Wednesday, 28 April 2021 00:00

ስለዚያችም ምድር ክፉ የተናገሩ ሞቱ (ዘኊ.፲፬፥፴፯)

Written by  ቀሲስ ዐብይ ሙሉቀን

Overview

እግዚአብሔር አምላካችን የሰውን ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ አልቆና አክብሮ በአርአያው ሲፈጥረው ስሙን ቀድሶ ክብሩን እንዲወርስ ነው። ስሙን ቀድሶ ክብሩን ይወርስ ዘንድ የሚያስችሉ ሕዋሳትንም በሚገባ አድሎታል። የተሰጠውን ሕዋሳት በአግባቡ ቢጠቀምባቸው ክብርን ያገኛል። ዐይኑን በአግባቡ ቢጠቀምበት መጻሕፍትን አንብቦ፣ መልካም ነገርን ሠርቶ ይድንበታል፣ ይጸድቅበታል።  በአግባቡ  ካልተጠቀሙበት ግን ሞትን ያስከትላል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት በቅዱስ ወንጌል  “ቀኝ ዐይንህ ብታስትህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሁለት ዐይና ሆነህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትገባ ይልቅ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና” (ማቴ.፭፥፳፱) ተብሎ የተመዘገበው እግዚአብሔር በሰጠን የአካል ክፍል ልንጠቀምበትም ልንጎዳበትም እንደምንችል ሲያስተምረን ነው። የዐይንን እንደማሳያ እንደተመለከትን ሁሉ የአንደበትም የሌላውም የሰውነት ክፍሎቻችን እንዲሁ ነው። በአንደበታቸው የተጠቀሙትንና የተጎዱትን በዚህ ጽሑፍ እንመለከታለን። ለዚህ መነሻ እንዲሆነን አንድ ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ እናንሣ።    “ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው የተመለሱት ሰዎች ስለርስዋ በማኅበሩ ሁሉ ፊት አጕረመረሙ። ስለዚያችም ምድር ክፉን ነገር ተናገሩ፤ ስለዚያችም ምድር ክፉ የተናገሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሠፍት ሞቱ፤ ምድሪቱ ግን መልካም ነበረች። ነገር ግን ምድሪቱን ሊሰልሉ ከሄዱ ሰዎች የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በሕይወት ኖሩ።” (ዘኊ.፲፬፥፴፮-፴፯) እንዲል። በዚህ ምንባብ ላኪ፣ ተላኪ. መልእክት፣ የመልእክት ምክንያት፣ ተላኪዎች ሲመለሱ ይዘውት የተመለሱት ጉዳይ ወዘተ ይዳሠሣሉ።

 

፩. ላኪ፡-  በዚህ ምንባብ የመልእክቱ ባለቤትና መልእክተኞችን የላከው እስራኤልን ከግብፅ ምድር አውጥቶ ወደ ከነዓን እየመራ ሊወስዳቸው ለዚህ አገልግሎት የተጠራው ሙሴ ነው። ሙሴ በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እስራኤልን ከፈርዖን ግዞት፣ ከግብፅ ባርነት ያድን ዘንድ በመልካም ጥበቃው ከሞት ያዳነው ሰው ነው። እግዚአብሔር እስራኤልን ይታደጋቸው ዘንድ ሙሴን ለምክንያትነት አዘጋጅቶታልና በሰው ዘንድ እጅግ የሚከብድ ፈተና ቢደርስበትም ሁሉን እንድንችል የሚያደርግ እግዚአብሔር እየረዳው ፈተናውን ሁሉ አልፎ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ለማውጣት፣ ባሕረ ኤርትራን ለማሻገር፣ በበረሃ እየመገበ ለመምራት በቅቷል። እንደመሪነቱም ከነዓን ከመግባታቸው በፊት ስለከነዓን መረጃ ያስፈልጋቸው ስለነበር ዐሥራ ሁለት ሰላዮችን ላከ።

