ሐመረ ጽድቅ
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ሐመር
    • የማኅበሩ መልእክት
    • ትምህርተ ሃይማኖት
    • እናስተዋውቃችሁ
    • የጥያቄዎቻችሁ መልስ
    • ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት
    • ኪነ ጥበብ
    • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን
    • ከዓለም ማእዘናት
    • ዐውደ ስብከት
    • ዐቢይ ጉዳይ
  • ስምዓ ጽድቅ
    • ርእሰ አንቀጽ
    • አጫጭር ዜናዎች
    • ሪፖርታዥ
    • ቤተ አብርሃም
    • ፍሬ ከናፍር
    • የሕፃናት ዓምድ
    • ትዝብት
    • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ
  • ሙሉ ሕትመቶች
    • ሐመር በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • ሐመር በ ዓ.ም.
      • 1985
      • 1986
      • 1987
      • 1988
      • 1989
      • 1990
      • 1991
      • 1992
      • 1993
      • 1994
      • 1995
      • 1996
      • 1997
      • 1998
      • 1999
      • 2000
      • 2001
      • 2002
      • 2003
      • 2004
    • ሐመር በዓመት
      • 1ኛ ዓመት
      • 2ኛ ዓመት
      • 3ኛ ዓመት
      • 4ኛ ዓመት
      • 5ኛ ዓመት
      • 6ኛ ዓመት
      • 7ኛ ዓመት
      • 8ኛ ዓመት
      • 9ኛ ዓመት
      • 10ኛ ዓመት
      • 11ኛ ዓመት
      • 12ኛ ዓመት
      • 13ኛ ዓመት
      • 14ኛ ዓመት
      • 15ኛ ዓመት
      • 16ኛ ዓመት
      • 17ኛ ዓመት
      • 18ኛ ዓመት
      • 19ኛ ዓመት
      • 20ኛ ዓመት
    • ስምዓ ጽድቅ በወር
      • መስከረም
      • ጥቅምት
      • ህዳር
      • ታህሣሥ
      • ጥር
      • የካቲት
      • መጋቢት
      • ሚያዝያ
      • ግንቦት
      • ሰኔ
      • ሐምሌ
      • ነሐሴ
    • አዳዲስ ሙሉ ሕትመቶች
      • አዲስ ሐመር
      • አዲስ ስምዐ ጽድቅ
  • ያግኙን

የቆዩ እትሞች

በ PDF መልኩ በቀላሉ ያውርዱ

የጌታችን ትንሣኤ

Details
Written by: እህተ ሚካኤል
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1282
  • የሕፃናት ዓምድ

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን .. . በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን

አሰሮ ለሰይጣን  .  . . . . . አግዐዞ ለአዳም

ሰላም  . . . . . . . . . . . . እምይእዜሰ

ኮነ  . . . . . . . . . . . . . .ፍሥሐ ወሰላም

ልጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!

ልጆች! የዛሬውን ጽሑፍ ከላይ ባለው ቃል ለምን  እንደጀመርን ታውቃላችሁ? ከትንሣኤ ጀምሮ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ያሉትን ፶ ቀናት ክርስቲያኖች ሰላምታ የምንለዋወጠው በዚህ መልኩ ስለሆነ ነው። ልጆች እናንተም ሰላምታ ስትለዋወጡ ‹‹ ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን. . . ›› እያላችሁ ሰላምታ መለዋወጥ አለባችሁ።

ልጆች! ባለፈው እትማችን በዐቢይ ጾም ስያሜ ስለተሰጣቸው ስምንቱ ሳምንታት እና ታሪካቸው እንዲሁም ስለ ሰሙነ ሕማማት በተከታታይ ጽፈንላችሁ ነበር አስታወሳችሁ? ጎበዞች! ዛሬ ደግሞ ስለ ትንሣኤ እና ዳግማይ ትንሣኤ ጽፈንላችኋልና ተከታተሉን። 

ትንሣኤ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበረ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። በሰንበት ማታ ለእሑድ አጥቢያ መግደላዊት ማርያም እና ሁለተኛዋ ማርያም እንደ አይሁድ ልማድ የጌታችንን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ወደ መቃብሩ መጥተው ነበረ። ማርያም መግደላዊት እና ሁለተኛዋ ማርያም እየቀረቡ ሲሄዱ የመቃብሩን ድንጋይ ማን ያንከባልልልናል እያሉ እየተነጋገሩ ነበር። 

ከመቃብሩ ሲደርሱ ግን የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆኖ ነበር። መልአኩም ጌታችን ተቀብሮበት የነበረበት መቃብር ላይ ተገጥሞ የነበረውን ድንጋይ አንከባሎ በላዩ ላይ ተቀመጠ። ሴቶቹም ነጭ በረዶ የመሰለ ልብስ የለበሰውንና መልኩ እንደመብረቅ የሆነውን መልአክ ባዩ ጊዜ ፈሩ። መልአኩም ሴቶቹን ‹‹እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና። እንደተናገረ ተነሥቷል ከዚህ የለም፤ እርሱ እንደተናገረ ተነሥቷል ፤ ነገር ግን ኑና ተቀብሮበት የነበረውን ቦታ እዩ. . . ›› አላቸው (ማቴ ፳፰፥፥፬።)

ሴቶቹም ከደስታቸው ብዛት የተነሣ ወደ መቃብሩ ፈጥነው ሄዱ መቃብሩም ባዶ ነበረ መልአኩ እንደነገራቸው ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው ጌታችን መነሣቱን ነገሩአቸው። ከሐዋርያትም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መቃብሩ ሮጠው ሄዱ መቃብሩም ባዶ ነበርና ጌታ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን አረጋገጡ።  

ልጆች! ሴቶቹ ከተመለሱ በኋላ የመቃብሩ ጠባቂዎች ወደ አይሁድ አለቆች ሄደው ክርስቶስ  በመቃብር ውስጥ አለመኖሩን ነገሯቸው ምክንያቱም የካህናት አለቆች የክርስቶስን መቃብር እንዲጠብቁ አዘዋቸው ነበርና እጅግ ደነገጡ። ለጠባቂዎቹም ብዙ ገንዘብ ሰጥተው እንዲዋሹ ነገሩአቸው። ‹‹እኛ ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀው ወሰዱት ብላችሁ በከተማው ውስጥ አውሩ›› (ማቴ. ፳፰፥፲፩—፲፬) አሏቸው። ጠባቂዎችም እንደተነገራቸው በከተማው ውስጥ እየዞሩ ይህን ማውራት ጀመሩ። ልጆች! የካህናት አለቆች ለምን ይህ ያደረጉ ይመስላችኋል? ክርስቶስ በምድር ላይ ተመላልሶ በሚያስተምርበት ጊዜ የካህናት አለቆችና ጻፎች እንደሚይዙት ፣ የሞት ፍርድ እንደሚፈርዱበትና እንደሚሰቅሉት ከተቀበረ በኋላ በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ተናግሮ ነበርና የጌታችንን ትንሣኤ ላለመቀበል እና ተነሣ ብሎ ላለማመን ነው። 

ልጆች! በዚያው ቀን በዕለተ እሑድ ሁለት ሰዎች ኤማሁስ ወደምትባለው መንደር ሲሄዱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸው። እነርሱም የጌታችንን መነሣት ለሐዋርያት ሊናገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ በደረሱም ጊዜ ጌታችንን እንዴት እንዳዩት ፣ ከእነርሱም ጋር ለማዕድ ተቀምጦ እንጀራን ቆርሶ በሰጣቸው ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። ይህንንም እየተነጋገሩ ሳለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ቆሞ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን፤አትፍሩ፤ እኔ ነኝ›› (ሉቃ.፳፬፥፴፮ ) አላቸው። ሐዋርያት ግን እጅግ ፈሩ መንፈስም ያዩ መስሎአቸው ነበር። ጌታችን ግን ‹‹ኑና እዩኝ መንፈስ እንደ እኔ ሥጋና አጥንት የለውም›› በማለት  የተወጉ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። ሐዋርያትም እጅግ ደስ አላቸው። 

ልጆች! ትንሣኤን የምናከብረው ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ስለተነሣ ነው። ይህች ዕለትም ሰንበት ተብላ በክርስቲያኖች ዘንድ ትከበራለች። ምክንያቱም ጌታችን የተነሣባት የከበረች ዕለት ናትና። 

ዳግማይ ትንሣኤ

ዳግማይ ትንሣኤ ማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በስምንተኛው ቀን በዕለተ እሑድ ሐዋርያት በአንድ ቤት ተሰብስበው ሳለ ለሁለተኛ ጊዜ የተገለጠበት ቀን ስለሆነ ነው። ይህ ዕለት ጌታችን የተጠራጠረውን ቶማስን ና ዳሰኝ በማለት እንዲዳስሰው ያደረገበት ዕለት ነው። ልጆች! በመጀመሪያው እሑድ ጌታ ከመቃብር እንደተነሣ ሐዋርያት ወደተሰበሰቡበት ቤት ሲሄድ ቶማስ አልነበረም ተመልሶ ሲመጣ ሐዋርያት ‹‹ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል ብለው በነገሩት ጊዜ አላመናቸውም።ሐዋርያት የነገሩትን ያላመነበት ምክንያትም ቶማስ ከሰዱቃውያን ወገን ስለነበረ ነው። ሰዱቃውያን ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን አያምኑምና (ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ ይነሣል ብለው አያምኑም ነበርና ስለዚህ ነው) ማቴ. ፳፪፥፳፫። ቶማስም ክርስቶስ ተነሣ ሲባል የተጠራጠረው በዚያ ምክንያት ነው። ሐዋርያት በነገሩት ጊዜ ‹‹በዕለተ አርብ በጦር የተወጋ ጎኑን ካላየሁ እጆቼንም በተወጋው ጎኑ ካልከተትኩ አላምንም ›› ብሎ ነበር።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሣ በስምንተኛው ቀን ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት ሲገለጥ ቶማስም እዚያ ነበርና ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ዮሐ.፳፥፳፮ አላቸው። ቶማስንም ጠርቶ ‹‹ ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን›› (ዮሐ.፳፥፳፯) አለው። ቶማስም ጣቶቹን በተበሳው የጌታችን ጎን አስገብቶ ነበር በዚያ ሰዓት እጁ እሳት ውስጥ እንደገባ ጅማት ኩምትር ብላ ስለነበር ‹‹ ጌታዬ አምላኬም›› ዮሐ.፳፥፳፰ ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም ቶማስን ‹‹አንተ ስለአየኸኝ አምነሃል ሳያዩኝ የሚያምኑብኝ ግን ብፁዓን ናቸው›› ብሎታል።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በስምንተኛው ቀን ለደቀ መዛሙርቱ መገለጡ በፊተኛው ትንሣኤ ሲገለጥላቸው ቶማስ ስላልነበር እርሱን ለማሳመን ነው። ሌላው ጌታችን የተነሣባት እለተ እሑድ የከበረች የክርስቲያኖች የዕረፍት ቀን መሆንዋን ሲያጸናላቸው እና እንዲያከብሯት ሊያሣስባቸው ነው። 

ልጆች! ስለትንሣኤ እና ዳግማይ ትንሣኤ ምንነት በመጠኑም ቢሆን ልንገልጽላችሁ ሞክረናል። እናንተም በዓሉን አውቃችሁ በደንብ ልታከብሩት ይገባል። ዳግመኛ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ! መልካም በዓል ይሁንላችሁ! በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ ደኅና ሁኑ እሺ ልጆች!

አገልጋይ ሆይ! ስንት ቋንቋ ታውቃለህ?

Details
Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1207
  • ትዝብት

ክርስትና ለመላው ዓለም ሕዝብ መንፈሳዊ ነጻነት እንዲሰጥ የተሰጠን የእውነት መንገድ መሆኑን አብ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ በገለጠው ፍቅር የታወቀ ነው። በዚህም መሠረት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ፣ መልእክተኛ አድርጎ የመረጣቸውን ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።›› (ማቴ. ፳፰፥ ፲፱) በማለት አዟቸዋል። 

የዓለም ሕዝቦች ደግሞ ልዩ ልዩ ቋንቋና ባህል ያላቸው በብዙ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው። እንኳን በዓለም በአንድ ሀገር እንኳን ብዙ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ማኅበረሰቦች ይኖራሉ። ለዚህም ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ምሳሌ ነች።

የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ለእነዚህ ብዙ ሕዝቦች መድረስ ስላለበት አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የዓለም ሕዝቦችን ቋንቋ ገልጦላቸዋል። በኢየሩሳሌም የነበሩ ከተለያዩ ግዛቶች የመጡ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦‹‹ እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?›› (የሐዋ. ፪፥ ፮—፯)

ይህ የሚያመለክተው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የወንጌል መልእክተኞች ለሁሉም የተላኩና የሁሉም አገልጋይ ስለሆኑ የሚያገልግሏቸውን የየሀገሩን ሕዝቦችና የሀገራቸውን የተለያዩ ማኅበረሰቦች ቋንቋና ባህል ማወቅ እንደሚገባቸው ነው። የጥንት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አብዛኞቹ ከአንድ በላይ ቋንቋ የሚያውቁና በሚያውቁትም ቋንቋ በቃል በማስተማር፣ መጻሕፍትን በመጻፍ፤ መጻሕፍትን በመተርጎም በርካታ አገልግሎት ሰጥተዋል። 

በኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክም እነ ቅዱስ ፍሬምናጦስ ግዕዝን ጽርዕን ሱርስትን በማወቃቸው ወደ ግእዝ ተርጉመው ለማስተማር፣ ሥርዓትን በውል ለመሥራት የአብያተ ክርስቲያናትን ግንኙነት ለማጠናከር አውለውታል። አባ ሰላማ መተርጉምም ስሙን የተላበሰበትን ድንቅ ሥራ የሠራው ከአረብኛ በርካታ መጻሕፍትን በመተርጎሙ ነበር። እጨጌ ዕንባቆም ከአረብኛ ግእዝን በማወቃቸው መጻሕፍትን ለማስተማሪያነት ጽፈዋል። እነዚህና መሰል ምስጉን ሰዎች እውነተኛ አገልጋዮችና የፍቅር ሰዎች በመሆናቸው ለብዙ ወገኖች የሚጠቅሙ ትምህርቶችን በተሰጣቸው የቋንቋ ጸጋና ክህሎት ሰጥተዋል።

