Saturday, 27 February 2021 00:00

“በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” (ኢዩ.፪÷፲፪)

Written by  ዲ/ን ተስፋዬ ምትኩ

Overview

ቸርነት፣ ደግነት፣ ምሕረትና ይቅር ባይነት የባሕርይ ገንዘቦቹ የሆኑለት አምላካችን እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠራቸው የሰው ልጆችን ከመንገዱ በመውጣት በጠላት ወጥመድ ተይዘው እንዳይቀሩ “ወደ እኔ ተመለሱ” እያለ ዘወትር ይጣራል። ይህ ጥሪ የንስሓ ጥሪ ነው። ንስሓ የቃሉ ትርጒም መጸጸት መቆጨት፣ በሠሩት ክፉ ተግባር ማዘን ማለት ነው። (ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ ፰፻፸፰) በሌላ በኩል ደግሞ ንስሓ በሙሉ ልብ መመለስንና መለወጥን ያመለክታል። የሰው ልጅ ድካም የሚስማማውን ሥጋ እንደ መልበሱ ይደክማል፤ ይዝላልም። ከእውነት መንገድ፣ ከጽድቅ፣ ከሕይወት፣ ወጥቶ ይስታል። ይሁን እንጂ የሚያስብ አእምሮና የሚያመዛዝን ኅሊና ያለው ፍጡር እንደመሆኑ የሠራውን ስሕተት አስተውሎ መጸጸቱ የማይቀር ነው። ጸጸቱ የሐሳብ ለውጥ መኖሩን ያመለክታላል። ነገር ግን የሐሳብ ለውጥ ብቻ  መፍትሔ አይሆንምና በተግባር መለወጥ አለበት። በሐሳብም በተግባርም መለወጥ ማለት ደግሞ አጠቃላይ የሕይወት ለውጥ መሆኑን ያስገነዝበናል። ንስሓ የሚባለውም ይህ ነው። ማለትም በመጀምሪያ ያለንበትን ሁኔታ ቆም ብለን ማሰብ፤ ያለንበት ሁኔታ ከትክክለኛው የሕይወት መስመር የወጣ እንደሆነ መጸጸትና መቆጨት፤ ቀጥሎም የበደልነውና የተጣላነው ሰው ካለ ይቅርታ መጠየቅና መታረቅ፣ ከሁሉ በላይ ሕጉን በመተላለፍ ያሳዘንነው አምላካችን ይቅር እንዲለን ደጅ መጥናት ንስሓ ይባላል። ከንስሓ በኋላም ወደ ትትክለኛው መንገድ በመመለስ አዲስ ሕይወት መጀመር ይጠበቅብናል።

 

ጠቅለል አድርገን ስንመለከት ንስሓ እኖር እከብር ባይ ኅሊና የሚያሳስበንን ሥጋዊ ፍላጎት ተከትለን፣ ስላጠፋነው ጥፋት ስለ በደልነውም በደል ምሕረትና ይቅርታ የምንጠይቅበት ለኃጢአትና ለጥፋት የጋበዘንን ሥጋችንን የምንገሥጽበትና የምንቀጣበት፣ የእግዚአብሔርንም ቸርነት ደጅ የምንጠናበት ሥርዓት ነው። ይህም ማለት አስቀድመን በተከተልነው ክፉ ሐሳብና በፈጸምነው የጥፋት ተግባር የምንቆጭበት፣ የምንጸጸትበት፣ራሳችንን የምንወቅስበት ወደኋላም ተመልሰን የቀደመ ስሕተታችንን ላለመድገም ቃል የምንገባበት ሥርዓት ነው። ለዚህ ደግሞ “ልጆቼ ወደ እኔ ተመለሱ” እያለ ዘወትር የሚጠራንን የአምላካችንን ድምፅ መስማት ይጠበቅብናል። ነቢዩ ኢዮኤልም ይህንኑ ሲናገር ነው “አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” ያለው። (ኢዩ.፪÷፲፪) እዚህ ላይ ዋይታና፣ ልቅሶ፣ የሚሉ ቃላት ንስሓን የሚያመለክቱ ናቸው። ንስሓ አውቀን በድፍረት ሳናውቅ በስሕተት በሠራነው ጥፋት ተቆጭተን ወዮልኝ ባላደርገው ምን ነበር እያልን ራሳችንን የምንወቅስበት ሥርዓት ነውና። 

