Thursday, 21 January 2021 00:00

ወአግዐዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ (ቅዱስ ያሬድ ድጓ ዘአስተርእዮ)

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

ይህ ዓለም ድካም፣ ውጣ ውረድ፣ ጊዜያዊ ሀብት፣ ወዘተ የበዛበት ኃላፊ ዓለም ነው። ይህ ዓለም ምንም ኃላፊ፣ ጠፊ ቢሆንም የማይታየውንና የማያልፈውን ሰማያዊውን ዓለም ተስፋ አድርገን ወደ ዘለዓለማዊው ሕይወት የሚያስገባን ሥራ እየሠራን የምንኖርበት ዓለም ነው። ይህ ዓለም ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ “ዓለሙ ያልፋል፤ ምኞቱም ያልፋል” (፩ዮሐ. ፪፥፲፯) በማለት እንደገለጸልን የሚያልፍ የሚጠፋ እንጂ ለዘለዓለም የምንኖርበት ቦታ አይደለም። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የእመቤታችንን ዕረፍት በአዘከረበት ድጓው “ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ፤ ወአግዐዛ እምእኵይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ ወረሰየ ይዝክሩ ስማ ውስተ ኵሉ ምድር፤ ለዚች ሴት የአብ  ብዕለ ጸጋው በእርሷ ላይ ወጣ፤ ከክፉ ወደ መልካም፣ ከሞት ወደ ሕይወት ነጻ አወጣት ወይም ወሰዳት፤ በምድር ሁሉ ስሟን ይጠሩ ዘንድም አደረገ ” በማለት አስረዳን። በዚህ ምንባብ ሊቁ ሊነግረን የፈለገው በእናታችን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የአብ ጸጋው እንዳደረባት፣ ከክፉ ወደ መልካም፣ ከሞት ወደ ሕይወት እንዳሸጋገራት፣ እንዲሁም በምድር ሁሉ ሰዎች ስሟን ሲዘክሩ እንደሚኖሩ ነው። ዘርዘር ያለውን ጉዳይ እንደሚከተለው እንመለከታለን።

 

፩ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ” (ሉቃ. 1፣28) በማለት እንዳመሰገናት ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ይህ ጸጋ ከባሕርይ አምላክ ከእግዚአብሔር የተገኘ መሆኑን በመግለጽ የአብ ጸጋ ለዚች ሴት ወጣ እያለ ያስረዳል። የእመቤታችንን ጸጋ ዘርዝሮ ይህን ያህላል ማለት አይቻልም። መልአኩም  “ጸጋን የተመላሽ” አላት እንጂ ጸጋሽ ይህ  ነው ብሎ ዘርዝሮ አልተናገረም። ትውልድም እንዲሁ ጸጋን የተመላሽ እያለ ሲያመሰግናት ይኖራል እንጂ ዘርዝሮ መጨረስ አይችልም። 

ሌሎች ቅዱሳን ጸጋ ቢኖራቸውም እንደ እመቤታችን ጸጋን የተመላችሁ አልተባለላቸውም። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ “መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው። ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ።” (፩ቆሮ. ፲፪፥፬-፭) በማለት እንደተናገረው ለሰው ሁሉ ሰጪው አንድ ቢሆንም ልዩ ልዩ ጸጋ አለ። ይሁን እንጂ ሌሎች ፍጥረታት ጸጋን የተመላችሁ አልተባሉም። እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን “ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ” ተብላለች።

እንደ ሊቁ አገላለጽ ይህ ጸጋ የእግዚአብሔር ነው። ከላይም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸው ጸጋው ልዩ ልዩ ቢሆንም ሰጪው አንድ ነው። እርሱም እግዚአብሔር ነው። ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ በድንግል ማርያም ላይ ወጣ (ታየ) ተባለ። ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ንጽሕናዋን ጠብቃ እንድትኖር ስላስቻላት የእርሱን ጸጋ መቀበል ብቻ ሳይሆን በተአምረ ማርያም እንደተገለጸው “መልኳ እንደ አምላክ መልክ ነው” ተባለላት። 