በአሁን ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቋንቋ ጉዳይ መነጋገሪያና መጨቃጨቂያ ሆኖ ሲታይባት ነገሩን በትዝብት የሚያዩ ቁጥራቸው ቀላል አይሆንም። ቤተ ክርስቲያን በውጪ ሀገር ለሚኖሩ በርካታ አፍሪካውያንንና በሌላም አህጉር ለሚኖሩ አገልግሎቷን ለሚፈልጉ ወገኖች አገልግሎት በስፋት መስጠት ነበረባት። ቤተ ክርስቲያን እኅትነቷን ከሚፈልጉ አኃት አብያተ ክርስቲያናትና ጥንታውያን የኦርቶዶክስነት መሠረት ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር ኢኪዩሜኒዝም ወይም ዓለም ዓቀፋዊ ግንኙነትን ማጠናከር ይጠበቅባት ነበር። የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪኳን አስተምህሮዋን ትውፊቷን ልዩ ልዩ የሃይማኖት ሥርዓቶቿን ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማስተዋወቅ፣ ላላመኑት መንገር ማሳመን ነበረባት። ቤተ ክርስቲያን ከውጪ ያልተተረጎሙ በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ የምእመናንን ሕይወት የሚያንጹ፣ በሃይማኖት የሚያጸኑ መጻሕፍትን ተርጉማ ማቅረብ ነበረባት። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጪ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥም ላሉ ላመኑና ለላመኑ ማኅበረሰቦች በየቋንቋቸው አግልግሎት መስጠት፣ መገልገያ መጻሕፍትን በየቋንቋቸው ተርጉማ ማቅረብ ነበረባት። 

እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ግን እስከ አሁን ድረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ የቋንቋዎች ማሰልጠኛ ተቋም የለም። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ቋንቋና ባህሎች የሚጠኑበት ተቋም የለም። ይህ ባለመኖሩ ደግሞ አገልጋይ ደቀ መዛሙርት ከአንድ በላይ ሁለት ሦስት ቋንቋዎችን በማወቅ በበቂ ሁኔታ በዓለምና በሀገር ውስጥ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ተዘዋውረው ማስተማር፣ መጻሐፍትን ጽፈው ማቅረብ አልቻሉም። ቤተ ክርስቲያን በቅርሶቿ ኢትዮጵያን እንደምታኮራ ሁሉ የብዙ ቋንቋዎች ባለቤት ሆና እንደ መጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን የብዙ ቋንቋና ባህል ማኅደር ሆና መቀጠል አልቻለችም።  

ቤተ ክርስቲያን ግዕዝና አማርኛን በማሳደግና በማስፋፋት ሚና እንዳላት ሁሉ አሁንም በርካታ የውጪና የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በማስፋፋት ዓለም ዓቀፋዊት ባሕርይዋን ተላብሳ መገኘት ግዴታዋ ነው፡ በተለይ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ቢያንስ አረብኛ ቋንቋን ሱርስትን የሚያውቁ በርከት ያሉ ሊቃውንት ሊኖሯት ይገባል። የጥንት ኦርቶዶክሳውያንን መጻሕፍት ለመመርመርና ታሪካቸውን ለማጥናት የግሪክና የራሺያኛ ቋንቋ የሚያውቁ በርካታ ሊቃውንት ሊኖሯት ይገባል። 

ስብከተ ወንጌልን ለዓለም ለማድረስና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ማንነት ለዓለም ለመግለጥ ደግሞ ቢያንስ የእንግሊዝኛና፣ የፈርንሳይኛ ቋንቋዎችን ያጠኑ አገልጋዮች በስፋት መበራከት ይኖርባቸው ነበር። በሀገር ውስጥ ቋንቋዎቹን የሚናገሩ አማኝ ክርስቲያኖች በርካታ ቢኖሩም አገልጋዮች ግን ከግእዝና አማርኛ በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ሁለትም ሦስትም ደርበው በመያዝ ሐዋርያዊ ወግ መላበስ ነበረባቸው።  

አሁን በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያን ያሏት አግልጋዮች ቢኖሩ እንኳን ጥቂቶችና በራሳቸው ጥረት አቅም የፈጠሩ፣ ጸጋን የተላበሱ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ግን ይህን አገልግሎት ተቋማዊ አድርጋ በመያዝ በትኩረት ልትሠራበት ይገባል። በመንፈሳዊ ኮሌጆችና የካህናት ማሠልጠኛዎች ቋንቋ ትምህርት ማጥናትና ማበልጸጊያ ክፍሎችም ኖረው በውል ሊሠራባቸው ይገባል። ይህ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ለኦርቶዶክሳዊ አገልግሎት አምባሳደሮች ከመሆን አልፈው ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ክብርና አግልግሎትም አስተዋጽኦ እስከማበርክት ይደርሳሉ። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ በቁጭት መሥራትና ከችግር መውጣት ያስፈልጋል እንላለን።

‹‹በተደጋጋሚ በሕልሜ ዝሙት ስፈጽም አድራለሁ እንደ ኃጢአት ይቆጠርብኝ ይሆን?››

Details
Written by: በዝግጅት ክፍሉ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 7512
  • ምሥጢሬን ላካፍላችሁ

የተወደዳችሁ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደምን አላችሁ? አሜን የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን። የክርስትና ስሜ ወልደ ሚካኤል ይባላል። የምኖረው ጎባ ከተማ ነው። በሞያዬ መምህርና የ፴፪ ዓመት ወጣት ነኝ። ትዳር አልያዝኩም፣ እጮኛም የለኝም የምኖረውም ብቻዬን ነው። ጠንካራ ክርስቲያን ባልሆንም አልፎ አልፎ በሰንበት ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እሳለማለሁ እጸልያለሁ። 

ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! በተደጋጋሚ የማየው አጸያፊ ሕልም እየረበሸኝ ተቸግሬአለሁ። እሱም ተኝቼ ሳለ በሕልሜ ዝሙትን ስፈጽም አያለሁ። ዝሙትን የምፈጽመው ከተለያዩ ሰዎች ጋር ነው አንዳንዶቹን አውቃቸዋለሁ አንዳንዱቹን በመልክም በስምም የማላውቃቸው ናቸው። በሕልሜ ዝሙት ከፈጸምኩ በኋላ በእውን ያደረኩት ይመስለኝና ደንግጬ እነሣለሁ። በዚያ ሰዓት የዘር ፈሳሽ በሰውነቴ በልብሴ ላይ አገኛለሁ። በማግሥቱ ከሰው ጋር መገናኘት ያስጠላኛል ቤተ ክርስቲያን መሄድ እስኪያስፈራኝ ድረስ ራሴንም እንደርኩስ፣ እንደተረገመ ሰው እቆጥራለሁ።  ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! ይህ ለብዙ ጊዜ የተቸገርኩበት የኔ ምሥጢር ነው። ለሰው ለምቀርባቸው ጓደኞቼ እንኳ ለማማከር እፈልግና ፍርሃት እና ይሉኝታ ይይዘኛል። በዚህም እጅግ ተቸግሬአለሁ። እናንተ ለብዙዎቹ ጥያቄዎች እና ቸግሮች መልስ እንዲሁም መፍትሔ ስትሰጡ አያለሁና የኔንም ጥያቄ ትመልሱልኛላችሁ ብዬ በማመን በውስጤ ይዠየው የቆየሁትን ምሥጢር ወደ እናንተ ለመጻፍ ተገደድኩ። እባካችሁ ከችግሬ የምላቀቅበትን መፍትሔ ጠቁሙኝ። ለመሆኑ በሕልሜ ዝሙት መፈጸሜ ኃጢአት ይሆንብኝ ይሆን?     

ውድ ጠያቂያችን ወልደ ሚካኤል በቅድሚያ በሕይወትህ የተቸገርክበትን ጉዳይ ደብቀህ ብቻህን ከመብሰልሰልና ከመጨነቅ  ይልቅ መፍትሔ አገኛለሁ ብለህ ልታካፍለን ወደ እኛ በመጻፍህ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግንሃለን። በመቀጠል እንዲህ ዓይነት ገጠመኞች ያንተ ብቻ ሳይሆኑ በብዙ ሰዎች ወንዶች እና ሴቶች ላይ የሚከሰቱ ነገሮች ናቸውና አብዝተህ ልትጨነቅ አይገባህም። 

በተደጋጋሚ የምታየው ሕልም ኃጢአት ነው ኃጢአት አይደለም የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ከምንነቱ መነሳት አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነት ሕልሞች ‹‹ ሕልመ ሌሊት›› በመባል ይታወቃሉ። ሕልመ ሌሊት ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ሰዎች በሚተኙበት እና በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ በሚሆኑበት ሰዓት ክፉ ክፉ ሕልሞችን በማሳየት ይፈታተናቸዋል። ከነዚህ ክፉ ክፉ ሕልሞች መካከል አንደኛው የሴትን ወይም የወንድን ገላ በማሳየት አሊያም ወንድና ሴት ተራክቦ ሲፈጽሙ በማሳየት ሰውየውን ወይም ሴትየዋን ለዚህ ዓይነት እኩይ ሐሳብ እንዲገዙ ያደርጓቸዋል፡ ይህ ሰው ባየው ወይም ይህች ሴት ባየችው  ሕልም ይሳቡና በሕልማቸው ዝሙት ሲፈጽሙ ያድራሉ። 

እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ጸዋግ(ኅሡም) በመባል ይታወቃል። ይህም ማለት በሌላ አነጋገር ክፉ ሕልም ማለት ነው። በመጽሐፈ መነኰሳት ላይ ‹‹ሰይጣናት የሰውን ልጅ ቀን ቀን ክፉ ሐሳብ በማሳሰብና በማሠራት በሌሊት ደግሞ ዝሙት የሞላበት አጸያፊ ሕልም ያሳዩታል›› በማለት ሰይጣን ምን ያህል የሰውን ልጅ አእምሮ በመቆጣጠር በሕልሙ ሳይቀር አጸያፊ ሕልም በማሳየት እንዴት እንደሚዋጋ በዚህ መረዳት እንችላለን። 

እንዲህ ዓይነቱ የሰይጣን ፈተና ወይም ድርጊት ወንዱን ወይም ሴትዋን ለሕልመ ሌሊት ወይንም ለዝንየት አሳልፎ ይሰጣል። ‹‹ሕልመ ሌሊት(ዝንየት) አንድ ወንድ ወይም ሴት እንደ ገሀዱ ዓለም በሚመስል ሩካቤ ከሰውነት ፈሳሽ የሚወጣበት ሂደት ነው። በመሆኑም ሕልመ ሌሊት ወይም ዝንየት ጾታ ሳይለይ በሁለቱም ላይ የሚከሰት ነው። ውድ ወንድማችን እንደነገርከን እኛም እንደተረዳንህ አንተም በነዚህ ሂደቶች ውስጥ እንደምታልፍ ነው። በመጀመሪያ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ዝሙትን ስትፈጽም ታያለህ ቀጥሎ ሕልመ ሌሊት(ዝንየት) ይመታሃል። ይህ ዋናው መገለጫ ነውና።  

ሕልመ ሌሊት በተለያዩ መንገዶች ሊከሠት ወይም ሊመጣብን ይችላል። ከነዚያም መካከል አንዱ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው በጥንተ ጠላታችን በሰይጣን አማካኝነት ሌት በተኛንበት በምትሐት የማይገባ ነገር በማሳየት እና እኛም በስሜት ወደዚያ እንድንገባ በማድረግ በሕልማችን ሩካቤን እንድናደርግ በመገፋፋት ነው። ሁለተኛው የዝሙት መንፈስ ያለባቸው ሰዎች ለዚህ ኃጢአት በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው። ይህም ማለት አንድ ሰው በአእምሮው ስለዝሙት የሚያስብ በልቡናው የሚያመላልስ ከሆነ በሕልሙ ከመፈጸም አልፎ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ሊፈትነው ይችላል።  እንዲህ ዓይነቱ የዝሙት መንፈስ በአብዛኛው የሚታየው ያላገቡ እና ወጣቶች ላይ ሲሆን አልፎ አልፎ ያገቡ ሰዎችም ላይ ይከሠታል።

ውድ ወንድማችን! ሰዎች በጠለቀ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው የሚከሠት በሕልም ዝሙት መፈጸም(ሩካቤ መፈጸም) እንደ ኃጢአት እንዲቆጠርና እንዳይቆጠር የሚያደርጉ የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ:: ስለዚህ በደፈናው ሕልመ ሌሊትን ኃጢአት ነው ወይም አይደለም ማለት አይቻልም:: ነገር ግን እንደ ኃጢአት እንዲቆጠር የሚያደርጉ ሁኔታዎች አሉ እነሱም፦

- የሰው ልጅ አጋንንት የሚያቀርቡለትን እንዲህ ዓይነቱን ፈተና ደስ እያለው ሲቀበል

- ወደ ዝሙት የሚያመሩ ማንኛውንም ነገሮች ሲጠቀም ለምሳሌ ከዝሙት ጋር የተያያዙ  መጻሕፍትን፣ መጽሔት ጋዜጣ ሲያነብ አሊያም ከዚህ ዓይነት ነገር ጋር የተያያዙ ፊልሞችን ሲያይ . . . ወዘተ

- ወደ ዝሙት የሚገፋፉ ነገሮችን ከመቃወም ይልቅ ሲቀበል 

- ኃጢአትን እንደ ኃጢአት ቆጥሮ ሳይናዘዝባት ሲቀር  

- ስለ ተቃራኒ ጾታ አብዝቶ ሲመኝ እና በዚያ መንገድ ሲመጣ እንዲሁም

- ማር ይስሐቅ በአንቀጽ ፳ ምዕራፍ ፩ ላይ ‹‹በኃይል አብዝቶ መመገብ ከወጣትነት ኃጢአት ጋር ተያይዞ ሐሳብን በግድ እንዲያመጣ ያደርጋሉ›› እንዲል አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት ሕልመ ሌሊት ያየ ሰው 