ስለዚህ ንስሓን ስናስብ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን መዘንጋት የለብንም እነሱም፡- መናዘዝ፣ የሚሰጠንን ቀኖና መፈጸምና፣ ለኃጢአታችን ሥርየት የተሠዋልንን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙን መቀበል የሚሉት ሲሆኑ እነዚህንም ከዚህ በታች በዝርዝር እንመለከታቸዋለን። 

፩. ኃጢአትን መናዘዝ፡-

የራስን ጥፋት አውቆ ለእግዚአብሔርም ለሰውም መናገር መናዘዝ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አስተምህሮ መናዘዝ ስንል ሰው በሐሳብ፣ በንግግር እና በተግባር በፈጸመው ኃጢአት ተጸጽቶ “እባክህ ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቀኝ” ብሎ ጥፋቱን ለካህን ዘርዝሮ የሚናገርበት ሥርዓት ነው። አንድን ተነሳሒ እና ካህንን የንስሓ ልጅና አባት የሚያሰኘው ዋናው ጉዳይም ይህ ነው። የንስሓ ልጅም የንስሓ አባት የመያዙ መሠረታዊ ጉዳይ ይኸው ነው። 

መናዘዝ የሚለውን ቃል ስናነሣ በሉቃስ ወንጌል የተጻፈውን የጠፋው ልጅ ታሪክ መመልከት ይጠቅመናል። ታሪኩ እንደሚነግረን፡- አንድ አባት ሁለት ልጆች ነበሩት።

ከሁለቱ አንዱ /ታናሹ/ ድርሻውን ተካፍሎ ለመውጣት ፈለገ። አባቱም ከሀብቱ ለልጁ ሊደርሰው ይገባል ያለውን ድርሻውን ከፍሎ ሰጠው። ልጁም ድርሻውን ተቀብሎ ወደ ሩቅ ሀገር በመሄድ ሀብቱን አባክኖ ጨረሰ። ኋላም በሚኖርበት ሀገር ጽኑ ራብ በሆነ ጊዜ ለአንድ ገበሬ እሪያ ለማሰማራት ተቀጠረ። ከመራቡም የተነሣ እሪያዎች ከሚበሉት አሰር ሊመገብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠው ግን  አልነበረም። ያን ጊዜም “ወደ ልቡ ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ” አለ። እንዳለውም አደረገ። አባቱንም “አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም” አለው። አባቱ ግን ገና ሩቅ ሳለ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ጎረቤቶቹንም ጠርቶ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይበለን ብሎ ታላቅ ድግስ ደገሰ ይለናል (ሉቃ.፲፭፥፲፩-፴፪)። 

ይህን ምሳሌዊ ትምህርት በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ሊቃውንት በብዙ መንገድ ያመሠጥሩታል። እኛ ግን አንዱን ብቻ ብንመለከት የሁለት ልጆች አባት የተባለው የሁሉ ፈጣሪና አባት እግዚአብሔር ነው። ሁለቱ ልጆች ደግሞ ቅዱሳን መላእክትና አዳም /የሰው ልጆች/ ፣ የጠፋው ልጅ ማለትም ታናሹ የተባለው አዳም ፣ ወደ ልቡ መመለሱ ደግሞ ንስሓ ለመግባት መወሰኑን፣ ጥፋተኛ ነኝና ልጅህ ልሆን አይገባኝም አገልጋይህ አድርገኝ ማለቱም ጥፋተኛነቱን አምኖ፣ ተጸጽቶ መናዘዙን ያስረዳልናል።  

የሰው ልጅ የለበሰው ሥጋ ለኃጢአት የሚስማማ ከመሆኑ የተነሣ ዕለት ዕለት አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስሕተት እንዲሁም በቸልተኝነት ሕገ እግዚአብሔርን ይተላለፋል። በዚህም ምክንያት ከቤተ እግዚአብሔርና ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይርቃል። ይህም የኅሊና ዕረፍት፣ የአእምሮ ሰላም፣ የልብ ደስታ እንዲሁም የሰማያዊ ርስት ተስፋንም ያሳጣዋል። ያን ጊዜም ያዝናል፤ ይከፋል፤ ወደ ልቡም ተመልሶ መፍትሔ ይፈልጋል። መፍትሔው ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ሽማግሌ መፈለግ ነው። ይህ ሽማግሌም ካህን ነው። ካህን ደግሞ እንደ ሽማግሌነቱ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቀኝ ብሎ ሲመጣ አስታርቅህ ዘንድ ጥፋትህ ምንድን ነው ብሎ ይጠይቃል። እርቅ ፈላጊውም ጥፋቱን(ኃጢአቱን) ዘርዝሮ ይናገራል። እንግዲህ መናዘዝማለት ይህ ነው። 

