሁም በቸልተኝነት ሕገ እግዚአብሔርን ይተላለፋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከቤተ እግዚአብሔርና ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይርቃል፡፡ ይህም የሕሊና ዕረፍት፣ የአእምሮ ሰላም፣ የልብ ደስታ እንዲሁም ሰማያዊ ርስትን የሚያወርስ ተስፋንም ያሳጣዋል፡፡ ያን ጊዜም ያዝናል፤ ይከፋል፤ ወደ ልቡም ተመልሶ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ መፍትሔውም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ሽማግሌ መፈለግ ነው፡፡ ይህ ሽማግሌም ካህን ነው፡፡ ካህኑም እንደ ሽማግሌነቱ ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቀኝ ብሎ የመጣበትን ሰው አስታርቅህ ዘንድ ጥፋትህ ምንድን ነው ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ እርቅ ፈላጊውም ጥፋቱን (ኃጢአቱን) ዘርዝሮ ይናገራል፡፡ መናዘዝ የሚባለውም ይህ ነው፡፡ ኃጢአትን ለካህን የመናዘዝ ሥርዓት በኦሪት የነበረ፣ በወንጌል የቀጠለ ነው፡፡ ለምሳሌ በኦሪት “ወንድ ወይም ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፍ ዘንድ ሰው የሚሠራውን ኃጢአት ቢሠራ በዚያም ሰው ላይ በደል ቢሆንበት በሠራው ኃጢአቱ ላይ ይናዘዝ” (ዘፀ.፭፥፮) ተብሎ ተጽፏል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢአትን ለካህን መናዘዝ እንደሚገባ ለምጻሞች ቀርበው ኢየሱስ ሆይ ማረን እያሉ ወደ እርሱ ሲመጡ “ወደ ካህን ሒዱና ራሳችሁን አስመርምሩ” በማለት ወደ ካህናት ልኳቸዋል፡፡ ሔደውም ራሳቸውን ለካህን ሲያስመረምሩ (ኃጢአታቸውን ሲናዘዙ) ከበደላቸው ነጽተዋል(ሉቃ.፲፯፥፲፪-፲፭)። ራስህን ለካህን አሳይ ያለውም ለምጽ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ በሽታ ስለነበረ (ዘሌ.፲፫፥፵፭-፵፮) ከጊዜያዊውም፣ ለዳግም ሞት ከሚያበቃው ሞትም እንዲድን ነው። ለኃጢአት በሽታ መድኃኒቱ ንስሓ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ፪. ቀኖናን ተቀብሎ መፈጸም ቀኖና (canon) የሚለው ቃል ምንጩ ጽርዕ (የግሪክ) ነው። ትርጓሜውም መቃ፣ መስፈሪያ፣ መለኪያ፣ መለካት መቊጠር ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ፲፱፻፵፰፣ ገ.፯፻፺፱)። ከንስሓ ጋር በተያያዘ ያለው ትርጒም “አንድ ተነሳሒ በካህኑ ፊት ኃጢአቱን ከተናዘዘ በኋላ ካህኑ ለኃጢአት ማስተሥረያ የሚሰጠው የመንፈሳዊ ቅጣት መጠንና ዓይነት” ማለት ነው፡፡ ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ሁሉ ካህኑ ኃጢአተኛውን ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ሽማግሌ እንደ መሆኑ መጠን እርቁ እንዲፈጸም ጥፋተኛው ግለሰብ የሚጠበቅበትን መንፈሳዊ ግዴታ ለይቶ ማሳወቁ የማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱም እርቅ ሲደረግ የበደለው አካል ይቅርታ ለማግኘት፣ የተበደለው አካል ደግሞ ይቅርታ ለማድረግ በየግላቸው ሊወጡት የሚገባቸው ድርሻ አለና፡፡ በዚህም መሠረት የተነሳሒ ድርሻ በፍጹም ልብ ከመመለስ በተጨማሪ የበደለውን መካስ፣ የቀማውን መመለስ እንዲሁም በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በዕንባና በዋይታ ወደ እግዚአብሔር ማልቀስ ነው፡፡ ይቅርታ ማድረግ ግን ምሕረትና ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነው የእግዚአብሔር ነው፡፡ ካህኑ ለኃጢአተኛው ሰው እግዚአብሔር ይቅር ይልህ ዘንድ መንፈሳዊ ተግባራትን ፈጽም ብሎ የሚያዝዘው ትእዛዝ ቀኖና ይባላል፡፡ ይኸውም በብሉይ ኪዳን የኃጢአት፣ የበደል፣ የደኅንነት ወዘተ. መሥዋዕት ተብለው የፍየል፣ የበግ፣ የርግብ ወዘተ መሥዋዕት በማቅረብ ይፈጸም የነበረ ሲሆን በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ጹም፣ ጸልይ፣ ስገድ፣ መጽውት የሚለው መጠን እንደካህኑ ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ቀኖና በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አስተምህሮ መሠረት ሰው ከስሕተቱ የሚታረምበት መንፈሳዊ ተግሣጽ ሲሆን ይህ ግን ምድራውያን ነገሥታት ለወንጀለኞች እንደሚሰጡት ቅጣት የሚታይ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ይቅር የሚለው ኃጢአተኛነቱን አምኖ በማዘኑ፣ በመቆጨቱና ከጥፋቱ በመመለሱ እንጂ ስለበደሉ በሚከፍለው ካሳ ብዛት አይደለምና፡፡ ለዚህም ቀደም ብለን ባየነው የጠፋው ልጅ ታሪክ ላይ ልጁ ለመናዘዝ ወደ አባቱ እየመጣ ሳለ “አባቱ ግን ገና ሩቅ ሳለ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው” (ሉቃ.፲፭፥፳) የሚለው የሚያሳየው የአባቱን ርኅራኄ እንጂ ቀኖናው ከኃጢአቱ አቻ መሆኑን አይደለም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” (፩ኛ ጴጥ.፬፥፫) ባለው መሠረት ነው።አባቶቻችንም ይህንን መሠረታዊ ትምህርት አብነት አድርገው ኃጢአተኛው በኃጢአት ባሳለፈበት ዘመን ፈንታ ቀሪ ዘመኑን በጽድቅ ጎዳና እንዲመላለስ የሚያበቃውን ቀኖና ይሰጡታል፡፡ ሐዋርያው “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” በማለት መናገሩ ከተመለሳችሁ ይበቃል ማለቱ አይደለም፡፡ በኃጢአት ፈንታ ፈቃደ እግዚአብሔርን ፈጽሙ ማለቱ እንጂ፡፡ አባቶች ካህናትም በዚሁ መሠረት ለኃጢአተኛ ሰው በቀማህበት ፈንታ መጽውት፣ ያለ ልክ በመብላትና በመጠጣት፣ በስካር፣ በኃጢአት ባሳለፍክበት ዘመን ፈንታ ጹም፣ ጸልይ፣ ስገድ በማለት ለኃጢአተኛው ቀኖና የሚሰጡት መንፈሳዊውን ጣዕም እንዲቀምስ ነው፡፡ እንዲያውም አባቶቻችን ለባለጸጋ ጾምን፣ ምንም ለሌለው ድሃ ምጽዋትን በማዘዝ ኃጢአተኞች ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም በሰውነታቸው ላይ ጨክነው መወሰንን እንዲለማመዱ ያዛሉ፡፡ ምክንያቱም ለባለጸጋ ምግብ በቤት ውስጥ ሞልቶ ተርፎ እያለ መጾም፣ ለድሃ ደግሞ ቆጥቦ ያስቀመጠውን ወይም ለምኖ ያገኘውን ገንዘብ መመጽወት ከባድ ነውና፡፡ ይሁንና ድሃ ጦሙን አድሮም ቢሆን ይመጸውታል፤ ባለጸጋም ለተወሰነ ቀን ነውና እንደምንም ራቡን ታግሦ ይጾማል፡፡ ከዚህም የተነሣ ሰውነታቸው ኃጢአትን ከመጸየፍ በተጨማሪ ለጽድቅ መታዘዝንም ይለማመዳል፡፡ ስለዚህ ተነሳሕያን የሚሰጣቸውን ቀኖና በዛ ብለው ሳያንጎራጉሩ፣ አነሰም ብለው ሳይጠራጠሩ በካህኑ ቀኖና ላይ የእግዚአብሔር ቸርነት እና የተነሳሒው ትሩፋት ተጨምሮበት ከታላቅ በደልና ኃጢአት እንደሚያነፃቸው አምነው ቀኖናቸውን ተቀብለው መፈጸም ይገባቸዋል፡፡ ፫. ሥጋውንና ደሙን መቀበል በክርስትና አስተምህሮ የአገልግሎቶች ሁሉ መደምደሚያው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ነው፡፡ የካህናትና የመምህራን መሾም ዋና ግቡ ምእመናንን አስተምረው ለሥጋውና ለደሙ ማብቃት ነው፡፡ ምክንያቱም የመንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ ግቡ ሰማያዊ ርስት መውረስ ነውና፡፡ ያለክርስቶስ ሥጋና ደም ደግሞ ሰማያዊ ርስት ማለትም የዘለዓለም ሕይወት የለም፡፡ ምክንያቱም “..እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፤ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም” (ዮሐ.፮፣ ፶) ተብሎ ተጽፏልና፡፡ በጠፋው ልጅ ታሪክ አስቀድመን እንደተመለከትነው ልጁ ወደ አባቱ ቤት ሲመለስ አባቱ ፍሪዳ አርዶ፣ ድግስ ደግሶ ተቀብሎታል፡፡ የጠፋው ልጅ አዳም ነው፡፡ የጠፋውን አዳምን ፍለጋ የመጣው ደግሞ ክርስቶስ ነው፡፡ “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና” (ሉቃ.