Wednesday, 07 April 2021 00:00

መከራ በክርስትና ሕይወት

Written by  ዲ/ን ደረጄ ድንቄ

Overview

መከራ ምንድን ነው? መከራ ማለት ፈተና፣ ጭንቅ  ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ተርጕመውት እናገኛለን። (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ  ገጽ ፭፻፺፩) እንዲሁም ሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን ትንሣኤ አማርኛ-ግእዝ መዝገበ ቃላት በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ፈተና፣ ሀውክ፣ ሥቃይ  የሚል አቻ ትርጉም ሰጥተውት እናገኛለን። (ትንሣኤ አማርኛ-ግእዝ መዝገበ ቃላት  ገጽ ፳) ክርስቲያን ማለት ከውኃ እና ከመንፈስ በመጠመቅ ክርስቶስን የለበሰ ፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆነ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።›› (ገላ. ፫፥፳፯) እንዲል። ክርስቶስ ይህን ዓለም የወደደው ወይም ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር የገለጠው ደግሞ ራሱን ለመከራ  አሳልፎ በመስጠትና በሥቃይ ውስጥ ነው። ጌታም ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፤ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› (ማቴ. ፲፮፥፳፬) ሲል በሰጠው ትእዛዝ ውስጥ  ክርስቲያኖች በጥምቀት ለለበሱት አምላክ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጡበት መንገድም መከራ እንደሆነ ልብ ይሏል! በአጠቃላይ የክርስትና ሕይወት ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ደስታ የሚገኝበት ምድራዊ መከራ በዚህ ዓለም ሳለ የማይለየው ሕይወት ነው። 

 

በአንድ ወቅት ጌታችን መከራ እንደሚቀበል ለደቀ መዛሙርቱ በሚነግራቸው ሰዓት፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አይሁንብህ!›› (ማቴ.፲፮፥፳፪) ባለ ጊዜ ጌታችን ገሥፆት ነበር። ከዚህ ተግሣጽ በኋላ ግን ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስትና እና መከራ አለመለያየት እንዲህ ይመክራል ‹‹ወዳጆች ሆይ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደመጣባችሁ አትደነቁ›› ካለ በኋላ ይቀጥልና ‹‹የክርስቲያን ወገን እንደሆኑ  መከራን መቀበል ግን፤ ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር›› (፩ጴጥ. ፬፥፲፪-፲፮) ይላል።  ቅዱስ ሉቃስም ‹‹ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፉአቸው፤ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው››፤ በማለት ስለ ሐዋርያት ሥቃይ ከጻፈ በኋላ ‹‹እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ›› (ሐዋ. ፭፥፵፩) ይለናል። ሐዋርያት አካላዊ ሥቃዩ ሳይሰማቸው ቀርቶ ሳይሆን፤ የሁሉ ባለቤት ከሆነ አምላክ ጋር ዘወትር አብረው የሚሠሩ ናቸውና  ልባቸው በሰማያዊው ደስታ ዕረፍትንና ሰላምን ያገኝ ስለ ነበር ነው። በእርግጥ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› (ዮሐ. ፲፮፥፴፫) በማለት በማያሻማ መልኩ በግልጽ ነግሮናል። 

መከራ ከየት ይመጣል?

አስቀድመን እንደጠቀስነው መከራ ስንል ሥቃይ፣ ሕመም፣ ደዌ፣ ቸነፈር፣ ጦርነት ወይም ሰላም ማጣት፣ ረኀብ ሊሆን ይችላል። መከራ የሚመጣባቸው መንገዶች የተለያዩ ሲሆኑ፤ ለዚህ ጽሑፍ የመከራን ምንጭ በሦስት ከፍለን እንመለከታለን። 

ሀ. ከራስ፡- መከራ ከራሳችን የሥጋ ምኞት (ኃጢአት) የተነሣ ሊመጣ ይችላል፡ የሰው ልጅ ሥልጣን ለማግኘት፤ ገንዘብ ለማግኘት፤ ተቀባይነት አግኝቶ ታዋቂ ለመሆን፤ ራሱን ከሌላው አስበልጦ ለማስቀመጥ ካለው መሻት የተነሣ፤ ቀላል ወይም ከባድ መከራዎችን በራሱ ላይ ሊያመጣ ይችላል። እነዚህ ፍላጎቶች ኃላፊና ጠፊ ቢሆኑም እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት የሚሄድበት መንገድ ግን ራስን እንዲሁም ብዙዎችን ለመከራ፣ ለሥቃይና ለችግር ሊዳርግ ችሏል። በዓለማችን ብሎም በሀገራችን ላይ ያየናቸው አሁንም የምናያቸው ጦርነቶች፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ መጠፋፋቶች፣ ሕመሙ (ደዌው)፣ በዘር መከፋፈሉ ለዚህ ጥሩ ማስረጃዎች ናቸው። 

