Saturday, 25 September 2021 00:00

በዓላቱ መንፈሳዊ ዕሴታቸውን እንዳይለቁ

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

ብዙዎች በልበ ሙሉነት ‹‹ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ናት›› ብለው ሲናገሩ በርካታ ምክንያቶችን በመጥቀስ ነው፡፡ ታሪኳ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቷ፣ በዓላቷ፣ የሕዝቦቿ አብሮ የመኖር ባህል፣መከባበር፣ እንግዳ መቀበል፣ አለባበስ ስያሜውን እንድታገኝ ካስቻሏት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ምእመናን የነዚህ መንፈሳዊ ዕሴቶች ባለቤት በመሆን ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ እምነታችን በእነዚህ ዕሴቶች ያሸበረቀ ልዩ መስተጋብር ያለውና በሌሎች ዘንድ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሀገራችን በዓለም ደረጃ እንድትታወቅ፣ ክፍ ብላም እንድትታይ አስችሏታል፡፡ የዘመን መለወጫው፣ የደመራ፣ የልደት፣ የጥምቀቱና የፋሲካው ክብረ በዓላት የበዓሉ ባለቤት ከሆነው ከኦርቶዶክሳዊው ምእመን አልፈው በሀገሪቱ ላይ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ የሞቁ የደመቁ፣ ግዘፍ ነሥተው የሚታዩ ናቸውና፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ምእመናን ልጆቿ እነዚህን መንፈሳዊ ዕሴቶች ለመጠበቅ የሚያደርጉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ቀላል አይደለም፡፡ በታሪክ የሀገር መሪዎች የነበሩ ነገሥታቱ ሳይቀሩ በግንባር ቀደምነት ይሳተፉባቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች አሻራቸው ሳይጠፋ ዘመናትን ተሻግረው እዚህ ደርሰዋል፡፡ ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከአባቶች ወደ ልጆች በቅብብሎሽ እዚህ የደረሰው መንፈሳዊ በዓላችን ከትላንት በሰፋ፣ ባሸበረቀ ለሌሎች መስህብ በሆነ መልኩ ሲከናወን ማየትን ያህል የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ ዛሬ ዛሬ እነዚህ በዓላት ከፍ ባለ ደረጃ እንዲከበሩ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በተለይም ወጣቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ በዓላት ከመድረሳቸው በፊት በየአካባቢው ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች አብያተ ክርስቲያናትን፣ መንገዶችን በማጽዳት፣ ሰደቅ ዓላማ በመስቀል፣ ምእመናንን በማስተናገድ፣ ጸበል ጸዲቅ በማዘጋጀት የሚደረገው መንፈሳዊ ርብርብ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያን ያለን መፈሳዊ ቅንዓት እና ተነሣሽነት በመንፈሳዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረተና ፈሪሃ እግዚአብሔር የታከለበት ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ጥሩ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ በብዙዎች ሳይሆን በአንዳንዶች ዘንድ የሚታይ እና ነቀፌታን የሚያስከትል አገልግሎት ዘወትር ክርስቲያናዊ ተግባሩ ማድረግ በቤተ ክርስቲያን ስምም ሆነ በአካባቢዋ እንዳይሠራ መከላከል የሁሉም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል፣ የድርሻውን ለመወጣት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣውን የቤተ ክርስቲያን ልጅ በመጀመሪያ ቃለ እግዚአብሔርን በማስተማር መንፈሳዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የሚሰጠውን አገልግሎት መንፈሳዊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በዓላትን ጠብቆ መስቀልና ጥምቀት በሚውሉበት ቀን ብቻ  የሚመጣውን ትውልድ ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ተገቢ መሆኑን፣ በጾምና በጸሎት ዘወትር ቤተ ክርስቲያን መሳለምና ማስቀደስ በንስሓ ሕይወት ውስጥ መኖርና ከቅዱስ ቁርባን