በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ ኦ እግዝእትየ ማርያም ሰላም ለኪ፤ እመቤቴ ሆይ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ።
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳታቋርጥ በምትጸልየው የዘወትር ጸሎት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ካስተማረው አቡነ ዘበሰማያት ቀጥሎ የሚጸለይ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ያቀረበው የምስጋናና የሰላምታ ጸሎት ነው። ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ የአንድነት የሦስትነት ምስጋና ካቀረበች በኋላ ለእመቤታችንም ምስጋና ታቀርባለች ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ - ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድም ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል›› ብላ ካመሰገነች በኋላ ‹‹ስብሐት ለእግዝትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፤ አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና ይገባል›› በማለት ታመሰግናለች።
በስግደትም እንዲሁ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ የአንድነት የሦስትነት የባሕርይ የአምላክነት ስግደት በኋላ ለእመቤታችንም የባለሟልነት፣ የመወደድና የእናትነት ስግደት ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐተ ስግደተ እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእንዘ ሠለስቱ አሐዱ ይሤለሱ በአካላት ወይትወሐዱ በመለኮት፤ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ለሚሆን አምላክ እሰግዳለሁ።›› በማለት አንድነት ሦስትነትን የሚመሰክረው ኃይለ ቃል ከተነገረ በኋላ፡- ‹‹እሰግድ ለእዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ - አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምም እሰግዳለሁ›› በማለት እንደተገለጸው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በተግባር ትገልጠዋለች።
ለእመቤታችን የምንሰግድበት ምክንያት መስተብቁዕ ዘመስቀል በተባለው የቤተ ክርስቲያን የጸሎት ክፍል ‹‹ለማርያምሰ ዘንሰግድ ላቲ እስመ ነሥአ ሥጋ እምሥጋሃ እግዚአብሔር ፈጣሪሃ ወረከብነ ንሕነ መድኀኒት እምኔሃ - ለማርያምስ የምንሰግድላት እግዚአብሔር ፈጣሪዋ ከእርሷ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ስለነሳ ከእርሷም መድኀኒትን ስላገኘን ነው›› በማለት ይገልጻል። ወደ ጥንተ ነገራችን (የገብርኤል ሰላምታ) እንመለስ ቅዱስ ሉቃስ ይህንን ሲዘግብ ከላኪው ከተላኪው ከተላከበት ቦታ የተላከላትንም በማስረዳት ነው። የተላከበትን ጊዜ ሲገልጽ ‹‹ወበሳድስ ወርኅ ተፈነወ ገብርኤል መልአክ እምኀበ እግዚአብሔር፤ በስድሰተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተላከ›› (ሉቃ.፩፥፳፮) እንዲል። ስድስተኛ ወር የተባለው ቅዱስ ገብርኤል ለዘካርያስ ኤልሳቤጥ እንደምትፀንስ፣ ዮሐንስ እንደሚፀነስ በመሠዊያው አጠገብ ተገልጾ ባናገረበት በስድስተኛው ወር ሲል ነው። ወይም በአዳም በደል ምክንያት ዓለም በድቅድቅ ጨለማ በኖረበት ለአዳም ተስፋ በተሰጠበት የሰው ልጅ የኀጢአትና የዲያብሎስ ባርያ በሆነበት በስድስተኛው ሺህ ቅዱስ ገብርኤል መልእክተኛ ሆኖ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ አንዲት ድንግል ተላከ ማለት ነው።