በብሉይ ኪዳን በኖኅ ዘመን የተፈጸመው ልዩ መከራና ጥፋት ከሰው ልጆች በደል የተነሣ የመጣ ነበር (ዘፍ. ፯፥፲)፤ በሰዶምና ገሞራ የሆነው ለዐይንም ለጆሮም እንግዳ የሆነው መከራና ጥፋትም ከሰው ልጆች ደካማ ምኞት ወይም ኃጢአት የተነሣ የመጣ ነው (ዘፍ. ፲፱፥፳፬)። ለእስራኤላውያን የ፵ ቀን ጉዞ የ፵ ዓመት የሆነበት፤ ሕዝቡ በነዘር እባብ ተነድፎ ያለቀበት እንዲሁም ሌሎች ለገጠሟቸው ብዙዎቹ መከራዎች ምክንያት የሆነው የራሳቸው የፈቃድ ጥመትና ለፈጣሪ ሕግ አለመገዛታቸው ነው።(ዘኁ. ፲፬፥፴፬፤ ዘኁ. ፳፩፥፮)

እንደ አንድ ግለሰብ ከተመለከትነው ደግሞ ትእዛዙን በመተላለፍ ሕጉን በመጣስ ከእግዚአብሔር እየለዩን ያሉት አብዛኛዎቹ ምክንያቶች የራሳችን ያልተገደቡ የሥጋ ምኞቶቻችን ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም›› (፩ዮሐ. ፪፥፲፭) ይላል ፤ ቅዱስ ያዕቆብም ‹‹ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።›› (ያዕ. ፲፥፲፬) በማለት አንዱ የፈተናዎቻችን ወይም የመከራዎቻችን ምንጭ የራሳችን ምኞት መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል።

ለ. ከዲያብሎስ፡-  መከራ ወይም ፈተና ከዲያብሎስ ሊመጣ ይችላል። ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ፊት ነሥቶ አሳፍሮ መለሰው እንጂ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በገዳመ ቆሮንቶስ  አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ዲያብሎስ  በትዕቢት፤ በፍቅረ ንዋይና በስስት ፈትኖት ነበር። ቅዱስ ሉቃስ ይህን ሲገልጠው ‹‹ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ›› (ሉቃ.፬፥፲፫) ይላል።  ዲያብሎስ ሥራውን ይሠራ ዘንድ የእኛን ደካማ ፍላጎት መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ‹‹ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም መንገድ አትስጡት›› (ኤፌ.፬፥፳፮) ይላል። ይህም ዲያብሎስ በደካማ ፍላጎታችን ወይም ምኞታችን ተጠቅሞ ፈተናና መከራ ሊያመጣብን እንደሚችል የሚጠቁም ነው። በሌላ አገላለጽ በወንድማማች መካከል ያለን ፍቅር ማጣት ዲያብሎስ ለበለጠው መከፋፈልና መለያየት ይጠቀምበታል። በሰዎች መካከል ያለን የቃላት ጦርነት፤ ከፍ ወዳለው ፍጹም መጠላላት እና አካላዊ መጠፋፋት ያሳድገዋል። 

ሌላው ደግሞ እንደ ኢዮብ በእግዚአብሔር ፊት መወደድና ክብር ሲኖረን፤ ሰይጣን ያለ ዕረፍት ጽኑዕ መከራዎችን ያመጣብናል ‹‹ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው›› (ኢዮ. ፪፥፯) ይላል። መጽሐፍ ‹‹ባለጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› (፩ጴጥ. ፭፥፰) እንዲል፤ ባለጋራችን ፈተና እና መከራን በማብዛት ምርኮን ያገኝ ዘንድ ያለ ዕረፍት ዘወትር ይተጋል።

