ሀ. ዓለምን የሚያሳርፈው
ይህን ዓለም በልዩ ጥበቡ ፈጥሮ የሚጠብቀው፣ የሚመግበው፣ ከድካሙ የሚያሳርፈው አምላክ እግዚአብሔር ነው። ይህ ዓለም ከድካሙ የሚያሳርፈው፣ ከውድቀቱ የሚያነሣው፣ ከሕማሙ የሚፈውሰውና ከመከራው ሁሉ የሚያወጣው አጥቶ ለ፶፻፭፻ ዘመን ያህል በመከራ ውስጥ ኑሯል። ይሁን እንጂ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ይህን ዓለም ከድካሙ አሳረፈው። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና” (ማቴ.፲፩፥፳፰-፴) በማለት እንደተናገረ ለዓለሙ ሁሉ ያልተቻለውን ሸክም ከላዩ ላይ አንሥቶ ከድካሙ ያሳረፈው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልደ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እግዚአብሔር አምላክ በሥጋም ሆነ በነፍስ የደከሙትን ከድካማቸው ያስርፋቸው ዘንድ ይቻለዋል። በሥጋ ለደከሙት ኃይል ሥጋዊ፣ በመንፈስ ለደከሙት ደግሞ ኃይል መንፈሳዊ በመስጠት ከድካማቸው ያሳርፋቸው ዘንድ ይቻለዋል። በባሕርዩ ድካመ የሌለበት አምላክ “እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በስድስተኛው ቀን ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ” (ዘፍ.፪፥፪) ተብሎ ተነገረለት። ይህ የሆነው የእኛን ዕረፍተ ሥጋ ሲባርክ ነው። እርሱ ሥራ በፈጸመ ጊዜ ዐረፈ እንደተባለ ሁሉ እኛንም በሊቀ ነቢያት ሙሴ አማካኝነት ሰው ብቻ ሳይሆን እንስሳት ሁሉ እንዲያርፉ አዝዞናል።
ይህን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ “የሰንበትን ቀን ትቀድሳት ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛዋ ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ናት፤ አንተ ወንድ ልጅህም፣ ሴት ልጅህም፣ ሎሌህም፣ ገረድህም፣ አህያህም፣ ከብትህም፣ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርስዋ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፏልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል፤ ቀድሶታልም።” (ዘፀ.፳፥፰-፲፩) ተብሎ ተጽፎ እናገኘዋለን። አስቀድሞ ለሰው ልጅ እንደሚያሻው አውቆ ዕረፍትን በዚህ መልኩ እንዳዘጋጀለት ሁሉ አማናዊውን ዕረፍት ሊያድለን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የእኛን ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ዓለም መጣ። ስለዚህ “ለዓለም ዘየዓርፎ፤ ዓለምን የሚያሳርፈው” ተብሎ ተነገረለት።
ለ. የሰውን ሥጋ ለበሰ
እግዚአብሔር አምላካችን ዓለምን ያድንበት ዘንድ የመረጠው እና የወደደው የድኅነት መንገድ የሰውን ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ዓለም በመምጣት ወይም በሥጋ መገለጥ ነበር። ይህ የማዳን ሥራ የተገለጠበት መንገድም ምሥጢረ ሥጋዌ ተብሏል። ይህም ጥበቡ ሊቃውንቱን እጅግ አስደንቋቸው እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል ብለዋል። የተራቆቱትን የሚያለብሰው አምላክ የሰውን ሥጋ ለበሰ፤ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የሰውን ልጅ ብቻ ሳይሆን “ ኪነ ጥበቡ መንክር ወዕፁብ ለዘሀሎ መልዕልተ አርያም አርአየ ሥልጣኖ ላዕለ ሞት ዘከለሎ ለሰማይ በዋክብት ብሩሃን። ወለምድርኒ አሠርገዋ በጽጌያት ንጹሓን አርአየ ሥልጣኖ ላዕለ ሞት፤ በላይ በአርያም ያለው አምላክ ጥበቡ እጅግ ይደንቃል፤ ሥልጣኑን በሞት ላይ አሳየ፤ ሰማይ በብሩሃን ከዋክብት የሸፈነ፣ ምድርንም በንጹሓን አበቦች ያስጌጠ አምላክ ጥበቡ እጅግ ድንቅ ነው” (ድጓ ዘዮሐንስ) በማለት የተናገረለት አምላክ የእኛን ሥጋ ለበሰ።