- በማር ይስሐቅ አንቀጽ ፳ ምዕራፍ ፪ ላይ ‹‹ ከሰውነቱ ምንጭ የሚነቃ ርኩስ ዘር በዝቶ ሳለ የፈሰሰ ጎስቋላ ምንጣፉ፣ ልብሱ፣ ደስ የተሰኘ ሥጋው ሁለንተናው የረከሰ ነው። ሥጋ ሁል ጊዜ ያነቃዋልና ዘር የሚፈሰው በሌሊት ብቻ አይደለም ። ሕሊናውንም ያረክሰዋል። ›› ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ እና ከላይ በተዘረዘሩ ምክንያቶች ሁሉ ኃጢአት ይሆንበታል ማለት ነው። 

ነገር ግን አንድ ሰው በንቁ ልቡናውእያለ በቀን የሚመጡበትን ኃጢአት እየተቃወመ ሳለ በተኛ ጊዜ ሆኖ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት ቢያገኘው) በሕልሙ የፈጸመው ወይም ሕልመ ሌሊቱ ኃጢአት አይሆንበትም።

ውድ ወንድማችን ሕልመ ሌሊት(ዝንየት) ያገኘው ሰው ኃጢአት የሚሆንበት እና የማይሆንበት ምክንያት እንዳለ ሆኖ በቤተ ክርስቲያ ሥርዓት ፦

- ሕልመ ሌሊት ያገኘው ሰው በዕለቱ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል አይችልም፣ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ይከለከላል (መግባት ካለበት እንኳ ልብሱን እና ገላውን ታጥቦ በማግስቱ ነው)፣  በመኝታ ወቅት ሕልመ ሌሊት ሊከሰት ስለሚችል በቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ መተኛት አይቻልም፣ ወደ ቤተ መቅደስ ፈጽሞ መግባት ባይቻልምመላ ሰውነትንና ልብስን ካጠቡ በኋላ በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ቅጽር በመግባት መጸለይ፣ ትምህርት መማር ጉባኤ መካፈል የተፈቀደ ነው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ገጽ ፻፳፬።

ሌላው በሕልም ከሚደረጉ እኩይ ነገሮች ለመራቅ ሕልሙን ደስ እየተሰኙ አለማሰብ፣‹‹ ሌሊት በሕልም ከሴት ጋር የተገናኘህ መስሎህ ዘር ቢወርድህ በመዓልት አታስባት›› እንዲል መጽሐፈ መነኰሳት ለሌሊት ሕልም የጋበዘህን እኩይ ሐሳብ በቀን መቃወም ተገቢ ነው። ሕልመ ሌሊት በሚታይበት ጊዜ ቸል ብሎ ከመተኛት ተነስቶ ተጣጥቦ መጸለይ ቢቻል መስገድ ጾርን ያጠፋል። እንዲሁም በመኝታ ሰዓት ምግብ አብዝቶ አለመብላትና ውሃን አብዝቶ አለመጠጣት ከእንዲህ ዓይነቱ ፈተና ይታደጋልና ተግባራዊ ማድረጉ ጠቃሚ ነው።

ውድ ወንድማችን ወልደ ሚካኤል ከላይ በመግቢያው ላይ በዝርዝር ልትገልጽልን እንደሞከርከው እንዲህ ዓይነቱ መጥፎ ድርጊት እንደገጠመህ እንጂ በምን ምክንያት እንዳገኘህ አልገለጥክልንም። ከላይ ያነሳኸው ማብራሪያ እንዳለ ሆኖ ወደ አንተ ስንመጣ በሕልምህ ዝሙት ስትሠራ ማየትህና በሕልመ ሌሊት መመታትህ ቀን ወይም በማንኛው ሰዓት ስለ ዝሙት ወይም ስለተቃራኒ ጾታ አብዝተህ በማሰብ ፣ የተለያዩ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ መጽሐፍ፣ መጽሔት አሊያም ጋዜጣ በማንበብ፣ እንዲሁም ፊልሞችን በማየት ምክንያት ከሆነ ይህ የመጣብህ ጦር ኃጢአት ነውና ንስሓ ልትገባ ይገባል። 

ከእንዲህ ዓይነቱ ፈተና ለመሸሽ ወይም ለመራቅ እኩይ የሆኑ የዝሙት ሐሳቦች ከመጡብህ በተቻለ መጠን በጾም በጸሎት በስግደት ከውስጥህ ልታስወግዳቸው እንዲሁም አጥብቀህ ልትቃወማቸው ይገባል። ምክንያቱም በንቁ ልቡናህ ቀን አጥብቀህ ከተቃወምከው እና ከልብህ አውጥተህ ከሰደድከው ሌሊት በሕልም ወደ አንተ ተመልሶ አይመጣምና ነው።

በእርግጥ ዘር ፍሰት (ሕልመ ሌሊት) ማየት የአፍላ ጉልምስና ከሆኑት ምልክቶች አንዱ ሲሆን ሰዎች በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው ሕልመ ሌሊት ወይም ዝንየት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ለዘር የበቁ ወጣቶች ተኝተው ሳለ በጠለቀ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው ሕልም በሚያልሙበት ወቅት ይታያቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሕልም ‹‹ ሕልመ ጽምረት(የመስቆርርት ሕልም) ይባላል። ሕልሙን ያየ ሰውም ዝንየት አገነኝ (ሕልመ ሌሊት መታኝ) ይላል። 

ውድ ወንድማችን ምንም ዓይነት እኩይ የዝሙት ሐሳብ በውስጥ ሳይኖር እንዲህ ዓይነት ዝንየት ሲያገኝህ ተነሥተህ መላ አካልህን በመታጠብ ጸሎት ማድረስ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳትገባ በርቀት ሁነህ ሄደህ መጸለይ፣እንዲሁም መስገድ፣ በጉባኤ ሰዓት ጉባኤ መካፈል ትችላለህ። ነገር ግን ዝንየት ባገኘህ ቀን ጸበል መጠጣት ቅዱስ ቁርባን መቀበል አትችልም። በአጠቃላይ ከእንዲህ ዓይነቱ ጾር ለመሸሽ አብዝቶ መጸለይ ፣ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መስገድ፣ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ፊልሞችን አለማየት፣ ጋዜጣና መጽሔቶችን አለማንበብ እንዲሁም የምንወስደውን ምግብ እና መጠጥ በመጠኑ ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚህም ባሻገር ከንስሓ አባትህ ጋር መመካከር ሌላውና ትልቁ መፍትሔም ነው። ውድ ወንድማችን ወልደ ሚካኤል ከላይ ከሰጠንህ ምክር በላይ ደግሞ እግዚአብሔር አምላክ ከዚህ ጾር ያወጣህ ዘንድ ጸሎታችን ነው እግዚአብሔር ይርዳህ።

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ መንግሥታዊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1418
  • አጫጭር ዜናዎች
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ መንግሥታዊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ላይ የተቀናጀና የታቀደ መንግሥታዊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን ግንቦት ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች የመንግሥት መዋቅርን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንን በልዩ ልዩ መንገድ ሲያጠቋትና ክርስቲያኖችን ሲገድሉ፤ ሲያሳድዱና ሲያፈናቅሉ እንደነበር ማኅበሩ ገልጦ በዚህ ሁኔታ ላይ ለጠፋው ጥፋት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ ሳይጠይቅ መቆየቱ እንዳሳዘነው ገልጧል። 

“በቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ይዞታዎች ላይ አንዳንድ አካላት ያለ አግባብ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መንግሥት መልስ ለመስጠት የሚያሳየው ቁርጠኝነትና በሌሎች ቤተ እምነቶች ላይ ላልተከሠቱ ችግሮችም እንደተከሠቱ አድርጎ ይቅርታ ሲጠይቅ ይስተዋላል” ያለው ማኅበሩ ይህ ድርጊቱም በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው የተቀናጀ ጥቃት በመንግሥት በኩል የሚፈጸም ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረጉንም አንሥቷል። 

መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲወስን የቤተ ክርስቲያንን መብት በመጋፋትና ፍትሕን በማዛባት ሳይሆን በዕውቀትና በሕግ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ያሳሰበው ማኅበሩ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በሀገሪቱ ለሚደርሰው የሰላም መደፍረስ ችግር ኃላፊነቱን ሊወስድ እንደሚገባው  አሳስቧል። 

በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ችግር ውስጥ መውደቋን ምእመናን በትክክል እንዲረዱ ያስገነዘበው ማኅበሩ ቀደምት አባቶቻችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ስደት የተቀበሉበትን መንገድ ለመከተል መዘጋጀት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርቧል።   

ሀገርና ሰላም ወዳድ ኢትዮጵውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን የተቀናጀና የተደራጀ መገፋትና ስደት በመረዳት ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንዲቆሙና የበኩላቸውን እንዲያደርጉም ማኅበሩ ጠይቋል።

ቤተ ክርስቲያን የዴር ሱልጣን ገዳምን ከወረራ የታደጉ አካላትን አመሰገነች

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1147
  • አጫጭር ዜናዎች

በሰሙነ ሕማማትና በትንሣኤ በዓል ወቅት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ላይ የግብፅ መነኮሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ያደረጉትን ወረራ የታደጉ አካላትን በመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት ሚያዚያ ፳፰ቀን  ፳፻፲፫ ዓ.ም በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ቤተ ክርስቲያን አመሰገነች። 

በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኘው ጥንታዊውና ታሪካዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ የሆነው የዴር ሱልጣን ገዳም ላይ ግብጻውያን አሁን 

ድረስ ያለማቋረጥ  በሚፈጥሩት ትንኮሳና ግጭት የቤተ ክርስቲያንን የባለቤትነት መብት ለመንጠቅ በሚያደርጉት 

ጥረት በተረጋጋ ሁኔታ ገዳሙን ለማስተዳደርና ለማልማት እዳልተቻለ መግለጫው አስገንዝቧል። 

በየዓመቱ የትንሣኤ በዓልን ለማክበር ዝግጅት በሚደረግበት ወቅትና በበዓላት አከባበር ላይ ግብጻውያኑ የሚፈጥሩት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የጠቀሰው መግለጫው በዚህ ዓመትም በበዓለ ትንሣኤ አከባበር ላይ በተደራጀና በተጠና መልኩ በቤተ ክርስቲያን ይዞታ ላይ ግልጽ የሆነ ወረራ ከመፈጸማቸው ባሻገር በአባቶች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም ድብደባ መፈፀማቸው ተመላክቷል። 

ችግሩ ከተፈጠረ ጀምሮ በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለ ሙሉ ሥልጣን ክቡር አምባሳደር ረታ ዓለሙ፣ መንበረ ጵጵስናው፣ የገዳሙ መነኰሳትና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የእስራኤል የሀገር ውሰጥ የደኅንነት ምክትል ሚኒስቴር አቶ ጋዲ ይቫርከን እገዛ አድርገዋል። የሕግ የበላይነትን በማስከበርና ግብጻውያኑን በፖሊስ ከአካባቢው በማወስጣት ችግሩ በቁጥጥር ሥር ውሎ የትንሣኤ በዓል በሰላም መከበር እንደቻለ በመግለጫው ተገልጧል። 

በተለይ በወቅቱ የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆምና የገዳሙ ዋና መጋቢ አባ ዘበአማን ሳሙኤል ከአበው መነኮሳት ጋር በጋራ ባሰሙት ጥሪ ችግሩን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደተቻለ ያስረዳው መግለጫው የኢስራኤል የሀገር ውስጥ ምክትል የደኅንነት ሚኒስቴር አቶ ጋዲ ይቫርከን ግብጻውያን የወረሩትን የገዳሙ ክፍል ቶሎ ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸው በመግለጫው ተጠቅሷል። 

በገዳሙ የተፈጠረውን ችግር ቶሎ በቁጥጥር ሥር በማዋልና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይዞታ በማስጠበቅ የትንሣኤ በዓል በሰላም እንዲከበር ላደረጉ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ መነኮሳት፣ የእስራኤል የሀገር ውሰጥ የደኅንነት ምክትል ሚኒስቴር አቶ ጋዲ ይቫርከን፣ በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ክቡር አቶ ረታ ዓለሙ እንዲሁም በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመግለጫው ምስጋና ቀርቦላቸዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት የቤተ ክርስቲያን ይዞታ እንዲከበር ከእስራኤል መንግሥት ጋር በጋራ እንዲሠራ፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  በጋራ ጫና እንዲፈጥሩና የሃይማኖት ወገኖቻችን የሆኑት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከጥፋት ተግባራቸው በመቆጠብ ለዘመናት የቆየውን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትስስር እንዳይሸረሸር ማድረግ እንደሚገባቸው በመግለጫው ጥሪ ቀርቧል።   

 

የዴር ሡልጣን ገዳም የነገ ዕጣ ፈንታ

Details
Written by: በዝግጅት ክፍሉ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1239
  • ርዕሰ አንቀጽ

ከ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በገዳምነት ይጠቀሙበትና ይኖሩበት  እንደነበረ የሚጠቀስለት የዴር ሡልጣን ገዳም በተለያየ ጊዜ በተለያዩ አካላት የባለቤትነት ጥያቄ ሲነሣበት መቆየቱ ይታወቃል። በተለይ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት እና  በተለያየ መንገድ አዲስ ታሪክ በመፍጠር ገዳሙን ለመንጠቅ ሙከራ ስታደርግ መቆየትዋን ጭምር ማኅበረ ቅዱሳን በ፳፻፲፩ ዓ.ም ባሳተመው ‹‹ስምዐ ተዋሕዶ›› ልዩ ዕትም መጽሐየት ስለ ዴር ሡልጣን የተለያዩ ሊቃውንትንና የታሪክ ድርሳናትን ዋቢ በማድረግ ጽፎት እናገኛለን። 

በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ጌታ በተወለደበት፣ በአደገበት፣ በአስተማረበት፣ በተሰቀለበት፣ በተቀበረበት እንዲሁም በተነሣበት በጎልጎታ ተራራ የተመሠረተው የዴር ሡልጣን ገዳም በኢትዮጵያውያን ነገሥታት፣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ባለሀብቶች እና መነኰሳት እንደተሠራ የታሪክ መዛግብት የሚናገሩ ሲሆን  እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ገዳሙን እና በገዳሙ የሚኖሩ ኢትዮጵያን መነኰሳት ሲረዱ መኖራቸው ይታወቃል። ገዳሙ ከንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ርስት ሆኖ መቆየቱ ሲገለገሉበት መቆየታቸው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ‹‹ዜና ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም›› በሚለው መጽሐፋቸው ተገልጾ እናገኛለን። በዘመን ብዛት እና በተለያዩ ሁኔታዎች ግብፅን የመሳሰሉ ‹‹የእኔ ነው›› ባዮችን አፍርቶ እስከ ዛሬ ድረስ መፍትሔ ያልተበጀለት የውዝግብ ምክንያት ሲሆን መቆየቱን ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ‹‹ ኢየሩሳሌምን እወቁ›› በሚለው ሌላኛው መጽሐፋቸው ላይ ጽፈውት እናገኛለን። 

ገዳሙ የውዝግብ መነሻ ከመሆኑም ባሻገር ከዘመን ብዛት የተነሣ በማርጀቱ በመፈራረስ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተጨማሪም ለዘመናት በውስጡ የሚኖሩ የበላይ ጠባቂ አባቶች ካህናትና መነኰሳት የሚገባቸው እንክብካቤ እየተደረገላቸው አለመሆኑ . . . ወዘተ ለገዳሙ የዘመናት ተድዳሮት ሆነው ቆይተዋል። እነዚህንና የመሳሰሉ ችግሮችን እያስተናገደች ያለችው የገዳሙ ባለቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳሙን ማደስ እንኳን በማትችልበት መልኩ  መብቷን ተነፍጋ ቆይታለች። 

በመሠረቱ የዴር ሡልጣን ገዳም ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርስ እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስም ጭምር ነው። ኢትዮጵያ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዚህ ታላቅ ቅርስ ባለቤት መሆናቸው በዓለም ላይ ታላቅ ክብር የሚያሠጣቸው ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት፣ በተቀበረበት እና በተነሣበት ታሪካዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ ኢትዮጵያውያን አስበው እና አስቀድመው ገዳም መመሥረታቸው በዚያ ዘመን የበረውን የኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ሥልጣኔ፣ ብልህነት እና አርቆ አስተዋይነት የሚገለጽበት ቋሚ ምስክር ጭምርም ነው የዴር ሡልጣን ገዳም። 

ሆኖም እንደ ታሪካዊ አመጣጡ፣ እንደ ባለቤትነታችን ለዴር ሡልጣን ገዳም እየሰጠነው ያለው ትኩረት በጣም አናሳ ነው። ግብፃውያኑ ያልነበሩበትን ያልኖሩበትን ይህን የተቀደሰ ቦታ ቀምቶ ለመውሰድ ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ተራው ሕዝብ ድረስ ዓላማ አድርገው ሲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እንደሚገባው ይዞታውን ለማስከበር ብዙ ርቀት ሲሄዱ አልታዩም። ባለቤት ሆነው የማያውቁ፣ በታሪክ ያልነበሩ በጉልበት የራሳቸው ለማድረግ አዲስ ታሪክ ለመፍጠር ሲሯሯጡ ኢትዮጵያውያን ዝም ብለው መመልከት የለባቸውም። ይልቁንም ስለ ዴር ሡልጣን የሚናገሩትን የታሪክ ድርሳናት ወደ ፊት በማምጣት የገዳሙ ባለቤት መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። 

ከጥቁር ሕዝቦች መካከል ተለይታ በሀገረ በእስራኤል በተቀደሰችው ከተማ በኢየሩሳሌም የገዳማት ይዞታዎች ያሏት ኢትዮጵያ መሪዎቿ እንደ ሀገር ከፊት ቀድመው ይዞታዋን በማስከበር ረገድ ከአቻቸው የእስራኤል መንግሥት  ጋር በመነጋገር ዘመናት ለቆየው ችግር እልባት ሊሰጡት ይገባል። ምክንያቱም ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የሀገርም ቅርስ ነውና መንግሥት እንደ መንግሥት ሊያስብበት ይገባል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበላይ አካላት የሆኑት ቅዱስ ሲኖዶስና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስለ ዴር ሡልጣን የተጻፉ የታሪክ መዛግብትን አደራጅተው በማቅረብ የገዳሙን ታሪካዊ ባለቤትነት ማረጋገጥ ከእነርሱ ይጠበቃል። ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም የሚያትቱ በርካታ የታሪክ ድርሳናት ከኢትዮጵያውያን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽፈዋልና እነዚያን ታሪካዊ ድርሳናት በማስረጃነት በማቅረብ እስከ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ድረስ በመሞገት የባለቤትነት መብትን ማስከበር ተገቢ ነው። 

በገዳሙ የሚኖሩ መነኮሳት እና በየጊዜው ለገዳሙ የሚመደቡ የበላይ አባቶች በሚነሣው ውዝግብ ውስጥ የገዳሙን ባለቤትነት ለማረጋገጥ ብዙ መንገድ መሄዳቸው ቢታወቅም ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከቤተ ክህነቱ የሚሰጧቸው ድጋፎች አናሳ በመሆናቸው ችግሩ ዘላቂ እልባት ማግኘት አልቻለም። በመሆኑም መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኅብረት የዴር ሡልጣንን የባለቤትነት መብት ከዳር ሊያደርሱት ይገባል። 

በአሁኑ ሰዓት በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለ ሙሉ ሥልጣን ክቡር አምባሳደር ረታ ዓለሙ የገዳሙ የበላይ አባቶችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያሉትን ጥረት ከማመስገን ባሻገር ከጎን በመሆን ጭምር መንግሥት እንደ መንግሥት ከአቻው የእስራኤል መንግሥት ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአቻ አኃት አብያተ ክርስቲያናት በተለይም ከግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ውይይት በማድረግ ለዘመናት የዘለቀውን ችግር ለዘመናት መፍታት ይጠበቅባቸዋል። 

ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለመሳለም በየጊዜው የሚሄዱ በሀገር ውስጥ ያሉም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በበኩላቸው  በግብፃውያን ለመነጠቅ ጫፍ ላይ የደረሰውን የዴር ሡልጣን ገዳም ጉዳይ እልባት ያገኝ ዘንድ ድምጻቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሰማት ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ከቤተ ክህነት የበላይ አባቶች ጋር በመነጋገር ከገዳሙ ጋር ተጣብቀው በየጊዜው ከግብፃያን የሚደርስባቸውን ትንኮሳና ጫና ተቋቁመው ያሉ በኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን ገዳም አባቶችን በሞራልም ሆነ በገንዘብ መደገፍ ተገቢ ነው።

የዓለም ማዕከላዊ ቦታ በሆነቸው በኢየሩሳሌም የሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም የኢትዮጵያውያን ቅርስ ነውና ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ቅርስነት ተመልክተው ከቤተ ክርስቲያን ጎን ሊቆሙ ይገባል።  በተለይ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በግልና በኅብረት በመሆን የገዳማችን ባለቤትነት ይረጋገጥ ዘንድ  በቤተ ክህነቱም ሆነ በመንግሥት ላይ ጫና ሊያደርጉ ይገባል። በየጊዜው የሚነሣው የግብፃውያን ትንኮሳ እና ‹‹የእኔ ነው›› ባይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቆም ዘንድ ያዝ ለቀቅ በሆነ መልኩ ሳይሆን በሀገር ውስጥም ሆነ በተለያየ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም፣ የሕግ ሰዎችን በአማካሪነት በመያዝ እና ታሪካዊ ሰነዶችን በመረጃነት በማቅረብ የዴር ሡልጣንን የባለቤትነት ጥያቄ ለዘለቄታው ካልተመለሰ የነገ ዕጣ ፈንታው እጅግ አሳሳቢ ይሆናል።

 

‹‹መመሪያውን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ማኅበሩና መዋቅሩ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ›› - (አቶ ውብሸት ኦቶሮ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ) ክፍል ሁለት

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1257
  • ሪፖርታዥ
‹‹መመሪያውን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ማኅበሩና መዋቅሩ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ›› -                            (አቶ ውብሸት ኦቶሮ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ)                         ክፍል ሁለት

ማንኛውም አባል በመመሪያው ከተከለከለው የአመራርነት መደብ አገልግሎቱን ከጨረሰ በፈለገው የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ገብቶ የማገልገል መብቱ የተጠበቀ ነው። እንዲህ ዓይነቱን አባል ማኅበሩ የሚገድብበት ወይም የሚከለክልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም። ብዙዎች ብዥታ የሚፈጥርባቸውና የማይገባቸው ይሄ ነው።አንዴ አመራር ከሆኑ ዕድሜ ልካቸውን አመራር የሆኑ የሚመስላቸው አሉ። ከዚህ በፊት ማብራሪያ መስጠት ያላስፈለገው እነዚህ ሰዎች ያልተከለከሉ አባላት በመሆናቸውም ጭምር ነው። 

መመሪያው ስለአሁን ነው እንጂ ስላለፈው ወይም ስለወደፊቱ ስለማያወራ ነው ከዚህ በፊት መግለጫ ወይም ማብራሪያ መስጠት ያላስፈለገው። በሰነዱም ላይ ይኸው ነው በግልጽ የጠቀመጠው። መመሪያው የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር አባላት ይላል እንጂ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር የነበሩት አይልም። ብዣታው አሁንም ግልጽ ሊሆን ይገባል መመሪያው የሚከለክለው በአገልግሎት ላይ ባሉበት ጊዜ ብቻ ነው። ለአገልግሎት ተመልሰው ሲመጡ በግልጽ አባል አለመሆናቸውን ገልጸው ወደ አገልግሎት ሊገቡ ሲሉ የተቀመጠ ቅደም ተከተል አለ። ከፖለቲካ አባልነት ወጥተው እና ጨርሰው አገልግሎት ላይ እስከተመደቡ ድረስ በአገልግሎት ላይ እስከቆዩ ድረስ ከዚያ አባልነት ውጪ መሆናቸውን ብቻ ነው ማኅበሩ የሚከታተለው።  ከዚያ በኋላ ያለው የራሳቸው ግለሰባዊ መብታቸው ነው። ይህንንም መመሪያው  መከልከል አይችልም።

አባላት ወደ ፖለቲካው ዓለም ሲገቡም ሆነ የመንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ሲደርሱ ከማኅበሩ አገልግሎት እንዲርቁ የሚያስገድድ አንዳች ነገር የለም። ሰዎች ወደ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ሲወጡ ባለባቸው የሥራ ጫና እና መደራረብ ምክንያት ከአገልግሎት ሊርቁ ይቻላሉ እንጂ በማኅበሩ አካባቢ ገፊ ነገር የለም። 

ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተከታይ ወይም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ እርከን ላይ ያለ የማኅበሩ አባል በተከለከሉት የአገልግሎት መደብ ላይ አያገለግልም እንጂ ከዚያ ውጪ ባሉት የአገልግሎት መደቦች ላይ ሊያገለግል ይችላል። በእርግጥ ወደ ማኅበሩ ሲመጣ እንደ ሥልጣኑ ወይም እንደ ፖለቲካ አቋሙ ሳይሆን መንፈሳዊ ሆኖ ነው የሚያገለግለው፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የበላይ እና የበታች ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ወደ ማኅበሩ ሲመጣ ግን ሁሉም እኩል ሆኖ ነው የሚያገለግለው። መድረኩም ለዚህ ምቹ አይደለም። በዚህ ምክንያት አባል ሆኖ ስለሚያገለግሉ ብቻ ባላቸው የፖለቲካም ሆነ የመንግሥት ሥልጣን ተጽእኖ መፍጠር አይችሉም በዚህም ስጋት የለብንም። ይህ ልምድ ትላንት ነበረ ፣ዛሬም አለ ነገም በሩ ክፍት ነው።  

በእርግጥ ማኅበሩ ብዙ አባል ብዙ መዋቅር እንደመያዙ መጠን ይሄን መዋቅር ለመጠቀም የተለያዩ አካላት ፍላጎት አይኖራቸውም ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ብዙዎች ሊኖራቸው ይችላል ፍላጎቱን መከልከል አይቻልም። የራሳቸው ፍላጎት ነውና ዓላማቸውን ለማሳካት ፍላጎት ማሳየታቸው ወንጀል አይደለም፤ ማኅበሩ ይህ ፍላጎት እውን እንዳይሆን ነው የሚሠራው፣ የሚከለክለውም።  በመዋቅራችን እንዳስቀመጥነው የማኅበራችን መልካም ስም መዋቅር ዝና ንብረት ሀብት ለዚህ መጠቀም እንደማይቻል መመሪያው ይከለክላል።  ሁለተኛው የማኅበሩን መዋቅር የሚወክሉ ወይም ደግሞ የበላይ ሆነው የሚመሩ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉት አባሎቻችን ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ ስናደርግ ዋና ዓላማው ይሄነው። መዋቅርን ለሌላ ነገር መጠቀም እንዳይቻል ለመከልከል ነው።

ከሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ኦርቶዶክሳውያን በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ማኅበረ ቅዱሳን  በማንም ላይ ተጽዕኖ አላደረሰም ከዚህ ጋር በተያያዘም ምንም የተገደበ ነገር የለም። ሰዎች እንዲህ ሊያስቡ ቢችሉም የማኅበሩ መመሪያ ትላንትም ዛሬም ያለው አንድ ነው።  ማኅበሩ ገለልተኝነቱን ለማረጋገጥ ሲል ከከለከላቸው አባላት ውጪ የከለከላቸው ሌሎች አባላት የሉም። በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መሳተፍ የፈለጉትን ፓርቲ መደገፍ የአባላት ግላዊ ምርጫቸው እና መብታቸው ነው።