፪. ወአግዐዛ

ነጻነት በባርነት ለተያዘ ሰው ብቻ አይደለም። አስቀድሞ እንዳይያዝ ማድረግም ነጻነትን ማደል ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  የዚህ ዓለም ሐሳብ፣ የሀብት ፍላጎት፣ የሥጋ ምኞት፤ የዐይን አምሮት ያልነበረባት ንጽሕት፣ ድንግልና ቅድስት ናት። ይሁን እንጂ  በዚህ ዓለም በኖረችበት ዘመኗ ብዙ መከራ ተቀብላለች።  ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ወደዚህ ዓለም በተገለጠ ጊዜ፣ በእርሱ ምክንያት ብዙ መከራ ተቀብላለች፤ ተሰዳለች፤ ተርባለች፤ ተጠምታለች። 

እመቤታችን ድንግል ማርያም ያገኘችው ነጻነት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን በላከው መልእክቱ “ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናልና። እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ “ (ገላ. ፬፥፴፩- ፭፥፩) በማለት እንደተናገረው ያለ ነጻነት አይደለም። ጥንቱኑ የአዳም ልጅ በሙሉ በተያዘበት የባርነት ቀንበር አልተያዘችምና። ነገር ግን ከላይም እንደተገለጸው ይህ ዓለም መከራ የበዛበት፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሥጋ ሥራ “ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት፣ ጣዖት ማምለክ፣ ሥራይ ማድረግ፣ መጣላት፣ ኩራት፣ የምንዝር ጌጥ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ጥርጥር፣ ፉክክር፣ ምቀኝነት፣ መጋደል፣ ስካር፣ ይህንም የመሰለው ሁሉ ነው” ብሎ በመዘርዘር እንደገለጸልን ይህ ሁሉ የሚሠራበት ነው። በዕረፍቷ ይህ ሁሉ የኃጢአት ሥራ ካለበት፣ መከራ ከበዛበት ዓለም ነጻ ሁናለች። ከዚህ ምንባብ ፅንሰ ሐሳብ ሳንወጣ በአጭሩ ሊቁ ከምን ከምን ነጻ አደረጋት አለን? የሚለውን እንመልከት። 

ሀ. እምእኵይ ውስተ ሠናይ፡- ሊቁ ነጻ አደረጋት ብሎ ከዘረዘራቸው ነጥቦች አንዱ “ከክፋት ወደ መልካም”  ነው። ከላይ እንደተገለጸው ከመልካም ነገር ውጭ በሕይወቷ ሌላ ክፉ ነገር የለም። እርሷ “በሐሳብሽም ንጽሕት ነሽ” የተባለች ስለሆነች ክፉ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ማሰብም የለባትም። ይሁን እንጂ የኖረችው ክፉ በሚሠራበት ዓለም ነውና ክፉ ሥራ ከሚሠራበት ዓለም  መልካም ነገር ብቻ ወደሚታሰብበት፣ ወደሚነገርበትና ወደሚሠራበት ዓለም ወሰዳት እያለ ይነግረናል።

እግዚአብሔር አምላካችን እናቱን ድንግል ማርያምን ከሁሉም ነገር የጠበቃት ገና ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ነው። ይህንም ሐሳብ ቅዱስ ያሬድ “መንፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ፤ መንፈስ ቅዱስ ከእናቷ ማኅፀ ጀምሮ ጠበቃት” (ምንጭ) በማለት ያስረዳናል። ገና ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጠበቃት ያለን ሊቁ አሁን በዚህኛው ክፍል ደግሞ ዕረፍቷን ምክንያት አድርጎ ከክፉ ወደ መልካም ነጻ አደረጋት ሲለን ከላይም እንደገለጽነው ክፉ ከሚሠራበት ዓለም፣ ክፉ ከሞላበት ዓለም መልካም ነገር ብቻ ወደሚታሰብበት ዓለም ወሰዳት ማለቱ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል።