የእኛን ሥጋ ለብሷልና በረደው፤ በመሆኑም በልደቱ ጊዜ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም የበለስ ቅጠል አለበሰችው፤ እንስሳት እስትንፋሳቸውን ገበሩለት፤ አዳምን የጸጋ ልብስ ያለበሰ እርሱ ተራቆተና የሚለብሰው አጣ፤ ረቂቅና ሰማያዊ ልብስ የሆነውን ብርሃን አልብሶ ብርሃን አጎናጽፎ በመንፈሳዊው ልደት የሚወልደን አምላክ የእኛን ግዙፍ ሥጋ ለበሰ። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም በውዳሴው “የመመኪያችን ዘውድ፣ የድኅነታችን መጀመሪያ፣ የንጽሕናች መሠረት እኛን ለማዳን ሰው የሆነ የግዚአብሔርን ቃል በወለደችልን በድንግል ማርያም ሆነልን” (ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ) በማለት እንደተናገረ እኛን ያድን ዘንድ የእኛ ሥጋ ለበሰ።
ወንጌላዊው ዮሐንስም “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ያም ቃል እግዚአብሔር ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ ሆነ።” (ዮሐ. ፩፥፩-፫) በማለት ቀዳማዊነቱን፣ሁሉ በእርሱ ሆነ ብሎ ዓለማትን ሁሉ የፈጠረ አምላክ መሆኑን ከነገረን በኋላ ይህ ዓለምን የፈጠረው አምላክ እኛን ለማዳን ሲል የእኛን ሥጋ መልበሱን ደግሞ “ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛም አደረ” (ዮሐ. ፩፥፲፬) በማለት አስረዳን። ስለዚህ ሊቁ ዓለምን የሚያሳርፈው ስለኛ የሰውን ሥጋ የለበሰው በማለት ይህ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የሰውን ሥጋ ለብሶ በዚህ ዓለም የተገለጠው አምላክ ዓለማትን ሁሉ የፈጠረ መሆኑን አስረዳን።
ሐ. አስቀድሞ እንደተጻፈ
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን በአበው ምሳሌ በነቢያት ትንቢት አስቀድሞ የተነገረ ነው። ነገሩን አስቀድሞ በኦሪት ያጻፈው በነቢያትም ያናገረው መሆኑን በተመለከተ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “አቅዲሙ ነገረ በኦሪት አቅዲሙ ነገረ በኦሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሐት ዘይዜንዋ ለጽዮን ቃለ ትፍሥሕት። ወካዕበ ይቤ በአፈ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም፤ ዘያበርህ ላዕለ ጻድቃን መርዓዊሃ ለቤተ ክርስቲያን ይርዳዕ ዘተኀጕለ ያስተጋብእ ዝርዋነ መጽአ ውስተ ዓለም፤ ወልድ በክብር በምስጋና እንደሚመጣ አስቀድሞ በኦሪት ተናገረ፤ ዳግመኛም በዳዊት አፍ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው አለ፤ በጻድቃን ላይ የሚያበራው ወደዚህ ዓለም የመጣው ብርሃን ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ሙሽራ የጠፉትን ይመልስ ዘንድ፣ የተበተኑትንም ይስበስብ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ።” (ድጓ ዘአስተምህሮ) በማለት አስቀድሞ በኦሪት የተጻፈ በነቢያትም የተነገረ መሆኑን ይመስክራል።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ከማረጉ አስቀድሞ ለሐዋርያት በአስተማራቸው መጽሐፈ ኪዳን (ትምርተ ኅቡአት) “ዘበነቢያት አቅደመ ተዐውቆ ወበ ሐዋርያት ተሰብከ ወእመላእክት ተአኵተ ወእምኀበ ኵሉ ተሰብሐ፤ በነቢያት መታወቅን አስቀደመ፤ በመላእክት ተመሰገነ፤ በሁሉ ዘንድም ተመሰገነ” ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይወርዳል ይወለዳል፤ የእኛን መከራ ተቀብሎ ያድነናል። እየተባለ በነቢያቱ እንደተነገረ ከሰማየ ሰማያት ወረደ፤ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ፤ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ ይህን ዓለም አዳነ። ይህ ሁሉ አስቀድሞ የተነገረ፣ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፈ ስለሆነ ሊቁም አስቀድሞ እንደተጻፈ አለን።