ማኅበሩ እስከዛሬ አባላት በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መልካም ነገር እንዲመጣ፣ እንዲፈጠር ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ከጊቢ ጉባኤ ጀምሮ ሲያስተምር ነው የመጣው። አባላት  ለወገናቸው ፣ለቤተ ክርስቲያናቸው ፣ ለሀገራቸው የሚጠቅም ሥራን መሥራት አለባቸው ብሎ ማኅበረ ቅዱሳን በጽኑ ያምናል። ለዚህ ደግሞ አንድ ሰው እንደዜጋ፣ እንደተማረ ሰው ድርብ ኃላፊነት አለበት በማለት በጊቢ ጉባኤ ሲያስተምር ነው የቆየው። ሕዝቡን በታማኝነት በመልካም ሥነ ምግባር ማገልገል አለባችሁ ብሎ ነው ማኅበሩ የሚያስተምራቸው። አባላት በየትኛውም ፖለቲካዊ ጉዳይ አባል ይሁኑ፣ ሀገራቸውን ያገልግሉ ወደማኅበሩ መድረክ ሲመጡ ግን ለአገልግሎት ብቻ ይምጡ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ፣አቋማቸውን እዚያ ያስቀምጡ እዚህ ሲመጡ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ይምጡ የሚል አቋም ነው ማኅበሩ ያለው።

ምናልባት አባላት ወደ ተለያዩ ፓርቲዎች ሲገቡ መዋቅሩን ተጠቅመው ይሆን እንዴ? እነዚህን አባላት ያመጡ የሚል ዓይነት ግምቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚያ ባለፈ ግን  የማኅበሩ መዋቅር በዚህ ቀን በዚህ ቦታ ለፖለቲካ ዓላማ ለፖለቲካ ሥራ እንዲህ አድርጎ ተጠቅሞአል የሚል በተጨባጭ የቀረበ መረጃና ማስረጃ የለም። ከቀረበ ለወደፊቱ ለመያዝ ዝግጁ ነው። ማንኛውም አካል የማኅበሩ መዋቅር ለዚህ አገልግሎት ውሏል ካለ ማኅበሩ አጣርተን ለማስተካከል መልስ ለመስጠት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው። እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ በየትኛውም መልኩ አባላቶቻችን አመራሮቻችን በየደረጃው ያሉት ኃላፊዎቻችን ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው። ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቅድሚያ የሚሠጡ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን እውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን ለመስጠት የመጡ ቁርጠኛ አቁዋም ያላቸው አባላት ናቸው። ከማኅበሩ ሕግና መመሪያ ውጪ ይህን ዓላማ ይጠቀማሉ ብለን አንጠረጥርም። 

ሌላው ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ተጠቅመው መዋቅሩን መጠቀሚያ ሊያደርጉት አይችሉም። በዚህ በኩል የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ለዚህ መግቢያ ቀዳዳ አይሰጥም። በመጀመሪያ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሲመጡ በኃላፊነት ወይም በአመራርነት አይመጡም አባል ሆነው በሆነ ክፍል ነው ሊያገለግሉ የሚችሉት። ስለዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ዝቅተኛ ነው ማለት ነው። ኃላፊነት ቦታ ላይ ሲሆኑ ነው ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉት። ከዚህ ጋር ተያይዞ በማኅበረ ቅዱሳን የሁሉም ሰው ሐሳብ እኩል ይከበራል። አንድ ሰው ባለ ሥልጣን ስለሆነ የበለጠ ተደማጭ የሚሆንበት መድረክ የለም የሁሉም  ሰው ድምጽ እኩል ነው። ውሳኔ የሚወሰነው እንኳን ሁሉም ሰው ሲስማማ ነው። ስለዚህ ሁሉም አባላት እኩል መብት አላቸው ማለት ነው። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የበላይ እና የበታች ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፤ እዚህ ሲመጣ ግን ሁሉም እኩል ሆኖ ነው የሚያገለግለው። መድረካችንም ለዚህ ምቹ አይደለም።

ማኅበሩ ስላለው ማኅበራዊ ሱታፌ  በማኅበሩ መመሪያ አንቀጽ ሰባት ላይ ማኅበሩ ያለው ማኅበራዊ ሱታፌ በሚል ወደ ስምንት ነጥቦች ተቀምጠዋል። ባለፉት ዓመታት በሀገራችን  ብዙ አለመግባባቶችና ግጭቶች አይተናል። ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ የሆኑ ብዙ ችግሮች በሀገሪቱ ተፈጥረዋል ከዚህ አንፃር በሀገራዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች የሚከሠቱ ያለመግባባትን በማስታረቅ ሥራ ላይ መሳተፍ እንደ ሃይማኖት ተቋም ሲሠራ ቆይቷል። ከዚህ በፊት በመድረክ መግለጫ ባነንሰጥም በምንቸለው መልኩ እንዲህ አይነት ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ስንሠራ ነው የቆየነው። 

ማኅበሩ ከላይ እስከታች ያሉትን መዋቅሮች እየተጠቀመ ከአጋርና ከተባባሪ አካላት ጋር እየሆነ ግጭቶች መቅረት የሚችሉበትን፣ አለመግባባቶች የሚያስከትሉትን ጦርነቶች፣ የሚያመጡትን ጉዳት እያሳየ  የሰላምን ጥቅም ደግሞ ሲያስተምር ቆይቷል በመመሪያው ላይ የተካተተውም አጽንኦት እንዲሰጠው ነው። ወደፊትም ግጭቶችን ስለማስቀረት አለመግባባትን ስለማስወገድ በሰፊው የምንሠራ ነው የሚሆነው። በመመሪያው ላይ አጽንኦት እንዲያገኝና በተለይ ሀገራች አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ጉዳዩ አድርጎ መሥራት ስለአለበት አንድ ዋና ጉዳይ አድርገን አስቀምጠናል። 

ሌላው ማኅበራዊና ሰብአዊ ልማት ለማስፋፋት ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ረገድም  በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተፈጠረው ችግር ለረኃብ፣ለእርዛት የተዳረጉ ወገኖቻችን ከመደገፍ ዝም ብለን አልተቀመጥንም። የምንችለውን ድርሻ መወጣት አለብን ብለን ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ያሉትን ምእመናንን በማስተባበር በሁሉም አቅጣጫ ላሉ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣ ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ ስንሞክር የምችለውንም ስናደርግ ነበር፤ አሁንም እያደረግን ነው ያለነው። የወረርሽኝ፣ የሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ የሆኑትን የማኅበረሰብ ክፍሎች በመርዳት ረገድ ከማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት ጋርም የምንሠራቸው ሥራዎች አሉን። በተለይ  መዋቅሮቻችንን በመጠቀም  ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ፣  ከአጥቢያዎች ጋር በመሆን ስንሠራ ቆይተናል። አሁንም እንዲህ ያሉ ሥራዎችን አጠናክረን እንደምንሠራ ለመግለጽ ነው መመሪያችን ውስጥ ያካተትነው። መዋቅሮቻችንም ይህንን ትኩረታችንንና ጉዳዮቻችንን አውቀው እና ትኩረት ሰጥተው ነው እንዲሠሩ ለማሳሰብ የምፈልገው።

ከላይ በዝርዝር ያናቸውንና የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻርም ማኅበሩ እና መዋቅሩ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። በማኅበሩ ሁሉም መዋቅር ላይ ያሉ አካላት ይሄን መመሪያና ሌሎችም መመሪያዎችን በአግባቡ የመተግበር፣ የመጠበቅ ፣የማስጠበቅ ድርሻ ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንፃር ሙሉ በሙሉ ወስደው አባላት እንዲረዱት በማድረግ  ካልተፈለገ ተጽዕኖ ነፃ በማድረግ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ይህን ትልቁን ድርሻ የሚወሰዱት ማኅበሩ እና በመዋቅሩ ላይ ያሉ ኃላፊዎች ናቸው። መመሪያን ለሁሉም መዋቅር አውርደናል ሁሉም መዋቅር ያውቃሉ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥራዎችን ሠርተናል። ይህን ለወደፊቱ በሰፊው ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ከአባላቱ ጋር እየተወያዩ ግልጽ እያደረጉ እንዲሄዱ እናደርጋለን። ሁለተኛ አባላቱ ናቸው አባላቱ ኃላፊነት የሚሰማቸው ያላቸውን ጊዜ ያላቸውን ጉልበት ዕውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን እናውል በረከት እናግኝ ብለው የመጡ አባላት ናቸው እና እነዚህ አባላት እንኩዋን ተነግሯቸው ሳይነገራቸውም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ስለዚህ አባላት ትልቅ ድርሻ አላቸው ማለት ነው። 

የሀገራችንን አሁናዊ ሁኔታና እየደረሠ ያለውን ምርጫ በተመለከተ ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ ሁሉም የሚያውቀው ሲሆን ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል የሚል አቋም ነው ያለን። የሚመለከተው አካል ይህንንን ግጭት፣ አለመግባባት ባጠቃላይ የሰው ሕወት የሚቀጥፉ ነገሮችን እንዴት ማስቀረት እንችላለን? የሚለው ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው። ከሁሉም ሕይወት ይቀድማል ፣ሰው ይቀድማል ምርጫ ቢደረግ ለሰው ሰውን ለማስተዳደር ነው ሰው ከሌለ ሕዝብ ከጠፋ የሚመረጠው አካል ምንድነው የሚመራው? የሚያስተዳድረው?

ስለዚህ ከሁሉ ነገር በፊት የሰው ልጅ ደኅንነት መቅደም አለበት፤ የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር ነው ክቡር የሆነውን የሰው ልጆችን ሕይወት የሚያጠፋ ነገር ሁላችንም በመጠንቀቅ መጠበቅ አለብን። ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀን ግንዛቤ እንፈጥራለን ስንልም ይሄንን ነው የሚወቀድመው ነገር መቅደም አለበት። ቅድመ ምርጫ፣ ጊዜ ምርጫ፣ ድኅረ ምርጫ ከግጭት ካለመግባባት መለያየቶች ሊኖሩ ይችላሉ ነገር ግን አለመግባባቶችን በውይይት ከመፍታት አንፃር በሐሳብ ብልጫ የመሸናነፍን ባህል ማዳበር አለብን። አሁንም ያሉ ችግሮች በሙሉ በሰከነ አእምሮ ሊታዩ ይገባል ሽግሌዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣የሚመለከታቸው የሃይማኖት አባቶችም ይህንን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። ሁሉም ነገር የሚሆነው ሰላም ሲኖር ነውና።

ግጭቶች፣ አለመግባባቶች ቦታ ስለወሰዱ ትኩረት ማግኘት ያለባቸው ነገሮች ትኩረት እያገኙ አይደለም።  በቅርብ ጊዜ እንኳን ያለውን ብናይ አሰቦት ገዳም ላይ የተነሣው እሳት ሀገርን ያጠፋ፤ በ፳ እና በ፴ ዓመት የማንተካቸውን ቅርሶች አገር በቀል የሆኑ ዛፎች በሙሉ ወድመዋል። ይህ የሚያሳየው ግጭቶች ሁሉ ትኩረታችንን እየወሰዱብን እንደሆነ ነው። ስለዚህ ትኩረት መስጠት ካለብን ነገሮች ላይ መረባረብ ቸል ማለት አይገባም። ሁሉም ነገር የሚሆነው ሰላም ሲሆን ነውና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል። ስለዚህ ደግሞ ሁሉም  ድርሻውን ሊወጣ ይገባል የሚለው መልእክታችን ነው።

 

“ የአብነት መምህራን የቤተ ክርስቲያን ዓይኖች ናቸው” - ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም

Details
Written by: መጽሐፈ ሲራክ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1601
  • ቤተ አብርሃም
“ የአብነት መምህራን የቤተ ክርስቲያን ዓይኖች ናቸው”                                                              - ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም

የዛሬው የቤተ አብርሃም ዐምድ እንግዳችን ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም ይባላሉ። ከተድባበ ማርያም ቀጥሎ በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነገሥታቱ በአብርሃ ወአፅብሃ (ኢዛና ና ሳይዛና)  ዘመነ ንግሥና  እንደተተከለ በሚነገርለት የማኅደረ ስብሐት ኦፍና ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም እና የድጓ መምህር ናቸው።  በሰሜን ሸዋ ዞን መርሐ ቤቴ ወረዳ ዓለም ከተማ ከሚገኘው የማኅደረ ስብሐት ኦፍና ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ፴፭ ዓመታት ወንበር ዘርግተው በማስተማር ብዙ መምህራን ሊቃውንትን አፍርተዋል። ከሕይወት ልምዳቸው፣ ከአብነት ትምህርት ቤት ሕይወታቸው እንደሚከተለው አካፍለውናልና እንከታተላቸው። 

ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ይህን ቃለ መጠይቅ እንድናደርግ ፈቃደኛ በመሆንዎ በእግዚአብሔር ሥም እናመሰግናለን። ሙሉ ስምዎትን ከነማዕረግዎ እንዲሁም በደብሩ የአገልግሎት ድርሻዎትን ጭምር  ቢገልጹልን? 

ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም፦ እኔም መጠይቅ ምላሽ እንድሰጥ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። ሊቀ ጠበብት በቃሉ ሥዩም እባላለሁ በደብሩ  የአቋቋም እና የድጓ መምህር ነኝ።   

ስምዐ ጽድቅ፦  አባታችን የት፣ መቼ ተወለዱ? የልጅነት ሕይወትዎ በተለይ የአብነት ት/ት ቤት ሕይወትዎ ምን ይመስላል?  