ይህንን ጽንሰ ሐሳብ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹ወሶበ ርእየ ንጽሕናኪ ለሊሁ እግዚአብሔር አብ ፈነወ ኀቤኪ መልአኮ ብርሃናዌ ዘስሙ ገብርኤል፤ እርሱ ቅሉ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የተባለ ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንቺ ላከ›› (ቅዳሴ ማርያም) በማለት የተናገረውን መተርጕማኑ ደግሞ “ተርታ መልአክ ያይደለ ባለሟሉን፣ ያልታወቀውን ያይደለ የታወቀውን፣ መልአከ ጽልመት ያይደለ ብርሃናዊውን መልአክ ወደ አንቺ ሰደደው” በማለት አብራርተውታል።
ድንግልን እንዲያበሥር የተላከው ቅዱስ ገብርኤል መልአክ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲገልጽ ‹‹ሶበ ተወልደ እምድንግል ዐቀበ ድንግልናሃ እንበለ ሙስና እስመ ቀዳሚ ሔዋን ኮነት ድንግለ ወአስሐታ ዲያብሎስ ለማርያም ድንግል አብሠራ ገብርኤል፤ ከድንግል በተወለደ ጊዜ ድንግልናዋን ባለመለወጥ አጸናው ቀድሞ ሔዋን ድንግል ነበረችና ዲያብሎስ አሳታት እንጂ ድንግል ማርያምን ግን ገብርኤል አበሠራት›› (ሃ.አ.ዮ.አፈ. ምዕ.፷፯ ክፍ ፲፩፥፫፤ ዘፍ. ፫፥፩-፪፤ ሉቃ. ፩፥፳፮) ሔዋን የዲያብሎስን ቃል ሰምታ መቀበሏ እና ድንግል ማርያም ደግሞ የመልአኩን ቃል ሰምታ መቀበሏ ያመጣውንም ውጤት ሲገልጥ እንዲህ ይላል ‹‹ወባሕቱ ለሔዋንሰ አስሐታ ዲያብሎስ ወወለደት ቃየልሃ ዘውእቱ ምክንያተ ሞት ወማርያምሰ ሶበ አብሠራ መልአክ ወለደት ቃለ በሥጋ ዘውእቱ መራሔ ኵሉ ኀበ ሕይወት ዘለዓለም፤ ነገር ግን ሔዋንን ዲያብሎስ አሳታት የሞት ምክንያት የሚሆን ቃየልን ወለደች ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች›› (ሃ.አ.ዮ.አፈ. ምዕ.፷፯ ክፍ ፲፩፥፬)
ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ ንጽሕት፣ ቅድስትና ብፅዕት ወደ ሆነችው ድንግል ማርያም የያዘውን መልእክት ያመጣ ዘንድ በአምሳለ ብእሲ ተገለጠ፤ እሳታዊው መልአክ ከእግዚአብሔር ተላከ፤ የተሠወረ ምሥጢር ይዞ ከእግዚአብሔር የተላከው መንፈሳዊው መልአክ ከሰማይ ሠራዊት መካከል መጣ። እርሱም ብላቴናይቱን አግኝቶ ሰላምታ ሰጣት በላይ በሰማይ በሚኖረው በእግዚአብሔር እንደታዘዘው ምሥጢሩን ገለጠው።
የንጉሡ እናት በሆነችው በድንግል ፊት ጎንበስ ብሎ ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ሊገባትና ልትቀበለው በምትችል ንግግር አነጋገራት። በመለኮታዊ ጸጋ ውበት የተመላሽ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን፤ የጽድቅ ፀሐይ እናት የሆንሽ ማርያም ሆይ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ የተቀደሱ ነገሮች መናገሻ የሆንሽና በበጎነት የተመላሽ ሆይ ሰላም ባንቺ ላይ ይሁን፤ የምሥጢራት መሸሸጊያ በከበረ ጸጋ የተመላሽ መርከብ ነሽ፤ ከሴቶች ሁሉ ተለይተሸ የተባረክሽ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን፤ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ። እያለ የምስጋና ነጠብጣብን በፊቷ ያወርድ ጀመረ። ይህንን የመልአኩን ድንቅ የሰላምታ ቃል ወንጌላዊው ‹‹በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባለው ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር መልአኩም ወደ እርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ካንቺ ጋር ነው ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት›› (ሉቃ. ፩፥፳፮-፳፱) በማለት ይገልጻል።