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ።” (ዕብ.፩፥፩) በማለት እንዳስረዳው ይህ ሁሉ አስቀድሞ በብዙ ምሳሌና በብዙ ትንቢት የተነገረ ነው። በመሆኑም ይህ ዓለምን የሚያሳርፈውን፤ ስለ እኛ የሰውን ሥጋ የለበሰውን፤ ይህንም አስቀድሞ በኦሪትና በነቢያት ያናገረውን አምላክ አረጋዊው ስምዖን በዐይኖቹ ያይ ዘንድ በተስፋ ሲጠብቅ ኖረ።
መ. ስምዖን በተስፋ ተቀመጠ
ተስፋ በሃይማኖት የመኖራችን አንዱ መገለጫው ነው። እግዚአብሔር ያደርግልኛል ብሎ አምኖ የሚደረግልንን ነገር በተስፋ መጠበቅ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖራችን በእግዚአብሔርም ለማመናችን መገለጫው ነው። ስምዖን የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲተረጕም “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠዋለች።” (ኢሳ. ፯፥፲፬) የሚለውን ንባብ ሲያነብ ከበደው። ድንግል እንዴት በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ልትወልድ ትችላለች በማለት ተቸገረና ድንግል የሚለውን ሴት እያለ መጻፍ ጀመረ። ያን ጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ መጥቶ ይህን እስክታይ አትሞትም ብሎት ነበርና እስከ ክርስቶስ መወለድ ድረስ ቆይቷል። ይህን ቅዱስ ሉቃስ “በኢየሩሳሌምም ስሙ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ጻድቅና ደግ ሰው ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን ደስታቸውን ያይ ዘንድ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ነበር። የእግዚአብሔርንም መሢሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። (ሉቃ.፪፥፳፭-፳፮) በማለት ጽፎት እናገኛለን።
ከአዳም ጀምሮ የሰው ልጅ በሙሉ የእግዚአብሔርን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። የሰው ልጅ ድኅነትን አገኛለሁ ከሲኦል እወጣለሁ፣ እከብራለሁ፣ የተወሰደብኝ ሁሉ ይመለስልኛል ወዘተ. ብሎ ተስፋ ያደረገ ሲሆን መላእክትም የሰው ልጅ ድኅነት እጅግ ደስ ስለሚያሰኛቸው የእርሱን መምጣት ይጠባበቁ ነበር። ሊያዩትም ይመኙ ነበር። በጸሎተ ኪዳን “ዘያፈትዎሙ ለመላእክት ከመ የሐውጽዎ፤ ይጎበኙት ዘንድ የሚያስመኛቸው” ተብሎ እንደተጻፈ። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም “ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ” (፩ጴጥ. ፩፥፲፪) ብሎ እንደጻፈልን መላእክቱ ሳይቀሩ ይመኙት ነበር። ከእነዚህ ከሰው ልጆችና ከመላእክት በተለየ ሁኔታ ዕረፍተ ሥጋም ሳያገኝ የመሢሑን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ የነበረው ስምዖን አረጋዊ መሆኑን ሊቁ “ስምዖን ካህን ነበረ እንዘ ይሴፎ፤ ስምዖን ካህን ተስፋ እያደረገ ነበረ” በማለት ይስረዳናል።
ሠ. ስምዖን ካህን ታቀፈው
የመሢሑን መምጣት በተስፋ ይጠባበቅ የነበረው አረጋዊ ጊዜው በደረሰ ጊዜ መንፈስ አነሣሥቶት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ። በዚያም የኦሪቱን ሕግ ሊፈጽም በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ የወሰዱትን ሕፃኑን አገኘው፤ ታቀፈውም። ይህም በቅዱስ ወንጌል “መንፈስም ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደው፤ ዘመዶቹም በሕግ የተጻፈውን ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ጌታችን ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደስ ባገቡት ጊዜ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ በክንዱ ታቀፈው፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነው።” (ሉቃ.፪፥፳፯-፳፰) ተብሎ ተጽፎ እናገኘዋለን።
ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና በጆሮአችን የሰማነውን፣ በዐይኖቻችንም ያየነውን፣ የተመለከትነውንም፣ እጆቻችንም የዳሰሱትን እንነግራችኋለን” (፩ዮሐ.፩፥፩) ብሎ እንደጻፈው ቅድመ ዓለም የነበረው ዓለምን የፈጠረው፣ ዓለምን ያዳነው አምላክ፣ በባሕርይው የማይታየው አምላክ የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ፣ በሐዋርያት እጅ የሚዳሰስ፣ በሐዋርያት ዐይን የሚታይ፣ በሐዋርያት ጆሮ የሚሰማ ሆነ። ይህን አምላክ ስምዖን አረጋዊ ታቀፈው። ቃል አይታይም የእኛን ሥጋ ሲዋሐድና በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ የማይታየው ታየ፤ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ፤ ዘመን የማይቆጠርለት አምላክ ዘመን ተቆጠረለት።
እግዚአብሔር በባሕርዩ አይታይም። ወንጌላዊው ዮሐንስ “በአባቱ ዕቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ገለጠልን እንጂ እግዚአብሔርንስ ከቶ ያየው የለም“ (ዮሐ. ፩፥፲፰) በማለት እንደነገረን በእኛ አእምሮ አይመረመርም፣ በዐይነ ሥጋ አይታይም፣ ይሁን እንጂ “ወኮነ ሰብአ ከማነ ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ፤ ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደ እኛ ሰው ሆነ” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) ተብሎ እንደተነገረ የእኛን ሥጋ ተዋሕዷልና በስምዖን ዕቅፍ ተይዞ ታየ።
ረ. ያሳርፈው ዘንድ ለመነ
ሰው ዕድሜ ቢጨመርለት ይፈልጋል። በተለይም የሰማያዊውን ዓለም ሕይወት ያልተረዱትና በዚህ ዓለም ያለውን ድሎት የሚያስቀድሙ አካላት ዕድሜያቸው ቢጨመርላቸው ይፈልጋሉ። አረጋዊ ስምዖን ግን “አሰናብተኝ” በማለት ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም መሄድን መረጠ። በቅዱስ ወንጌል “እንዲህም አለ አቤቱ እንዳዘዝህ ዛሬ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ። ዐይኖቼ ትድግናህን አይተዋልና። በወገንህ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ለአሕዛብ ብርሃንን ለወገንህ ለእስራኤልም ክብርን ትገልጥ ዘንድ” (ሉቃ.፪፥፳፱-፴፩) ተብሎ እንደጻፈ አረጋዊው ስምዖን ዕረፍቱን መረጠ።
ሰማያዊውና ዘለዓለማዊው ሕይወት ሲገባቸው ከዚህ ዓለም ሕይወት ይልቅ የወዲያኛውን ዓለም ይመርጣሉ። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ፈጽሜ ግዳጄን ጨርሻለሁ፤ የማርፍበት ዕድሜዬም ደርሷል። መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄያለሁ። እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም” (፪ጢሞ.፬፥፮-፰) በማለት እንደተናገረ ከዚህ ዓለም ኑሮው ይልቅ የወዲያኛውን ዓለም ሕይወት መርጧል። ይህም ቅዱሳን ከዚህ ዓለም ኑሮ ይልቅ የወዲያኛውን ዓለም እጅግ አብዝተው የሚወዱት መሆናቸውን ያስረዳናል።
ሥጋ ለለበሰ ሁሉ ይህ ሞት የሚቀር አይደለም። ይሁን እንጂ እንደማይቀር እያወቅን ቢሆንም ሞታችንን አንፈልገውም። በሥጋዊ ሐሳብ ስንመላለስ የሚታየውን ብቻ እናስቀድምና በዚህ መኖራችንን አብዝተን እንመኛለን። አረጋዊው ስምዖን ግን “የኖርኩት ይበቃኛል ከዚህ በኋላ ብትወድስ ባሪያህን ታሰናብተዋለህ” እያለ ዕረፍቱን ሲለምን እንመለከታለን። አረጋዊው ስምዖን ዕረፍቱን መመኘቱን ብቻ ሳይሆን እንደ ሕፃን ሕገ ኦሪትን ሊፈጽም በእናቱ ዕቅፍ ወደቤተ መቅደስ የመጣው አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን፣ ዕረፍተ ሥጋ ዕረፍተ ነፍስ የሚሰጥ እርሱ መሆኑን በሚገባ ተረድቷል። መረዳቱንም “እነሆ ይህ ሕፃን ከእስራኤል መካከል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ይሆን ዘንድ የተሰየመ ነው” (ሉቃ.፪፥፴፬) በማለት በተናገረው ቃል መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ለሚያምኑበት ሁሉ ዕረፍተ ሥጋ ዕረፍተ ነፍስን የሚያድል አምላክ መሆኑን ስለተረዳና ስላመነ እንዲያሳርፈው ለመነው።
ሰ. ደካማው ሽማግሌ ነበልባሉን እንዴት ታቀፈው?