ይህ ኃጢአትን ለካህን የመናዘዝ ሥርዓት በኦሪትም በወንጌልም ተጽፏል። ለምሳሌ በኦሪት  «ወንድ ወይም ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፍ ዘንድ ሰው የሚሠራውን ኃጢአት ቢሠራ በዚያም ሰው ላይ በደል ቢሆንበት በሠራው ኃጢአቱ ላይ ይናዘዝ»  ተብሎ ተጽፏል። (ዘፀ.፭፥፮) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢአትን ለካህን መናዘዝ እንደሚገባን ሲናገር ለምጻሞቹ ኢየሱስ ሆይ ማረን እያሉ ወደርሱ ሲመጡ «ወደ ካህን ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ» በማለት ወደ ካህናት ልኳቸዋል። ሄደውም ራሳቸውን ለካህን ሲያሳዩ (ኃጢአታቸውን ሲናዘዙ) ከበደላቸው ነጽተዋል። (ሉቃ.፲፯፥፲፪-፲፭) ራስህን ለካህን አሳይ ማለቱም ለምጽ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ በሽታ ስለነበረ ነው። (ዘሌ.፲፫፥፵፭-፵፮) ለኃጢአት በሽታ መድኃኒቱ ንስሓ መሆኑ የታወቀ ነው። 

የንስሓ ልጆች ለካህናት የተሰጣቸውን የማሰርና የመፍታት ሥልጣን አምነው ኃጢአታቸውንና በደላቸውን ሳይደብቁና ሳይሳቀቁ ለካህን መናዘዝ አንዱ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። ይህን ከማድረጋቸው በፊት ግን ልክ እንደ ጠፋው ልጅ ወደ ልባቸው መመለስና ቆም ብለው ማሰብ የኃጢአተኝነትን ስሜት መራራነት መረዳት ዳግመኛም ወደ ኃጢአት ላለመመለስ መወሰን ኃጢአት በመሥራታቸው የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ ማሳዘናቸውን እያሰቡ የንስሐ ኀዘን ማዘን በመጨረሻም «በምድር ያሰራችሁት በሰማይም የታሰረ በምድር የፈታችሁት በሰማይም የተፈታ ይሆናል» (ማቴ.፲፰፥፲፰)። እንዲሁም «ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል» (ዮሐ.፳፥፳፫)። ተብሎ ለካህናት የተሰጣቸውን ሰማያዊ ሥልጣን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። በመጨረሻም ሁሉን የሚያየውን ልብና ኵላሊትን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን በማሰብ እንደነሱ ሰው የሆነውን ካህኑን በመፍራት /በማፈር/ የሠሩትን ኃጢአት አንድም ሳያስቀሩ ዘርዝሮ መናዘዝ የተነሳሕያን መሠረታዊ ግዴታቸው ነው።

፪. ቀኖናን ተቀብሎ መፈጸም፡-

ቀኖና ካኖን /canon/ ከሚለው የጽርዕ /የግሪክ/ ቃል የተወሰደ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም መቃ፣ መስፈሪያ፣ መለኪያ፣  መለካት መቁጠር ማለት ነው። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፯፺፱) ከንስሓ ጋር በተያያዘ ያለውም ትርጒም “አንድ ተነሳሒ በካህኑ ፊት ኃጢአቱን ከተናዘዘ በኋላ ካህኑ ለኃጢአት ማስተሥረያ የሚሰጠው የመንፈሳዊ ቅጣት ቁጥር መጠንና ዓይነት” ማለት ነው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ሁሉ ካህኑ ኃጢአተኛውን ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ሽማግሌ እንደ መሆኑ መጠን እርቁ እንዲፈጸም ጥፋተኛው ግለሰብ የሚጠበቅበትን መንፈሳዊ ግዴታ ለይቶ ማሳወቁ የማይቀር ነው። ምክንያቱም እርቅ ሲደረግ የበደለው አካል ይቅርታ ለማግኘት የተበደለው አካል ደግሞ ይቅርታ ለማድረግ በየግላቸው ሊወጡ የሚገባቸው ድርሻ አለና። በዚህም መሠረት የተነሳሒ ድርሻ በፍጹም ልብ ከመመለስ፣ በተጨማሪ የበደለውን መካስ የቀማውን መመለስ እንዲሁም በጾም በጸሎት፣ በስግደት፣ በዕንባና በዋይታ ወደ እግዚአብሔር ማልቀስ ነው። ይቅርታ ማድረግ ግን ምሕረትና ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ  የሆነው የእግዚአብሔር ነው። 