፲፱፥፲) እንዲል፡፡ ለአዳም ልጆች የሕይወት ምግብ ሊሆን የታረደው ፍሪዳም ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡ በቀራንዮ ኮረብታ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ፣ ደሙን አፍስሶ መሥዋዕት ሆኗልና፡፡ ጌታችን በዕለተ ዓርብ መሥዋዕት ከመሆኑ አስቀድሞ ሐሙስ ማታ “እንጀራን አንሥቶ ባርኮ ቈርሶ እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው፤ እንዲሁም ጽዋውን አንሥቶ አመስግኖ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” (ማቴ.፳፮፥፳፮) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም የክርስቶስ ሥጋና ደም ለእኛ የሕይወት ምግብና መጠጥ ሆኖ መቅረቡን የሚናገር ነው፡፡ ስለዚህ እኛም የዘለዓለም ሕይወት ለማግኘትና ሰማያዊ ርስትን ለመውረስ የክርስቶስን ሥጋና ደም መቀበል ይኖርብናል፡፡ “ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል” (ዮሐ.፮፥፶፮-፶፯) የሚለውም ይህንኑ የሚያስገነዝበንነው፡፡ በኦሪቱ በነበረው የመሥዋዕት ሕግ እስራኤላውያን የፋሲካውን በግ ሲመገቡ ጫማቸውን ተጫምተው፣ ወገባቸውን ታጥቀው፣ ኩፌታቸውን ደፍተው በትራቸውን ይዘው እየተቻኮሉ እንዲመገቡ ታዘው ነበር (ዘፀ.፲፪፥፲፩)፡፡ ይህም ዛሬ ላለነው ክርስቲያኖች ምሳሌ ሆኖን የአማናዊውን በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል በጎ ምግባር ሠርተን፣ ወንጌሉን ተጫምተን፣ የንጽሕናን ዝናር ታጥቀን፣ አክሊለ ሦክን፣ ነገረ መስቀሉን እየዘከርን (መስቀሉን ተመርኩዘን)፣ ሞት እንዳለብን በማሰብ እንዳይቀድመን ፈጥነን ንስሓ በመግባት ሥጋውንና ደሙን መመገብ የሚገባን መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ቀደም ብለን ባየነው የጠፋው ልጅ ታሪክም አባት ልጁ ከጠፋበት ሲመለስ ፊሪዳውን ከማረዱ በፊት “ባሪያዎቹን ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ ስጡት” በማለት ልጁ ታጥቦ ንጹሕ የሆነውን ልብስ ለብሶና አዲስ ጫማ ተጫምቶ እንዲዘጋጅ ነበር ያደረገው፡፡ ልጁን ወደ ልቡ እንዲመለስና የአባቱን ቤት እንዲያስብ ያደረገው ረሃብ ነበር፡፡ “እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ አለ” በማለት መናገሩ ምስክር ነው፡፡ ከአባቱ ቤት ካለው ማዕድ ለመቀበል ግን አስቀድሞ ያንን ማዕድ አቋርጦ በመውጣት የበደለውን አባቱን ይቅርታ መጠየቅ ነበረበት፡፡ ስለሆነም አባቱን ማረኝ አለው፡፡ አባቱም ይቅር አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ከፊሪዳው ተመገበ፡፡ እኛም ገና በአርባና በሰማንያ ቀናችን ጀምረን ስንመገብ የኖርነውን ሥጋውንና ደሙን መቀበል አቋርጠን ወደ ተለያየ የኃጢአት ሕይወት ብንገባም እንኳ ወደ ልባችን ተመልሰን ሥጋውንና ደሙን ለመቀበል ስንመጣ አስቀድመን ስለጥፋታችን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚገባን ያስገነዝበናል፡፡ ይህም ሥጋውንና ደሙን ለመቀበል ንስሐ ገብተን መዘጋጀት የሚገባ መሆኑን ይገልጣል። አንድም የንስሓ ጉዞ መጨረሻው በክርስቶስ ሥጋና ደም መታተም የሚገባው መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ በአጠቃላይ ሰው በኃጢአቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር ከተለየ በንስሓ መመለስ ይኖርበታል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችንም በነቢዩ ላይ አድሮ አምላካዊ ጥሪውን ያስተላለፈውና “ወደ እኔ ተመለሱ” እያለ የሚጠራን ለንስሓ ነው፡፡ ስለሆነም ሁላችንም በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰን፣ ቅዱስ ሥጋውን በልተን፣ ክቡር ደሙን ጠጥተን ከቅዱሳን ማኅበር እንዲጨምረን የሚጠበቅብንን መወጣት አለብን፡፡ በንስሓ ተመልሰን በቤቱ እንድንኖር እግዚአብሔር በቸርነቱ፣ ቅዱሳን በአማላጅነታቸው አይለዩን። አሜን!!   
Read 1692 times