ሊቁን እጅግ ያስደነቀው ይህ ነገር ነው። አረጋዊው ስምዖን በመጀመሪያ ሊሆን ያለውን ለማመን ተቸገረ፤ እርሱ የታቀፈው ነበልባል ደግሞ በደካማው ሽማግሌ ዕቅፍ ታየ። አረጋዊወ ስምዖን ለማመን የተቸገረበትንም ድንቅ ምሥጢር ፈጸመ፤ አረጋዊው ስምዖን ምን አልባትም ለሦስት ለአራት መቶ ዘመናት በመኖሩ ብሉየ መዋዕል የተባለ ሽማግሌ ቢሆንም አስቀድሞ ማመን የተቸገረበትን ረቂቅ ምሥጢር የፈጸመው አምላክ ደግሞ ቅድመ ዓለም በንግሥናው የነበረ ንጉሥ ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው” (መዝ.፸፫፥፲፪) በማለት እንዳስረዳን ከዘመናት በፊት የነበረ፤ ዓለምን የፈጠረ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ.፩፥፩) እንዲል። ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ ነው። ነቢዩ ዳዊት “አንተ ግን አንተ ነህ ዓመትህም ከቶ አያልቅም” (መዝ.፻፩፥፳፯) በማለት እንደተናገረው በዘመናት የማይወሰን አምላክ ነው። እንዲህ ያለውን አምላክ መታቀፍ እጅግ ያስደንቃልና በአድናቆት ተናገረ።
እሳት በባሕርዩ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ አይደለም። ይሁንም እንጂ ከብረት ጋር ሲዋሐድ የጋለውን ብረት ባለሙያዎች በመቆንጠጫ ይይዙታል። በቅዱስ ወንጌል “እግዚአብሔርንስ ከቶ ማንም ያየው የለም” (ዮሐ.፩፥፲፰) የተባለው አምላክ የእኛን ሥጋ ለብሶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ግን በአንዲት ብላቴና ማሕፀን የሚወሰን፣ ባለሙያው “ና ሕፃኑን ግረዝ” ተብሎ የሚመጣበት፣ የኦሪትን ሕግና ሥርዓት ሊፈጽም ወደ ቤተ መቅደስ የሚሄድ፣ እንዲሁ አረጋዊው ስምዖንም የሚታቀፈው ሆነ። ቅዱስ ያሬድ ይህ ድንቅ ሥራ ስላስደነቀው “ደካማው ሽማግሌ ነበልባሉን እንዴት ታቀፈው?” በማለት በአድናቆት ተናገረ።
ለሙሴ በደብረ ሲና ሲገለጥለት ነበልባሉ ከሐመልማሉ ሐመልማሉ ከነበልባሉ ተዋሕዶ ነበር። እንደሊቃውንቱ አገላለጽ ነበልባሉ የመለኮት፣ ሐመልማሉ ደግሞ መለኮተ የተዋሐደው ሥጋ ምሳሌ ነው። ሊቁ አባ ሕርያቆስም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ቅዳሴው “እሳት በላዒ ለአማፅያን ለእለ ይክሕዱ ስሞ፣ እሳት ማሕየዊ ለርቱዐነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ፤ ለአመፀኞች የሚባላ እሳት ነው፤ እንደፈቃዱ ለሚጓዙትና ልባቸው ቅን ለሆኑት የሚያድን እሳት ነው” (ቅዳሴ ማርያም) በማለት እንደገለጸው አምላክ እሳት ነው። ግን አንድ ደካማ ሽማግሌ ታቀፈው። ሊቁ ይህ ስላስደነቀው “ደካማው ሽማግሌ ነበልባሉን እንዴት ታቀፈው?” በማለት በአድናቆት ተናገረ።
የክርስቶስ ሰው መሆንና ወደዚህ ዓለም መምጣት ለሚያምኑት የሚደንቅ፣ ለማያምኑት ደግሞ እየረቀቀባቸው የሚሰናከሉበት ነው። ሊቁ ግን በእምነት መነጽርነት ተገልጾለት እንደሌሎች በመጠራጠር ሳይሆን በማመንና በማድነቅ እየተመለከተ በውስጡ የተፈጠረውን አድናቆት ይናገራል። ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ አንድ ሽማግሌ ታቀፈው፤ በእርግጥም የሚደንቅ ነው።
በአጠቃላይ ሊቁ ዓለምን የሚያሳርፈው፣ እኛን ለማዳን የእኛን ሥጋ የለበሰው፣ በአንድ አረጋዊ ዕቅፍ የታየው፣ አረጋዊውም አምላክነቱን ተረድቶ እንዲያሳርፈው የለመነው አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑ ያስረዳናል። እኛም እንደ አረጋዊው ስምዖን ዕረፍተ ሥጋ ዕረፍተ ነፍስን የሚያድል አምላክ መሆኑን በማመን እንደንማጸነው፤ እንደ ቅዱስ ያሬድም ምሥጢሩን ተረድተን የተረዳነውንም ለሌላው እንድናስረዳ፤ ይህንንም ድንቅ ምሥጢር በማመን ከፍጹም እምነት ከሚገኘው በረከት እንድንሳተፍ እግዚአብሔር ይፍቀድልን።