ሙሴ በዚያ ዘመን ማለትም ትምህርት አልተስፋፋም፣ ቴክኖሎጂ አልነበረም፣ ሥልጣኔ አልዳበረም፣ ወዘተ በሚባልበት ዘመን ሰላዮችን አዘጋጅቶ ልኳል።  ይህን ተግባር በአሁኑ እይታ ብንመለከተው ሙሴ በዚያ ጊዜ የመረጃና ደኅንነት መሥሪያ ቤት አቋቁሞ ነበር ማለት ነው። በሰዎቹ አስተሳሰብ ወንድ ልጅ እንዳናይ በተባለበት ዘመን ከመታየት አልፎ እንዲህ ያለ ለምክንያት ድኅነት የሚበቃ እጅግ ጥበበኛና ታላቅ ሰው ተገኝቷል።

፪. ተላኪ፡- የሙሴን መልእክት ይዘው ወደ ከነዓን ያቀኑት አካላት ዐሥራ ሁለቱ ሰላዮች ናቸው። እነዚህ አካላት የተላኩት እነርሱን ሊመራቸው እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ በሾመው በሙሴ ነው። የተላኩበት ቦታም በአግባቡ ደርሰዋል። በእግዚአብሔር ቸርነት በረአብ  የደግነት ሥራ ምክንያት ከጠላት ድነው ወደ ሀገራቸው ገብተዋል። የሄዱበትንም ጉዳይ ፈጽመው ያዩትንና የተመለከቱትን እንደተረዱበት መጠን ይዘው ተመልሰዋል።  

፫.የተላኩበት ቦታ፡- እስራኤል ይወርሷት ዘንድ አስቀድሞ እግዚአብሔር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም  “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” (ዘፍ.፲፪፥፯) በማለት እንደተናገረው ይወርሷት ዘንድ ተስፋ ወደሚያደርጓት ወደ  ከነዓን  ነው። ከነዓን ደግሞ የተስፋይቱ ምድር እየተባለች የምትጠራዋ፣ እስራኤላውያን እንወርሳታለን ብለው በተስፋ የአርባ ዓመት የእግር ጉዞ የተጓዙባት ናት። እስራኤላውያን ከነበረባቸው የፈርዖን ግዛት ለመውጣትና በነፃነት ለመኖር፣ የሚፈልጓትን ከነዓንን ለማግኘት የቀኑ ሐሩር የሌሊቱ ቍር ተፈራረቀባቸው። 

ይህች የከነዓን ምድር እንወርሳታለን ብለን በተስፋ የምንጠባበቃት የገነት ምሳሌ ናት። ሊቃውንቱ በትርጓሜ እንዳስረዱን ግብፅ የሲኦል ምሳሌ ስትሆን ከነዓን ደግሞ የገነት ምሳሌ ናት። ቤተ ክርስቲያንም በምድር ያለች ገነት ትባላለች። ስለዚህ ስለከነዓን ክፉ ያወሩት እንደ ሞቱ  ዛሬም በምድር ያለች ገነት ስለተባለችዋ ስለ  ቤተ ክርስቲያን ክፉ ወሬን የሚያመላልሱ መጨረሻቸው ሞት ይሆናል። 

ወደ ተስፋይቱ ምድር ተልከው መከራውን አጉልተው በማሳየት የሚያስፈራና የሚያጠራጥር ክፉ ወሬ ያመጡ እንዳሉ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ያሉ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቸርነት ያልተረዱ ወዮ ላችሁ” የሚሉ  በቅዱስ ወንጌል “እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።” (ማቴ.፲፩፥፳፰-፴) በማለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት በመዘንጋት ሰውን ወደ ንስሓ የሚመልስ ትምህርት ከማስተማር ይልቅ ፈርቶና ተስፋ ቆርጦ እንዲሸሽ የሚያደርጉ ብዙ ናቸው።