መልአኩ የተላከው ከእግዚአብሔር ነው ‹‹ዘእግዚአብሔር ፈነዎ ይነግር ቃለ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል›› (ዮሐ.፫፥፴፬) ተብሎ እንደተጻፈ የሚናገረው የእግዚአብሔርን ነገር ነው መልአኩ ወደ እርሷ ገብቶ ከተናገረው ጀምሮ ያለውን ባጭሩ እንይ መልአኩ እመቤታችንን ያናገራትና ሰላምታ ያቀረበበት ሦስት ጊዜና ሦስት ቦታ ላይ ነው። እመቤታችን በቤተ ዮሴፍ ሳለች የዮሴፍን ልጆች ዘመድ ዘመድ ለማለት ባጭር ታጥቃ ውኃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ወርዳ ውኃ ቀድታ ስትመለስ መንገድ ላይ የመጀመሪያውን ድምፅ (ሰላምታ) ሰምታለች። ይህንንም ዘወር ብላ አንዳች እናቴን ሔዋንን ያሳትክ ሰይጣን ትሆን ብላ ትታው ሄደች። ሁለተኛው እንስራዋን ስታወርድ ከቤት ውስጥ ያንኑ ቃል ደገመላት። ይህ ነገር የመንፈስ ቅዱስ ይሁን ወይስ የሰይጣን ነገሩን ከቤተ መቅደስ (ከቤተ እግዚአብሔር) ሆኖ ሊረዱት ይገባል ብላ ሳትዘገይ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሄዳለች። ከደናግለ እስራኤል የተካፈለችውን ሐርና ወርቅ እያስማማች ስትፈትል መልአኩ ወደ እርሷ ገብቶ (ወደ እርሷ ባሕርይ ተመልሶ እየወደቀ እየተነሣ እየታጠቀ እየፈታ በአምሳለ ሰያብ አረጋዊ ሰውነቱ ክት አንደበቱ ነገር አያሳትት በሚባል ሽማግሌ ሰላምታ አቀረበላት። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ወእንዘ ትፈትል ወርቀ ወሜላተ አስተርአያ ገብርኤል ግብተ፤ ሐርና ወርቁን እያስማማች ስትፈትል ወደ እርሷ ገብቶ ታያት›› በማለት ገልጾታል የቦታ ነው ቢሉ እርሷ ወዳለችበት ቤት ገባ የመገለጥ ነው ቢሉ ባሕርይዋን መሰለላት፤ መስሎም ታያት ሲል ቦአ መልአክ ኀቤሃ አለ።
በሰላምታው አራት ድንቅ ድንቅ ነገሮችን አካቷል። እነርሱም፡-
- ተፈሥሒ ፍሥሕት
- ኦ ምልዕተ ጸጋ
- እግዚአብሔር ምስሌኪ
- ቡርክት አንቲ እምአንስት
እነዚህን የሰላምታ ቃላት እያንዳንዳቸውን እናያቸዋለን ከመልአኩ ለእመቤታችን የቀረቡ ወንጌላዊው በጥንቃቄ ያሰፈራቸው በዚህ መነሻነት ብዙ ሊቃውንት የተረጎሙአቸው የተነተኑአቸው ናቸው።
፩. ተፈሥሒ ፍሥሕት፤ ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ
የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር በመለየታቸው ደስታ ከራቃቸው አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናትን ቈጥረው ባሉበት ዘመን “ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ” በማለት ለድንግል ማርያም መልካም ዜናን ተናገረ። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የእመቤታችንን ነገር በተናገረበት አንቀጹ በምዕራፍ ስልሳ ስምንት በክፍል ሃያ ስድስት ላይ እመቤታችንን ደስ ይበልሽ እያልን የምናመሰግንበትን ነገር እንዲህ ይገልጸዋል። ‹‹የጠፋ በግ አዳምን የፈለገው ባገኘውም ጊዜ የተሸከመው እውነተኛ ቸር ጠባቂ ካንቺ የተወለደ እመቤቴ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ›› እንዲል። ሊቁ ለእመቤታችን ከሚያቀርበው ሰላምታ በተጨማሪ ሰላምታውን የሚያቀርብላት ቅድስት ድንግል ማርያም የወለደችው ቸር ጠባቂ መሆኑንም ያስረዳናል። በቅዱስ ወንጌል ‹‹የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግ የሞተውን ሊያድን መጥቷል›› (ሉቃ. ፲፬፥፲) ፤ ‹‹እውነተኛ እረኛ እኔ ነኝ እውነተኛ እረኛ ራሱን ስለ በጎቹ ይሰጣል›› (ዮሐ. ፲፥፲፩) ተብሎ እንደተጻፈ ቅድስት ድንግል ማርያም የወለደችው እራሱን ለበጎቹ የሚሰጥ፣ እውነተኛና ቸር እረኛ ነው። ስለዚህ ይህን ቸር እረኛ የወለደች እናቱ ድንግል ማርያምን ደስ ይበልሽ እያልን እናመሰግናታለን።