እንግዲህ ካህኑ ለኃጢአተኛው ሰው እግዚአብሔር ይቅር ይልህ ዘንድ መንፈሳዊ ተግባራትን ሥራ ብሎ የሚያዝዘው ትእዛዝ ቀኖና ይባላል።  ይኸውም በብሉይ ኪዳን የኃጢአት፣ የበደል፣ የደኅንነት ወዘተ መሥዋዕት ተብለው የፍየል የበግ የርግብ... መሥዋዕት በማቅረብ ይፈጸም የነበረ ሲሆን በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ጹም፣ ጸልይ፣ ስገድ፣ መጽውት… ወዘተ በመሳሰሉት እንደካህኑ ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል። 

ቀኖና በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አስተምህሮ መሠረት ሰው ከስሕተቱ የሚታረምበት መንፈሳዊ ተግሣጽ ሲሆን ይህ ግን ምድራውያን ነገሥታት ለወንጀለኞች እንደሚሰጡት ቅጣት የሚታይ አይደለም። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ይቅር የሚለው ኃጢአተኛነቱን አምኖ በማዘኑ፣ በመቆጨቱና ከጥፋቱ በመመለሱ  እንጂ ስለበደሉ በሚከፍለው ካሳ ብዛት አይደለምና። ለዚህም ነው ቀደም ብለን ባየነው የጠፋው ልጅ ታሪክ ላይ ልጁ ለመናዘዝ ወደ አባቱ እየመጣ ሳለ “አባቱ ግን ገና ሩቅ ሳለ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው” የሚለው። (ሉቃ.፲፭፥፳) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያው መልእክቱ ላይ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” ባለው መሠረት ነው። (፩ኛ ጴጥ.፬፥፫) አባቶቻችንም ይህንን መሠረታዊ እውነት ሳይዘነጉ ኃጢአተኛው በኃጢአት ባሳለፈበት ዘመን ፈንታ ቀሪ ዘመኑን በጽድቅ ጎዳና እንዲመላለስ ያዝዛሉ።

ሐዋርያው “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” ሲል በቃ ቁጭ በሉ ማለቱ አይደለም። በዚያ ፈንታ ፈቃደ እግዚአብሔርን አድርጉ ለማለት እንጂ። አባቶች ካህናትም በዚሁ መሠረት ለኃጢአተኛ ሰው በቀማህበት ፈንታ መጽውት፣ ያለ ልክ በመብላትና በመጠጣት በስካር በኃጢአት ባሳለፍክበት ዘመን ፈንታ ጹም ጸልይ ስገድ በማለት ለኃጢአተኛው ቀኖና ይሰጡታል። ይህም ተገቢ ነው። 

እንዲያውም አባቶቻችን ለባለጸጋ/ ጾምን፤ ለድሃ /ምንም ለሌለው ችግረኛ/ ምጽዋትን በማዘዝ ኃጢአተኞች ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም በሰውነታቸው ላይ ጨክነው መወሰንን እንዲለማመዱ ያዛሉ። ምክንያቱም ለባለጸጋ ምግብ በቤት ውስጥ ሞልቶ ተርፎ እያለ መጾም፣ ለድሃ ደግሞ ቆጥቦ ያስቀመጠውን ወይም ለምኖ ያገኘውን ገንዘብ መመጽወት ከባድ ነውና። ይሁንና ድሃ ጦሙን አድሮም ቢሆን ይመጸውታል ባለጸጋም ለተወሰነ ቀን ነውና እንደምንም ራቡን ታግሦ ይጾማል። ከዚህም የተነሣ ሰውነታቸው ኃጢአትን ከመጸየፍ በተጨማሪ ለጽድቅ መታዘዝንም ይለማመዳል። 