 ለ. እሞት ውስተ ሕይወት፡-  ሞት በብዙ መንገድ ይተረጎማል።  የሥጋ ከነፍስ መለየት፣ ኃጢአት ሠርቶ ከእግዚአብሔር መለየት፣ በነፍስ ወደ ሲኦል ብሎም ወደ ገሃነም መውረድ ይህ ሁሉ ሞት ይባላል። የነፍስ ከሥጋ መለየት ጊዜው ይዘገይ ይሆናል እንጂ ለሁሉም ሰው  አይቀርም። ማለትም የአንደኛው ይረዝም የሌላኛው ደግሞ ያጥር እንደሆነ እንጂ ሥጋ ለለበሰ ሁሉ የተሠራ ነው። ይህን አስመልክቶ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “ኢትፍርህዎ ለሞት ፍርህዋ ለኃጢአት እስመ ሞትሰ ኢየኃድገክሙ ዘበላዕሉ ኀልዩ ወአኮ ዘበምድር፤ ሞትን አትፍሩት ኃጢአትን ፍሯት፤ ሞትማ አይተዋችሁምና የሰማያዊውን አስቡ የምድራዊውንም አይደለም” (ጾመ ድጓ ዘቅድስት) በማለት ይህ የነፍስ ከሥጋ መለየት በሁሉም ዘንድ ያለ እንደሆነ ያስረዳናል።

የነፍስ ከሥጋ መለየት የማይቀር ብቻ አይደለም በሃይማኖት ጸንቶ በጎ ምግባር ሠርቶ ለኖረ ሰው ሕይወቱ ነው። ይህንንም አስመልክቶ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ ሞቶሙሰ ለጻድቃን ሕይቶሙ ውእቱ እስመ ለጻድቅ ይትሌዓል ቀርኑ በክብር፣ ጻድቃን እለ አሥመርዎ ለእግዚኦሙ ምድረ ብርህተ ወጽዕዱተ ይወርሱ፤ የጻድቃን ሞታቸው ሕይወታቸው ነው። የጻድቅ ክብሩ ከፍ ከፍ ይላልና። እግዚአብሔርን ያስደሰቱት ጻድቃን ብርህት የሆነች ምድርን ይወርሳሉ።” (ቅዱስ ያሬድ ድጓ) በማለት አስረድቷል። በአንጻሩ ደግሞ በሃይማኖት ሳይኖሩ በጎ ምግባር ሳይሠሩ ለኖሩት ደግሞ የሞት ሞት ነው።

ኃጢአት ሠርቶ ከእግዚአብሔር መለየትና በነፍስ ወደ ሲኦል ብሎም ወደ ገሃነመ እሳት መውረድ ግን ለማንም የተፈቀደ አይደለም። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉም ሃይማኖቱን አጽንቶ በጎ ምግባር ሠርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲገባ ነው። ይሁን እንጂ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንድንገባም ይፈቅድልናል እንጂ አስገድዶ አያስገባንምና ሰማያዊውን ርስት የሚያስወርስ ሥራ ካልሠራን ልንገባ አንችልም። ስለዚህ በሃይማኖት ጸንቶ በጎ ምግባር ሲሠራ የኖረ ሰው ገነት መንግሥተ ሰማያት ይገባል። በአጭሩ ሞት ማለት የነፍስ ከሥጋ መለየት፣ ኃጢአት ሠርቶ ከእግዚአብሔር መለየትና በነፍስ ወደ ሲኦል ብሎም ወደ ገሃነመ እሳት መውረድ ነው።