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አያይዞም ‹‹እግዚአብሔር በሲኦል የጣላት የሔዋን ጽኑ ፍዳ ባንቺ የጠፋ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ›› በማለት ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ፤ በሔዋን ምክንያት የገነት በር ተዘጋብን በድንግል ማርያም ምክንያት ተከፈተልን›› (ውዳሴ ማርያም) ብሎ የገለጸውን ያጠነክርልናል። ገነት ሲዘጋ ሔዋንና ልጆቿ ሁሉ ወደ ሲኦል ተጥለዋል፤ በጽኑ ፍዳ ውስጥም ኖረዋል። ይህ ጽኑ ፍዳ የተወገደልን አምላክ ከእመቤታችን ሰው በመሆኑ ነውና ለእንዲህ ያለው ክብር ምክንያት የሆነች ድንግል ማርያምን ሊቃውንቱ ተባብረው ደስ ይበልሽ አሏት።
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምንሰግድለት ቃል ካንቺ ይወለድ ዘንድ ዓለም ሳይፈጠር የነበረ እግዚአብሔር አንቺን የወደደ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ። እኔ ሐዋርያ የሆንኩለት የጌታ እናቱ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ማኅተመ ድንግልናሽን ያለመለወጥ የጠበቀውን አማኑኤልን የወለድሽ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ። እያለ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ተከትሎ ያመሰግናታል፤ እኛም ደስ ይበልሽ እንላታለን። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የጀመረውን ሰላምታ መሠረት አድርገው ያመሰገኑት ሊቃውንት በርካታ ናቸው። ለማሳያ ያህል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን እንደጠቀስን ከሌሎችም የተወሰነ እንጥቀስ።
ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው “ኦ ምልዕተ ጸጋ ኦ ሙኀዘ ፍሥሐ፤ ጸጋን የተመላሽ የተድላ የደስታ መፍሰሻ” (ቅዳሴ ማርያም) እያለ ያመሰግናታል። ሊቁ እርሷ ደስታን የተመላች ናትና የተድላ የደስታ መፍሰሻ በማለት ገለጻት። እርሷ ምልዕተ ጸጋ ሁና በአማላጅነቷ ለሚያምን ሁሉ ጸጋን ታሰጣለችና የተድላ የደስታ መፍሰሻ አላት።
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም ‹‹ተፈሥሒ ኦ ወላዲተ እግዚእ ሐሤቶሙ ለመላእክት፤ የመላእክት ተድላ ደስታቸው አምላክን የወለድሽ ደስ ይበልሽ፤ የመላእክት ዜና ትንቢታቸው ንፅሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ የዓለሙን ሁሉ ተድላ ደስታ የሆነውን የመልአኩን ቃል ተቀብለሽዋልና ደስ ይበልሽ›› (ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ) እያለ የተድላ የደስታ የሰላም የፍቅር መገኛ የሆነችውን እመ ብርሃንን ያመሰግናታል። እኛም እነሱን አብነት አድርገን በዘወትር ጸሎታችን ‹‹ተፈሥሒ ፍሥሕት›› እያልን እናመሰግናታለን።
፪. ኦ ምልዕተ ጸጋ፤ ጸጋን የተመላሽ