ሐ. ከእግዚአብሔር፡- መከራ ለበረከትና ለሰማያዊ ዋጋ ከእግዚአብሔር ሊመጣ ይችላል፡ እግዚአብሔር አብርሃምን ልጁን ይሠዋለት ዘንድ አዝዞት ነበር፤ ይህ ለአብርሃም ከእግዚአብሔር የቀረበ ትልቅ አስጨናቂ ፈተና ነበር። (ዘፍ. ፳፪፥፩-፲፭) ፤ አብርሃም ግን የታዘዘውን ለመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት የእምነቱን ታላቅነት ገልጧል። በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን የሐዋርያትን እምነት ሲፈትን እናገኛለን። ጌታችን ወደ ታንኳ ገብቶ ከተኛ በኋላ ፤ ታንኳይቱ በማዕበል ተጨንቃ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ከመጨነቃቸው የተነሣ፦ ‹ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን› እያሉ አስነሡት። ‹‹እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው። ከዚህ በኋላም ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ›› (ማቴ. ፰፥፳፫) ይላል። ደቀ መዛሙርቱ ነገ ትልቁን መከራ ይቀበላሉና፤ ከወዲሁ በፈተና ውስጥ ማለፍን ያለማምዳቸው ዘንድ እንዲሁም መከራ  የመሸከም አቅማቸውን ለማሳደግ ይህን ፈተና ለእነርሱ አቀረበላቸው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ‹‹የዚህን ዓለም ድል ነሺዎች ሐዋርያትን ብቻ ይዞ ወደ መርከብ ገባ›› በማለት፤ ጌታችን ወደ ታንኳው ከመግባቱ አስቀድሞ ብዙ ሰዎች የተከተሉት ቢሆንም  በታንኳው ለሚመጣው መከራ ግን የተመረጡት ደቀ መዛሙርቱ ብቻ መሆናቸውን ይገልጣል። ቅዱስ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር የሆኑ ፈተናዎችን ‹‹ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፤ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።›› (፩ቆሮ.፲፥፲፫) ሲል  ይገልጠዋል።

በመከራ ውስጥ የእግዚአብሔር ዝምታ

በቅዱስ ወንጌል እንደተገለጠው ፤ ታንኳይቱን ማዕበል እስኪደፍናት ድረስ በሆነው ፈተና ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ ተጨንቀው ሳለ ጌታችን ግን ተኝቶ ደቀ መዛሙርቱ እስኪቀሰቅሱት ድረስ አልተነሣም ነበር። (ማቴ. ፰፥፳፫) በአስጨናቂ ማዕበል ውስጥ ሆኖ መንቃት የሌለበት እንደምን ያለ እንቅልፍ ነው? ሳያውቅ ቀርቶ ነው እንዳንል ጌታችንም ከእንቅልፉ እንደተነሣ፤ ‹ምን ተፈጠረ? ምንስ አገኛችሁ?› አላለም፤ ይልቁንም ‹እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ?› አላቸው እንጂ። የእግዚአብሔር ዝምታ ካለማወቅ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ መሆኑን ነቢዩ ‹‹እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር።›› (ኤር. ፳፫፥፳፫) በማለት ይናገራል። ጥበበኛው ቅዱስ ሰሎሞንም ምንም ክርስቶስ በሥጋው ተኛ ቢባልም በመለኮቱ ግን ሁሉን አዋቂ መሆኑን ‹‹እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል›› (መኃ. ፭፥፪) በማለት ይገልጠዋል።  

በኪዳን ጾሎት ላይ ‹‹እምቅድመ ሕሊና ኵሎ የአምር፤ ወእምቅደመ ሕሊና ይፈትን ወዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ፤ ከሕሊና አስቀድሞ ሁሉን የሚያውቅ፤ ከሐሳብ አስቀድሞ ሁሉን የሚመረምር፤ ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ የሚሠጠን›› (ኪዳን ዘነግህ ክፍል ፪) ይላል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ደቀ መዛሙርቱ እስኪቀሰቅሱት ድረስ የክርስቶስን ከእንቅልፍ አለመነሣት እንዲህ ይገልጠዋል ‹‹እግዚአብሔር የምንፈልገውን ሳንነግረው ያውቀዋል፤ ጸሎት የምናደርገው እግዚአብሔርን ልንመራው ወይም ልናዝዘው አይደለም፤ ይልቁንም እኛ ስንለምን እርሱ እና እኛ መካከል ያለው ግንኙነት ይገለጥ ዘንድ፤ ራሳችንን ዝቅ አድርገን ስንለምነው ትሕትናን ገንዘብ እንድናደርግና ኃጢአታችንን እናስታውስ ዘንድ ነው›› ይላል። (The Nicene and Post Nicene Fathers Volume 10 First Series; Chrysostom: Homilies on the Gospel Of St. Mattew; Page 290)  

አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ዝምታ አሕዛብ እንኳን ‹‹እውነት በእነርሱ ዘንድ የለችም፤ ፈጣሪያቸውም የለም›› ብለው እስኪናገሩ ድረስ ሊደርስ ይችላል። የንጹሓን ደም መፍሰስ፤ የአብያተ ክርስቲያናት እና ንዋያተ ቅድሳት መንደድ፤ የአገልጋዮች ሥቃይና ሞት፤ የሴቶች እና ሕፃናት መደፈር መነወር፤ እነዚህ ሁሉ ሲሆኑ ‹‹አሕዛብ አምላካቸው ወዴት ነው?  እንዳይሉ፤ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይወቁ›› (መዝ. ፸፰፥፲) እስክንል ድረስ እግዚአብሔር ዝም ሊል ይችላል። ወዳጄ ሆይ! እግዚአብሔር እንኳን የገጠመህን፣ በልብህ ያለውን አልፎም ስለነገህ ያውቃል! ነገር ግን የአንተን ድርሻ እንድትወጣ፣ የእምነትህንም ጽናት ያይ ዘንድ ይፈልጋል፤ ነገሩ ቢከብድህ የማይቻልህ ቢሆን በጸሎትህ ቀስቅሰው፤ እርሱ ጥያቄዎችህን ሁሉ ይመልሳል። ቅዱስ ጳውሎስ እና በርናባስ ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል›› (ሐዋ.፲፬፥፳፩) ያሉትንም ዘወትር አትርሳ!!!

በመከራ ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር አብሮነት

መከራ እና ፈተና ሲበዛ ‹‹እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን እንጂ እንዲህ አንሆንም ነበር››  ብለን ራሳችንንም ሰዎችንም እንሞግታለን። እውነት ነው! በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር በመራቃችን የሚመጡብን መከራዎች አሉ፤ እንዲህ ያሉ ፈተናዎችን ንስሓ ገብቶ ማሳለፍ ይገባል፤ ይህ ማለት ግን ሁሉም ፈተናዎች ከኃጢአት ብቻ የተነሣ ይመጣሉ ማለት አይደለም፤ ንስሓ ገብተን ጥሩ መንፈሳዊ ሕይወት እየኖርን ፈተናና መከራ ሊበረታብን ይችላል። በተጨማሪም የመከራ መደራረብና የፈተናዎች መብዛት የእግዚአብሔርን ከእኛ ጋር አለመኖር አያሳይም። 

ፈጣሪ እያለ ፍጡር ሲጨነቅ ፤ ክርስቶስ እያለ ማዕበል ሲበረታ ‹‹“ክርስቶስ  ከእኔ ጋር ባይኖር እንጂ ፈተና ባልበዛብኝ ነበር” አትበል። እርሱን ስትከተል ከእርሱ ጋር ስትኖር የእርሱ የሆነው መስቀሉም ከአንተ ጋር ነውና፤ ልብህን አታዘናጋ! “ፈልጎ ያገኘህ በመስቀሉ ነውና፤ አንተም ፈልገህ የምታገኘው በመስቀሉ ነው!።›› አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ‹‹ልበ ሰነፎች ሆይ! (በጴጥሮስ ልብ ውስጥ ያለውን) መከራ አለመቀበልንና አለመሞትን ስላልወደደለት ጴጥሮስን እንደገሠጸው አትሰሙምን?›› (መጽሐፈ ምሥጢር ምዕራፍ ፲፭፥፲) በማለት መከራ መንፈሳዊ ትርጕም ያለው መሆኑን ይነግረናል። ሁላችንም በልጅነታችን ምሥጢራትን ስንካፈል፤ የክርስቶስ ቤተ መቅደስ ሆነን እርሱ በእኛ ውስጥ አድሯል፤ በእኛ ውስጥ ያለውን ጌታ የምንወደው ከሆነ፤ መስቀሉን ተቀብለን እኛ እንሸከመው፤ ‹‹ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ዕለት ዕለትም ይከተለኝ›› (ሉቃ. ፱፥፳፫) እንዳለ መድኃኔ ዓለም። በመሆኑም እግዚአብሔርን የያዙ ሰዎች የበለጠ ይፈተናሉ። ምሳሌ የሌላት እመቤታችን ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን ለሚመጡብን መከራዎች መሪያችን ምሳሌያችን ናት። ደቀ መዛሙርቱም ‹‹እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› ያለውን አምላክ ይዘው፤ ብዙ ጭንቅና መከራዎችን ተቀብለዋል። 

