ውድ አንባብያን ባለፈው ዕትማችን የቅጽል ዓይነቶችን ጀምረን የተወሰኑትን የውስጠዘ የቅጽል ዓይነቶች መመልከታችን ይታወሳል። የተወሰኑትን ደግሞ በዚህ ዕትም እንመለከታለን። መልካም ንባብ።
መስም ቅጽል
መስም ቅጽል ባዕድ ቅጽል ተብሎም ይጠራል። ይህ የቅጽል ዓይነት ከግስ የሚመሠረት ሲሆን ባዕድ ፊደል “መ” ን ሁሌም በመነሻነት ይጠቀማል። ይህ ቅጽል በሳድስ በሣልስም ይጨርሻል።
ይህ ቅጽል እንደ ሳድስ ውስጠዘ በአምስት መንገድ ይተረጎማል። ይህም በአድራጊ፣ በተደራጊ፣ በአስደራጊ፣ በተደራራጊና በአደራራጊ ይፈታል ማለት ነው። ይህን አስመልክቶ መምህር ዕንባቆም የግእዝ ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ ለተማሪዎች በልዩ አቀራረብ የተዘጋጀ በተሰኘ መጽሐፋቸው “መስም /ባዕድ/ ቅጽል በባዕድ ቀለም “መ” የሚጀምር ውስጠዘ ሲሆን አማርኛው እንደ ሳድስ ውስጠዘ በአንድ ተነቦ በአምስት ይተረጎማል።” በማለት ይገልጹትና በምሳሌም ሲያስረዱ “ መቅትል፡- የገደለ፣ የተገደለ፣ ያስገደለ፣ የተገዳደለ፣ ያገዳደለ” ተብሎ እንደሚፈታ ይገልጻሉ። (ገጽ.፷፯)
መምህር ኀይለ ኢየሱስ መንግሥትም የልሳነ ግእዝ መማሪያ በተሰኘ መጽሐፋቸው “መስም ቅጽል፡- ዝንቱኒ ዘመደ ቅጽል ይወጽእ እምነ ግስ ወይትነሣእ ኵለሄ በ “መ” ፊደል ወባሕቱ ይፌጽም በሳድስ ፊደል አምሳሊሁ ለሳድስ ቅጽል፤ ይህ የቅጽል ዓይነት ከግስ የሚመሠረት ሁሌም እንደ ሳድስ ቅጽል በሳድስ ፊደል ብቻ የሚጨርስ ነው።” በማለት ያስረዳሉ። (፳፻፲፪፣ገጽ.፹፰) መምህር ኀይለ ኢየሱስ ምንነቱን በዚህ መንገድ ከገለጹት በኋላ በምሳሌ ሲያስረዱ
ግስ መስም ቅጽል (ነጠላ) መስም ቅጽል በብዙ
ደንገጸ (ደነገጠ) መደንግጽ መደንግጻን/ት
ተንበለ (ለመነ) መተንብል መተንብላን/ት
ፈከረ (ተረጎመ) መፈክር መፈክራን/ት
ዘመረ (አመሰገነ) መዘምር መዘምራን/ት
በማለት ሁሌም በ “መ” እንደሚጀምር መጨረሻውም ሳድስ ፊደል እንደሆነ ይገልጻሉ። መምህር ኃይለ ኢየሱስ በሳድስ ብቻ ይጨርሳል ይበሉ እንጂ በሣልም እንደሚጨርስ መመልከት ይቻላል።
መምህር ዕንባቆም መስም ሣልስ ቅጽል የሚባል እንዳለና በሣልስ እንደሚጨርስ ቀተለ ከሚለውም ግስ መቅተሊ የሚል መስም ሣልስ ቅጽል እንደሚወጣ ሲተረጎምም እንደ መስም ሳድስ ቅጽል በአምስቱም አዕማድ እንደሚተረጎም ያስረዳሉ። ለምሳሌ መቅተሊ የሚለው መስም ሣልስ ቅጽል የገደለ፣ የተገደለ፣ ያስገደለ፣ ያገዳደለ፣ የተገዳደለ ተብሎ እንደሚተረጎም ገልጸዋል።
መምህር አስበ ድንግል ግእዝ ልሳነ ኢትዮጵያ በተሰኘ መጽሐፋቸው “መስም ሣልስ ቅጽል” ብለው “መንጽሒ፣ መፍቀሪ፣ መስተፍሥሒ ፣መቅለሊ…” የሚሉትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። (፳፻፱፣ ገጽ.፳፱)