ጠቢቡ ሰሎሞን በመኀልዩ ‹‹ኵለንታኪ ሠናይት እንተ ኀቤየ አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ፤ ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ ምንም ነውር የለብሽም” (መኃ. ፬፥፯) በማለት የነቢብም የኀልዮም የገቢርም ኃጢአት የሌለባትን የእመቤታችንን ንጽሕና ቅድስና ፍጽምና መስክሯል። በሌላ ቦታም ‹‹መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ አንቺ ግን ከሁሉ ትልቂአለሽ እጅግም ትበልጫለሽ›› (ምሳ. ፴፩፥፳፱) ይላል። ከሁሉ መብለጧ መላቋ ደግሞ ምልዕተ ጸጋ በመሆኗ ነው። ሊቁ አባ ሕርያቆስ ‹‹ኦ ምልዕተ ጸጋ ኦ ሙኀዘ ፍሥሐ፤ ጸጋን የተመላሽ የተድላ የደስታ መፍሰሻ ሆይ›› በማለት እንደመሰከረላት። ጸጋ ማለት ሀብት ስጦታ ማለት ነው ለእመቤታችን ተከፍሎ የቀረባት ጸጋ የለም በወንጌል እንደተገለጸው እግዚአብሔር ጸጋውን ሰፍሮ አይሰጥም። ይህ ማለት ለእያንዳንዱ በልክ በልኩ ጸጋ ተቀባዩ የሚችለውን ያክል ይሰጣል እንጂ ማለት ነው። ለቅዱሳኑ ሁሉ የተሰጣቸው በሚችሉትና በሚገባቸው ልክ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው›› (፩ቆሮ. ፲፪፥፬) ብሎ እደተናገረ። እመቤታችን ግን በመልአኩ አንደበት ‹‹ምልዕተ ጸጋ›› ተብሎ እንደተነገረው ጸጋ ያልተከፈለባት ናት።
ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹አይ ልቡና ወአይ ነቢብ ወአይ ሰሚዕ ዘይክል አእምሮ ዝንቱ ምሥጢር መንክራተ ዘይትነበብ ላዕሌሃ፤ ስለ እርሷ ድንቅ ሆኖ የሚነገረው ይህንን ምሥጢር ማወቅ የሚቻለው ምን ልብ ነው መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው›› በማለት በምልዕተ ጸጋነቷ ያገኘችውን ክብርና ባለሟልነት ይገልጻል።
፫. እግዚአብሔር ምስሌኪ (እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው)
እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው የሚለው አገላለጽ “የቀድሞ አባቶችም በዮሴፍ ላይ ቀንተው ወደ ግብፅ ሀገር ሸጡት፣ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበር” (ሐዋ.፯፥፱-፲) እንደተባለው አይደለም። ወይም መልአኩ ለጌዴዎን ተገልጦ “አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነው” (መሳ.፮፥፲፪) እንዳለው አይደለም። እንዲሁ ጌታም ለሐዋርያቱ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” (ማቴ.፳፰፥፳) ብሎ እንደተናገረው አይደለም።
እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ሲል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ በማሕፀኗ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አድሮ ሐሊበ ድንግልናዋን እየጠባ ያደገበት ፍጹም ሰው የሆነበትን ምሥጢር ሲገልጥ “እግዚአብሔር ምስሌኪ” አለ ይህንንም ቅዱስ ቄርሎስ በሃይማኖተ አበው ‹‹እግዚአብሔር አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ የሚተካከለው እርሱ ቀምቶ እግዚአብሔር የሆነ አይደለም እራሱን አዋርዶ የተገዥ ባሕርይን ገንዘብ አደረገ።