እግዚአብሔር ድንግል ማርያምን ከየትኛው ሞት ነው ነጻ ያደረጋት ብለን ስንጠይቅ ከላይ ከተዘረዘሩት መካከል የነፍስ ከሥጋ መለየት ከላይም እንደገለጽነው በሁሉም የተሠራ ስለሆነ ከዚህ ነጻ  አልሆነችም። በመሆኑም ይህን ሞት ቀምሳለች። ሊቁ ይህን ሞት መቅመሷን ብቻ ሳይሆን ሰው ናትና ከሞት ጋር የነበራትን ግንኙነትም ሲገልጽ “እፎኑመ እመ አምላክ በከየት ደንጊፃ ከመ ኵሉ ሰብእ ሞት ሶበ ሐወጻ፣ ዮሐንስ በልብሱ ከደነ ገጻ፤ የአምላክ እናት እንዴት ደንግጣ አለቀሰች? እንደ ሰው ሁሉ ሞት በጎበኛት ጊዜ፤ ዮሐንስ በልብሱ ፊቷን ሸፈናት” (ድጓ ዘአስተርእዮ) በማለት ያስረዳል። አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም  ሞት ሲመጣባት አይታ ደነገጠች።

ልጇም  ይህን ሞት እንድትቀምሰው አድርጓታል። ይህ ያስደነቀው ሊቅ “ለምንት ይዜኃር ኃያል በኀይሉ፤ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ፤ ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ፤ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይመካል? ባለጸጋስ በሀብቱ ብዛት ለምን ይመካል? ክርስቶስ ሞትን ለሥጋ ዘመዱ (ለእናቱ) አላዳላም። ለሚሞት ሰውማ ሞት ይገባል የማርያም ሞት ግን ለሁሉም ይደንቃል።” (ነግሥ ዘአስተርእዮ) በማለት እጅግ ያስደነቀውን ነገር በማንሣት እኛንም ያስደንቀናል። ስለዚህ ሞትን ለእናቱም አላዳላም ከተባለ ከየትኛው ሞት ነው ነፃ አደረጋት የሚለን? የሚለውን ማንሣትና ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

ድንግል ማርያም ከሞተ ሥጋ አልቀረችም። ሌሎቹ ሁለቱ ግን ማለትም ኃጢአት ሠርቶ ከእግዚአብሔር መለየትና በነፍስ ወደ ሲኦል ብሎም ወደ ገሃነመ እሳት መውረድ በእርሷ ዘንድ የሌሉ ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ካለማየት ነጻ አደረጋት፤ ከኃጢአት ነጻ አደረጋት፤ በነፍስ ወደ ገሃነመ እሳት ከመውረድም ነጻ አደረጋት። ይህ ብቻ አይደለም ኃጢአት ከሚሠራበት ዓለምም ነጻ አደረጋት። ሞት ካለበት ማለት ኃጢአት ከሚሠራበት፣ የሥጋ ምኞት ከነገሠበት፣ ኃላፊ ጠፊ የሆነው ሁሉ ካለበት ዓለም ነጻ አወጣት። ከዚህ  ሁሉ ዓለም ነጻ አውጥቶ ሕይወት ወዳለበት፣ ዘለዓለማዊ ዕረፍት ወዳለበት ደስታው ወደማያልቅበት ዓለም ወሰዳት ማለት ነው።     

 

፫. ይዝክሩ ስማ ውስተ ኵሉ ምድር፡- 

እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ በኢሳይያስ ላይ አድሮ “ሰንበቴን ቢጠብቁ ደስ የሚያሰኘንንም ቢመርጡ በቃል ኪዳኔም ጸንተው ቢኖሩ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምንም እሰጣቸዋለሁ” (ኢሳ.፶፮፥፬-፭) በማለት ለወዳጆቹ ሊሰጣቸው የሚችለውን ጸጋ ተናግሯል። ከላይ የተዘረዘሩትን ብቻ ሳይሆን የአምላክ እናት የሆነች ድንግል ማርያምን ዙፋኑ ያደረጋት እናቱን ደግሞ ከዚህ በላይ የሆኑ ጸጋዎችን አድሏታል። ስለዚህ በምድር ሁሉ ስሟን እንዲጠሩ አደረገ በማለት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ያስረዳናል።