ሊቀ ጠበብት፦ ቀኑን እና ወሩን ለይቼ ባላውቀውም የተወለድኩት በ፲፱፻፵፰ ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን መርሐ ቤቴ ወረዳ ልዩ ስሙ በሬቻ ገነተ ጊዮርጊስ በሚባል ደብር ነው። ፯ ዓመት ሲሞላኝ እናትና አባቴ በዚያው ደብር ከሚገኝ 

የአብነት ት/ቤት አስገቡኝ። በዚያ የመጀመሪያው ፊደል ያስቈጠሩኝ መምህሬ አባ አሰፋ ይባሉ ነበር። እሳቸው በማረፋቸው አባ ነጋሽ ከሚባሉ መምህር  ቀጠልኩ። ከሰባት እስከ አሥራ አንድ ዓመቴ ድረስ ከፊደል ጀምሮ መውዳሴ ማርያም፣ ዳዊት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ማዕረገ ዲቁናን ተቀበልኩ። 

ከዚያ በረመሽድ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለአራት ዓመት በዲቁና አገልግያለሁ። አራት ዓመት በዲቁና እንዳገለገልኩ አሥራ አምስት ዓመት ሲሞላኝ ወደ ላይ ቤት ዓለም ከተማ ማኅደረ ስብሐት ቅዱስ አማኑኤል በመሄድ የድጓ መምህር ከነበሩት መምህር በቃሉ ባይነሳኝ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ እና ድጓ ከየኔታ የማነ ብርሃን መዝገበ ቅዳሴ፣ ከአለቃ ሐረገወይን ዝማሬ መዋሥዕት፣ ከመምህር ዕፁብ አቋቋም ተምሬአለሁ። 

ወደ ቤጌምድር በማቅናትም ዘመንዬ በዓለ እግዚአብሔር ከሚባል ደብር መምህር ከነበሩት እና አሁንም ድረስ በሕይወት ካሉት (አዲስ አበባ ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር ናቸው) ከመምህር ዘካርያስ ቅኔን ከነአገባቡ አጠናቀቅሁ። ከዚያም ጎንደር በመሄድ ከየኔታ ሄኖክ ወልደ ሚካኤል (የአቋቋም መምህር) ዘንድ ለስድስት ዓመት ያህል አቋቋም ተምሬ አጠናቅቄአለሁ። እሳቸውም ብቃቴን አይተው ወገራ ወረዳ አይባ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ከምትባል ደብር እንዳስተምር ፈቅደው ስለላኩኝ ለሦስት ዓመት ያህል አቋቋም አስተምሬአለሁ። 

በዚያም በማስተምርበት ጊዜ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቻለሁ። በሦስቱ ዓመት ብቻ ያስተማርኩአቸው ከ፪፻ በላይ ይሆናሉ።  ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላም በ፲፱፻፸፰ ዓ.ም ወደ ትውልድ ሀገሬ ዓለም ከተማ ተመልሼ በማኅደረ ስብሐት ኦፍና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ማስተማር ጀመርኩ ማለት ነው። እንግዲህ እስከ አሁን በዚሁ ሞያ ነው ያለሁት ወደ ፴፭ ዓመት ሆኖኛል፤ ወንበር ዘርግቼ ማስተማር ከጀመርኩ ማለት ነው።

ስምዐ ጽድቅ፦  በዚህን ያህል የማስተማር ዘመንዎ ምን ያህል ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል? ከዚሁ ጋር  ‹ኦፍና› ማለት ምን ማለት ነው? አያይዘው ቢመልሱልን?  

ሊቀ ጠበብት፦ በዚህ ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ለአገልግሎት ብቁ የሆኑ ከ፮፻ በላይ የሚሆኑ አገልጋዮችን አውጥቻለሁ። ሌላው ‹ኦፍና› የቤተ ክርቲያኑ መጠሪያ ሲሆን ሁለት ትርጉም ያለው ነው አንዱ ‹ኦፍና› ማለት ወደ መልካም ቦታ መርቶ የሚያደርስ ታላቅ ጎዳና ማለት ሲሆን ፤ሁለተኛው ‹ኦፍና› ማለት እግዚአብሔር የቀረበው ቦታ ማለት ነው።  

ስምዐ ጽድቅ፦ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የቤተሰብዎ አስተዋጽኦ ምን ያህል ነበረ?

ሊቀ ጠበብት ፦ ቤተሰቦቼ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያልነበራቸው  ምእመናን ስለነበሩ የእነርሱ ፍላጎት ለዲቁና ያህል ተምሬ በትዳር ተወስኜ እንድኖር ማለትም ከእነርሱ እንዳልርቅ ነበር። እዚህ መድረሴ የእግዚአብሔር ምርጫ ነው ብዬ አምናለሁ። ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ ነው እዚህ የደረስኩት ማለት ነው። እነርሱም ብዙ አልቆዩም ዐሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ሁለቱም በተከታታይ ስለሞቱ ብቸኛ ነበርኩ። ነገር ግን እግዚአብሔርም  በሄድኩበት አልጣለኝም። ‹‹ሰዓሊ ለነ ቅድስት›› እያልኩ ስሟን የምጠራው እመቤታችን ከጎኔ ስላለች በእርስዋ ምልጃ ነው እዚህ የደረስኩት።

ስምዐ ጽድቅ፦ በአብነት ትምህርት ቤት ሕይወትዎ በሁሉም ነገር አብነት ሆነውኛል የሚሏቸው ሊጥቀሱልን ይችላሉ ? በተለይ ከመምህራኑ 

ሊቀ ጠበብት ፦ ብዙዎቹ መምህራን ለኔ አብነት ናቸው። በሕይወተ ሥጋ የሌሉም ያሉም አሉ። በሕይወተ ሥጋ ካሉት መምህር ዘካርያስ በማስተማር (እውቀት) አብነቴ ናቸው። የኔታ ሄኖክ ስመ ክርስትናቸው ወልደ ሊባኖስ፣ የኔታ ዕፁብ ስመ ክርስትናቸው ገብረ ኢየሱስ፣ መምህር በቃሉ የድጓ መምህሬ ‹‹ድጓን ተመራመር›› ያሉኝ እና ስማቸውን የስሜ መጠሪያ እንዲሆን የሰጡኝ ቅን መምህር ነበሩ። ሌላው በመጀመሪያ ዳዊት ያስደገሙኝ መምህር ገብረ መስቀል በሕይወቴ ውስጥ ለዛሬው ማንነቴ አብነት የሆኑኝ ናቸው።ዛሬም ዳዊት በደገምኩ ቊጥር  የክርስትና ሥማቸውን  በጸሎቴ አነሳለሁ፤ በፍፁም ከሕሊናዬ አይወጡም። ምክንያቱም ያምንም ደመወዝ በቅንነት ከእውቀታቸው ሳይሰስቱ ያስተማሩኝ ናቸውና። ያሉትን እያሰብኩ የሌሉትን ‹እግዚኦ ዐዕረፍ ነፍሳተ መምህራን› እያልኩ እጸልያለሁ።  እውነት ለመናገር በሕይወት ኖረው እንደአቅሜ ብረዳቸው ኖሮ ደስ ይለኝ ነበረ። 

ከማስተማር በተጨማሪ የኔታ ዕፁብ በእውነት ትሑት መምህር ናቸው። ከትንሹም ከትልቁም ጋር መዋል የሚችሉ ቅን አባት ናቸው። በምሁርነትም ታዋቂ ናቸው ቃለ እግዚአብሔር የሚይዝላቸውን በጣም ይወዱ ነበረ። የራሳቸው ማዕድ አልነበራቸውም ከተማሪ ጋር አንድ ላይ ነበር የሚበሉት። ተማሪ ሲራብ ሲራቆት ደስ አይላቸውም ‹‹ልብስ የለህም ወይ?›› ብለው ይጠይቃሉ የሌለው ተማሪ ካዩ የራሳቸውን ነው የሚሰጡት። የድጓ መምህሩ የኔታ በቃሉ የቃለ እግዚአብሔር ሰው ናቸው። ስናጠፋ ይቈጡናል፤ ነገር ግን ለራሳችን ብለው ነው። አስተምረውን ሲጠፋብን ‹‹የት ሄደህ ነው የሚጠፋብህ›› ብለው ይቈጡናል። በትጋት እንድንከታተል ነው። 

ስምዐ ጽድቅ፦ አገልግሎት ከጀመሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን የት የት አገለገሉ?

ሊቀ ጠበብት ፦ በልጅነቴ ለአራት ዓመታት ያህል በረመሽድ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዲቁና አገልግያለሁ። በአፍላነቴ ወገራ ወረዳ አይባ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ለሦስት ዓመታት አቋቋም አስተምሬአለሁ። በዚያን ጊዜ ፳፬ ሰዓት ነበር የማስተምረው። ሳስተምር በሁለት መንገድ ነው በወንበር (በጉባኤ ቤቱ)  በቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ። ዋናው ነገር ለተማሪ ቤተ ክርስቲያን ናት የምታስተምረው። በወንበር የተማሩትን ቀለም መነሻ መድረሻውን በትክክል በተግባር እንዲያውቁ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ሰዓት በሁለት ሰዓት እንዲደወል አደርግና ግዴታ ማኅሌት እንቆማለን። ለምሳሌ በትንሣኤ፣ በዳግም ትንሣኤ በጰራቅሊጦስ የትንሣኤን ቀለም ከመዝሙር ጀምረን ፍፃሜው እንዲዘለቅ አደርግ ነበር።

በዚያ ላይ የከበሮ አመታት፣ የጽናጸል አወራወር፣ ማቆም ማሳረፍ፣ የወረቦች አመላለሶች አጠቃላይ የማኅሌቱን ሥርዓት በተግባር እንዲዲለማመዱ አደርግ ነበረ። ወደዚህም ደብር ከመጣሁ በኋላ በዚሁ መንገድ ነው የማስተምራቸው በቃል እና በተግባር ሁሉን በደንብ እንዲረዱት ነው የምፈልገው። በተፈጥሮዬ ለይስሙላ አስተምሬ ብትለው በለው ባትለው የራስህ ጉዳይ አልልም። የተማረውን ትምህርት ግዴታ በተግባር እንዲተረጉምልኝ ጥረት አደርጋለሁ። ዛሬ ግን ተማሪም ቀዝቀዝ እያለ እየሄደ ነው፤ ድካምም እየመጣ ነው ፤ እኔ እንኳ ለማስተማር አይደክመኝም ተማሪው ግን ሰንፏል እንደዱሮው አይደለም።

ስምዐ ጽድቅ፦ ምክንያቱ ምንድነው ? 

ሊቀ ጠበብት፦ ዛሬ ዛሬ ተማሪው እየሰነፈ ነው እውነቱን ለመናገር ከድሮው ቀንሷል። ዛሬ ሞባይል አለ ይቀርጽና ያን መስማት ይፈልጋል፤ ቢሆንም ከሰውነቱ አይዋሐድም አይቀረጽም  በቃል አይያዝም ተማሪውን አስንፎታል። ትምህርት ለተማሪው ከሰውነቱ የሚያዋሕደው ያን ቃለ እግዚአብሔር በደንብ አድርጎ ሲቀጽለው ነው። ዛሬ ከላይ ከላይ ነው መቃረም የሚፈልጉት እኔ ግን ተዉ በሚገባ ተማሩ እያልኳቸው ነው። 

በእርግጥ ሁሉም በመጻሕፍት ታትመዋል ቢሆንም እንደጥንቱ በቃላቸው ነው መያዝ ያለባቸው። ተማሪዎች በቃላቸው እንዲይዙ እቈጣጠራለሁ ‹‹ሲጠፋችሁ ያን ተመልከቱ እንጂ መጽሐፍ ማየት ሞባይል ማዳመጥ ያሰንፋችኋል፤ መጀመሪያ በቃላችሁ በደንብ ያዙ›› እያልኩ እመክራቸዋለሁ። እኔ ስማር በጎንደርም በሌሎቹም ቦታዎች እንዲህ አይደለም ሞባይል የለም በቃላችን ነበር ሁሉን የምናጠናው። ተማሪው በቃሉ እንዲይዝ በቻልኩት መጠን እመክራለሁ እቈጣጠራለሁ። በዚህ ሂደት አገልግሎቴ ድሮም አሁንም አንድ ነው።

ስምዐ ጽድቅ፦ በአሁኑ ሰዓት በቊጥር ምን ያህል ተማሪዎች አሉ?

ሊቀ ጠበብት፦ በአሁኑ ሰዓት ወደ ፷ (ስልሳ)ተማሪዎች አሉ እነዚህ ተማሪዎች ይህን የአብነቱን ከዘመናዊው ትምህርት ጋር እያፈራረቁ እየተማሩ ነው። እኔም ተስፋ እንዳይቆርጡ ዘመናዊውንም ይህንንም ተማሩ እያልኩ እያበረታታሁ ነው።  

ስምዐ ጽድቅ ፦ የተማሪው ቊጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነውና መሠረታዊ ችግሩ ምንድነው?