መሳተፍ በሚችሉበት መንገድ ማስተማር የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት ያቀናልና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይ የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ በዓላት ላይ የሚታዩ የሥነ ምግባር ግድፈቶችን ለማረም ከአገልግሎት በፊት እና በኋላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በየዋህነት እና በስመ ኦርቶዶክሳዊነት ደፋ ቀና የሚሉትን ሰብስቦ መሠረታዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በመንፈስ ተጀመርው በሥጋ በሚያልቁ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን በዓላት ላይ በሚደረጉ አገልግሎቶች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግድ ሊላት ይገባል፡፡ ዛሬ ዛሬ ብዙዎች በቤተ ክርስቲያን ስም ተሰባስበው አገልግሎቱን በሥጋዊ መንገድ ሲያከናውኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያፈነገጠ ልብስ ለብሰው፣ በአካላዊ ቁመናቸው ፍጹም ዓለማዊ ሆነው፣ በተንጨባረረ ፀጉር በቤተ ክርስቲያን ዐደባባይ ላይ የሚቆሙ መንፈሳዊ አገልጋዮች በመጀመሪያ መንፈሳዊ ማድረግ እና መምከር ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብሎም ከመንፈሳውያን አባቶችና እናቶች እንዲሁም ወንድሞችና እኅቶች ይጠበቃል፡፡  ታላላቅ የቤተ ክርስቲያንን በዓላትን አስመልክቶ ለሰንደቅ ዓላማ፣ ለጸበል ጸዲቅ፣ ለቄጠማ እየተባሉ ከየምእመናኑ የሚሰበሰቡ በርካታ ገንዘቦች ለታለመላቸው ዓላማ ሳይውሉ ቀርተው የግለሰቦችን ኪስ የሚያደልቡ፣ ከመንፈሳዊነት ባፈነገጠ መልኩ ለመዝናናት፣ ለመጠጥ ሲውሉ ማየት ሥርዓት እየሆነ መጥቷልና ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ሊባል ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የቤተ ክርስቲያንን ስም የሚያጎድፍ መንፈሳዊ በዓላቱንም የሚያጠለሽ ድርጊት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያና በቤተ ክርስቲያን ስም ሲደረግ እያዩ እንዳላዩ አልፎ ሂያጅ ከመሆን ቆም ብሎ ትክክለኛውን ነገር በመንገር እና በመገሠጽ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት ተገቢ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ በእነዚህ ታላላቅ በዓላት አገልግሎት ስም በየሰፈሩ የተደራጁ በርካታ ወጣቶችና፣ ማኅበራት ቢኖሩም በትክክለኛው መንገድ ቤተ ክርስቲያንን እየደገፉ ያሉት የትኞቹ ናቸው? የሚለው ግን አጠያያቂ ነው፡፡ ከላይ ለማንሣት እንደሞከርነው መንፈሳዊ ቅንዓቱ ፣ የቤተ ክርስቲያን ፍቅሩ፣ ለአገልግሎት መትጋቱ ቢኖርም አንዳንዶቹ በዓመት አንድ ጊዜ የሚመጡ የመስቀል ወፍ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ምግብና መጠጥ ብቻ የሚያሰባስባቸው የስም ክርስቲያኖች በመሆናቸው እነዚህን ከመንፈሳውያኑ አገልጋዮች ለይቶ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ማስተማር ይገባል፡፡ በቤተ ክርስቲያን በዓላት ስም የሚደረጉ የሠፈር ልዩ ልዩ ዝግጅቶች አቅጣጫቸውን እየሳቱ ነውና በየአካባቢ የምንገኝ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አባቶች እና እናቶች ትክክለኛውን መንገድ በማሳየት፣ በማስተማር ማስተካከል ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ በየሰፈሩ ወጣቶች እና የአካባቢው ምእመናን ተሰብስበው ደመራ በመለኮስ የመስቀል በዓልን ያከብራሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር መሰባሰባቸው እሰይ የሚያሰኝ ቢሆንም ያለ ዕውቀት የሚሄዱትን በማስተማር፣ ዝግጅቱ መንፈሳዊ እንዲሆን ቃለ እግዚአብሔር እንዲሰጥ በማድረግ፣ ከዘፈን ይልቅ መንፈሳዊነቱን ጠብቆ በመዝሙር እንዲሆን ማድረግ በአጠቃላይ በዓላት መንፈሳዊ ዕሴታቸውን እንዳይለቁ ለማድረግ በያለንበት የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡              
Read 546 times