ይህን ሐሳብ በመልአኩና በቅድስት ኤልሳቤጥ አንደበት ከተመሰገነችና ጌታን ከፀነሰች በኋላ ከዚህ በኋላስ በአንድ መልአክና በአንዲት ሴት ብቻ ተመስግኜ አልቀርም   “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰) ስትል አስቀድማ ተናግራለች። በእርሷ አንደበት “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” ብላ እንደተናገረች፣ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ “ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ” (መዝ.፵፬፥፲፯) በማለት እንደተናገረ ሌሎችም ነቢያት አስቀድመው በትንቢት እንደተናገሩላት እግዚአብሔርም ይህን ጽኑዕ ቃል ኪዳን አጽንቶላት  በምድር ሁሉ ስሟን እንዲጠሩ አደረገ።

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ኵሉ ትውልድ ያስተበፅዑኪ፤ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉሻል” (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ) በማለት ተናግሯል። እግዚአብሔር አምላካችን ከዚህ ውጣ ውረድ ካለበት፣ ድካም ከበዛበት፣ ኃጢአት ከሚሠራበት፣ ፈቃደ ሥጋ ከነገሠበት ዓለም ወስዶ በቀኙ እንድትቀመጥ አደረገ። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፣ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኍብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” (መዝ.፵፬፥፱) በማለት እንደተናገረ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠች።

ከሞት ወደ ሕይወት አሸጋገራት ማለት ከላይም እንደተገለጸው ሞት ነበረባት ማለት አይደለም። ሞት በሰፈነበት ዓለም ስትኖር ሞት ያልነካት፣ ሞት ሰልጥኖ በነበረበት ዘመን ንጽሕት ሁና የተገኘች ከፍጥረታት ሁሉ የተለየች ናት። ምንም የተለየች ብትሆንም ሞት ባለበት ዓለም ኖራለችና ከዚህ ሞት ካለበት ዓለም ሞት ወደሌለበት  ሕይወት ወደ ሰፈነበት ዓለም ወሰዳት በማለት ያስረዳል።  

ከዚህ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም  ወስዶ ትውልድ ሁሉ ለዘለዓለም ሲዘክሯት፣ በስሟ ሲማጸኑ፣ ለምነው የፈለጉትን ሲያገኙ እንዲኖሩ አደረገ። ለምን ያመሰግኗታል የሚል ቢኖር ደግሞ ይህን አስመልክቶ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “ሰብእ ወእንስሳ ወኵሉ ዘሥጋ ያስተበፅዑኪ እስመ ለዘይሴስዮሙ በሐሊበ አጥባትኪ ሐፀንኪዮ፤ ሰው እንስሳና ሥጋዊ ፍጥረት ሁሉ ያመሰግኑሻል። የሚመግባቸውን በጡትሽ ወተት አሳድገሽዋልና” (አርጋኖን ዘሰኑይ) በማለት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፍጥረታት ሁሉ እንደሚያመሰግኗት ከገለጸ በኋላ ለምን እንደሚያመሰግኗት ምክንያቱን ሲያብራራ ደግሞ ፍጥረታትን ሁሉ የሚመግበውን አምላክ ጡቷን አጥብታ በማሳደጓ እንደሆነ ያስረዳል።

በአጠቃላይ እግዚአብሔር አምላካችን እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍተ ሥጋን አድሎ ክፉ ሥራ ከሚሠራበት ዓለም መልካም ሥራ ወደሚሠራበት ዓለም፣ ኃጢአት፣ እልቂት ሞት፣ ወዘተ ካለበት ዓለም ሕይወት ወዳለበት ዓለም ወሰዳት። እርሷን ከዚህ ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ቢወስዳትም ዘለዓለማዊና የማይጠፋ ስም አድሏታልና ትውልድ ሁሉ ስሟን ሲዘክሯት እንዲኖሩ አደረገ። እኛንም ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም በረከት አድሎን፣ በሃይማኖት ጸንተን በንጽሕና በቅድስና ኑረን ነጻነት ወደ ሰፈነበት ዓለም እንዲያሸጋግረን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን። 

 

Read 762 times