መለኮትስ እንደ ሰው በድንግል ማሕፀን የዕለት ፅንስ በመሆን በድንግል ማሕፀን ሳለ በሰማይም በምድርም ምሉዕ ነው ለፅንሱ ወራት ዘጠኝ ወር እስኪፈጸም ድረስ እንደሰው ሁሉ በየጥቂቱ አደገ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ከእርሷ በነሳው ሥጋ ወለደችው በጨርቅም ጠቅልላ በበረት አስተኛችው ፍጹም መለኮቱ የሰውን ሥጋ ተዋሐደ ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ሆኖ ሠላሳ ዘመን እስኪሞላው ድረስ በአካል በጥበብ በሕዋሳት መጽናት በየጥቂቱ አደገ›› (ሃ.አ.ዘቄ ም ፸፩ ክ ፫ ቁ ፮-፯) በማለት እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ጋር የሆነው በተዋሕዶ ማለትም ሥጋዋንና ነፍሷን በመዋሐድ መሆኑን ያስረዳል።
አባ ጊዮርጊስም ይህንን ድንቅ ምሥጢር በሰዓታቱ እንዲህ ይገልጸዋል ‹‹በእንተ ሥጋ ወነፍስ አጽም ወደም ጸጉር ወአስራው ዘነሳእከ እምኔሃ ወረሰይኮ አሐደ ምስለ መለኮትከ ዘእንበለ ፍልጠት ኢ ውላጤ ወዘእንበለ ቱስሕት ኢ ቡአዴ በከመ መሀሩነ አበው፤ አባቶቻችን እንዳስተማሩን ከእርሷ የነሳኸውን ሥጋና ነፍስ አጥንትና ደም ጸጉርና ጅማት ከመለኮትህ ጋር ያለመለየት ያለመለወጥ ያለመጨመር ያለመነጠል አንድ አደረግኸው›› በማለት ፍጹም የሆነውን ተዋሕዶ ይገልጻል። ስለዚህ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው ማለት በኅድረት ሳይሆን በኵነት፣ ማለትም በረድኤት፣ በጸጋ ሳይሆን በተዋሕዶ መሆኑን እንረዳለን።
፬. ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ
ይህ ቃል ሰማያዊው ቅዱስ ገብርኤልና ምድራዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ የተባበሩበት ቃል ነው። ከሴቶች ተለይተሽ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለብሽ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እያማለድሽ የምታሰጭ ነሽ ሲሏት ‹‹ቡርክት አንቲ እም አንስት›› ብለዋታል። ይህንንም ቅዱስ ቄርሎስ በሃ.አበው ‹‹ለዘመዶቹ ታዘዘ ይህችውም ያለ ዘርአ ብእሲ የወለደችው እናቱ ናት በሥጋ ከእርሷ መወለዱም እንደ ሴቶች መፅነስ ሥርዓት ልማድ አይደለም ከሴቶች መፅነስ ሥርዓት ልማድ የተለየ ነው እንጂ ድንግል በሥጋ ያለ ዘርአ ብእሲ ወለደችው›› (ሃ.ዘቄ ም.፸ ክ.፪ ቁ.፳፭) ብሎ እንደተናገረ እናትነትን ከድንግልና ድንግልናን ከእናትነት አስተባብራ የያዘች ብቸኛ ሴት ድንግል ማርያም ብቻ ናት። ስለዚህ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ ተባለች።
ጠቢቡ ሰሎሞንም በመኃልዩ ‹‹ርግቤ መደምደሚያዬ አንዲት ናት›› (መኃ.፮፥፱) ብሎ እንዳመሰገነ እመቤታችን በኀልዮ፣ በነቢብ በገቢር ንጽሕት ናትና ‹‹የዓቢ ክብራ ለማርያም እምኩሎሙ ቅዱሳን፤ የእመቤታችን ክብር ከቅዱሳን ክብር ሁሉ ይበልጣል፣ ይእቲ ተዓቢ እምኪሩቤል ወትፈደፍድ እምሱራፌል፤ ይቺ ከኪሩቤል ትበልጣለች ከሱራፌልም ትልቃለች››፤ ‹‹ቡርክት አንቲ አምአንስት ወቡሩክ ፍሬ ከርስኪ፤ አንቺ ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው›› እያልን ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር እናመሰግናታለን።
በአጠቃላይ እመቤታችን ቅደስት ድንግል ማርያም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ እንደተሰጣት ፍጥረታት ሁሉ ያመሰግኗታል። እርሷም “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ.፩፥፵፰) ብላ እንደተናገረችው ትውልድ ሁሉ ያመሰግኗታል። እኛም መልአኩን፣ ሊቃውንቱን ሁሉ አብነት አድርገን ሰላም እልሻለሁ ልንላት ይገባል። ወላዲተ አምላክነቷን አምነን፣ በአማላጅነቷ ተማፅነን ርስተ መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ እግዚአብሔር ይፍቀድልን።
ምልጃ በረከቷን ለሁላችን ያድለን። አሜን!!!