ሊቀ ጠበብት ፦ ተማሪ የቀነሰበት የመጀመሪያው መሠረታዊ ችግር ልቦናው ተረጋግቶ እንዳይማር ወቅቱ አስቸጋሪ መሆኑ ነው። ተማሪው ተረጋግቶ እንዳይማር የምግብ እና የልብስ ችግር አለበት። በኛ ጊዜ እንዲህ ችግር አልነበረም ፪፻ እና ፫፻ ተማሪ ነበር የሚማረው ያውም በየመንደሩ እየዞርን እየለመንን። መንደር ተካፍለን ነበር የምንለምነው ሕዝቡም ደግ ነበር ‹‹ በእንተ ስማ ለማርያም›› ብሎ ተማሪ ደጅ ከቆመ ነውር ነው ምግብ ሳይሰጡ አይሸኙትም በዓል ሲመጣ በክብር ተጠርቶ ነው። ዛሬ ተማሪው ወደ ገጠር ሄዶ ለመለመን ያፍራል ፣ ይሳቀቃል።

ሕዝቡም እንደድሮ አይደለም ተማሪ ሲለምን ‹‹ሠርተህ አትበላም?›› የሚል መልስ ለተማሪው  ይሰጣል። ሕዝቡ በጥሩ ዓይን አያያቸውም እና ችግር ነው።

እነዚህ አሁን ያሉት የተለያየ ሥራ እየሠሩ ራሳቸውን ለመደጎም ይሞክራሉ። ለምሳሌ ሙሬ (መጥረጊያ)፣ ወንፊት እያዞሩ ይሸጣሉ የአጨዳና የአረም ጊዜም ለሥራ ይሠማራሉ። በከተማውም የቀን ሥራ (ሲሚንቶ ማመላለስ፣ ድንጋይ ማጋዝ) የመሳሰሉትን ይሠራሉ። እንደዚህ ሆነው ነው የሚማሩት በዚህ የተነሳ ነው ተማሪ እየሸሸ ያለው። ከዚህም ሌላ ‹‹ራሴን የማያስችል ትምህርት ምን ያደርጋል? እኔ ራሴን የማያስችል ትምህርት ተማርኩ አልተማርኩ ምን ይጠቅመኛል?›› በማለት ተስፋ የሚቆርጡት ብዙዎች ናቸው። ‹‹እነ የኔታ ዛሬ ምን ደሞዝ አላቸው? ነው ጥያቄው እነሱ ምን አገኙና ነው እኛ የምንማረው?›› ይላሉ። 

አሁን ትንሽ በማኅበረ ቅዱሳን የተያዘ ሥራ አለ በዚህ ጥሩ መንፈሳዊ ሥራ እየተሠራ ነው ያለው።  በኮረና በሽታ ብቻ እንኳ ብዙ እርዳታ ባለፈው ተደርጎላቸዋል። ከዚያን ወዲህ ነው ልባቸው የተረጋጋው። ችግራቸው ጠንክረውና ልባቸውን አስፍተው እንዳይማሩ ቃለ እግዚአብሔርን በትክክል እንዳይከታተሉ የሚበሉት፣ የሚለብሱት የላቸውም። እኛ ድሮ በርኖስ፤ ደበሎ እየለበስን ነበር የምንማረው፣ ተባዩ እከኩ ስንት ነገር ነበር? እርሱ የለም ቀርቷል። የዛሬዎቹ የሚፈልጉት ንጹህ ልብስ ነው ያን ለማግኘት ነው የሚጣጣሩት እኛ ግን በላያችን ላይ ምንም ቢወርድ ብንታመም ህልማችን ከሁሉ በላይ ቃለ እግዚአብሔር ነው። 

ባጠቃላይ ተማሪዎቹ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ብለው ነው የሚያስቡት። የሚፈለገው እርዳታ ነው ባለፈው በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በመጣው እርዳታ ብዙ ተማሪዎች ረክተዋል። በጣም ተስፋ የሚያስቆርጣቸው ኅብስተ ሠርክ  ማጣታቸው ነው። ከዚህ ውጪ ደግሞ የሚኖሩበት ጎጆ የላቸውም ጎጆውን ለመሥራት እንኳ እንጨት እና ሣር ችግር ነው። ተማሪው  እንጨት እና ሣር በመግዛት በተቻለው መጠን ባህሉ ትውፊቱ እንዳይጠፋ እያደረገ ነው። አሁን ግን አንገብጋቢውና ትልቁ ችግራቸው ቀለብና ልብስ ነው።

ስምዐ ጽድቅ፦ የአብነት ትምህርት ቤቱ እንዳይስፋፋ በእርግጥ ምግብ፣ ልብስ እና መጠለያ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆኑ ነው የሚታየው ችግሩ እንዴት ይፈታል ይላሉ?

ሊቀ ጠበብት፦ በመጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ቤተ ክህነቱ አብነት ትምህርት ቤቶቹ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። ይህን ስል ሙሉ ለሙሉ ትኩረት አልሰጠም እያልኩ አይደለም፤ ግን ብዙ ይቀራል። ቤተ ክህነት በየገጠሩ ያሉትን የአብነት ትምህርት ቤቶች በጀት ሊመድብላቸው ይገባል። የአብነት መምህራኑ ብዙዎችን ያፈሩ ዘንድ በወንበራቸው እንዲጸኑ በሥርዓት ሊያዙ፣ የተሻለ ክፍያ ሊያገኙ ይገባል የቤተ ክርስቲያን ዓይን ናቸውና። ቤተ ክርስቲያን ነገ የሊቃውንት ድኀ እንዳትሆን ዛሬ አብነት ት/ቤት ላይ መሥራት ተገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ የተለያዩ ማኅበራት የቤተ ክርስቲያን ልጆች የአብነት ት/ቤቱ እንዳይነጥፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል። ማኅበረ ቅዱሳን በተለያዩ ቦታዎች ባሉ የአብነት ት/ቤቶች ላይ እየሠራ ያለውን እኛም ስላየን ሊበረታታ ይገባል። ሌሎችም የእነርሱን ፈለግ ቢከተሉ ጥሩ ነው። ባጠቃላይ የአብነት ት/ቤት ምንጩ እንዳይደርቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እላለሁ።

ስምዐ ጽድቅ፦ ከማስተማር በተጨማሪ የሠሩት ሥራ ይኖር ይሆን? ለምሳሌ መጽሐፍ በመጻፍ

ሊቀ ጠበብት፦  ከማስተማር በተጨማሪ የጎንደርን ይትበሃል ጽፌ ታትሟል። ሌላው በዚህ በኛ ደብር ያለውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የየበዓላቱን ያሬዳዊ ወረቦች የመሳሰሉት የተካተቱበት መጽሐፍ አዘጋጅቻለሁ ነገር ግን ገና አልታተመም።

ስምዐ ጽድቅ ፦ በሕይወት ዘመንዎ የተደሰቱበት ወይም ያዘኑበት ገጠመኝ ካለ ቢገልጹልን?

ሊቀ ጠበብት፦ እንግዲህ መልካም እና ክፉ ነገሮች አንድ ላይ ነው የሚሄዱት ተወራርሰው ነው የሚኖሩት። የተደሰትኩባቸው ጊዜያት ነበሩ፤በተቃራኒው ከባድ ፈተና ደርሶብኝ ያውቃል። ከመልካሙ ልነሳና በሕይወት ዘመኔ የተደሰትኩበት ቀን ወገራ ከምትገኘው አይባ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ከምትባል ደብር መምህሬ እንዳስተምር ፈቅደውልኝ ለማስተማር የሔድኩበት ጊዜ ነው። ሌላው በየቀኑ ከተማሪዎች ጋር ስለምውልና ስለማስተምር ደስተኛ ነኝ። በሕይወቴ ክፉ ገጠመኝ ወይም ያዘንኩበት የምለው ተማሪ ቤት ሆኜ የታመምኩበትን ጊዜ ነው።

ቅኔ ቤት እያለሁ ቅኔ ልቀኝ ሥላሴ እንደደረስኩ በጣም ታመምኩ፤ ብዙ በሽታ ነበረብኝ፣ ራሴን ያዞረኝ ነበር። በዚያ ምክንያት በዐቢይ ጾም ጉባኤ አቋርጬ ጠበል ሄድኩ በረሃ ላይ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ጠበል ነበረ ዐቢይ ጾም እስከሚያልቅና እስከ ሆሣዕና ድረስ እዚያው ነበርኩ የእግዚአብሔር ምሕረት ቅርብ ነውና ተጠምቄ ዳንኩ። የሚገርመው ወደ ጸበል ስሄድ እግዚአብሔርን በጸሎት‹‹ ይህን ጠላት ያመጣብኝን ፈተና ከላዬ አንሣልኝ፣ አምላክነትህና አዳኝነትህን ልመስክር ልመሰክር›› ብዬ ተስዬ ነበር። ጸበሉ ዋሻ ነው እዚያ ሰው የለኝም ብቻዬን ነበርኩ እዚያ ሆኜ ዳዊት እደግም እጸልይ ነበር። ቅድም እንዳልኩት ቅኔ ቤት ሥላሴ (የቅኔ ክፍል) ላይ አቋርጬ ነበር የሄድኩትና መምህሬ ሙቶ ነው ብለው  እንዲፈልጉኝ ተማሪዎችን በየቦታው ልከው ነበረ። ስመለስ ‹‹የት ቆይተህ ነው?›› አሉኝ ‹‹ፀበል ነበርኩ›› አልኳቸው በዚያው ትምህርቴን ቀጠልኩ በሕማማት መጥቼ ጀምሬ አንድ ሁለት ወር እንደተማርኩ ሰኔ አካባቢ ቅኔ አስቀኙኝ ይሄ እንግዲህ የእግዚአብሔርን አምላክነቱን፣ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ያየሁበት ከባዱን ፈተና ያለፍኩበት ነውና አምላኬን እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ።

ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ስለሰጡን ቃለ መጠይቅ በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለን?

ሊቀ ጠበብት፦  እኔም በእግዚአብሔር ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

“ ራስን መከላከል የጦርነት አዋጅ አይደለም” “ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በሀገራዊ ፖለቲካ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ መምከርና ማስተማር አለባት” ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገ/ ክርስቶስ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ክፍል አንድ

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1259
  • ፍሬ ከናፍር
“ ራስን መከላከል የጦርነት አዋጅ አይደለም” “ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በሀገራዊ ፖለቲካ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ መምከርና ማስተማር አለባት”                              ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገ/ ክርስቶስ በኢ/ኦ/ተ/ቤተ/ክ  የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ                              ክፍል አንድ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ተደጋጋሚና ሁሉን አቀፍ የሆነ ጥቃት ሲፈጸምባት ቆይቷል። እየተፈጸመባት ያለውን ተደጋጋሚ ጥቃት በሆደ-ሰፊነት ከማለፍ ውጭ በጠላቶቿ ላይ የአፀፋ ርምጃ ልውሰድ ጉዳቱንም ለዓለም ላሳውቅ ሳትል ጉዳቷ እንደተዳፍነ ዘመናትን ተሻግሯል። ጠላቶቿም ከጊዜ ወደ ጊዜ የልብ ልብ እየተሰማቸው በማናለብኝነት በበደል ላይ በደል ይጨምራሉ። ጉዳቷን የሚቀንሱ ልትሠራቸው የሚገቡ የውስጥና የውጭ ጉዳዮች እንዳሉባት ቢታወቅም እየደረሰባት ያለውን ጥቃት በቅጡ ገልጾ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስረዳት የሚያግዛትን አሠራር ቤተ ክርስቲያኗ ባለመዘርጋቷ ከገጠማት ፈተና በቶሎ ለመውጣት ተቸግራለች። ይህ ደግሞ በዋናነት የሚዲያ አጠቃቀሟ ደካማ መሆንና የሕዝብ ግንኙነት ተቋም ያለመመሥረቷ ውጤት ነው። 

ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያን ሚዲያ አቋቁማ እስካሁን ድረስ የተወሰነ እንቅስቃሴ እያደረገች ቢሆንም የታሰበውን ያህል እየሠራ ነው ለሚለው ግን ጥያቄ ያስነሳል። የሚዲያውን ድክመት የሕዝብ ግንኙነት ተቋምን በማቋቋም ማካካስ እንደሚቻልም ከተለያዩ አሠራሮች መረዳት ይቻላል። ይህንን ቤተ ክርስቲያኗ የተረዳችው በሚመስል ሁኔታ በቅርቡ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያን አቋቁማለች። የተቋቋመውን የሕዝብ ግንኙት መምሪያ የሥራ ሂደትን እና የቤተ ክርስቲያኗን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ከሆኑት ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገ/ ክርስቶስ ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው  አቅርበነዋል። መልካም ንባብ። 

ስምዐ ጽድቅ፡- የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው አመሠራረትና የአገልግሎት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ይግለጹልኝ?

ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገ/ክርስቶስ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንደ አዲስ የተቋቋመው ከሦስት ወራት በፊት ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ትኩረት ሰጥተን ተቋሙን የማደራጀት ሥራ ሠርተናል። ቢሮዎች በጥሩ ሁኔታ ተደራጅተዋል፤ የዋና መምሪያ ኃላፊ፤ የምክትል መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የጸሓፊ ቢሮዎች ተስተካክለው ተዘጋጅተዋል። ሁሉም ቢሮዎች በተሟላ ቁሳቁስ ተደራጅተዋል። የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ከተቋቋመ በኋላም ሁሉም አህጉረ ስብከት የራሳቸውን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንዲያቋቁሙ በተላለፈው መመሪያ መሠረት እንዲያቋቁሙ እና ያቋቋሙትን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ያለበትን ሁኔታ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተደርጓል። በደብዳቤ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት እስካሁን ድረስ አሥራ ስድስት አህጉረ ስብከት ምላሽ ሰጥተዋል። የቀሩ ሌሎች አህጉረ ስብከትም ያቋቋሙትን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እስከ ጥቅምት የ፳፻፲፫ ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በሪፖርት አሳውቀዋል። ከዚህ በኋላ የሃምሳ አራቱ አህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ላይ ሥልጠና የሚሰጣቸው ይሆናል። ሥልጠናው የሕዝብ ግንኙነት መመሪያና አሠራር ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ሥልጠናውን የወሰዱ የመምሪያ ኃላፊች ወደየሀገረ ስብከቶቻቸው ሲመለሱ በወረዳና በአጥቢያ ደረጃ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያን ያቋቁማሉ። በወረዳና በአጥቢያ ላሉ አገልጋዮችም ተመሣሣይ ሥልጠና ይሰጣሉ። በቤተ ክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነትና በአጥቢያዎች መካከል የተጠናከረ የግንኙነት መረብ ይዘረጋል። ይህ የግንኙነት መረብ የመረጃ ልውውጡና ፍሰቱ የተጠናከረ እንዲሆን ያግዛል። ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች በተዘረጋው የመገናኛ መረብ አማካይነት እንድንለዋወጥ ይረዳል። ስለሆነም የሕዝብ ግንኙነት መምሪያውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ አጥቢያ ድረስ መዘርጋት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫችን ይሆናል።

መመሪያው አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ለመቆጣጠር፤ የቅርብ ክትትል ለማድረግና በየአህጉረ ስብከቱ ለሚያጋጥሙ ችግሮች በአጭር ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት የሚያግዝ አሠራር ይኖረዋል። ለሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ግብዓት ይሆናሉ ተብሎ የሚታሰቡ ጉዳዮች ሁሉ  በመምሪያው በተዘረጋው መረብ አማካይነት በየሳምንቱ የምንለዋወጥ ይሆናል። የመምሪያው አገልግሎት እጅግ የተሣካና የተፋጠነ እንዲሆን በዓለማችን አሉ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሁሉ እንጠቀማለን። የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም የተሻለ ተግባር እያከናወን እንገኛለን። 

ስምዐ ጽድቅ፡- ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት የአሠራር ሂደትን በትክክል በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ለመተግበር ማስተባበሪያው ምን ያህል ዝግጁ ነው?