፬. የተላኩበት ምክንያት፡- ሰዎቹ ወደ ከነዓን የተላኩት ሊሰልሉ ነበር። ሙሴ ዐሥራ ሁለቱንም ሰላዮች ሲልክ ምድሪቱ ውስጥ ወይም ከነዓን ውስጥ ያለውን ሁኔታ ቀድሞ መረዳት ስለፈለገ ነበር። ከላይም እንደተገለጸው ሙሴ ያደረገውን ሥራ ማለትም እንደ ዛሬው ሥልጣኔው ባልተስፋፋበት ዘመን አስቀድሞ መረጃን መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ፣ ምን አልባትም በየዋህነት ቢሄዱ ሊያጋጥማቸው የሚችል ችግር እንዳለ መረዳት በዚህ ዘመን ሁኔታ ሲመዘን እጅግ የሚደንቅ ነገር ሆኖ እናገኘዋለን። ዛሬም ቢሆን በእያንዳንዳችን ሕይወትም ሆነ እንደቤተ ክርስቲያን ነገ ምን መልካም ነገር ወይም ክፉ ነገር ሊገጥም ይችላል ብሎ ማሰብ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስተምረን ነው። 

ይህ ሲባል ግን በቅዱስ ወንጌል የተጻፈውንም መዘንጋት የለብንም። በቅዱስ ወንጌል “እናንተስ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ለነገ አትጨነቁ፤ ነገ ለራስዋ ታስባለችና፤ ለቀኒቱ ክፋቷ ይበቃታል” (ማቴ.፮፥፴፫-፴፬) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ ማለት ግን አታስቡ ማለት አይደለም። ፈልጉ የሚሉና አትጨነቁ የሚሉ ቃላት መኖራቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ፈልጉ ከተባልን እናስባለን። ደግሞም የሚያስብ ልቡና ሰጥቶ አታስቡ የሚል አምላክ አይደለም። ከአቅም በላይ መጨነቅ ግን አያስፈልግም፣ አይገባምም። መጨነቅና ማሰብ እጅግ የተለያዩ መሆናቸውንም መረዳት ያስፈልጋል። 

፭. መልክተኞች ያመጡት ነገር፡- መልክተኞቹ ሀገሪቱ ላይ ስላለው የኃይል አሰላለፍ፣ የጦር ሁኔታ፣ የሀገሪቱን ለመኖር ምቹ መሆን በአግባቡ ተመልክተዋል። ይሁን እንጂ ያለውን ሁኔታ የተረዱበትና የተገነዘቡበት መጠን የተለያየ ነበር። በዚህም የተነሣ ይዘውት የመጡት ወሬ የተለያየ ነው። ከፊሎቹ (ዐሥሩ) ክፉና አስደንጋጭ ወሬ ሁለቱ ግን ተስፋ የሚሰጥ መልካም ወሬ አመጡ። 

ሀ. ክፉ ወሬ ያመጡ መልክተኞች፡- ስለሀገሪቱ ሰዎች ኃያልነትና አስፈሪነት የሚገልጽ ክፉ ወሬን ያመጡት ዐሥሩ መልክተኞች ናቸው። ክፉ ወሬ ለማንም የማይበጅ ሀገርን የሚያጠፋ ነው። ከዚህም የተነሣ ክፉና ሐሰተኛ ወሬን መስማት እንደሌለበት ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ተነግሮት ነበር። “የሐሰተኛ ወሬን አትቀበል፤ ከዐመፀኛ ጋር አትቀመጥ። ለዐመፅ ከብዙ ሰው ጋር አንድ አትሁን፤ ፍርድንም ለማጣመም ከብዙ ሰው ጋር አትጨመር” (ዘፀ.፳፫፥፩-፪) እንዲል።