በመከራ የመጽናት ዋጋ 

በኃጢአት ምክንያት የሚያገኘን መከራ፤ ለሰማያዊው ሕይወት የእግዚአብሔር የንስሓ ጥሪ መሆኑን ዘወትር ማስታወስ ያስፈልጋል። ‹‹የሟቹን ሞት አልፈቅድምና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።›› (ሕዝ. ፲፰፥፴፪) ይላል። ስለዚህ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣን መከራ ንስሓ በመግባት መሻገር ይገባል። 

በመከራ ውስጥ መጽናት በምድር ልዩ ልዩ ጸጋዎችን የሚያሰጠን፤ በሰማይ ደግሞ ሰማያዊ አክሊል የምናገኝበት ነው። ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና›› (ያዕ. ፩፥፲፪) ይላል ፤ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ ‹‹አሥር ቀንም መከራ ትቀበላላችሁ ፤ እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ›› (ራእ. ፪፥፲)  በማለት በመከራ የሚገኘውን ክብር ይገልጸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ባህል አሥር ቍጥር ሙሉ ፍጹም ነገርን ይወክላል፤ ስለዚህም ክብርና ዋጋ ከመቀበል በፊት መከራው ፍጹምና ሙሉ እንደሚሆን ባለምሥጢሩ ሐዋርያ በምሥጢር ነገሮናል። 

በመከራ ውስጥ ጸንቶ ሰማያዊ ዋጋ ለመቀበል ፤ አንደኛው መሠረታዊ ነገር ጸሎት ነው። የሰው ልጅ ለመኖር መተንፈስ አለበት፤ ሰው አየር ካጣ መተንፈስ ካልቻለ ነፍሱ ከሥጋው ትለያለች፤ አየርን በኋላ እፈልገዋለሁ የሚል የለም። ያለምንም የጊዜ ገደብ የሰው ልጆች ይሹታል። አየር የዚህን ያህል ካስፈለገ፤ አየርን የፈጠረ አምላክ ለሰው ልጆች ምን ያህል ያስፈልግ ይሆን? ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ [For we ought to think of God even more often than we draw our breath› ‹‹እግዚአብሔርን ከምትተነፍሰው አየር በላይ አስታውሰው››  (Gregory of Nazianzus on The Five Theological Orations; Page 4)] ይላል። እንደ አንድ ክርስቲያን ስለ አሁን፣ ስለወደፊት፤ ስለተደረገልን፣ ስላልተደረገልን፣ ስለሚደረግልን ነገር ሁሉ እንድንጸልይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ቅዱስ ዮሐንስ ቅሊማቆስ ‹‹የጸሎትን በትር በእጃችሁ ከጨበጣችሁ አትወድቁም፤ ብትወድቁም አወዳደቃችሁ ለሞት የሚያደርስ አይሆንም›› (John Climacus, On the Ladder of Divine Ascent) ሲል ይመክረናል። እንኳን ፈተና ገጥሞን ይቅርና በደኅናው ሰዓትም አንድ ክርስቲያን ከጸሎት ሕይወት መለየት እንደሌለበት፤ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ‹‹ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ›› (ማቴ. ፳፮፥፵፩) በማለት ካዘዘን ከጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተከትሎ ቅዱስ ጳውሎስ  ‹‹ሳታቋርጡ  ጸልዩ›› (፩ተሰ. ፭፥፲፯) በማለት ይመክረናል። እንዲሁም በሐዋርያት እግር የተተኩ ቀደምት ሊቃውንትም ያስተማሩን ጸሎት ከክርስቲያን ሕይወት ሊለይ የማይገባው መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ነው። 

በአጠቃላይ እውነተኛ አማኝ የሆነ ሁሉ በዚህ ዓለም ስላለው መከራ፣ የመከራ መምጫ፣ በመከራ ጊዜ እግዚአብሔር ለምን ዝም እንደሚል፣ በመከራ መታገሥ ሊያስገኘው የሚችለውን ጸጋ ወዘተ. ሁሉ  በአግባቡ በመረዳት መርከብ በተባለች ቤተ ክርስቲያን በመጽናት፣ የመርከቧን ቀዛፊ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የዚህን ዓለም ፈተና ሁሉ በማለፍ ወደብ ከተባለችው ከመንግሥተ ሰማያት ሊያስገባ የሚያስችለውን ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት መኖር ይገባል። ስለዚህ ቅዱስ መስቀሉን ይዘን ጌታችንን በመከራው መስለነው፤ በትዕግሥትና በጽናት ቆመን መንግሥቱን ለመውረስ ያብቃን!!!   

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Read 3320 times