ሊቀ ሥዩማን እስክንድር፡- የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ስለተቋቋመ ብቻ መደበኛ የቢሮ ሥራ ብቻ አድርገን አናየውም። መምሪያው በዋናነት የቤተ ክርስቲያን አንደበት ነው የሚሆነው። ትልቁ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ክፍልም ነው የሚሆነው። መምሪያው የቤተ ክርስቲያኗን ታላቅነት በሚመጥንና በተቀመጡ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ሂደቶች የሚመራ ይሆናል። የመተዳደሪያ ደንቡም ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የሕዝብ ግንኙነት መመሪያዎችን መሠረት ያደረገ ሲሆን ደንቡ ተዘጋጅቶ በቋሚ ሲኖዶስ ጸድቆ ለአገልግሎት እንዲውል ለማስተባበሪያው ገቢ ተደርጓል። መመሪያውን መሠረት አድርጎም የማስፋትና የማደራጀት ብርቱ ሥራ ይጠይቃል። ይህ ሥራም እጅግ ፈታኝና ከባድ ይሆናል፤ በተወሰነ የአገልጋይ አቅምም የሚሠራ አይሆንም። የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው በደንብ እንዲጠናከር ከአባቶች ጀምሮ የሁሉን ባለድርሻ አካል ርብርብ ይጠይቃል። የበጀት ድጋፍና የተባባሪ አካላት እገዛ ያስፈልገዋል። ተባባሪ አካላት ተቋሙን ለማሳደግ የራሳቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። በዚህ ረገድ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በጋራ  እየሠራን ነው። ከማኅበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን። በተለይ የቁሳቁስና የሥልጠና ድጋፍ በዋናነት ይደረግልናል ብለን እናምናለን። ተቋሙን ለማሻሻል ከሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እንዲሁ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራ ይሆናል። 

ለሦስት ወራት ያህል ማስተባበሪያውን የማደራጀት ሥራ ላይ ትኩረት አድርገን ስንሠራ የቆየን ቢሆንም ከሥር ከሥር ግን የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ናቸው ብለን ያመንባቸውን ተግባራት ስናከናውን ቆይተናል። ለሕዝበ ክርስቲያኑ እውነተኛና ታማኝነት ያለውን መረጃ ስናደርስ ቆይተናል። 

ስምዐ ጽድቅ፡- የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያው በሰው ኀይል ሲደራጅ ምን ምን ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ያስገባል ይላሉ?

ሊቀ ሥዩማን እስክንድር፡- የሰው ኃይሉ ሲደራጅ የግድ በሕዝብ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ ወይም ማስተርስ ዲግሪ ያላቸውን አጥቢያ ላይ ወይም በሌሎች መምሪያዎች ላይ በኃላፊነት እናስቀምጣለን ማለት አደለም። የቤተ ክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ የሚደራጀው ቤተ ክርስቲያኗ ባላት የሰው ኃይል አቅም ልክ ሲሆን ትምህርታቸውን በተቀራራቢ የትምህርት ዘርፍ ያጠናቀቁና በቤተ ክርስቲያኗ ባሉ መንፈሳዊ ኮሌጆች ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ወንድሞች እና እኀቶች በመምሪያው ውስጥ በቋሚነት ተቀጥረው የሚያገለግሉ ይሆናል። ይህ ማለት በዘመናዊና በመፈንሳዊ ትምህርት በቂ እውቀት ያላቸውና መሠረታዊ የኮምፒውተር ክህሎት ያካበቱ ሊሆኑ ይገባል። የሰው ኃይሉም በነዚህ መስፈርቶች የሚደራጅ  ይሆናል። ቅጥር ከተፈጸመ በኋላም ተደጋጋሚ የሆኑ የአቅም ማጎልበቻ የሕዝብ ግንኙነት ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የተቋቋመው የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በሀገረ ስብከትና በአጥቢያ ደርጃ የሚቋቋሙ መምሪያዎችን የሰው ኃይል፤ የቁሳቁስና የሥልጠና ድጋፍ ያደርጋል። 

በአንድ ጊዜ የሕዝብ ግንኙነት ተግባራት ማማ ላይ ለመውጣት የታሰበ ሳይሆን ቀስ በቀስ በማደራጀት ፍጹም ሙያዊ ተግባራት ብቻ የሚከናወኑበት መምሪያ የማድረግ እቅድ ተይዞ ነው ወደ ሥራ የተገባው። ቤተ ክርስቲያኗ በዚህ ሰዓት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንዲደራጅ መወሰኗ በራሱ ትልቅ ርምጃ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱን ደረጃ በሚመጥን መልኩ መምሪያውን ለማደራጀት ግን ትጋትና ጠንካራ ሥራን ይጠይቃል። የሕዝብ ግንኙነት መምሪያውን በደንብ በማደራጀት ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግና ፍጹማዊ የሆነ መዋቅራዊ አሠራርን የተላበሰ እንዲሆን  በኛ በኩል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

 

የአፍሪካ  ክርስቲያኖች ለከፍተኛ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  አስታወቀች

Details
Written by: ካሳሁን ለምለሙ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 15 May 2021
Hits: 1119
  • አጫጭር ዜናዎች
የአፍሪካ  ክርስቲያኖች ለከፍተኛ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  አስታወቀች

በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ክርስቲያኖች ለከፍተኛ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሪፖርት ማስታወቋን ኦርቶዶክስ ታይምስ ዘገበ፡፡ 

በተለይ በናይጀሪያ ክርስቲያኖች ላይ እተፈጸመ ያለው ጥቃት የዓለምን ትኩረት እየሳበ መምጣቱን ያነሳው ዘገባው ሀገሪቱም በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው የዓለም ሀገራት መካከል ቀዳሚ መሆኗን አስታውሷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም በናይጀሪያ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከ2011 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሦስተኛ እንደጨመረ ዘገባው አስረድቶ ከዓለም በአሰቃቂ ሁኔታ ከሚገደሉ ክርስቲያኖች መካከል ዘጠና በመቶ ያህሉን እንደሚይዙ አስታውቋል፡፡ 

በመላው ዓለም በግፍ ከተገደሉት አራት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ አንድ ክርስቲያኖች መካከል አራት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሦስት ያህሉ ናይጀሪያውያን ክርስቲያኖች እንደሆኑ ያነሳው ዘገባው ለክርስቲያኖች የሞትና የስጋት ምክንያት የሆነው ደግሞ “ቦኮሐራም” የተባለው የሽብር ቡድን መሆኑን በዘገባው ተገልጧል፡፡ የሽብር ቡድኑም እንደ እኤአ ከ፳፻፲፩ ዓ.ም ጀምሮ በናይጀሪያ ጥቃት እንሚፈጽም ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡  

በሶማሊያ፣ በኬንያ እንዲሁም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት “አልሸባብ” የተባለው የሽብር ቡድንም  በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ እልቂት እየፈጸመ እንደሚገኝ የገለጠው ዘገባው የሽብር ቡድኑ በአብዛኛው የከተማ አውቶብሶችን በማስቆም ክርስቲያኖችን ከሙስሊሞችና በመለየት በክርስቲያኖች ላይ አሰቃቂ ጥቃት እንደሚፈጽም ተመላክቷል፡፡ 

በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ተዘጋጅቶ የቀረበው ሪፖርት ‹‹የአፍሪካ ክርስቲያኖች ሁኔታ›› በሚል ርእስ  ሲሆን በዋናነት በቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶ የውጭ ግንኙነት ክፍል በኩል ተዘጋጅቶ በሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በይነ መረብ በኩል እንደወጣ ዘገባው የስረዳል፡፡ 

በተለያየ ጊዜ በአክራሪዎች ጥቃት ለተፈጸመባቸው የኢትዮጰያና የናይጄሪያ ክርስቲያኖች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ያስረዳው ዘገባው የአፍሪካ ክርስቲያኖችን ጥቃት በመረጃ በማስደገፍ ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ 

 

ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ)

Details
Written by: በእህተ ሚካኤል
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 28 April 2021
Hits: 1317
  • የሕፃናት ዓምድ

ልጆች! ባለፉት ሁለት እትሞቻችን በዐቢይ ጾም (በጾመ ሁዳዴ) ውስጥ ከሚገኙ ሳምንታት እና መጠሪያዎቻቸው ውስጥ ከዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ ‹‹ዘወረደ››፣ ‹‹ቅድስት››፣ ‹‹ምኩራብ››፣‹‹መጻጉዕ›› ፣‹‹ደብረ ዘይት›› እና ‹‹ገብር ኄርን›› ስያሜያቸውንና ታሪካቸውን ነግረናችሁ ነበር። ስያሜያቸውንና ታሪካቸውን በደንብ እንደተረዳችሁ ተስፋ እናደርጋለን። እነሆ በዚህ ዝግጅት ደግሞ ስለ ‹‹ኒቆዲሞስ››፣ ‹‹ሆሣዕና›› እንዲሁም ስለ ሰሙነ ሕማማት ይዘንላችሁ ቀርበናል ተከታተሉን። 

7. ኒቆዲሞስ 

ልጆች! ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ኒቆዲሞስ›› በመባል ይጠራል። ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን ሲሆን ኢየሩሳሌም ውስጥ ካሉት የአይሁድ አለቆች እና መምህራን አንዱ ነው። ኒቆዲሞስ የብሉይ ኪዳንን ትምህርት ጠንቅቆ የሚያውቅና መምህር ፣ በሀብት ደረጃ ከፍ ያለ ሀብት ያለው ከመሆኑም በላይ የአይሁድ አለቃና ባለ ሥልጣንም ነው። ኒቆዲሞስ ወንጌልን ለመማር ከአይሁድ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣ መምህረ አይሁድ ነው። (ዮሐ ፫፥፩—፳፩)

Read more: ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ)

የቅዱሳት ሥዕላት ክብር ከየት ወደ የት?

Details
Written by: ኪኑኪሩ ከአዲስ አበባ
Category: ስምዓ ጽድቅ
Published: 28 April 2021
Hits: 3345
  • ትዝብት

ቅዱሳት ሥዕላት በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ አላቸው። የሥላሴዎች፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢሱስ ክርስቶስ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የቅዱሳን መላእክት፣ የቅዱሳን ሰማዕታት ሥነ ሥዕል መሣል ብሎም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማድረግ እና ለጸሎት እና ለትምህርት መጠቀም የተለመደ ነው። አብያተ ክርስቲያናቱንም ሆነ ገዳማቱን ካለ ቅዱሳት ሥዕላት ማስብ አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቻችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ በቅዱሳት ሥዕላቱ ፊት በመቆም፣ በመንበርከክ እንዲሁም በመስገድ ጸሎት እናደርሳለን፣ ሰላምታ እናቀርባለን ፣ ምልጃ እንጠይቃለን። በቤታችንም ለቅዱሳት ሥዕላት የተለየ ቦታ አዘጋጅተን በክብር በማስቀመጥ ለጸሎት አገልግሎት እንጠቀምባቸዋለን።

ቅዱሳት ሥዕላት በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤታችን ለጸሎት የምንጠቀመው ዝም ብለን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትመጣውን አብነት አድርገን ነው። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን የኪሩብን ሥዕል በሥርየት መከደኛው ላይ እንዲያዘጋጅ፣ በዚያም ላይ ተገልጦ እንደሚያነጋግረው ነግሮታል (ዘጸ ፳፭፥፲፰—፳፪።) በሐዲስ ኪዳንም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ‹‹ምስለ ፍቁር ወልዳ ›› ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ሥሏታል። ቅዱስ ኤፍሬም በእሑድ ውዳሴ ማርያም ላይ ‹‹በእግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ አንቺ ነሽ›› በማለት በብሉይ ኪዳን በእግዚአብሔር አዛዥነት በሙሴ ሠሪነት የተከናወነውን የሥነ ሥዕል ምንነት ያጠናክርልናል።

Read more: የቅዱሳት ሥዕላት ክብር ከየት ወደ የት?

Page 5 of 19

  • 1
  • 2
  • 3
  • 4
  • 5
  • 6
  • 7
  • 8
  • 9
  • 10

የቅጅ መብት © ማኅበረ ቅዱሳን 2012 ዓ.ም.

ዋናው ማዕከል | Afaan Oromoo | English |አሜሪካ ማዕከል | አውሮፓ ማዕከል | ካናዳ ማዕከል | ትሩፋት
MK Facebook MK Telegram MK Youtube
አጫጭር ዜናዎች የሕፃናት ዓምድ ትዝብት ሪፖርታዥ ቤተ አብርሃም ፍሬ ከናፍር ምሥጢሬን ላካፍላችሁ ርዕሰ አንቀጽ Oct ኪነ ጥበብ June ዐውደ ስብከት sept እናስተዋውቃችሁ ትምህርተ ሃይማኖት Nov Mar Apr ዐቢይ ጉዳይ ክርስትና በማኅበራዊ ሕይወት የነገዋ ቤተ ክርስቲያን የጥያቄያዎቻችሁ መልስ July የማኅበሩ መልእክት Jan Aug May 1997 13 ከዓለም ማእዘናት