ስለ ከነዓን ክፉ ወሬ ያመጡት ሰዎች የእግዚአብሔርን ቸርነት በአግባቡ ያልተረዱት ናቸው። የእግዚአብሔርን ቸርነት በአግባቡ ቢረዱት ኑሮ ባሕር ከፍሎ ጠላት ገድሎ፣ መና አውርዶ ደመና ጋርዶ፣ ዐለት ሰንጥቆ ውኃ አፍልቆ እየመገበና እየጠበቀ ከግብፅ ምድር አውጥቶ በበረሃ እየመራቸው ያለውን አምላክ ባልተጠራጠሩትና የሰዎችን ኀያልነት አጉልተው ባልተናገሩ ነበር። የእግዚአብሔርን ቸርነት በአግባቡ የተረዱት ኢያሱና ካሌብ ግን ምንም እንኳን ሰዎቹ ኀያላን ቢሆኑም በእግዚአብሔር ቸርነት እንወርሳታለን በማለት ተናገሩ። 

ለ. መልካም ወሬ ያመጡት፡- የተስፋይቱን ምድር ሊወርሱ እንደሚችሉ  በተስፋ የተናገሩ  ኢያሱና ካሌብ ናቸው። የእግዚአብሔር ሰው ሁል ጊዜ የሚናገረው ለሰው መልካም የሆነውን ነው። ሰው የሚድንበትን፣ ሰው የነገ ተስፋ የሚሰንቅበትን፣ ወደ ፊት ብሩህ ተስፋ የሚይዝበትን መልካም ወሬ ያወራል። 

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ሰላምን የሚያወራ መልካም የምሥራችንም የሚናገር፣ መድኃኒትንም የሚያወራ፣ ጽዮንንም አምላክሽ ነግሦአል፤ የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።” (ኢሳ.፶፪፥፯) በማለት ተናግሯል። መልካም ነገርን የሚናገር ሰው አንደበቱ ብቻ ሳይሆን እግሩም ያማረ ነው ይባልለታል። አንድ ሰው ይመጣል ተብሎ ባልታሰበበት ጊዜ ሲመጣ “በእውነት አመጣጥህ መልካም ነውን” ተብሎ ይጠየቃል። ምን አልባትም በመጣበት ወቅት መልካም ነገር የማይከሠት ከሆነ ሰውየው ሳይቀር “እግረ ደረቅ”፣ “ገደ ቢስ” ይባላል። ከዚህ አልፎ ደግሞ የሚናገረው ነገር ሰው የሚያስቀይም ከሆነ እጅግ የተጠላ ይሆናል። 

ኢያሱና ካሌብ ግን የተመለከቱት ነገር ምንም የሚያስፈራ ቢሆንም በእግዚአብሔር ቸርነት ሁሉ እንደሚቻል አምነው እንወርሳታለን በማለት መልካም ነገርን ተናገሩ። እንደነዚህ መልካም ነገርን መናገር የሚችሉትን ሰዎች ልበ አምላክ ዳዊት “የጻድቅ አፉ ጥበብን ይማራል፤ አንደበቱም ጽድቅን ይናገራል። የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው።” (መዝ.፴፮፥፴) በማለት ይገልጻቸዋል። መልካም ወሬ የሚባለውም ይህ ነው።

ሐ. የክፉ ወሬ ውጤት፡- ስለ ተስፋይቱ ምድር ስለ ከነዓን ክፉ ወሬ ያመጡት መጨረሻቸው ሞት ነበር። የክፉ ነገር ውጤቱ መቼም ቢሆን ሞት ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ “ለኃጢአት ትገዙ በነበረበት ጊዜ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። በዚያን ጊዜ ሥራችሁም እነሆ ዛሬ ታፍሩበታላችሁ መጨረሻው ሞት ነውና” (ሮሜ ፮፥፳፫) በማለት እንደተናገረው ክፉ የተናገሩት አካላት ውጤታቸው ሞት ሆኗል። ነገሩ ሐሰትና ክፉ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የሚነገርበት መንገድና ዐውድም በራሱ ወሳኝነት አለው። 