ስለዚህ ተነሳሕያን የተሰጣቸው ቀኖና በዛ ብለው ሳያንጎራጉሩ አነሰም ብለው ሳይጠራጠሩ በካህኑ ቀኖና ላይ የእግዚአብሔር ቸርነት እና የተነሳሒው ትሩፋት ተጨምሮ ከታላቅ በደልና ኃጢአት እንደሚያነፃቸው አምነው ቀኖናቸውን መቀበልና መፈጸም ይገባቸዋል።

፫. ሥጋውንና ደሙን መቀበል፡-

በክርስትና አስተምህሮ የአገልግሎቶች ሁሉ መደምደሚያው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ነው። የካህናትና የመምህራንም መሾም ዋና ግቡ ምእመናንን አስተምረው ለሥጋውና ለደሙ ማብቃት ነው። ምክንያቱም የመንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ ግቡ ሰማያዊ ርስት መውረስ ነውና። ያለክርስቶስ ሥጋና ደም ደግሞ ሰማያዊ ርስት ማለትም የዘለዓለም ሕይወት የለም። ምክንያቱም “..እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።”  (ዮሐ.፮፥፶)ተብሎ ተጽፏል። 

በየጠፋው ልጅ ታሪክ አስቀድመን እንደተመለከትነው ልጁ ወደ አባቱ ቤት ሲመለስ አባቱ ፊሪዳ አርዶ ድግስ ደግሶ ተቀብሎታል። የጠፋው ልጅ አዳም ነው። የጠፋውን አዳምን ፍለጋ የመጣው ደግሞ ክርስቶስ ነው። “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና” (ሉቃ.፲፱፥፲)እንዲል። ለአዳም ምግብ ሊሆን የታረደው ፍሪዳም ራሱ ክርስቶስ ነው። በቀራንዮ ኮረብታ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ መሥዋዕት ሆኖአልና። ዓርብ መሥዋዕት ከመሆኑ በፊት ሐሙስ ማታ ላይም “እንጀራን አንሥቶ ባርኮ ቈርሶ እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው፣ በማለት እንዲሁም ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቷቸዋል። ይህም የክርስቶስ ሥጋና ደም ለእኛ የሕይወት ምግብና መጠጥ ሆኖ መቅረቡን የሚናገር ነው (ማቴ.፳፮፥፳፮)። 

ስለዚህ እኛም የዘለዓለም ሕይወት ለማግኘትና ሰማያዊ ርስትን ለመውረስ የክርስቶስን ሥጋና ደም መቀበል የግድ ነው። “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።” የሚለውም ይህንኑ የሚያስገነዝበን ነው (ዮሐ.፮፥፶፮-፶፯)።

ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙንም ለመቀበል አስቀድሞ ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ የሚገባ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ “ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት” (፩ኛቆሮ.፲፩፥፳፯) በማለት ይመክረናል። አያይዞም ሥጋውና ደሙ ዕዳ እንዳይሆንብን ማድረግ ያለብንን ጥንቃቄም ሲናገር “ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤” ብሏል (፩ኛቆሮ.፲፩፥፳፰)። 

ራሱን ይፈትን ማለቱም “እኔ ምንድን ነኝ ኃጢአተኛ ወይስ ንጹሕ?” ብሎ ራሱን በመጠየቅ መቼም ንጹሕ የለምና በደሉን ለካህን ተናዝዞ ካህኑ የሚሰጠውን ቀኖና ተቀብሎ ከፈጸመ በኋላ ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ማለቱ ነው። ለዚህ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምጻሞቹ ማረን ሲሉት በመጀመሪያ ሂዱና ራሳችሁን ለካህን አስመርምሩ ያላቸው። ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን ቃል መሠረት በማድረግ ሥጋውንና ደሙን ተቀብለው ክርስቶስን ለመዋሐድ የሚመጡትን ሁሉ ሂዱና ራሳችሁን ለካህን አስመርምሩ ትላቸዋልች። ራሳቸውን ፈትነው ኃጢአተኛነታቸውን አምነው ለካህን ከተናዘዙ በኋላ ቀኖናቸውን ፈጽመው ለሚመጡት ሥጋውንና ደሙን ትሰጣቸዋለች። ይህን ሳያደርጉ ለሚመጡት ግን ካህኑ “የቀማውን ሳይመልስ የበደለውን ሳይክስ ኃጢአቱንም ለካህን ሳይናዘዝ የመጣ ካለ እኔ ከደሙ ንጹሕ ነኝ” በማለት እያስጠነቀቀ ሥጋውንና ደሙን ይሰጣል። ቅዱስ ጳውሎስም “ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።” በማለት አስጠንቅቋል (፩ኛቆሮ.፲፩፥፳፱)። 