ከላይ በመምህር ዕንባቆም፣ በመምህር ኀይለ ኢየሱስና በመምህር አስበ ድንግል የተገለጸውን መነሻ አድርገን መስም ቅጽል ምን ማለት ነው የሚለውን ስናጠቃልል ከግስ የሚመሠረት፣ በዋና ግሱ ላይ በማይገኝ ባዕድ ፊደል። “መ” የሚጀምር በዚህም ባዕድ ቅጽል ተብሎ የሚጠራ፣ በሳድስና በሣልስ ፊደል የሚጨርስ የቅጽል ዓይነት ነው። መስም ቅጽል እንደ ሳድስ ቅጽል ሁሉ በአድራጊ፣ በተደራጊ፣ በአስደራጊ፣ በተደራራጊና በአደራራጊ የሚፈታ የቅጽል ክፍል ነው።
መድበል ቅጽል፡-
መድበል ማለት አመድበለ አከማቸ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ስብስብ፣ ክምችት፣ አንድነት የሚል ትርጉም ይሰጠናል። ይህን አስመልክቶ መምህር ዕንባቆም የግእዝ ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ ለተማሪዎች በልዩ አቀራረብ የተዘጋጀ በተሰኘ መጽሐፋቸው “መድበል ማለት አንድነት፣ ክምችት፣ ጥቅል፣ ድምር፣ የተዳበለና የተጋራ፣ የሚታይና የማይታይ፣ የፍጥረት ስብስብ፣ ሁሉም ጾታ የሚጠሩበት ስያሜ ሲሆን በአንድ ተነቦ በአምስት አዕማድ ይተረጎል። ለምሳሌ፡- ቀተልት፡- የገደሉ፣ የተገደሉ፣ ያስገደሉ፣ የተገዳደሉ፣ ያገዳደሉ” በማለት ምንነቱን ከነምሳሌው ያስረዳሉ። (ገጽ ፷፰)
መድበል ቅጽል በብዙ ቁጥር በወንድ በሴት እንደሚነገር መምህር ኀይለ ኢየሱስ የልሳነ ግእዝ መማሪያ በተሰኘ መጽሐፋቸው “ዝንቱ ዘመደ ቅጽል ይትነገር ኵለሄ በብዙኅ ለብእሲ ወለብእሲት ወዝኒ ይትመሠረት እምነ ግስ፤ ይህ የቅጽል ዓይነት ሁል ጊዜ በብዙ ቊጥር በወንድ በሴት ይነገራል፤ የሚመሠረተውም ከግስ ነው ” በማለት ያስረዳሉ።
መድበል ቅጽል መነሻው የግሱን መነሻ ያደርግና መድረሻው ግን “ት” ይሆናል።
ምሳሌ፡- ቀደመ (ቀደመ) በሚለው ግስ መድበሉ ቀደምት ይሆናል።
ጸሐፈ (ጻፈ) በሚለው ግስ መድበሉ ጸሐፍት ይሆናል።
ነግሠ (ነገሠ) በሚለው ግስ መድበሉ ነገሥት ይሆናል።
ግሱ በ “ተ” ፣ “ጠ “፣ “ደ” መድረሻነት የሚነገር ከሆነ ደግሞ የመጨረሻውን ፊደል ማለትም ት፣ ጥ፣ ድ ን በማጥበቅ ትን ሳይጠቀም ይጨርሳል።
ምሳሌ፡- ከበተ (ሸሸገ) በሚለው ግስ መድበሉ ከበት (ት ይጠብቃል) ይሆናል።
ፈለጠ (ለየ) በሚለው ግስ መድበሉ ፈለጥ (ጥ ይጠብቃል) ይሆናል።
ሰገደ (ሰገደ) በሚለው ግስ መድበሉ ሰገድ (ድ ይጠብቃል) ይሆናል።
ውድ አንባብያን ከላይ የቀረበው ትምህርት ግልጽ እንደሆነላችሁ ተስፋ እናደርጋለን።
እናንተ ደግሞ የሚከተሉትን ግሶች በመጠቀም መስም ቅጽል በሣልስና በሳድስ እና መድበል ቅጽል መሥርታችሁ አሳዩ።
ተ.ቁ
ግስ
መስምሳድስ ቅጽል
መስም ሣልስ ቅጽል
መድበል ቅጽል
፩
ከሠተ
፪
ተለወ
፫
ተንበለ
፬
ነበረ
፭
ሜጠ
፮
ሰፈነ
፯
ነገደ