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  ልጇን ከሄሮድስ ለማዳን ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በተሰደደች ጊዜ መንገድ ላይ ደክሟቸው እንደተቀመጡ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ደረሰባቸው። ዮሳም ወዲያውኑ እንደደረሰ “የቤተ ልሔም ሕፃናት አልቀዋል፤ እናንተ እዚህ ተቀምጣችኋል” በማለት ፈጥነው ተነሥተው ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ሲናገር ምንም እንኳ እርሱ የተናገረው ለእነርሱ ከማዘን አንጻር ቢሆንም ጌታችን መድኃኒታችን ግን እናቴን አስደንግጠሃታልና ዳግም እስክመጣ ድረስ ከዚች ደንጊያ ላይ ዕረፍ ብሎ እንዲሞት አድርጎታል። ይህንንም በማኅሌተ ጽጌ እመቤታችን ድንግል ማርያምን ያመሰገነው አባ ጽጌ ድንግል “ዮሳ ወልደ ዮሴፍ ምንተ ገብረ ኃጢአተ፣ ዘያደነግጸኪ ዜና በእንተ ዘአምጽአ ግብተ፣ አኮኑ ጻስቅ በትእዛዘ ጽጌኪ ሞተ፤ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ምን ኃጢአት ሠራ? የሚያስደነግጥሽ ዜናን ድንገት ስላመጣ ጻድቁ በልጅሽ ትእዛዝ ሞቷልና።” (ማሕሌተ ጽጌ) በማለት ገልጾታል።

ዮሳ የተናገረው ነገር እውነት ነው። ግን የተናገረበት ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ነበር። ዛሬም ጉዳዩ እውነታ ሊኖረው ይችላል። ይሁን እንጂ የምንናገርበት መንገድ፣ እውነትም ቢሆን ጊዜው ቦታውና ሁኔታው ተገቢ ካልሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝንና የምንድንበት ሳይሆን የምንሞትበት ይሆናል። ዐሥሩ ሰላዮች የተናገሩት እውነት ነበር ሰዎቹ የሚያስፈሩ፣ የሚያስጨንቁ ነበሩ፤ ግን የተናገሩበት መንገድ የእግዚአብሔርን ቸርነት የዘነጉበት ሁኔታ ስለሆነ ያመጡት መረጃ የሞታቸው ምክንያት ሆናቸው። 

መ. የመልካም ወሬ ውጤት፡- መልካም ወሬን ያመጡት ሁለቱ ሰላዮች ማለትም ኢያሱና ካሌብ ውጤታቸው በሕይወት መኖር ነበር። እውነትንና መልካም ነገርን የያዘ ለጊዜው ደካማ ቢመስልም ፍጻሜው ግን ያማረ ይሆናል። ይህን በተመለከተ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “በክብርና በውርደት፣ በምርቃትና በርግማን እንደ አሳቾች ስንታይ እውነተኞች ነን። እንደማይታወቁ ስንታይ የታወቅን ነን፤ እንደ ሰነፎች ስንታይም ልባሞች ነን፤ እንደሙታን ስንታይ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆንም አንገደልም። ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስተኞች ነን፤ እንደ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን እናበለጽጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ በእጃችን ነው” (፪ቆሮ.፮፥፰-፲) በማለት እንደገለጸው ምንም በሰው ዘንድ ጠቀሜታው ፈጥኖ ባይታይም መጨረሻው ግን ያማረ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን ስለእርሱ መልስ ይሰጡበታል። ከአነጋገርህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከአነጋገርህም የተነሣ ይፈረድብሃልና” በማለት እንዳስተማረው የምንናገረው ነገር በሕይወት ለመኖርና ላለመኖር እጅግ ትልቅ ድርሻ አለው። መልካም መናገር ያስከብራል፣ ያሸልማል፤ በሕይወት እንድንኖር ያደርገናል። በአንጻሩ ክፉ መናገር ደግሞ ያዋርዳል፣ ያስቀጣል፣ ሞትንም ያስከትላል። 