በኦሪቱ በነበረው የመሥዋዕት ሕግም እስራኤላውያን የፋሲካውን በግ ሲመገቡ ጫማቸውን ተጫምተው፣ ወገባቸውን ታጥቀው፣ ኩፌታቸውን ደፍተው በትራቸውን ይዘው እየተቻኮሉ እንዲመገቡ ታዘው ነበር (ዘፀ.፲፪፥፲፩)። “ይህም ዛሬ ላለነው ክርስቲያኖች ምሳሌ ሆኖን የአማናዊውን በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል በጎ ምግባር ሠርተን፣ ወንጌሉን ተጫምተን፣ የንጽሕናን ዝናር ታጥቀን አክሊለ ሦክን ነገረ መስቀሉን እየዘከርን (መስቀሉን ተመርኩዘን) ሞት እንዳለብን በማሰብ እንዳይቀድመን ፈጥነን ንስሓ በመግባት ሥጋውንና ደሙን መመገብ የሚገባን መሆኑን ያስገነዝበናል። 

ቀደም ብለን ባየነው የጠፋው ልጅ ታሪክም  አባት ልጁ ከጠፋበት ሲመለስ ፊሪዳውን ከማረዱ በፊት “ባሪያዎቹን ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ” በማለት ልጁ ታጥቦ ንጹሕ የሆነውን ለብሶና ተጫምቶ እንዲዘጋጅ ነበር ያደረገው። እንደሚታወቀው ያንን ልጅ ወደ ልቡ እንዲመለስና የአባቱን ቤት እንዲያስብ ያደረገው ረኃብ ነበር። “እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ አለ” እንዲል። ከአባቱ ቤት ካለው ማዕድ ለመቀበል ግን አስቀድሞ ያንን ማዕድ አቋርጦ በመውጣት የበደለውን አባቱን ይቅርታ መጠየቅ ነበረበት። 

ስለሆነም አባቱን ማረኝ አለው። አባቱም ይቅር አለው። ከዚያ በኋላ ከፊሪዳው ተመገበ። እኛም ገና በአርባና በሰማንያ ቀናችን ጀምረን ስንመገብ የኖርነውን ሥጋውንና ደሙን አቋርጠን ወደ ተለያየ የኃጢአት ሕይወት ብንገባም እንኳ ወደ ልባችን ተመልሰን ሥጋውንና ደሙን ለመቀበል ስንመጣ አስቀድመን ስለ ጥፋታችን ይቀርታ መጠየቅ እንደሚገባን ያስገነዝበናል። ይህም ሥጋውንና ደሙን ለመቀበል ንስሐ ገብተን መዘጋጀት የሚገባ መሆኑን አንድም የንስሓ ጉዞ መጨረሻው በክርስቶስ ሥጋና ደም መደምደም /መቋጨት/ የሚገባ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል።

በአጠቃላይ ሰው በኃጢአቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር ከተለየ በንስሓ መመለስ ይኖርበታል። እግዚአብሔር አምላካችንም በነቢዩ ላይ አድሮ አምላካዊ ጥሪውን ያስተላለፈውና “ወደ እኔ ተመለሱ” እያለ የሚጠራን ለንስሓ ነው። ስለሆነም ሁላችንም በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰን ቅዱስ ሥጋውን በልተን ክቡር ደሙን ጠጥተን ከቅዱሳን ማኅበር እንዲጨምረን የራሳችንን ድርሻ መወጣት አለብን። በንስሓ ተመልሰን በቤቱ እንድንኖር እግዚአብሔር በቸርነቱ ቅዱሳን በአማላጅነታቸው አይለዩን አሜን።

Read 483 times