ዛሬም የሆነውን የሚደብቁ ያልሆነውን ሆነ የሚሉ፣ ሰውን ወደ መልካም ነገር ሳይሆን ወደ ግጭትና ወደ ጦርነት እንዲገፋፉ የሚያደርጉ ብዙ ሰዎቹ ናቸው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ የዕለተ ምጽአትን ምልክት ለጠየቁት ደቀ መዛሙርቱ “ጦርነትን የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ፤ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው” (ማቴ.፳፬፥፮) ፤ “ጦርነትንና የጦርነትንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ይሆን ዘንድ አለውና፤ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው።” (ማር.፲፫፥፯) በማለት አስረድቷቸዋል። ስለዚህ በየቦታው የጦርነት ወሬ የሚያወሩ፣ የሆነውን ሳይሆን ያልሆነውን እየተናገሩና እየጻፉ ሰውን ከሰው የሚያጋጩ በርካቶች ናቸው።

ሐዋርያው ያዕቆብ  “ምላስ እሳት ናት፤ እነሆ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት፤ ሥጋችንን ትበላዋለች፤ ውሳጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች፤ ከገሃነም  ይልቅ ታቃጥላለች። የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ ለሰው ይገዛል፤ ተገዝቷልም። የሰውን ምላስ ግን መግዛት የሚቻለው የለም፤ ክፉ ናት ዐቅምም የላትም፤ የሚገድል መርዝንም የተመላች ናት። በእርስዋ እግዚአብሔር አብን እናመሰግነዋለን፤ በእርስዋም በአርአያ እግዘአብሔር የተፈጠረ ሰውን እንረግመዋለን” (ያዕ.፫፥፮-፱)  በማለት አንደበታችን ምን መሆን እንዳለበት ያስረዳናል። ስለዚህ አንደበታችን የተፈጠረልን ልንናገርበት ነው። ይሁን እንጂ የምንናገረው ግን የእግዚአብሔርን ቃል እና መልካም የሆነውን ሁሉ ሊሆን ይገባል።

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በድጓው “ይጹም ዐይን ይጹም ልሳን እዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ኅሱም በተፋቅሮ፤ ዐይን ይጹም፣ አፍም ይጹም ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም” በማለት የተናገረው ኅዋሳችን የተሰጠን መልካም ነገርን ልንጠቀምበት ነው። ነገር ግን ከመጠቀም አልፎ ልንጎዳበት የምንችለውን ሥራ ከመሥራት ግን መቆጠብ ይኖርብናል። መጾም የሚባለውም ከእህልና ከውኃ መከልከል ብቻ እንዳልሆነ ሊቁ ነግሮናል። ጎረቤቶቻችንን የሚያሳዝን ወሬን ከመናገር፣ ዐይናችን የእኛ ያልሆነውን ከመመልከትና ባልንጀራችንን ከማሳዘን  ወዘተ. ሁሉን መከልከል ይኖርብናል።

የሚሆነውንም የማይሆነውንም ነገር እየተናገሩ ሰውን ከመጉዳት ይልቅ ያለንበት ወቅቱ አስቸጋሪ ነውና ይህን አስቸጋሪ ወቅት ማለፍ እንድንችል መጾም ያስፈልጋል። እንዲሁ የሰዎችን አእምሮ የሚጎዳ ክፉ ወሬን ከምነግራቸው በችግራቸው ደርሰን ልናጽናናቸው፣ ካለባቸው ረኀብና ጥም ልንታደጋቸው ይገባል። በመጽሐፈ ጦቢት “ከገንዘብህ ምጽዋት ስጥ፤ ምጽዋትንም በምትመጸውት ጊዜ በገንዘብህ አትንፈግ፤ ከድኃም ፊትህን አትመልስ። እግዚአብሔርም ፊቱን ከአንተ አይመልስም። ባለህ መጠን የሚቻልህን ያህል ምጽዋት አድርግ። ጥቂትም ቢሆን ለመስጠት አትፈር፤ ምጽዋት መስጠት መልካም  ድልብን ታደልብልሃለችና። ምጽዋት በመከራ ቀን ከሞት ታድናለችና። ወደ ጨለማም ከመሄድ ትጠብቅሃለችና። ምጽዋትም ለሚያደርጋት ሁሉ በልዑል ፊት መልካም ስጦታ ናት።” (ጦቢ. ፫፥፯-፲፩) ተብሎ እንደ ተነገረ እግዚአብሔርን  ደስ የሚያሰኘውን ለእኛም የሚጠቅመንን መልካም ሥራ መሥራት ይኖርብናል። 

እንዲሁም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ብፁዕ ውእቱ ዘኮነ ኬንያ ለነፍሱ፤ ብፁዕ ውእቱ ዘተግኅሠ እምኃጢአት፤ ብፁዕ ውእቱ በአፉሁ ዘኢተናገረ ከንቶ፤ ብፁዕ ውእቱ በከመ በዓቱ ዘኮኖ ፀዓቱ፤ ብፁዕ ውእቱ ዘኮኖ ልቡ ሠረገላ ለጸሎት፤ ብፁዕ ውእቱ፤ ለነፍሱ ጥበበኛ የሆነ ብፁዕ ነው፤ ከኃጢአት የራቀ ብፁዕ ነው፤ በአፉ ከንቱ ነገርን ያልተናገረ ብፁዕ ነው፤ መጨረሻው እንደ መጀመሪያው የሆነለት ብፁዕ ነው፤ ልቡ የጸሎት ሠረገላ የሆነለት ብፁዕ ነው።” (ጾመ ድጓ ዘገብር ኄር) በማለት ከኃጢአት የራቀ፣ በአፉ ከንቱ ነገርን ያልተናገረ፣ ልቡ የጸሎት ሠረገላ የሆነለት፣ ንዑድ ክቡር የተመሰገነ መሆኑን ያስረዳናል።

በአጠቃላይ ሰው በዚህ ዓለም ጊዜያዊም ቢሆን ይኖርበት ዘንድ በተሰጠው በዚህች ምድር ሲኖር የሚገባውን እየሠራ የሚገባውን እያገኘ፣ ለማያልፈውና ዘለዓለማዊው ዓለም መሥራት እንዳለበት መረዳት የግድ ነው። ሰው በማኅበር ይኖር ዘንድ የተፈቀደለት ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልገውም ነገር ነው። ማንም በራሱ ምሉእ አይደለም። ስለዚህ ከራሱ የሚጎድለውን ከሌላው ያገኛል። እርሱ የጎደለውን ከሌላ እንደሚያገኝ ሁሉ በአንጻሩ እርሱም ለሌላ የሚሰጠው ብዙ ነገር አለው። በዚህ ጊዜ ግን የሚገባውን እየተናገረ፣ ከክፉ ነገር ርቆ፣ ሰውነቱን ከኃጢአት አርቆ፣ በአንደበቱ፣ በዐይኑ፣ በእጁ፣ በእግሩ ወዘተ በሰውነት ክፍሎቹ ሁሉ ከሚመጣ በደል ታግሦ መኖር አለበት። በሃይማኖት ጸንቶ በጎ ምግባር ሠርቶ ከሰው ጋር በፍቅር ኑሮ፣ በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ መኖር ያስፈልጋል። እንዲህ ያደረገ ሰው መጨረሻው ዘለዓለማዊ ሕይወት ያለበትን ሰማያዊውን ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል። ሁላችንንም ስሙን ቀድሰን፣ መንግሥቱን ወርሰን ለመኖር ያብቃን አሜን።

Read 638 times